በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጣፋጭና መራራ የሆነ መልእክት

ጣፋጭና መራራ የሆነ መልእክት

ምዕራፍ 24

ጣፋጭና መራራ የሆነ መልእክት

ራእይ 6--ራእይ 10:1 እስከ 11:19

ርዕሰ ጉዳይ:- የትንሹ የመጽሐፍ ጥቅልል ራእይ፤ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ያጋጠሙ ሁኔታዎች፤ የሰባተኛው መለከት መነፋት

ራእዩ የሚፈጸምበት ጊዜ:- ኢየሱስ ከነገሠበት ከ1914 ጀምሮ እስከ ታላቁ መከራ

1, 2. (ሀ) ሁለተኛው ወዮታ ምን ውጤት አስከትሎአል? ይህ ወዮታ አልቋል የሚባለው መቼ ነው? (ለ) አሁን ዮሐንስ ከሰማይ ሲወርድ የተመለከተው ምንድን ነው?

ሁለተኛው ወዮታ ታላቅ ጥፋት አስከትሎ ነበር። “የሰዎች ሲሶ” በሆነችው ሕዝበ ክርስትናና በመሪዎችዋ ላይ መቅሰፍት ሆኖ ነበር። በመንፈሳዊ ሙታን መሆናቸውም ተጋልጦአል። (ራእይ 9:15) ይህ ሁሉ ከተፈጸመ በኋላ ሦስተኛው ወዮታ ምን ሊያመጣ እንደሚችል ዮሐንስን ሳያስገርመው አይቀርም። ይሁን እንጂ ጥቂት እንጠብቅ። ሁለተኛው ወዮታ ራእይ 11:14 ላይ የተገለጸው ሁኔታ ላይ እስክንደርስ ድረስ አይፈጸምም። ከዚያ በፊት ዮሐንስ ራሱ ተሳታፊ የሚሆንበት ነገር ሲፈጸም ይመለከታል። ራእዩ በጣም አስፈሪ በሆነ ትዕይንት ይጀምራል።

2 “ሌላም ብርቱ መልአክ ደመና ተጎናጽፎ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ፤ በራሱም ላይ ቀስተ ደመና ነበረ፣ ፊቱም እንደ ፀሐይ እግሮቹም እንደ እሳት ዓምዶች ነበሩ።”—ራእይ 10:1

3. (ሀ) ‘ብርቱው መልአክ’ ማን ነው? (ለ) በራሱ ላይ ቀስተ ደመና መታየቱ ምን ትርጉም አለው?

3 ይህ “ብርቱ መልአክ” ማን ነው? ከሌላ የሥራ ምድብ አንፃር የታየው ከፍ ያለ ክብር የተቀዳጀው ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ ግልጽ ነው። እርሱም ደመና ተጎናጽፎ ስለነበረ ሊታይ አይችልም ነበር። ይህም ዮሐንስ ቀደም ብሎ ስለ ኢየሱስ የተናገረውን ቃል ያስታውሰናል። “እነሆ ከደመና ጋር ይመጣል፣ ዓይንም ሁሉ የወጉትም ያዩታል” ብሎ ነበር። (ራእይ 1:7፤ ከ⁠ማቴዎስ 17:2-5 ጋር አወዳድር።) በራሱ ላይ ያለው ቀስተ ደመና ዮሐንስ ቀደም ሲል በይሖዋ ዙፋን ዙሪያ የተመለከተውን “በመልኩም መረግድን የመሰለውን ቀስተ ደመና” ያስታውሰናል። (ራእይ 4:3፤ ከ⁠ሕዝቅኤል 1:28 ጋር አወዳድር።) ይህ ቀስተ ደመና በአምላክ ዙፋን ዙሪያ ያለውን ሰላምና እርጋታ ያመለክታል። በተመሳሳይም በመልአኩ ራስ ላይ ያለው ቀስተ ደመና ልዩ የሰላም መልእክተኛ፣ በትንቢት የተነገረለት የይሖዋ “የሰላም መስፍን” መሆኑን ያመለክታል።—ኢሳይያስ 9:6, 7

4. የብርቱው መልአክ ፊት (ሀ) ‘እንደ ፀሐይ ሆኖ’ መታየቱ (ለ) የመልአኩ እግሮች ‘እንደ እሳት ዓምድ’ መሆናቸው ምን ያመለክታል?

4 የብርቱው መልአክ ፊት “እንደ ፀሐይ” ነበረ። ዮሐንስ ቀደም ሲል ኢየሱስን በመለኮታዊው ቤተ መቅደስ በተመለከተበት ጊዜ ፊቱ “በኃይል እንደሚበራ እንደ ፀሐይ ነበረ።” (ራእይ 1:16) ኢየሱስ “የጽድቅ ፀሐይ” እንደመሆኑ መጠን በክንፎቹ ፈውስ ይዞ የይሖዋን ስም ለሚፈሩ ሁሉ ያበራላቸዋል። (ሚልክያስ 4:2) የዚህ መልአክ ፊት ብቻ ሳይሆን እግሮቹም ጭምር ታላቅ ክብር ነበራቸው። “የእሳት ዓምድ” ይመስሉ ነበር። ጠንካራ ቁመናው ይሖዋ ‘ሥልጣን በሰማይና በምድር ለሰጠው’ ለኢየሱስ የሚገባ ነው።—ማቴዎስ 28:18፤ ራእይ 1:14, 15

5. ዮሐንስ በብርቱው መልአክ እጅ ውስጥ ምን ተመልክቶአል?

5 ዮሐንስ አሁንም በመቀጠል የሚከተለውን ተመልክቶአል:- “የተከፈተችንም ታናሽ መጽሐፍ በእጁ ያዘ። ቀኝ እግሩንም በባሕር ላይ ግራውንም በምድር ላይ አኖረ።” (ራእይ 10:2) አሁንም ሌላ ጥቅልል ተመለከተ። ይኸኛው ጥቅልል ግን የታሸገ ወይም የታተመ አልነበረም። ብዙም ሳንቆይ ከዮሐንስ ጋር በጣም አስደናቂ የሆኑ መግለጫዎችን ለመመልከት እንችላለን። ከዚያ በፊት ግን የሚከተለውን መቅድም እንመለከታለን።

6. (ሀ) የኢየሱስ እግሮች በምድርና በባሕር ላይ መርገጣቸው ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) መዝሙር 8:5-8 ሙሉ በሙሉ የተፈጸመው መቼ ነበር?

6 ስለ ኢየሱስ ወደተሰጠው መግለጫ እንመለስ። እግሮቹ ሙሉ በሙሉ በሥልጣኑ በሚቆጣጠራቸው ምድርና በባሕር ላይ አርፈዋል። ይህም በትንቢታዊው መዝሙር እንደተገለጸው ሆኖአል። “ከመላእክት እጅግ ጥቂት [ኢየሱስን] አሳነስኸው፣ በክብርና በምስጋና ዘውድ ከለልኸው። በእጆችህም ሥራ ሁሉ ላይ ሾምኸው፣ ሁሉን ከእግሮቹ በታች አስገዛህለት፣ በጎችንም ላሞችን ሁሉ ደግሞም የምድረ በዳውን እንስሶች የሰማይንም ወፎች የባሕርንም ዓሦች በባሕር መንገድ የሚሄደውንም ሁሉ።” (መዝሙር 8:5-8፤ በተጨማሪም ዕብራውያን 2:5-9ን ተመልከት።) ይህ መዝሙር ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ በነገሰበትና የመጨረሻው ዘመን በጀመረበት በ1914 ሙሉ በሙሉ ተፈጽሞአል። ስለዚህ ዮሐንስ በራእይ የተመለከተው ነገር ፍጻሜውን ያገኘው ከ1914 ጀምሮ ነው።—መዝሙር 110:1-6፤ ሥራ 2:34-36፤ ዳንኤል 12:4

ሰባቱ ነጎድጓዶች

7. ብርቱው መልአክ የጮኸው እንዴት ነው? የጩኸቱስ ትርጉም ምንድን ነው?

