በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ሰላም በሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ የሚገኝ ሕይወት

ሰላም በሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ የሚገኝ ሕይወት

ሰላም በሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ የሚገኝ ሕይወት

በዚህች ትንሽ ጽሑፍ ውስጥ ያለውን ስዕል ሲመለከቱ ምን ይሰማዎታል? በዚህ ላይ የሚያዩትን ሰላም፣ ደስታና ብልጽግና ለማግኘት ልብዎ አይጓጓምን? መጓጓቱ የማይቀር ነው። ይሁን እንጂ ይህ ዓይነቱ ሁኔታ በምድር ላይ አንድ ቀን ይመጣል ብሎ ማሰብ ሕልም ወይም ቅዠት ነውን?

አብዛኞቹ ሰዎች እንደዚህ ብለው የሚያስቡ ይመስላል። ጥቂቶቹን ብቻ እንኳ ብንጠቅስ ጦርነት፣ ዓመፅ፣ ረሀብ፣ በሽታና እርጅና በዛሬው ጊዜ የምናያቸው እውነታዎች ናቸው። ይሁን እንጂ ተስፋ የምናደርግበት ምክንያት አለን። መጽሐፍ ቅዱስ የወደፊቱን ጊዜ በማስመልከት “ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን” በማለት ይናገራል።—2 ጴጥሮስ 3:13፤ ኢሳይያስ 65:17

በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት እነዚህ “አዲስ ሰማያት” እና “አዲስ ምድር” ቃል በቃል አዲስ ግዑዛን ሰማያት ወይም አዲስ ምድር አይደሉም። የሚታዩት ምድርና ሰማያት ፍጹም ሆነው ስለተሠሩ የሚጐድላቸው ነገር የለም፤ ለዘላለም እንደሚኖሩም መጽሐፍ ቅዱስ ያሳያል። (መዝሙር 89:36, 37፤ 104:5) “አዲስ ምድር” በምድር ላይ የሚኖር ጻድቅ የሆነ ኅብረተሰብ ሲሆን “አዲስ ሰማይ” ደግሞ ይህን ምድራዊ ኅብረተሰብ የሚያስተዳደር ፍጹም የሆነ ሰማያዊ መንግሥት ወይም መስተዳደር ይሆናል። ይሁን እንጂ “አዲስ ምድር” ወይም በጣም ግሩም የሆነ አዲስ ዓለም እንደሚመጣ ለማመን የሚያስችል ተጨባጭ ምክንያት አለንን?

እንደዚህ ያለ በጣም ጥሩ ሁኔታ አምላክ ለዚህ ምድር የነበረው የመጀመሪያው ዓላማ ክፍል መሆኑን መገንዘብ ይገባናል። አምላክ የመጀመሪያዎቹን ባልና ሚስት በምድራዊ ዔደን ገነት ውስጥ አስቀመጣቸውና “ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሉአት” በማለት ድንቅ የሆነ ሥራ ሰጣቸው። (ዘፍጥረት 1:28) አዎ፤ አምላክ ለእነሱ የነበረው ዓላማ ልጆችን እንዲወልዱና ገነትን በምድር ሁሉ እንዲያስፋፉ ነበር። በኋላ አምላክን ላለመታዘዝ ቢመርጡና ለዘላለም ለመኖር የማይበቁ መሆናቸው ቢረጋገጥም የመጀመሪያው የአምላክ ዓላማ አልተለወጠም። ይህ ዓላማ በአዲስ ዓለም ውስጥ መፈጸም ይኖርበታል።—ኢሳይያስ 55:11

እንዲያውም አቡነ ዘበሰማያት (ወይም አባታችን ሆይ) የተባለውን ጸሎት ሲያቀርቡ የአምላክ መንግሥት እንድትመጣ መጠየቅዎ ነው። ሰማያዊ መንግሥቱ በምድር ላይ ያለውን ክፉ ነገር ሁሉ አጥፍታ በዚህ አዲስ ዓለም ላይ እንድትገዛ መጸለይዎ ነው። (ማቴዎስ 6:9) አምላክ “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ” በሚለው የተስፋ ቃሉ መሠረት ይህን ጸሎት እንደሚመልስ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን።—መዝሙር 37:29

በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ የሚኖረው ሕይወት

የአምላክ መንግሥት ለምድር አቻ የማይገኝላቸው ብዙ በረከቶችን ታመጣለች። አምላክ ሕዝቦቹ በምድር ላይ ተደስተው እንዲኖሩ ለማስቻል አስቦት የነበረውን ጥሩ ነገር ሁሉ ታከናውናለች። ጥላቻና አለምክንያት የሌላውን ዘር በክፉ ማየት ይቀራል። በመጨረሻም በምድር ላይ የሚኖር እያንዳንዱ ሰው ለሌላው እውነተኛ ወዳጁ ይሆንለታል። አምላክ ከምድር ዳር እስከ ምድር ዳር ጦርነትን እንደሚያስቀር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተስፋ ሰጥቷል:- “ሕዝብም በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሳም፣ ሰልፍም ከእንግዲህ አይማሩም።”—መዝሙር 46:9፤ ኢሳይያስ 2:4

