በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትምህርቱ ከአይሁድ፣ ከሕዝበ ክርስትናና ከእስልምና ሃይማኖቶች ጋር ተቀላቀለ

ትምህርቱ ከአይሁድ፣ ከሕዝበ ክርስትናና ከእስልምና ሃይማኖቶች ጋር ተቀላቀለ

ትምህርቱ ከአይሁድ፣ ከሕዝበ ክርስትናና ከእስልምና ሃይማኖቶች ጋር ተቀላቀለ

“ሃይማኖት፣ ሰዎች ከሞት በኋላ የተሻለ ሕይወት የማግኘት፣ ዳግም የመወለድ ወይም ደግሞ የሁለቱም ዕጣዎች ተካፋይ የመሆን ተስፋ ይዘው አንድ ቀን መሞታቸው እንደማይቀር አምነው እንዲቀበሉ ማድረግ የሚቻልበትም አንዱ መንገድ ነው።”​—⁠ጀርመናዊ ደራሲ ጌርሃርት ኸርም

1. አብዛኞቹ ሃይማኖቶች ከሞት በኋላ ስለሚኖረው ሕይወት የሚሰጡት ተስፋ በየትኛው መሠረታዊ እምነት ላይ የተመሠረተ ነው?

ሁሉም ሃይማኖቶች ማለት ይቻላል፣ የወዲያኛውን ሕይወት በተመለከተ የሚሰጡት ተስፋ ሰው የማትሞት ነፍስ እንዳለችውና በሚሞትበት ጊዜ ነፍሱ ወደ ሌላ ዓለም እንደምትሄድ ወይም ወደ ሌላ አካል እንደምትሸጋገር በሚገልጸው እምነት ላይ የተመሠረተ ነው። ከዚህ በፊት ባለው ክፍል ላይ እንደተገለጸው ነፍስ አትሞትም የሚለው እምነት የምሥራቃውያን ሃይማኖቶች ከተመሠረቱበት ጊዜ ጀምሮ አብሯቸው የኖረ ዋነኛ የእምነታቸው ክፍል ነው። ይሁን እንጂ የአይሁድ፣ የሕዝበ ክርስትናና የእስልምና ሃይማኖቶችስ? ነፍስ አትሞትም የሚለው ትምህርት በእነዚህ እምነቶች ውስጥ ትልቅ ቦታ ሊያገኝ የቻለው እንዴት ነው?

የአይሁድ ሃይማኖት የግሪክ ጽንሰ ሐሳቦችን ቀሰመ

2, 3. ኢንሳይክሎፔድያ ጁዳይካ እንደሚገልጸው ከሆነ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ነፍስ አትሞትም ብለው ያስተምራሉ?

2 የአይሁድ ሃይማኖት የተመሠረተው ከ4,000 ዓመታት በፊት በአብርሃም ዘመን ነው። የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች መጻፍ የጀመሩት በ16ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ሲሆን ተጽፈው የተጠናቀቁት ደግሞ ሶቅራጥስና ፕላቶ ነፍስ አትሞትም የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ ባዳበሩበት ወቅት ነው። እነዚህ ቅዱሳን ጽሑፎች ነፍስ አትሞትም ብለው ያስተምራሉ?

3 ኢንሳይክሎፔድያ ጁዳይካ እንዲህ ሲል መልሱን ይሰጠናል:- “ነፍስ አትሞትም የሚል ግልጽና ጠንካራ የሆነ እምነት የተመሠረተውና . . . ከአይሁድና ከክርስትና እምነት የመሠረት ድንጋዮች አንዱ የሆነው ከመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን በኋላ ነው።” በተጨማሪም “በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ነፍስ የሚለው ቃል ሰውየውን በጠቅላላ የሚያመለክት ነበር። ስለዚህ ነፍስ ከሥጋ የተለየች ነገር እንደሆነች ተደርጋ አትታይም ነበር” ሲል ይገልጻል። የጥንቶቹ አይሁዶች በሙታን ትንሣኤ ያምኑ ነበር፤ ይህ ደግሞ “ነፍስ አትሞትም . . . ከሚለው እምነት ተለይቶ መታየት አለበት” ሲል ኢንሳይክሎፔድያው ያመለክታል።

4-6. ነፍስ አትሞትም የሚለው መሠረተ ትምህርት ከአይሁድ እምነት “የመሠረት ድንጋዮች አንዱ” ሊሆን የቻለው እንዴት ነው?

