በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በሞት ወቅት ነፍስ ምን ትሆናለች?

በሞት ወቅት ነፍስ ምን ትሆናለች?

በሞት ወቅት ነፍስ ምን ትሆናለች?

“ነፍስ እንደማትሞትና ሰውየው ከሞተ በኋላ በሕይወት እንደምትቀጥል፣ ሥጋው ግን እንደሚበሰብስ የሚገልጸው መሠረተ ትምህርት የክርስቲያናዊ ፍልስፍና እና ሃይማኖታዊ ትምህርት አንዱ የመሠረት ድንጋይ ነው።”​—⁠“ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔድያ”

1. ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔድያ ነፍስ ከሞት በኋላ ሕያው ሆና ትቀጥላለች የሚለውን ትምህርት በተመለከተ የትኛውን ሐቅ ሳይሸሽግ ተናግሯል?

ይሁን እንጂ ከላይ የተጠቀሰው የማመሳከሪያ ጽሑፍ “ከሞት በኋላም ነፍስ በሕይወት ትቀጥላለች የሚለው ሐሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ ሰፍሮ አይገኝም” ሲል ሐቁን ሳይሸሽግ ተናግሯል። ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ በሞት ወቅት ነፍስ ምን ትሆናለች ብሎ ያስተምራል?

ሙታን አንዳች አያውቁም

2, 3. ሙታን በምን ሁኔታ ላይ ይገኛሉ? ይህን የሚገልጹት ጥቅሶችስ የትኞቹ ናቸው?

2 ሙታን የሚገኙበት ሁኔታ በመክብብ 9:​5, 10 ላይ በሚከተለው መንገድ በግልጽ ሰፍሮ እናገኘዋለን:- “ሙታን ግን አንዳች አያውቁም . . . በሲኦል ሥራና አሳብ እውቀትና ጥበብ አይገኙም።” ስለዚህ ሞት ከሕልውና ውጪ መሆን ማለት ነው። መዝሙራዊው ሰዎች በሚሞቱበት ጊዜ “ወደ ዐፈር ይመለሳሉ፤ በዚያኑ ቀን ዕቅዳቸው ሁሉ ያከትማል” ሲል ጽፏል።​—⁠መዝሙር 146:​4 የ1980 ትርጉም

3 ስለዚህ ሙታን ምንም አያውቁም፤ ምንም ማድረግም አይችሉም። አምላክ በአዳም ላይ በፈረደ ጊዜ “አፈር ነህና፣ ወደ አፈርም ትመለሳለህ” ሲል ገልጿል። (ዘፍጥረት 3:​19) አምላክ ከምድር አፈር ሠርቶ ሕይወት ሳይሰጠው በፊት አዳም ከሕልውና ውጪ ነበር። ሲሞት ቀድሞ ወደ ነበረበት ሁኔታ ተመልሷል። ቅጣቱ ሞት እንጂ ወደ ሌላ ዓለም መዛወር አልነበረም።

ነፍስ ልትሞት ትችላለች

4, 5. ነፍስ ልትሞት እንደምትችል የሚያሳዩ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምሳሌዎች ጥቀስ።

4 አዳም ሲሞት ነፍሱ ምን ሆነች? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ነፍስ” የሚለው ቃል ብዙውን ጊዜ ራሱን ሰውየውን እንደሚያመለክት አስታውስ። ስለዚህ አዳም ሞተ ስንል አዳም የተባለው ነፍስ ሞተ ማለታችን ነው። ይህ አባባል ነፍስ አትሞትም ብሎ ለሚያምን ሰው እንግዳ ሊሆንበት ይችላል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ “ኃጢአት የምትሠራ ነፍስ እርስዋ ትሞታለች” ሲል ይገልጻል። (ሕዝቅኤል 18:​4) ዘሌዋውያን 21:​1 (NW) ስለ “ሞተ ነፍስ” (“አስከሬን” ጀሩሳሌም ባይብል) ይናገራል። ናዝራውያን ወደ “ማንኛውም የሞተ ነፍስ (NW)” (“ሬሳ” የ1954 እትም) አጠገብ እንዳይደርሱ ታዝዘው ነበር።​—⁠ዘኁልቁ 6:​6

