በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከሞት በኋላ ሕይወት አለ?

ከሞት በኋላ ሕይወት አለ?

ከሞት በኋላ ሕይወት አለ?

“ዛፍ ቢቆረጥ ደግሞ ያቆጠቁጥ ዘንድ . . . ተስፋ አለው። በውኑ ሰው ከሞተ ተመልሶ ሕያው ይሆናልን?”​—⁠ሙሴ፣ ጥንታዊ ነቢይ

1-3. ብዙዎች የሚወዱትን ሰው በሞት ሲያጡ መጽናኛ ለማግኘት የሚሞክሩት እንዴት ነው?

በኒው ዮርክ ከተማ በአንድ የሬሳ ማቆያ ክፍል ውስጥ የሟቹ ቤተሰቦችና ጓደኞች ክፍት በሆነው የሬሳ ሳጥን አጠገብ ጸጥ ብለው በሰልፍ ያልፋሉ። የ17 ዓመቱን ልጅ አስከሬን ትኩር ብለው ይመለከታሉ። የትምህርት ቤት ጓደኞቹ ሊለዩት አልቻሉም። ኬሞቴራፒ የተባለው ሕክምና ፀጉሩን የጨረሰው ከመሆኑም በላይ ይዞት የነበረው የካንሰር በሽታ ሰውነቱን አመንምኖታል። እውነት ይህ ጓደኛቸው ነው? ከጥቂት ወራት በፊት ብዙ ሐሳብ የሚያፈልቅ፣ በርካታ ጥያቄዎች በአእምሮው የሚመላለሱበትና ጥሩ ጉልበት የነበረው ተጫዋች ልጅ ነበር! በሐዘን የተዋጠችው እናቱ ልጅዋ አሁንም በሆነ መንገድ በሕይወት እንዳለ አድርጋ በማሰብ መጠነኛ ተስፋና መጽናኛ ለማግኘት እየሞከረች ነው። እንባዋን እያፈሰሰች ከዚህ በፊት በተማረችው መሠረት “ይህን ጊዜ ቶሚ ደስ ብሎታል። አምላክ እኮ ቶሚ በሰማይ ከእሱ ጋር እንዲሆን ስለፈለገ ወስዶታል” እያለች በተደጋጋሚ ትናገራለች።

2 ወደ 11,000 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቃ በምትገኘው ጃምናጋር በምትባል አንዲት የሕንድ ከተማ ሦስት ወንዶች ልጆች ነጋዴ የነበሩትን የ58 ዓመት አባታቸውን አስከሬን ለማቃጠያ በተረበረበው እንጨት ላይ ተጋግዘው አኖሩ። ፀሐያማ በሆነው ቀን ረፋዱ ላይ የመጀመሪያው ልጅ የተከመረውን እንጨት በችቦ በመለኮስና ጥሩ መዓዛ ያለው የተለያዩ ቅመማ ቅመሞችና የዕጣን ድብልቅ በአባቱ በድን አካል ላይ በማፍሰስ አስከሬኑን የማቃጠሉ ሥነ ሥርዓት እንዲጀመር አደረገ። እሳቱ ሲቀጣጠል የሚሰጠው ድምፅ ብራህማው እየደጋገመ በሚናገራቸው “ለዘላለም የማትሞተው ነፍስ የሁሉ የበላይ ከሆነው ኃይል ጋር አንድ ለመሆን የምታደርገውን ጥረት እንድትገፋበት እንመኛለን” የሚል ትርጉም ባላቸው የሳንስክሪት ማንትራዎች ቃላት ይዋጣል።

3 ሦስቱ ወንድማማቾች አስከሬኑን የማቃጠሉን ሥነ ሥርዓት እየተመለከቱ ሁሉም በልባቸው ‘ከሞት በኋላ ሕይወት አለ በሚለው ጽንሰ ሐሳብ አምናለሁ?’ እያሉ ራሳቸውን ይጠይቃሉ። በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተማሩ እንደመሆናቸው መጠን ለዚህ ጥያቄ የተለያየ ምላሽ ይሰጣሉ። ታናሽየው ልጅ ውድ አባታቸው በሪኢንካርኔሽን ተለውጠው የተሻለ ሕይወት እንደሚያገኙ ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ነው። መካከለኛው ልጅ ሙታን ልክ እንቅልፍ እንደተኛ ሰው ምንም ነገር አይሰሙም ወይም አያውቁም የሚል እምነት አለው። ታላቅየው ደግሞ ስንሞት ምን እንደምንሆን ማንም በእርግጠኝነት መናገር አይችልም የሚል እምነት ስላለው ሞት እንዲሁ የማይቀር ሐቅ መሆኑን ብቻ ለመቀበል ይሞክራል።

ጥያቄው አንድ፣ መልሱ ግን ብዙ

4. የሰውን ዘር ለብዙ ዘመናት ግራ ሲያጋባ የኖረው የትኛው ጥያቄ ነው?