7 ዮሐንስ ስለዚህ ብርቱ መልአክ ሲያሰላስል ይኸው መልአክ አቋረጠውና “እንደሚያገሣም አንበሳ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። በጮኸም ጊዜ ሰባቱ ነጎድጓድ በየድምፃቸው ተናገሩ።” (ራእይ 10:3) እንዲህ ያለው ከፍተኛ ጩኸት የዮሐንስን ትኩረት እንደሚስብ የታወቀ ነው። ኢየሱስ “የይሁዳ ነገድ አንበሳ” መሆኑን ያረጋግጣል። (ራእይ 5:5) በተጨማሪም ይሖዋም አንዳንድ ጊዜ እንደ አንበሳ እንዳገሳ የተነገረበት ጊዜ እንዳለ ዮሐንስ ሳይገነዘብ አልቀረም። ይሖዋ እንደ አንበሳ ማግሳቱ የመንፈሳዊ እስራኤልን መሰብሰብና አጥፊ የሆነውን “የይሖዋ ቀን” መምጣት በትንቢት የሚያበስር ነበር። (ሆሴዕ 11:10፤ ኢዩኤል 3:14, 16፤ አሞጽ 1:2፤ 3:7, 8) ስለዚህ የዚህ ብርቱ መልአክ ግሣት በምድርና በሰማይ ላይ ተመሳሳይ የሆነ ታላቅ ነገር እንደሚፈጸም ያበስራል። ሰባቱ ነጎድጓድ ለሚናገሩት ነገር መክፈቻ ሆኖአል።

8. ‘የሰባቱ ነጎድጓዶች ድምፅ’ ምንድን ነው?

8 ዮሐንስ ቀደም ሲል ከይሖዋ ዙፋን ነጎድጓድ ሲወጣ ሰምቶ ነበር። (ራእይ 4:5) ጥንት በዳዊት ዘመን እውነተኛው ነጎድጓድ አንዳንድ ጊዜ “የይሖዋ ድምፅ” እንደሆነ ተነግሮ ነበር። (መዝሙር 29:3 NW) በኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎት ጊዜ ይሖዋ የራሱን ስም ለማክበር ዓላማ እንዳለው በአሳወቀ ጊዜ ድምፁ ለብዙዎች እንደ ነጎድጓድ ሆኖ ተሰምቶአቸው ነበር። (ዮሐንስ 12:28, 29) ስለዚህ ‘የሰባቱ ነጎድጓድ ድምፅ’ የይሖዋ ዓላማ መግለጫዎች ናቸው ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ነው። ነጎድጓዶቹ “ሰባት” መሆናቸው ዮሐንስ የሰማው ነገር ሙሉና ጉድለት የሌለው መሆኑን ያመለክታል።

9. ከሰማይ የመጣ ድምፅ ምን ትዕዛዝ ሰጠ?

9 አሁን እናዳምጥ! ሌላ ድምፅ ይሰማል። ለዮሐንስ እንግዳ ሊሆንበት የሚችል ትዕዛዝ የሚሰጥ ድምፅ ነው። “ሰባቱ ነጎድጓድ በተናገሩ ጊዜ ልጽፍ አሰብሁ፤ ከሰማይም:- ሰባቱ ነጎድጓድ የተናገሩትን ነገር በማኅተም ዝጋው፣ አትጻፈውም የሚል ድምፅ ሰማሁ።” (ራእይ 10:4) ዮሐንስ የነጎድጓዶቹን መልእክት ለመስማትና መዝግቦ ለማቆየት ጓጉቶ ነበር። በዛሬው ጊዜም የዮሐንስ ክፍል ይሖዋ መለኮታዊ ዓላማውን እንዲገልጽለትና ጽሑፍ አውጥቶ ለሰዎች ለማሳወቅ እንዲችል በጣም ጓጉቶ ነበር። ይሁን እንጂ ይሖዋ ዓላማውን የሚገልጠው ራሱ በወሰነው ጊዜ ብቻ ነው።—ሉቃስ 12:42፤ በተጨማሪም ዳንኤል 12:8, 9ን ተመልከት።

የቅዱሱ ምሥጢር መፈጸም

10. ብርቱው መልአክ የማለው በማን ነው? ምንስ አስታወቀ?

10 ከዚያ በፊት ግን ይሖዋ ዮሐንስ እንዲፈጽም ያዘጋጀለት ሥራ ነበር። ሰባቱ ነጎድጓዶች ከተሰሙ በኋላ ብርቱው መልአክ እንደገና መናገር ጀመረ። “በባሕርና በምድርም ላይ ሲቆም ያየሁት መልአክ ቀኝ እጁን ወደ ሰማይ አሻቅቦ ዘረጋ፣ ሰማይንና በእርሱም ያሉትን ምድርንና በእርስዋም ያሉትን፣ ባሕርንና በእርሱም ያሉትን በፈጠረው፣ ከዘላለምም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ሆኖ በሚኖረው ምሎ ወደ ፊት አይዘገይም” አለ። (ራእይ 10:5, 6) ብርቱው መልአክ የማለው በማን ነው? ከፍ ያለ ክብር የተቀዳጀው ኢየሱስ የማለው በራሱ ሳይሆን የሁሉ የበላይ በሆነው ባለሥልጣን፣ በማይሞተው የሰማያትና የምድር ፈጣሪ በይሖዋ ነው። (ኢሳይያስ 45:12, 18) መልአኩ በዚህ መሐላው አምላክ እንደማይዘገይ አረጋግጦአል።

