በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አስተማማኝ ተስፋ

አስተማማኝ ተስፋ

አስተማማኝ ተስፋ

“የሰው ልጅ ከተወለደበት ቅጽበት አንስቶ በማንኛውም ጊዜ ሊሞት ይችላል፤ በመሆኑም አንድ ቀን ይህ ሐቅ እውን መሆኑ አይቀርም።”​—⁠አርኖልድ ቶይንቤ፣ ብሪታንያዊ ታሪክ ጸሐፊ

1. የሰው ልጅ የትኛውን ሐቅ ለመቀበል ተገዷል? ይህስ ምን ጥያቄዎች ያስነሳል?

ከላይ የተጠቀሰውን ታሪካዊ ሐቅ ማን ሊክድ ይችላል? የሰው ልጅ መራራውን የመሞት ሐቅ ለመቀበል ተገዷል። የምንወደው ሰው ሲሞት የከንቱነት ስሜት ይሰማናል! በመሆኑም በሞት ያጣነውን ሰው ዳግመኛ ማግኘት ጨርሶ የማይታሰብ ነገር ይሆንብናል። በሞት የተለዩንን የምንወዳቸውን ሰዎች ዳግመኛ ልናገኛቸው እንችል ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሙታን ምን ተስፋ ይሰጣል? የሚከተለውን ታሪክ ተመልከት።

‘ወዳጃችን ሞቶአል’

2-5. (ሀ) ኢየሱስ ወዳጁ አልዓዛር ሲሞት ከሞት የማስነሳት ፍላጎትና ችሎታ እንዳለው ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) ተአምራዊው ትንሣኤ አልዓዛርን ዳግመኛ ሕያው ያደረገው ከመሆኑም በላይ ሌላ ምን ነገር አከናውኗል?

2 ጊዜው 32 እዘአ ነው። አልዓዛር ከኢየሩሳሌም 3 ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ በምትገኝ ቢታንያ ተብላ በምትጠራ አነስተኛ ከተማ ማርታና ማርያም ከተባሉ እህቶቹ ጋር ይኖር ነበር። እነዚህ ሰዎች የኢየሱስ የቅርብ ወዳጆች ነበሩ። አንድ ቀን አልዓዛር በጠና ይታመማል። ሁኔታው ያሳሰባቸው እህቶቹ ወዲያውኑ ከዮርዳኖስ ወንዝ ባሻገር ለነበረው ለኢየሱስ መልእክት ላኩበት። ኢየሱስ አልዓዛርንና እህቶቹን ይወዳቸው ስለነበረ ብዙም ሳይቆይ ወደ ቢታንያ ለመሄድ ተነሳ። ኢየሱስ በመንገድ ላይ ሳሉ ደቀ መዛሙርቱን “ወዳጃችን አልዓዛር ተኝቶአል፤ ነገር ግን ከእንቅልፉ ላስነሣው እሄዳለሁ” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ ምን ማለቱ እንደሆነ ወዲያውኑ ስላልገባቸው በግልጽ “አልዓዛር ሞተ” አላቸው።​—⁠ዮሐንስ 11:​1-15

3 ማርታ፣ ኢየሱስ ወደ ቢታንያ እየመጣ መሆኑን ስታውቅ ልትቀበለው ወጣች። ኢየሱስ የደረሰባት ሐዘን በጣም ስለተሰማው “ወንድምሽ ይነሣል” ሲል አጽናናት። ማርታ “በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ እንዲነሣ አውቃለሁ” ብላ መለሰችለት። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል” አላት።​—⁠ዮሐንስ 11:​20-25

4 ከዚያ በኋላ ኢየሱስ ወደ መቃብሩ ሄደና መቃብሩ የተዘጋበትን ድንጋይ እንዲያነሱ አዘዘ። ጮክ ብሎ ከጸለየ በኋላ “አልዓዛር ሆይ፣ ወደ ውጭ ና” ብሎ አዘዘ። ሁሉም ወደ መቃብሩ አተኩረው እያዩ ሳለ አልዓዛር ከመቃብሩ ውስጥ ወጣ። ኢየሱስ ለአራት ቀናት ሞቶ የነበረውን ሰው ዳግመኛ ወደ ሕይወት በመመለስ አልዓዛርን ከሞት አስነሳው!​—⁠ዮሐንስ 11:​38-44