4 ታዲያ ይህ መሠረተ ትምህርት ከአይሁድ ሃይማኖት “የመሠረት ድንጋዮች አንዱ” ሊሆን የቻለው እንዴት ነው? ታሪክ መልሱን ይሰጠናል። በ332 ከዘአበ ታላቁ እስክንድር ብዙዎቹን የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች በቅጽበት ድል አድርጎ ያዘ። ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ አይሁዶች እጃቸውን ዘርግተው ተቀበሉት። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው አይሁዳዊው ታሪክ ጸሐፊ ፍላቪየስ ጆሴፈስ እንዳለው ከሆነ ከ200 ዓመታት በፊት የተጻፈውንና እስክንድር “የግሪክ ንጉሥ” ሆኖ ስለሚቀዳጃቸው ድሎች በግልጽ የሚናገረውን በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘውን ትንቢትም አሳይተውታል። (ዳንኤል 8:​5-8, 21) የእስክንድር ተተኪዎች የግሪክን ቋንቋ፣ ባህልና ፍልስፍና በመላ ግዛቱ በማስፋፋት የእስክንድርን የሄለናይዜሽን ዕቅድ ተግባራዊ ማድረግ ቀጠሉ። የግሪክና የአይሁድ ባሕሎች መዋሃዳቸው የማይቀር ሆነ።

5 አስቀድሞ በሦስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን ወደ ግሪክኛ በመተርጎም ሰፕቱጀንት የተባለውን የመጀመሪያ የትርጉም ሥራ ማዘጋጀት ተጀምሮ ነበር። በዚህ የትርጉም ሥራ አማካኝነት ብዙ አሕዛብ የአይሁድ ሃይማኖትን ከፍ አድርገው መመልከትና ከእምነቱ ጋር በሚገባ መተዋወቅ ጀመሩ፤ እንዲያውም አንዳንዶቹ ወደ ይሁዲነት ተለወጡ። በሌላ በኩል ደግሞ አይሁዶች የግሪክን አስተሳሰብ እየተማሩ ነበር፤ አልፎ ተርፎም አንዳንዶቹ በአይሁዶች ታሪክ የመጀመሪያዎች ፈላስፎች ሆኑ። በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ ይኖር የነበረው የእስክንድርያው ፊሎ ከእነዚህ የአይሁድ ፈላስፎች አንዱ ነበር።

6 ፊሎ ፕላቶን ከፍ አድርጎ ይመለከተው የነበረ ከመሆኑም በላይ የአይሁድ እምነትን በተመለከተ በግሪክ ፍልስፍና ላይ የተመሠረተ ትንተና ለመስጠት ሞክሯል። “ፊሎ የፕላቶን ፍልስፍና ከመጽሐፍ ቅዱሳዊው ወግና ልማድ ጋር ቀላቅሎ አንድ በጣም ለየት ያለ ውህደት በመፍጠር ከጊዜ በኋላ ለተነሱት የክርስትና [እና የአይሁድ] ፈላስፎች መንገዱን ጠርጎላቸዋል” ሲል ሄቨን—⁠ኤ ሂስትሪ የተባለው መጽሐፍ ይገልጻል። ፊሎ ስለ ነፍስ የነበረው እምነት ምንድን ነው? መጽሐፉ በመቀጠል እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “በፊሎ እምነት መሠረት አንድ ሰው ሲሞት ነፍሱ ሰውየው ከመወለዱ በፊት ወደነበረችበት ወደ ቀድሞ ሁኔታዋ ትመለሳለች። ነፍስ በመንፈሳዊው ዓለም የምትኖር ነገር በመሆኗ በሥጋ ውስጥ ሆና የምታሳልፈው ሕይወት አጭር ከመሆኑም በላይ ብዙውን ጊዜ አሳዛኝ ነው።” ነፍስ አትሞትም ብለው ያምኑ ከነበሩት የአይሁድ ፈላስፎች መካከል በ10ኛው መቶ ዘመን ይኖር የነበረው የታወቀው አይሁዳዊ ሐኪም አይዚክ ኢዝራሊ እና በ18ኛው መቶ ዘመን ይኖር የነበረው ፈላስፋው ጀርመናዊ አይሁድ ሞሰስ ሜንደልሰን ይገኙበታል።

7, 8. (ሀ) ታልሙድ ነፍስን የሚገልጸው እንዴት ነው? (ለ) ከጊዜ በኋላ የተዘጋጀው ምሥጢራዊው የአይሁዶች ሥነ ጽሑፍ ስለ ነፍስ ምን ይላል?