11, 12. (ሀ) “ከእንግዲህ ወዲህ አይዘገይም” የሚለው አነጋገር ምን ትርጉም አለው? (ለ) ወደ ፍጻሜ የመጣው ነገር ምንድን ነው?

11 እዚህ ላይ “መዘግየት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ክሮኖስ ቃል በቃል ሲተረጎም “ጊዜ” ማለት ነው። በዚህም ምክንያት አንዳንዶች የመልአኩ ቃል ጊዜ ማለቂያ ያለው ይመስል “ከእንግዲህ ወዲያ ጊዜ አይኖርም” ተብሎ መተርጎም አለበት ብለዋል። ይሁን እንጂ እዚህ ላይ የተጠቀሰው ክሮኖስ የተባለ ቃል ጠቃሽ አመልካች የለውም። ስለዚህ ቃሉ የሚያመለክተው አጠቃላይ ጊዜን ሳይሆን “አንድን ጊዜ” ወይም “የተወሰነን ጊዜ” ነው። በሌላ አነጋገር ይሖዋ የሚዘገይበት ጊዜ አይኖርም ማለት ነው። ክሮኖስ ከተባለው ቃል የተወሰደውን የግሪክኛ ግሥ ሐዋርያው ጳውሎስ ከ⁠ዕንባቆም 2:3, 4 ላይ ጠቅሶ በ⁠ዕብራውያን 10:37 ላይ “ሊመጣ ያለው . . . አይዘገይም” ሲል ጽፎአል።

12 “ወደፊት አይዘገይም” የሚሉት ቃላት በዛሬው ጊዜ ላሉት በዕድሜ የገፉ የዮሐንስ ክፍል አባሎች በጣም የሚያጓጉ ናቸው። መዘግየት የማይኖረው በምን ረገድ ነው? ዮሐንስ እንዲህ በማለት ይነግረናል:- “ዳሩ ግን ሰባተኛው መልአክ ሊነፋ ባለው ጊዜ ድምፁም በሚሰማበት ዘመን ለባሪያዎቹ ለነቢያት የምስራች እንደ ሰበከላቸው የእግዚአብሔር ምሥጢር ይፈጸማል።” (ራእይ 10:7) ይሖዋ ቅዱስ ምሥጢሩን በተሳካ ሁኔታ ወደ ታላቅ ፍጻሜ የሚያደርስበት ጊዜ ቀርቦአል።

13. የአምላክ ቅዱስ ምሥጢር ምንድን ነው?

13 ይህ ቅዱስ ምሥጢር ምንድን ነው? በኤደን ገነት ውስጥ ቃል የተገባልንን የተስፋ ዘር የሚመለከት ምሥጢር ነው። ዋነኛ ዘር የሆነውም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። (ዘፍጥረት 3:15፤ 1 ጢሞቴዎስ 3:16) በተጨማሪም ዘሩን ያስገኘችውን ሴት ማንነት የሚመለከት ምሥጢር ነው። (ኢሳይያስ 54:1፤ ገላትያ 4:26-28) ከዚህም በላይ የዘሩን ክፍል ሁለተኛ ደረጃ አባሎችና ዘሩ የሚነግስበትን መንግሥት የሚያጠቃልል ነው። (ሉቃስ 8:10፤ ኤፌሶን 3:3-9፤ ቆላስይስ 1:26, 27፤ 2:2፤ ራእይ 1:5, 6) ልዩ ስለሆነው ስለዚህ ሰማያዊ መንግሥት የሚናገረው ምሥራች በዚህ የመጨረሻ ቀን በምድር በሙሉ መሰበክ ይኖርበታል።—ማቴዎስ 24:14

14. ሦስተኛው ወዮታ ከአምላክ መንግሥት ጋር የተዛመደው ለምንድን ነው?

