በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአምላክ እስራኤሎችን ማተም

የአምላክ እስራኤሎችን ማተም

ምዕራፍ 19

የአምላክ እስራኤሎችን ማተም

ራእይ 4--ራእይ 7:1-17

ርዕሰ ጉዳይ:- 144,000ዎቹ ታተሙ፣ እጅግ ብዙ ሰዎች በይሖዋ ዙፋንና በበጉ ፊት ቆመው ታዩ

ራእዩ የሚፈጸምበት ጊዜ:- ክርስቶስ በዙፋን ላይ ከተቀመጠበት ከ1914 ጀምሮ እስከ ሺው ዓመት ግዛት

1. ታላቁ የመለኮታዊ ቁጣ ቀን በሚጀምርበት ጊዜ “ማን ሊቆም ይችላል?”

“ማን ሊቆም ይችላል?” (ራእይ 6:17) አዎ፣ በእውነትም ማን ሊቆም ይችላል? ታላቁ የመለኮታዊ ቁጣ ቀን የሰይጣንን ሥርዓት ፈጽሞ ሲያጠፋ የዓለም ገዥዎችና ሕዝቦች ይህንን ጥያቄ ሊጠይቁ ይችላሉ። ለእነርሱ እልቂቱ የሰው ዘሮችን በሙሉ የሚያጠፋ መስሎ ይታያል። ይሁን እንጂ የሰው ልጆችን በሙሉ የሚያጠፋ ጥፋት ይሆናልን? የአምላክ ነቢይ እንዲህ በማለት ማረጋገጫ ስለሚሰጠን ደስ ሊለን ይገባል:- “የእግዚአብሔርን [“የይሖዋን፣” NW] ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል።” (ኢዩኤል 2:32) ሐዋርያው ጴጥሮስና ሐዋርያው ዮሐንስ ይህንን ቁም ነገር ያረጋግጡልናል። (ሥራ 2:19-21፤ ሮሜ 10:13) አዎ፣ የይሖዋን ስም የሚጠሩ ሁሉ ከጥፋቱ ይድናሉ። እነዚህ የይሖዋን ስም የሚጠሩ ሰዎች እነማን ናቸው? የሚቀጥለው ራእይ ሲገለጥ እነማን እንደሆኑ እንመለከታለን።

2. ከይሖዋ የፍርድ ቀን የሚድኑ ሰዎች መኖራቸው አስደናቂ የሚሆነው ለምንድን ነው?

2 የይሖዋን የበቀልና የፍርድ ቀን በሕይወት የሚያልፍ ሰው መኖሩ በእርግጥም የሚያስደንቅ ነገር ነው። ይህንንም ሌላው የአምላክ ነቢይ በሚከተለው ሁኔታ ገልጾታል:- “እነሆ የእግዚአብሔር [“የይሖዋ፣” NW] አውሎ ነፋስ እርሱም ቁጣው የሚያገለባብጥ አውሎ ነፋስ ወጥቶአል። የዓመፀኞችንም ራስ ይገለባብጣል። የእግዚአብሔር [“የይሖዋ፣” NW] ጽኑ ቁጣ የልቡን አሳብ ሠርቶ እስኪፈጽም ድረስ አይመለስም በኋለኛው ዘመን ታስተውሉታላችሁ።” (ኤርምያስ 30:23, 24) በዚህ አውሎ ነፋስ ሳንነካ ለማለፍ በአፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል።—ምሳሌ 2:22፤ ኢሳይያስ 55:6, 7፤ ሶፎንያስ 2:2, 3

አራቱ ነፋሳት

3. (ሀ) ዮሐንስ የተመለከተው መላእክት የሚያከናውኑትን የትኛውን ልዩ አገልግሎት ነው? (ለ) ‘አራቱ ነፋሳት’ የምን ምሳሌ ናቸው?

