በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአምላክ መንግሥት ተወለደ!

የአምላክ መንግሥት ተወለደ!

ምዕራፍ 27

የአምላክ መንግሥት ተወለደ!

ራእይ 7--ራእይ 12:1-17

ርዕሰ ጉዳይ:- ሰማያዊቷ ሴት ወለደች፤ ሚካኤል ከሰይጣን ጋር ተዋግቶ ወደ ምድር ጣለው

ራእዩ የሚፈጸምበት ጊዜ:- ኢየሱስ ዙፋን ላይ ከተቀመጠበት ከ1914 ጀምሮ እስከ ታላቁ መከራ

1. ከ⁠ራእይ ምዕራፍ 12 እስከ 14 ላይ የተገለጹትን ምልክቶች መረዳታችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?

ተከድኖ የነበረው የአምላክ ቅዱስ ምሥጢር ተገልጦአል። (ራእይ 10:7) በመሲሑ የሚተዳደረው የይሖዋ መንግሥት አሁን እውን ሆኖአል። በመግዛት ላይ ነው! የመንግሥቱ መገኘት ለሰይጣንና ለዘሮቹ ጥፋት የሚያመጣ ሲሆን ለአምላክ ሰማያዊ ድርጅት ዘሮች ግን ታላቅ ድል የሚያስገኝ ነው። ሰባተኛው መልአክ ገና ስለ ሦስተኛው ወዮታ የሚገልጥልን ነገር ስላለው መለከቱን መንፋቱን አላቆመም። (ራእይ 11:14) ከ⁠ራእይ 12 እስከ 14 ባሉት ምዕራፎች ውስጥ የተገለጹት ምልክቶች በዚህ ወዮታና የአምላክን ቅዱስ ምሥጢር በመፈጸሙ ተግባር የተጠቃለሉትን ነገሮች እንድንረዳ የማስተዋል ችሎታችንና አድናቆታችንን ያሰፉልናል።

2. (ሀ) ዮሐንስ ምን ታላቅ ምልክት ተመለከተ? (ለ) የታላቁ ምልክት ትርጉም የተገለጸው መቼ ነው?

2 አሁን ዮሐንስ ታላቅ ምልክት አየ። ይህ ምልክት የአምላክን ሕዝቦች ትኩረት የሚስብ ነው። በጣም አስደናቂ የሆነ ትንቢታዊ ራእይ የሚያስተዋውቅ ሲሆን የዚህም ራእይ ትርጉም በመጋቢት 1, 1925 መጠበቂያ ግንብ እትም ላይ “የብሔር መወለድ” በሚል ርዕሰ ትምህርትና በ1926 ደግሞ ነፃ መውጣት በተባለው መጽሐፍ ተብራርቶ ነበር። ይህ መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት ያስቻለው ደማቅ ብርሃን በይሖዋ ሥራ እድገት ላይ ታሪካዊ የሆነ ምዕራፍ ከፍቶአል። ስለዚህ ዮሐንስ ድራማውን ሲገልጽልን እናዳምጥ:- “ታላቅ ምልክትም በሰማይ ታየ፣ ፀሐይን ተጎናጽፋ ጨረቃ ከእግሮችዋ በታች ያላት በራስዋም ላይ የአሥራ ሁለት ከዋክብት አክሊል የሆነላት አንዲት ሴት ነበረች። እርስዋም ፀንሳ ነበር፣ ምጥም ተይዛ ልትወልድ ተጨንቃ ጮኸች።”—ራእይ 12:1, 2

3. በሰማይ የታየችው ሴት ምንድን ነች?

3 ዮሐንስ ለመጀመሪያ ጊዜ በሰማይ ላይ አንዲት ሴት ተመለከተ። እርግጥ ይህች ሴት ቃል በቃል እውነተኛ ሴት አልነበረችም። ምሳሌያዊት ወይም ለአንድ ነገር የቆመች ሴት ነበረች። (ራእይ 1:1) ታዲያ ይህች ሴት ምን ታመለክታለች? በመንፈስ በተነገሩት ትንቢቶች ውስጥ አንዳንድ ጊዜ ሴቶች ከትላልቅ አካላት ጋር የተጋቡ ድርጅቶችን አመልክተዋል። በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ እስራኤል የይሖዋ አምላክ ሚስት እንደሆነች ተገልጾአል። (ኤርምያስ 3:14) በግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ደግሞ የቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤ የክርስቶስ ሙሽራ እንደሆነ ተነግሮአል። (ራእይ 21:9-14) ዮሐንስ እዚህ ላይ የተመለከታት ሴትም ባል ያላት ሴት ነች። ልትወልድም ተቃርባለች። ታዲያ ባልዋ ማን ነው? የወለደችው ልጅ ቆየት ብሎ “ወደ እግዚአብሔርና ወደ ዙፋኑ” ተነጥቆአል። (ራእይ 12:5) ስለዚህ የሕጻኑ አባት ይሖዋ እንደሆነ አስታውቆአል ማለት ነው። ዮሐንስ የተመለከታት ሴትም የይሖዋ ምሳሌያዊ ሚስት መሆን ይኖርባታል ማለት ነው።

4. የአምላክ ምሳሌያዊት ሚስት ልጆች እነማን ናቸው? ዮሐንስ የተመለከታትን ሴት ሐዋርያው ጳውሎስ ምን ሲል ጠርቶአታል?

4 ከስምንት መቶ ዘመናት ገደማ በፊት ይሖዋ ለዚህች ምሳሌያዊ ሚስቱ “ልጆችሽም ከእግዚአብሔር [“ከይሖዋ፣” NW] የተማሩ ይሆናሉ” ብሎ ነበር። (ኢሳይያስ 54:5, 13) ኢየሱስም ይህንን ትንቢት ጠቅሶ እነዚህ ልጆች በኋላ የቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤ አባላት የሆኑት ተከታዮቹ እንደሆኑ አመልክቶአል። (ዮሐንስ 6:44, 45) ስለዚህ እነዚህ የአምላክ ልጆች የተባሉት የዚህ ጉባኤ አባሎች በተጨማሪም የአምላክ ምሳሌያዊ ሚስት ልጆች ናቸው። (ሮሜ 8:14) ሐዋርያው ጳውሎስም “ላይኛይቱ ኢየሩሳሌም ግን በነፃነት የምትኖር ናት፣ እርስዋም እናታችን ናት” በማለት መረጃውን ያጠቃልላል። (ገላትያ 4:26) ስለዚህ ዮሐንስ የተመለከታት “ሴት” “ላይኛይቱ ኢየሩሳሌም” ናት።

5. የይሖዋ ምሳሌያዊ ሚስት 12 ከዋክብት በራስዋ ላይ ያደረገች ስለሆነች ላይኛይቱ ኢየሩሳሌም ምንድን ነች ማለት ነው?