5 ነፍስ የሚለው ቃል በ1 ነገሥት 19:​4 (NW) ላይ ተመሣሣይ በሆነ መንገድ ተሠርቶበታል። እጅግ ተጨንቆ የነበረው ኤልያስ “ነፍሱ እንድትሞት” ለምኖ ነበር። በተመሳሳይም ዮናስ “ሞትን [“ነፍሱ እንድትሞት፣” NW] ፈለገና:- ከሕይወት ሞት ይሻለኛል አለ።” (ዮናስ 4:​8) በተጨማሪም ኢየሱስ “ነፍስ . . . ማጥፋት (የ1980 ትርጉም)” የሚል ሐረግ ተጠቅሟል፤ ይህንንም የ1954 እትም “መግደል” ብሎ ተርጉሞታል። (ማርቆስ 3:​4) ስለዚህ የነፍስ መሞት የሰውየውን መሞት የሚያመለክት ነው።

‘መውጣት’ እና ‘መመለስ’

6. መጽሐፍ ቅዱስ የራሄል ነፍስ ‘በምትወጣበት ጊዜ’ ሲል ምን ማለቱ ነው?

6 ይሁን እንጂ ሁለተኛ ልጅዋን ስትወልድ በአሳዛኝ ሁኔታ ስለሞተችው ስለ ራሄልስ ምን ማለት ይቻላል? በዘፍጥረት 35:​18 ላይ “እርስዋም ስትሞት ነፍስዋ በምትወጣበት ጊዜ ስሙን ቤንኦኒ ብላ ጠራችው፤ አባቱ ግን ብንያም አለው” የሚል ቃል እናነባለን። ይህ ምንባብ ራሄል በምትሞትበት ጊዜ ከእሷ የወጣ ሕያው ነገር እንደነበራት ያመለክታልን? በፍጹም፣ አያመለክትም። “ነፍስ” የሚለው ቃል አንድ ሰው ያለውን ሕይወትም ሊያመለክት እንደሚችል አስታውስ። ስለዚህ በዚህ ረገድ የራሄል “ነፍስ” በአጭሩ የሚያመለክተው “ሕይወቷን” ነው። ሌሎች መጽሐፍ ቅዱሶች “ነፍሷ በምትወጣበት ጊዜ” የሚለውን ሐረግ “ሕይወቷ ሲያከትም” (ኖክስ)፣ “የመጨረሻዋን እስትንፋስ ስትተነፍስ” (ጀሩሳሌም ባይብል) እና “ሕይወቷ በተለያት ጊዜ” (ባይብል ኢን ቤዚክ ኢንግሊሽ) እያሉ የተረጎሙት ለዚህ ነው። ራሄል ስትሞት ከእሷ ተለይቶ የሄደ ሕያው የሆነ አንድ ምስጢራዊ ነገር እንዳለ የሚጠቁም ምንም ፍንጭ የለም።

7. ከሞት የተነሳው የመበለቷ ልጅ ነፍስ ‘ወደ እርሱ የተመለሰችው’ በምን መንገድ ነው?

7 ይህ ሁኔታ በ1 ነገሥት ምዕራፍ 17 ላይ ተመዝግቦ ከሚገኘው የአንዲት መበለት ልጅ ትንሣኤ ጋር ተመሳሳይ ነው። በቁጥር 22 ላይ እንደተገለጸው ኤልያስ በልጁ ላይ ተኝቶ ሲጸልይ “እግዚአብሔርም የኤልያስን ቃል ሰማ፤ የብላቴናው ነፍስ ወደ እርሱ ተመለሰች፣ እርሱም ዳነ።” እዚህም ላይ “ነፍስ” የሚለው ቃል “ሕይወትን” ያመለክታል። በመሆኑም ኒው አሜሪካን ስታንዳርድ ባይብል “የልጁ ሕይወት ወደ እርሱ ተመለሰችና እንደገና ሕያው ሆነ” ይላል። አዎ፣ ልጁ መልሶ ያገኘው ሕይወት እንጂ ረቂቅ የሆነች ነገር አይደለም። ይህም ኤልያስ “እነሆ፣ ልጅሽ [ልጁን በጠቅላላ ያመለክታል] በሕይወት ይኖራል” ብሎ ለልጁ እናት ከተናገረው ቃል ጋር ይስማማል።​—⁠1 ነገሥት 17:​23

“የሽግግር ወቅትን” በተመለከተ ያለው አወዛጋቢ ጉዳይ

8. ክርስቲያን ነን የሚሉ ብዙ ሰዎች በትንሣኤ ወቅት ምን ነገር ይከናወናል ብለው ያምናሉ?