7 በአይሁዶች አስተሳሰብና ሕይወት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደረው ሌላው ነገር ከሁለተኛው መቶ ዘመን እዘአ ጀምሮ እስከ መካከለኛው ዘመን ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ በረቢዎች የተጠናቀረውና ከጊዜ በኋላ የተጨመሩትን ትንተናዎችና ማብራሪያዎች ጨምሮ የቃል ሕግ የሚባለው ፍሬ ሐሳብ አጠር ባለ መልኩ የተጻፈበት የታልሙድ መጽሐፍ ነው። “ታልሙድን ያዘጋጁት ረቢዎች” ይላል ኢንሳይክሎፔድያ ጁዳይካ፣ “ነፍስ ከሞት በኋላም በሕይወት ትቀጥላለች ብለው ያምኑ ነበር።” እንዲያውም ታልሙድ ሙታን ከሕያዋን ጋር ግንኙነት እንደሚያደርጉ ይናገራል። “[ረቢዎች] የፕላቶ ፍልስፍና ባሳደረባቸው ተጽዕኖ ሳይሆን አይቀርም” ይላል ኢንሳይክሎፔድያ ኦቭ ሪሊጅን ኤንድ ኤቲክስ፣ “ነፍሳት ሥጋ ለብሰው ከመምጣታቸውም በፊት በሕይወት የነበሩ ነገሮች ናቸው ብለው ያምኑ ነበር።”

8 ከጊዜ በኋላ ደግሞ ካባላ የተባለው ምሥጢራዊው የአይሁዶች የሥነ ጽሑፍ ሥራ ይባስ ብሎ ሪኢንካርኔሽንን ማስተማር ጀመረ። ዘ ኒው ስታንዳርድ ጁውሽ ኢንሳይክሎፔድያ ይህን እምነት በተመለከተ እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “ትምህርቱ የመጣው ከሕንድ ሳይሆን አይቀርም። . . . ይህ ትምህርት በካባላ እምነት ውስጥ መጀመሪያ ብቅ ያለው ባሂር በተባለው መጽሐፍ ውስጥ ሲሆን ዞሃር በተባለው መጽሐፍ ውስጥ ከተካተተበት ጊዜ ጀምሮ በሃሲድ እምነትና ሥነ ጽሑፍ ውስጥ ከፍተኛ ሚና በመጫወት ከአምላክ ጋር ምሥጢራዊ ግንኙነት ማድረግ ይቻላል ብለው በሚያምኑት ሰዎች ዘንድ ሰፊ ተቀባይነት አግኝቷል።” በአሁኑ ጊዜ በእስራኤል ውስጥ ሪኢንካርኔሽን በሰፊው ተቀባይነት ያገኘ የአይሁድ ትምህርት ሆኗል።

9. በዛሬው ጊዜ ያሉት አብዛኞቹ የአይሁድ ሃይማኖት ቡድኖች ነፍስ አትሞትም በሚለው ጽንሰ ሐሳብ ላይ ያላቸው አቋም ምንድን ነው?

9 ስለዚህ ነፍስ አትሞትም የሚለው ትምህርት ከአይሁድ እምነት ጋር የተቀላቀለው የግሪክ ፍልስፍና ባሳደረው ተጽዕኖ ሲሆን ጽንሰ ሐሳቡ በዛሬው ጊዜ በአብዛኞቹ የሃይማኖቱ ቡድኖች ውስጥ ተቀባይነት አግኝቷል። ትምህርቱ ከሕዝበ ክርስትና እምነት ጋር ስለ ተቀላቀለበት ሁኔታስ ምን ማለት ይቻላል?

