በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ስለ ነፍስ እውነቱን ማወቁ ለውጥ ያመጣል

ስለ ነፍስ እውነቱን ማወቁ ለውጥ ያመጣል

ስለ ነፍስ እውነቱን ማወቁ ለውጥ ያመጣል

“እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል።”​—⁠ዮሐንስ 8:​32

1. ስለ ነፍስም ሆነ ስለ ሞት ያሉንን እምነቶች መመርመራችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

ሞትንና የወዲያኛውን ሕይወት በተመለከተ ያሉት እምነቶች በአብዛኛው በአንድ ሰው ሃይማኖታዊና ባህላዊ አስተዳደግ ላይ የተመኩ ናቸው። ቀደም ሲል እንዳየነው እነዚህ እምነቶች ነፍስ ለበርካታ ጊዜያት ዳግም ስትወለድ ከቆየች በኋላ የመጨረሻ ግቧ ላይ ትደርሳለች ከሚለው አንስቶ አንድ ሰው አንዴ የሚያሳልፈው ሕይወቱ የመጨረሻ ዕጣውን ይወስነዋል የሚለውን ትምህርት የመሳሰሉ የተለያዩ ጽንሰ ሐሳቦችን የያዙ ናቸው። በመሆኑም አንድ ሰው በመጨረሻ የሁሉ የበላይ ከሆነው ኃይል ጋር አንድ እሆናለሁ የሚል ጠንካራ እምነት ሊኖረው ይችላል፤ ኒርቫና ወደሚባለው የመጨረሻ ግብ ላይ እደርሳለሁ ብሎ የሚያስብም ሊኖር ይችላል፤ ሌላው ደግሞ ሰማያዊ ሽልማት አገኛለሁ የሚል እምነት ሊኖረው ይችላል። ታዲያ እውነቱ የትኛው ነው? እምነታችን በአመለካከታችን፣ በድርጊታችንና በውሳኔዎቻችን ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር በመሆኑ ለዚህ ጥያቄ መልስ የማግኘቱ ጉዳይ ሊያሳስበን አይገባምን?

2, 3. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ነፍስ በሚሰጠው ሐሳብ ላይ ሙሉ እምነት መጣል የምንችለው ለምንድን ነው? (ለ) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተገለጸው መሠረት ነፍስን በተመለከተ እውነተኛው ነገር ምንድን ነው?

2 በዓለም ላይ ከሚገኙት ጽሑፎች ሁሉ እጅግ ጥንታዊ መጽሐፍ የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ የሰውን ልጅ ታሪክ የመጀመሪያው ሰብዓዊ ነፍስ ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ ይተርክልናል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት ትምህርቶች ከሰው ልጆች ፍልስፍናዎችና ወጎች የጠሩ ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ነፍስ እውነተኛውን ነገር በግልጽ ይነግረናል:- ነፍስህ አንተ ራስህ ነህ፤ ሙታን ሙሉ በሙሉ ከሕልውና ውጪ ናቸው፤ አምላክ በአእምሮው የያዛቸው ደግሞ እሱ በወሰነው ጊዜ ይነሳሉ። ይህን ማወቅህ ለአንተ ምን ትርጉም ሊኖረው ይችላል?

3 ኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮቹን “እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል” ብሏቸው ነበር። (ዮሐንስ 8:​32) አዎ፣ እውነት ነፃ ያወጣል። ሆኖም ስለ ነፍስ እውነተኛውን ነገር ማወቃችን ነፃ የሚያወጣን ከምንድን ነው?

ከፍርሃትና ከተስፋ መቁረጥ ስሜት ነፃ መውጣት

4, 5. (ሀ) ስለ ነፍስ እውነተኛውን ነገር ማወቃችን የትኛውን ፍርሃት ያስወግድልናል? (ለ) የትንሣኤ ተስፋ ቀሳፊ በሆነ በሽታ ተይዛ ለነበረች ወጣት ድፍረት የሰጣት እንዴት ነው?

4 “አብዛኞቹ ሰዎች ሞትን የሚፈሩ ከመሆኑም በላይ ጭራሹኑ ስለ ሞት ማሰብ አይፈልጉም” ሲል ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፔድያ ይናገራል። “በምዕራቡ ዓለም ‘ሞት’ የሚለውን ቃል ራሱ የሚያነሳው የለም ማለት ይቻላል” ሲሉ አንድ ታሪክ ጸሐፊ ተናግረዋል። አንዳንድ ኅብረተሰቦች ብዙውን ጊዜ አንድ ሰው መሞቱን ለመግለጽ “አለፈ” ወይም “አረፈ” የሚሉትን ዓይነት አባባሎች ይጠቀማሉ። ሞት ለአብዛኞቹ ሰዎች ምስጢር በመሆኑ ሞትን የሚፈሩት ስለሞት የሚያውቁት ነገር ባለመኖሩ ነው። ስንሞት ምን እንደምንሆን እውነተኛውን ነገር ማወቃችን ይህን ፍርሃት ያስወግድልናል።