14 በእርግጥም ከዚህ ምሥራች የበለጠ አስደሳች ዜና ሊኖር አይችልም። ሆኖም ግን ሦስተኛው ወዮታ በ⁠ራእይ 11:14, 15 ላይ ከመንግሥቱ ጋር ተያይዞአል። ለምን እንዲህ ሆነ? የሰይጣንን ሥርዓት ለሚመርጡ ሰዎች የአምላክ ምሥጢር ተፈጽሞአል ወይም የአምላክ መሢሐዊ መንግሥት ቀርቦአል የሚለው ምሥራች በመለከት መነፋቱ ወዮታ ነው። (ከ⁠2 ቆሮንቶስ 2:16 ጋር አወዳድር።) በጣም የሚወዱት ዓለማዊ ሥርዓት ሊጠፋ ቀርቦአል ማለት ነው። ይህን እንደ ማዕበል የሚያስገመግመውን ማስጠንቀቂያ የሚያሰሙት ሰባት ነጎድጓዶች ድምፅ የይሖዋ የበቀል ቀን እየቀረበ ሲመጣ ይበልጥ ግልጽና ጮክ ያለ ሆኖአል።—ሶፎንያስ 1:14-18

የተከፈተው ጥቅልል

15. ከሰማይ የተሰማው ድምፅና ብርቱው መልአክ ለዮሐንስ ምን ነገረው? በዮሐንስስ ላይ ምን ውጤት ያስከትላል?

15 ዮሐንስ ሰባተኛው መለከት የሚነፋበትንና የአምላክ ቅዱስ ምሥጢር የሚፈጸምበትን ጊዜ በሚጠባበቅበት ጊዜ ተጨማሪ ሥራ ተሰጠው። “ከሰማይም የሰማሁት ድምፅ እንደገና ሲናገረኝና:- ሂድና በባሕርና በምድር ላይ ከሚቆመው መልአክ በእጁ ያለችውን የተከፈተችውን መጽሐፍ ውሰድ ሲል ሰማሁ። ወደ መልአኩም ሄጄ:- ታናሺቱን መጽሐፍ ስጠኝ አልሁት። እርሱም:- ውሰድና ብላት ሆድህንም መራራ ታደርገዋለች በአፍህ ግን እንደ ማር ትጣፍጣለች አለኝ። ከመልአኩም እጅ ታናሺቱን መጽሐፍ ወስጄ በላኋት በአፌም እንደ ማር ጣፋጭ ሆነች። ከበላኋትም በኋላ ሆዴ መራራ ሆነ። በብዙ ወገኖችና በአሕዛብም በቋንቋዎችም በነገሥታትም ላይ እንደገና ትንቢት ትናገር ዘንድ ይገባሃል ተባለልኝ።”—ራእይ 10:8-11

16. (ሀ) ነቢዩ ሕዝቅኤል ዮሐንስ አጋጥሞት የነበረውን ዓይነት ሁኔታ ያጋጠመው እንዴት ነው? (ለ) ትንሹ የመጽሐፍ ጥቅልል ለዮሐንስ የጣፈጠውና ከዋጠው በኋላ ግን የመረረው ለምንድን ነው?

16 ዮሐንስ ያጋጠመው ሁኔታ ነቢዩ ሕዝቅኤል በባቢሎን ምድር በምርኮ ላይ በነበረበት ጊዜ ያጋጠመውን ሁኔታ ይመስላል። እርሱም በአፉ ጣፋጭ የሆነ ጥቅልል እንዲበላ ታዝዞ ነበር። ወደ ሆዱ ከዋጠው በኋላ ግን ለዓመጸኛው የእስራኤል ቤት መራራ የሆነ ትንቢት የመናገር ኃላፊነት ጥሎበታል። (ሕዝቅኤል 2:8 እስከ 3:15) ከፍ ያለ ክብር የተቀዳጀው ኢየሱስ ክርስቶስ ለዮሐንስ የሰጠው የተከፈተ ጥቅልልም እንዲሁ መለኮታዊ መልእክት ነበር። ዮሐንስ “በብዙ ወገኖችና በአሕዛብም በቋንቋዎችም በነገሥታትም ላይ” መስበክ ነበረበት። ይህ ጥቅልል ምንጩ መለኮታዊ ስለሆነ ጥቅልሉን መብላቱ ጣፋጭ ሆኖለታል። (ከ⁠መዝሙር 119:103⁠ና ከ⁠ኤርምያስ 15:15, 16 ጋር አወዳድር።) ይሁን እንጂ ለሕዝቅኤል እንደተሰጠው ጥቅልል ለዓመፀኞቹ የሰው ልጆች ደስ የማያሰኙ ነገሮችን የሚተነብይ ጥቅልል በመሆኑ ከሰውነቱ ጋር ለማዋሃድ መራራ ሆኖበታል።—መዝሙር 145:20

17. (ሀ) ዮሐንስ “እንደገና” ትንቢት እንዲናገር የነገሩት እነማን ናቸው? ይህስ ምን ማለት ነው? (ለ) ዮሐንስ የተመለከተው አስደናቂ ትርዒት የሚፈጸመው መቼ ነው?

