በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘የታረዱ ነፍሳት’ ዋጋቸውን ተቀበሉ

‘የታረዱ ነፍሳት’ ዋጋቸውን ተቀበሉ

ምዕራፍ 17

‘የታረዱ ነፍሳት’ ዋጋቸውን ተቀበሉ

1. የምንኖረው በየትኛው ጊዜ ነው? ይህስ ለመሆኑ ምን ማስረጃ አለን?

የአምላክ መንግሥት ትገዛለች! የነጩ ፈረስ ጋላቢ ድሉን ለመፈጸም ተቃርቦአል! ቀዩ ፈረስ፣ ጥቁሩ ፈረስና ግራጫው ፈረስ በምድር ሁሉ ላይ እየጋለቡ ነው! ኢየሱስ ስለንጉሣዊ መገኘቱ የተናገራቸው ትንቢቶች በመፈጸም ላይ መሆናቸው ምንም አያከራክርም። (ማቴዎስ ምዕራፍ 24 እና 25፤ ማርቆስ ምዕራፍ 13፤ ሉቃስ ምዕራፍ 21) አዎ፣ የምንኖረው በዚህ የነገሮች ሥርዓት የመጨረሻ ቀኖች ውስጥ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) ነገሩ እንዲህ ከሆነ በጉ ኢየሱስ ክርስቶስ የዚህን መጽሐፍ ጥቅልል አምስተኛ ማህተም ሲፈታ የሚሆነውን ነገር እንመልከት። አሁን የምንመለከተው የትኛውን ራእይ ነው?

2. (ሀ) አምስተኛው ማህተም በተፈታ ጊዜ ዮሐንስ ምን ተመለከተ? (ለ) ምሳሌያዊ መሠዊያ በሰማይ ስለመኖሩ በማንበባችን ልንደነቅ የማይገባን ለምንድን ነው?

2 ዮሐንስ የሚከተለውን ቀስቃሽ ራእይ ይገልጽልናል:- “አምስተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ፣ ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ጠበቁት ምስክር የታረዱትን የሰዎች ነፍሳት ከመሠዊያ በታች አየሁ።” (ራእይ 6:9) ዮሐንስ የተመለከተው ይህ ነገር ምንድን ነው? መሥዋዕት የሚቀርብበት መሰዊያ በሰማይ ላይ ሊኖር ይችላልን? አዎ፣ ዮሐንስ ስለ መሰዊያ ሲናገር የመጀመሪያ ጊዜው ነው። ከዚህ ቀደም ሲል ይሖዋ በዙፋን ላይ ስለመቀመጡ፣ በዙፋኑ ዙሪያ ስለነበሩት ኪሩቤሎች፣ መስተዋት ስለሚመስለው ባሕር፣ ስለ መብራቶቹና ዕጣን ይዘው ስለነበሩት 24 ሽማግሌዎች ገልጾ ነበር። እነዚህ ነገሮች በሙሉ በእሥራኤል ምድር ላይ በነበረው የይሖዋ ቤተ መቅደስ ውስጥ የነበሩትን ነገሮች የሚመስሉ ናቸው። (ዘጸአት 25:17, 18፤ 40:24-27, 30-32፤ 1 ዜና 24:4) ስለዚህ በሰማይ ላይ መሰዊያ መታየቱ አዲስ ነገር ሊሆንብን ይገባልን?—ዘጸአት 40:29

3. (ሀ) በጥንቱ የእስራኤላውያን ቤተ መቅደስ በነበረው መሠዊያ ሥር ነፍሳት ይፈስሱ የነበረው እንዴት ነው? (ለ) ዮሐንስ የተገደሉ ምሥክሮችን ነፍሳት በሰማይ በነበረው ምሳሌያዊ መሠዊያ ሥር የተመለከተው ለምንድን ነው?