በመጨረሻ መላዋ ምድር ገነታዊ የአትክልት ስፍራ ትሆናለች። መጽሐፍ ቅዱስ:- “ምድረ በዳውና ደረቁ ምድር ደስ ይላቸዋል፣ በረሀውም ሐሴት ያደርጋል እንደ ጽጌረዳም ያብባል።  . . . በምድረበዳ ውኃ በበረሃም ፈሳሽ ይፈልቃልና። ደረቁ ምድር ኩሬ፣ የጥማትም መሬት የውኃ ምንጭ ትሆናለች” ይላል።—ኢሳይያስ 35:1, 6, 7

ገነት በምትሆነዋ ምድር ውስጥ የምንደሰትባቸው ብዙ ምክንያቶች ይኖራሉ። ሰዎች የሚበሉት አጥተው አይራቡም። መጽሐፍ ቅዱስ “ምድር ፍሬዋን ሰጠች” ይላል። (መዝሙር 67:6፤ 72:16) ፈጣሪያችን ቃል እንደገባው ሁሉም ሰው በሥራው ፍሬ ይደሰታል:- “ወይኑንም ይተክላሉ ፍሬውንም ይበላሉ። . . . ሌላም እንዲበላው አይተክሉም”—ኢሳይያስ 65:21, 22

በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ሰዎች በግዙፍ ሕንፃዎች ወይም በደሳሳ ጐጆዎች ውስጥ አይታጨቁም። አምላክ “ቤቶችንም ይሠራሉ ይቀመጡባቸውማል . . . ሌላ እንዲቀመጥበት አይሠሩም” በማለት ዓላማውን ገልጾልናል። (ኢሳይያስ 65:21–23) በዚህም ምክንያት ሰዎች ውጤት የሚያገኙበት አርኪ ሥራ ይኖራቸዋል። ሕይወት አሰልቺ አይሆንም።

ከጊዜ በኋላ የአምላክ መንግሥት በዔደን ገነት ውስጥ በእንስሳት መካከል፤ እንዲሁም በእንስሳትና በሰዎች መካከል የነበረው ሰላማዊ ዝምድና እንዲመለስ ታደርጋለች። መጽሐፍ ቅዱስ:- “ተኩላ ከበግ ጠቦት ጋር ይቀመጣል፣ ነብርም ከፍየል ጠቦት ጋር ይተኛል፤ ጥጃና የአንበሳ ደቦል ፍሪዳም በአንድነት ያርፋሉ፤ ታናሽም ልጅ ይመራቸዋል” ይላል።—ኢሳይያስ 11:6–9፤ ሆሴዕ 2:18 [በአማርኛ መ/ቅ ቍጥር 20]

እስቲ ሁኔታውን በደንብ ያስቡት። ገነት በምትሆነዋ ምድር ላይ ሁሉም ዓይነት በሽታና አካለ ስንኩልነት ይፈወሳል! የአምላክ ቃል:- “በዚያ የሚቀመጥ ‘ታምሜአለሁ’ አይልም” በማለት ያረጋግጥልናል። (ኢሳይያስ 33:24) አምላክ “እንባዎችን ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ስቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፤ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና።”—ራእይ 21:4

እርስዎ ይህን ሕይወት እንዴት ማግኘት ይችላሉ?

አምላክ ጽድቅ በሚሰፍንበት አዲስ ዓለም ውስጥ ስለሚኖረው ሕይወት በሰጠው ተስፋ ልብዎ እንደሚነካ የተረጋገጠ ነው። ይሁን እንጂ አንዳንዶች እንዲህ ዓይነቱ በረከት በጣም ጥሩ በመሆኑ ሊፈጸም የማይችል ነው ብለው ያስባሉ። ይሁን እንጂ ለአፍቃሪው አምላክ የሚከብድ ነገር የለም።—መዝሙር 145:16፤ ሚክያስ 4:4

እርግጥ፤ በምትመጣዋ ምድራዊት ገነት ውስጥ ለዘላለም ለመኖር ከፈለግን ልናሟላቸው የሚገቡ ብቃቶች አሉ። ኢየሱስ አንዱን ትልቅ ብቃት ለአምላክ ባቀረበው ጸሎቱ ላይ አመልክቷል:- “እውነተኛ አምላክ የሆንከውን አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት” ብሏል።—ዮሐንስ 17:3

ስለዚህ በእርግጥ አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ ለመኖር የምንፈልግ ከሆነ በመጀመሪያ የአምላክን ፈቃድ መማርና ማድረግ ይገባናል። “ዓለምና ምኞቱ ያልፋሉ፣ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ” ግን ከአፍቃሪው ፈጣሪያችን በሚዘንበው በረከት እየተደሰተ ለዘላለም ይኖራል።—1 ዮሐንስ 2:17

ሌላ መግለጫ ካልተሰጠ በስተቀር የተጠቀሱት ጥቅሶች የተወሰዱት በ1954 ከተተረጐመው የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ነው።