በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአምላክ የፍርድ ቀን—የሚያስገኘው አስደሳች ውጤት!

የአምላክ የፍርድ ቀን—የሚያስገኘው አስደሳች ውጤት!

ምዕራፍ 41

የአምላክ የፍርድ ቀን—የሚያስገኘው አስደሳች ውጤት!

ራእይ 15--ራእይ 20:11 እስከ 21:8

ርዕሰ ጉዳይ:- አጠቃላይ ትንሣኤ፣ የፍርድ ቀን፣ አዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር የሚያስገኙአቸው በረከቶች

ራእዩ የሚፈጸምበት ጊዜ:- በሺው ዓመት የግዛት ዘመን

1. (ሀ) አዳምና ሔዋን ኃጢአት በሠሩ ጊዜ የሰው ልጅ ምን ነገር አጣ? (ለ) እስከ አሁን ያልተለወጠው የትኛው የአምላክ ዓላማ ነው? ይህንንስ እንዴት እናውቃለን?

ሰብዓዊ ፍጥረቶች እንደመሆናችን መጠን የተፈጠርነው ለዘላለም ለመኖር ነው። አዳምና ሔዋን የአምላክን ትዕዛዝ ቢጠብቁ ኖሮ ፈጽሞ አይሞቱም ነበር። (ዘፍጥረት 1:28፤ 2:8, 16, 17፤ መክብብ 3:10, 11) ኃጢአት በሠሩ ጊዜ ግን ለራሳቸውም ሆነ ለልጆቻቸው ፍጽምናና ሕይወት አሳጡ። በሰው ልጆች ሁሉ ላይ ሞት የማይሸነፍ ባላጋራ በመሆን ነገሠ። (ሮሜ 5:12, 14፤ 1 ቆሮንቶስ 15:26) ይሁን እንጂ ፍጹማን የሰው ልጆችን በገነቲቱ ምድር ላይ ለማኖር አምላክ ያወጣው ዓላማ አልተለወጠም። ለሰው ልጆች ባለው ታላቅ ፍቅር ተነሳስቶ ‘ለብዙዎቹ’ የአዳም ልጆች ፍጹም ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ የሰጠውን አንድያ ልጁን ኢየሱስን ወደ ምድር ላከው። (ማቴዎስ 20:28፤ ዮሐንስ 3:16) አሁን ኢየሱስ የራሱ መሥዋዕት ያስገኘውን ሕጋዊ መብት በመጠቀም ያመኑትን የሰው ልጆች በገነታዊ ምድር ወደ ፍጹም ሕይወት ሊመልስ ይችላል። (1 ጴጥሮስ 3:18፤ 1 ዮሐንስ 2:2) የሰው ልጅ የሚደሰትበትና ሐሴት የሚያደርግበት ትልቅ ምክንያት ይኖረዋል።—ኢሳይያስ 25:8, 9

2. ዮሐንስ በ⁠ራእይ 20:11 ላይ ምን ነገር ገልጾልናል? ‘ታላቁ ነጭ ዙፋን’ ምንድን ነው?

2 ሰይጣን በጥልቁ ውስጥ ከታሠረ በኋላ የኢየሱስ የሺህ ዓመት ግዛት ይጀምራል። አምላክ “ባዘጋጀው ሰው እጅ በዓለሙ ላይ በጽድቅ” ሊፍርድ የቀጠረው “ቀን” ይጀምራል። (ሥራ 17:31፤ 2 ጴጥሮስ 3:8) ዮሐንስ እንዲህ ይላል:- “ታላቅና ነጭ ዙፋንን በእርሱም ላይ የተቀመጠውን አየሁ፣ ምድርና ሰማይም ከፊቱ ሸሹ፣ ስፍራም አልተገኘላቸውም።” (ራእይ 20:11) ይህ “ታላቅ ነጭ ዙፋን” ምንድን ነው? “የሁሉም ዳኛ” የሆነው የአምላክ የፍርድ ወንበር ነው እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም። (ዕብራውያን 12:23) አሁን ከኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት መጠቀም የሚገባቸው ሰዎች እነማን እንደሚሆኑ ይፈርዳል።—ማርቆስ 10:45

3. (ሀ) የአምላክ ዙፋን “ታላቅ” እና “ነጭ” መሆኑ ምን ያመለክታል? (ለ) በፍርድ ቀን ፈራጅ የሚሆነው ማን ነው? የሚፈርደውስ በምን መሠረት ነው?

