በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የእባቡን ጭንቅላት መቀጥቀጥ

የእባቡን ጭንቅላት መቀጥቀጥ

ምዕራፍ 40

የእባቡን ጭንቅላት መቀጥቀጥ

ራእይ 14--ራእይ 20:1-10

ርዕሰ ጉዳይ:- የሰይጣን ወደ ጥልቁ መጣል፣ የሺው ዓመት ግዛት፣ የሰው ልጅ የመጨረሻ ፈተናና የሰይጣን መጥፋት

ራእዩ የሚፈጸምበት ጊዜ:- ከታላቁ መከራ መጨረሻ እስከ ሰይጣን መጥፋት

1. የመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት አፈጻጸም እንዴት ነበር?

የመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ምን እንደሆነ ትዝ ይልሃልን? ይህ ትንቢት የተነገረው ይሖዋ ለእባቡ “በአንተና በሴቲቱ መካከል፣ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፣ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፣ አንተም ሰኮናውን ትቀጠቅጣለህ” ባለ ጊዜ ነበር። (ዘፍጥረት 3:15) አሁን የዚህ ትንቢት ፍጻሜ ወደ መጨረሻው ታላቅ መደምደሚያ እየተጠጋ ነው! ሰይጣን በይሖዋ ሰማያዊ ሴት መሰል ድርጅት ላይ ስለፈጸመው የውጊያ ታሪክ በዝርዝር ተመልክተናል። (ራእይ 12:1, 9) የሃይማኖት፣ የፖለቲካና የከፍተኛ ንግድ ድርጅቶች የሚገኙበት የሰይጣን ምድራዊ ዘር በሴቲቱ ዘር ላይ ማለትም በኢየሱስ ክርስቶስና በ144,000 ቅቡዓን ተከታዮቹ ላይ በዚችው ምድር ላይ አሰቃቂ የሆነ የስደት ናዳ ሲያወርዱ ኖረዋል። (ዮሐንስ 8:37, 44፤ ገላትያ 3:16, 29) ሰይጣን ኢየሱስ በሥቃይ እንዲገደል አድርጎአል። ይሁን እንጂ አምላክ ታማኝ ልጁን በሦስተኛው ቀን ስላስነሳው ከተረከዝ ቁስል የበለጠ ጉዳት አላስከተለበትም።—ሥራ 10:38-40

2. እባቡ የሚቀጠቀጠው እንዴት ነው? የእባቡ ምድራዊ ዘሮች ምን ይሆናሉ?

2 እባቡና ዘሮቹስ? ሐዋርያው ጳውሎስ በ56 እዘአ ገደማ ላይ በሮማ ለነበሩት ክርስቲያኖች ረዥም ደብዳቤ ጽፎ ነበር። ይህን ደብዳቤውን ሲያጠቃልል “የሰላምም አምላክ ሰይጣንን ፈጥኖ ከእግራችሁ በታች ይቀጠቅጣል” በማለት አጽናንቶአቸዋል። (ሮሜ 16:20) ይህ ላይ ላዩን ብቻ የሚያሳምም ቀላል ቁስል አይደለም። ሰይጣን መቀጥቀጥ ይኖርበታል። ጳውሎስ እዚህ ላይ የተጠቀመበት ቃል የግሪክኛውን ሲንትሪቦ ነው። ይህም ቃል እንደ ውኃ እስኪፈስስ ድረስ መጨፍለቅ፣ መርገጥ፣ ሙሉ በሙሉ እስኪጠፋ ድረስ ማድቀቅ የሚል ትርጉም አለው። ይህን የመሰለው እርምጃ በእባቡ ሰብዓዊ ዘሮች ላይ የሚፈጸመው በጌታ ቀን ውስጥ ሲሆን ታላቂቱ ባቢሎንና የዓለም ፖለቲካዊ ሥርዓት ከንግድና ከውትድርና ሸሪኮቹ ጋር በሚቀጠቀጡበት በታላቁ መከራ ወደ ታላቁ መደምደሚያው ይመጣል። (ራእይ ምዕራፍ 18 እና 19) በዚህ መንገድ ይሖዋ በሁለቱ ዘሮች መካከል የኖረውን ጠላትነት ወደ ታላቁ መደምደሚያው ያመጣዋል። የአምላክ ሴት ዘር በምድራዊው የእባብ ዘር ላይ ድል ይቀዳጃል። ከምድርም ገጽ ፈጽሞ ይጠፋል!

ሰይጣን ወደ ጥልቁ ተጣለ

3. ዮሐንስ ሰይጣን ምን እንደሚደረግ ይነግረናል?

3 ይሁን እንጂ ለሰይጣንና ለዘሮቹ የተጠበቀላቸው ነገር ምንድን ነው? ዮሐንስ እንደሚከተለው በማለት ይነግረናል:- “የጥልቁንም መክፈቻና ታላቁን ሰንሰለት በእጁ የያዘ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ። የቀደመውንም እባብ ዘንዶውን እርሱም ዲያብሎስና ሰይጣን የተባለውን ያዘው። ሺህ ዓመትም አሰረው፣ ወደ ጥልቅም ጣለው አሕዛብንም ወደ ፊት እንዳያስት ሺህ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ በእርሱ ላይ ዘግቶ ማኅተም አደረገበት፤ ከዚያም በኋላ ለጥቂት ጊዜ ይፈታ ዘንድ ይገባዋል።”—ራእይ 20:1-3

4. የጥልቁ መክፈቻ ያለው መልአክ ማን ነው? ይህንንስ እንዴት እናውቃለን?

4 ይህ መልአክ ማን ነው? የይሖዋን ቀንደኛ ጠላት ከቦታው ለማስወገድ የሚችል ከሆነ በጣም ከፍተኛ ኃይል ያለው መልአክ መሆን ይኖርበታል። በተጨማሪም “የጥልቁንም መክፈቻና ታላቁን ሰንሰለት” ይዞአል። ታዲያ ይህ መግለጫ ቀደም ስንል የተመለከትነውን ራእይ አያስታውሰንምን? አዎ፣ የአንበጦቹ ንጉሥ “የጥልቁ መልአክ” እንደሆነ ተገልጾ ነበር። (ራእይ 9:11) ስለዚህ አሁንም በድጋሚ ዋነኛው የይሖዋ ስም አስከባሪ፣ ከፍ ያለ ክብር የተቀዳጀው ኢየሱስ ክርስቶስ እርምጃ ሲወስድ እንመለከታለን። ይህ ሰይጣንን ከሰማይ የወረወረው፣ በታላቂቱ ባቢሎን ላይ የፈረደውና “የምድርን ነገሥታትና ጭፍሮቻቸውን” አርማጌዶን ላይ የደመሰሰው ሊቀ መልአክ ከእርሱ ያነሰ ሌላ መልአክ ሰይጣን ወደ ጥልቁ የሚጣልበትን ወሳኝ እርምጃ እንዲወስድ አይፈቅድም።—ራእይ 12:7-9፤ 18:1, 2፤ 19:11-21

5. የጥልቁ መልአክ ሰይጣን ዲያብሎስን ምን ያደርገዋል? ለምንስ?