5 ይሁን እንጂ ላይኛይቱ ኢየሩሳሌም ምንድን ነች? ጳውሎስ “ላይኛይቱ” ስላለና ዮሐንስ በራእይ ያያት በሰማይ እንዳለች ስለሆነ ምድራዊ ከተማ እንዳልሆነች ግልጽ ነው። ከ“አዲሲቱ ኢየሩሳሌም” ጋርም አንድ አይደለችም፤ ምክንያቱም አዲሲቱ ኢየሩሳሌም የክርስቶስ ሙሽራ ነች እንጂ የይሖዋ ሚስት አይደለችም። (ራእይ 21:2) አሥራ ሁለት ከዋክብት በራስዋ ላይ ጭና እንደነበረ አስተውሉ። አሥራ ሁለት ቁጥር በድርጅታዊ ሁኔታ ሙሉ መሆንን ያመለክታል። * ስለዚህ እነዚህ 12 ከዋክብት በምድር ላይ የነበረችውን የጥንቷን ኢየሩሳሌም የሚመስል ሰማያዊ ድርጅታዊ መዋቅር የሚያመለክቱ ይመስላል። ላይኛይቱ ኢየሩሳሌም ይሖዋን በማገልገልም ሆነ ለይሖዋ ልጆችን በማስገኘት እንደ ሚስት የሚያገለግለው የይሖዋን መንፈሳዊ ፍጥረታት ያቀፈች ጽንፈ ዓለማዊ ድርጅት ነች።

6. (ሀ) ዮሐንስ የተመለከታት ሴት ፀሐይን የተጎናጸፈች፣ ከእግሮችዋ በታች ጨረቃ ያላትና የከዋክብት አክሊል የደፋች መሆንዋ ምን ያመለክታል? (ለ) የእርጉዝዋ ሴት በምጥ መያዝ የምን ምሳሌ ነው?

6 ይህች ሴት ፀሐይን እንደተጎናጸፈችና ከእግርዋም በታች ጨረቃ እንዳለ ዮሐንስ ተመልክቶአል። በዚህ ላይ አክሊል የሆኑላትን ከዋክብት ስንጨምር ሙሉ በሙሉ በሰማያዊ ብርሃናት ተከብባለች ማለት ነው። የአምላክ ሞገስ በቀንዋና በሌሊትዋ ላይ ያበራላታል። ይህ ሁሉ ዕፁብ ድንቅ ለሆነው ለይሖዋ ሰማያዊ ድርጅት የሚስማማ ምልክት ነው። በተጨማሪም ምጥ የጀመራት ነፍሰ ጡር ሴት ነበረች። መለኮታዊ እርዳታ እንዲሰጣት መጮኋ የምትወልድበት ጊዜ መድረሱን ያመለክታል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ምጥ አንድ ትልቅ ውጤት ለማስገኘት የሚያስፈልገውን አድካሚ ሥራ ያመለክታል። (ከ⁠መዝሙር 90:2፤ ከ⁠ምሳሌ 25:23 [NW] እና ከ⁠ኢሳይያስ 66:7, 8 ጋር አወዳድር።) የይሖዋ ሰማያዊት ድርጅት ለዚህ ታሪካዊ የሆነ የመውለጃ ጊዜ ስትዘጋጅ የምጥ ጣር ይዞአት እንደነበረ አያጠራጥርም።

ትልቁ ቀይ ዘንዶ

7. ዮሐንስ በሰማይ የተመለከተው ሌላው ምልክት ምንድን ነው?

7 ዮሐንስ ቀጥሎ የተመለከተው ምንድን ነው? “ሌላም ምልክት በሰማይ ታየ፤ እነሆም ታላቅ ቀይ ዘንዶ ሰባት ራሶችና አሥር ቀንዶችም ነበሩት በራሶቹም ላይ ሰባት ዘውዶች ነበሩ፣ ጅራቱም የሰማይን ከዋክብት ሲሶ እየሳበ ወደ ምድር ጣላቸው። ዘንዶውም ሴቲቱ በወለደች ጊዜ ሕፃንዋን እንዲበላ ልትወልድ ባላት ሴት ፊት ቆመ።”—ራእይ 12:3, 4

8. (ሀ) ታላቁ ቀይ ዘንዶ ማን ነው? (ለ) ዘንዶው ሰባት ራሶች፣ አሥር ቀንዶችና በእያንዳንዱም ራስ ላይ ዘውድ ያለው መሆኑ ምን ያመለክታል?

8 ይህ ዘንዶ “የቀደመው እባብ” ሰይጣን ነው። (ራእይ 12:9፤ ዘፍጥረት 3:15) ያደነውን ጨርሶ ለመዋጥ የሚችል ባለ ሰባት ራስ አስፈሪና አጥፊ ዘንዶ ነው። መልኩም ቢሆን እንግዳና ያልተለመደ ነው። ሰባቱ ራሶችና አሥሩ ቀንዶች በ⁠ራእይ ምዕራፍ 13 ላይ የተገለጸው ፖለቲካዊ አውሬ ፈጣሪ መሆኑን ያመለክታሉ። በተጨማሪም ይህ አውሬ ሰባት ራሶችና አሥር ቀንዶች አሉት። ሰይጣን በእያንዳንዱ ራስ ላይ አንዳንድ ዘውድ፣ በጠቅላላው ሰባት ዘውዶች ስለጫነ በዚህ አውሬ የተወከሉት የዓለም ኃይላት በሙሉ በሰይጣን ግዛት ሥር እንዳሉ እርግጠኞች ለመሆን እንችላለን። (ዮሐንስ 16:11) አሥሩ ቀንዶች ሰይጣን በዚህ ዓለም ላይ ለነበረው ፍጹም ሥልጣን ተስማሚ ምሳሌዎች ናቸው።

9. ዘንዶው በጅራቱ “የሰማይን ከዋክብት ሲሶ” ወደ ምድር ስቦ ማውረዱ ምን ያመለክታል?

9 በተጨማሪም ዘንዶው በመንፈሳዊው ዓለም ላይ ሥልጣን አለው። በጅራቱ “የሰማይን ከዋክብት ሲሶ” እየጎተተ አውርዶአል። ከዋክብት መላእክትን ሊያመለክቱ ይችላል። (ኢዮብ 38:7) “ሲሶ” ወይም አንድ ሦስተኛ ስለተጠቀሰ በቀላሉ የማይገመት ብዛት ያላቸው መላእክት በሰይጣን እንደተሳሳቱ ያመለክታል። እነዚህ መላእክት በሰይጣን ቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ ሊያመልጡ አይችሉም። ወደ አምላክ ቅዱስ ድርጅት ሊመለሱ አይችሉም። በንጉሣቸው ወይም በገዥያቸው በሰይጣን የሚጎተቱ አጋንንት ሆነዋል። (ማቴዎስ 12:24) በተጨማሪም ሰይጣን ወደ ምድር ጥሎአቸዋል። ይህም ሰይጣን ዓመፀኞቹን የአምላክ ልጆች ገፋፍቶ ወደ ምድር እንዲወርዱና ከሰዎች ሴት ልጆች ጋር አብረው እንዲኖሩ ባደረገበት በኖህ ዘመን የተፈጸመውን የሚያመለክት እንደሆነ አያጠራጥርም። እነዚህ ‘ኃጢአት የሠሩ መላእክት’ ቅጣታቸውን እንዲቀበሉ ሲል አምላክ እንጦርጦስ በተባለው ወህኒ ቤት የሚመስል ሁኔታ ውስጥ አኑሮአቸዋል።—ዘፍጥረት 6:4፤ 2 ጴጥሮስ 2:4፤ ይሁዳ 6

10. ቀጥሎ የታዩት የትኞቹ ተጻራሪ ድርጅቶች ናቸው? ዘንዶውስ ሴቲቱ እንደ ወለደች ልጅዋን ሊውጥ የፈለገው ለምንድን ነው?