3 የአምላክ ዙፋን “ታላቅ” ነው። ይህም ይሖዋ የጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዥ በመሆኑ ያለውን ክብርና ታላቅነት ያመለክታል። “ነጭ” መሆኑ ደግሞ ምንም ዓይነት እንከን የማይገኝበትን ጻድቅነቱን ያመለክታል። የሰው ልጅ የመጨረሻ ፈራጅ ይሖዋ ነው። (መዝሙር 19:7-11፤ ኢሳይያስ 33:22፤ 51:5, 8) ይሁን እንጂ የፈራጅነት ሥራውን ለኢየሱስ ክርስቶስ በውክልና ሰጥቶአል። “ፍርድን ሁሉ ለወልድ ሰጠው እንጂ አብ በአንድ ሰው ስንኳ አይፈርድም።” (ዮሐንስ 5:22) ከኢየሱስ ጋር ደግሞ የሺህ ዓመት ‘ዳኝነት የተሰጣቸው’ 144,000 ተባባሪዎቹ አሉ። (ራእይ 20:4) ቢሆንም በፍርዱ ቀን በእያንዳንዱ ሰው ላይ የሚደርሰው ነገር የሚወሰነው በይሖዋ የጽድቅ ደረጃ እየተለካ ነው።

4. “ምድርና ሰማይ” ሸሹ ሲባል ምን ማለት ነው?

4 “ምድርና ሰማይ የሸሹት” እንዴት ነው? ይህ ሰማይ ስድስተኛው ማህተም በተፈታ ጊዜ እንደ መጽሐፍ ጥቅልል ከሸሸው ሰማይ ጋር አንድ ነው። እርሱም “እግዚአብሔርን የማያመልኩት ሰዎች እስከሚጠፉበት እስከ ፍርድ ቀን ድረስ” የተጠበቁትን ሰብዓውያን ገዥ ኃይሎች ያመለክታል። (ራእይ 6:14፤ 2 ጴጥሮስ 3:7) ምድር በዚህ አገዛዝ ሥር የኖረው የተደራጀ የነገሮች ሥርዓት ነው። (ራእይ 8:7) አውሬውና የምድር ነገሥታት እንዲሁም ጭፍሮቻቸው የአውሬውን ምልክት ከተቀበሉትና ምስሉን ከሚያመልኩት ሰዎች ጋር ሲጠፉ የዚህ ምድርና ሰማይ ሽሽት ይሆናል። (ራእይ 19:19-21) በሰይጣን ምድርና ሰማይ ላይ ፍርድ ከተፈጸመ በኋላ ታላቁ ፈራጅ ሌላ የፍርድ ቀን ያውጃል።

የሺህ ዓመቱ የፍርድ ቀን

5. አሮጌው ምድርና አሮጌው ሰማይ ከሸሹ በኋላ ለፍርድ የሚቀሩት እነማን ናቸው?

5 አሮጌው ምድርና አሮጌው ሰማይ ከሸሹ በኋላ ለፍርድ የሚቀሩት እነማን ናቸው? የ144,000ዎቹ ቅቡዓን ቀሪዎች ሊሆኑ አይችሉም። ምክንያቱም እነዚህ ቀደም ሲል ተፈርዶላቸው ታትመዋል። ከአርማጌዶን በኋላ በምድር ላይ በሕይወት የሚገኙ ቅቡዓን ካሉ፣ እነርሱም ብዙ ሳይቆዩ መሞትና በትንሣኤ አማካኝነት ሰማያዊ ሽልማታቸውን ማግኘት ይገባቸዋል። (1 ጴጥሮስ 4:17፤ ራእይ 7:2-4) ይሁን እንጂ ከታላቁ መከራ የወጡት በሚልዮን የሚቆጠሩ እጅግ ብዙ ሰዎች “ከዙፋኑ ፊት” ቆመው ታይተዋል። እነዚህ ሰዎች ቀደም ብሎም ቢሆን በፈሰሰው የኢየሱስ ደም በማመናቸው ምክንያት እንደ ጻድቃን ተቆጥረው ከጥፋቱ ተርፈዋል። ቢሆንም ኢየሱስ ወደ “ሕይወት ውኃ ምንጭ” ስለሚመራቸው ፍርዳቸው በሺው ዓመት ግዛት ውስጥ መቀጠል ይኖርበታል። በዚያ ጊዜ ወደ ሰብዓዊ ፍጽምና ከደረሱና በመጨረሻ ከተፈተኑ በኋላ ሙሉ በሙሉ ጻድቃን ሆነው ይቆጠራሉ። (ራእይ 7:9, 10, 14, 17) ታላቁን መከራ በሕይወት ያለፉትና በሺው ዓመት ግዛት ውስጥ ለእጅግ ብዙ ሰዎች የሚወለዱላቸው ልጆች በተመሳሳይ በዚሁ የሺህ ዓመት ጊዜ ውስጥ ፍርድ መቀበል ያስፈልጋቸዋል።—ከ⁠ዘፍጥረት 1:28፤ ከዘፍጥረት 9:7⁠ና ከ⁠1 ቆሮንቶስ 7:14 ጋር አወዳድር።