3 ከዚህ መሰዊያ በታች ወይም ሥር “ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ጠበቁት ምስክር የታረዱት ሰዎች ነፍሳት” ነበር። ይህ ምን ማለት ነው? እነዚህ ሰዎች አረማውያን ግሪኮች ያምኑ እንደነበረው ሥጋ የተለያቸው ረቂቅ ነፍሳት አልነበሩም። (ዘፍጥረት 2:7፤ ሕዝቅኤል 18:4) ከዚህ ይልቅ ነፍስ ወይም ሕይወት በደም ይመሰል እንደነበረ ዮሐንስ ያውቃል። በጥንቱ የአይሁዳውያን ቤተ መቅደስ ያገለግሉ የነበሩት ካህናት ለመሥዋዕት የሚቀርብ እንስሳ በሚያርዱበት ጊዜ ደሙን በመሰዊያው ዙሪያ ወይም ‘የሚቃጠል መሥዋዕት ይቀርብበት በነበረው መሰዊያ’ ግርጌ ይረጩ ነበር። (ዘሌዋውያን 3:2, 8, 13፤ 4:7፤ 17:6, 11, 12) ስለዚህ የእንስሳው ነፍስ ከመሰዊያው ጋር የቅርብ ዝምድና ነበረው። ይሁን እንጂ የእነዚህ የአምላክ አገልጋዮች ነፍስ ወይም ደም በሰማይ በምሳሌያዊ መሰዊያ ሥር የታየው ለምንድን ነው? የእነርሱ ሞት እንደ መሥዋዕታዊ ሞት ተደርጎ ስለሚታይ ነው።

4. በመንፈስ የተወለዱ ክርስቲያኖች አሟሟት መሥዋዕታዊ ሞት የሆነው በምን መንገድ ነው?

4 በእርግጥም የአምላክ የመንፈስ ልጆች በመሆን የሚወለዱ ሁሉ መሥዋዕታዊ ሞት ይሞታሉ። በይሖዋ ሰማያዊ መንግሥት ውስጥ በሚኖራቸው የሥራ ድርሻ ምክንያት በምድር ላይ የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋቸውን እንዲክዱ ወይም መሥዋዕት እንዲያደርጉ የአምላክ ፈቃድ ሆኖአል። በዚህ ረገድ ለይሖዋ ሉዓላዊነት ሲሉ መሥዋዕታዊ ሞት ለመሞት ፈቃደኛ ይሆናሉ። (ፊልጵስዩስ 3:8-11፤ ከፊልጵስዩስ 2:17 ጋር አወዳድር።) ዮሐንስ በመሠዊያው ሥር ሆነው የተመለከታቸው ሁሉ በዚሁ ዓይነት የሞቱ ናቸው። በጊዜያቸው የይሖዋን ቃልና ሉዓላዊነት በመደገፍ በሰጡት የቅንዓት አገልግሎት ምክንያት በሰማዕትነት የተገደሉ ናቸው። ነፍሳቸው የተገደለው “ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ጠበቁት ምስክርነት [ማርቲሪያን]” ምክንያት ነው።

5. ታማኝ የሆኑ ሰዎች ነፍሳት ሞተው እያሉ ለበቀል የሚጮሁት እንዴት ነው?

5 ትዕይንቱ መታየቱን ቀጠለ:- “በታላቅ ድምፅም እየጮኹ:- ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ እስከ መቼ ድረስ አትፈርድም፣ ደማችንንስ በምድር በሚኖሩት ላይ እስከ መቼ አትበቀልም? አሉ።” (ራእይ 6:10) መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚገልጸው ሙታን አንዳች ነገር የማይሰሙና የማያውቁ ከሆነ ነፍሳቸው ወይም ደማቸው ለበቀል የሚጮኸው እንዴት ነው? (መክብብ 9:5) ቃየን አቤልን ከገደለው በኋላ የጻድቁ የአቤል ደም ጮሆ አልነበረምን? በዚያ ጊዜ ይሖዋ ለቃየን “ምን አደረግህ? የወንድምህ የደሙ ድምፅ ከምድር ወደ እኔ ይጮኻል” ብሎት ነበር። (ዘፍጥረት 4:10, 11፤ ዕብራውያን 12:24) የአቤል ደም ቃል በቃል ይናገር ነበር ማለት አልነበረም። ከዚህ ይልቅ አቤል በግፍ የተገደለ ንጹሕ ሰው ስለነበረ ለገዳዩ ተገቢው ቅጣት እንዲሰጥ ፍትሕ ይጠይቅ ነበር ማለት ነው። በተመሳሳይም እነዚህ ክርስቲያን ሰማዕታት ምንም ወንጀል የሌለባቸው ነበሩ። በዚህም ምክንያት ፍትሕ የሚጠይቀው ተገቢ የፍርድ በቀል ሊሰጣቸው ይገባል። (ሉቃስ 18:7, 8) በዚህ ዓይነት የሞቱት ሰዎች በጣም ብዙ ስለሆኑ የበቀሉ ጩኸት በጣም ከፍ ያለ ነው።—ከ⁠ኤርምያስ 15:15, 16 ጋር አወዳድር።

6. ይሖዋ በ607 ከዘአበ የተበቀለው ለየትኛው የንጹሐን ሰዎች ደም ነው?