8 ክርስቲያን ነን የሚሉ ብዙ ሰዎች ወደፊት ሥጋና ዘላለማዊ የሆኑት ነፍሳት እንደገና የሚገናኙበት ትንሣኤ አለ ብለው ያምናሉ። ከዚያም ከሞት የተነሱት ሰዎች ዕጣ ፈንታቸውን ይቀበላሉ፤ ጥሩ አኗኗር የነበራቸው ሰዎች ሽልማት ሲቀበሉ ክፉዎች የነበሩት ደግሞ የበቀል እርምጃ ይወሰድባቸዋል።

9. “የሽግግር ወቅት” የሚለው አባባል ምን ማለት ነው? አንዳንዶች በዚህ ወቅት ነፍስ ምን ትሆናለች ይላሉ?

9 ይህ ጽንሰ ሐሳብ ግልጽ ይመስላል። ሆኖም ነፍስ አትሞትም የሚል ጠንካራ እምነት ያላቸው ሰዎች ነፍስ በሞትና በትንሣኤ መካከል ባለው ጊዜ ውስጥ ምን ትሆናለች ለሚለው ጥያቄ መልስ ለመስጠት ይቸገራሉ። እንዲያውም በአብዛኛው “የሽግግር ወቅት” እየተባለ የሚጠራው ይህ ጊዜ ለብዙ ዘመናት ግምታዊ ሐሳብ ሲሰጥበት ቆይቷል። አንዳንዶች በዚህ ወቅት ላይ ነፍስ ወደ ሰማይ ለመግባት የሚያስችላትን ብቃት እንድታገኝ ቀላል ከሆኑ ኃጢአቶች መንጻት ወደምትችልበት ወደ መንጽሔ ትገባለች ይላሉ። *

10. ነፍሳት ከሞት በኋላ መንጽሔ ውስጥ ይቆያሉ ብሎ ማመን ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነው ለምንድን ነው? በአልዓዛር ላይ የደረሰው ሁኔታስ ይህን የሚያረጋግጠው እንዴት ነው?

10 ይሁን እንጂ ቀደም ሲል እንዳየነው ነፍስ የሚለው ቃል በአጭሩ የሚያመለክተው ሰውየውን ነው። ሰውየው ሞተ ማለት ነፍሱ ሞተ ማለት ነው። ስለዚህ ከሞት በኋላ ምንም የሚያውቀው ነገር አይኖርም። አልዓዛር በሞተ ጊዜ ኢየሱስ ክርስቶስ በመንጽሔ፣ ነፍሳት የክርስትና ጥምቀት ባለመቀበላቸው ምክንያት ወደ ሰማይ እንዳይገቡ በሚታገዱበት ቦታ ወይም ደግሞ በሌላ “የሽግግር ወቅት” ላይ እንዳለ አድርጎ አልተናገረም። ከዚህ ይልቅ በአጭሩ “አልዓዛር ተኝቶአል” ሲል ተናግሯል። (ዮሐንስ 11:​11) በሞት ወቅት ነፍስ ምን እንደምትሆን ትክክለኛውን ነገር በሚገባ የሚያውቀው ኢየሱስ አልዓዛር ምንም የሚያውቀው ነገር እንዳልነበረና ከሕልውና ውጪ እንደነበረ ያምን ነበር።

መንፈስ ምንድን ነው?

11. “መንፈስ” የሚለው ቃል አንድ ሰው ሲሞት ከሥጋው ተለይታ የምትኖርን ነገር ሊያመለክት የማይችለው ለምንድን ነው?