3 ይሖዋ ይህን ቁጣውን ከመግለጹ በፊት የሰማይ መላእክት ልዩ የሆነ አገልግሎት ይፈጽማሉ። ይህንን አገልግሎታቸውን ዮሐንስ በራእይ ተመልክቶአል። “ከዚህም በኋላ በአራቱ በምድር ማዕዘን ቆመው አራት መላእክት አየሁ። እነርሱም ነፋስ በምድር ቢሆን ወይም በባሕር ወይም በማንም ዛፍ እንዳይነፍስ አራቱን የምድር ነፋሳት ያዙ።” (ራእይ 7:1) ይህ ነገር ዛሬ ለእኛ ምን ትርጉም አለው? እነዚህ አራት ነፋሳት ክፉ በሆነው ምድራዊ ኅብረተሰብ ላይ፣ እንደ ባሕር በሚናወጠው ክፉ የሰው ዘር ላይ፣ እንዲሁም በምድር ሕዝቦች ድጋፍና እርዳታ በሚንቀሳቀሱት ዛፍ መሰል ገዥዎች ላይ የሚወርደውን የጥፋት ፍርድ በጥሩ ሁኔታ የሚያመለክቱ ምሳሌዎች ናቸው።—ኢሳይያስ 57:20፤ መዝሙር 37:35, 36

4. (ሀ) አራቱ መላእክት ምን ያመለክታሉ? (ለ) አራቱ ነፋሳት መለቀቃቸው በሰይጣን ምድራዊ ድርጅት ላይ ምን ውጤት ያስከትላል?

4 እነዚህ አራት መላእክት የጥፋቱን ፍርድ እስከተወሰነው ጊዜ ድረስ አግደው እንዲያቆዩ ይሖዋ የሚጠቀምባቸውን አራት የመላእክት ክፍሎች የሚወክሉ መሆናቸው ምንም አያጠራጥርም። መላእክቱ አግደውት የነበረውን የመለኮታዊ ቁጣ ነፋስ በአንድ ጊዜ ከሰሜን፣ ከደቡብ፣ ከምሥራቅና ከምዕራብ ሲለቁ በጣም ከፍተኛ የሆነ ጥፋት ይደርሳል። ይሖዋ በአራቱ ነፋሳት አማካኝነት የኤላም ሰዎችን በበታተነበት ጊዜ የደረሰውን ሁኔታ የሚመስል ቢሆንም ከዚያ በጣም የበለጠና የከፋ ይሆናል። (ኤርምያስ 49:36-38) ይሖዋ አሞናውያንን ካጠፋበት “አውሎ ነፋስ” የበለጠ ከፍተኛ ጥፋት የሚያስከትል ይሆናል። (አሞጽ 1:13-15) ይሖዋ ሉዓላዊነቱን ለዘላለም በሚያረጋግጥበት የቁጣ ቀን ጸንቶ ለመቆም የሚችል አንድም የሰይጣን ድርጅት ክፍል አይኖርም።—መዝሙር 83:15, 18፤ ኢሳይያስ 29:5, 6

5. የኤርምያስ ትንቢት የአምላክ ፍርድ መላውን ምድር የሚያጠቃልል መሆኑን እንድንረዳ የሚያስችለን እንዴት ነው?

5 የአምላክ ፍርድ መላውን ምድር የሚያጠፋ እንደሚሆን እርግጠኛ ለመሆን እንችላለንን? አሁንም ነቢዩ ኤርምያስ የሚለውን እናዳምጥ። “እነሆ፣ ክፉ ነገር ከሕዝብ ወደ ሕዝብ ይወጣል፣ ጽኑም አውሎ ነፋስ ከምድር ዳርቻ ይነሣል። በዚያም ቀን የእግዚአብሔር [“የይሖዋ፣” NW] ግዳዮች ከምድር ዳር ጀምሮ እስከ ምድር ዳር ድረስ ይሆናሉ።” (ኤርምያስ 25:32, 33) ይህች ዓለም በጨለማ የምትዋጠው ይህ “ጽኑ አውሎ ነፋስ” በሚመጣበት ጊዜ ነው። የዚህ ዓለም ገዥዎች ተጠራርገው ይጠፋሉ። (ራእይ 6:12-14) ይሁን እንጂ የወደፊቱ ሁኔታ ለሁሉ ሰው የጨለመ አይሆንም። ታዲያ አራቱ ነፋሳት ታግደው እንዲቆዩ የተደረገው ለማን ሲባል ነው?