6. (ሀ) ዮሐንስ የትኛውን ታላቅ ሕዝብ ተመለከተ? “ታላላቆችና ታናናሾች” የሚለው ቃል ምን ያመለክታል? (ለ) በአምላክ ዝክር ውስጥ ያሉ በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከሙታን መነሳታቸው የማይቀረው ለምንድን ነው?

6 ይሁን እንጂ ዮሐንስ ታላቁን መከራ በሕይወት ካለፉት እጅግ ብዙ ሰዎች የበለጠ ብዛት ያለው ሕዝብ ተመልክቶአል። በሺህ ሚልዮን የሚቆጠሩ ይሆናሉ። “ሙታንንም ታናናሾችንና ታላላቆችን በዙፋኑ ፊት ቆመው አየሁ፣ መጻሕፍትም ተከፈቱ።” (ራእይ 20:12ሀ) “ታናናሾችና ታላላቆች” ባለፉት ስድስት ሺህ ዓመታት በዚህች ምድር ላይ ኖረው የሞቱትን ከፍተኛ ከበሬታ የነበራቸውንና ተራ የሆኑትን ሰዎች ያጠቃልላል። ሐዋርያው ዮሐንስ ከራእይ መጽሐፍ በኋላ ጥቂት ቆይቶ በጻፈው ወንጌል ውስጥ ኢየሱስ ስለ አብ ሲናገር “የሰው ልጅም ስለሆነ ይፈርድ ዘንድ ሥልጣን ሰጠው። በመቃብር [“በመታሰቢያ መቃብር፣” NW] ያሉቱ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል። መልካምም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉና በዚህ አታድንቁ” ብሎ ነበር። (ዮሐንስ 5:27-29) ይህ በጣም ሰፊ የሆነ አስደናቂ ፕሮጀክት ነው። በታሪክ ዘመናት ሁሉ የኖሩት የቀብር ቦታዎችና ሞት እንዳልነበሩ ይሆናሉ። በአምላክ ዝክር ውስጥ ያሉት እነዚህ ቁጥር ስፍር የሌላቸው ሙታን የሚነሱት ቀስ በቀስ በየተራ መሆን ይኖርበታል። ይህም የሚሆነው ከሞት የሚነሱት ሰዎች በመጀመሪያ ላይ የቀድሞ አኗኗራቸውንና ሥጋዊ ድካማቸውን እንዲሁም ዝንባሌያቸውን ለመከተል ስለሚፈልጉ ከእነርሱ ጋር ሲወዳደሩ በቁጥር አነስተኛ የሆኑት እጅግ ብዙ ሰዎች በዚህ ምክንያት የሚነሳውን ችግር ለመቋቋም እንዲችሉ ነው።

የሚነሱትና የሚፈረዱት እነማን ናቸው?

7, 8. (ሀ) የትኛው የመጽሐፍ ጥቅልል ነው የተከፈተው? ከዚያ በኋላ ምን ይሆናል? (ለ) ትንሣኤ የማይኖራቸው የትኞቹ ሰዎች ናቸው?

7 ዮሐንስ በመቀጠል እንዲህ ይላል:- “ሌላ መጽሐፍም ተከፈተ እርሱም የሕይወት መጽሐፍ ነው፤ ሙታንም በመጻሕፍት ተጽፎ እንደ ነበረ እንደ ሥራቸው መጠን ተከፈሉ። ባሕርም በእርሱ ውስጥ ያሉትን ሙታን ሰጠ፣ ሞትና ሲኦልም በእነርሱ ዘንድ ያሉትን ሙታን ሰጡ፣ እያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን ተከፈለ።” (ራእይ 20:12ለ, 13) በጣም የሚያስደንቅ ትዕይንት ነው! ‘ባሕሩ፣ ሞትና ሲኦል’ እያንዳንዳቸው የየራሳቸው ድርሻ አላቸው። ቢሆንም እነዚህ ቃላት በተናጠል የሚወሰዱና የተለያየ ትርጉም ያላቸው አይደሉም። * ዮናስ በዓሣ ሆድ ውስጥ በነበረበትና በዚህም ምክንያት በባሕር መካከል በነበረበት ጊዜ በሲኦል ወይም በሔድስ ውስጥ እንደነበረ ተናግሮአል። (ዮናስ 2:3) አንድ ሰው በአዳማዊ ሞት መዳፍ ውስጥ የታሰረ ከሆነ በሲኦል ወይም በሔድስ ውስጥ ያለ ሊሆን ይችላል። እነዚህ ትንቢታዊ ቃላት ማንም ተረስቶ እንደማይቀር ዋስትና የሚሰጡ ናቸው።

8 እርግጥ ቁጥራቸው በትክክል ያልታወቀ ትንሣኤ ሙታን የማያገኙ ሰዎች አሉ። ከእነዚህም መካከል ኢየሱስንና ሐዋርያትን ያልተቀበሉት ጸሐፊዎችና ፈሪሣውያን፣ ሃይማኖታዊው ‘የዓመፅ ሰው’ እንዲሁም ‘የወደቁ’ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ይገኛሉ። (2 ተሰሎንቄ 2:3፤ ዕብራውያን 6:4-6፤ ማቴዎስ 23:29-33) በተጨማሪም ኢየሱስ በዓለም መጨረሻ ጊዜ ‘ለዲያብሎስና ለመላእክቱ ወደተዘጋጀው የዘላለም እሳት’ ማለትም ወደ ዘላለም ጥፋት ስለሚጣሉ ፍየል መሰል ሰዎች ተናግሮአል። (ማቴዎስ 25:41, 46) እነዚህም ትንሣኤ አያገኙም።

9. ሐዋርያው ጳውሎስ በትንሣኤ ልዩ መብት የሚሰጣቸው ሰዎች እንደሚኖሩ የገለጸው እንዴት ነው? ከእነዚህስ ሰዎች መካከል እነማን ይኖራሉ?

9 በሌላው በኩል ደግሞ በትንሣኤ ጊዜ ልዩ ሞገስ የሚደረግላቸው ሰዎች ይኖራሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ ይህንን ሲያመለክት “ጻድቃንም ዓመፀኞችም ከሙታን ይነሱ ዘንድ እንዳላቸው ተስፋ በእግዚአብሔር ዘንድ አለኝ” ብሎአል። (ሥራ 24:15) በምድራዊው ትንሣኤ ረገድ ‘ከጻድቃኑ’ መካከል እንደ አብርሃምና እንደ ረዓብ ጻድቃን ተብለው የአምላክን ወዳጅነት ያገኙ ሌሎች ብዙ ታማኝ ወንዶችና ሴቶች ይገኛሉ። (ያዕቆብ 2:21, 23, 25) በዚሁ ቡድን ውስጥ በዘመናችን ለይሖዋ ታማኝነታቸውን ጠብቀው የሞቱ ጻድቃን ሌሎች በጎች ይገኛሉ። እንደነዚህ ያሉት ታማኝ ፍጹም አቋም ጠባቂዎች ሁሉ በኢየሱስ የሺህ ዓመት ግዛት መጀመሪያ ላይ ከሞት የሚነሱ ይመስላል። (ኢዮብ 14:13-15፤ 27:5፤ ዳንኤል 12:13፤ ዕብራውያን 11:35, 39, 40) ከእነዚህ ከሞት ከሚነሱት ጻድቃን መካከል ብዙዎቹ ምድርን ወደ ገነት በመመለሱ ሥራ የበላይ ተመልካቾች በመሆን ልዩ የአገልግሎት መብት እንደሚሰጣቸው አያጠራጥርም።—መዝሙር 45:16 የ1980 ትርጉም፤ ከ⁠ኢሳይያስ 32:1, 16-18፤ ከኢሳይያስ 61:5⁠ና ከኢሳይያስ 65:21-23 ጋር አወዳድር።

10. ከሞት የሚነሱት “ዓመፀኞች” እነማን ናቸው?

10 ይሁን እንጂ በ⁠ሥራ 24:15 ላይ የተጠቀሱት “ዓመፀኞች” እነማን ናቸው? እነዚህ በታሪክ ዘመናት ሁሉ በተለይም ‘ባለማወቅ ዘመናት’ የሞቱትን እጅግ ብዙ ሰዎች ያጠቃልላሉ። (ሥራ 17:30) እነዚህ ሰዎች በተወለዱበት ሥፍራና በኖሩበት ዘመን ምክንያት ለይሖዋ ፈቃድ ስለመገዛት ለመማር አጋጣሚ ያላገኙ ናቸው። በተጨማሪም የመዳንን መልእክት ሰምተው በጊዜያቸው እርምጃ ያልወሰዱ ወይም ራሳቸውን ወደ መወሰንና ወደ መጠመቅ ደረጃ ከመድረሳቸው በፊት የሞቱ ሰዎች አሉ። እንደነዚህ ያሉት ሰዎች በዚህ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት በተሰጣቸው አጋጣሚ እንዲጠቀሙ ከፈለጉ በትንሣኤ ጊዜ በአስተሳሰባቸውና በአኗኗራቸው ለውጥ ማድረግ ይኖርባቸዋል።

የሕይወት መጽሐፍ

11. (ሀ) “የሕይወት መጽሐፍ” ምንድን ነው? በዚህስ መጽሐፍ ውስጥ የተጻፈው የማን ስም ነው? (ለ) በሺው ዓመት የግዛት ዘመን የሕይወት መጽሐፍ ክፍት ሆኖ የሚቆየው ለምንድን ነው?

11 ዮሐንስ ስለ “ሕይወት መጽሐፍ” ተናግሮአል። ይህ መጽሐፍ ከይሖዋ ዘንድ የዘላለም ሕይወት ማግኘት የሚገባቸው ሰዎች ስም የያዘ መዝገብ ነው። የኢየሱስ ቅቡዓን ወንድሞች ስም፣ የእጅግ ብዙ ሰዎች ስም፣ እንደ ሙሴ ያሉት የጥንት ታማኝ ሰዎች ስም በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግቦአል። (ዘጸአት 32:32, 33፤ ዳንኤል 12:1፤ ራእይ 3:5) እስከዚህ ጊዜ ድረስ ግን ከሙታን ከተነሱት “ዓመፀኞች” መካከል ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ የተጻፈላቸው ሰዎች የሉም። ስለዚህ ብቃት ያገኙ ሁሉ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ለመጻፍ እንዲችሉ የሕይወት መጽሐፍ በሺው ዓመት ግዛት በሙሉ ክፍት ሆኖ ይቆያል። በጥቅልሉ ወይም በመጽሐፉ ውስጥ ስማቸው የማይጻፉ ሁሉ “ወደ እሳቱ ባሕር” ይጣላሉ።—ራእይ 20:15፤ ከ⁠ዕብራውያን 3:19 ጋር አወዳድር።

12. የአንድ ሰው ስም በተከፈተው የሕይወት መጽሐፍ ውስጥ መጻፉ የሚወሰነው በምንድን ነው? በዚህስ ረገድ ይሖዋ የሾመው ፈራጅ ምሳሌ የሚሆነን እንዴት ነው?

12 በዚያ ጊዜ የአንድ ሰው ስም ክፍት በሆነው የሕይወት መጽሐፍ ውስጥ መጻፉና አለመጻፉ የሚወሰነው በምንድን ነው? ወሳኝ የሚሆነው ቁልፍ ጉዳይ በአዳምና በሔዋን ዘመንም እንደነበረው ለይሖዋ ታዛዥ መሆን ነው። ሐዋርያው ዮሐንስ ለተወዳጅ ክርስቲያን ባልንጀሮቹ እንደጻፈው “ዓለምና ምኞቱም ያልፋሉ። የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚፈጽም ግን ለዘላለም ይኖራል።” (1 ዮሐንስ 2:4-7, 17 የ1980 ትርጉም) በታዛዥነት ጉዳይ ዋነኛው አርዓያ ይሖዋ የሾመው ፈራጅ ነው። “ምንም ልጅ ቢሆን [ኢየሱስ] ከተቀበለው መከራ መታዘዝን ተማረ። ከተፈጸመም በኋላ . . . ለሚታዘዙለት ሁሉ የዘላለም መዳን ምክንያት ሆነላቸው።”—ዕብራውያን 5:8, 9

ሌሎቹን የመጽሐፍ ጥቅልሎች መክፈት

13. ከሙታን የሚነሱት ሰዎች ታማኝነታቸውን ማረጋገጥ የሚኖርባቸው እንዴት ነው? የትኛውንስ ሥርዓት መከተል ይኖርባቸዋል?