5 ማርታ ቀድሞውንም በትንሣኤ ተስፋ ታምን ነበር። (ዮሐንስ 5:​28, 29፤ 11:​23, 24) አልዓዛርን ዳግመኛ ሕያው በማድረግ የተፈጸመው ተአምር የማርታን እምነት ያጠናከረው ከመሆኑም በላይ ሌሎች እምነት እንዲያድርባቸው አድርጓል። (ዮሐንስ 11:​45) ይሁን እንጂ “ትንሣኤ” የሚለው ቃል ቀጥተኛ ትርጉሙ ምንድን ነው?

“ይነሣል”

6. “ትንሣኤ” የሚለው ቃል ምን ማለት ነው?

6 “ትንሣኤ” የሚለው ቃል አናስታሲስ ከተባለው የግሪክኛ ቃል የተተረጎመ ሲሆን ቃል በቃል ሲተረጎም “ዳግመኛ መቆም” ማለት ነው። ግሪክኛውን የተረጎሙት የዕብራይስጥ ተርጓሚዎች አናስታሲስ የሚለውን ቃል ቴኪያት ሐሜቲም በሚሉት የዕብራይስጥ ቃላት የፈቱት ሲሆን ትርጉሙም “የሙታን ወደ ሕይወት መመለስ” ማለት ነው። * ስለዚህ ትንሣኤ ሞቶ የነበረ ግለሰብ ቀድሞ የነበረው ሕይወት እንዲመለስለት በማድረግ በሞት አማካኝነት በድን ከነበረበት ሁኔታ ማስነሳትን ይጨምራል።

7. ይሖዋ አምላክም ሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰዎችን ከሞት ማስነሳት የማያስቸግራቸው ለምንድን ነው?

7 ይሖዋ አምላክ ወሰን የሌለው ጥበብና ፍጹም የሆነ የማስታወስ ችሎታ ያለው በመሆኑ አንድን ሰው በቀላሉ ሊያስነሳው ይችላል። ሙታን በሕይወት በነበሩበት ዘመን የነበራቸውን አኗኗር፣ ባሕርያቸውን፣ የግል ታሪካቸውንና ማንነታቸውን በተመለከተ ያለውን እያንዳንዱን ዝርዝር ሁኔታ ማስታወስ ለእሱ ቀላል ነገር ነው። (ኢዮብ 12:​13፤ ከኢሳይያስ 40:​26 ጋር አወዳድር።) በተጨማሪም ይሖዋ የሕይወት ምንጭ ነው። ስለዚህ አዲስ አካል በማዋቀር የቀድሞውን ስብዕና አላብሶ ያንኑ ሰው ዳግመኛ ሕያው ሊያደርገው ይችላል። ከዚህም በላይ በአልዓዛር ሁኔታ ላይ እንደታየው ኢየሱስ ክርስቶስ ሙታንን ለማስነሳት ፍላጎቱም ሆነ ችሎታው አለው።​—⁠ከሉቃስ 7:​11-17 እና 8:​40-56 ጋር አወዳድር።

8, 9. (ሀ) ትንሣኤና ነፍስ አትሞትም የሚለው ትምህርት የማይጣጣሙት ለምንድን ነው? (ለ) ከሞት መላቀቅ የሚቻልበት መፍትሔ ምንድን ነው?