ሕዝበ ክርስትና የፕላቶን ፍልስፍናዎች ተቀበለች

10. አንድ የታወቁ ስፔናዊ ምሁር ኢየሱስ ነፍስ አትሞትም በሚለው ጽንሰ ሐሳብ ላይ ስለነበረው እምነት ምን ብለው ደምድመዋል?

10 እውነተኛ ክርስትና የተቋቋመው በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ነው። የታወቁት የ20ኛው መቶ ዘመን ስፔናዊ ምሁር ሚገል ደ ኡናሙኖ ኢየሱስን አስመልክተው እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “እንደ [ግሪኩ] የፕላቶ ፍልስፍና ነፍስ አትሞትም የሚል እምነት አልነበረውም፤ ከዚህ ይልቅ እንደ አይሁዳውያኑ እምነት በሥጋ ትንሣኤ ያምን ነበር። . . . ትክክለኛ ትንታኔ በተሰጠበት በማንኛውም መጽሐፍ ላይ የዚህን ማስረጃ ማግኘት ይቻላል።” እንዲህ ሲሉ ደምድመዋል:- “ነፍስ አትሞትም የሚለው እምነት . . . የአረማውያን ፍልስፍናዊ እምነት ነው።”

11. የግሪክ ፍልስፍና ከክርስትና እምነት ጋር መቀላቀል የጀመረው መቼ ነው?

11 ይህ “የአረማውያን ፍልስፍናዊ እምነት” ወደ ክርስትና ሰርጎ የገባው መቼና እንዴት ነው? ኒው ኢንሳይክሎፔድያ ብሪታኒካ እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “ከ2ኛው መቶ ዘመን እዘአ አጋማሽ ጀምሮ የግሪክን ፍልስፍና በተወሰነ ደረጃ የተማሩ ክርስቲያኖች የራሳቸውን አእምሮ ለማርካትና የተማሩ አረማውያንን ወደ ክርስትና ለመለወጥ ሲሉ እምነታቸውን ከግሪክ ፍልስፍና አኳያ መግለጽ እንዳለባቸው ሆኖ ተሰማቸው። ይበልጥ ተስማምቷቸው የነበረው የፕላቶ ፍልስፍና ነበር።”

12-14. ኦሪጀንና ኦውግስቲን የፕላቶን ፍልስፍና ከክርስትና ጋር በመቀላቀል ረገድ ምን ሚና ተጫውተዋል?

12 እንዲህ ዓይነቶቹ ሁለት የጥንት ፈላስፎች በሕዝበ ክርስትና መሠረተ ትምህርቶች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድረዋል። አንዱ የእስክንድርያው ኦሪጀን (ከ185-254 እዘአ ገደማ) ሲሆን ሌላው ደግሞ የሂፖው ኦውግስቲን (354-430 እዘአ) ነው። ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔድያ እነሱን አስመልክቶ እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “ነፍስ መንፈሳዊ ነገር ከመሆኗም በላይ ዘላለማዊ ናት የሚለው ፍልስፍናዊ ጽንሰ ሐሳብ ተቀባይነት እንዲያገኝ ያደረጉት በምሥራቅ፣ ኦሪጀን በምዕራብ ደግሞ ቅዱስ ኦውግስቲን ናቸው።” ኦሪጀንና ኦውግስቲን ነፍስን በተመለከተ የነበራቸው ጽንሰ ሐሳብ በምን ላይ የተመሠረተ ነበር?

13 ኦሪጀን የእስክንድሪያው ክሌመንት ተማሪ ነበር፤ ክሌመንት ደግሞ “ግሪኮች ነፍስን በተመለከተ የነበራቸውን እምነት በቀጥታ ከወሰዱት አባቶች የመጀመሪያው” እንደነበረ ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔድያ ይገልጻል። ፕላቶ ስለ ነፍስ የነበረው አመለካከት በኦሪጀን ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሮ መሆን አለበት። የሃይማኖት ምሁር የሆኑት ቨርነር ዬገር “[ኦሪጀን] ነፍስን በተመለከተ ከፕላቶ የወሰዳቸውን ስፍር ቁጥር የሌላቸው ትምህርቶች በክርስትና መሠረተ ትምህርት ውስጥ አስገብቷል” ሲሉ ዘ ሃርቫርድ ቲኦሎጂካል ሪቪው በተባለው መጽሐፍ ላይ ገልጸዋል።