13 እነዚህ ከሙታን የተነሱ ሰዎች ታዛዥ መሆናቸውን የሚያሳዩት እንዴት መሆን ይኖርበታል? ኢየሱስ ራሱ እንደሚከተለው በማለት ሁለቱን ታላላቅ ትዕዛዛት ጠቅሶአል። “ከትዕዛዛቱ ሁሉ ፊተኛይቱ እስራኤል ሆይ፣ ስማ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] አምላካችን አንድ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ነው። አንተም በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም አሳብህ በፍጹምም ኃይልህ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] አምላክህን ውደድ የምትል ናት። ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት። ሁለተኛይቱም ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የምትል እርስዋን የምትመስል ይህች ናት።” (ማርቆስ 12:29-31) በተጨማሪም መከተል የሚኖርባቸው በሚገባ የታወቁ የይሖዋ መሠረታዊ ሥርዓቶች አሉ። ከእነዚህም መካከል ከስርቆት፣ ከመዋሸት፣ ከነፍስ ግድያና ከፆታ ብልግና መራቅ ይገኙበታል።—1 ጢሞቴዎስ 1:8-11፤ ራእይ 21:8

14. የትኞቹ ሌሎች መጻሕፍት ይከፈታሉ? በእነዚህስ መጻሕፍት ውስጥ ምን ተጽፎአል?

14 ይሁን እንጂ ዮሐንስ በሺው ዓመት ግዛት ውስጥ የሚከፈቱ ሌሎች መጻሕፍትን ጠቅሶአል። (ራእይ 20:12) እነዚህ መጻሕፍት ምንድን ናቸው? ይሖዋ ለተወሰኑ ሁኔታዎች የሚያስፈልጉ የተወሰኑ መመሪያዎችን የሰጠባቸው ጊዜያት ነበሩ። ለምሳሌ ያህል በሙሴ ዘመን እሥራኤላውያን ቢጠብቁአቸው ሕይወት ሊያስገኙላቸው የሚችሉ ዝርዝር ሕጎችን ሰጥቶአቸው ነበር። (ዘዳግም 4:40፤ 32:45-47) በመጀመሪያው መቶ ዘመን ደግሞ ታማኝ ሰዎች በክርስትና ሥርዓት ሥር የይሖዋን መሠረታዊ ሥርዓቶች እንዲከተሉ የሚረዱአቸው አዳዲስ መመሪያዎች ተሰጥተው ነበር። (ማቴዎስ 28:19, 20፤ ዮሐንስ 13:34፤ 15:9, 10) አሁን ደግሞ ዮሐንስ “ሙታን በመጻሕፍት ተጽፎ እንደነበረ እንደ ሥራቸው መጠን” እንደተከፈሉ ተናገረ። ስለዚህ የእነዚህ መጻሕፍት መከፈት ይሖዋ በሺው ዓመት ዘመን ለሰው ልጆች ያወጣውን ብቃት የሚያሳውቅ ይሆናል። ታዛዥ የሰው ልጆች እነዚህን በመጽሐፍ ጥቅልል ውስጥ የተገለጹትን ደንቦችና ሕጎች በሥራ በማዋል ዕድሜያቸውን ሊያስረዝሙና በመጨረሻም የዘላለም ሕይወት ሊያገኙ ይችላሉ።

15. በትንሣኤ ጊዜ ምን ዓይነት የትምህርት ዘመቻ አስፈላጊ ይሆናል? የትንሣኤ ቅደም ተከተል እንዴት ሊሆን ይችላል?