11 መጽሐፍ ቅዱስ ሰው ሲሞት “መንፈሱ ትወጣለች ወደ መሬትም ይመለሳል” ይላል። (መዝሙር 146:​4 የ1879 እትም) ይህ ማለት መንፈሱ ቃል በቃል ከሥጋው ተለይቶ ሰውየው ከሞተም በኋላ ሕያው ሆኖ ይቀጥላል ማለት ነውን? አይደለም፤ ምክንያቱም መዝሙራዊው ቀጥሎ “በዚያ ቀን አሳቡ ሁሉ ይጠፋል [NW]” (“አስተሳሰቡ ሁሉ ያከትማል፣” ኒው ኢንግሊሽ ባይብል) ይላል። ታዲያ መንፈስ ምንድን ነው? አንድ ሰው በሚሞትበት ጊዜ ከሰውየው ‘የሚወጣውስ’ እንዴት ነው?

12. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “መንፈስ” ተብለው የተተረጎሙት የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቃላት ምን ያመለክታሉ?

12 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “መንፈስ” ተብለው የተተረጎሙት ቃሎች (የዕብራይስጡ ሩአሕ፤ የግሪኩ ፕኒውማ) መሠረታዊ ትርጉማቸው “እስትንፋስ” ማለት ነው። በመሆኑም በአር ኤ ኖክስ የተዘጋጀው ትርጉም “መንፈሱ ትወጣለች” ከማለት ይልቅ “እስትንፋሱ ከሥጋው ትለያለች” የሚለውን ሐረግ ይጠቀማል። (መዝሙር 145:​4፣ ኖክስ) ሆኖም “መንፈስ” የሚለው ቃል ከመተንፈስም የበለጠን ነገር ያመለክታል። ለምሳሌ ያህል ዘፍጥረት 7:​22 በዓለም አቀፉ የጥፋት ውኃ ወቅት በሰውና በእንስሳት ሕይወት ላይ ስለደረሰው ጥፋት ሲናገር እንዲህ ይላል:- “በየብስ የነበረው በአፍንጫው የሕይወት ነፍስ [“ኃይል፣” NW፤ ወይም መንፈስ፤ በዕብራይስጥ ሩዋሕ] እስትንፋስ ያለው ሁሉ ሞተ።” ስለዚህ “መንፈስ” በሕያዋን ፍጥረታት ሁሉ፣ በሰውም ሆነ በእንስሳት ውስጥ የሚሠራውንና በእስትንፋስ የሚንቀሳቀሰውን የሕይወት ኃይል ሊያመለክት ይችላል።

13. መንፈስ ከኤሌክትሪክ ዥረት ጋር ሊመሳሰል የሚችለው በምን መንገድ ነው?

13 ለምሳሌ ያህል:- የኤሌክትሪክ ዥረት (current) አንድን መሣሪያ ሊያሠራው ይችላል። ዥረቱ ካቆመ ግን መሣሪያውም መሥራቱን ያቆማል። ዥረቱ ብቻውን አይሠራም። በተመሳሳይም አንድ ሰው ሲሞት መንፈሱ የሰውነቱን ሕዋሳት ማሠራቱን ያቆማል። መንፈሱ ከአካሉ ተለ​ይቶ ወደ ሌላ ዓለም አይሄድም።​—⁠መዝሙር 104:​29 NW

14, 15. አንድ ሰው ሲሞት መንፈሱ ወደ አምላክ የሚመለሰው እንዴት ነው?

14 ታዲያ መክብብ 12:​7 (የ1879 እትም) አንድ ሰው በሚሞትበት ጊዜ “መንፈስም ወደ ሰጠው ወደ እግዚአብሔር ይመለሳል” የሚለው ለምንድን ነው? ይህ ማለት መንፈሱ ቃል በቃል ጠፈርን አቋርጦ ወደ አምላክ ይሄዳል ማለት ነውን? እንደዚያ ማለት አይደለም። መንፈስ የሕይወት ኃይል መሆኑን አስታውስ። ይህ የሕይወት ኃይል ከወጣ በኋላ ዳግመኛ ሊመልሰው የሚችለው አምላክ ብቻ ነው። ስለዚህ መንፈሱ “ወደ እግዚአብሔር ይመለሳል” ሲባል የሰውየው የወደፊት ሕይወት ተስፋ ሙሉ በሙሉ የተመካው በአምላክ ላይ መሆኑን ያመለክታል።

15 አንድን ሰው መንፈሱን ወይም የሕይወት ኃይሉን በመመለስ ዳግመኛ ሕያው ሊያደርገው የሚችለው አምላክ ብቻ ነው። (መዝሙር 104:​30) ታዲያ አምላክ እንደዚያ የማድረግ አሳብ አለውን?