የአምላክ ባሮች መታተም

6. መላእክቱ አራቱን ነፋሳት ገትተው እንዲይዙ የሚያዝዘው ማን ነው? ይህስ ለምን ነገር ጊዜ ያስገኛል?

6 ዮሐንስ በመቀጠል አንዳንዶች ለመዳን እንዴት ምልክት እንደሚደረግባቸው ይገልጻል። እንዲህ ይላል:- “የሕያው አምላክ ማኅተም ያለው ሌላ መልአክ ከፀሐይ መውጫ ሲወጣ አየሁ፣ ምድርንና ባሕርንም ሊጎዱ ለተሰጣቸው ለአራቱ መላእክት በታላቅ ድምፅ እየጮኸ የአምላካችንን ባሪያዎች ግምባራቸውን እስክናትማቸው ድረስ ምድርን ቢሆን ወይም ባሕርን ወይም ዛፎችን አትጉዱ አላቸው።”—ራእይ 7:2, 3

7. አምስተኛው መልአክ ማን ነው? ማንነቱን እንድናውቅ የሚረዳን የትኛው ማስረጃ ነው?

7 ይህ አምስተኛ መልአክ ስሙ ማን እንደሆን ባይገለጽም ከፍ ያለ ክብር የተቀዳጀው ጌታ ኢየሱስ እንደሆነ የሚያረጋግጥልን በቂ ማስረጃ አለን። ኢየሱስ የመላእክት አለቃ በመሆኑ እዚህ ላይ በተጠቀሱት መላእክት ላይ ሥልጣን እንዳለው ተመልክቶአል። (1 ተሰሎንቄ 4:16፤ ይሁዳ 9) ይህ መልአክ የፍርድ ቅጣት ለማስፈጸም “ከፀሐይ መውጫ” እንደሚመጡት ነገሥታት፣ እንደ ይሖዋና እንደ ክርስቶስ፣ እንዲሁም የጥንትዋን ባቢሎን ለማዋረድ እንደ መጡት እንደ ዳርዮስና እንደ ቂሮስ ከምሥራቅ ይወጣል። (ራእይ 16:12፤ ኢሳይያስ 45:1፤ ኤርምያስ 51:11፤ ዳንኤል 5:31) በተጨማሪም ይህ መልአክ ቅቡዓን ክርስቲያኖችን የማተም ሥራ ስለተሰጠው ኢየሱስን ይመስላል። (ኤፌሶን 1:13, 14) ከዚህም በላይ ነፋሳቱ በሚለቀቁበት ጊዜ በአሕዛብ ላይ ፍርድ የሚያስፈጽመውን ሰማያዊ ሠራዊት የሚመራው ኢየሱስ ነው። (ራእይ 19:11-16) ስለዚህ የአምላክ ባሪያዎች ታትመው እስኪያልቁ ድረስ የሰይጣን ምድራዊ ድርጅት ጥፋት እንዲዘገይ የሚያዝዘው ኢየሱስ ነው ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ነው።

8. የማተሙ ሥራ ምንድን ነው? የተጀመረውስ መቼ ነው?

8 ይህ ማኅተም ምንድን ነው? እነዚህ የአምላክ ባሮችስ እነማን ናቸው? የማተሙ ሥራ የተጀመረው የመጀመሪያዎቹ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች በመንፈስ ቅዱስ በተቀቡበት የጰንጠቆስጤ ዕለት በ33 እዘአ ነው። በኋላም አምላክ ‘አሕዛብን ሁሉ’ መጥራትና መቀባት ጀመረ። (ሮሜ 3:29፤ ሥራ 2:1-4, 14, 32, 33፤ 15:14) ሐዋርያው ጳውሎስ ቅቡዓን ክርስቲያኖች የክርስቶስ ንብረት ለመሆናቸው ዋስትና እንዳላቸው ከገለጸ በኋላ “ደግሞም ያተመን የመንፈሱንም መያዣ በልባችን የሰጠን” አምላክ እንደሆነ ጽፎአል። (2 ቆሮንቶስ 1:21, 22፤ ከራእይ 14:1 ጋር አወዳድር።) ስለዚህ እነዚህ ባሪያዎች የአምላክ መንፈሳዊ ልጆች የመሆን መብት ሲሰጣቸው ሰማያዊ ውርሻቸውን ከመቀበላቸው በፊት ልጅነታቸውን የሚያረጋግጥ ምልክት፣ ማኅተም ወይም ዋስትና ይቀበላሉ። (2 ቆሮንቶስ 5:1, 5፤ ኤፌሶን 1:10, 11) ይህ ከሆነ በኋላ እንደሚከተለው ለማለት ይችላሉ:- “የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ይመሰክራል። ልጆች ከሆንን ወራሾች ደግሞ ነን ማለት የእግዚአብሔር ወራሾች ነን፣ አብረንም ደግሞ እንድንከበር አብረን መከራ ብንቀበል ከክርስቶስ ጋር አብረን ወራሾች ነን።”—ሮሜ 8:15-17

9. (ሀ) በመንፈስ ከተወለዱት የአምላክ ልጆች ቀሪዎች ምን ዓይነት ጽናት ይፈለጋል? (ለ) የቅቡዓን ፈተና የሚቀጥለው እስከ መቼ ድረስ ነው?

9 “አብረን መከራ ብንቀበል”፤ ይህ አነጋገር ምን ማለት ነው? ቅቡዓን ክርስቲያኖች የሕይወትን አክሊል እንዲያገኙ እስከ ሞት ድረስ በታማኝነት መጽናት ይኖርባቸዋል። (ራእይ 2:10) ‘አንድ ጊዜ የዳነ ለሁልጊዜ ድኖአል’ እንደሚባለው አይደለም። (ማቴዎስ 10:22፤ ሉቃስ 13:24) ከዚህ ይልቅ “መጠራታችሁንና መመረጣችሁን ታጸኑ ዘንድ ከፊት ይልቅ ትጉ” ተብለው ተመክረዋል። በመጨረሻም እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ “መልካሙን ገድል ተጋድዬአለሁ፣ ሩጫውን ጨርሼአለሁ፣ ሃይማኖትን ጠብቄአለሁ” ለማለት መቻል ይኖርባቸዋል። (2 ጴጥሮስ 1:10, 11፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:7, 8) ስለዚህ በዚህ ምድር ላይ የቀሩት በመንፈስ የተወለዱ የአምላክ ልጆች ኢየሱስና ኢየሱስን የተከተሉት መላእክት የተፈተኑና የታመኑ “የአምላካችን ባሪያዎች” መሆናቸውን በማረጋገጥ ‘በግንባራቸው ላይ’ የማይፋቅ ማኅተም እስኪያትሙላቸው ድረስ ፈተናውና ብጠራው መቀጠል ይኖርበታል። በዚያ ጊዜ የሚደረገው ማኅተም ዘላለማዊ ምልክት ይሆናል። አራቱ የመከራ ነፋሳት በሚለቀቁበት ጊዜ ከመንፈሣዊ እስራኤላውያን መካከል በሥጋ በምድር ላይ በሕይወት የሚቀሩ ቢኖሩም እንኳን የመጨረሻውን ማኅተም ይቀበላሉ። (ማቴዎስ 24:13፤ ራእይ 19:7) የአባሎቹ ቁጥር ይሟላል።—ሮሜ 11:25, 26

የሚታተሙት ስንት ናቸው?

10. (ሀ) የታተሙት ሰዎች ቁጥር የተወሰነ መሆኑን የሚያመለክቱ ጥቅሶች የትኞቹ ናቸው? (ለ) የታተሙት ሰዎች ጠቅላላ ቁጥር ስንት ነው? የተዘረዘሩትስ እንዴት ነው?

