በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ነፍስ ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ነፍስ ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ነፍስ ምን ይላል?

“ሰውም ሕይወት ያለበት ነፍስ ሆነ።”​—⁠ዘፍጥረት 2:​7 የ1879 እትም

1. መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ነፍስ የሚያስተምረውን ትምህርት ማወቅ እንድንችል ምን መመርመር ይኖርብናል?

ቀደም ሲል እንዳየነው ነፍስን በተመለከተ ያሉት እምነቶች በርካታና የተለያዩ ናቸው። እምነታቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ እንደሆነ የሚናገሩ የእምነት ክፍሎች እንኳ የነፍስን ምንነትና ስንሞት ምን እንደምንሆን የሚሰጡት አስተያየት የተለያየ ነው። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ነፍስ ምን ብሎ ያስተምራል? የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ነፍስ” ተብለው የተተረጎሙትን የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቃላት ፍቺዎች መመርመር ይኖርብናል።

“ነፍስ” ሕያው ፍጡር ነው

2, 3. (ሀ) በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ “ነፍስ” ተብሎ የተተረጎመው የትኛው ቃል ነው? የቃሉስ መሠረታዊ ትርጉም ምንድን ነው? (ለ) ዘፍጥረት 2:​7 “ነፍስ” የሚለው ቃል ሰውየውን በጠቅላላ እንደሚያመለክት የሚያረጋግጠው እንዴት ነው?

2 “ነፍስ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል ነፈሽ ሲሆን በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች (በአብዛኛው ብሉይ ኪዳን ተብለው በሚጠሩት) ውስጥ 754 ጊዜ ተጠቅሶ ይገኛል። ነፈሽ ማለት ምን ማለት ነው? ዘ ዲክሽነሪ ኦቭ ባይብል ኤንድ ሪሊጅን እንደሚለው ከሆነ ቃሉ “ብዙውን ጊዜ መላውን ሕያው አካልና ግለሰቡን በጠቅላላ ያመለክታል።”

3 ለምሳሌ ያህል ዘፍጥረት 2:​7 (የ1879 እትም) እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “እግዚአብሔርም አምላክ ሰውን ፈጠረ መሬት ከምድር ባፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስ እፍ አለበት። ሰውም ሕይወት ያለበት ነፍስ ሆነ።” አዳም ነፍስ ያለው ሆነ እንዳልተባለ ልብ በል፤ ዶክተር የሆነ ሰው ዶክተር ነው እንደሚባል ሁሉ አዳምም ራሱ ነፍስ ነበር። ስለዚህ “ነፍስ” የሚለው ቃል ሰውየውን በጠቅላላ ሊያመለክት ይችላል።

4, 5. (ሀ) “ነፍስ” የሚለው ቃል ሰውየውን በጠቅላላ እንደሚያመለክት የሚያሳዩ ምሳሌዎች ጥቀስ። (ለ) ዘ ዲክሽነሪ ኦቭ ባይብል ኤንድ ሪሊጅን ሰው ነፍስ ነው የሚለውን አባባል የሚደግፈው እንዴት ነው?

4 የሚከተሉትን ዓይነት ሐረጎች የምናገኝባቸው የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ከዳር እስከ ዳር ይህን ግንዛቤ የሚደግፉ ናቸው:- “ነፍስ ኃጢአት ቢሠራ” (ዘሌዋውያን 5:​1 NW)፣ “በዚያውም ቀን ስራ የምትሰራበት ነፍስ ሁሉ” (ዘሌዋውያን 23:​30 የ1879 እትም)፣ “ሰው ነፍስ አፍኖ ቢወስድ” (ዘዳግም 24:​7 NW)፣ “ነፍሱም . . . ተጨነቀች” (መሳፍንት 16:​16)፣ “ነፍሴን የምትነዘንዙ፣ . . . እስከ መቼ ነው?” (ኢዮብ 19:​2)፣ “ከኀዘን የተነሣ ነፍሴ እንቅልፍ አጣች።”​—⁠መዝሙር 119:​28 NW

5 በእነዚህ ምንባቦች ውስጥ ነፍስ ከሞት በኋላ በሕይወት የምትኖር ረቂቅ ነገር እንደሆነች የሚጠቁም አንዳችም ፍንጭ አናገኝም። “በሞት የተለየን የምንወደው ሰው ‘ነፍስ’ ከጌታ ጋር ለመሆን ሄዳለች ወይም ደግሞ ‘ነፍስ አትሞትም’ የሚለው አነጋገር በብሉይ ኪዳን ውስጥ ከተገለጸው እምነት ጋር ሙሉ በሙሉ ይጋጫል” ሲል ዘ ዲክሽነሪ ኦቭ ባይብል ኤንድ ሪሊጅን ይገልጻል።

6, 7. በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ “ነፍስ” ተብሎ የተተረጎመው ቃል የትኛው ነው? የቃሉስ መሠረታዊ ትርጉም ምንድን ነው?