4 ከሞት በኋላ ሕይወት አለ? የሚለው ጥያቄ የሰውን ልጅ ለብዙ ሺህ ዓመታት ግራ ሲያጋባ የኖረ ጥያቄ ነው። “የሃይማኖት ምሁራን እንኳ ሳይቀሩ [ይህ ጥያቄ] ሲቀርብላቸው አፋቸው ይተሳሰራል” ሲሉ ሃንስ ኩንግ የተባሉ የካቶሊክ ምሁር ተናግረዋል። ላለፉት በርካታ ዘመናት በየትኛውም ኅብረተሰብ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ይህን ርዕሰ ጉዳይ ሲያወጡና ሲያወርዱ ኖረዋል፤ ለጥያቄው ሥፍር ቁጥር የሌላቸው መልሶች ይሰጣሉ።

5-8. የተለያዩ ሃይማኖቶች ከሞት በኋላ አለ ስለሚባለው ሕይወት ምን እያሉ ያስተምራሉ?

5 ብዙ ስመ ክርስቲያኖች በመንግሥተ ሰማያትና በሲኦል ያምናሉ። ሂንዱዎች ደግሞ አንድ ሰው ከሞተ በኋላ በሪኢንካርኔሽን ተለውጦ መኖር ይቀጥላል የሚል እምነት አላቸው። በእስልምና ሃይማኖት ማዕከል ረዳት የሆኑት አሚር ሚአዊያ ስለ እስልምና እምነት ሲናገሩ “ከሞት በኋላ የፍርድ ቀን እንዳለ እናምናለን፤ አምላክ ፊት ማለትም አላህ ፊት ስትቀርቡ ልክ ችሎት ፊት እንደቀረባችሁ ያህል ነው” ብለዋል። በእስልምና እምነት መሠረት አላህ የእያንዳንዱን ሰው አኗኗር ይመረምርና ወይ ወደ ገነት ያስገባዋል አለዚያም እሳታማ ሲኦል ይከተዋል።

6 በስሪ ላንካ ቡድሂስቶችም ሆኑ ካቶሊኮች የቤተሰባቸው አባል ሲሞት የቤቱን በሮችና መስኮቶች ወለል አድርገው ይከፍታሉ። ፋኖስ አብርተው የሬሳ ሳጥኑን የሟቹ እግር ፊት ለፊት ባለው በር ትይዩ እንዲሆን አድርገው ያስቀምጡታል። እንዲህ ማድረጋቸው የሟቹ መንፈስ ወይም ነፍስ ከቤቱ እንዲወጣ ምቹ ሁኔታ ይፈጥርለታል ብለው ያምናሉ።

7 በዌስተርን አውስትራሊያ ዩኒቨርሲቲ የሚሠሩት ሮናልድ ኤም በርንት የአውስትራሊያ አቦርጂኖች “ሰዎች ሊጠፋ የማይችል መንፈስ አላቸው” ብለው ያምናሉ ሲሉ ገልጸዋል። አንዳንድ የአፍሪካ ጎሳዎች ተራ ሰዎች ሲሞቱ ጣረ ሞት የሚሆኑ ሲሆን ታዋቂ ሰዎች ደግሞ መናፍስት በመሆን ክብር የሚሰጣቸውና አቤቱታ የሚቀርብላቸው የማይታዩ የማኅበረሰቡ መሪዎች ሆነው ያገለግላሉ ብለው ያምናሉ።

8 በአንዳንድ አገሮች የሙታን ነፍሳት የሚባሉትን በተመለከተ ያሉት እምነቶች የአካባቢው ባሕልና የስመ ክርስትና ትምህርቶች ድብልቅ ውጤቶች ናቸው። ለምሳሌ ያህል በምዕራብ አፍሪካ የሚገኙ ብዙ ካቶሊኮችና ፕሮቴስታንቶች አንድ ሰው ሲሞት ማንም ሰው የሟቹን መንፈስ እንዳያይ ለማድረግ ሲባል መስታወቶችን ሁሉ የመሸፈን ልማድ አላቸው። ከዚያም ሰውየው ከሞተ ከ40 ቀን በኋላ ቤተሰቦቹና ወዳጆቹ የሰውየውን ነፍስ ወደ ሰማይ ማረግ በማስመልከት ድግስ ይደግሳሉ።

የጋራ ጭብጥ

9, 10. አብዛኞቹ ሃይማኖቶች በየትኛው መሠረታዊ እምነት ይስማማሉ?