10 ኢየሱስ ለነዚህ ሊታተሙ የተዘጋጁ ሰዎች እንዲህ ብሎ ነበር:- “አንተ ታናሽ መንጋ መንግሥትን ሊሰጣችሁ የአባታችሁ በጎ ፈቃድ ነውና አትፍሩ።” (ሉቃስ 12:32) እንደ ራእይ 6:11 እና ሮሜ 11:25 ያሉት ሌሎች ጥቅሶችም የዚህ ታናሽ መንጋ ቁጥር አስቀድሞ የተወሰነና የተመጠነ እንደሆነ ያመለክታሉ። የሚከተሉት የዮሐንስ ቃላት ይህንን ያረጋግጣሉ። “የታተሙትንም ቁጥር ሰማሁ፣ ከእስራኤል ልጆች ነገድ ሁሉ የታተሙት መቶ አርባ አራት ሺህ ነበሩ። ከይሁዳ ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ ታተሙ፣ ከሮቤል ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፣ ከጋድ ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፣ ከአሴር ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፣ ከንፍታሌም ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፣ ከምናሴ ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፣ ከስምዖን ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፣ ከሌዊ ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፣ ከይሳኮር ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፣ ከዛብሎን ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፣ ከዮሴፍ ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፣ ከብንያም ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ ታተሙ።”—ራእይ 7:4-8

11. (ሀ) 12ቱ ነገዶች መጠቀሳቸው ሥጋዊ እስራኤላውያንን የሚያመለክት ሊሆን የማይችለው ለምንድን ነው? (ለ) የራእይ መጽሐፍ 12ቱን ነገዶች የዘረዘረው ለምንድን ነው? (ሐ) በአምላክ እስራኤል ውስጥ የንግሥና ወይም የክህነት ሹመት የተሰጠው ብቸኛ ነገድ ያልኖረው ለምንድን ነው?

11 ታዲያ ይህ ቃል ሥጋዊ እስራኤልን የሚያመለክት አይደለምን? አይደለም። ምክንያቱም የ⁠ራእይ 7:4-8 የነገዶች ዝርዝር ከተለመደው የነገዶች ዝርዝር ይለያል። (ዘኍልቁ 1:17, 47) እዚህ ላይ የተገለጸው ዝርዝር ሥጋዊ አይሁዶችን በየነገዳቸው የሚከፋፍል ሳይሆን መንፈሳዊው እስራኤል ከሥጋዊው እስራኤል ጋር የሚመሳሰል ድርጅታዊ መዋቅር እንዳለው የሚያመለክት ነው። የተመዛዘነና የተመጣጠነ ድርጅት ነው። የዚህ አዲስ ብሔር አባሎች ከአሥራ ሁለት ነገዶች የተውጣጡ 144,000 ሰዎች ናቸው። ይህም ሲባል እያንዳንዱ ነገድ 12,000 አባላት አሉት ማለት ነው። በዚህ የአምላክ እስራኤል ውስጥ ለብቻው የንግስና ወይም የክህነት ሥልጣን የተሰጠው ነገድ የለም። መላው ብሔር እንደ ነገሥታት ሆኖ ይገዛል፣ እንደ ካህናትም ሆኖ ያገለግላል።—ገላትያ 6:16፤ ራእይ 20:4, 6

12. 24ቱ ሽማግሌዎች በበጉ ፊት የ⁠ራእይ 5:9, 10ን ቃላት መዘመራቸው ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?

12 መንፈሳዊ እስራኤል ሆኖ ለመመረጥ የመጀመሪያ ዕድል የተሰጠው ለሥጋዊ አይሁዳውያንና ወደ ይሁዲነት ገብተው ለነበሩ የተገረዙ ሰዎች ቢሆንም ከዚህ ሕዝብ መካከል በዚህ ዕድል የተጠቀሙት በጣም ጥቂቶች ብቻ ነበሩ። በዚህም ምክንያት ይሖዋ ጥሪውን ለአሕዛብም ጭምር ዘረጋ። (ዮሐንስ 1:10-13፤ ሥራ 2:4, 7-11፤ ሮሜ 11:7) አይሁዳውያን ያልሆኑ ሰዎች አስቀድሞ “ከእስራኤል መንግሥት” ርቀው እንደነበሩት የኤፌሶን ሰዎች በአምላክ መንፈስ ታትመው የቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤ አባሎች ለመሆን ቻሉ። (ኤፌሶን 2:11-13፤ 3:5, 6፤ ሥራ 15:14) ስለዚህ 24ቱ ሽማግሌዎች በበጉ ፊት እንደሚከተለው ብለው መዘመራቸው የተገባ ነበር:- “በደምህም ለእግዚአብሔር ከነገድ ሁሉ ከቋንቋም ሁሉ ከወገንም ሁሉ ከሕዝብም ሁሉ ሰዎችን ዋጅተህ ለአምላካችን መንግሥትና ካህናት ይሆኑ ዘንድ አደረግሃቸው፣ በምድርም ላይ ይነግሣሉ።”—ራእይ 5:9, 10

