በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የነፍስ ዘላለማዊነት የመሠረተ ትምህርቱ ምንጭ

የነፍስ ዘላለማዊነት የመሠረተ ትምህርቱ ምንጭ

የነፍስ ዘላለማዊነት የመሠረተ ትምህርቱ ምንጭ

“የሰው ልጅ ከመንፈሳዊ ሕይወቱ ጋር በተያያዘ ከሞትኩ በኋላ ምን እሆናለሁ የሚለውን ጥያቄ ያህል አእምሮውን ያስጨነቀው ሌላ ርዕሰ ጉዳይ የለም።”​—⁠“ኢንሳይክሎፔድያ ኦቭ ሪሊጅን ኤንድ ኤቲክስ”

1-3. ሶቅራጥስና ፕላቶ ነፍስ አትሞትም የሚለውን አስተሳሰብ ያስፋፉት እን​ዴት ነው?

አንድ የ70 ዓመት ምሁርና አስተማሪ ሃይማኖትን በማቃለልና የወጣቶችን አእምሮ በትምህርቱ በመበከል ወንጀል ተከሰሰ። ጉዳዩ በችሎት ፊት እየታየ በነበረበት ወቅት አስደናቂ የሆነ የመከላከያ ሐሳብ አቅርቦ የነበረ ቢሆንም አድሏዊው ሕዝባዊ ሸንጎ ጥፋተኛ ነህ ብሎ ሞት ፈረደበት። አረጋዊው አስተማሪ ከመገደሉ ከጥቂት ሰዓታት በፊት በዙሪያው ተሰብስበው የነበሩትን ተማሪዎች ነፍስ የማትሞት መሆኗንና ሞት ሊፈራ የሚገባው ነገር እንዳልሆነ ለማሳመን በርካታ የመከራከሪያ ሐሳቦችን አቀረበ።

2 ይህ ሞት የተፈረደበት ሰው በአምስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ይኖር የነበረው የታወቀው የግሪክ ፈላስፋ ሶቅራጥስ ነው። * የእሱ ተማሪ የነበረው ፕላቶ እነዚህን ክንውኖች አፖሎጂ እና ፌዶ በተባሉት የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ውስጥ ዘግቧቸዋል። ሶቅራጥስና ፕላቶ ነፍስ አትሞትም የሚለውን ትምህርት ካስፋፉት ግንባር ቀደም ሰዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። ሆኖም የትምህርቱ ምንጭ እነሱ አይደሉም።

3 ከዚህ ቀጥሎ እንደምንመለከተው የሰው ነፍስ አትሞትም የሚለው አስተሳሰብ ምንጩ እጅግ ጥንታዊ ነው። ይሁን እንጂ ሶቅራጥስና ፕላቶ ጽንሰ ሐሳቡን በማዳበርና ወደ ፍልስፍና ትምህርትነት በመለወጥ በእነሱ ዘመን ለነበረውና ከእነሱ ዘመን በኋላ ለመጡት የተማሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ይበልጥ ማራኪ አድርገው ሊያቀርቡት ችለዋል።

ከፓይታጎረስ እስከ ፒራሚዶች

4. ግሪካውያን ከሶቅራጥስ በፊትም እንኳ ስለ ወዲያኛው ዓለም ምን አመለካከት ነበራቸው?

4 ግሪኮች ከሶቅራጥስና ከፕላቶ በፊትም ቢሆን ነፍስ ከሞትም በኋላ ሕያው ሆና ትቀጥላለች ብለው ያምኑ ነበር። በስድስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ይኖር የነበረው የታወቀው ግሪካዊ የሒሳብ ሊቅ ፓይታጎረስ ነፍስ እንደማትሞትና አንድ ሰው ሲሞት ነፍሱ ወደ ሌላ አካል እንደምትሸጋገር ያምን ነበር። ከእሱ በፊት ይኖር የነበረውና የመጀመሪያው ግሪካዊ ፈላስፋ እንደሆነ የሚነገርለት የሚሊጢኑ ቴልዝ ሰዎች፣ እንስሳትና ዕፅዋት ብቻ ሳይሆኑ ብረትን የመሳብ ኃይል ያላቸው እንደ ማግኔት ያሉ ነገሮችም የማትሞት ነፍስ አለቻቸው የሚል አስተሳሰብ ነበረው። ጥንታውያኖቹ ግሪኮች የሙታን መናፍስት የስቲክስን ወንዝ ተሻግረው የሙታን ዓለም ተብሎ ወደሚጠራው ከመሬት በታች ያለ ሰፊ ዓለም ይሄዳሉ ይሉ ነበር። እዚያ ከደረሱ በኋላም ፈራጆች ነፍሳቱን በረጅም ግንብ በታጠረ እስር ቤት ውስጥ እንዲሰቃዩ አሊያም ደግሞ በገነት ውስጥ እንዲደሰቱ ይበይኑባቸዋል።

5, 6. ፋርሳውያን ስለ ነፍስ የነበራቸው አመለካከት ምን ነበር?