8 ይሁን እንጂ ቅዱስ ጽሑፋዊው የትንሣኤ ትምህርት ነፍስ አትሞትም ከሚለው መሠረተ ትምህርት ጋር አይጣጣምም። ነፍስ የማትሞትና ከሞት በኋላም በሕይወት የምትቀጥል ነገር ከሆነች ማንም ሰው ከሞት መነሳት ወይም ዳግመኛ ሕያው መሆን አያስፈልገውም። ማርታ ከሞት በኋላ በሌላ ሥፍራ ስለምትኖር የማትሞት ነፍስ ምንም የጠቀሰችው ነገር የለም። አልዓዛር በሕይወት ለመቀጠል ወደ ሌላ መንፈሳዊ ዓለም ተጉዟል የሚል እምነት አልነበራትም። ከዚህ ይልቅ አምላክ የሞትን ውጤቶች ለመቀልበስ ዓላማ እንዳለው ታምን ነበር። “በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ እንዲነሣ አውቃለሁ” ብላለች። (ዮሐንስ 11:​23, 24) አልዓዛርም ቢሆን ከሞት በኋላ ስላለ ሕይወት ምንም የተናገረው ነገር የለም። ምንም የሚናገረው ነገር አልነበረም።

9 መጽሐፍ ቅዱስ በሚለው መሠረት ነፍስ ሟች ከመሆኗም በላይ ለሞት መፍትሔው ትንሣኤ ነው። ሆኖም አዳም በምድር ላይ ከኖረበት ዘመን አንስቶ በቢልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሞተዋል። ታዲያ የሚነሱት እነማን ናቸው? የትስ ነው የሚነሱት?

‘በመታሰቢያ መቃብር ያሉት ሁሉ’

10. ኢየሱስ በመታሰቢያ መቃብር ውስጥ ያሉትን በተመለከተ ምን ተስፋ ሰጥቷል?

10 ኢየሱስ ክርስቶስ “በመቃብር [“በመታሰቢያ መቃብር፣” NW] ያሉት ሁሉ ድምፁን [የኢየሱስን] የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ . . . ይወጣሉ” ብሏል። (ዮሐንስ 5:​28, 29) አዎ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ይሖዋ በአእምሮው የያዛቸው ሁሉ እንደሚነሱ ተስፋ ሰጥቷል። በቢልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በሕይወት ኖረው አልፈዋል። ከእነዚህ መካከል አምላክ በአእምሮው የያዛቸውና ትንሣኤያቸውን በመጠባበቅ ላይ የሚገኙት የትኞቹ ናቸው?

11. ከሞት የሚነሱት እነማን ናቸው?

11 የይሖዋ አገልጋዮች ሆነው የጽድቅ ጎዳና የተከተሉ ሁሉ ይነሣሉ። ሆኖም በሚልዮን የሚቆጠሩት ሌሎች ሰዎች ከአምላክ የጽድቅ መስፈርቶች ጋር ይስማሙ እንደሆነና እንዳልሆነ ማሳየት የሚችሉበት አጋጣሚ ሳያገኙ የሞቱ ናቸው። አንድም ይሖዋ ያወጣቸውን ብቃቶች አያውቁም፤ አለዚያም ደግሞ አስፈላጊውን ለውጥ ለማድረግ በቂ ጊዜ አላገኙም። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ጻድቃንም ዓመፀኞችም ከሙታን እንደሚነሱ’ ስለሚናገር እነዚህም ሰዎች ቢሆን በአምላክ አእምሮ ውስጥ ያሉ ናቸው።​—⁠ሥራ 24:​15

12. (ሀ) ሐዋርያው ዮሐንስ ትንሣኤን በተመለከተ ምን ራእይ ተመልክቷል? (ለ) ወደ “እሳት ባሕር” የተጣለው ምንድን ነው? ይህ አባባልስ ምን ማለት ነው?

