በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ሰማያዊ ዙፋን ክብርና ግርማ

የይሖዋ ሰማያዊ ዙፋን ክብርና ግርማ

ምዕራፍ 14

የይሖዋ ሰማያዊ ዙፋን ክብርና ግርማ

ራእይ 2​--ራእይ 4:1 እስከ 5:14

ርእሰ ጉዳይ:- በአምላክ የፍርድ ዙፋን ፊት የተፈጸሙ አስደናቂ ክንውኖች

ራእዩ የሚፈጸምበት ጊዜ:- ይህ ራእይ የሚገልጸው ከ1914 ጀምሮ በሰማይና በምድር ያለ ፍጥረት በሙሉ ይሖዋን እስከሚያወድስበት እስከ ሺው ዓመት መጨረሻና ከዚያም በኋላ የሚሆኑትን ነገሮች ነው።—ራእይ 5:13

1. ዮሐንስ በሚገልጽልን ራእይ ላይ አጥብቀን ማተኮር የሚኖርብን ለምንድን ነው?

ዮሐንስ መንፈሳችንን የሚያነሳሳ ሌላ ራእይ ይነግረናል። አሁንም በመንፈስ በጌታ ቀን ውስጥ ነው። ስለዚህ እርሱ የሚገልጽልን ነገር በዚህ ዘመን ውስጥ ለምንኖረው ለእኛ የጠለቀ ትርጉም ይኖረዋል። ይሖዋ በእነዚህ ራእዮች አማካኝነት ሰማያዊ ነገሮችን እንዳንመለከት ያደረገንን መጋረጃ ገፍፎ በምድር ላይ ስለሚፈጸመው ፍርድ ያለውን የራሱን አመለካከት ያሳየናል። ከዚህም በላይ እነዚህ ራእዮች ተስፋችን ሰማያዊም ሆነ ምድራዊ በይሖዋ ዓላማ ውስጥ ያለንን ቦታ እንድናስተውል ይረዱናል። ስለዚህ ሁላችንም “ዘመኑ ቀርቦአልና የሚያነበው፣ የትንቢቱን ቃል የሚሰሙትና በውስጡ የተጻፈውን የሚጠብቁት ብጹዓን ናቸው” በማለት ዮሐንስ በተናገረው ቃል ላይ ማተኮራችንን መቀጠል ይኖርብናል።—ራእይ 1:3

2. አሁን ዮሐንስ እንዴት ያለ ሁኔታ አጋጠመው?

2 ዮሐንስ ቀጥሎ የተመለከተው ነገር በዚህ ዘመን የሚኖር ሰው በቪድዮ አይቶት ከሚያውቀው ነገር ሁሉ እጅግ የላቀ ነው። እንዲህ ሲል ጽፎአል:- “ከዚህ በኋላም አየሁ፣ እነሆም በሰማይ የተከፈተ ደጅ፣ እንደ መለከትም ሆኖ ሲናገረኝ የሰማሁት ፊተኛው ድምፅ:- ወደዚህ ውጣና ከዚህ በኋላ ሊሆን የሚያስፈልገውን ነገር አሳይሃለሁ አለ።” (ራእይ 4:1) ዮሐንስ በራእይ አማካኝነት ይሖዋ ወደሚገኝበት፣ ሰብዓዊ ጠፈረተኞች ከመረመሩት ጠፈር በላይ እጅግ ከፍ ብሎ ወደሚገኘው፣ በግዑዙ አጽናፈ ዓለም ውስጥ ከሚገኙት ረጨቶች እጅግ ወደራቀው የማይታይ ሰማያት ጠልቆ ገባ። በተከፈተ በር አልፎ እንደሚገባ ሰው ወደ ውስጥ አለፈና የይሖዋ ዙፋን የሚገኝበትን ከፍተኛውን መንፈሳዊ ዓለም አስደናቂ ገጽታዎች ዓይኑ እስኪጠግብ ተመለከተ። (መዝሙር 11:4፤ ኢሳይያስ 66:1) እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው!

3. እንደ መለከት ያለ ድምፅ ምን ነገር ያስታውሰናል? ይህስ ድምፅ ከማን የመጣ ነበር?

3 መጽሐፍ ቅዱስ ይህ “ፊተኛ” ወይም የመጀመሪያ ድምፅ የማን ድምፅ እንደሆነ ለይቶ አይናገርም። ይህ ድምፅ ቀደም ሲል እንደተሰማው እንደ ኢየሱስ ድምፅ እንደመለከት ያለ ኃይል ነበረው። (ራእይ 1:10, 11) ይህ ድምፅ ይሖዋ በሲና ተራራ ላይ መገኘቱን ለማሳወቅ የተነፋውን መለከት ያስታውሰናል። (ዘጸአት 19:18-20) የመለከቱ ጥሪ የቀረበው ከይሖዋ እንደሆነ አያጠራጥርም። (ራእይ 1:1) በሩን የከፈተውም ዮሐንስ በራእይ አማካኝነት የይሖዋ ሉዓላዊነት በሰለጠነበት ግዛት ውስጥ ከሚገኙት ቦታዎች ሁሉ የበለጠ ቅዱስ ወደሆነው ሥፍራ እንዲገባ ነው።

ይሖዋ የሚገኝበት አንጸባራቂ ሁኔታ

4. (ሀ) የዮሐንስ ራእይ ለቅቡዓን ክርስቲያኖች ምን ትርጉም አለው? (ለ) በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ላላቸውስ ምን ትርጉም አለው?