15 በጣም ሠፊ የሆነ የቲኦክራቲካዊ ትምህርት ዘመቻ አስፈላጊ ይሆናል። በ2005 የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ በአማካይ 6,061,534 የሚሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን በተለያዩ ቦታዎች መርተዋል። በትንሣኤ ጊዜ ግን በመጽሐፍ ቅዱስና በአዳዲሶቹ መጻሕፍት ላይ የተመሠረቱ ቁጥር ስፍር የሌላቸው ብዙ ጥናቶች ይመራሉ። የአምላክ ሕዝቦች በሙሉ አስተማሪዎች መሆንና በትጋት መሥራት ያስፈልጋቸዋል። ትንሳኤ ያገኙትም ቢሆኑ እድገት እያሳዩ በሄዱ መጠን በጣም ሰፊ በሆነው በዚህ የትምህርት ፕሮግራም እንደሚካፈሉ አያጠራጥርም። የትንሣኤው ቅደም ተከተል በሕይወት የሚገኙት የቀድሞ ቤተሰቦቻቸውንና ያውቁአቸው የነበሩትን ሰዎች የመቀበልና የማስተማር ደስታ በሚያገኙበትና የተነሱት ደግሞ በተራቸው ሌሎችን ለመቀበል በሚችሉበት መንገድ የሚከናወን ይመስላል። (ከ⁠1 ቆሮንቶስ 15:19-28, 58 ጋር አወዳድር።) በአሁኑ ጊዜ እውነትን በማሰራጨት ተግተው የሚሠሩት ከስድስት ሚልዮን የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች በትንሣኤ ጊዜ እንደሚሰጣቸው ተስፋ ለሚያደርጉት መብት ጥሩ መሠረት እየጣሉ ናቸው።—ኢሳይያስ 50:4፤ 54:13

16. (ሀ) በሕይወት መጽሐፍ ወይም ጥቅልል ውስጥ የማይጻፈው የእነማን ስም ነው? (ለ) ትንሣኤያቸው “የሕይወት” ትንሣኤ የሚሆንላቸው እንዴት ያሉ ሰዎች ናቸው?

16 ኢየሱስ ስለ ምድራዊው ትንሣኤ ሲናገር ‘መልካም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ፣ ክፉ ያደረጉ ደግሞ ለፍርድ ትንሣኤ ይነሳሉ’ ብሎ ነበር። እዚህ ላይ “ሕይወት” እና “ፍርድ” ተቃራኒ ነገሮች እንደሆኑ ተደርገው ተገልጸዋል። ይህም ከሙታን ከሚነሱት መካከል በመንፈስ አነሳሽነት በተጻፉት ቅዱሳን ጽሑፎችና በጥቅሶቹ ላይ የተመሠረተ ትምህርት ከተሰጣቸው በኋላ “ክፉ ያደረጉ” ሁሉ ለሕይወት የማይበቁ እንደሆኑ ይፈረድባቸዋል ማለት ነው። (ዮሐንስ 5:29) በታማኝነት ሲመላለሱ ከቆዩ በኋላ በአንድ ምክንያት በሺው ዓመት ጊዜ ውስጥ ወደተሳሳተ መንገድ ዘወር የሚሉ ሁሉ ከእነዚህ የተለየ ዕጣ አያጋጥማቸውም። ተጽፈው የነበሩ ስሞች ሊፋቁ ይችላሉ። (ዘጸአት 32:32, 33) በሌላው በኩል ደግሞ በመጽሐፍ ጥቅልሎቹ ውስጥ የተጻፉትን በታዛዥነት የሚጠብቁ ሁሉ ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ እንደተመዘገበ ይኖራል። በሕይወትም ይኖራሉ። ለእነርሱ ትንሣኤያቸው “የሕይወት” ትንሣኤ ይሆንላቸዋል።

የሞትና የሲኦል ፍጻሜ

17. (ሀ) ዮሐንስ ቀጥሎ እንዴት ያለ አስደናቂ ድርጊት ይገልጽልናል? (ለ) ሔድስ ባዶ የሚሆነው መቼ ነው? (ሐ) በአዳም ምክንያት የመጣው ሞት “ወደ እሳት ባሕር” የሚጣለው መቼ ነው?