10 በዚህ መንገድ ሁለት ተጻራሪ ድርጅቶች በግልጽ መታየት ጀምረዋል። እነርሱም በሴቲቱ የተመሰለው የይሖዋ ሰማያዊ ድርጅትና የአምላክን ጽንፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት የሚገዳደረው የሰይጣን አጋንንታዊ ድርጅት ናቸው። ታላቁ የሉዓላዊነት ጥያቄ መልስ ማግኘት ይኖርበታል። ይሁን እንጂ መልስ የሚያገኘው እንዴት ነው? ሰይጣን አሁንም አጋንንቱን ከኋላው እየጎተተ እንደ ጨካኝ አውሬ የሚውጠውን ለመፈለግ ይዞራል። ሴቲቱ የምትወልድበትን ጊዜ ይጠባበቅ ነበር። ይህ ሲጠበቅ የኖረው ሕጻን እርሱንም ሆነ ሲገዛው የኖረውን ዓለም እንደሚያጠፋ ስለሚያውቅ ሊውጠው ይፈልጋል።—ዮሐንስ 14:30

ልጅ፣ ወንድ ልጅ

11. ዮሐንስ የሴቲቱን ልጅ መወለድ የገለጸው እንዴት ነው? ልጁስ “ልጅ፣ ወንድ ልጅ” የተባለው ለምንድን ነው?

11 አሕዛብ አምላክ ጣልቃ ሳይገባባቸው እንዲገዙ የተፈቀደላቸው ጊዜ በ1914 ተፈጸመ። (ሉቃስ 21:24) ሴቲቱም በዚህ በተወሰነው ጊዜ ልጅዋን ወለደች። “አሕዛብንም ሁሉ በብረት በትር ይገዛቸው ዘንድ ያለውን ልጅ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ልጅዋም ወደ እግዚአብሔርና ወደ ዙፋኑ ተነጠቀ። ሴቲቱም ሺህ ከሁለት መቶ ስድሳ ቀን በዚያ እንዲመግቡአት በእግዚአብሔር ተዘጋጅቶላት ወደ ነበረው ስፍራ ወደ በረሀ ሸሸች።” (ራእይ 12:5, 6) ሕጻኑ “ልጅ፣ ወንድ ልጅ” ነበር። ዮሐንስ በዚህ ድርብ ስም የተጠቀመው ለምንድን ነው? አሕዛብን ለመግዛት ሙሉ ብቃት፣ ችሎታና ኃይል ያለው መሆኑን ለማመልከት ነው። በተጨማሪም የሕጻኑ መወለድ በጣም አስደሳችና ታላቅ ክንውን መሆኑን ያጎላል። የአምላክን ቅዱስ ምሥጢር በመፈጸም ረገድ ዋነኛ ድርሻ የሚያበረክት ድርጊት ነው። እንዲያውም ይህ ወንድ ልጅ “አሕዛብን ሁሉ በብረት በትር” የሚገዛቸው ነው!

12. (ሀ) ይሖዋ በመዝሙር መጻሕፍት ውስጥ ስለ ኢየሱስ በትንቢት ምን ቃል ገብቶ ነበር? (ለ) ሴቲቱ “አሕዛብን በብረት በትር ይቀጠቅጣቸው ዘንድ ያለውን ወንድ ልጅ” መውለድዋ የምን ምሳሌ ነው?

12 ይህን ሐረግ ከዚህ በፊት አልሰማችሁትምን? አዎ፣ ይሖዋ ስለ ኢየሱስ ትንቢት ሲናገር “በብረት በትር ትጠብቃቸዋለህ፣ እንደ ሸክላ ሠሪ ዕቃም ትቀጠቅጣቸዋለህ” ብሎ ነበር። (መዝሙር 2:9) በተጨማሪም ስለ ኢየሱስ የሚከተለው ትንቢት ተነግሮ ነበር። “እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] የኃይልን በትር ከጽዮን ይልክልሃል፣ በጠላቶችህም መካከል ግዛ።” (መዝሙር 110:2) ስለዚህ ዮሐንስ የተመለከተው ልደት ኢየሱስ ክርስቶስን በቅርብ የሚመለከት ነው። ኢየሱስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደ ዘመናችን አቆጣጠር ከድንግል መወለዱን ወይም በ33 እዘአ ከሙታን ተነስቶ መንፈሳዊ ሕይወት ማግኘቱን የሚያመለክት አይደለም። ወይም ከሥጋዊ አካል ወደ መንፈሳዊ አካል ተለውጦ ወደ ሌላ ዓለም መዛወሩን የሚያመለክት አይደለም። የአምላክ መንግሥት በ1914 መወለዱንና ወደ 20 ለሚጠጉ መቶ ዘመናት በሰማይ ሆኖ ሲጠባበቅ የቆየው ኢየሱስ ንጉሥ ሆኖ ዘውድ መጫኑን የሚያመለክት ነው።—ራእይ 12:10

13. ወንዱ ልጅ ‘ወደ አምላክና ወደ ዙፋኑ መወሰዱ’ ምን ያመለክታል?

13 ይሖዋ ሚስቱን ወይም አዲስ የተወለደውን ልጁን ሰይጣን እንዲውጥበት ፈጽሞ አይፈቅድም። ወንዱ ልጅ ሲወለድ “ወደ እግዚአብሔርና ወደ ዙፋኑ” ተነጥቆአል። ይህ በመደረጉም ይሖዋ ቅዱስ ስሙን ለማስቀደስ በመሣሪያነት የሚጠቀምበት የዚህ አዲስ የተወለደ መንግሥት ጠባቂና ተንከባካቢ ሆኖአል። ሴቲቱም በዚሁ ጊዜ አምላክ በምድረ በዳ ወዳዘጋጀላት ሥፍራ ሸሽታለች። ይህን በተመለከተ በኋላ ተጨማሪ ማብራሪያ ይሰጣል። በተጨማሪም ሰይጣን በሰማይ በተወለደው መንግሥት ላይ ጉዳት ሊያደርስ ፈጽሞ የማይችልበትን ሁኔታ የሚፈጥር ታላቅ ክንውን የሚፈጸምበት መድረክ ተመቻቸ። ታዲያ ይህ ክንውን ምንድን ነው?