4 ዮሐንስ ምን ነገር ተመለከተ? የተመለከተውንና ያጋጠመውን አስደናቂ ሁኔታ ሲነግረን እናዳምጥ:- “ወዲያው በመንፈስ ነበርሁ እነሆም፣ ዙፋን በሰማይ ቆሞአል በዙፋኑም ላይ ተቀማጭ ነበረ።” (ራእይ 4:2) ዮሐንስ ከመቅጽበት በአምላክ አንቀሳቃሽ ኃይል አማካኝነት ወደ ይሖዋ ዙፋን በመንፈስ ተወሰደ። ዮሐንስ ምን ያህል ተደስቶ ይሆን! እርሱና ሌሎች ቅቡዓን ክርስቲያኖች ‘ሕያው ተስፋ፣ የማይጠፋ፣ እድፈትም የሌለበት፣ የማያልፍ ርስት’ በተጠበቀላቸው በሰማይ ያለውን አስደናቂ ትርዒት እንዲመለከት ተደረገ። (1 ጴጥሮስ 1:3-5፤ ፊልጵስዩስ 3:20) በምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር ተስፋ ለሚያደርጉ ሰዎችም ቢሆን የዮሐንስ ራእይ ጥልቅ ትርጉም አለው። ይሖዋ የሚገኝበትን ሥፍራ ክብርና ግርማ እንዲሁም ይሖዋ በአሕዛብ ላይ በሚፈርድበትና በኋላም በምድር ላይ የሚኖሩትን ሰዎች በሚያስተዳድርበት ጊዜ የሚጠቀምበትን የሰማያዊ አገዛዝ መዋቅር እንዲገነዘቡ ይረዳቸዋል። በእውነትም ይሖዋ በጣም ታላቅ የሆነ የድርጅት አምላክ ነው።

5. ዮሐንስ የተመለከተው የቃል ኪዳኑ ታቦት መክደኛ ምሳሌ የሆነው ለየትኛው እውነተኛ ነገር ነው?

5 ዮሐንስ በሰማይ የተመለከተው ነገር በምድረ በዳ ከነበረው ድንኳን ጋር በአብዛኛው ይመሳሰላል። ይህን ድንኳን እሥራኤላውያን እውነተኛ አምልኮ የሚፈጽሙበት ቤተ መቅደስ እንዲሆናቸው የሠሩት ከ1,600 ዓመታት በፊት ነበር። በዚህ ድንኳን ውስጥ በነበረው ቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ የቃል ኪዳኑ ታቦት ይገኝ ነበር። ይሖዋ ይናገር የነበረው ከንጹሕ ወርቅ ከተሰራው ከታቦቱ መክደኛ በላይ ነበር። (ዘጸአት 25:17-22፤ ዕብራውያን 9:5) ስለዚህ የታቦቱ መክደኛ የይሖዋ ዙፋን ምሳሌ ሆኖ አገልግሎአል። አሁን ደግሞ ዮሐንስ ይህ ነገር ምሳሌ የሆነለትን እውነተኛ ነገር ተመለከተ። የጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዢ የሆነው ጌታ ይሖዋ በጣም ከፍተኛ በሆነው ሰማያዊ ዙፋኑ ታላቅ ግርማ ተጎናጽፎ ተቀምጦአል።

6. ዮሐንስ የገለጸው ነገር ስለ ይሖዋ እንዴት ያለ ግምት እንዲኖረን ያደርጋል? ይህስ ተገቢ የሚሆነው ለምንድን ነው?

6 ዮሐንስ ከእርሱ በፊት የይሖዋን ዙፋን በራእይ ተመልክተው እንደነበሩት ሌሎች ነቢያት በዙፋኑ ላይ የተቀመጠው ቅዱስ አምላክ ምን እንደሚመስል ዝርዝር መግለጫ አልሰጠንም። (ሕዝቅኤል 1:26, 27፤ ዳንኤል 7:9, 10) ቢሆንም ዮሐንስ በዙፋኑ ላይ የተቀመጠው ምን መስሎ እንደታየው በሚከተሉት ቃላት ገልጾልናል። “ተቀምጦም የነበረው በመልኩ የኢያስጲድንና የሰርዲኖን ዕንቁ ይመስል ነበር። በመልኩም መረግድን የመሰለ ቀስተ ደመና በዙፋኑ ዙሪያ ነበረ።” (ራእይ 4:3) እንዴት ያለ ታላቅና አምሳያ የሌለው ግርማና ክብር ነው! ዮሐንስ ያስተዋለው እንደ ክቡር ድንጋይ የሚያንጸባርቅና ያማረ፣ እርጋታና ጸጥታ የተሞላ ውበት ነበር። ይህም ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ ስለ ይሖዋ ሲናገር “የብርሃናት ሁሉ አባት” ካለው ጋር የሚስማማ ነው። (ያዕቆብ 1:17) ራሱ ዮሐንስም የራእይን መጽሐፍ ከጻፈ ከጥቂት ጊዜ በኋላ “እግዚአብሔር ብርሃን ነው፣ ጨለማም በእርሱ ዘንድ ከቶ የለም” ሲል ጽፎአል። (1 ዮሐንስ 1:5) በእውነትም ይሖዋ በጣም ታላቅ ግርማና ክብር ያለው አምላክ ነው።

7. በይሖዋ ዙፋን ዙሪያ ቀስተ ደመና ከመታየቱ ምን ትምህርት ልናገኝ እንችላለን?