14 አንዳንድ የሕዝበ ክርስትና ተከታዮች ኦውግስቲንን ታላቅ ጥንታዊ ፈላስፋ አድርገው ይመለከቱታል። ኦውግስቲን ወደ “ክርስትና” ከመለወጡ በፊት በ33 ዓመቱ ለፍልስፍና ከፍተኛ ፍቅር ስላደረበት ኒኦፕላቶኒስት ሆኖ ነበር። * ወደ ክርስትና ከተቀየረም በኋላ የኒኦፕላቶኒዝም አስተሳሰቡን አልለወጠም። “በኦውግስቲን አእምሮ ውስጥ የአዲስ ኪዳኑ ሃይማኖት የግሪክ ፍልስፍና ከሆነው የፕላቶ እምነት ጋር ፍጹም የሆነ ውሕደት ፈጥሮ ነበር” ሲል ዘ ኒው ኢንሳይክሎፔድያ ብሪታኒካ ይገልጻል። ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔድያ “በምዕራቡ ዓለም እስከ 12ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ ድረስ ተቀባይነት አግኝቶ ይሠራበት የነበረው [ኦውግስቲን ስለ ነፍስ ያስተማረው] መሠረተ ትምህርት በአብዛኛው . . . ከኒኦፕላቶኒዝም የተወሰደ ነው” ሲል ሐቁን በግልጽ ተናግሯል።

15, 16. በ13ኛው መቶ ዘመን የአርስቶትል ትምህርቶች ያገኙት ተወዳጅነት ቤተ ክርስቲያን ነፍስ አትሞትም በሚለው ትምህርት ላይ የነበራትን አቋም ለውጦታልን?

15 በ13ኛው መቶ ዘመን የአርስቶትል ትምህርቶች በአውሮፓ ውስጥ ተቀባይነት እያገኙ ሄደው ነበር፤ ለዚህ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረገው ነገር በአርስቶትል መጣጥፎች ላይ ሰፊ ትንተና የሰጡ የአረብ ምሁራን የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች በላቲን ቋንቋ መዘጋጀታቸው ነው። ቶማስ አኩዊናስ የተባሉ አንድ የካቶሊክ ምሁር የአርስቶትል አስተሳሰብ በጣም ማረካቸው። አኩዊናስ ባዘጋጁዋቸው ጽሑፎች አማካኝነት የአርስቶትል አመለካከት ከፕላቶ አመለካከት የበለጠ በቤተ ክርስቲያኒቱ ትምህርት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያሳድር ችሏል። ይሁን እንጂ ይህ ሁኔታ ነፍስ አትሞትም በሚለው ትምህርት ላይ ምንም ለውጥ አላመጣም።

16 አርስቶትል ነፍስ ከሥጋ የምትለያይ ነገር እንዳልሆነችና ከሞት በኋላ ብቻዋን በሕይወት እንደማትቀጥል ያምን የነበረ ከመሆኑም በላይ በሰው ውስጥ ያለ ዘላለማዊ ነገር ቢኖር የማይጨበጥና ረቂቅ የሆነ የማሰብ ችሎታ እንደሆነ ገልጿል። ነፍስን በተመለከተ የተሰጠው ይህ አስተያየት ነፍሳት ከሞት በኋላም በሕይወት ይቀጥላሉ ከሚለው የቤተ ክርስቲያን እምነት ጋር የሚጣጣም አልነበረም። ስለዚህ አኩዊናስ ነፍስ የማትሞት መሆኗን በቂ ማስረጃ በማቅረብ ማሳመን ይቻላል በሚል አርስቶትል ስለ ነፍስ የነበረውን አመለካከት አሻሻሉት። በመሆኑም ነፍስ አትሞትም የሚለው የቤተ ክርስቲያን እምነት ሳይለወጥ ቀረ።

17, 18. (ሀ) በ16ኛው መቶ ዘመን የተካሄደው ተሃድሶ ስለ ነፍስ የሚሰጠውን ትምህርት ለውጦታልን? (ለ) አብዛኞቹ የሕዝበ ክርስትና የእምነት ክፍሎች ነፍስ አትሞትም በሚለው ጽንሰ ሐሳብ ላይ ያላቸው አቋም ምንድን ነው?