በሰማይ ጦርነት ተደረገ!

14. (ሀ) ዮሐንስ እንደሚነግረን ሰይጣን ዳግመኛ በመንግሥቲቱ ላይ ጥቃት እንዳያደርስ የሚያደርገው ምን እርምጃ ይወሰድበታል? (ለ) ሰይጣንና አጋንንቱ ታግደው የሚቆዩት በየትኛው አካባቢ ነው?

14 ዮሐንስ እንዲህ ሲል ይነግረናል:- “በሰማይም ሰልፍ ሆነ፤ ሚካኤልና መላእክቱ ዘንዶውን ተዋጉ። ዘንዶውም ከመላእክቱ ጋር ተዋጋ፣ አልቻላቸውምም፣ ከዚያም ወዲያ በሰማይ ስፍራ አልተገኘላቸውም። ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው፣ ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፤ ወደ ምድር ተጣለ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ።” (ራእይ 12:7-9) ስለዚህ የአምላክን ቅዱስ ምስጢር ወደ ፍጻሜ የሚያመጣው አስደናቂ ክንውን የሰይጣን ከሰማይ መወርወር ይሆናል። አጋንንቱም ከእርሱ ጋር ወደ ምድር ይጣላሉ። መላውን ምድር አምላኩ እስኪሆንለት ድረስ ያሳተው ሰይጣን ዲያብሎስ ዓመፁን በጀመረበት በዚህ ምድር አካባቢ ተወስኖ ይቆያል።—2 ቆሮንቶስ 4:3, 4

15, 16. (ሀ) ሚካኤል ማን ነው? ይህንንስ እንዴት እናውቃለን? (ለ) ሰይጣንን ከሰማይ የሚጥለው ሚካኤል መሆኑ ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?

15 ይህን ታላቅ ድል በይሖዋ ስም የሚያስገኘው ማን ነው? ሚካኤልና መላእክቱ እንደሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። ይሁን እንጂ ሚካኤል ማን ነው? “ሚካኤል” የሚለው ስም ትርጉሙ “እንደ አምላክ ያለ ማን ነው?” ማለት ነው። ስለዚህ ሚካኤል ከይሖዋ ጋር የሚወዳደር ማንም ሊኖር እንደማይችል በማረጋገጥ የይሖዋን ጽንፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ እንደሚፈልግ የተረጋገጠ ነው። በ⁠ይሁዳ ቁጥር 9 ላይ “የመላእክት አለቃ ሚካኤል” ተብሎአል። “የመላእክት አለቃ” የሚለው የማዕረግ ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሰጠው ለኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ መሆኑን ማስተዋል ተገቢ ነው። * ጳውሎስ ስለ እርሱ ሲናገር እንዲህ ብሎአል:- “ጌታ ራሱ በትእዛዝ በመላእክት አለቃም ድምፅ በእግዚአብሔርም መለከት ከሰማይ ይወርዳልና።” (1 ተሰሎንቄ 4:16) “የመላእክት አለቃ” ማለት “ሊቀ መላእክት” ማለት ነው። ስለዚህ የራእይ መጽሐፍ ስለ “ሚካኤልና መላእክቱ” መናገሩ ሊያስደንቅ አይገባም። መጽሐፍ ቅዱስ መላእክቱ ለጻድቁ የአምላክ አገልጋይ እንደሚገዙ በሚናገርባቸው ሌሎች ቦታዎችም ኢየሱስን ይጠቅሳል። በዚህም ምክንያት ጳውሎስ “ጌታ ኢየሱስ ከሥልጣኑ መላእክት ጋር ከሰማይ በእሳት” ስለመገለጡ ተናግሮአል።—2 ተሰሎንቄ 1:7፤ በተጨማሪም ማቴዎስ 24:30, 31⁠ንና ማቴዎስ 25:31ን ተመልከት።

16 እነዚህና ሌሎች ጥቅሶች ሚካኤል ተብሎ የተጠራው በሰማያዊ ቦታው ላይ ያለው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም ወደሚል የማይቀር መደምደሚያ ያደርሰናል። አሁን በዚህ የጌታ ቀን ውስጥ “ይሖዋ ይገስጽህ” ብሎ ሰይጣንን አይናገረውም። አሁን የፍርድ ጊዜ ስለሆነ ኢየሱስ ሚካኤል በመሆን ክፉዉን ሰይጣንና አጋንንታዊ መላእክቱን ከሰማይ ወደ ታች ጥሏቸዋል። (ይሁዳ 9፤ ራእይ 1:10) በዙፋን ላይ የተቀመጠው አዲስ ንጉሥ እንደመሆኑ መጠን ይህን ርምጃ የሚወስደው እርሱ መሆኑ የተገባ ነው። ከዚህም ሌላ በኤደን ላይ ተስፋ የተሰጠበትና የእባቡን ጭንቅላት በመጨፍለቅ ለዘላለም የሚያጠፋው ዘር እርሱ ነው። (ዘፍጥረት 3:15) ኢየሱስ ሰይጣንን ከሰማይ አስወጥቶ አሁን ወደዚያ የመጨረሻ የማጥፋት ርምጃ እየገሰገሰ ነው።

“ሰማያት ደስ ይበላችሁ”

17, 18. (ሀ) ሰይጣን ከሰማይ በመጣሉ በሰማይ እንዴት ያለ ስሜት እንደተፈጠረ ዮሐንስ ገልጾአል? (ለ) ዮሐንስ የሰማው ታላቅ ድምፅ ከየት የመነጨ ነበር?

17 በሰይጣን ላይ ይህን የመሰለ ታላቅ ውድቀት በደረሰበት ጊዜ በሰማይ እንዴት ያለ ደስታ እንደተፈጠረ ዮሐንስ ይነግረናል:- “ታላቅም ድምፅ በሰማይ ሰማሁ እንዲህ ሲል:- አሁን የአምላካችን ማዳንና ኃይል መንግሥትም የክርስቶስም ሥልጣን ሆነ፣ ቀንና ሌሊትም በአምላካችን ፊት የሚከሳቸው የወንድሞቻችን ከሳሽ ተጥሎአልና። እነርሱም ከበጉ ደም የተነሣ ከምስክራቸውም ቃል የተነሣ ድል ነሡት፣ ነፍሳቸውንም እስከ ሞት ድረስ አልወደዱም። ስለዚህ፣ ሰማይና በውስጡ የምታድሩ ሆይ፣ ደስ ይበላችሁ!”—ራእይ 12:10-12ሀ