7 ዮሐንስ በዙፋኑ ዙሪያ መረግድ የመሰለ ወይም ደማቅ አረንጓዴ መልክ ያለው ቀስተ ደመና ተመልክቶ እንደነበረ አስተውል። እዚህ ላይ ቀስተ ደመና ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል (አይሪስ) ክብ ቅርጽ ያለውን ነገር ያመለክታል። ቀስተ ደመና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ተጠቅሶ የምናገኘው ስለ ኖኅ ዘመን በሚናገረው ታሪክ ላይ ነው። የጥፋቱ ውኃ ጋብ ብሎ ከቆመ በኋላ ይሖዋ በደመናው ውስጥ ቀስተ ደመና እንዲታይ አደረገና ቀስተ ደመናው የምን ምሳሌ እንደሆነ ሲገልጽ የሚከተለውን ተናገረ። “ቀስቴን በደመና አድርጌአለሁ፣ የቃል ኪዳኑም ምልክት በእኔና በምድር መካከል ይሆናል። በእኔና በእናንተ መካከል፣ ሕያው ነፍስ ባለውም ሥጋ ሁሉ መካከል ያለውን ቃል ኪዳኔን አስባለሁ፣ ሥጋ ያለውንም ሁሉ ያጠፋ ዘንድ ዳግመኛ የጥፋት ውኃ አይሆንም።” (ዘፍጥረት 9:13, 15) ታዲያ ዮሐንስ በሰማይ በራእይ የተመለከተው ነገር ምን ነገር ያስታወሰናል? የተመለከተው ቀስተ ደመና በአሁኑ ጊዜ የዮሐንስ ክፍል ከይሖዋ ጋር ያለውን የመሰለ ሰላማዊ ዝምድና ማበጀት አስፈላጊ መሆኑን ሳያስገነዝበው አልቀረም። በተጨማሪም ይሖዋ በሚገኝበት ሥፍራ ያለውን ጸጥታ፣ ሰላምና እርጋታ ያስገነዝበዋል። ይህም ሰላምና እርጋታ ይሖዋ በአዲሲቱ ምድር ማኅበረሰብ ላይ ድንኳኑን ሲዘረጋ በታዛዥ የሰው ልጆች ሁሉ ላይ ይሰፍናል።—መዝሙር 119:165፤ ፊልጵስዩስ 4:7፤ ራእይ 21:1-4

24ቱን ሽማግሌዎች ማንነት ማወቅ

8. ዮሐንስ በዙፋኑ ዙሪያ ምን ተመለከተ? እነዚህስ የምን ምሳሌ ናቸው?

8 ዮሐንስ በጥንቱ የመገናኛ ድንኳን ውስጥ ካህናት ተሹመው ያገለግሉ እንደነበር ያውቃል። በዚህም ምክንያት ቀጥሎ የሚገልጸውን ነገር በመመልከቱ ሳይደነቅ አይቀርም። “በዙፋኑ ዙሪያም ሀያ አራት ዙፋኖች ነበሩ፣ በዙፋኖቹም ላይ ነጭ ልብስ ለብሰው በራሳቸውም የወርቅ አክሊል ደፍተው ሀያ አራት ሽማግሌዎች ተቀምጠው ነበር።” (ራእይ 4:4) አዎን እዚህ ላይ ዮሐንስ በካህናት ምትክ እንደ ነገሥታት በዙፋን ላይ የተቀመጡና አክሊል የደፉ 24 ሽማግሌዎች ተመለከተ። እነዚህ ሽማግሌዎች እነማን ናቸው? ከሙታን ተነስተው ይሖዋ ቃል ገብቶላቸው የነበረውን ሰማያዊ ቦታ የተቀበሉ ቅቡዓን የክርስቲያን ጉባኤ አባሎች እንጂ ሌላ ሊሆኑ አይችሉም። ይህን እንዴት ልናውቅ እንችላለን?

9, 10. 24ቱ ሽማግሌዎች ሰማያዊ ክብርና ማዕረግ ያገኘውን የቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤ እንደሚያመለክቱ እንዴት ለማወቅ እንችላለን?

9 በመጀመሪያ ደረጃ አክሊል ወይም ዘውድ ደፍተዋል። ቅቡዓን ክርስቲያኖች ‘የማይጠፋ አክሊል’ እንደሚሰጣቸውና ሞት የማይደፍረው ዘላለማዊ ሕይወት እንደሚወርሱ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (1 ቆሮንቶስ 9:25፤ 15:53, 54) እነዚህ 24 ሽማግሌዎች በዙፋን ላይ የተቀመጡ ስለሆኑ በዚህ ጥቅስ ውስጥ የወርቁ አክሊል ንጉሥዊ ሥልጣንን ያመለክታል። (ከ⁠ራእይ 6:2፤ 14:14 ጋር አወዳድር።) ይህም 24ቱ ሽማግሌዎች ሰማያዊ ሥልጣን ያላቸውን ቅቡዓን የኢየሱስ ፈለግ ተከታዮች ያመለክታሉ የሚለውን መደምደሚያ ይደግፋል፤ ምክንያቱም ኢየሱስ ከእርሱ ጋር በመንግሥቱ ዙፋን ላይ እንደሚቀመጡ ቃል ገብቶላቸዋል። (ሉቃስ 22:28-30) ከኢየሱስና ከእነዚህ 24 ሽማግሌዎች በስተቀር መላእክት እንኳን በይሖዋ ፊት የንግሥና ሥልጣን እንደተሰጣቸው አልተነገረም።

10 ይህም ኢየሱስ ለሎዶቅያ ጉባኤ ከገባው ቃል ጋር ይስማማል። “ድል ለነሣው ከእኔ ጋር በዙፋኔ ላይ ይቀመጥ ዘንድ እሰጠዋለሁ።” (ራእይ 3:21) ይሁን እንጂ የ24ቱ ሽማግሌዎች ሰማያዊ ሹመት በመንግሥታዊ ግዛት ብቻ የተወሰነ አይደለም። በራእይ መጽሐፍ መግቢያ ላይ ዮሐንስ ስለ ኢየሱስ “መንግሥትም ለአምላኩና ለአባቱም ካህናት እንድንሆን ላደረገ” ብሎአል። (ራእይ 1:5, 6) እነዚህ ሽማግሌዎች ነገሥታትና ካህናት ናቸው። “የእግዚአብሔርና የክርስቶስ ካህናት ይሆናሉ፣ ከእርሱም ጋር ይህን ሺህ ዓመት ይነግሣሉ።”—ራእይ 20:6

11. የሽማግሌዎቹ ቁጥር 24 መሆኑ ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው? ይህስ ቁጥር ምን ያመለክታል?