13. የኢየሱስ ግማሽ ወንድም የነበረው ያዕቆብ መልእክቱን “ለተበተኑት አሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች” መጻፉ ትክክል የነበረው ለምንድን ነው?

13 የክርስቲያን ጉባኤ “የተመረጠ ትውልድ፣ የንጉሥ ካህናት፣ ቅዱስ ሕዝብ” ነው። (1 ጴጥሮስ 2:9) በሥጋዊ እስራኤል ምትክ የአምላክ ሕዝብ በመሆን “እውነተኛ እስራኤል” ሆነ። (ሮሜ 9:6-8፤ ማቴዎስ 21:43) * በዚህም ምክንያት የኢየሱስ ግማሽ ወንድም የነበረው ያዕቆብ የሽማግሌነት መልእክቱን “ለተበተኑ ለአሥራ ሁለቱ ወገኖች” ብሎ መጻፉ ተገቢ ነበር። በመጨረሻ ላይ ቁጥራቸው 144,000 ለሚደርሰው የቅቡዓን ክርስቲያኖች ዓለም አቀፍ ጉባኤ መጻፉ ነበር።—ያዕቆብ 1:1

የዘመናችን የአምላክ እስራኤል

14. ይሖዋ ምሥክሮች ከመጀመሪያ ጀምሮ የመንፈሳዊ እስራኤል አባሎች ቁጥር ቃል በቃል 144,000 መሆኑን ያምኑ እንደነበረ የሚያመለክተን ምንድን ነው?

14 የሚያስገርመው ቻርልስ ቴዝ ራስል የመንፈሳዊ እስራኤል አባሎች ቃል በቃል 144,000 ግለሰቦች እንደሚሆኑ ተገንዝቦ ነበር። በ1904 በታተመው የቅዱሳን ጽሑፎች ጥናት ስድስተኛ ጥራዝ በሆነውና አዲስ ፍጥረት በተባለው መጽሐፍ ላይ እንደሚከተለው ጽፎ ነበር:- “የምርጦቹ (የተመረጡት ቅቡዓን) የተቆረጠና የተወሰነ ቁጥር በራእይ ውስጥ (ራእይ 7:4፤ 14:1) በተደጋጋሚ እንደተገለጸው ‘ከሰዎች መካከል የተዋጁ’ 144,000 ሰዎች እንደሚሆኑ የምናምንበት በቂ ምክንያት አለን።” በ1930 በመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በታተመው ብርሃን አንደኛ መጽሐፍ በተባለው መጽሐፍ ላይም በተመሳሳይ “144,000ዎቹ የክርስቶስ አካል አባላት የተመረጡ፣ የተቀቡና የታተሙ እንደሆኑ” ተገልጾአል። የይሖዋ ምሥክሮች እስከ ዛሬ ድረስ አለምንም ማወላወል የመንፈሳዊ እስራኤል አባላት 144,000 ቅቡዓን ክርስቲያኖች እንደሆኑ ያምናሉ።

15. የጌታ ቀን ከመጀመሩ ቀደም ብሎ ቅን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የአሕዛብ ዘመን ከተፈጸመ በኋላ ሥጋዊ አይሁዳውያን ምን ዓይነት መብት እንደሚያገኙ ያምኑ ነበር?