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.9 ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔድያ እንደሚለው ከሆነ “[የቤተ ክርስቲያን] አባቶች በጥቅሉ ሲታይ መንጽሔ አለ በሚለው እምነታቸው ላይ ምንም ጥርጣሬ የላቸውም።” ሆኖም ይኸው የማመሳከሪያ ጽሑፍ “የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ስለ መንጽሔ የምታስተምረው ትምህርት በቅዱስ ጽሑፉ ላይ ሳይሆን በወግ ላይ የተመሠረተ ነው” ሲል ሐቁን ሳይሸሽግ በግልጽ ተናግሯል።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የቀድሞ ሕይወት ትውስታዎች

አንድ ሰው ሲሞት ከሥጋው ተለይታ የምትኖር ነገር ከሌለች አንዳንዶች ስለሚናገሯቸው የቀድሞ ሕይወት ትውስታዎች ምን ማለት ይቻላል?

የሂንዱ ምሁር የሆኑት ኒኪላናንዳ ‘ከሞት በኋላ የሚያጋጥሙ ሁኔታዎችን ምክንያታዊ በሆነ መንገድ መግለጽ አይቻልም’ ሲሉ ተናግረዋል። የሃይማኖት ምሁር የሆኑት ሃንስ ኩንግ “ሃይማኖቶች ዘላለማዊነትን በተመለከተ ያላቸውን እምነት የሚያሳዩ ምሳሌዎች” በተባለው ንግግራቸው ላይ እንዲህ ብለዋል:- “በአብዛኛው ልጆች የሚናገሩትን ወይም ደግሞ በሪኢንካርኔሽን በሚያምኑ አገሮች ሲነገር የሚሰማውን የትኛውንም የቀድሞ ሕይወት ታሪክ ትውስታ ትክክለኛነት ማረጋገጥ አይቻልም።” በተጨማሪም እንዲህ ሲሉ አክለው ተናግረዋል:- “አብዛኞቹ [በመስኩ ተሠማርተው ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ከልባቸው የሚሠሩ ተመራማሪዎች] ማስረጃ አድርገው የሚያቀርቧቸው ተሞክሮዎች አንድ ሰው በምድር ላይ በተደጋጋሚ ጊዜ መኖሩን አጥጋቢ በሆነ መንገድ የሚያሳምኑ እንዳልሆኑ ያምናሉ።”

አንተ ራስህ የቀድሞ ሕይወት ትውስታዎች እንዳሉህ ሆኖ ቢሰማህስ? እንዲህ ዓይነቱ ስሜት በተለያዩ ምክንያቶች ሊመጣ ይችላል። አብዛኛው ወደ አእምሯችን የሚገባው መረጃ ቀጥተኛ በሆነ መንገድ ወይም ደግሞ ወዲያውኑ ስለማንጠቀምበት በውስጠ ሕሊናችን በሆነ ስውር ቦታ ይቀመጣል። አንዳንድ ሰዎች የረሷቸውን ነገሮች ማስታወስ ሲጀምሩ እነዚህን ነገሮች በቀድሞ ሕይወታቸው ያሳለፏቸው ነገሮች እንደሆኑ አድርገው ይተረጉሟቸዋል። ሆኖም በአሁኑ ሕይወታችን ካሳለፍናቸው ነገሮች ሌላ በቀድሞ ሕይወት ያሳለፍናቸው ነገሮች ስለመኖራቸው ምንም ማረጋገጫ አናገኝም። አብዛኛው የምድር ነዋሪ ምንም ዓይነት የቀድሞ ሕይወት ትውስታ የሌለው ከመሆኑም በላይ ከዚህ ቀደም በሕይወት እንደኖረ አድርጎ አያስብም።