5 በኢራን ወይም በፋርስ ምሥራቃዊ ክፍል በሰባተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ዞራስተር የሚባል ነቢይ ተነስቶ ነበር። ይህ ሰው ዞራስትሪያኒዝም ተብሎ የሚጠራ የአምልኮ ሥርዓት አቋቋመ። ይህም ከግሪክ በፊት ኃያል መንግሥት በመሆን የዓለምን መድረክ ተቆጣጥራ የነበረችው የፋርስ ግዛት ሃይማኖት ነበር። የዞራስተር ቅዱሳን ጽሑፎች እንዲህ ይላሉ:- “የጻድቁ ነፍስ ዘላለማዊ ሆና ከሁሉ የላቀ ደስታ ታገኛለች፤ የውሸታሙ ነፍስ ግን ስትሰቃይ ትኖራለች። እነዚህ ሕጎች አሁራ ማዝዳ [“ጥበበኛ አምላክ” ማለት ነው] በሉዓላዊ ሥልጣኑ የደነገጋቸው ናቸው።”

6 ነፍስ አትሞትም የሚለው ትምህርት ከዞራስትሪያን ሃይማኖት በፊት በነበረ የኢራን ሃይማኖት ውስጥም የነበረ እምነት ነው። ለምሳሌ ያህል የጥንቶቹ የኢራን ጎሳዎች የሞቱ ሰዎች ነፍሳት ከመሬት በታች ባለው ዓለም የሚጠቀሙበትን ምግብና ልብስ ያዘጋጁ ነበር።

7, 8. ጥንታውያን ግብጾች ሥጋ ከሞተ በኋላ ነፍስ ሕያው ሆና ስለመቀጠሏ ምን ዓይነት እምነት ነበራቸው?

7 ከሞት በኋላ ሕይወት አለ የሚለው እምነት በግብጻውያን ሃይማኖት ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው እምነት ነበር። ግብጻውያን የሙታን ነፍሳት ከመሬት በታች ያለው ዓለም ዋነኛ አምላክ በሆነው በኦሳይረስ ፊት ይዳኛሉ ብለው ያምኑ ነበር። ለምሳሌ ያህል በ14ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የተዘጋጀ ነው ተብሎ የሚነገርለት አንድ የፓፒረስ ሰነድ የሙታን አምላክ የሆነው አኒዩበስ የጸሐፊውን የሀኒፈርን ነፍስ ወደ ኦሳይረስ ሲወስደው ያሳያል። ሕሊናውን የሚወክለው የጸሐፊው ልብ የእውነትና የፍትሕ አምላክ በጭንቅላቷ ላይ ከምትሰካው ላባ ጋር ይመዘናል። ቶት የተባለ ሌላ አምላክ ውጤቱን ይመዘግባል። የሀኒፈር ልብ በጥፋት ድርጊት የተሞላ ባለመሆኑ ክብደቱ ከላባው ያነሰ ሆኖ ተገኝቷል፤ በመሆኑም ወደ ኦሳይረስ ዓለም እንዲገባ የተፈቀደለት ከመሆኑም በላይ ዘላለማዊነት ተሰጥቶታል። በተጨማሪም ይህ የፓፒረስ ሰነድ አንድ ሰው ከሞተ በኋላ ልቡ ፈተናውን ማለፍ ካቃታት ሟቹን የምትውጥ ሴት ጭራቅ ሚዛኑ አጠገብ ቆማ ያሳያል። ከዚህም ሌላ ግብጻውያን ነፍስ በሕይወት መቀጠል የምትችለው ሥጋው በጥሩ ሁኔታ ተጠብቆ ሊቆይ ከቻለ ነው የሚል እምነት ስለነበራቸው አስከሬኖችን ያደርቁ የነበረ ከመሆኑም በላይ የፈርዖኖቻቸውን አስከሬኖች በጣም ግዙፍ በሆኑ ፒራሚዶች ውስጥ ያስቀምጧቸው ነበር።

8 ስለዚህ የተለያዩ የጥንት ኅብረተሰቦች አንድ የጋራ ትምህርት ነበራቸው ማለት ነው፤ ሁሉም ነፍስ አትሞትም ብለው ያምኑ ነበር። ሁሉም ይህን ትምህርት ያገኙት ከአንድ ምንጭ ይሆን?