5 ታላቁ ቀይ ዘንዶ ከሰማይ በተጣለ ጊዜ “ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ” ተብሎ ተጠርቶ ነበር። (ራእይ 12:3, 9) አሁን ደግሞ ተይዞ ወደ ጥልቁ የሚጣልበት በደረሰበት በዚህ ጊዜ ‘የቀደመው እባብ ዘንዶው፣ እርሱም ዲያብሎስና ሰይጣን’ በመባል ምንነቱ ሙሉ በሙሉ ተገልጾአል። ይህ ስመ ጥፉ የሆነ መዋጥን የሚወድ፣ አሳች፣ ስም አጥፊና ተቃዋሚ በሰንሰለት ታሥሮ በተዘጋውና በታሸገው ‘ጥልቅ ውስጥ’ ይጣላል። ይህም የሆነው ‘ከእንግዲህ ወዲህ አሕዛብን እንዳያስት’ ነው። ሰይጣን በጥልቁ ውስጥ ታስሮ በሚቆይበት በዚህ የሺህ ዓመት ጊዜ በጥልቅ ጉድጓድ ውስጥ እንደተጣለ እሥረኛ በሰው ልጆች ላይ ምንም ዓይነት ተጽዕኖ አይኖረውም። የጥልቁ መልአክ ሰይጣንን ከጽድቅ መንግሥቱ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንዳይኖረው ሙሉ በሙሉ ያገልለዋል። ለሰው ልጆች ታላቅ እፎይታ ይሆናል።

6. (ሀ) አጋንንትም ወደ ጥልቁ እንደሚጣሉ ምን ማረጋገጫ አለን? (ለ) በዚህ ጊዜ ምን ሊጀምር ይችላል? ለምንስ?

6 አጋንንትስ ምን ይሆናሉ? እነርሱም ቢሆኑ “ለፍርድ የተጠበቁ” ናቸው። (2 ጴጥሮስ 2:4) ሰይጣን ‘ብዔል ዜቡል የአጋንንት አለቃ’ ተብሎ ተጠርቶአል። (ሉቃስ 11:15, 18፤ ማቴዎስ 10:25) ታዲያ እነዚህ ለብዙ ዘመናት የሰይጣን አጫፋሪዎች ሆነው የቆዩ አጋንንት በአለቃቸው ላይ የደረሰው ዓይነት ፍርድ ሊደርስባቸው አይገባምን? አጋንንት ይህን ጥልቅ ለብዙ ዘመን ሲፈሩት ቆይተዋል። አንድ ጊዜ ከኢየሱስ ጋር ሲገናኙ “ወደ ጥልቁም ሊሄዱ እንዳያዛቸው” ለምነውት ነበር። (ሉቃስ 8:31) ሆኖም ሰይጣን ወደ ጥልቁ ሲጣል መላእክቱም ከእርሱ ጋር አብረው ወደ ጥልቁ እንደሚጣሉ የተረጋገጠ ነው። (ከ⁠ኢሳይያስ 24:21, 22 ጋር አወዳድር።) ሰይጣንና አጋንንቱ በጥልቁ ውስጥ ከታሠሩ በኋላ የኢየሱስ ክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት መጀመር ይችላል።

7. (ሀ) ሰይጣንና አጋንንቱ በጥልቁ ውስጥ በሚቆዩበት ጊዜ እንዴት ባለ ሁኔታ ይኖራሉ? ይህንንስ እንዴት እናውቃለን? (ለ) ሔድስና ጥልቁ አንድ ናቸውን? (የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።)

7 ሰይጣንና አጋንንቱ በጥልቁ ውስጥ በሚቆዩበት ጊዜ ሊንቀሳቀሱና ሊሠሩ ይችላሉን? “አስቀድሞ ነበረ፣ አሁንም የለም፣ ከጥልቁም ይወጣ ዘንድ አለው” የተባለለትን ባለ ሰባት ራስ ቀይ አውሬ እናስታውስ። (ራእይ 17:8) በጥልቁ ውስጥ በነበረበት ጊዜ “አሁንም የለም” ተብሎ ነበር። ከሞተ አስከሬን ባልተሻለ ሁኔታ የማይንቀሳቀስና ምንም ነገር ሊሠራ የማይችል ሆኖ ነበር። በተመሳሳይም ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ኢየሱስ ሲናገር “ወደ ጥልቁ ማን ይወርዳል? አትበል። ይህ ክርስቶስን ከሙታን ለማውጣት ነው” ብሎአል። (ሮሜ 10:7) ኢየሱስ በዚያ ጥልቅ ውስጥ በነበረበት ጊዜ በድን ነበር። * እንግዲያው ሰይጣንና አጋንንቱ በጥልቁ ውስጥ በሚቆዩበት የሺህ ዓመት ጊዜ ከሞት ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ ከምንም ሥራና እንቅስቃሴ ታግደው ይኖራሉ ማለት ነው። ይህ ለጽድቅ ወዳዶች ሁሉ ትልቅ የምሥራች ነው።

የሺህ ዓመት ፈራጆች

8, 9. ዮሐንስ በዙፋን ላይ ስለሚቀመጡት ምን ይነግረናል? እነዚህስ እነማን ናቸው?

8 ከሺው ዓመት በኋላ ሰይጣን ለጥቂት ጊዜ ከጥልቁ ይፈታል። የሚፈታው ለምንድን ነው? ዮሐንስ የዚህን መልስ ከመስጠቱ በፊት በዚህ ዘመን መጀመሪያ ላይ ስለሚሆነው ነገር እንዲህ በማለት ይነግረናል:- “ዙፋኖችንም አየሁ፣ በእነርሱም ላይ ለተቀመጡት ዳኝነት ተሰጣቸው።” (ራእይ 20:4ሀ) እነዚህ በዙፋን ላይ የተቀመጡትና ከፍ ያለ ክብር ከተቀዳጀው ኢየሱስ ጋር በሰማይ የሚገዙት እነማን ናቸው?

9 ዳንኤል ‘የሰው ልጅ ከሚመስለው ጋር’ በመንግሥት እንደሚገዙ የተናገረላቸው “ቅዱሳን” ናቸው። (ዳንኤል 7:13, 14, 18) በይሖዋ ዙፋን ፊት በሰማያዊ ዙፋኖች ላይ ከተቀመጡት 24 ሽማግሌዎች ጋር አንድ ናቸው። (ራእይ 4:4) ከእነዚህ መካከል “እናንተስ የተከተላችሁኝ፣ በዳግመኛ ልደት የሰው ልጅ በክብሩ ዙፋን በሚቀመጥበት ጊዜ፣ እናንተ ደግሞ በአሥራ ሁለቱ የእሥራኤል ነገድ ስትፈርዱ በአሥራ ሁለት ዙፋን ትቀመጣላችሁ” ሲል ቃል የገባላቸው 12 ሐዋርያት ይገኛሉ። (ማቴዎስ 19:28) ከእነዚህም ጋር ጳውሎስና ታማኝነታቸውን ጠብቀው የጸኑት የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ይጨመራሉ። (1 ቆሮንቶስ 4:8፤ 6:2, 3) ከዚህም በላይ ድል የነሱት የሎዶቅያ ጉባኤ አባላት ይኖራሉ።—ራእይ 3:21

10. (ሀ) ዮሐንስ 144,000ዎቹን ነገሥታት ምን በማለት ይገልጽልናል? (ለ) ዮሐንስ ቀደም ሲል በተናገረው መሠረት ከ144,000ዎቹ መካከል እነማን ይገኛሉ?