11 ዮሐንስ በዙፋኑ ዙሪያ 24 ሽማግሌዎችን ተመልክቶአል። ይሁን እንጂ 24 ቁጥር ምን ልዩ ትርጉም አለው? በጥንትዋ እሥራኤል የነበሩ ታማኝ ካህናት ለእነዚህ ሽማግሌዎች በብዙ መንገድ ጥላ ሆነዋል። ሐዋርያው ጴጥሮስ ለቅቡዓን ክርስቲያኖች እንዲህ ሲል ጽፎአል:- “የተመረጠ ትውልድ፣ የንጉሥ ካህናት፣ ቅዱስ ሕዝብ፣ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ።” (1 ጴጥሮስ 2:9) የጥንቱ የአይሁዶች ክህነት በ24 ምድቦች ተከፍሎ ነበር። ቅዱሱ አገልግሎት ከዓመት እስከ ዓመት ሳይቋረጥ እንዲቀጥል እያንዳንዱ ክፍል የሚያገለግልበት ሣምንት እየተመደበለት በፈረቃ ያገለግሉ ነበር። (1 ዜና 24:5-19) ስለዚህ ዮሐንስ በራእይ የተመለከተው ሰማያዊ ክህነት በ24 ሽማግሌዎች መወከሉ ተገቢ ነበር፤ ምክንያቱም ይህ ክህነት ይሖዋን የሚያገለግለው ያለማቋረጥ ስለሆነ ነው። የእነዚህ ካህናት ቁጥር ሲሞላ እያንዳንዳቸው 6,000 ድል አድራጊዎች የሚኖሩባቸው 24 ምድቦች ይኖራሉ። ራእይ 14:1-4 እንደሚነግረን ከበጉ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በሰማያዊቱ ጽዮን እንዲቆሙ ‘ከሰው ልጆች መካከል የተዋጁት’ 144,000 (24 × 6,000) ናቸው። 12 ቁጥር ጥሩ ሚዛናዊነትን የጠበቀ መለኮታዊ ድርጅት ስለሚያመለክት 24 መሆኑ የዚህ ዝግጅት ጥንካሬ እጥፍ ወይም ከፍተኛ መሆኑን ያሳያል።

መብረቅ፣ ድምፅና ነጎድጓድ

12. ዮሐንስ ከዚህ ቀጥሎ ምን ነገር ተመለከተ? ምንስ ሰማ? ‘መብረቁ፣ ነጎድጓዱና ድምፁ’ ምን ነገር ያስታውሰናል?

12 ዮሐንስ ቀጥሎ የተመለከተውና የሰማው ነገር ምንድን ነው? “ከዙፋኑም መብረቅና ድምፅ ነጎድጓድም ይወጣል።” (ራእይ 4:5ሀ) የይሖዋ ሰማያዊ ኃይል ከሚገለጥባቸው አስደናቂ የሆኑ መንገዶች ጋር የሚስማማ ሌላ አስፈሪ መግለጫ ነበር። ለምሳሌ ያህል ይሖዋ በሲና ተራራ ላይ በወረደ ጊዜ የሆነውን ነገር ሙሴ እንዲህ ሲል ጽፎአል:- “በሦስተኛው ቀን በማለዳ ጊዜ ነጎድጓድ መብረቅ፣ ከባድም ደመና እጅግም የበረታ የቀንደ መለከት ድምፅ በተራራው ላይ ሆነ። . . . የቀንደ መለከቱም ድምፅ እጅግ በበረታና በጸና ጊዜ ሙሴ ተናገረ፣ እግዚአብሔርም በድምፅ መለሰለት።”—ዘጸአት 19:16-19

13. ከይሖዋ ዙፋን የሚወጣው መብረቅ ምን ያመለክታል?

13 ይሖዋ በጌታ ቀን ኃይሉንና መገኘቱን የገለጸው በከፍተኛ ሁኔታ ነበር። ዮሐንስ የተመለከተው ምልክቶችን ስለነበረ ይሖዋ የተገለጠው ቃል በቃል በእውነተኛ መብረቅ አልነበረም። ታዲያ መብረቁ የምን ምሳሌ ነው? የመብረቅ ብልጭታ ብርሃን ሊሰጥ ቢችልም ሰውንም ሊገድል ይችላል። ስለዚህ ይህ ከይሖዋ ዙፋን የወጣው መብረቅ የዕውቀትን ብርሃን፣ እንዲሁም እሳታማ የሆነውን የፍርድ መልእክቱን ያመለክታል።—ከ⁠መዝሙር 18:14፤ ከመዝሙር 144:5, 6፤ ከ⁠ማቴዎስ 4:14-17⁠ና ከማቴዎስ 24:27 ጋር አወዳድር።

14. በዘመናችን ድምፅ የተሰማው እንዴት ነው?

14 ድምፁስ የምን ምሳሌ ነው? ይሖዋ በሲና ተራራ ላይ በወረደበት ጊዜ አንድ ድምፅ ሙሴን አነጋግሮት ነበር። (ዘጸአት 19:19) በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙትን ትዕዛዞችና አዋጆች የተናገሩት ከሰማይ የወጡ ድምፆች ነበሩ። (ራእይ 4:1፤ 10:4, 8፤ 11:12፤ 12:10፤ 14:13፤ 16:1, 17፤ 18:4፤ 19:5፤ 21:3) በዛሬው ጊዜም ይሖዋ ለሕዝቦቹ ትዕዛዝና አዋጅ በመስጠት ለመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችና መሠረታዊ ሥርዓቶች ያላቸውን የመረዳት ችሎታ አብርቶላቸዋል። ብርሃን ሰጪ የሆኑ አዳዲስ እውቀቶች ብዙ ጊዜ በዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ላይ የተገለጹ ሲሆን በኋላም እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ታውጀዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ በታማኝነት ምሥራቹን ይሰብኩ ስለነበሩ ሰዎች ሲናገር እንዲህ ብሎ ነበር:- “በእውነት ድምፃቸው በምድር ሁሉ ላይ ቃላቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ወጣ።”—ሮሜ 10:18

15. በዚህ የጌታ ቀን ክፍል ከይሖዋ ዙፋን የወጣው እንዴት ያለ የነጎድጓድ ድምፅ ነው?