12 ሐዋርያው ዮሐንስ ከሞት የተነሱ ሰዎች በአምላክ ዙፋን ፊት ቆመው የሚያሳይ አስደሳች ራእይ ተመልክቷል። ይህን ራእይ በመግለጽ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ባሕርም በእርሱ ውስጥ ያሉትን ሙታን ሰጠ፣ ሞትና ሲኦልም በእነርሱ ዘንድ ያሉትን ሙታን ሰጡ፣ እያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን ተከፈለ። ሞትና ሲኦልም በእሳት ባሕር ውስጥ ተጣሉ። ይህም የእሳት ባሕር ሁለተኛው ሞት ነው።” (ራእይ 20:​12-14) ይህ ምን ማለት እንደሆነ እስቲ አስበው! በአምላክ አእምሮ ውስጥ ያሉት ሙታን ሁሉ የሰው ልጆች የጋራ መቃብር ከሆነው ከሔድስ ወይም ከሲኦል ይወጣሉ። (መዝሙር 16:​10፤ ሥራ 2:​31) ከዚያም “ሞትና ሲኦል” ሙሉ በሙሉ መጥፋትን ወደሚያመለክተው ወደ “እሳት ባሕር” ይጣላሉ። የሰው ልጆች የጋራ መቃብር ከናካቴው ይጠፋል።

የሚነሱት የት ነው?

13. አምላክ የተወሰኑ ሰዎች ከሞት ተነሥተው ሰማያዊ ሕይወት የሚያገኙበትን ዝግጅት ያደረገው ለምንድን ነው? ይሖዋ ለእነዚህ ሰዎች ምን ዓይነት አካል ይሰጣቸዋል?

13 አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ወንዶችና ሴቶች ከሞት ተነስተው ሰማያዊ ሕይወት ያገኛሉ። እነዚህ ሰዎች ነገሥታትና ካህናት ሆነው ከክርስቶስ ጋር የሚገዙ ከመሆናቸውም በላይ የሰው ዘር ከመጀመሪያው ሰው ከአዳም የወረሳቸውን የሞት ውጤቶች በሙሉ በማስወገዱ ሥራ ይካፈላሉ። (ሮሜ 5:​12፤ ራእይ 5:​9, 10) መጽሐፍ ቅዱስ በሚገልጸው መሠረት ቁጥራቸው 144,000 ብቻ ሲሆን ከታማኞቹ ሐዋርያት ጀምሮ ከክርስቶስ ተከታዮች መካከል የተመረጡ ናቸው። (ሉቃስ 22:​28-30፤ ዮሐንስ 14:​2, 3፤ ራእይ 7:​4፤ 14:​1, 3) ከሞት የሚነሱት እነዚህ ሰዎች በሰማይ መኖር እንዲችሉ ይሖዋ ለእያንዳንዳቸው መንፈሳዊ አካል ይሰጣቸዋል።​—⁠1 ቆሮንቶስ 15:​35, 38, 42-45፤ 1 ጴጥሮስ 3:​18

14, 15. (ሀ) አብዛኞቹ ሙታን ከሞት ሲነሱ ምን ዓይነት ሕይወት ያገኛሉ? (ለ) ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች ምን በረከቶች ያገኛሉ?

14 ይሁን እንጂ ከሞቱት መካከል አብዛኞቹ ከሞት ተነሥተው ምድራዊ ሕይወት ያገኛሉ። (መዝሙር 37:​29፤ ማቴዎስ 6:​10) ምን ዓይነት ምድር ላይ ነው የሚነሱት? በአሁኑ ጊዜ ምድር በግጭት፣ በደም መፋሰስ፣ በብክለትና በጠብ ተሞልታለች። ሙታን ዳግመኛ ሕያው የሚሆኑት በእንዲህ ዓይነቷ ምድር ላይ ከሆነ የሚያገኙት ደስታ ጊዜያዊ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ ፈጣሪ በአሁኑ ጊዜ ያለውን በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ያለ የዓለም ኅብረተሰብ በቅርቡ እንደሚያጠፋው ቃል ገብቷል። (ምሳሌ 2:​21, 22፤ ዳንኤል 2:​44) ከዚያ በኋላ ጻድቅ የሆነ አዲስ ሰብዓዊ ኅብረተሰብ ማለትም “አዲስ ምድር” እውን ይሆናል። (2 ጴጥሮስ 3:​13) “በዚያም የሚቀመጥ ታምሜአለሁ አይልም።” (ኢሳይያስ 33:​24) ሞት የሚያስከትለው ሥቃይ እንኳ ሳይቀር ይወገዳል፤ ምክንያቱም አምላክ “እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና።”​—⁠ራእይ 21:​4