10 ለእነዚህ “ለአምላክና ለበጉ በኩራት እንዲሆኑ ከሰው ልጆች መካከል የተዋጁ” ቅቡዓን ድል አድራጊዎች 144,000 ዙፋኖች ተዘጋጅተውላቸዋል። (ራእይ 14:1, 4) ዮሐንስ በመቀጠል እንዲህ ይላል:- “ስለ ኢየሱስም ምስክርና ስለ እግዚአብሔር ቃል ራሶቻቸው [“በመጥረቢያ፣” NW] የተቆረጡባቸውን ሰዎች ነፍሳት፣ ለአውሬውና ለምስሉም ያልሰገዱትን ምልክቱንም በግምባራቸው በእጆቻቸውም ላይ ያልተቀበሉትን አየሁ።” (ራእይ 20:4ለ) ስለዚህ ከእነዚህ ነገሥታት መካከል ቀደም ሲል አምስተኛው ማህተም በተፈታበት ጊዜ ይሖዋ ደማቸውን እስከ መቼ ድረስ ሳይበቀል እንደሚቆይ የጠየቁት ቅቡዓን ክርስቲያን ሰማዕታት ይገኙበታል። በዚያ ጊዜ ነጭ ልብስ ከተሰጣቸው በኋላ ጥቂት ጊዜ እንዲጠብቁ ተነግሮአቸው ነበር። አሁን ግን ታላቂቱ ባቢሎን ስለወደመች፣ የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ ብሔራትን ስላጠፋቸውና ሰይጣን ወደ ጥልቁ ስለተጣለ ደማቸውን ተበቅሎላቸዋል።—ራእይ 6:9-11፤ 17:16፤ 19:15, 16

11. (ሀ) “ራሶቻቸው [“በመጥረቢያ፣” NW] የተቆረጡባቸው” የሚለውን አነጋገር የምንረዳው እንዴት ነው? (ለ) 144,000ዎቹ በሙሉ መስዋዕታዊ ሞት ሞተዋል ልንል የምንችለው ለምንድን ነው?

11 እነዚህ 144,000 ንጉሣዊ ፈራጆች በሙሉ ቃል በቃል ‘ራሶቻቸው [“በመጥረቢያ፣” NW] ተቆርጠውባቸው’ ነበርን? ቃል በቃል ራሶቻቸው ተቆርጠውባቸው የሞቱት ጥቂቶች ብቻ ናቸው። ይህን የመሰለ መግለጫ የተሰጠው በማንኛውም መልክ በሰማዕትነት ለሞቱት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ከፍተኛ ቦታ ለመስጠት ነው። * (ማቴዎስ 10:22, 28) በእርግጥም ሰይጣን ሁሉንም ራሶቻቸውን በመጥረቢያ እያስቆረጠ ቢያስገድላቸው ይወድ ነበር። ይሁን እንጂ የኢየሱስ ቅቡዓን ወንድሞች በሙሉ የሰማዕትነት ሞት አልሞቱም። ብዙዎቹ የሞቱት በበሽታ ወይም በእርጅና ምክንያት ነው። ቢሆንም እነዚህም ቅቡዓን ክርስቲያኖች አሁን ዮሐንስ ከተመለከታቸው ጋር የሚቆጠሩ ናቸው። የሁሉም ሞት መሥዋዕታዊ ሞት እንደሆነ ተደርጎ ሊታይ ይችላል። (ሮሜ 6:3-5) በተጨማሪም አንዳቸውም ቢሆኑ የዚህ ዓለም ክፍል አልነበሩም። በዚህም ምክንያት ሁሉም በዓለም የተጠሉ ስለሆኑ በዚህ ዓለም ዓይን እንደ ሙታን ተቆጥረዋል። (ዮሐንስ 15:19፤ 1 ቆሮንቶስ 4:13) አንዳቸውም ቢሆኑ አውሬውን ወይም ምስሉን አላመለኩም። በሞቱበትም ጊዜ የአውሬው ምልክት አልተገኘባቸውም። ሁሉም በድል አድራጊነት ሞተዋል።—1 ዮሐንስ 5:4፤ ራእይ 2:7፤ 3:12፤ 12:11

12. ዮሐንስ ስለ 144,000ዎቹ ምን ይነግረናል? ወደ ሕይወት የመጡትስ መቼ ነው?

12 አሁን ግን እነዚህ ድል አድራጊዎች እንደገና ሕያው ሆነዋል። ዮሐንስ እንዲህ ሲል ይነግረናል:- “እነርሱ ከሞት ተነስተው ከክርስቶስ ጋር ሺህ ዓመት ነገሡ።” (ራእይ 20:4ሐ የ1980 ትርጉም) ታዲያ እንዲህ ሲባል እነዚህ ፈራጆች አሕዛብ እስኪጠፉና ሰይጣንና አጋንንቱ በጥልቁ ውስጥ እስኪታሠሩ ድረስ ከሙታን አይነሱም ማለት ነውን? በፍጹም አይደለም። አብዛኞቹ ከኢየሱስ ጎን ተሰልፈው በአርማጌዶን ጦርነት ይዋጋሉ ስለተባለ ሕያዋን ናቸው። (ራእይ 2:26, 27፤ 19:14) እንዲያውም ሐዋርያው ጳውሎስ እንደገለጸው የእነርሱ ትንሣኤ የሚጀምረው የኢየሱስ መገኘት ከሚሆንበት ከ1914 ጀምሮ ሲሆን አንዳንዶቹ ከሌሎች ቀድመው ይነሳሉ። (1 ቆሮንቶስ 15:51-54፤ 1 ተሰሎንቄ 4:15-17) ስለዚህ ሕይወት የሚያገኙት አንድ በአንድ ወደ ሰማይ ተነስተው የማይሞት ሕይወት በሚቀበሉበት ጊዜ ነው።—2 ተሰሎንቄ 1:7፤ 2 ጴጥሮስ 3:11-14

13. (ሀ) 144,000ዎቹ የሚገዙበትን የሺህ ዓመት ዘመን እንዴት መረዳት ይኖርብናል? ለምንስ? (ለ) የሂራፖሊሱ ፓፒያስ ሺውን ዓመት እንዴት ተረድቶ ነበር? (የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።)