15 ብዙውን ጊዜ ከብልጭታ በኋላ ነጎድጓድ ይከተላል። ዳዊት ነጎድጓድ ‘የይሖዋ ድምፅ እንደሆነ’ ተናግሮአል። (መዝሙር 29:3, 4 NW) ይሖዋ ለዳዊት ቆሞ ከጠላቶቹ ጋር በተዋጋለት ጊዜ ከይሖዋ ዘንድ ነጎድጓድ እንደወጣ ተነግሮ ነበር። (2 ሳሙኤል 22:14፤ መዝሙር 18:13) ይሖዋ “እኛም የማናስተውለውን ታላቅ ነገር” በሚያደርግበት ጊዜ ድምፁ እንደ ነጎድጓድ እንደሚሰማ ኤሊሁ ለኢዮብ ነግሮታል። (ኢዮብ 37:4, 5) በዚህ በአሁኑ የጌታ ቀን ክፍል ውስጥ ይሖዋ በጠላቶቹ ላይ ስለሚያደርጋቸው ታላላቅ ነገሮች በማስጠንቀቅ እንደ ነጎድጓድ ያለ ድምፅ አሰምቶአል። ይህ ምሳሌያዊ የነጎድጓድ ድምፅ በምድር ዙሪያ አስተጋብቶአል። ይህን ነጎድጓዳማ አዋጅ ሰምተህና የራስህንም ድምፅ በመጨመር ይበልጥ እንዲያስተጋባ ረድተህ ከሆነ በጣም ደስተኛ ነህ።—ኢሳይያስ 50:4, 5፤ 61:1, 2

የእሳት መብራቶችና የብርጭቆ ባሕር

16. ‘ሰባቱ የእሳት መቅረዞች’ ምን ያመለክታሉ?

16 ዮሐንስ ቀጥሎ ምን ተመለከተ? የሚከተለውን ተመልክቶአል:- “በዙፋኑም ፊት ሰባት የእሳት መብራቶች ይበሩ ነበር እነርሱም ሰባቱ የእግዚአብሔር መናፍስት ናቸው። በዙፋኑም ፊት ብርሌ የሚመስል የብርጭቆ ባሕር ነበረ።” (ራእይ 4:5ለ, 6ሀ) የሰባቱን መብራቶች ትርጉም ዮሐንስ ራሱ “እነርሱም ሰባቱ የእግዚአብሔር መናፍስት ናቸው” በማለት ነግሮናል። ሰባት ቁጥር የሚያመለክተው መለኮታዊ ሙላትን ነው። ስለዚህ ሰባቱ መብራቶች መንፈስ ቅዱስ የእውቀት ብርሃን ሲሰጥ በሙሉ ኃይል መሥራቱን ያመለክታሉ። የዮሐንስ ክፍል ይህ የእውቀት ብርሃን የተሰጠው ብርሃኑን ለምድር መንፈሳዊ ረሀብተኞች ከማስተላለፍ መብት ጋር ስለሆነ በጣም አመስጋኝ ነው። በየዓመቱ በመቶ ሚልዮን የሚቆጠሩ የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት ቅጂዎች 150 በሚያህሉ ቋንቋዎች ይህን ብርሃን ስለሚያንጸባርቁ ምንኛ አመስጋኞች መሆን ይገባናል!—መዝሙር 43:3

17. ‘ብርሌ የሚመስለው የብርጭቆ ባሕር’ የምን ምሳሌ ነው?

17 በተጨማሪም ዮሐንስ “ብርሌ የሚመስል የብርጭቆ ባሕር” ተመልክቶ ነበር። ይህስ ወደ ይሖዋ ሰማያዊ ቤተ መንግሥት ለሚጋበዙት ምን ምሳሌነት ይኖረዋል? ጳውሎስ፣ ኢየሱስ ጉባኤውን የቀደሰው እንዴት እንደሆነ ሲገልጽ ‘በውኃ መታጠብና ከቃሉ ጋር አንጽቶ ቀደሳት’ በማለት ተናግሯል። (ኤፌሶን 5:25, 26) ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት ለደቀ መዛሙርቱ “እናንተ ስለነገርኋችሁ ቃል አሁን ንጹሐን ናችሁ” ብሎ ነበር። (ዮሐንስ 15:3) ስለዚህ ይህ እንደ ብርሌ የጠራው የመስተዋት ባሕር የሚያነጻውን በጽሑፍ ተመዝግቦ የሚገኝ የአምላክ ቃል የሚያመለክት መሆን ይኖርበታል። ይሖዋ ወደሚገኝበት ሥፍራ የመጡት እነዚህ ንጉሣዊ ካህናት በቃሉ የነጹና የጠሩ መሆን ነበረባቸው!

እነሆ፣ “አራት እንስሶች”!

18. ዮሐንስ በዙፋኑ መካከልና በዙፋኑ ዙሪያ ምን ነገር ተመለከተ?

18 አሁን ደግሞ ዮሐንስ ሌላ ነገር ተመለከተ። እንዲህ ሲል ጻፈ:- “በዙፋኑም መካከል በዙፋኑም ዙሪያ በፊትና በኋላ ዓይኖች የሞሉአቸው አራት እንስሶች [“ሕያዋን ፍጥረታት፣” NW] ነበሩ።” —ራእይ 4:6ለ

19. አራቱ እንስሳት ወይም ሕያዋን ፍጥረታት የምን ምሳሌዎች ናቸው? ይህንንስ እንዴት እናውቃለን?