18 ዮሐንስ የሰማው የማንን ታላቅ ድምፅ ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ማን እንደሆነ አይነግረንም። ይሁን እንጂ በ⁠ራእይ 11:17 ላይ የተጠቀሰው ተመሳሳይ ድምፅ 144, 000ዎቹን ቅዱሳን ሊያመለክቱ በሚችሉበት በሰማያዊ ቦታቸው ከሚገኙት 24 ሽማግሌዎች የወጣ ነበር። (ራእይ 11:18) ስደት ይደርስባቸው የነበሩት ገና በምድር ላይ የቀሩ ቅቡዓን የአምላክ አገልጋዮች “ወንድሞቻችን” ስለተባሉ ይህ ቃል ከእነርሱ የመነጨ ሊሆን ይችላል። አለጥርጥር እነዚህ ታማኝ ግለሰቦች ሰይጣንና አጋንንት ጭፍሮቹ ከሰማይ ከተጣሉ በኋላ ወዲያው ትንሣኤ ስለሚያገኙ ድምፃቸውን ከዚህ ድምፅ ጋር ለማስተባበር እንደሚችሉ አያጠራጥርም።

19. (ሀ) የአምላክ ቅዱስ ምሥጢር መፈጸሙ ኢየሱስ ምን እንዲያደርግ መንገድ ይከፍትለታል? (ለ) ሰይጣን “የወንድሞቻችን ከሳሽ” ተብሎ መጠራቱ ምን ያመለክታል?

19 የአምላክ ቅዱስ ምሥጢር መፈጸም ኢየሱስ በይሖዋ መንግሥት ያለውን ሥልጣን እንዲይዝ ይጠይቃል። ስለዚህ አምላክ ታማኝ የሰው ልጆችን ነፃ ለማውጣት ያወጣው ታላቅ ዓላማ ይፈጸማል። ኢየሱስ በአሁኑ ጊዜ በምድር ላይ ለሚኖሩት ፈሪሐ አምላክ ያላቸው ደቀ መዛሙርቱ ብቻ ሳይሆን በአምላክ መታሰቢያ ውስጥ ለሚኖሩት ቁጥር ሥፍር የሌላቸው ሙታንም መዳንን ያመጣል። (ሉቃስ 21:27, 28) ሰይጣን “የወንድሞቻችን ከሳሽ” መባሉ በኢዮብ ላይ አቅርቦት የነበረው ክስ ሐሰት መሆኑ ቢረጋገጥም የአምላክን ምድራዊ አገልጋዮች ፍጹም አቋም ጠባቂነት መፈታተኑን እንዳላቆመ ያመለክታል። ሰው ለነፍሱ ሲል ያለውን ሁሉ ይሰጣል የሚለውን ክሱን በብዙ አጋጣሚዎች አቅርቦ ነበር ማለት ነው። ይሁን እንጂ የሰይጣን ጥረት ከንቱ ሆኖ ቀርቷል።—ኢዮብ 1:9-11፤ 2:4, 5

20. ታማኝ ክርስቲያኖች ሰይጣንን ድል የነሱት እንዴት ነው?

20 “ከበጉ ደም የተነሳ” ጻድቅ ሆነው የተቆጠሩት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ምንም ያህል ስደት ቢደርስባቸው ለአምላክና ለኢየሱስ ክርስቶስ መመስከራቸውን ቀጥለዋል። ይህ የዮሐንስ ክፍል ከ120 ዓመታት ለሚበልጥ ጊዜ የአሕዛብ ዘመን በ1914 ከመፈጸሙ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ታላላቅ ጉዳዮች ሲያመለክት ቆይቶአል። (ሉቃስ 21:24) በአሁኑ ጊዜ ደግሞ እጅግ ብዙ ሰዎች ከጎናቸው ተሰልፈው በታማኝነት በማገልገል ላይ ናቸው። ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዳቸውም ቢሆኑ “ሥጋን መግደል የሚቻላቸውን፣ ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን” አይፈሩም። ይህም በዘመናችን በይሖዋ ምሥክሮች ላይ በደረሱት ተሞክሮዎች ተደጋግሞ ተረጋግጦአል። በአፋቸው በሚናገሩት ቃልም ሆነ በጥሩ ክርስቲያናዊ ምግባራቸው ሰይጣን ሐሰተኛ መሆኑን ደጋግመው ስላረጋገጡ ድል ነስተውታል። (ማቴዎስ 10:28፤ ምሳሌ 27:11፤ ራእይ 7:9) ቅቡዓን ክርስቲያኖች ከሙታን ተነስተው ወደ ሰማይ ሲወሰዱ ወንድሞቻቸውን የሚከስሰው ሰይጣን በሰማይ ስለማይኖር በጣም ይደሰታሉ። የመላእክት ሠራዊት በሙሉ “በሰማይና በውስጡ የምታድሩ ሆይ! ደስ ይበላችሁ” የሚለውን ጥሪ ተቀብለው በደስታ የሚፈነድቁበት ጊዜ ነው።

ተፎካካሪ ወዮታ!

21. ሰይጣን በምድርና በባሕር ላይ ወዮታ ያመጣው እንዴት ነው?

21 ሰይጣን በሦስተኛው ወዮታ ምክንያት ሲንገላታ ስለቆየ አሁን የራሱን የረቀቀ ወዮታ በሰው ልጆች ላይ ለማውረድ ተነሳ። “ለምድርና ለባሕር ወዮላቸው፣ ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን እንዳለው አውቆ በታላቅ ቁጣ ወደ እናንተ ወርዶአልና።” (ራእይ 12:12ለ) ሰይጣን ከሰማይ መጣሉና መባረሩ በሰይጣን ቁጥጥር ስር የሚኖሩ ራስ ወዳድ የሰው ልጆች ለሚያበላሹአት ግዑዝ ምድር ወዮታ ሆኖአል። (ዘዳግም 32:5) ከዚህ ይበልጥ ግን ሰይጣን የሚመራበት ‘ግዛ ወይም አጥፋ’ የሚለው መርሆ የሰብዓዊው ኅብረተሰብ አውታር በሆነው ምሳሌያዊ ምድርና ተነዋዋጭ የሆነውን ሕዝብ በሚያመለክተው ባሕር ላይ ወዮታ አምጥቶአል። የሰይጣን ቁጣ በሁለቱ የዓለም ጦርነቶች ጊዜ በሰይጣን ቁጥጥር ስር የሚኖሩት ብሔራት እርስ በርሳቸው ባስነሱት ቁጣ ተንፀባርቆአል። እስከዚህም ጊዜ ድረስ ይህ አጋንንታዊ የቁጣ ፍንዳታ መታየቱ አልቀረም። ይሁን እንጂ በዚህ ሁኔታ ለብዙ ጊዜ አይቀጥልም! (ማርቆስ 13:7, 8) የዲያብሎስ ዘዴዎች ክፉ ሊሆኑ ቢችሉም ሦስተኛው ወዮታ ማለትም የአምላክ መንግሥት የሚወስደው እርምጃ በሚታየው የሰይጣን ድርጅት ላይ የሚያስከትለውን ውጤት ያህል ሊሆኑ አይችሉም!