15 ይሁን እንጂ በአሁኑ ጊዜ ለሥጋዊ እስራኤል አንድ ዓይነት የተለየ ሞገስ ሊሰጥ አይገባምን? የጌታ ቀን ከመምጣቱ በፊት በነበሩት ዓመታት ቅን የሆኑት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ገና የአምላክን ቃል እውነቶች ይመረምሩ የነበረበት ጊዜ ስለነበረ የአሕዛብ ዘመን ከተፈጸመ በኋላ አይሁዳውያን እንደገና በአምላክ ፊት የተለየ አቋም ይሰጣቸዋል የሚል አስተሳሰብ ነበር። በዚህም ምክንያት ጊዜው ቀርቦአል (የቅዱሳን ጽሑፎች ጥናት ሁለተኛ ጥራዝ) የተባለውና በ1889 የታተመው የሲ ቲ ራስል መጽሐፍ ኤርምያስ 31:29-34ን ለሥጋዊ አይሁዳውያን በመጥቀስ የሚከተለውን ብሎ ነበር:- “እስራኤል በአሕዛብ ግዛት ሥር ሆና ቅጣት የምትቀበልበት ዘመን [ከ607] ከክርስቶስ ልደት በፊት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እንደ ቀጠለ ዓለም በሙሉ ተመልክቶአል። ‘ሰባቱ ዘመናት’ ማለትም 2,520ዎቹ ዓመታት ከሚፈጸሙበት ከ1914 በፊት የእስራኤል ብሔር ተመልሶ ይደራጃል ብለን የምንጠብቅበት ምክንያት የለንም።” በዚያን ጊዜ የአይሁዳውያን ብሔር ተመልሶ የሚቋቋምበት ጊዜ በጣም የቀረበ መስሎ ነበር። በተለይ በ1917 ብሪታንያ በባልፉር መግለጫ አማካኝነት የፍልስጥኤምን ምድር የአይሁዳውያን አገር ለማድረግ ድጋፍ እንደምትሰጥ ቃል ከገባች በኋላ ይህ ግምት በጣም ተጠናክሮ ነበር።

16. የይሖዋ ምሥክሮች የክርስትናን መልእክት ለሥጋዊ አይሁዶች ለማድረስ ምን ልዩ ጥረት አድርገው ነበር? ምንስ ውጤት አገኙ?

16 ከመጀመሪያው የዓለም ጦርነት በኋላ የፍልስጥኤም ምድር በታላቋ ብሪታንያ ሞግዚትነት የሚተዳደር ግዛት ሆነ። በዚህም ምክንያት ብዙ አይሁዶች ወደዚች ምድር ለመመለስ ቻሉ። በ1948 የእስራኤል ፖለቲካዊ ብሔር ተወለደ። ታዲያ ይህ ሁሉ ክንውን አይሁዳውያን መለኮታዊ በረከት እንደሚያገኙ አያመለክትምን? የይሖዋ ምሥክሮች ለብዙ ዓመታት ይህን የመሰለ እምነት ነበራቸው። በዚህም ምክንያት በ1925 ለአይሁዳውያን ማጽናኛ የተባለ ባለ 128 ገጽ መጽሐፍ አትመው አወጡ። በ1929 ለአይሁዳውያን ታስቦ የተዘጋጀና ስለ ኢዮብ መጽሐፍ የሚያብራራ ሕይወት የተባለ ባለ 360 ገጽ መጽሐፍ ታትሞ ወጣ። በተለይ በኒውዮርክ ከተማ መሲሐዊውን መልእክት ለአይሁዳውያን ለማዳረስ ከፍተኛ ጥረት ተደርጎ ነበር። ጥቂት ግለሰቦች ለዚህ ጥረት አዎንታዊ ምላሽ ቢሰጡም እንኳን አብዛኞቹ አይሁዳውያን በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበሩት አባቶቻቸው የመሲሑን መገኘት ለመቀበል እምቢተኞች ሆነዋል።

17, 18. በምድር ላይ የነበሩ የአምላክ ባሮች ስለ አዲሱ ቃል ኪዳንና ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የተሐድሶ ትንቢቶች ምን ለመረዳት ቻሉ?