6 በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች (ብዙውን ጊዜ አዲስ ኪዳን ተብለው በሚጠሩት) ውስጥ ከመቶ ጊዜ በላይ “ነፍስ” እየተባለ የተተረጎመው ቃል ፕስኺ የተባለው ቃል ነው። ልክ እንደ ነፈሽ ሁሉ ይሄኛውም ቃል ብዙውን ጊዜ የሚያመለክተው ሰውየውን በጠቅላላ ነው። ለምሳሌ ያህል የሚከተሉትን ዐረፍተ ነገሮች ተመልከት:- “ነፍሴ ታውካለች።” (ዮሐንስ 12:​27) “በነፍስ ሁሉ ላይ ፍርሃት ወደቀ።” (ሥራ 2:​43 NW) “ነፍስ ሁሉ በበላይ ላሉት ባለ ሥልጣኖች ይገዛ።” (ሮሜ 13:​1) “የተጨነቁትን ነፍሳት አጽናኗቸው።” (1 ተሰሎንቄ 5:​14 NW) “ጥቂቶች ማለት ስምንት ነፍስ በውኃ የዳኑበት።”​—⁠1 ጴጥሮስ 3:​20

7 ልክ እንደ ነፈሽ ሁሉ ፕስኺ የሚለው ቃልም በግልጽ የሚያመለክተው በጠቅላላ ሰውየውን ነው። ኒጀል ተርነር የተባሉት ምሁር እንዳሉት ከሆነ ይህ ቃል “ሰውየውን ራሱን፣ አምላክ ሩአህ [መንፈስ] እፍ ያለበትን ሥጋዊ አካል ያመለክታል። . . . ቃሉ በይበልጥ የሚያመለክተው ሰውየውን በጠቅላላ ነው።”

8. እንስሳት ነፍሳት ናቸውን? አብራራ።

8 “ነፍስ” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰዎችን ብቻ ሳይሆን እንስሳትንም ያመለክታል። ለምሳሌ ያህል ዘፍጥረት 1:​20 (NW) ስለ ባሕር ፍጥረታት ሲገልጽ አምላክ “ውኃውም ብዛት ባላቸው ሕያው ነፍሳት ይሞላ” ሲል እንዳዘዘ ይናገራል። በተጨማሪም አምላክ በቀጣዩ የፍጥረት ቀን ላይ እንዲህ አለ:- “ምድሪቱ ሕያው ነፍስ ታውጣ በየዘመድዋ። እንስሳን ተንቀሳቃሽንም የምድርንም አራዊት ኢየዘመዱ።” (ዘፍጥረት 1:​24 የ1879 እትም፤ ከዘኁልቁ 31:​28 የ1879 እትም ጋር አወዳድር።) ስለዚህ “ነፍስ” ሰውንም ሆነ እንስሳን፣ በጠቅላላ ሕያው ፍጥረትን ሊያመለክት ይችላል።

“ነፍስ” የፍጡርን ሕይወትም ያመለክታል

9. (ሀ) “ነፍስ” የሚለው ቃል ምን ተጨማሪ ትርጉም ሊሰጠው ይችላል? (ለ) ይህ ትርጉም ሰው ራሱ ነፍስ ነው ከሚለው አባባል ጋር ይጋጫል?

9 አንዳንድ ጊዜ “ነፍስ” የሚለው ቃል አንድ ሰው ወይም እንስሳ ያለውን ሕይወት ያመለክታል። ይህ ሁኔታ ነፍስ የሚባለው ሰውየው ወይም እንስሳው ራሱ ነው የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ፍቺ አይለውጠውም። ይህን በምሳሌ ለማስረዳት:- አንድ ሰው በሕይወት አለ በምንልበት ጊዜ ሰውየው ሕያው ነው ማለታችን ነው። ሕይወት አለው ብለን ልንናገርም እንችላለን። በተመሳሳይም አንድ ሕያው የሆነ ሰው ነፍስ ነው። ሆኖም በሕይወት ባለበት ዘመን “ነፍስ” እንዳለው አድርጎ መናገርም ይቻላል።

10. “ነፍስ” የሚለው ቃል የሰውን ወይም የእንስሳን ሕይወት ሊያመለክት እንደሚችል የሚያሳዩ ምሳሌዎች ጥቀስ።

10 ለምሳሌ ያህል አምላክ ሙሴን “ነፍስህን የሚሹአት ሰዎች ሁሉ ሞተዋል” ብሎታል። (ዘጸአት 4:​19) የሙሴ ጠላቶች ሕይወቱን ለማጥፋት ይፈልጉ እንደነበረ ግልጽ ነው። “ነፍስ” የሚለው ቃል በሚከተሉት ዐረፍተ ነገሮች ውስጥም በተመሳሳይ መንገድ ተሠርቶበታል። “ስለ ነፍሳችን እጅግ ፈራን።” (ኢያሱ 9:​24) “ነፍሳቸውን ያድኑ ዘንድ ሸሹ።” (2 ነገሥት 7:​7) “ጻድቅ ሰው ለእንስሳው ነፍስ ይራራል።” (ምሳሌ 12:​10) “የሰው ልጅ . . . ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ” መጥቷል። (ማቴዎስ 20:​28) “በነፍሱ ተወራርዶ . . . እስከ ሞት ቀርቦአልና።” (ፊልጵስዩስ 2:​30) በሁሉም ሁኔታዎች “ነፍስ” የሚለው ቃል የተሠራበት “ሕይወትን” ለማመልከት ነው። *

11. “ነፍስ” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ስለተሠራበት መንገድ ምን ማለት ይቻላል?

11 ስለዚህ “ነፍስ” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተሠራበት መሠረት ሰውን ወይም እንስሳን ወይም ደግሞ ሰውየውም ሆነ እንስሳው ያላቸውን ሕይወት ያመለክታል። መጽሐፍ ቅዱስ ለነፍስ የሚሰጠው ፍቺ ግልጽ፣ ተለዋዋጭ ያልሆነና የሰው ልጆች ከፈጠሯቸው ውስብስብ የሆኑ ፍልስፍናዎችና አጉል እምነቶች የጠራ ነው። ይሁን እንጂ በሞት ጊዜ ነፍስ ምን ትሆናለች? ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት በመጀመሪያ የምንሞተው ለምን እንደሆነ ማወቅ ይኖርብናል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.10 ማቴዎስ 10:​28 ላይም “ሕይወትን” ለማመልከት “ነፍስ” የሚለው ቃል ገብቷል።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 20 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ሁሉም ነፍሳት ናቸው