17 የሥልጣኔ ዘመን መባቻ በሆኑት በ14ኛውና በ15ኛው መቶ ዘመናት የፕላቶ ፍልስፍና እንደገና ተወዳጅነት እያገኘ ሄዶ ነበር። እንዲያውም በኢጣሊያ የነበረው የታወቀው የማዲቺ ቤተሰብ በፕላቶ ፍልስፍና ላይ የሚካሄደውን ጥናት ለማስፋፋት በፍሎረንስ አንድ አካዳሚ እንዲቋቋም አስተዋጽኦ አድርጓል። በ16ኛውና በ17ኛው መቶ ዘመናት የአርስቶትል ፍልስፍና እየተዳከመ ሄደ። በተጨማሪም በ16ኛው መቶ ዘመን የተካሄደው ተሃድሶ ስለ ነፍስ ይሰጥ በነበረው ትምህርት ላይ ለውጥ አላመጣም። የፕሮቴስታንት የተሃድሶ አራማጆች በመንጽሔ ትምህርት ላይ ክርክር አንስተው የነበረ ቢሆንም ዘላለማዊ ቅጣት ወይም ሽልማት አለ የሚለውን አስተሳሰብ ተቀብለዋል።

18 በዚህ መንገድ ነፍስ አትሞትም የሚለው ትምህርት በአብዛኞቹ የሕዝበ ክርስትና የእምነት ክፍሎች ውስጥ ሥር ሰደደ። ይህን በመገንዘብ አንድ አሜሪካዊ ምሁር እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ለአብዛኛው የምዕራቡ ዓለም ኅብረተሰብ ሃይማኖት ከዘላለማዊነት ሌላ ትርጉም የለውም። የዘላለማዊነት ምንጭ አምላክ ነው።”

ዘላለማዊነትና እስልምና

19. እስልምና የተመሠረተው መቼ ነው? በማንስ አማካኝነት?

19 እስልምና የተመሠረተው መሐመድ በ40 ዓመቱ ገደማ ነቢይ ነኝ ብሎ በተነሳ ጊዜ ነበር። ሙስሊሞች ራእዮች የተገለጡለት ከ610 እዘአ ገደማ አንስቶ በ632 እዘአ እስከሞተበት ጊዜ ድረስ ባሉት ከ20 እስከ 23 የሚደርሱ ዓመታት ውስጥ ነው ብለው ያምናሉ። እነዚህ ራእዮች የሙስሊም ቅዱስ መጽሐፍ በሆነው በቁራን ውስጥ ተመዝግበው ይገኛሉ። እስልምና ወደ ሕልውና በመጣበት ጊዜ ፕላቶ ነፍስን በተመለከተ የነበረው ጽንሰ ሐሳብ ወደ አይሁድና ሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶች ሰርጎ ገብቶ ነበር።

20, 21. ሙስሊሞች ስለ ወዲያኛው ሕይወት ምን ብለው ያምናሉ?

20 ሙስሊሞች እምነታቸው ለጥንቶቹ ታማኝ ዕብራውያንና ክርስቲያኖች የተገለጡት ራእዮች የመጨረሻ ከፍተኛ ውጤት እንደሆነ አድርገው ያምናሉ። ቁራን ከዕብራይስጥም ሆነ ከግሪክ ቅዱሳን ጽሑፎች ይጠቅሳል። ሆኖም ቁራን ነፍስ አትሞትም በሚለው ትምህርት ረገድ በእነዚህ ጽሑፎች ላይ የሌለ ሐሳብ ይዟል። ቁራን ሰው ከሞተ በኋላ በሕይወት የምትቀጥል ነፍስ አለችው ብሎ ያስተምራል። በተጨማሪም ስለ ሙታን ትንሣኤ፣ ስለ ፍርድ ቀንና ነፍስ በሰማያዊ ገነት የአትክልት ስፍራ ውስጥ ስለምታገኘው ሕይወት አለዚያም ደግሞ በእሳታማ ሲኦል ውስጥ ስለሚደርስባት ቅጣት ይናገራል።