5 ለምሳሌ ያህል ማይክለን የተባለች የ15 ዓመት ወጣት የነበራትን ስሜት ተመልከት። ሉኪሚያ ይዟት ስለነበር በሚያሳዝን ሁኔታ ሞተች። ፖላ የተባለችው እናቷ ሁኔታውን ወደ ኋላ መለስ ብላ በማስታወስ እንዲህ ብላለች:- “ማይክለን ሞት ጊዜያዊ ነገር እንደሆነ ታውቅ ስለነበር ምንም እንደማያስፈራት ትናገር ነበር። አምላክ ስለሚያመጣው አዲስ ዓለምና በዚያ አዲስ ዓለም ውስጥ ከሞት ስለሚነሱት ሰዎች ብዙ ተነጋግረናል። ማይክለን በይሖዋ አምላክና በትንሣኤ ተስፋ ላይ ትልቅ እምነት ነበራት፤ ቅንጣት ያህል ጥርጣሬ አልነበራትም።” የትንሣኤ ተስፋ ይቺን ደፋር ወጣት ከሞት ፍርሃት ነፃ አውጥቷታል።

6, 7. ስለ ነፍስ እውነተኛውን ነገር ማወቃችን ከምን ዓይነት የተስፋ መቁረጥ ስሜት ነፃ ያወጣናል? አብራራ።

6 እውነት በማይክለን ወላጆች ላይ ምን ለውጥ አምጥቷል? “ትንሿን ልጃችንን በሞት ማጣታችንን እስከ ዛሬ ከደረሰብን ሁሉ የከፋ ሐዘን አሳድሮብናል” ሲል አባቷ ጄፍ ተናግሯል። “ሆኖም ይሖዋ በሰጠው የትንሣኤ ተስፋ ሙሉ በሙሉ እናምናለን፤ ውዷ ማይክለን ዳግመኛ እቅፋችን ውስጥ የምትገባበትን ቀን በጉጉት እንጠባበቃለን። ያን ጊዜ ምን ያህል እንደምንደሰት ገምቱት!”

7 አዎ፣ አንድ ሰው ስለ ነፍስ እውነተኛውን ነገር ማወቁ የሚወደው ሰው ሲሞት ሊደርስበት ከሚችለው የተስፋ መቁረጥ ስሜት ነፃ ያወጣዋል። እርግጥ ነው፣ የምንወደው ሰው ሲሞት የሚሰማንን ጥልቅ ሐዘን ሙሉ በሙሉ ሊያስወግድልን የሚችል ነገር የለም። ይሁን እንጂ የትንሣኤ ተስፋ ሐዘናችንን ሊቀንስልንና እንድንቋቋመው ሊረዳን ይችላል።

8, 9. ሙታን ስለሚገኙበት ሁኔታ እውነተኛውን ነገር ማወቃችን ከየትኛው ፍርሃት ነፃ ያደርገናል?

8 በተጨማሪም ሙታን ስለሚገኙበት ሁኔታ የሚገልጸውን ቅዱስ ጽሑ​ፋዊ እውነት ማወቃችን ሙታንን እንዳንፈራ ያደርገናል። ሙታንን በተመለከተ በአጉል እምነት ተጠፍረው የነበሩ ብዙዎች ይህን እውነት ከተማሩ በኋላ ከእርግማን፣ ከገድ፣ ከክታብና አስማታዊ ኃይል አላቸው ከሚባሉ ዕቃዎች ጋር በተያያዘ የነበራቸው ጭንቀት ተወግዷል፤ በተጨማሪም የቀድሞ አባቶቻቸውን ፍላጎት ለማሟላትና ተመልሰው እየመጡ በሕይወት የሚገኙትን ሰዎች እንዳያስፈራሩ ለመከላከል ሲሉ ብዙ ወጪ የሚጠይቁ መሥዋዕቶችን ማቅረብ ትተዋል። ሙታን ‘አንዳች የማያውቁ’ በመሆኑ እንዲህ ዓይነቶቹ ልማዶች ምንም ዋጋ የላቸውም።​—⁠መክብብ 9:​5

9 ነፍስን በተመለከተ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸው እውነት በእርግጥም ነፃ የሚያወጣና እምነት የሚጣልበት ነው። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ የዘረጋልህን በዓይነቱ ልዩ የሆነ ተስፋም ተመልከት።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ስለ ነፍስ እውነቱን ማወቅህ ሞትን ከመፍራት፣ ሙታንን ከመፍራትና የምትወደው ሰው ሲሞት ሊያድርብህ ከሚችለው የተስፋ መቁረጥ ስሜት ያላቅቅሃል