13 የሚገዙትና የሚፈርዱት ለሺህ ዓመት ነው። ይሁን እንጂ ይህ ሺህ ዓመት ቃል በቃል ሺህ ዓመት ነው ወይስ መጠኑ ያልተወሰነ ረዥም ዘመን? “ሺህ” በ⁠1 ሳሙኤል 21:11 ላይ እንደተመለከተው መጠኑ ያልተወሰነ ብዙ ቁጥርን ሊያመለክት ይችላል። እዚህ ላይ የተጠቀሰው “ይህ ሺህ ዓመት” ግን በ⁠ራእይ 20:5-7 ላይ ሦስት ጊዜ ስለተጠቀሰ ቃል በቃል ሺህ ዓመት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “ቀን ቀጥሮአልና፣ በዚያም ቀን ባዘጋጀው ሰው እጅ በዓለሙ ላይ በጽድቅ ሊፈርድ አለው” ባለ ጊዜ ይህ የፍርድ ዘመን አንድ “ቀን” እንደሆነ አመልክቶአል። (ሥራ 17:31) ጴጥሮስ በይሖዋ ዘንድ አንድ ቀን እንደ ሺህ ዓመት እንደሆነ ስለሚነግረን ይህ የፍርድ ቀን ቃል በቃል ሺህ ዓመት መሆኑ ተገቢ ነው። *2 ጴጥሮስ 3:8

የቀሩት ሙታን

14. (ሀ) ዮሐንስ ስለ “ቀሩት ሙታን” ምን ተናግሮአል? (ለ) ሐዋርያው ጳውሎስ የተናገረው ቃል ወደ ሕይወት መምጣት የሚለውን አባባል እንድንረዳ የሚያስችለን እንዴት ነው?

14 ይሁን እንጂ ሐዋርያው ዮሐንስ “የቀሩት ሙታን ግን ይህ ሺህ መት እስኪፈጸም ድረስ በሕይወት አልኖሩም” ካለ እነዚህ ነገሥታት የሚፈርዱት ማንን ነው? (ራእይ 20:5ሀ) አሁንም “በሕይወት አልኖሩም” የሚለውን አነጋገር ለመረዳት ከቃሉ አገባብ ጋር አስማምተን መመልከት ይኖርብናል። ይህ አነጋገር በተለያዩ ሁኔታዎች የተለያዩ ትርጉሞች ሊኖሩት ይችላል። ለምሳሌ ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ቅቡዓን ክርስቲያን ባልንጀሮቹ ሲናገር “በመተላለፋችሁና በኃጢአታችሁ ሙታን የነበራችሁ ቢሆንም አምላክ ሕያዋን አደረጋችሁ” ብሎአል። (ኤፌሶን 2:1 NW) አዎ፣ በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች በኢየሱስ መሥዋዕት በማመናቸው ምክንያት ጻድቃን ሆነው ስለተቆጠሩ በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንኳን ‘ሕያዋን’ ሆነው ነበር።—ሮሜ 3:23, 24

15. (ሀ) ከክርስትና በፊት የነበሩ የይሖዋ ምሥክሮች በአምላክ ፊት እንዴት ያለ አቋም አግኝተው ነበር? (ለ) ሌሎች በጎች ወደ ሕይወት የሚመጡት እንዴት ነው? ምድርን ሙሉ በሙሉ የሚወርሱት መቼ ነው?

15 በተመሳሳይም ከክርስትና በፊት የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች ከአምላክ ጋር ወዳጆች ስለነበሩ ጻድቃን እንደሆኑ ተቆጥረዋል። በዚህም ምክንያት አብርሃም፣ ይሥሐቅና ያዕቆብ በሥጋ ሙታን ቢሆኑም እንኳን “ሕያዋን” እንደሆኑ ተነግሮላቸዋል። (ማቴዎስ 22:31, 32፤ ያዕቆብ 2:21, 23) ይሁን እንጂ እነዚህም ሆኑ ከሙታን የሚነሱትና አርማጌዶንን በሕይወት የሚያልፉት የታማኝ ሌሎች በጎች ክፍል የሆኑት እጅግ ብዙ ሰዎች በአዲሱ ዓለም ውስጥ ከሚወለዱላቸው ልጆች ጋር ወደ ሰብአዊ ፍጽምና መድረስ ይኖርባቸዋል። ይህ ደግሞ የሚፈጸመው በሺው ዓመት የፍርድ ቀን በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት መሠረት ላይ በክርስቶስና በተባባሪ ነገሥታቱ አማካኝነት ነው። በዚህ ቀን መጨረሻ ላይ ፍጹም ሰዎች ስለሚሆኑ “የቀሩት ሙታን” ‘በሕይወት ይኖራሉ።’ ከዚያ በኋላ ወደፊት እንደምንመለከተው የመጨረሻ ፈተና ማለፍ ይኖርባቸዋል። ይሁን እንጂ ይህን ፈተና የሚቋቋሙት ፍጹማን ከሆኑ በኋላ ነው። ፈተናውን ካለፉ በኋላ ለዘላለም መኖር የሚገባቸውና ሙሉ በሙሉ ጻድቃን እንደሆኑ ይፈረድላቸዋል። “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፣ በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ” የሚለው ተስፋ ሙሉ በሙሉ ይፈጸምላቸዋል። (መዝሙር 37:29) ታዛዥ ለሆኑ የሰው ልጆች የተጠበቀላቸው ተስፋ በእርግጥም በጣም አስደሳች ነው!

የመጀመሪያው ትንሣኤ

16. ዮሐንስ ከክርስቶስ ጋር ነገሥታት ሆነው የሚገዙት ሰዎች የሚያገኙትን የተባረከ ተስፋ የገለጸው እንዴት ነው? ለምንስ?

16 አሁን “ከሞት ተነስተው ከክርስቶስ ጋር ሺህ ዓመት” ወደ ነገሡት እንመለስ። ዮሐንስ “ይህ የፊተኛው ትንሣኤ ነው” ሲል ጽፎአል። (ራእይ 20:5ለ) የመጀመሪያ የሆነው በምን መንገድ ነው? ይህንን ትንሣኤ ያገኙት “ለእግዚአብሔርና ለበጉ በኩራት” ስለሚሆኑ በጊዜው ቀደምትነት ምክንያት የመጀመሪያ ነው። (ራእይ 14:4) በዚህ ትንሣኤ የሚካፈሉት ከኢየሱስ ጋር በሰማያዊው መንግሥት ተባባሪ ገዥዎች ስለሚሆኑና በቀረው የሰው ዘር ላይ ፈራጆች ስለሚሆኑ በአስፈላጊነቱም የመጀመሪያው ነው። በዓይነቱም ቢሆን የመጀመሪያው ነው። ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ያለመሞትን ባሕርይ እንደተቀበሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተነገረላቸው ፍጥረታት ይህን የመጀመሪያውን ትንሣኤ ያገኙት ብቻ ናቸው።—1 ቆሮንቶስ 15:53፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:16

17. (ሀ) ዮሐንስ ቅቡዓን ክርስቲያኖች የሚያገኙትን የተባረከ ተስፋ የገለጸው እንዴት ነው? (ለ) “ሁለተኛው ሞት” ምንድን ነው? በ144,000ዎቹ ድል አድራጊዎች ላይ ‘ሥልጣን የማይኖረውስ’ ለምንድን ነው?