6 በተጨማሪም ሁኔታው ንጉሥ ምናሴ በ716 ከዘአበ የከዳተኛይቱን ይሁዳ ዙፋን በወረሰበት ጊዜ ከነበረው ሁኔታ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ምናሴ ብዙ ደም አፍስሶ ነበር። ምናልባትም ነቢዩ ኢሳይያስን ‘በመጋዝ ሳያሰነጥቀው’ አልቀረም። (ዕብራውያን 11:37፤ 2 ነገሥት 21:16) ምናሴ ውሎ አድሮ ንስሐ ቢገባና ወደ ጥሩ አቋም ቢመለስም ይህ የደም ወንጀል አልተወገደም ነበር። ባቢሎናውያን በ607 ከዘአበ የይሁዳን መንግሥት ባጠፉ ጊዜ “ምናሴ ስላደረገው ኃጢአት ሁሉ ስላፈሰሰውም ንጹሕ ደም ኢየሩሳሌምንም በንጹሕ ደም ስለሞላ ከፊቱ ያስወግዳቸው ዘንድ ይህ ነገር በእግዚአብሔር [“በይሖዋ፣” NW] ትእዛዝ በይሁዳ ላይ ሆነ፣ እግዚአብሔርም [“ይሖዋም፣” NW] ይራራ ዘንድ አልወደደም።”—2 ነገሥት 24:3, 4

7. የቅዱሳንን ደም በማፍሰስ በኩል ዋነኛው በደለኛ ማን ነው?

7 በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመናትም ሆነ በአሁኑ ጊዜ የአምላክን ምሥክሮች ከገደሉት ሰዎች መካከል ብዙዎቹ ከሞቱ ብዙ ጊዜ ሆኖአቸዋል። ይሁን እንጂ በሰማዕትነት እንዲገደሉ ያደረገው ድርጅት አሁንም በሕይወት ይገኛል፣ ከደም ዕዳም አልነጻም። ይህም የሰይጣን ምድራዊ ድርጅት፣ ማለትም ምድራዊ ዘሩ ነው። በዚህ ድርጅት ውስጥ ግንባር ቀደም ክፍል የሆነችው የሐሰት ሃይማኖት ግዛት የሆነችው ታላቂቱ ባቢሎን ነች። * ታላቂቱ ባቢሎን “በቅዱሳን ደምና በኢየሱስ ምሥክሮች ደም ሰክራ” ነበር። አዎ፣ “በእርስዋም ውስጥ የነቢያትና የቅዱሳን ደም በምድርም የታረዱ ሁሉ ደም ተገኘባት።” (ራእይ 17:5, 6፤ 18:24፤ ኤፌሶን 4:11፤ 1 ቆሮንቶስ 12:28) በጣም ከባድ የሆነ የደም ዕዳ ተጭኖአታል። ታላቂቱ ባቢሎን እስከኖረች ድረስ የገደለቻቸው ቅዱሳን ደም ለፍትሕ መጮሁን አያቆምም።—ራእይ 19:1, 2

8. (ሀ) በዮሐንስ ዘመን እነማን በሰማዕትነት ሞተው ነበር? (ለ) የሮማ ንጉሠ ነገሥታት እንዴት ያለ ስደት አነሳስተው ነበር?