የትምህርቱ ምንጭ

9. በጥንቱ የግብጽ፣ የፋርስና የግሪክ ዓለም ላይ ተጽዕኖ ያሳደረው የትኛው ሃይማኖት ነው?

9 “በጥንቱ ዓለም” ይላል ዘ ሪሊጅን ኦቭ ባቢሎንያ ኤንድ አሲሪያ የተባለው መጽሐፍ፣ “የባቢሎን ሃይማኖት በግብጽ፣ በፋርስና በግሪክ ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል።” መጽሐፉ በመቀጠል እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “በኤል-አማርና ፅላቶች ላይ እንደተገለጸው በቀድሞ ዘመን በግብጽና በባቢሎንያ መካከል ከነበረው ግንኙነት አንጻር ሲታይ የባቢሎናውያን አስተሳሰቦችና ልማዶች ወደ ግብጻውያን የጣዖት አምልኮ የሚሰርጹባቸው በርካታ አጋጣሚዎች እንደነበሩ ምንም አያጠራጥርም። በፋርስ የሚትራ የጣዖት አምልኮ የባቢሎናውያን ጽንሰ ሐሳቦች ያሳደሩትን ተጽዕኖ በግልጽ የሚያሳይ ነው . . . በጥንቱ የግሪክ አማልክት አፈ ታሪኮችና ተረቶች ውስጥ ብዙ ሴማዊ ትምህርቶች መኖራቸው በብዙ ምሁራን የታመነ ስለሆነ ተጨማሪ ሐተታ መስጠቱ አስፈላጊ አይደለም። እነዚህ ሴማዊ ትምህርቶች በአብዛኛው ከባቢሎን የተወረሱ ናቸው።” *

10, 11. ባቢሎናውያን ከሞት በኋላ አለ ስለሚባለው ሕይወት ምን አመለካከት ነበራቸው?

10 ይሁን እንጂ ባቢሎናውያን ሰው ከሞተ በኋላ ስለሚሆነው ነገር ያላቸው አመለካከት ግብጻውያን፣ ፋርሳውያንና ግሪካውያን ካላቸው አመለካከት በእጅጉ ይለይ የለምን? ለምሳሌ ያህል ኤፒክ ኦቭ ጊልጋሜሽ የተባለውን የባቢሎናውያን ጽሑፍ ተመልከት። በዕድሜ ገፍቶ የነበረው የባቢሎን ባለ ጀብዱ ጊልጋሜሽ ሞትን በመፍራት ዘላለማዊነትን ለማግኘት ብዙ ጥረት ቢያደርግም አልተሳካለትም። በጉዞው ወቅት ያገኛት መጠጥ ቤት ያላት አንዲት ሴት እየፈለገው ያለውን መጨረሻ የሌለው ሕይወት ሊያገኝ እንደማይችል በመግለጽ በአሁኑ ሕይወቱ በሚገባ እንዲጠቀምበት አበረታታችው። የጠቅላላ ታሪኩ መልእክት ሞት ሊወገድ የማይችል ነገር እንደሆነና የዘላለማዊነት ተስፋ የሕልም እንጀራ እንደሆነ የሚገልጽ ነው። ይህ ታሪክ ባቢሎናውያን በወዲያኛው ዓለም እንደማያምኑ ያሳያልን?

11 ዩ ኤስ ኤ ውስጥ በሚገኘው የፔንሲልቫንያ ዩኒቨርሲቲ የሚሠሩት ጁንየር ፕሮፌሰር ሞሪስ ያስትሮው እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ሕዝቡም ሆነ ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ የነበራቸው መሪዎች [የባቢሎንያ ማለት ነው] ሕይወት ከናካቴው ከሕልውና ውጪ ይሆናል ብለው አስበው አያውቁም። [በእነሱ አመለካከት] ሞት አንድ ሰው ወደ ሌላ ዓይነት ሕይወት የሚሸጋገርበት ድልድይ ነው፤ አንድ ሰው ዘላለማዊ ሊሆን አይችልም የሚለው እምነታቸው ማንም ሰው በሞት አማካኝነት ወደ ሌላ ሕይወት ከመሸጋገር ሊያመልጥ አይችልም የሚለውን አመለካከታቸውን ጎላ አድርጎ የሚያሳይ ነው።” አዎ፣ ባቢሎናውያንም ሕይወት ከሞት በኋላም በሌላ መልክ መኖሩን ይቀጥላል ብለው ያምናሉ። እንዲህ ዓይነት እምነት ያላቸው በመሆኑም አንድ ሰው ሲሞት ሰውየው በወዲያኛው ዓለም የሚጠቀምባቸውን ዕቃዎች አንድ ላይ ይቀብራሉ።

12-14. (ሀ) ከጥፋት ውኃ በኋላ ነፍስ አትሞትም የሚለው ትምህርት የተጸነሰው የት ነው? (ለ) መሠረተ ትምህርቱ በምድር ዙሪያ የተሰራጨው እንዴት ነው?