21 ሙስሊሞች ሰው ከሞተ በኋላ ነፍሱ ባርዛክ ወይም “ክፍል” ተብሎ በሚጠራ “ሰዎች ከሞቱ በኋላ እስከ ፍርድ ቀን ድረስ በሚቆዩበት ቦታ ወይም ሁኔታ” ትቆያለች ይላሉ። (ሱራ 23:​99,100 ቅዱስ ቁራን፣ የግርጌ ማስታወሻ) ነፍስ የሚፈጸመው ነገር ሁሉ ይሰማታል፤ ሰውየው ክፉ ከነበረ በዚያ ሥፍራ “የመቃብር ቅጣት” የሚባለው ነገር ይደርስባታል፤ ሰውየው ታማኝ ከነበረ ደግሞ ትደሰታለች። ሆኖም ታማኞቹም እንኳ ሳይቀሩ በሕይወት በነበሩበት ጊዜ በፈጸሟቸው ጥቂት ኃጢአቶች ሳቢያ ትንሽ እንዲሰቃዩ ይደረጋል። የሽግግሩ ወቅት አብቅቶ በፍርድ ቀን እያንዳንዱ ዘላለማዊ ዕጣውን ይቀበላል።

22. አንዳንድ የአረብ ፈላስፎች የነፍስን ዕጣ በተመለከተ ምን የተለያዩ ጽንሰ ሐሳቦች አቅርበዋል?

22 ነፍስ አትሞትም የሚለው ትምህርት በአይሁድና በሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶች ውስጥ ብቅ ያለው የፕላቶ ፍልስፍና ባሳደረው ተጽዕኖ ነው፤ በእስልምና ሃይማኖት ውስጥ ግን ጽንሰ ሐሳቡ ሃይማኖቱ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ያለ ነው። ይህ ማለት ግን የአረብ ምሁራን የእስልምናን ትምህርቶች ከግሪክ ፍልስፍና ጋር ለመቀላቀል ምንም ዓይነት ሙከራ አላደረጉም ማለት አይደለም። እንዲያውም የአርስቶትል ፍልስፍና በአረቡ ዓለም ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል። እንደ አቪሴና እና አቬሮዊዝ ያሉት የታወቁ የአረብ ምሁራን በአርስቶትል ንድፈ ሐሳብ ላይ የየራሳቸውን ትንተና ሰጥተዋል። ይሁን እንጂ የግሪክን ፍልስፍና እስልምና ስለ ነፍስ ከሚያስተምረው ትምህርት ጋር ለማጣጣም ባደረጉት ጥረት የተለያዩ ጽንሰ ሐሳቦች ሊይዙ ችለዋል። ለምሳሌ ያህል አቪሴና የሰው ነፍስ አትሞትም ሲል አቬሮዊዝ ደግሞ ይህን አመለካከት ተቃውሟል። ያም ሆነ ይህ ግን ነፍስ አትሞትም የሚለው የሙስሊሞች እምነት አልተለወጠም።

23. የአይሁድ፣ የሕዝበ ክርስትናና የእስልምና ሃይማኖቶች ነፍስ አትሞትም በሚለው ጉዳይ ላይ ምን አቋም አላቸው?

23 እንግዲያው የአይሁድ፣ የሕዝበ ክርስትናም ሆነ የእስልምና ሃይማኖቶች ነፍስ አትሞትም የሚለውን መሠረተ ትምህርት እንደሚያስተምሩ በግልጽ መረዳት ይቻላል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.14 በሦስተኛው መቶ ዘመን በሮም ውስጥ ፕሎታይነስ በፕላቶ ፍልስፍና ላይ ተመርኩዞ የፈለሰፈው አዲስ ዓይነት ፍልስፍና ማለትም የኒኦፕላቶኒዝም ተከታይ ማለት ነው።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ታላቁ እስክንድር የተቀዳጀው ድል የግሪክና የአይሁድ ባሕሎች እንዲደባለቁ አድርጓል

[በገጽ 15 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ከላይ የሚታየው ኦሪጀንና ኦውግስቲን የፕላቶን ፍልስፍና ከክርስትና ጋር ለመቀላቀል ሞክረዋል

[በገጽ 16 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ከላይ የሚታየው አቪሴና የሰው ነፍስ አትሞትም ሲል ገልጿል። አቬሮዊዝ ደግሞ ይህን አመለካከት ተቃውሟል