8 ዮሐንስ ራሱ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ጨካኙ እባብና ምድራዊ ዘሮቹ በማደግ ላይ በነበረው ጉባኤ ላይ በዘመቱ ጊዜ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በሰማዕትነት ሲገደሉ ተመልክቶ ነበር። ዮሐንስ ጌታችን ሲሰቀል፣ እስጢፋኖስ፣ የገዛ ወንድሙ ያዕቆብ፣ ጴጥሮስ፣ ጳውሎስና ሌሎች የቅርብ ጓደኞቹ ሲገደሉ ተመልክቶአል። (ዮሐንስ 19:26, 27፤ 21:15, 18, 19፤ ሥራ 7:59, 60፤ 8:2፤ 12:2፤ 2 ጢሞቴዎስ 1:1፤ 4:6, 7) በ64 እዘአ ላይ የሮማው ንጉሠ ነገሥት ኔሮ የሮማን ከተማ ያቃጠለው እርሱ እንደሆነ ይነገር የነበረውን ወሬ ለማስተባበል ሲል ቃጠሎውን በክርስቲያኖች ላይ አሳቦ ነበር። ታሲተስ የተባለው ታሪክ ጸሐፊ እንዲህ ሲል ይነግረናል:- “እነርሱም [ክርስቲያኖች] የተገደሉት ፌዝና ቀልድ በተሞላ ሁኔታ ነበር። አንዳንዶቹ በዱር አራዊት ቆዳ ከተሸፈኑ በኋላ ውሾች ቦጫጭቀው እንዲገድሉአቸው ሲደረግ፣ [በስቅላት]፣ * በጨለማ እንደጧፍ በመንደድ የሞቱም ነበሩ።” በንጉሠ ነገሥት ዶሚሽያን ዘመን ደግሞ (ከ81-96 እዘአ) ሌላ የስደት ማዕበል ተነስቶ ዮሐንስ ራሱ በጳጥሞስ ደሴት በግዞት እንዲታሰር ተደርጎአል። ኢየሱስ “እኔን አሳደውኝ እንደሆነ እናንተንም ያሳድዱአችኋል” ሲል የተናገረው ቃል በትክክል ተፈጽሞ ነበር።—ዮሐንስ 15:20፤ ማቴዎስ 10:22

9. (ሀ) ሰይጣን በአራተኛው መቶ ዘመን እዘአ ላይ እንዴት ያለ ትልቅ የማታለያ መሣሪያ አቋቋመ? ይህስ የየትኛው ድርጅት ዋነኛ ክፍል ሆነ? (ለ) በአንደኛውና በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ያሉ ገዥዎች የይሖዋ ምሥክሮችን ያሰቃዩት እንዴት ነው?

9 በአራተኛው መቶ ዘመን እዘአ ላይ ደግሞ ይህ አሮጌ እባብ፣ ሰይጣን ዲያብሎስ ከማታለያ ዘዴዎቹ ሁሉ እጅግ የረቀቀውን የሕዝበ ክርስትና የክህደት ሃይማኖት አቋቋመ። ይህ ሃይማኖት በክርስትና ልባስ የተሸፈነ ባቢሎናዊ ሥርዓት ብቻ ነበር። የእባቡ ዘር ዋነኛ ክፍል ከመሆኑም በላይ እርስ በርሳቸው በሚጋጩ ብዙ ኑፋቄዎች ሥር ተከፋፍሎአል። ሕዝበ ክርስትና እንደጥንትዋ ከሃዲ የይሁዳ ምድር ከፍተኛ የደም ዕዳ ተሸክማለች። በአንደኛውና በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ ከሁለቱም ተዋጊ ኃይላት ጎን ተሰልፋለች። እንዲያውም በሕዝበ ክርስትና ውስጥ የነበሩ አንዳንድ የፖለቲካ ገዥዎች በእነዚህ ጦርነቶች በማሳበብ ቅቡዓን የአምላክ አገልጋዮችን ገድለዋል። ኪርሸንካምፍ ኢን ዶችላንድ (በጀርመን አገር የአብያተ ክርስቲያናት ውጊያ) በተባለው የፍሪድሪሽ ዚፕፈል መጽሐፍ ላይ ሂትለር በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ስላደረሰው ስደት የቀረበው የግምገማ ጽሑፍ እንዲህ ይላል:- “[ከምሥክሮቹ መካከል] አንድ ሦስተኛ የሚያክሉት በቀጥታ በመግደያ መሣሪያ፣ ወይም በጭካኔ በተፈጸሙባቸው ድርጊቶች፣ ወይም በረሐብ፣ ወይም በበሽታ፣ ወይም በሥራ ብዛት ሞተዋል። ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ከባድ ግፍ ደርሶባቸዋል። ይህ ሁሉ የደረሰባቸው ለድርድር በማይቀርበው እምነታቸው ምክንያት እምነታቸውን ከብሔራዊው ሶሻሊስታዊ ርዕዮተ ዓለም ጋር ለማስማማት እምቢተኞች በመሆናቸው ነው።” በእርግጥም ስለ ሕዝበ ክርስትናም ሆነ ስለ ቀሳውስትዋ “በእጆችሽም የንጹሐን ድሆች ደም ተገኝቶአል” ሊባል ይቻላል።—ኤርምያስ 2:34 *

10. የእጅግ ብዙ ሰዎች ክፍል የሆኑ ወጣቶች በብዙ አገሮች እንዴት ያለ ስደት ደርሶባቸዋል?