17 ቅቡዓን እንዴት ያለ የተባረከ ተስፋ ይጠብቃቸዋል! ዮሐንስ እንደሚነግረን “በፊተኛው ትንሣኤ ዕድል ያለው ብፁዕና ቅዱስ ነው፤ ሁለተኛው ሞት በእነርሱ ላይ ሥልጣን የለውም።” (ራእይ 20:6ሀ) ኢየሱስ ለሰምርኔስ ክርስቲያኖች ቃል እንደገባው እነዚህ በመጀመሪያው ትንሣኤ የሚካፈሉት ድል አድራጊዎች “በሁለተኛው ሞት” አይጎዱም። “ሁለተኛው ሞት” የትንሣኤ ተስፋ የሌለው የዘላለም ጥፋት ነው። (ራእይ 2:11፤ 20:14) እነዚህ ድል አድራጊዎች ያለመሞትንና ያለመበስበስን ባሕርይ ስለሚወርሱ ሁለተኛው ሞት በእነርሱ ላይ “ሥልጣን” አይኖረውም።—1 ቆሮንቶስ 15:53

18. ዮሐንስ ስለ ምድር አዲስ ገዥዎች ምን ተናገረ? ምንስ ነገር ያከናውናሉ?

18 በሰይጣን የሥልጣን ዘመን ከኖሩት የምድር ነገሥታት ፈጽሞ የተለዩ ናቸው። እነዚህ ነገሥታት የሚገዙት ግፋ ቢል ለ50 ወይም ለ60 ዓመት ብቻ ነው። እንዲያውም የአብዛኞቹ የግዛት ዘመን ከጥቂት ዓመታት አላለፈም። ብዙዎቹ የሰው ልጆችን ጨቁነዋል። ያም ሆነ ይህ እነዚህ በየጊዜው የሚቀያየሩና ፖሊሲያቸውን የሚለዋውጡ ገዥዎች ለብሔራት ዘለቄታ ያለው ጥቅም ሊያስገኙ አይችሉም። የምድር አዲስ ገዥዎች ከእነዚህ የተለዩ መሆናቸውን ዮሐንስ ሲገልጽ “ዳሩ ግን የእግዚአብሔርና የክርስቶስ ካህናት ይሆናሉ፣ ከእርሱም ጋር ይህን ሺህ ዓመት ይነግሣሉ” ብሎአል። (ራእይ 20:6ለ) ከኢየሱስ ጋር ሆነው ለሺህ ዓመታት ብቸኛ ገዥ ሆኖ የሚያስተዳዳረውን መንግሥት ይመሠርታሉ። የኢየሱስ ፍጹም ሰብዓዊ መሥዋዕት ዋጋ ጥቅም ላይ እንዲውል በማድረግ የሚሰጡት የክህነት አገልግሎት ታዛዥ የሰው ልጆችን ወደ መንፈሣዊ፣ ሥነ ምግባራዊና አካላዊ የፍጽምና ደረጃ ከፍ ያደርጋቸዋል። ንጉሣዊ አገልግሎታቸው የይሖዋን ጽድቅና ቅድስና የሚያንጸባርቅ ምድር አቀፋዊ የሰው ልጆች ማኅበረሰብ እንዲቋቋም ያደርጋል። ለሺህ ዓመት የሚቆዩ ፈራጆች እንደመሆናቸው መጠን ከኢየሱስ ጋር ሆነው ታዛዥ የሰው ልጆችን ወደ ዘላለም ሕይወት በፍቅር ይመሩአቸዋል።—ዮሐንስ 3:16

የመጨረሻው ፈተና

19. በሺው ዓመት ግዛት መጨረሻ ላይ ምድርና የሰው ልጆች እንዴት ያለ ደረጃ ላይ ይደርሳሉ? በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ምን ያደርጋል?

19 የሺው ዓመት ግዛት በሚፈጸምበት ጊዜ መላዋ ምድር የመጀመሪያዋን ኤደን የመሰለች ትሆናለች። በማንኛውም መንገድ የተሟላች ገነት ትሆናለች። ፍጹም የሆነው የሰው ልጅ በዚያን ጊዜ በአምላክ ፊት አማላጅ የሚሆንለት ሊቀ ካህናት አያስፈልገውም። ምክንያቱም በዚያ ጊዜ የአዳማዊው ኃጢአት ርዝራዥ በሙሉ ይጠፋል። የመጨረሻ ጠላት የሆነው ሞት እንኳን ይሻራል። የክርስቶስ መንግሥት አምላክ በአንድ መንግሥት የሚተዳደር አንድ ዓለም ለመፍጠር ያወጣውን ዓላማ ሙሉ በሙሉ ይፈጽማል። ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ ኢየሱስ “መንግሥቱን ለእግዚአብሔር ለአባቱ አሳልፎ” ይሰጣል።—1 ቆሮንቶስ 15:22-26፤ ሮሜ 15:12

20. ዮሐንስ የመጨረሻ ፈተና በሚሆንበት ጊዜ ምን እንደሚሆን ነግሮናል?

20 አሁን የመጨረሻ ፈተና የሚሰጥበት ጊዜ ይሆናል። ይህ ፍጽምና ደረጃ ላይ የደረሰው የሰው ልጆች ዓለም በኤደን ከነበሩት የመጀመሪያ ሰዎች በተለየ ሁኔታ በፍጹም አቋሙ ይቀጥል ይሆንን? ዮሐንስ የሚሆነውን ነገር ይነግረናል:- “ሺሁም ዓመት ሲፈጸም ሰይጣን ከእስራቱ ይፈታል፣ በአራቱም በምድር ማዕዘን ያሉትን አሕዛብ፣ ጎግንና ማጎግን፣ እንዲያስታቸው ለሰልፍም እንዲያስከትታቸው ይወጣል፤ ቁጥራቸውም እንደ ባሕር አሸዋ የሚያህል ነው። ወደ ምድርም ስፋት ወጡ የቅዱሳንንም ሰፈርና የተወደደችውን ከተማ ከበቡ።”—ራእይ 20:7-9ሀ

21. ሰይጣን የመጨረሻ ሙከራውን የሚፈጽመው እንዴት ነው? ከሺው ዓመት ግዛት በኋላ እንኳን ሰይጣንን የሚከተሉ ሰዎች በመኖራቸው ልንደነቅ የማይገባን ለምንድን ነው?