22, 23. (ሀ) ዮሐንስ ዘንዶው ወደ ምድር ከተጣለ በኋላ የሆነውን ሲገልጽ ምን ምን ተናገረ? (ለ) ዘንዶው “ወንዱን ልጅ የወለደችውን ሴት” ሊያሳድድ የቻለው እንዴት ነው?

22 ሰይጣን ከሰማይ ከተጣለ ወዲህ በምድር ላይ የቀሩት የክርስቶስ ወንድሞች የሰይጣንን የቁጣ በትር ቀምሰዋል። ዮሐንስ እንዲህ በማለት ይነግረናል:- “ዘንዶውም ወደ ምድር እንደ ተጣለ ባየ ጊዜ ወንድ ልጅ የወለደችውን ሴት አሳደዳት። ከእባቡም ፊት ርቃ አንድ ዘመን፣ ዘመናትም፣ የዘመንም እኩሌታ ወደምትመገብበት ወደ ስፍራዋ ወደ በረሀ እንድትበር ለሴቲቱ ሁለት የታላቁ ንሥር ክንፎች ተሰጣት።”—ራእይ 12:13, 14

23 እዚህ ላይ ራእዩ በቁጥር 6 ላይ ሴቲቱ ልጅዋን ከወለደች በኋላ ከዘንዶው ሸሽታ ወደ በረሀ እንደሸሸች ወደተነገረው ሐሣብ መለስ ይላል። ሴቲቱ በሰማይ የምትኖር ከሆነችና ዘንዶው ደግሞ ወደ ምድር የተጣለ ከሆነ እንዴት ሊያሳድዳት ይችላል? ብለን እንጠይቅ ይሆናል። ሴቲቱ በዚህ ምድር ላይ ልጆች ወይም ዘሮች እንዳሉአት አስቡ። ቆየት ብሎም በዚሁ ራእይ ላይ ሰይጣን ዘርዋን በማሳደድ በሴቲቱ ላይ ያለውን ቁጣ እንደሚያሳይ ተገልጾአል። (ራእይ 12:17) በዚህች ምድር ላይ በሴቲቱ ዘር ላይ የሚደርሰው ነገር ሁሉ በሴቲቱ በራስዋ ላይ እንደ ደረሰ ነገር ሊቆጠር ይችላል። (ከማቴዎስ 25:40 ጋር አወዳድር።) በቁጥር እየጨመሩ የሄዱት የዘርዋ ባልንጀሮችም ይህ የሰይጣን ስደት ይደርስባቸዋል።

አዲስ ሕዝብ

24. የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች እስራኤላውያን ከግብፅ በወጡ ጊዜ ያጋጠማቸውን የመሰለ ተሞክሮ ያጋጠማቸው እንዴት ነው?

24 የኢየሱስ ወንድሞች አንደኛው የዓለም ጦርነት ይካሄድባቸው በነበሩት ዓመታት ሁሉ በተቻላቸው መጠን የምስክርነቱን ሥራ በታማኝነት ሲያካሂዱ ቆይተው ነበር። ይህ ሁሉ ሥራ የተፈጸመው ከሰይጣንና ከግብረ አበሮቹ የተፋፋመ ተቃውሞ እየደረሰባቸው ነበር። በኋላ ግን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ያከናውኑት የነበረው ሕዝባዊ ምሥክርነት ሙሉ በሙሉ እንደመቆም አለ። (ራእይ 11:7-10) ይህም የሆነው እሥራኤላውያን በግብፅ አገር ሳሉ የደረሰባቸውን የጭቆና ኑሮ የመሰለ ሁኔታ ባጋጠማቸው ጊዜ ነበር። ይሖዋ በሲና በረሐ እንደነበረው ወዳለ የእረፍት ቦታ በንስር ክንፍ ያመጣቸው በዚህ ጊዜ ነበር። (ዘጸአት 19:1-4) በተመሳሳይም ከ1918 እስከ 1919 ከነበረው የመራራ ስደት ጊዜ በኋላ ይሖዋ በሴቲቱ የተወከሉትን ምስክሮቹን ለእስራኤላውያን የእረፍት ሥፍራ የሆነላቸውን የሲና በረሐ ወደሚመስል መንፈሳዊ ሁኔታ አመጣቸው። ይህም የተደረገላቸው ለጸሎታቸው ምላሽ ለመስጠት ነው።—ከ⁠መዝሙር 55:6-9 ጋር አወዳድር።

25. (ሀ) ይሖዋ እስራኤላውያንን በምድረ በዳ መርቶ እንዳወጣ ሕዝቦቹን በ1919 መርቶ ያወጣው እንዴት ነው? (ለ) የዚህ ብሔር አባላት እነማን ናቸው? እንዴት ወዳለ ሁኔታስ መጥተዋል?

25 በምድረ በዳ ውስጥ ይሖዋ እስራኤላውያንን አንድ ብሔር አድርጎ በማቋቋም በመንፈሳዊም ሆነ በሥጋዊ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ሁሉ እየሰጠ መርቶአቸዋል። በተመሳሳይም ከ1919 ጀምሮ ይሖዋ የሴቲቱን ዘሮች መንፈሳዊ ብሔር አድርጎ አውጥቶአቸዋል። ይሁን እንጂ ይህን ብሔር ከ1914 ጀምሮ በሰማይ ሆኖ ሲገዛ ከቆየው መሲሐዊ መንግሥት ጋር ማሳሳት አይገባንም። ይህ አዲስ ብሔር በ1919 ታላቅ ክብር ወዳለው መንፈሳዊ ርስት ከገቡት በዚህ ምድር ላይ ከሚገኙ የቅቡዓን ክርስቲያኖች ቀሪዎች የተውጣጣ ነው። በአሁኑ ጊዜ ‘በጊዜው የሚያስፈልጋቸውን ምግብ ስለሚያገኙ’ ከፊታቸው ለሚጠብቃቸው ሥራ የሚያስፈልጋቸውን ብርታትና ጥንካሬ አግኝተዋል።—ሉቃስ 12:42፤ ኢሳይያስ 66:8

26. (ሀ) በ⁠ራእይ 12:6, 14 ላይ የተገለጸው ጊዜ ምን ያህል ርዝመት አለው? (ለ) የሦስት ተኩሉ ጊዜ ለምን ዓላማ የዋለ ነበር? የጀመረውና ያለቀውስ መቼ ነው?

26 ይህ የሴቲቱ ዘር የእረፍት ጊዜ የቆየው ለምን ያህል ጊዜ ነው? ለ1,260 ቀን እንደሆነ ራእይ 12:6 ይነግረናል። ራእይ 12:14 ደግሞ ዘመን፣ ዘመናትም፣ የዘመንም እኩሌታ ወይም በሌላ አነጋገር ሦስት ዓመት ተኩል እንደሆነ ይናገራል። ሁለቱም አነጋገሮች የሚያመለክቱት የሦስት ዓመት ተኩል ጊዜ ነው። ይህም ጊዜ በሰሜናዊው ንፍቀ ክበብ በሚገኙ አገሮች ከ1919 የጸደይ ወራት እስከ 1922 የበልግ ወራት የቆየው ጊዜ ነው። ይህ ጊዜ ተመልሰው ለተቋቋሙት የዮሐንስ ክፍል አባሎች የማገገሚያና እንደገና የመደራጃ ጊዜ ሆኖ ነበር።

27. (ሀ) ዮሐንስ በተናገረው መሠረት ዘንዶው ከ1922 በኋላ ምን አደረገ? (ለ) ሰይጣን በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የስደት ጎርፍ ያወረደበት ምክንያት ምንድን ነው?