19 እነዚህ እንስሶች ወይም ሕያዋን ፍጥረታት የምን ምሳሌ ናቸው? ሕዝቅኤል የተባለው ሌላ ነቢይ የገለጸው ነገር የዚህን ጥያቄ መልስ ለማወቅ ይረዳናል። ሕዝቅኤል ይሖዋን በሕያዋን ፍጥረታት በታጀበ ሰማያዊ ሰረገላ ላይ ተቀምጦ ተመልክቶ ነበር። (ሕዝቅኤል 1:5-11, 22-28) ሕዝቅኤል በሌላም ጊዜ ይህን በሕያዋን ፍጥረታት የታጀበውን የሠረገላ ዙፋን በድጋሚ ተመልክቶ ነበር። በዚህ ጊዜ ግን ሕያዋን ፍጥረቶቹ ኪሩቤሎች እንደሆኑ ተናግሮአል። (ሕዝቅኤል 10:9-15) ዮሐንስ የተመለከታቸው አራት እንስሳት ወይም ሕያዋን ፍጥረታት በይሖዋ መንፈሳዊ ድርጅት ውስጥ ከፍተኛ ማዕረግ ያላቸውን የአምላክ ብዙ ኪሩቤሎች የሚያመለክቱ መሆን ይኖርባቸዋል። በጥንቱ የመገናኛ ድንኳን ውስጥ የይሖዋ ዙፋን ምሳሌ በሆነው በቃል ኪዳኑ ታቦት መክደኛ ላይ ሁለት የወርቅ ኪሩቤሎች ይታዩ ስለነበር ዮሐንስ ኪሩቤሎች ከይሖዋ ጋር በጣም ተቀራርበው መመልከቱ እንግዳ ነገር አልሆነበትም። የይሖዋ ቃል የእሥራኤልን ሕዝብ ለማዘዝ የሚወጣው ከእነዚህ ኪሩቤሎች መሃል ነበር።—ዘጸአት 25:22፤ መዝሙር 80:1

20. አራቱ ሕያዋን ፍጥረታት “በዙፋኑም መካከል በዙፋኑም ዙሪያ ነበሩ” ሊባል የሚቻለው እንዴት ነው?

20 እነዚህ አራት እንስሳት ወይም ሕያዋን ፍጥረታት “በዙፋኑም መካከል በዙፋኑም ዙሪያ” የቆሙ ነበሩ። ይህ በእርግጥ ምን ማለት ነው? እያንዳንዳቸው በዙፋኑ ዙሪያ በእያንዳንዱ ጎን አጋማሽ ላይ በአራት አቅጣጫ እንደቆሙ ሊያመለክት ይችላል። በዚህም ምክንያት የቱዴይስ ኢንግሊሽ ቨርሽን ተርጓሚዎች የጥንቱን የግሪክኛ አነጋገር “ዙፋኑን በእያንዳንዱ ጎን ከብበውት ነበር” ብለው ተርጉመውታል። በሌላ በኩልም አነጋገሩ አራቱ እንስሳት ዙፋኑ በሚገኝበት በሰማይ ማዕከላዊ ቦታ ላይ እንደሚገኙ ሊያመለክት ይችላል። ዘ ጀሩሳሌም ባይብል ይህን ሐረግ ሲተረጉም “በዙፋኑ ዙሪያ በመካከል ላይ ቆመው ነበር” ያለው በዚህ ምክንያት ይሆናል። ያም ሆነ ይህ አስፈላጊው ነገር ኪሩቤሎቹ ሕዝቅኤል በይሖዋ ድርጅታዊ ሠረገላ አራት ማዕዘን ላይ ቆመው ከተመለከታቸው ኪሩቤሎች ጋር ሲወዳደር ለይሖዋ ዙፋን የነበራቸው ቅርበት ነው። (ሕዝቅኤል 1:15-22) ይህ ሁሉ ከ⁠መዝሙር 99:1 ቃል ጋር የሚስማማ ነው። “እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ነገሠ፣ . . . በኪሩቤል ላይ ተቀመጠ” ይላል።

21, 22. (ሀ) ዮሐንስ አራቱን እንስሳት ወይም ሕያዋን ፍጥረታት የገለጸው እንዴት ነው? (ለ) የእያንዳንዱ ሕያው ፍጥረት መልክ የምን ምሳሌ ሆኖአል?

21 ዮሐንስ የሚከተለውን በመናገር ይቀጥላል:- “ፊተኛውም እንስሳ አንበሳን ይመስላል፣ ሁለተኛውም እንስሳ ጥጃን ይመስላል፣ ሦስተኛውም እንስሳ እንደ ሰው ፊት ነበረው፣ አራተኛውም እንስሳ የሚበረውን ንስር ይመስላል።” (ራእይ 4:7) እነዚህ አራት እንስሶች በመልካቸው ይህን ያህል አንዳቸው ከሌላው የተለያዩ የሆኑት ለምንድን ነው? እነዚህ የተለያዩ እንስሳት የተለያዩ አምላካዊ ባሕርያትን የሚወክሉ ስለሆኑ ነው። የመጀመሪያው እንስሳ አንበሳ ነበር። አንበሳ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተለይ ፍትሕንና ጽድቅን በማስፈጸም ረገድ የድፍረት ምሳሌ ነው። (2 ሳሙኤል 17:10፤ ምሳሌ 28:1) ስለዚህ አንበሳው ድፍረት የተሞላበትን የፍትሕ ባሕርይ ማመልከቱ ተገቢ ነው። (ዘዳግም 32:4፤ መዝሙር 89:14) ሁለተኛው እንስሳ ጥጃ ወይም ወይፈን ይመስላል። ወይፈን እንዴት ያለ ባሕርይ ያስታውሳችኋል? ወይፈን ለእሥራኤላውያን በጣም የተወደደ ንብረት ሊሆን የቻለው ባለው ኃይል ምክንያት ነበር። (ምሳሌ 14:4፤ በተጨማሪም ኢዮብ 39:9-11 ተመልከት።) ስለዚህ ወይፈኑ ከይሖዋ የሚሰጠውን ታላቅ ኃይል ወይም ጉልበት ያመለክታል።—መዝሙር 62:11፤ ኢሳይያስ 40:26