17 ዮሐንስ እንደገና ትንቢት እንዲናገር የነገሩት ይሖዋ አምላክና ኢየሱስ ክርስቶስ እንደነበሩ አያጠራጥርም። ዮሐንስ በጳጥሞስ ደሴት ግዞተኛ ሆኖ የሚኖር ቢሆንም እስከዚህ ጊዜ ድረስ በራእይ መጽሐፍ ውስጥ በጻፈው ቃል አማካኝነት ስለ አሕዛብ፣ ስለ ቋንቋዎችና ስለ ነገሥታት ትንቢት ተናግሮአል። “እንደገና” የሚለው ቃል የቀረውን በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የተመዘገበ መልእክት መጻፍና ለሕዝብ ማሰራጨት እንደሚኖርበት ያመለክታል። ይሁን እንጂ እዚህ ላይ ዮሐንስ ራሱ በትንቢታዊ ራእይ ውስጥ መሳተፉን አትርሱ። ዮሐንስ የመዘገበው ትንቢት ብርቱው መልአክ በምድርና በባሕር ላይ የሚኖረውን የበላይነት ሥልጣን በሚቀበልበት በ1914 የሚፈጸም ትንቢት ነው። ታዲያ ይህ ሥዕላዊ መግለጫ በዚህ ዘመን ለሚኖሩት የዮሐንስ ክፍል አባሎች ምን ትርጉም ይኖረዋል?

ትንሽዋ የመጽሐፍ ጥቅልል በዛሬው ጊዜ

18. የጌታ ቀን በጀመረበት ጊዜ የዮሐንስ ክፍል አባሎች ስለ ራእይ መጽሐፍ ብርቱ የማወቅ ፍላጎት ያሳዩት እንዴት ነው?

18 ዮሐንስ የሚመለከተው ነገር የዮሐንስ ክፍል አባሎች በጌታ ቀን መጀመሪያ ላይ የሚያጋጥማቸውን ሁኔታ የሚያመለክት ነው። በዚያ ጊዜ የይሖዋን ዓላማ፣ ሰባቱ ነጎድጓዶች የሚኖራቸውን ትርጉም ጭምር ሙሉ በሙሉ አልተረዱም ነበር። ይሁን እንጂ ስለ ራእይ መጽሐፍ ለማወቅ ጠንካራ ፍላጎት ነበራቸው። ቻርልስ ቴዝ ራስል በሕይወት ዘመኑ በብዙዎቹ የራእይ መጽሐፍ ክፍሎች ላይ ማብራሪያ ሰጥቶ ነበር። በ1916 ከሞተ በኋላ ብዙዎቹ ጽሑፎቹ አንድ ላይ ተጠቃልለው ያለቀለት ምሥጢር በተባለ መጽሐፍ ታትመው ወጡ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን ይህ መጽሐፍ ለራእይ መጽሐፍ ማብራሪያነት የማይበቃ ሆኖ ተገኘ። የክርስቶስ ወንድሞች ቀሪዎች የዚህን በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ መጽሐፍ ትክክለኛ ትርጉም ለመረዳት ራእዩ መፈጸም እስከሚጀምርበት ጊዜ ድረስ መቆየት ነበረባቸው።

19. (ሀ) የሰባቱ ነጎድጓዶች ድምፅ ሙሉ በሙሉ ከመሰማቱ በፊት እንኳን ይሖዋ አምላክ በዮሐንስ ክፍል ይጠቀም የነበረው እንዴት ነው? (ለ) የተከፈተው ትንሽ ጥቅልል ለዮሐንስ ክፍል የተሰጠው መቼ ነው? ይህስ ለእነርሱ ምን ትርጉም ነበረው?