27 ይሁን እንጂ ዘንዶው ተስፋ ቆርጦ አልተወም። “እባቡም ሴቲቱ በወንዝ እንድትወሰድ ሊያደርግ ወንዝ የሚያህልን ውኃ ከአፉ በስተ ኋላዋ አፈሰሰ።” (ራእይ 12:15) “ወንዝ የሚያህል ውኃ” ወይም “እንደ ጎርፍ ያለ ውኃ” ምንድን ነው? (ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል) የጥንቱ ንጉሥ ዳዊት ተቃውመውት ስለነበሩ ክፉ ሰዎች ሲናገር “የምናምንቴ ሰዎች ፈጣን ጎርፍ” (NW) [“የከንቱ ሰዎች ወንዝ፣” ያንግ] ናቸው ብሎአል። (መዝሙር 18:4, 5, 16, 17) አሁንም በተመሳሳይ ሰይጣን ስደት የሚያነሳሳው “በምናምንቴ ሰዎች” ወይም በከንቱ ሰዎች አማካኝነት ነው። ከ1922 በኋላ ሰይጣን በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የስደት ጎርፍ ተፋባቸው። (ማቴዎስ 24:9-13) ይህም አካላዊ ድብደባን፣ በአዋጆች በመጠቀም ችግር መፍጠርን፣ እስራትን፣ በስቅላት ወይም በርሸና ወይም በመሰየፍ መግደልን ጭምር የሚያጠቃልል ነበር። (መዝሙር 94:20) የተዋረደው ሰይጣን ወደ ሰማያዊቱ የአምላክ ሴት እንዳይደርስ ስለተከለከለ በምድር ላይ ከዘርዋ የቀሩትን ለማጥቃትና በቀጥታም ሆነ ፍጹም አቋማቸውን አበላሽተው የአምላክን ሞገስ እንዲያጡ በማድረግ ሊያጠፋቸው በታላቅ ቁጣ ተነሳሳ። ይሁን እንጂ ውሳኔያቸው እንደ ኢዮብ ጠንካራና የማይናወጥ ሆኖአል። “እስከ ሞት ድረስ ፍጹምነቴን [“ፍጹም አቋሜን፣” NW] ከእኔ አላርቅም” ብለዋል።—ኢዮብ 27:5

28. የስደቱ ጎርፍ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ የነበረው እንዴት ነው?

28 ይህ ጭካኔ የተሞላበት የስደት ጎርፍ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ በጣም ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደረሰ። በአውሮፓ ውስጥ 12,000 ያህል የይሖዋ ምሥክሮች በናዚ የማጎሪያ ካምፖችና ወኅኒ ቤቶች ውስጥ ታጉረው ነበር። ሁለት ሺህ የሚያህሉም ተገድለዋል። የጦርነቱ ጌቶች ይገዙአቸው በነበሩት በኢጣልያ፣ በጃፓን፣ በኮሪያና በታይዋን አገሮች ታማኝ የይሖዋ ምሥክሮች ተመሳሳይ የሆነ የጭካኔ ድርጊት ተፈጽሞባቸዋል። ዲሞክራሲያዊ ናቸው በሚባሉት አገሮች እንኳን የይሖዋ ምሥክሮች ካቶሊኮች ካነሳሱአቸው ረብሸኞች ብዙ መከራ ደርሶባቸዋል። ትኩስ ሬንጅ ፈሶባቸውና የዶሮ ላባ ተሰክቶባቸው ከከተማ ተባርረዋል። ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች እንዲቋረጡና እንዲበተኑ ተደርጎአል። የይሖዋ ምሥክሮች ልጆችም ከትምህርት ቤቶች ተባርረዋል።

29. (ሀ) ዮሐንስ ካልታሰበ ቦታ ስለመጣው እርዳታ የገለጸው እንዴት ነው? (ለ) ምድሪቱ ሴቲቱን የረዳቻት እንዴት ነው? (ሐ) ዘንዶው ምን ሲያደርግ ቆይቶአል?

29 ይሁን እንጂ ካልተጠበቀ አቅጣጫ እርዳታ አገኙ። “ምድሪቱም ሴቲቱን ረዳቻት፣ ምድሪቱም አፍዋን ከፍታ ዘንዶው ከአፉ ያፈሰሰውን ወንዝ ዋጠችው። ዘንዶውም በሴቲቱ ላይ ተቆጥቶ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጠብቁትን የኢየሱስም ምስክር ያላቸውን ከዘርዋ የቀሩትን ሊዋጋ ሄደ።” (ራእይ 12:16, 17ሀ) “ምድሪቱ” ማለትም የሰይጣን ሥርዓት አባል የሆኑ ክፍሎች “ወንዙን” ወይም “ጎርፉን” መዋጥ ጀመሩ። በ1940ዎቹ ዓመታት የይሖዋ ምሥክሮች በዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ፍርድ ቤትና በሌሎች አገሮች በሚገኙ ባለ ሥልጣኖች የአምልኮ ነፃነትን የሚያስከብሩ በርካታ የፍርድ ውሣኔዎችን አገኙ። በመጨረሻም ተባባሪዎቹ መንግሥታት የናዚና ፋሽስት ኃይሎችን ደምስሰው በአምባገነኖች አገዛዝ ሥር ይማቅቁ ለነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች እፎይታ አስገኙ። የዘንዶው ቁጣ እስከ ዛሬ ድረስ ስላልቀዘቀዘ ስደቱ ሙሉ በሙሉ አላቆመም። “የኢየሱስ ምስክር ያላቸውን” በማሳደድ ቀጥሎአል። በብዙ አገሮች ታማኝ የይሖዋ ምሥክሮች በእሥር ቤቶች ውስጥ በመማቀቅ ላይ ናቸው። አንዳንዶችም ፍጹም አቋማቸውን በመጠበቃቸው ምክንያት ተገድለዋል። ይሁን እንጂ ከእነዚህ አገሮች መካከል በአንዳንዶቹ ባለ ሥልጣኖች ተጽዕኖአቸውን ላላ በማድረግ ላይ ናቸው። የይሖዋ ምሥክሮችም የበለጠ ነፃነት ማግኘት ጀምረዋል። * በዚህ መንገድ ምድሪቱ የስደቱን ጎርፍ መዋጥዋን ስለቀጠለች ትንቢቱ በትክክል ተፈጽሞአል።

30. (ሀ) ምድሪቱ ምን ለማድረግ የሚያስችል እርዳታ ሰጥታ ነበር? (ለ) የአምላክ ሕዝቦች ታማኝነትና ፍጹም አቋም ጠባቂነት ምን ውጤት አስገኝቶአል?