22 ሦስተኛው እንስሳ እንደ ሰው ያለ ፊት ነበረው። በምድር ላይ ታላቁ የፍቅር ባሕርይ ኖሮት በአምላክ ምሳሌ የተፈጠረው ፍጡር ሰው ብቻ ስለሆነ ይህ እንስሳ አምላካዊ ፍቅርን የሚያመለክት መሆን ይኖርበታል። (ዘፍጥረት 1:26-28፤ ማቴዎስ 22:36-40፤ 1 ዮሐንስ 4:8, 16) አለጥርጥር ኪሩቤሎቹ በይሖዋ ዙፋን ዙሪያ ሲያገለግሉ ይህን ባሕርይ ያሳያሉ። አራተኛውስ እንስሳ ምን ያመለክታል? ይህ እንስሳ የበራሪ ንሥር መልክ ነበረው። ስለ ንሥር አርቆ ተመልካችነት ይሖዋ ራሱ ተናግሮአል። “ዓይኑም በሩቅ ትመለከታለች” ብሎአል። (ኢዮብ 39:29) ስለዚህ ንሥር አርቆ ተመልካችነትን የሚያሳየውን ጥበብ ማመልከቱ ተገቢ ነው። ይሖዋ የጥበብ ሁሉ ምንጭ ነው። ኪሩቤሎቹም የእርሱን ትዕዛዞች በሚፈጽሙበት ጊዜ መለኮታዊውን ጥበብ ያሳያሉ።—ምሳሌ 2:6፤ ያዕቆብ 3:17

የይሖዋ ውዳሴ በሚያስተጋባ ድምፅ ተሰማ

23. አራቱ ሕያዋን ፍጥረታት በዓይን የተሞሉ መሆናቸው ምን ያመለክታል? ሦስት ጥንድ ክንፎች ያሉአቸው መሆናቸውስ ምን ነገርን አጥብቆ ይገልጻል?

23 ዮሐንስ መግለጫውን ይቀጥላል:- “አራቱም እንስሶች እያንዳንዳቸው ስድስት ክንፎች አሉአቸው፣ በዙሪያቸውና በውስጣቸውም ዓይኖች ሞልተውባቸዋል ‘ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ የነበረውና ያለው የሚመጣውም ሁሉንም የሚገዛ ጌታ [“ይሖዋ፣” NW] አምላክ’ እያሉ ቀንና ሌሊት አያርፉም።” (ራእይ 4:8) ዓይኖች የሞሉባቸው መሆናቸው አስተዋዮችና አርቆ ተመልካቾች መሆናቸውን ያመለክታል። አራቱ እንስሳት እንቅልፍ መተኛት ስለማያስፈልጋቸው በዚህ የአርቆ ተመልካችነት ችሎታቸው የማይጠቀሙበት ጊዜ የለም። “እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ልቡ በእርሱ ዘንድ ፍጹም የሆነውን ያጸና ዘንድ ዓይኖቹ በምድር ሁሉ ይመለከታሉ” የተባለለትን አምላክ ይመስላሉ። (2 ዜና 16:9) ኪሩቤሎች ይህን የሚያክሉ ብዙ ዓይኖች ስላሉአቸው በየትም ሥፍራ ያለውን ሊመለከቱ ይችላሉ። ከእይታቸው የሚያመልጥ ምንም ነገር የለም። ስለዚህ አምላክን በፍርድ ሥራው ለማገልገል የሚያስችል የተሟላ ብቃት አላቸው። አምላክን በተመለከተ “የእግዚአብሔር [“የይሖዋ፣” NW] ዓይኖች በስፍራ ሁሉ ናቸው ክፉዎችንና ደጎችን ይመለከታሉ” ተብሎአል። (ምሳሌ 15:3) ኪሩቤሎቹ ሦስት ጥንድ ክንፎች ስላሉአቸውና ሦስት ቁጥርም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ማጉላትን ወይም ማጥበቅን ስለሚያመለክት ኪሩቤሎች የይሖዋን ፍርድ ለማወጅና ለማስፈጸም በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ እንደ መብረቅ ባለ ከፍተኛ ፍጥነት ለመጓዝ ይችላሉ።

24. ኪሩቤሎች ይሖዋን የሚያወድሱት እንዴት ነው? ይህስ ምን ትርጉም አለው?

24 አሁን አድምጡ! ኪሩቤሎች ለይሖዋ የሚያቀርቡት የውዳሴ መዝሙር ልብን የሚመስጥ ጣዕም ያለው ዜማ ነው። እነርሱም “ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ የነበረውና ያለው የሚመጣውም ሁሉንም የሚገዛ ጌታ [“ይሖዋ።” NW] አምላክ” አሉ። አሁንም ቃሉ ሦስት ጊዜ መደጋገሙ የነገሩን ጥብቀት ያመለክታል። ኪሩቤሎቹ የይሖዋ አምላክን ቅድስና አጠንክረው ገልጸዋል። ከፍተኛውን የቅድስና ደረጃ የያዘውና የቅድስና መለኪያ የሆነው ይሖዋ አምላክ ነው። በተጨማሪም እርሱ “የዘላለም ንጉሥ” ነው። “አልፋና ኦሜጋ፣ የመጀመሪያውና የመጨረሻው፣ ፊተኛውና ኋለኛው” እርሱ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 1:17፤ ራእይ 22:13) ኪሩቤሎች የይሖዋን ወደር የለሽ ባሕርያት በፍጥረት ሁሉ ፊት በሚያውጁበት ጊዜ ትንሽ እንኳን አረፍ እንበል አይሉም።

25. ሕያዋን ፍጥረታቱና 24ቱ ሽማግሌዎች ይሖዋን በማክበርና በማወደስ የተባበሩት እንዴት ነው?