10 ከ1935 ጀምሮ ከእጅግ ብዙ ሰዎች ክፍል የሆኑ ብዙ ታማኝ ወጣቶች በብዙ አገሮች ስደት ደርሶባቸዋል። (ራእይ 7:9) ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በአውሮፓ ካለቀ በኋላም እንኳን በአንድ ከተማ 14 ወጣት የይሖዋ ምሥክሮች ተሰቅለው ተገድለዋል። ለስቅላት ያደረሳቸው ወንጀል ምን ነበር? “ከእንግዲህ ወዲህ ጦርነት” አንማርም ማለታቸው ነበር። (ኢሳይያስ 2:4) አሁን በቅርቡ ደግሞ በሩቅ ምሥራቅና በአፍሪካ ውስጥ ወጣት ወንዶች በዚሁ ጥያቄ ምክንያት ተደብድበው ተገድለዋል ወይም ተረሽነዋል። እነዚህ የኢየሱስ ቅቡዓን ወንድሞች ታማኝ ደጋፊዎች የሆኑት ወጣት ሰማዕታን ከሙታን ተነስተው ቃል በተገባልን አዲስ ምድር ላይ እንደሚኖሩ የተረጋገጠ ነው።—2 ጴጥሮስ 3:13፤ ከ⁠መዝሙር 110:3 NW፤ ከ⁠ማቴዎስ 25:34-40⁠ና ከ⁠ሉቃስ 20:37, 38 ጋር አወዳድር።

ነጭ ልብስ

11. ሰማዕታት የሆኑ ቅቡዓን ክርስቲያኖች “ነጭ ልብስ” የሚቀበሉት እንዴት ነው?

11 ሐዋርያው ጳውሎስ የጥንት ዘመን ሰዎችን እምነትና ፍጹም አቋም ጠባቂነት ከተረከ በኋላ እንዲህ አለ:- “እነዚህም ሁሉ በእምነታቸው ተመስክሮላቸው ሳሉ የተሰጠውን የተስፋ ቃል አላገኙም፣ ያለ እኛ ፍጹማን እንዳይሆኑ እግዚአብሔር ስለ እኛ አንዳች የሚበልጥ ነገርን አስቀድሞ አይቶ ነበርና።” (ዕብራውያን 11:39,  40) ጳውሎስና ሌሎቹ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ይጠብቁ የነበረው “የሚበልጥ ነገር” ምን ነበር? ዮሐንስ በራእይ ተመልክቶት ነበር። “ለእያንዳንዳቸውም ነጭ ልብስ ተሰጣቸው፣ እንደ እነርሱም ደግሞ ይገደሉ ዘንድ ያላቸው የባሪያዎች ባልንጀራዎቻቸውና የወንድሞቻቸው ቁጥር እስኪፈጸም ድረስ ገና ጥቂት ዘመን እንዲያርፉ ተባለላቸው።” (ራእይ 6:11) “ነጭ ልብስ” መቀበላቸው አለመሞትን የለበሱ መንፈሣዊ ፍጥረታት ሆነው ከሙታን ከመነሳታቸው ጋር ይዛመዳል። ከዚያ በኋላ በአምላክ ሰማያዊ ዙፋን ፊት ከሚያገለግሉት 24 ሽማግሌዎች ክፍል ለመሆን ይነሳሉ እንጂ የተገደሉ ነፍሳት ሆነው ከመሠዊያው ሥር አይተኙም። በሰማይም ንጉሣዊ መብት እንደተሰጣቸው የሚያመለክት ዙፋን ይሰጣቸዋል። በተጨማሪም “ነጭ መጎናጸፊያ” ለብሰዋል። ይህም በዚህ ሰማያዊ አደባባይ በይሖዋ ዙፋን ፊት የከበሬታ ቦታ ሊሰጣቸው የሚገቡ ጻድቃን እንደሆኑ የተፈረደላቸው መሆኑን ያመለክታል። ኢየሱስ በሰርዴስ ጉባኤ ለነበሩት ታማኝ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ከገባው ቃል ጋር የሚስማማ ድርጊት ነው። “ድል የነሳው እንዲሁ በነጭ ልብስ ይጎናጸፋል።”—ራእይ 3:5፤ 4:4፤ 1 ጴጥሮስ 1:4

12. ከሙታን የተነሱ ቅቡዓን ‘ጥቂት ጊዜ የሚያርፉት’ በምን መንገድ ነው? የሚያርፉትስ እስከ መቼ ድረስ ነው?