30 በዚህ መንገድ ምድሪቱ የአምላክ ሥራ 235 በሚያህሉ አገሮች እንዲስፋፋና ከስድስት ሚልዮን የሚበልጡ ታማኝ የምሥራች ሰባኪዎች እንዲገኙ ያስቻለውን ነፃነት አስገኝታለች። ከብሔራት ሁሉ የተውጣጡ እጅግ ብዙ ሰዎች ከሴቲቱ ዘር ቀሪዎች ጋር በመተባበር አምላክ ከዓለም ስለመለየት፣ በንጹሕ ሥነ ምግባር ስለ መመላለስና ወንድሞቻቸውን ስለ መውደድ የሰጠውን ትእዛዝ በመጠበቅ ላይ ናቸው። ስለ መሲሐዊትዋ መንግሥትም ይመሰክራሉ። ፍጹም አቋም ጠባቂነታቸው የሰይጣንን የስድብ ተግዳሮት ሐሰተኛ መሆኑን ስለሚያጋልጥ ሰይጣንና የሰይጣን ሥርዓት ሊጠፉ የሚገባቸው መሆኑን ያበስራል።—ምሳሌ 27:11

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.5 ከ12 የሥጋዊ እስራኤል ነገዶች፣ ከ12ቱ ሐዋርያት፣ ከ12ቱ የመንፈሳዊ እስራኤል ነገዶች፣ ከ12ቱ በሮች፣ ከ12ቱ መላእክትና ከ12ቱ የአዲሲቱ ኢየሩሳሌም መሠረቶች ጋር አወዳድር።—ራእይ 21:12-14

^ አን.15 ይሁን እንጂ ራእይ 12:9 ስለ “ታላቁ ዘንዶ[ና] . . . መላእክቱ” እንደሚናገር አስተውል። ስለዚህ ዲያብሎስ ራሱን አምላክ ለማድረግ ከመሞከሩም በተጨማሪ የመላእክት አለቃም ለመሆን ሞክሮአል። መጽሐፍ ቅዱስ ግን ይህን የማዕረግ ስም ሰጥቶት አያውቅም።

^ አን.29 በበርካታ አገሮች የሚገኙ ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች ለይሖዋ ምሥክሮች ነፃነት ሰጥተዋል። ከእነዚህ ውሳኔዎች አንዳንዶቹ በገጽ 92 ላይ በሚገኘው ሳጥን ውስጥ ተዘርዝረዋል።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 185 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

“ምድሪቱ አፍዋን ከፈተች”

የሰይጣን የስደት ጎርፍ በብዙ አገሮች ውስጥ በቅቡዓን ክርስቲያኖችና በባልንጀሮቻቸው ላይ ተለቆ ነበር። ይሁን እንጂ አብዛኛውን ጊዜ በሰይጣን በራሱ ሥርዓት ውስጥ የተፈጸሙ ሁኔታዎች ጎርፉ ተውጦ እንዲቀር አስችለዋል።

በዩናይትድ ስቴትስ የተነሳሳው ረብሻ የማነሳሳትና የማሳሰር ጎርፍ በአብዛኛው በ1940ዎቹ ዓመታት ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ባስተላለፋቸው ጥሩ ውሳኔዎች ምክንያት ተውጦአል።

በጀርመንና በጃፓን ግዛት ውስጥ በነበሩት አገሮች በ1945 የተነሳው አስከፊ ስደት ተባባሪዎቹ መንግሥታት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ድል በመንሳታቸው አክትሞአል።

በዶሚኒካን ሪፓብሊክ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ እገዳ በተደረገ ጊዜ ምሥክሮቹ ታስረው፣ ተገርፈውና በጠመንጃ ሰደፍ ተደብድበው ነበር። በ1960 በአምባ ገነኑ ራፋኤል ትሩጂሎ እና በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መካከል ግጭት ሲፈጠር በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የተደነገገው እገዳ ተነሳ።

በናይጄርያ የእርስ በርስ ጦርነት ይደረግ በነበረበት ጊዜ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ይደርስ የነበረው ቃጠሎ፣ አስገድዶ መድፈር፣ ድብደባ፣ ሥቃይና ግድያ የመንግሥት ኃይሎች ይህ ሁሉ አሰቃቂ ነገር ይፈጸምበት የነበረውን ተገንጣይ ክፍለ ሀገር አሸንፈው በቁጥጥር ሥር ሲያደርጉ አበቃ።

በእስፓኝ አገር የክርስቲያኖች ቤት ይደፈርና ክርስቲያኖችም ስለ አምላክ ስለተናገሩና ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችን ስላደረጉ የገንዘብና የእሥራት ቅጣት ይበየንባቸው ነበር። በ1970 መንግሥት ካቶሊክ ያልሆኑ ሃይማኖቶችን በተመለከተ ይከተለው በነበረው ፖሊሲ ላይ ለውጥ በማድረጉ የይሖዋ ምሥክሮች ሕጋዊ እውቅና ሲያገኙ ይህ ሁሉ ስደት አበቃ።

በፖርቱጋል አገር በመቶ የሚቆጠሩ ቤቶች አለፍርድ ቤት ማዘዣ ይፈተሹ ነበር። የይሖዋ ምሥክሮች አካላዊ ጉዳት ይደርስባቸውና በየእስር ቤቶች ይጣሉ ነበር። መጽሐፍ ቅዱሶቻቸውንም ይቀሙ ነበር። በ1974 ወታደራዊ አብዮት ተነስቶ የመንግሥት ለውጥ በተደረገና የመሰብሰብ ነፃነት የሚሰጥ ሕግ በወጣ ጊዜ ይህ የሽብር ፈጠራ ድርጊት ‘ተዋጠ።’

በአርጀንቲና አገር ይገዛ በነበረው ወታደራዊ መንግሥት ዘመን የይሖዋ ምሥክሮች ልጆች ከትምህርት ቤት ይባረሩ ነበር። በአገሪቱ የሚኖሩ ብዙ የይሖዋ ምሥክሮችም ምሥራቹን ስለ ሰበኩ ብቻ ይታሰሩ ነበር። ይህም ስደት በጊዜው የነበረው መንግሥት ለይሖዋ ምሥክሮች ማኅበር ሕጋዊ እውቅና በሰጠበት ዓመት በ1984 አቆመ።

[ገጽ 183 ላይ የሚገኝ ሰንጠረዥ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

1914 የመንግሥቲቱ መወለድ

1919 የአዲስ ሕዝብ መወለድ

1919-1922 የማገገሚያ ጊዜ

1922- የስደት ጎርፍ

[በገጽ 182 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ለምድር ወዮላት