17 ዮሐንስ ከዚህ ቀጥሎ በጣም አስደናቂ የሆነ ነገር ይገልጽልናል:- “ሞትና ሲኦልም በእሳት ባሕር ውስጥ ተጣሉ። ይህም የእሳት ባሕር ሁለተኛው ሞት ነው። በሕይወትም መጽሐፍ ተጽፎ ያልተገኘው ማንኛውም በእሳት ባሕር ውስጥ ተጣለ።” (ራእይ 20:14, 15) የሺህ ዓመቱ የፍርድ ቀን በሚፈጸምበት ጊዜ “ሞትና ሲኦል” ፈጽመው ይወገዳሉ። ይሁን እንጂ ይህ እስኪሆን ድረስ የሺህ ዓመት ጊዜ ያስፈለገው ለምንድን ነው? ሔድስ ወይም የሰው ልጆች የጋራ መቃብር የሆነው ሲኦል በአምላክ ዝክር ውስጥ የነበረ የመጨረሻው ሰው ከሙታን በተነሳ ጊዜ ባዶ ሆኖአል። ይሁን እንጂ ሰዎች በውርሻ የመጣ ኃጢአት እስካለባቸው ድረስ አዳማዊው ሞት በውስጣቸው አለ ማለት ነው። ከሞት ተነስተው በምድር ላይ የሚኖሩትም ሆኑ አርማጌዶንን በሕይወት ያለፉት እጅግ ብዙ ሰዎች የኢየሱስ ቤዛ ያስገኘው ዋጋ ሙሉ ተጠቃሚዎች ሆነው በሽታ፣ እርጅናና ሌሎች የተወረሱ ድካሞች እስኪወገዱላቸው ድረስ በመጻሕፍት ጥቅልል ውስጥ የተጻፈውን ሁሉ መታዘዝ ይኖርባቸዋል። ከዚያ በኋላ አዳማዊው ሞትና ሔድስ ወይም ሲኦል “ወደ እሳት ባሕር” ይጣላሉ፣ ለዘላለም ይጠፋሉ!

18. (ሀ) ሐዋርያው ጳውሎስ የኢየሱስ የንግሥና ግዛት ስለሚያስገኘው የተሳካ ውጤት የገለጸው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ ፍጽምና ያገኘውን የሰው ልጆች ቤተሰብ ምን ያደርጋል? (ሐ) በሺው ዓመት መጨረሻ ላይ ምን ሌሎች ነገሮች ይፈጸማሉ?

18 በዚህ መንገድ ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በጻፈው ደብዳቤ ላይ የገለጸው ፕሮግራም ሙሉ በሙሉ ይፈጸማል። “ጠላቶቹን ሁሉ ከእግሩ በታች እስኪያደርግ ድረስ [ኢየሱስ] ሊነግሥ ይገባዋልና። የኋለኛው ጠላት የሚሻረው [አዳማዊው] ሞት ነው።” ከዚያስ በኋላ ምን ይሆናል? “ሁሉ ከተገዛለት በኋላ ግን እግዚአብሔር ሁሉ በሁሉ ይሆን ዘንድ በዚያን ጊዜ ልጁ ራሱ ደግሞ ሁሉን ላስገዛለት ይገዛል።” በሌላ አባባል ኢየሱስ ‘መንግሥቱን ለእግዚአብሔር ለአባቱ ያስረክባል።’ (1 ቆሮንቶስ 15:24-28) አዎ፣ ኢየሱስ በቤዛዊ መሥዋዕቱ ዋጋ አዳማዊውን ኃጢአት ድል ከነሳ በኋላ ፍጹም የሆነ ሰብዓዊ ቤተሰብ ለአባቱ ለይሖዋ ያስረክባል። ሰይጣን የሚፈታውና በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ ለዘላለም ተጽፈው የሚኖሩትን ሰዎች ለመወሰን የሚደረገው የመጨረሻ ፈተና የሚሆነው ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ በሺው ዓመቱ ፍጻሜ አካባቢ ነው። የአንተም ስም ከእነዚህ ሰዎች መካከል እንዲገኝ “ተጋደል”!—ሉቃስ 13:24፤ ራእይ 20:5

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.7 ከባሕር ከሚነሱት ሙታን መካከል በኖህ ዘመን በጥፋት ውኃ የጠፉት ክፉ ሰዎች አይኖሩም። ይህ በእነርሱ ላይ የደረሰው ጥፋት በታላቁ መከራ በሚፈጸመው የይሖዋ ፍርድ በሚጠፉት ሰዎች ላይ እንደሚደርሰው ጥፋት የመጨረሻ ጥፋት ነው።—ማቴዎስ 25:41, 46፤ 2 ጴጥሮስ 3:5-7

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 298 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሺው ዓመት የግዛት ዘመን በሚከፈተው የመጽሐፍ ጥቅልል ውስጥ የተጻፈውን የሚታዘዙ ከሙታን የተነሱ “ዓመፀኞች” ሁሉ ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ ይጻፋል