17 አይሁዳውያን በግለሰብ ደረጃም ሆነ በብሔር ደረጃ በ⁠ራእይ 7:4-8 ላይም ሆነ ስለ ጌታ ቀን በሚናገሩ በሌሎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ላይ የተገለጸው እስራኤል እንዳልሆኑ ግልጽ ነበር። አይሁዳውያኑ የአባቶቻቸውን ወግ በመከተል በመለኮታዊው ስም ለመጠቀም እምቢተኞች ሆነዋል። (ማቴዎስ 15:1-3, 7-9) በ1934 በይሖዋ ምሥክሮች የታተመው ይሖዋ የተባለው መጽሐፍ ስለ ኤርምያስ 31:31-34 ሲያብራራ “አዲሱ ቃል ኪዳን ከሥጋዊ የእስራኤል ዘሮችም ሆነ ከጠቅላላው የሰው ዘሮች ጋር ምንም ዓይነት ዝምድና የለውም። . . . ለመንፈሳዊ እስራኤሎች ብቻ የተወሰነ ነው” ብሎአል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ተሐድሶ የተናገራቸው ትንቢቶች ለተፈጥሮ ወይም ለሥጋዊ አይሁዶችም ሆነ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባልና ኢየሱስ ክርስቶስ በ⁠ዮሐንስ 14:19, 30 እና ዮሐንስ 18:36 ላይ የተናገረለት ዓለም ክፍል ለሆነችው ፖለቲካዊት እስራኤል የሚሠሩ አይደሉም።

18 በ1931 በምድር ላይ የነበሩት የአምላክ ባሮች የይሖዋ ምሥክሮች የሚለውን ስም በታላቅ ደስታ ተቀበሉ። ‘ብርሃን ለጻድቃን ደስታም ለልበ ቅኖች ወጣ’ የሚለው የ⁠መዝሙር 97:11 ቃል ለእነርሱ እንደሚሠራ በሙሉ ልባቸው መናገር ችለዋል። ወደ አዲሱ ቃል ኪዳን የገባው መንፈሳዊ እስራኤል ብቻ መሆኑን በግልጽ ለማስተዋል ችለዋል። (ዕብራውያን 9:15፤ 12:22, 24) አንገተ ደንዳናዋ እስራኤልም ሆነች ጠቅላላው የሰው ዘር ከዚህ ቃል ኪዳን ምንም ዓይነት ተካፋይነት የላቸውም። ይህ እውቀት በቲኦክራቲካዊ የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ በጣም ብሩሕ ሆኖ የሚታይ መለኮታዊ ብርሃን እንዲፈነጥቅ አስችሎአል። ይህም ብርሃን ይሖዋ ወደ እርሱ ለሚቀርቡት የሰው ልጆች በሙሉ ምህረቱን፣ ፍቅራዊ ደግነቱንና እውነቱን እንዴት አብዝቶ እንደሚዘረጋላቸው ያሳያል። (ዘጸአት 34:6፤ ያዕቆብ 4:8) አዎ፣ ከአራቱ የጥፋት ነፋሳት መገታት የሚጠቀሙ ከአምላክ እስራኤል አባሎች የተለዩ ሰዎች ይኖራሉ። እነዚህ ሰዎች እነማን ሊሆኑ ይችላሉ? አንተስ ከእነዚህ ሰዎች መካከል ለመሆን ትችል ይሆንን? ከዚህ ቀጥለን እንመለከታለን።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.13 እስራኤል የሚለው ስም ትርጉም “አምላክ ይታገላል፣ ወይም ከአምላክ ጋር የሚታገል” ማለት መሆኑ ተገቢ ነው።—ዘፍጥረት 32:28ባለ ማጣቀሻው አዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ  114 ላይ የሚገኝ ባለ ሙሉ ገጽ ሥዕል]

[በገጽ 116 እና 117 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የእውነተኞቹ የአምላክ እስራኤል አባላት አጠቃላይ ምርጫ ከጰንጠቆስጤ ቀን 33 እዘአ ጀምሮ በ1935 በዋሽንግተን ዲ ሲ በተደረገው የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ ምድራዊ ተስፋ ያላቸውን እጅግ ብዙ ሰዎች ለመሰብሰብ ትኩረት እንዲደረግ እስከተነገረበት ጊዜ ድረስ ቀጥሎአል (ራእይ 7:9)