19 ይሁን እንጂ እንደ ዮሐንስ የሰባቱ ነጎድጓዶች ድምፅ ሙሉ በሙሉ ከመሰማቱ በፊት እንኳን ይሖዋ ተገልግሎባቸዋል። ከ1914 በፊት በነበሩት 40 ዓመታት በሙሉ በትጋት ሲሰብኩ ቆይተዋል። በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ወቅት ሥራቸውን በትጋት ለማከናወን ጥረት አድርገዋል። ጌታው በመጣ ጊዜ ለቤተሰቦቹ በጊዜው ምግብ ሲሰጡ የተገኙት እነርሱ ነበሩ። (ማቴዎስ 24:45-47) ስለዚህ በ1919 የተከፈተውን ትንሽ ጥቅልል ማለትም ለሰው ልጅ የሚሰበከውን ክፍት መልእክት የተቀበሉት እነርሱ ነበሩ። እንደ ሕዝቅኤል የያዙት መልእክት ታማኝ ላልሆነች ድርጅት ማለትም በሐሰት አምላክን አገለግለዋለሁ ለምትለው ሕዝበ ክርስትና የተላከ ነው። እንደ ዮሐንስ ለጥቂት ጊዜ ‘ስለ ሕዝቦች፣ ስለ ብሔራት፣ ስለ ቋንቋዎችና ስለ ብዙ ነገሥታት’ መስበክ ነበረባቸው።

20. ዮሐንስ የመጽሐፉን ጥቅልል መብላቱ ምን ያመለክታል?

20 ዮሐንስ የመጽሐፉን ጥቅልል መብላቱ የኢየሱስ ወንድሞች ይህንን ሥራ መቀበላቸውን ያመለክታል። ከዚህ በመንፈስ ከተጻፈው የአምላክ ቃል ክፍል ጋር ሙሉ በሙሉ ተዋህደዋል። ለሰውነታቸውም እንደ መብል ሆኖላቸዋል። ይሁን እንጂ የሚሰብኩት ቃል ለብዙ የሰው ልጆች አልዋጥ ያለውን የይሖዋ የፍርድ መልእክት የያዘ ነው። በ⁠ራእይ ምዕራፍ 8 ላይ የተተነበዩትን መቅሰፍቶች የያዘ ነው። ይሁን እንጂ ለእነዚህ ቅን ክርስቲያኖች እነዚህን የፍርድ መልእክቶች ማወቃቸውና መልእክቶቹን እንደገና በመናገር ይሖዋን ለማገልገል መቻላቸው ጣፍጦአቸው ነበር።—መዝሙር 19:9, 10

21. (ሀ) የትንሹ መጽሐፍ መልእክት ለእጅግ ብዙ ሰዎችም የሚጣፍጥ የሆነው እንዴት ነው? (ለ) ምሥራቹ ለተቃዋሚዎች አሳዛኝ ዜና የሆነባቸው ለምንድን ነው?

21 ከጊዜ በኋላ የጥቅልሉ መልእክት “ከሕዝብ፣ ከነገድና ከቋንቋ” ለተውጣጡትና በሕዝበ ክርስትና ውስጥ የሚፈጸሙትን ነገሮች እያዩ ለሚያዝኑና ለሚተክዙ ሰዎች ጣፋጭ ሆኖአል። (ራእይ 7:9፤ ሕዝቅኤል 9:4) እነዚህም ሰዎች ይሖዋ ለበግ መሰል ክርስቲያኖች ያዘጋጃቸውን አስደናቂ ዝግጅቶች በረጋና በሚጥም አነጋገር በመግለጽ ምሥራቹን ይሰብካሉ። (መዝሙር 37:11, 29፤ ቆላስይስ 4:6) ለተቃዋሚዎች ግን ይህ በጣም መጥፎ ዜና ነው። ለምን? ምክንያቱም መልእክቱ የሚታመኑበት ሥርዓት፣ እንዲያውም ጊዜያዊ እርካታና ደስታ አምጥቶላቸው የነበረው ሥርዓት እንደሚጠፋ የሚገልጽ ነው። ለእነርሱ ምሥራቹ የጥፋት መልእክት ነው።—ፊልጵስዩስ 1:27, 28፤ ከ⁠ዘዳግም 28:15⁠ና ከ⁠2 ቆሮንቶስ 2:15, 16 ጋር አወዳድር።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 160 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የዮሐንስ ክፍል እና ጓደኞቻቸው ለሁሉም የሰው ልጆች ጣፋጭና መራራ መልእክት ያውጃሉ