21 የሰይጣን የመጨረሻ ሙከራ ምን ውጤት ያስገኝ ይሆን? “በምድር ማዕዘን ያሉትን አሕዛብ ጎግንና ማጎግን” አስቶ ለጦርነት ያስከትታቸዋል። ከሺህ ዓመት የደስታና የሚያንጽ ቲኦክራቲካዊ የግንባታ ዘመን በኋላ ከሰይጣን ጎን የሚሰለፍ ማን ሊኖር ይችላል? ሰይጣን ፍጹም የነበሩትን አዳምንና ሔዋንን በኤደን ገነት ውስጥ በደስታ እየኖሩ ሳሉ ሊያስታቸው እንደቻለ መዘንጋት የለብንም። የመጀመሪያው ዓመፅ ያስከተለውን አስከፊ ውጤት ተመልክተው የነበሩትን የሰማይ መላእክት ለማሳት ችሎአል። (2 ጴጥሮስ 2:4፤ ይሁዳ 6) ስለዚህ የአምላክ መንግሥት አስደሳች በሆነ ሁኔታ ለአንድ ሺህ ዓመት ያህል ካስተዳደረ በኋላ እንኳን ሰይጣንን ለመከተል የሚታለሉ ፍጹማን ሰዎች መኖራቸው ሊያስደንቀን አይገባም።

22. (ሀ) ‘በአራቱ የምድር ማዕዘን’ ያሉ አሕዛብ የሚለው አነጋገር ምን ያመለክታል? (ለ) ዓመፀኞቹ “የማጎጉ ጎግ” የተባሉት ለምንድን ነው?

22 መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህን ሰዎች “በምድር ማዕዘን ያሉት አሕዛብ” ብሎ ይጠራቸዋል። ይሁን እንጂ ይህ ማለት የሰው ልጅ እንደገና እርስ በርሳቸው በተለያዩና በተነጣጠሉ ብሔሮች ይከፋፈላል ማለት አይደለም። እነዚህ ሰዎች ከይሖዋ ጻድቅና ታማኝ ተገዥዎች ተለይተው በዛሬው ዘመን የሚኖሩት ብሔራት የሚያሳዩትን የመሰለ መጥፎ መንፈስ እንደሚያሳዩ ያመለክታል። በሕዝቅኤል ትንቢት እንደተጠቀሰው የማጎጉ ጎግ በምድር ላይ የተቋቋመውን ቲኦክራቲካዊ መንግሥት ለማጥፋት “ክፉ አሳብ” አስበው ይነሳሉ። (ሕዝቅኤል 38:3, 10-12) በዚህም ምክንያት “የማጎግ ጎግ” ተብለው ተጠርተዋል።

23. የዓመፀኞቹ ብዛት “እንደ ባሕር አሸዋ” መሆኑ ምን ያመለክታል?

23 በዚህ ዓመፅ ከሰይጣን ጋር የሚተባበሩት ሰዎች ቁጥር “እንደ ባሕር አሸዋ” ይሆናል። ይህስ ምን ያህል ነው? ቁጥራቸው በቅድሚያ የተወሰነ አይደለም። (ከ⁠ኢያሱ 11:4⁠ና ከ⁠መሳፍንት 7:12 ጋር አወዳድር።) የዓመፀኞቹ ጠቅላላ ብዛት እያንዳንዱ ግለሰብ ለሰይጣን ሽንገላና ማታለያ በሚሰጠው ምላሽ ላይ የተመካ ነው። ቢሆንም “የቅዱሳንን ሰፈርና የተወደደችውን ከተማ” ከብቦ ለመያዝ የሚያስችል ኃይል እንዳላቸው ስለሚሰማቸው ቁጥራቸው በቀላሉ የሚገመት እንደማይሆን የታወቀ ነው።

24. (ሀ) “የተወደደችው ከተማ” ማን ነች? የምትከበበውስ እንዴት ነው? (ለ) “የቅዱሳን ሰፈር” ምን ያመለክታል?

24 “የተወደደችው ከተማ” ከፍ ያለ ክብር የተቀዳጀው ኢየሱስ በ⁠ራእይ 3:12 ላይ ለተከታዮቹ የተናገረላት ከተማ መሆን ይኖርባታል። ይህችን ከተማ ‘የአምላኬ ከተማ፣ ከአምላኬ ዘንድ የምትወርደው አዲሲቱ ኢየሩሳሌም’ ሲል ጠርቶአታል። ታዲያ ሰማያዊ ድርጅት ከሆነች እነዚህ ምድራዊ ኃይሎች እንዴት ሊከብቡአት ይችላሉ? “የቅዱሳንን ሰፈር” ስለሚከቡ ነው። ካምፕ ወይም ሰፈር የሚመሠረተው ከከተማ ውጭ ነው። ስለዚህ ‘የቅዱሳን ሰፈር’ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ከምትገኝበት ከሰማይ ውጭ በምድር ላይ የሚኖሩትንና የይሖዋን መንግሥታዊ ዝግጅት በታማኝነት የሚደግፉትን የሚያመለክት መሆን ይኖርበታል። በሰይጣን የሚመሩት ዓመፀኞች እነዚህን ታማኝ ሰዎች ሲያጠቁ ጌታ ኢየሱስ በራሱ ላይ እንደተፈጸመ ጥቃት አድርጎ ይቆጥረዋል። (ማቴዎስ 25:40, 45) እነዚህ “አሕዛብ” ሰማያዊቱ ኢየሩሳሌም ምድርን ገነት በማድረግ ያስገኘችውን ውጤት ሁሉ ለማጥፋት ይሞክራሉ። ስለዚህ “የቅዱሳንን ሰፈር” ሲያጠቁ “የተወደደችውንም ከተማ” ማጥቃታቸው ይሆናል።

የእሳትና የዲን ባሕር

25. ዓመፀኞቹ “በቅዱሳን ሰፈር ላይ” የሚያደርሱት ጥቃት ስለሚያስከትለው ውጤት ዮሐንስ ምን ተናግሮአል? ይህስ በሰይጣን ላይ ምን ያስከትልበታል?

25 ታዲያ ይህ የሰይጣን የመጨረሻ ሙከራ ይሳካ ይሆንን? በፍጹም አይሳካም። የማጎጉ ጎግ በዘመናችን በመንፈሳዊ እስራኤላውያን ላይ የሚፈጽመው ጥቃት እንደማይሳካ ሁሉ የመጨረሻ ጥቃቱም ቢሆን አይሳካም። (ሕዝቅኤል 38:18-23) ዮሐንስ የጥቃቱን ውጤት እንደሚከተለው በማለት ይገልጻል:- “እሳትም ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወርዳ በላቻቸው። ያሳታቸውም ዲያብሎስ አውሬውና ሐሰተኛው ነቢይ ወዳሉበት ወደ እሳቱና ወደ ዲኑ ባሕር ተጣለ።” (ራእይ 20:9ለ-10ሀ) በዚህ ጊዜ የቀደመው እባብ ሰይጣን ዲያብሎስ በጥልቁ ውስጥ ከመታሰር አልፎ ተቀጥቅጦና ደቅቆ በእሳት እንደተቃጠለ ያህል ሙሉ በሙሉ ከሕልውና ውጭ ይሆናል።

26. “የእሳቱና የዲኑ ባሕር” ቃል በቃል የሥቃይ ቦታ ሊሆን የማይችለው ለምንድን ነው?

