የበላይ አካሉ መልእክት
ውድ ወንድሞችና እህቶች፦
“ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን [እያጠመቃችሁ] ደቀ መዛሙርት አድርጉ።” ይህን ተልእኮ የምንፈጽመው አምላክንና ሰዎችን ስለምንወድ ነው። (ማቴ. 28:19, 20፤ ማር. 12:28-31) ፍቅር ትልቅ ኃይል አለው። “ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ” ያላቸውን ሰዎች ልብ ይማርካል።—ሥራ 13:48
ቀደም ባሉት ጊዜያት፣ መግቢያዎችን በቃላችን ለመያዝና ጽሑፎችን ለማበርከት ትኩረት እንሰጥ ነበር። አሁን ደግሞ ከሰዎች ጋር በመጨዋወት ክህሎት ላይ መሥራት እንፈልጋለን። የእኛን ሳይሆን የሰዎችን ትኩረት የሚስቡ ነገሮችን አንስተን በመጨዋወት ፍቅር እንዳለን እናሳያለን። ይህ ደግሞ እንደ ሁኔታው መሆንን ይጠይቃል፤ ግለሰቡ ምን እንደሚያሳስበው ወይም ምን እንደሚፈልግ በሚገባ ማሰብም ይኖርብናል። ታዲያ ይህ ብሮሹር ይህን ለማድረግ የሚያግዘን እንዴት ነው?
ብሮሹሩ 12 ምዕራፎች አሉት፤ በፍቅር ሰዎችን ደቀ መዛሙርት ለማድረግ የሚረዱንን 12 ባሕርያት ያጎላሉ። እያንዳንዱ ምዕራፍ በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ላይ የተመሠረተ ነው፤ ኢየሱስ ወይም በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖረ አንድ ወንጌላዊ ያንን ባሕርይ በአገልግሎቱ ላይ ያሳየው እንዴት እንደሆነ ይብራራል። ዓላማችን መግቢያዎችን በቃላችን መያዝ ሳይሆን ሰዎችን እንደምንወዳቸው ማሳየት የምንችልባቸውን መንገዶች መፈለግ ነው። እያንዳንዱ ባሕርይ ለሁሉም የአገልግሎት ዘርፎች የሚጠቅም ነገር አለው፤ በዚህ ብሮሹር ላይ ግን ውይይት ለመጀመር፣ ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመምራት ይበልጥ የሚያስፈልጉ ባሕርያትን በክፍል በክፍል እንመለከታለን።
እያንዳንዱን ምዕራፍ ስታነብ፣ አንድ ነገር እንድታደርግ እናበረታታሃለን፤ በአካባቢህ ያሉ ሰዎችን በምታነጋግርበት ወቅት፣ በምዕራፉ ላይ የተብራራውን ባሕርይ ማሳየት የምትችለው እንዴት እንደሆነ በጥሞና አስብ። ለይሖዋና ለሰዎች ያለህ ፍቅር እያደገ እንዲሄድ ጥረት አድርግ። ከየትኛውም ክህሎት በላይ ደቀ መዛሙርት ለማድረግ የሚረዳህ ይህ ፍቅር ነው።
ከእናንተ ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘን የማገልገል መብታችንን ከፍ አድርገን እንመለከተዋለን። (ሶፎ. 3:9) ሰዎችን ለመውደድና ደቀ መዛሙርት ለማድረግ ስትተጉ የይሖዋ የተትረፈረፈ በረከት እንዳይለያችሁ ምኞታችን ነው!
ወንድሞቻችሁ
የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል