በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መልስ ማግኘት የሚቻለው ከየት ነው?

መልስ ማግኘት የሚቻለው ከየት ነው?

መልስ ማግኘት የሚቻለው ከየት ነው?

“የዘላለማዊ ሥቃይ ጽንሰ ሐሳብ አምላክ ለፍጥረታት ፍቅር አለው ከሚለው እምነት ጋር ይጋጫል። . . . ነፍስ ማስተካከያ ማድረግ የምትችልበት ዕድል እንኳ ሳታገኝ ለጥቂት ዓመታት በሠራቻቸው ስህተቶች የተነሳ ለዘላለም ትቀጣለች ብሎ ማመን የምክንያታዊነትን መሠረታዊ ሥርዓት እንደ መጣስ ይቆጠራል።”​—⁠ኒኪላናንዳ፣ የሂንዱ ፈላስፋ

1, 2. ስለ ወዲያኛው ሕይወት የተለያዩ እምነቶች በመኖራቸው ምን ጥያቄዎች ይነሳሉ?

እንደ ሂንዱው ፈላስፋ ኒኪላናንዳ በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ብዙ ሰዎች ስለ ዘላለማዊ ሥቃይ የሚገልጸው ትምህርት አእምሯቸውን ይረብሻቸዋል። ልክ እንደዚሁም ሌሎች ሰዎች የኒርቫና ግብ ላይ መድረስና ከታኦ ጋር አንድ መሆንን የመሳሰሉ ጽንሰ ሐሳቦችን መረዳት ያዳግታቸዋል።

2 ሆኖም በምሥራቁም ሆነ በምዕራቡ ዓለም ያሉት ሃይማኖቶች ነፍስ አትሞትም በሚለው ጽንሰ ሐሳብ የተነሳ ስለ ወዲያኛው ሕይወት ግራ የሚያጋቡ የተለያዩ እምነቶች አዳብረዋል። ስንሞት ምን እንደምንሆን በትክክል ማወቅ ይቻላልን? ነፍስ በእርግጥ የማትሞት ነችን? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት የምንችለው ከየት ነው?

ሳይንስና ፍልስፍና

3. ሳይንስ ወይም ደግሞ ሳይንሳዊው የምርምር ዘዴ ከሞት በኋላ ያለውን ሕይወት በተመለከተ ለሚነሱት ጥያቄዎች መልስ ይሰጣልን?

3 ሳይንስ ወይም ደግሞ ሳይንሳዊው የምርምር ዘዴ የወዲያኛውን ሕይወት በተመለከተ ለሚነሱት ጥያቄዎች መልስ ይሰጣልን? አንዳንድ ተመራማሪዎች በሞት አፋፍ ላይ ወይም ደግሞ ‘ከሥጋ ውጪ’ ስለነበሩ ሰዎች በሚገልጹ በቅርብ ጊዜ የወጡ ዘገባዎች ላይ በመመርኮዝ ከሞት በኋላ ስላለው ሕይወት አስተያየት ለመስጠት ሞክረዋል። የካቶሊክ ሃይማኖታዊ ምሁር የሆኑት ሀንስ ኩንግ “ሞት ወደ ብርሃን የሚያሸጋግር ድልድይ ነውን?” በሚል ርዕስ በሰጡት ንግግር ላይ ተመራማሪዎቹ የሰጧቸውን አንዳንድ አስተያየቶች በመጥቀስ እንዲህ ሲሉ ደምድመዋል:- “እንዲህ ዓይነቶቹ ገጠመኞች ከሞት በኋላ ሕይወት ሊኖር ይችላል ሊያሰኙ የሚችሉ አይደሉም፤ እነዚህ ሁኔታዎች ከሞት በፊት ያሉትን የመጨረሻ አምስት ደቂቃዎች እንጂ ከሞት በኋላ ያለውን ዘላለማዊ ሕይወት የሚጠቁሙ አይደሉም።” አክለውም እንዲህ ብለዋል:- “ከሞት በኋላ ሕይወት ሊኖር ይችላል ወይ የሚለው ጥያቄ በሕይወት ላለ ሰው አንገብጋቢ ጥያቄ ነው። የሕክምናው ዓለም ለዚህ ጥያቄ መልስ መስጠት ካልቻለ መልሱን ከሌላ አቅጣጫ መፈለግ ያሻል።”

4. ፍልስፍና የተለያዩ ሃይማኖቶች የወዲያኛውን ሕይወት አስመልክተው ከሚሰጧቸው ብዙ ተስፋዎች መካከል መልሱን እንድናገኝ ሊረዳን ይችላልን?

4 ፍልስፍናስ? የተለያዩ ሃይማኖቶች የወዲያኛውን ሕይወት አስመልክተው ከሚሰጧቸው ብዙ ተስፋዎች መካከል ትክክለኛውን መልስ ሊጠቁመን ይችላልን? የፍልስፍና ምርምር “በግምታዊ ሐሳቦች ላይ የተመሠረቱ እንቅስቃሴዎችን” ያቀፈ ነው ሲሉ የ20ኛው መቶ ዘመን ፈላስፋ የሆኑት ብሪታንያዊው በርትራንድ ራስል ተናግረዋል። ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፔድያ እንደሚገልጸው ከሆነ ፍልስፍና “የምርመራ ዓይነት፣ የጥናት ሂደት፣ ግምገማ፣ ማብራሪያና ግምታዊ አስተሳሰብ” ነው። ስለወዲያኛው ሕይወት የሚሰጡት የፍልስፍና ግምታዊ ሐሳቦች በጣም የተለያዩ ናቸው፤ አንዳንዶቹ ዘላለማዊነት እንዲሁ ምኞት ብቻ ነው ሲሉ ሌሎቹ ደግሞ የእያንዳንዱ ሰው መብት እንደሆነ አድርገው ይገልጻሉ።

መልሶቹን የሚሰጥ በዓይነቱ ልዩ የሆነ ምንጭ

5. እስከ ዛሬ ከተጻፉት ጽሑፎች ሁሉ ጥንታዊው መጽሐፍ የትኛው ነው?

5 ይሁን እንጂ ሕይወትንና ሞትን በተመለከተ ለሚነሱት አንገብጋቢ ጥያቄዎች ትክክለኛ መልሶች የያዘ መጽሐፍ አለ። ይህ መጽሐፍ በጥንታዊነቱ ግንባር ቀደሙን ሥፍራ የያዘ ነው፤ አንዳንዶቹ የመጽሐፉ ክፍሎች የተጠናቀሩት ከ3,500 ዓመታት ገደማ በፊት ነው። የዚህ መጽሐፍ የመጀመሪያው ክፍል የተጻፈው በሂንዱ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሚገኙት ጥንታውያን መዝሙራት ማለትም ቬዳዎች ከመዘጋጀታቸው ጥቂት መቶ ዘመናት አስቀድሞና ቡድሃ፣ ማሃቪራና ኮንፊሺየስ ከኖሩበት ዘመን አንድ ሺህ ዓመት ገደማ አስቀድሞ ነው። ይህ መጽሐፍ ተጽፎ ያለቀው መሐመድ እስልምናን ከማቋቋሙ ከ500 ዓመታት በፊት በ98 እዘአ ነው። ይህ በዓይነቱ ልዩ የሆነ የላቀ ጥበብ ምንጭ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። *

6. መጽሐፍ ቅዱስ ነፍስ ምን እንደሆነች ሊነግረን ይችላል ብለን መጠበቅ የምንችለው ለምንድን ነው?

6 መጽሐፍ ቅዱስ በውስጡ የያዘው ጥንታዊ ታሪክ በዛሬው ጊዜ የሚገኝ የትኛውም መጽሐፍ ከያዘው ጥንታዊ ታሪክ ይበልጥ ትክክለኛ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቦ የሚገኘው ታሪክ ከሰብዓዊው ቤተሰብ መጀመሪያ አንስቶ ይተርካል፤ በተጨማሪም በምድር ላይ ሕያው ልንሆን የቻልነው እንዴት እንደሆነ ይገልጻል። አልፎ ተርፎም ሰዎች ከመፈጠራቸው በፊት ስለነበረው ጊዜ ይናገራል። እንዲህ ዓይነቱ መጽሐፍ በእርግጥም ሰው እንዴት እንደተፈጠረና ነፍስ ምን እንደሆነች እንድንገነዘብ ሊረዳን ይችላል።

7, 8. ስንሞት ምን እንሆናለን ለሚለው ጥያቄ እውነተኛና አጥጋቢ መልሶች እንደሚሰጠን በመተማመን መጽሐፍ ቅዱስን መመርመር የምንችለው ለምንድን ነው?

7 ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ በትክክል ፍጻሜያቸውን ያገኙ ትንቢቶችን የያዘ መጽሐፍ ነው። ለምሳሌ ያህል የሜዶንና የፋርስ እንዲሁም የግሪክ ኃያላን መንግሥታትን አነሳስና አወዳደቅ አስቀድሞ በዝርዝር ተንብዮአል። እነዚህ ትንቢቶች ሙሉ በሙሉ ትክክል ስለነበሩ አንዳንድ ተቺዎች ትንቢቶቹ የተጻፉት ሁኔታዎቹ ከተከሰቱ በኋላ እንደሆነ አድርገው ለማስረዳት ከንቱ ሙከራ አድርገዋል። (ዳንኤል 8:​1-7, 20-22) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙ አንዳንድ ትንቢቶች በእኛ ዘመን አንድ በአንድ እየተፈጸሙ ነው። *​—⁠ማቴዎስ ምዕራፍ 24፤ ማርቆስ ምዕራፍ 13፤ ሉቃስ ምዕራፍ 21፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:​1-5, 13

8 ማንኛውም ሰው ምንም ያህል ዐዋቂ ቢሆን ወደፊት የሚሆኑትን ሁኔታዎች ሙሉ በሙሉ በትክክል መተንበይ አይችልም። ይህን ማድረግ የሚችለው ሁሉን ማድረግ የሚያስችል ኃይልና ጥበብ ያለው የአጽናፈ ዓለሙ ፈጣሪ ብቻ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:​16, 17፤ 2 ጴጥሮስ 1:​20, 21) መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥም አምላክ ያስጻፈው መጽሐፍ ነው። እንዲህ ዓይነቱ መጽሐፍ ስንሞት ምን እንሆናለን ለሚለው ጥያቄ እውነተኛና አጥጋቢ መልስ ሊሰጠን እንደሚችል ምንም ጥርጥር የለውም። በመጀመሪያ ይህ መጽሐፍ ስለ ነፍስ ምን እንደሚል እንመልከት።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.5 ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን ለሰው ሁሉ የሚሆን መጽሐፍ የተባለውን ብሮሹር ተመልከት።

^ አን.7 ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን መጽሐፍ ቅዱስ—⁠የአምላክ ቃል ነው ወይስ የሰው? የተባለውን መጽሐፍ ተመልከት።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እስከ ዛሬ ከተጻፉት ሁሉ እጅግ ጥንታዊ የሆነው መጽሐፍ

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አስተማማኝና አጥጋቢ መልሶች የሚሰጠው መጽሐፍ