26 “የእሳቱና የዲኑ ባሕር” ቃል በቃል የመሠቃያ ቦታ ሊሆን እንደማይችል ቀደም ስንል ተረድተናል። (ራእይ 19:20) ሰይጣን በዚያ ሥፍራ ለዘላለም የሚሠቃይ ከሆነ ይሖዋ በሕይወት ሊያቆየው ይገባል ማለት ነው። ሕይወት ደግሞ ሥጦታ ነው እንጂ ቅጣት አይደለም። ለኃጢአት የሚሰጥ ቅጣት ሞት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ደግሞ የሞቱ ፍጥረታት ምንም ዓይነት ሕመም አይሰማቸውም። (ሮሜ 6:23፤ መክብብ 9:5, 10) ከዚህም በላይ ሞት ራሱ ከሔድስ ጋር ወደዚሁ የእሳትና የዲን ባሕር ውስጥ እንደተጣለ ከዚህ ዝቅ ብለን እናነባለን። ሞትና ሔድስ ወይም ሲኦል ምንም ዓይነት ሕመም ሊሰማቸው እንደማይችል የታወቀ ነው!—ራእይ 20:14

27. በሰዶምና በገሞራ ላይ የደረሰው ነገር የእሳትና የዲን ባሕር የሚለውን አነጋገር እንድንረዳ የሚያስችለን እንዴት ነው?

27 ይህ ሁሉ የእሳቱና የዲኑ ባሕር ምሳሌያዊ መሆን ይኖርበታል የሚለውን ሐሳብ የሚያጠናክር ነው። ከዚህም በላይ እሳትና ባሕር መጠቀሱ የጥንቶቹ ሰዶምና ገሞራ የደረሰባቸውን እጣ ያስታውሰናል። እነዚህ ከተሞች በክፋታቸው ምክንያት አምላክ አጥፍቶአቸዋል። ጊዜው በደረሰ ጊዜ ይሖዋ “በሰዶምና ገሞራ ላይ ከእግዚአብሔር [“ከይሖዋ፣” NW] ዘንድ ከሰማይ እሳትና ዲን አዘነበ።” (ዘፍጥረት 19:24) በሁለቱ ከተሞች ላይ የደረሰው ቅጣት ‘የዘላለም እሳት ቅጣት’ ተብሎአል። (ይሁዳ 7) ይሁን እንጂ እነዚህ ሁለት ከተሞች ዘላለማዊ ቅጣት አልደረሰባቸውም። ከዚህ ይልቅ ከወራዳ ነዋሪዎቻቸው ጋር ለዘላለም ከምድር ገጽ ተጠርገው ጠፍተዋል። እነዚህ ከተሞች በአሁኑ ጊዜ አይገኙም። የት ሥፍራ ላይ እንደነበሩም አስረግጦ ሊናገር የሚችል ሰው የለም።

28. የእሳቱና የዲኑ ባሕር ምንድን ነው? ከሞት፣ ከሔድስና ከጥልቁ የሚለየውስ እንዴት ነው?

28 መጽሐፍ ቅዱስ ከዚህ ጋር በመስማማት የእሳቱንና የዲኑን ባሕር ትርጉም ሲሰጠን “ይህም የእሳት ባሕር ሁለተኛው ሞት ነው” ይላል። (ራእይ 20:14) ይህ ሥፍራ ክፉዎች ለዘላለም የሚሠቃዩበት ሳይሆን ሞተው የሚቀሩበት ሥፍራ ከሆነውና ኢየሱስ ገሃነም ሲል ከጠራው ቦታ ጋር አንድ እንደሆነ ግልጽ ነው። (ማቴዎስ 10:28) ምንም ዓይነት የትንሣኤ ተስፋ የሌለበት ፍጹም ጥፋት ነው። በዚህም ምክንያት ሞት፣ ሔድስ ወይም ሲኦልና ጥልቁ የሚከፈቱበት ቁልፍ ሲኖር የዲኑንና የእሳቱን ባሕር ግን የሚከፍት ቁልፍ ስለመኖሩ አልተጠቀሰም። (ራእይ 1:18፤ 20:1) በውስጡ የያዛቸውን ምርኮኞች ፈጽሞ አይመልስም።—ከ⁠ማርቆስ 9:43-47 ጋር አወዳድር።

ቀንና ሌሊት ለዘላለም መሠቃየት

29, 30. ዮሐንስ ስለ ዲያብሎስ፣ ስለ አውሬውና ስለ ሐሰተኛው ነቢይ ምን ተናግሮአል? ይህንንስ የምንረዳው እንዴት ነው?

29 ዮሐንስ ስለ አውሬው፣ ስለ ሐሰተኛው ነቢይና ስለ ዲያብሎስ ሲናገር “ለዘላለምም እስከ ዘላለም ቀንና ሌሊት ይሣቀያሉ” ይላል። (ራእይ 20:10ለ) ታዲያ ይህ ምን ማለት ሊሆን ይችላል? ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው አውሬ፣ ሐሰተኛው ነቢይና እንደ ሞትና ሔድስ የመሰሉት ምሳሌያዊ ነገሮች ቃል በቃል መከራና ሥቃይ ይቀበላሉ ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ አይደለም። ስለዚህ ሰይጣን ለዘላለም እስከ ዘላለም ይሠቃያል ብለን የምናምንበት ምንም ምክንያት የለንም። ሙሉ በሙሉ ይጠፋል።

30 እዚህ ላይ “ይሣቀያሉ” ተብሎ የተጠቀሰው ባሳኒዞ የተባለው የግሪክኛ ቃል መሠረታዊ ትርጉሙ “አንድን ማዕድን ለመፈተን በድንጋይ ላይ መፋቅ” ማለት ነው። ሁለተኛው ትርጉም ደግሞ “እያሠቃዩ መጠየቅና መመርመር” ነው። (ዘ ኒው ቴየረስ ግሪክ፣ ኢንግሊሽ ሌክሲከን ኦፍ ዘ ኒው ቴስታመንት) የዚህን የግሪክኛ ቃል ትርጉም ከቃሉ አገባብ ጋር ስናስተያይ በሰይጣን ላይ የሚደርሰው ነገር እንደ መፈተኛ ድንጋይ የይሖዋን አገዛዝ ትክክለኛነትና ጻድቅነት ለዘላለም እስከ ዘላለም የሚያረጋግጥ እንደሆነ ያመለክታል። በሉዓላዊ ገዥነቱ ላይ የተነሳው ጥያቄ ለአንዴና ለሁልጊዜ ምላሽ ያገኛል። ከዚያ በኋላ በይሖዋ ሉዓላዊነት ላይ የሚነሳ ግድድር ስህተት መሆኑ እንዲረጋገጥ ረዘም ላለ ጊዜ መፈተን አያስፈልገውም።—ከ⁠መዝሙር 92:1, 15 ጋር አወዳድር።

31. “ሥቃይ” ከሚለው ትርጉም ጋር ተዛማጅነት ያላቸው ሁለት የግሪክኛ ቃላት በሰይጣን ዲያብሎስ ላይ የሚፈጸመውን ቅጣት እንድንረዳ የሚረዱን እንዴት ነው?

31 በተጨማሪም ከዚሁ ቃል ጋር የሚዛመደው ባሳኒዞተስ የተባለው ቃል ትርጉሙ “የሚያሠቃይ” ማለት ሲሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የወህኒ ቤት ዘበኛን ለማመልከት ተሰርቶበታል። (ማቴዎስ 18:34) ሰይጣንም በዚህ አተረጓጎም መሠረት በእሳት ባሕር ውስጥ ለዘላለም ይታሠራል። ከዚያ ሊወጣ ፈጽሞ አይችልም። በመጨረሻም ዮሐንስ በሚገባ በሚያውቀው በግሪክኛው የሰፕቱጅንት መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ባሳኖዝ የተባለው ተዛማጅ ቃል ወደ ሞት የሚያደርስን ውርደት አመልክቶአል። (ሕዝቅኤል 32:24, 30) ይህም ሰይጣን የሚደርስበት ቅጣት በእሳቱና በዲን ባሕር ውስጥ የውርደት ዘላለማዊ ሞት እንደሚሆን ያመለክታል። ሥራውም አብሮት ይሞታል።—1 ዮሐንስ 3:8

32. አጋንንት ምን ዓይነት ቅጣት ይፈጸምባቸዋል? ይህንንስ እንዴት እናውቃለን?

32 አጋንንት አሁንም በዚህ ቁጥር ላይ አልተጠቀሱም። ታዲያ እነርሱም በሺው ዓመት ፍጻሜ ላይ ከሰይጣን ጋር ተለቀው ከእርሱ ጋር የዘላለም ሞት ቅጣት ይቀበላሉ ማለት ነውን? አዎ፣ ብለን እንድንመልስ የሚያስችለን በቂ ማስረጃ አለን። ኢየሱስ በተናገረው የበጎችና የፍየሎች ምሳሌ ላይ ፍየሎች “ለሰይጣንና ለመላእክቱ ወደ ተዘጋጀ ወደ ዘላለም እሳት” እንደሚሄዱ ገልጾአል። (ማቴዎስ 25:41) “የዘላለም እሳት” የሚለው ሐረግ ሰይጣን የሚጣልበትን የእሳትና የዲን ባሕር የሚያመለክት መሆን ይኖርበታል። የዲያብሎስ መላእክት ከዲያብሎስ ጋር ከሰማይ ተጥለዋል። በሺው ዓመት ግዛት መጀመሪያ ላይም ከእርሱ ጋር በጥልቁ ውስጥ ታስረዋል። በመጨረሻም ከእርሱ ጋር በእሳቱና በዲኑ ባሕር ውስጥ ተጥለው መጥፋት ይገባቸዋል።—ማቴዎስ 8:29

33. በዚያ ጊዜ የሚፈጸመው የትኛው የ⁠ዘፍጥረት 3:15 ትንቢት ነው? የይሖዋ መንፈስ የዮሐንስን ትኩረት የሳበው ወደ ምን ጉዳይ ነው?

33 በዚህ መንገድ በ⁠ዘፍጥረት 3:15 ላይ የተመዘገበው ትንቢት የመጨረሻ ክፍል ይፈጸማል። ሰይጣን ወደ እሳቱ ባሕር በሚጣልበት ጊዜ ጭንቅላቱ እንደ ብረት በጠነከረ ተረከዝ እንደተደፈጠጠ እባብ ይሞታል። እርሱና አጋንንቱ ለዘላለም ይጠፋሉ። ከዚህ በኋላ በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ዳግመኛ አልተጠቀሱም። የይሖዋ መንፈስ እነዚህን በትንቢት ካስወገደ በኋላ ምድራዊ ተስፋ ላላቸው ሰዎች በጣም አሳሳቢ ወደሆነ ጉዳይ ትኩረቱን ይመልሳል። “ከነገሥታት ንጉሥና” ‘ከእርሱ ጋር ካሉ ከተጠሩና ከተመረጡም ከታመኑም’ ግዛት የሰው ልጅ ምን ጥቅም ያገኛል? (ራእይ 17:14) የዚህን መልስ ለመስጠት ዮሐንስ ወደ ሺው ዓመት ግዛት መጀመሪያ ይመልሰናል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.7 ሌሎች ጥቅሶች ኢየሱስ ሞቶ በነበረበት ጊዜ ሔድስ ውስጥ እንደነበረ ይገልጻሉ። (ሥራ 2:31) ይሁን እንጂ ሔድስና ጥልቁ አንድ ናቸው ብለን ማሰብ የለብንም። አውሬውና ሰይጣን ወደ ጥልቁ እንደተጣሉ ቢነገርም ወደ ሔድስ እንደወረዱ የተነገረላቸው ሰዎች ብቻ ናቸው። በዚያም ከሞት የሚነሱበትን ጊዜ እየጠበቁ አንቀላፍተው ይቆያሉ።—ኢዮብ 14:13፤ ራእይ 20:13

^ አን.11 መጥረቢያ (በግሪክኛ ፔሌኩስ) በሮማ ባህላዊ የመግደያ መሣሪያ የነበረ ቢመስልም በዮሐንስ ዘመን ግን በአብዛኛው ጥቅም ላይ ይውል የነበረው ሠይፍ ነበር። (ሥራ 12:2) ስለዚህ እዚህ ላይ የተጠቀሰው ፔፔሌኪስሜኖን የተባለው የግሪክኛ ቃል (“በመጥረቢያ ተቆረጡ”) ባጭሩ “ተገደሉ” ማለት ነው።

^ አን.13 የሂራፖሊሱ ፓፒያስ የመጽሐፍ ቅዱስ ዕውቀቱን ያገኘው የራእይ ጸሐፊ ከሆነው ከዮሐንስ ተማሪዎች ነው ተብሎ ይታመናል። እርሱም የአራተኛው መቶ ዘመን ታሪክ ጸሐፊ የሆነው ዩሴብየስ እንደገለጸው ክርስቶስ ቃል በቃል ለሺህ ዓመት እንደሚገዛ ያምን ነበር። (ዩሴብየስ ግን በዚህ አይስማማም ነበር።)— የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ዩሴብየስ 3፣ 39

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 293 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሙት ባሕር። ሰዶምና ገሞራ የነበሩበት ስፍራ ይህ ሊሆን ይችላል

[በገጽ 294 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

“በአንተና በሴቲቱ መካከል በዘርህና በዘሯ መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፣ አንተም ሰኮናውን ትቀጠቅጣለህ”