12 ይህ ሰማያዊ ትንሣኤ ኢየሱስ በ1914 ዘውድ ከጫነና ሰይጣንና አጋንንቱን ከሰማይ ጠራርጎ በማውጣት ንጉሣዊ ድሉን ለመጀመር ግልቢያ ከጀመረ በኋላ በ1918 እንደ ጀመረ የሚያሳይ በቂ ማስረጃ አለ። ሆኖም ግን እነዚህ ከሙታን የተነሱ ቅቡዓን “የወንድሞቻቸው ቁጥር እስኪፈጸም ድረስ ገና ጥቂት ዘመን እንዲያርፉ” ተነግሮአቸዋል። ገና በምድር ላይ የቀሩት የዮሐንስ ክፍል አባሎች በመከራና በስደት ተፈትነው ታማኝነታቸውን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል። ከመካከላቸውም አንዳንዶቹ ይገደሉ ይሆናል። በመጨረሻ ግን ታላቂቱ ባቢሎንና ፖለቲካዊ ወዳጆችዋ ላፈሰሱት ንጹሕ ደም ሁሉ ብድራቱን ይከፍላሉ። ይህ እስከሚሆንበት ጊዜ ግን ከሙታን የተነሱት ቅቡዓን በሰማይ የተሰጣቸውን ሥራ እያከናወኑ ይቆያሉ። ያርፋሉ ሲባል የይሖዋን በቀል በትዕግሥት ይጠብቃሉ ማለት ነው እንጂ አለምንም ሥራ ቁጭ ብለው ይቆያሉ ማለት አይደለም። (ኢሳይያስ 34:8፤ ሮሜ 12:19) የሐሰት ሃይማኖትን ጥፋት ከተመለከቱና “የተጠሩና የተመረጡ ታማኞች” በመሆን በዚህ ምድር ላይ በቀረው የሰይጣን ክፉ ዘር ላይ የቅጣት ፍርድ በማውረድ ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ሲተባበሩ የዕረፍታቸው ጊዜ ያበቃል።—ራእይ 2:26, 27፤ 17:14፤ ሮሜ 16:20

‘ሞተው የነበሩት ቀድመው ይነሣሉ’

13, 14. (ሀ) ሐዋርያው ጳውሎስ በገለጸው መሠረት ሰማያዊው ትንሣኤ የጀመረው መቼ ነው? ከሙታን የተነሱትስ እነማን ናቸው? (ለ) በጌታ ቀን በሕይወት የሚገኙት ቅቡዓን ወደ ሰማይ የሚነሱት መቼ ነው?

13 አምስተኛው ማህተም ሲፈታ የተገኘው ዕውቀት ስለ ሰማያዊው ትንሣኤ ከሚናገሩ ሌሎች ጥቅሶች ሁሉ ጋር ይስማማል። ለምሳሌ ያህል ሐዋርያው ጳውሎስ የሚከተለውን ጽፎ ነበር:- “በጌታ [“በይሖዋ፣” NW] ቃል የምንላችሁ ይህ ነውና፣ እኛ ሕያዋን ሆነን ጌታ እስኪመጣ ድረስ የምንቀር ያንቀላፉቱን አንቀድምም። ጌታ ራሱ በትዕዛዝ በመላእክትም አለቃ ድምፅ በእግዚአብሔር መለከት ከሰማይ ይወርዳልና፣ በክርስቶስም የሞቱ አስቀድመው ይነሣሉ፣ ከዚያም በኋላ እኛ ሕያዋን ሆነን የምንቀረው ጌታን በአየር ለመቀበል ከእነርሱ ጋር በደመና እንነጠቃለን። እንዲሁም ሁልጊዜ ከጌታ ጋር እንሆናለን።”—1 ተሰሎንቄ 4:15-17