25 ሰማየ ሰማያት በይሖዋ ውዳሴ አስተጋባ! ዮሐንስ ገለጻውን ቀጠለ:- “እንስሶቹም በዙፋን ላይ ለተቀመጠው ከዘላለምም እስከ ዘላለም በሕይወት ለሚኖረው ለእርሱ ክብርና ውዳሴ ምስጋናም በሰጡት ጊዜ፣ ሀያ አራቱ ሽማግሌዎች በዙፋን ላይ በተቀመጠው ፊት ወድቀው ከዘላለም እስከ ዘላለም በሕይወት ለሚኖረው እየሰገዱ:- ‘ጌታችን [“ይሖዋ፣” NW] አምላካችን ሆይ:- አንተ ሁሉን ፈጥረሃልና ስለፈቃድህም ሆነዋልና ተፈጥረውማልና ክብር ውዳሴ ኃይልም ልትቀበል ይገባሃል’ እያሉ በዙፋኑ ፊት አክሊላቸውን ያኖራሉ።” (ራእይ 4:9-11) በቅዱሳን ጽሑፎች በሙሉ ለአምላካችን፣ ለሉዓላዊው ጌታ ለይሖዋ ታላቅ የአክብሮት ውዳሴ ከቀረበባቸው ጊዜያት አንዱ ይህ ነው።

26. 24ቱ ሽማግሌዎች አክሊላቸውን በይሖዋ ፊት አውልቀው ያስቀመጡት ለምንድን ነው?

26 24ቱ ሽማግሌዎች ኢየሱስ ያለው ዓይነት አስተሳሰብ ስላላቸው በይሖዋ ፊት አክሊላቸውን አውልቀው አኑረዋል። በአምላክ ፊት ራሳቸውን ከፍ ከፍ ማድረግ ፈጽሞ ሊያስቡ የማይችሉት ነገር ነው። ንጉሥ የሆኑበት ዓላማ ኢየሱስ ዘወትር እንደሚያደርገው ለይሖዋ ክብርና ምሥጋና ለማምጣት ብቻ ነው። (ፊልጵስዩስ 2:5, 6, 9-11) ራሳቸውን በማዋረድ ዝቅተኛ መሆናቸውን አምነው ይቀበላሉ። ገዥነታቸውም በይሖዋ ሉዓላዊነት ላይ የተመካ መሆኑን ይናገራሉ። በዚህ መንገድ ሁሉን ነገር ለፈጠረው አምላክ ክብርና ውዳሴ በመስጠት ረገድ ከኪሩቤሎችና ከሌሎች ታማኝ ፍጥረታት ጋር በአንድ ልብ ይስማማሉ።—መዝሙር 150:1-6

27, 28. (ሀ) ዮሐንስ ስለተመለከተው ራእይ የሰጠን መግለጫ እንዴት ሊነካን ይገባል? (ለ) ዮሐንስ ከዚህ ቀጥሎ ስለሚመለከተውና ስለሚሰማው ነገር ምን ጥያቄ ይነሳል

27 ዮሐንስ ስለተመለከተው ራእይ የጻፈውን ይህን ቃል ካነበበ በኋላ ልቡ የማይቀሰቀስበት እንዴት ያለ ሰው ነው? በጣም የሚያስደንቅ ውብ ትዕይንት ነው! ምሳሌው ይህን የሚመስል ከሆነ እውነተኛው የይሖዋ ዙፋን ምን ይመስል ይሆን? የይሖዋ ክብርና ግርማ ማንኛውም አድናቂ ልብ ያለው ሰው ከአራቱ እንስሳትና ከ24ቱ ሽማግሌዎች ጋር በመተባበር በጸሎትና ስሙን ለሕዝብ በማወጅ ይሖዋን እንዲያወድስ ሊገፋፋው ይገባል። ክርስቲያኖች በዛሬው ጊዜ ምሥክሮች የመሆን መብት ያገኙት እንዲህ ላለው ታላቅ አምላክ ነው። (ኢሳይያስ 43:10) የዮሐንስ ራእይ የሚሠራው አሁን እኛ በምንኖርበት የጌታ ቀን ውስጥ እንደሆነ እናስታውስ። “ሰባቱ መናፍስት” እኛን ለመምራትና ለማጠንከር ዝግጁ ሆነው በመጠባበቅ ላይ ናቸው። (ገላትያ 5:16-18) ዛሬ ቅዱሳን ሆነን ቅዱሱን አምላክ እንድናገለግል የሚረዳን የአምላክ ቃል አለልን። (1 ጴጥሮስ 1:14-16) በእውነትም የዚህን ትንቢት ቃል በማንበባችን ደስተኞች ነን። (ራእይ 1:3) ይህ የትንቢት ቃል ለይሖዋ ታማኞች እንድንሆንና ዓለም የይሖዋን ውዳሴ ከመዘመር እንቅፋት እንዲሆንብን እንዳንፈቅድ የሚገፋፋን እንዴት ያለ ብርቱ ኃይል ነው!—1 ዮሐንስ 2:15-17

28 እስከ አሁን ድረስ ዮሐንስ የገለጸልን በተከፈተው በር እንዲገባ በተጋበዘበት ጊዜ በሰማይ ላይ የተመለከተውን ነገር ነበር። ከሁሉ የበለጠ ግምት የሚሰጠው ግን ይሖዋ ሙሉ ግርማውንና ክብሩን ተጎናጽፎ በሰማያዊ ዙፋኑ ላይ እንደተቀመጠ መግለጹ ነው። ከድርጅቶች ሁሉ የበለጠ ኃይል ባለው ድርጅት ታጅቧል። ይህም ድርጅት ታላቅ ውበት፣ ግርማና ታማኝነት ተላብሶአል። መለኮታዊው ችሎት ተሰይሞአል። (ዳንኤል 7:9, 10, 18) አንድ ትልቅ ነገር ሊፈጸም መንገዱ ተጠርጎአል። ይህ የሚፈጽመው ነገር ምንድን ነው? እኛንስ እንዴት ይነካናል? ትዕይንቱ ሲገለጽ እንመልከት!

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ  75 ላይ የሚገኝ ባለ ሙሉ ገጽ ሥዕል]

[በገጽ  78 ላይ የሚገኝ ባለ ሙሉ ገጽ ሥዕል]