15 አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ ገሮች “በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል።” (መዝሙር 37:​11) የክርስቶስ ኢየሱስና የ144,000 ተባባሪ ገዥዎቹ ሰማያዊ መንግሥት ታዛዥ የሆኑትን የሰው ልጆች ቀስ በቀስ የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን አዳምና ሔዋን ወዳጡት የፍጽምና ደረጃ ያደርሷቸዋል። ከሞት የሚነሡትም ሰዎች በዚያን ጊዜ ከሚኖሩት የምድር ነዋሪዎች መካከል ይሆናሉ።​—⁠ሉቃስ 23:​42, 43

16-18. ትንሣኤ ለሟች ቤተሰቦች ምን ዓይነት ደስታ ያስገኝላቸዋል?

16 መጽሐፍ ቅዱስ ትንሣኤ ለሟቾቹ ቤተሰቦች ምን ዓይነት ደስታ እንደሚያስገኝ የሚያሳይ ፍንጭ ይሰጠናል። በናይን ትኖር የነበረችው መበለት ኢየሱስ ወደ ቀብር ሥነ ሥርዓት እየተጓዙ የነበሩትን ሰዎች አስቁሞ አንድ ልጅዋን ከሞት ሲያስነሳላት ምን ዓይነት ደስታ ተሰምቷት እንደነበረ ገምተው! (ሉቃስ 7:​11-17) ከጊዜ በኋላ ኢየሱስ በገሊላ ባሕር አቅራቢያ የ12 ዓመቷን ልጃገረድ ዳግመኛ ሕያው ሲያደርጋት ወላጆቿ “እጅግ ፈነደቁ (NW)።”​—⁠ማርቆስ 5:​21-24, 35-42፤ በተጨማሪም 1 ነገሥት 17:​17-24ንና 2 ነገሥት 4:​32-37ን ተመልከት።

17 በአሁኑ ጊዜ በሞት አንቀላፍተው የሚገኙ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከሞት ሲነሱ ሰላማዊ በሆነ አዲስ ዓለም ውስጥ የመኖር አጋጣሚ ያገኛሉ። ይህ ሁኔታ በዚህ ብሮሹር መግቢያ ላይ ለተጠቀሱት ለቶሚና ለነጋዴው እንዴት ያለ አስደሳች አጋጣሚ እንደሚፈጥርላቸው እስቲ አስበው! ቶሚ ገነት በሆነች ምድር ላይ ከሞት ሲነሳ እናቱ የምታውቀው ያው ቶሚ ይሆናል፤ ሆኖም ሕመም የሚባል ነገር አይኖረውም። እናቱ አጠገቡ ሆና ልትደባብሰው ልታቅፈውና ፍቅሯን ልትገልጽለት ትችላለች። በተመሳሳይም በሕንድ ይኖሩ የነበሩት ነጋዴም ማብቂያ በሌለው የዳግም መወለድ ዑደት ተጠፍሮ ከመያዝ ይልቅ አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ ዓይናቸውን ገልጠው ልጆቻቸውን የማየት ዕጹብ ድንቅ የሆነ ተስፋ ይጠብቃቸዋል።

18 በአሁኑ ጊዜ በሕይወት ያሉ ሰዎችም ስለ ነፍስ፣ ስንሞት ስለሚገጥመን ሁኔታና ስለ ትንሣኤ ተስፋ እውነቱን ማወቃቸው በሕይወታቸው ላይ ትልቅ ለውጥ ሊያሳድር ይችላል። ይህ ሊሆን የሚችለው እንዴት እንደሆነ እንመልከት።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.6 “ትንሣኤ” የሚለው ቃል በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ባይገኝም እንኳ የትንሣኤ ተስፋ በኢዮብ 14:​13፣ በዳንኤል 12:​13 እና በሆሴዕ 13:​14 ላይ ቁልጭ ብሎ ተገልጿል።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ትንሣኤ ዘላቂ ደስታ ያስገኛል