14 እነዚህ ቁጥሮች የሚነግሩን ታሪክ በጣም የሚያስደንቅ ነው። ቀደም ሲል የሞቱት ቅቡዓን ኢየሱስ በሚገኝበት ጊዜ በሕይወት ከሚኖሩት የኢየሱስ ቅቡዓን ወንድሞች፣ ማለትም እርሱ በሚገኝበት ጊዜ በምድር ላይ ከሚኖሩት ቅቡዓን ቀሪዎች ቀድመው ወደ ሰማይ ይወሰዳሉ። እነዚህ ከክርስቶስ ጋር ህብረት ኖሮአቸው የሞቱ ሰዎች ቀድመው ይነሳሉ። ኢየሱስ ትኩረቱን ወደ እነርሱ በመመለስ ይወርድና ወደ መንፈሣዊ ሕይወት አስነስቶ “ነጭ ልብስ” ያጎናጽፋቸዋል። ከዚህ በኋላ ደግሞ በምድር ላይ በሕይወት የሚገኙት ምድራዊ ሕይወታቸውን ይጨርሳሉ። ከመካከላቸውም ብዙዎቹ በተቃዋሚዎች እጅ ይገደላሉ። ይሁን እንጂ ከእነርሱ በፊት እንደነበሩት ወንድሞቻቸው በሞት አንቀላፍተው አይቆዩም። ከዚህ ይልቅ ወዲያው እንደሞቱ ‘በቅጽበት ዓይን ተለውጠው’ ወደ ሰማይ ይወሰዱና ከኢየሱስና የኢየሱስ አካል ክፍል ከሆኑት ወንድሞቻቸው ጋር አብረው ይኖራሉ። (1 ቆሮንቶስ 15:50-52፤ ከ⁠ራእይ 14:13 ጋር አወዳድር።) ስለዚህ የቅቡዓን ክርስቲያኖች ትንሣኤ የጀመረው አራቱ የአፖካሊፕስ ፈረሰኞች መጋለብ እንደ ጀመሩ ነው።

15. (ሀ) አምስተኛው ማህተም መፈታቱ ምን ዓይነት የምሥራች ሆኖአል? (ለ) የነጩ ፈረስ ድል አድራጊ ጋላቢ ግልቢያውን የሚደመድመው ምን በማድረግ ነው?

15 የዚህ የጥቅልሉ አምስተኛ ማህተም መፈታት እስከ ሞት ድረስ ታማኝነታቸውን ጠብቀው ድል ለነሱት ቅቡዓን ፍጹም አቋም ጠባቂዎች የምሥራች ሆኖላቸዋል። ለሰይጣንና ለዘሮቹ ግን የምሥራች አልሆነላቸውም። ድል አድራጊው ጋላቢ በነጩ ፈረስ ላይ የሚያደርገውን ግልቢያ ምንም ሳያግደው በመቀጠል ‘በክፉው የተያዘው ዓለም’ ፍርድ ወደሚቀበልበት ቀን ይደርሳል። (1 ዮሐንስ 5:19) ይህም በጉ ስድስተኛውን ማህተም በፈታ ጊዜ ግልጽ ሆኖአል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.7 የታላቂቱ ባቢሎን ማንነት በምዕራፍ 33 ውስጥ በሰፊው ተብራርቶአል።

^ አን.8 በባለ ማጣቀሻው የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም ገጽ 1577፣ 5c “የመከራ እንጨት” በሚለው ርዕስ ሥር ካለው መግለጫ ጋር አወዳድር።

^ አን.9 ስለ ሃይማኖት የደም ወንጀለኛነት በምዕራፍ 36 ላይ ሰፋ ያለ ማስረጃ ቀርቦአል።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 102 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

‘የታረዱ ነፍሳት’

የማክሊንቶክና ስትሮንግ ሳይክሎፒድያ የሂውግኖት ሃይማኖት ተከታዮች ከሆኑ ፈረንሣውያን ወላጆች የተወለደውን የ18ኛው መቶ ዘመን እንግሊዛዊ ፕሮቴስታንት ጆን ጆርቲንን በመጥቀስ እንዲህ ብሎአል:- “ስደት በተጀመረበት ቦታ ሁሉ የክርስትና መጨረሻ ሆኖአል። . . . የስደቱ መጠን ጣሪያ ላይ የደረሰውና ከፍተኛ ኃይል አግኝቶ በወንጌል ሃይማኖት ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ማሳደር የጀመረው ክርስትና የሮማ ግዛት ሃይማኖት ከሆነና ለክርስትና ቀሳውስት ከፍተኛ ሀብትና ብልጽግና መስጠት በተጀመረ ጊዜ ነበር።”

[በገጽ 103 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ለእያንዳንዳቸውም ነጭ ልብስ ተሰጣቸው”