9 ስንሞት ምን እንሆናለን ለሚለው ጥያቄ የሚሰጡት መልሶች እንደ መልስ ሰጪዎቹ ባህልና እምነት የተለያዩ ናቸው። ሆኖም አብዛኞቹ ሃይማኖቶች በአንድ መሠረታዊ ሐሳብ ላይ ይስማማሉ:- የማትሞትና ከሞት በኋላ በሕይወት የምትቀጥል ነፍስ፣ መንፈስ ወይም ደግሞ ጣረ ሞት በሰው ውስጥ አለች ይላሉ።

10 ነፍስ አትሞትም የሚለው እምነት በሕዝበ ክርስትና ሥር በሚገኙ በሺህ የሚቆጠሩ ሃይማኖቶችና ኑፋቄዎች ሁሉ ዘንድ ይታመንበታል ማለት ይቻላል። በአይሁድ እምነት ውስጥም ትልቅ ቦታ የሚሰጠው መሠረተ ትምህርት ነው። በሂንዱኢዝም ሃይማኖት ይህ እምነት አንድ ሰው ከሞተ በኋላ በሪኢንካርኔሽን ተለውጦ መኖር ይቀጥላል ለሚለው ትምህርት ዋና መሠረት ነው። እስላሞች ነፍስ ከሥጋ ጋር የምትጣመር ነገር እንደሆነችና ሥጋው ከሞተም በኋላ በሕይወት የምትቀጥል ነገር እንደሆነች አድርገው ያምናሉ። እንደ አፍሪካን አኒሚዝም፣ ሺንቶና አልፎ ተርፎም ቡዲዝምን የመሳሰሉ ሌሎች እምነቶች በዚሁ ጭብጥ ላይ ተመሥርተው የተለያዩ ትምህርቶች ያስተምራሉ።

11. አንዳንድ ምሁራን ነፍስ አትሞትም የሚለውን አስተሳሰብ እንዴት ይመለከቱታል?

11 አንዳንዶች ደግሞ ከዚህ በተቃራኒው ሕይወት በሞት ያከትማል የሚል አመለካከት አላቸው። ስሜታዊውና አእምሯዊው ሕይወት ከሥጋ በተለየችና ሰብዓዊ ባልሆነች የማትታይ ነፍስ ውስጥ መኖሩን ይቀጥላል የሚለው አስተሳሰብ ለእነዚህ ሰዎች አይዋጥላቸውም። የ20ኛው መቶ ዘመን ደራሲና ምሁር የሆኑት ስፔናዊው ሚገል ደ ኡናሙኖ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ነፍስ አትሞትም ብሎ ማመን ነፍስ ዘላለማዊ ሆና እንድትኖር መመኘት ማለት ነው፤ ሆኖም እንዲህ ዓይነቱ ምኞት አንድ ሰው ምክንያታዊነትን ወደ ጎን ገሸሽ እንዲያደርግ ተጽዕኖ ያሳድርበታል።” ነፍስ አትሞትም የሚለውን እምነት ካልተቀበሉት ሰዎች መካከል የታወቁት የጥንት ፈላስፎች አርስቶትልና ኤፒኩረስ፣ ሐኪሙ ሂፖክራተስ፣ ስኮትላንዳዊው ፈላስፋ ዴቪድ ሁም፣ የአረቡ ምሁር አቬሮዊዝና ሕንድ ነፃነቷን ባወጀች ጊዜ የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚንስትር የሆኑት ጃዋሃርላል ኔህሩ ይገኙበታል።

12, 13. ነፍስ አትሞትም የሚለውን ትምህርት በተመለከተ የትኞቹ አስፈላጊ ጥያቄዎች ይነሳሉ?

12 ጥያቄው በእርግጥ የማትሞት ነፍስ አለችንን? የሚል ነው። ነፍስ በእርግጥ ሟች ከሆነች እንዲህ ዓይነቱ የሐሰት ትምህርት በዛሬው ጊዜ ያሉት የአብዛኞቹ ሃይማኖቶች ዋነኛ ክፍል ሊሆን የቻለው እንዴት ነው? ሐሳቡ የመነጨው ከየት ነው? በተጨማሪም አንድ ሰው ሲሞት ነፍሱ ከሕልውና ውጪ የምትሆን ከሆነ ሙታን ምን ተስፋ ሊኖራቸው ይችላል?

13 ለእነዚህ ጥያቄዎች እውነተኛና አጥጋቢ መልሶች ማግኘት እንችላለንን? አዎ፣ እንችላለን! እነዚህና ሌሎች ጥያቄዎች በሚቀጥሉት ገጾች ላይ መልስ ያገኛሉ። በመጀመሪያ ግን፣ ነፍስ አትሞትም የሚለው መሠረተ ትምህርት እንዴት እንደተጸነሰ እንመርምር።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]