12 ነፍስ አትሞትም የሚለው ትምህርት በጥንቷ ባቢሎንም የነበረ ትምህርት እንደሆነ በግልጽ መረዳት ይቻላል። ትክክለኛ ታሪክ ያዘለው መጽሐፍ ማለትም መጽሐፍ ቅዱስ በሚገልጸው መሠረት የባቤል ወይም የባቢሎን ከተማ የተመሠረተችው ከኖህ የልጅ ልጅ በተወለደው በናምሩድ አማካኝነት ነው። * በኖህ ዘመን ከደረሰው ዓለም አቀፍ የጥፋት ውኃ በኋላ በምድር ላይ አንድ ቋንቋና አንድ ሃይማኖት ብቻ ነበር። ናምሩድ ከተማዋን በመቆርቆርና አንድ ትልቅ ግንብ በመገንባት ሌላ ሃይማኖት አቋቋመ። የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ እንደሚያሳየው በባቤል የቋንቋ ዝብርቅ ከተፈጠረ በኋላ ጥረታቸው ያልሰመረላቸው ግንበኞች ሃይማኖታቸውን ይዘው በየፊናቸው ተበታተኑ። (ዘፍጥረት 10:​6-10፤ 11:​4-9) በዚህ መንገድ የባቢሎን ሃይማኖታዊ ትምህርቶች በመላው ምድር ላይ ተሰራጩ።

13 ናምሩድ የሞተው በሰው እጅ ተገድሎ ነው የሚል ከጥንት ጀምሮ የሚነገር አፈ ታሪክ አለ። ናምሩድ ከሞተ በኋላ ባቢሎናውያን ከተማቸውን የመሠረተና የገነባ የመጀመሪያ ንጉሥ አድርገው በመመልከት ከፍተኛ ክብር እንደሚሰጡት የታወቀ ነው። ማርዱክ (ሜሮዳክ) የተባለው አምላክ የባቢሎን መስራች ተደርጎ ስለሚታይ አንዳንድ ምሁራን ማርዱክ ባቢሎናውያን ያመልኩት የነበረውን ናምሩድን ይወክላል ይላሉ። ይህ አባባል ትክክል ከሆነ ሰው የማትሞት ነፍስ አለችው የሚለው አስተሳሰብ ሌላው ቢቀር ናምሩድ በሞተበት ዘመን ይታመንበት ነበር ማለት ነው። ያም ሆነ ይህ የታሪክ ገጾች እንደሚያሳዩት ነፍስ አትሞትም የሚለው ትምህርት የተጸነሰው ከጥፋት ውኃ በኋላ በባቤል ወይም በባቢሎን ውስጥ ነው።

14 ይሁን እንጂ ይህ መሠረተ ትምህርት በዘመናችን ባሉት በአብዛኞቹ ሃይማኖቶች ውስጥ ዋነኛ ትምህርት ሊሆን የቻለው እንዴት ነው? የሚቀጥለው ክፍል ይህ ትምህርት ወደ ምሥራቃውያን ሃይማኖቶች እንዴት እንደገባ ያብራራል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.2 ከዘአበ ማለት “ከዘመናችን አቆጣጠር በፊት” ማለት ሲሆን እዘአ የሚለው ደግሞ ብዙውን ጊዜ ኤ ዲ (አኖ ዶሚኒ) ማለትም “በጌታችን ዓመት” ተብሎ የሚጠራውን “እንደ ዘመናችን አቆጣጠር” የሚለውን አነጋገር ያመለክታል።

^ አን.9 ኤል-አማርና በ14ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ እንደተገነባች የሚነገርላት የግብጿ ከተማ የአክታተን ፍርስራሽ የሚገኝበት ቦታ ነው።

^ አን.12 ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን መጽሐፍ ቅዱስ—⁠የአምላክ ቃል ነው ወይስ የሰው? የተባለውን መጽሐፍ ከገጽ 37-54 ተመልከት።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 6 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ግብጻውያን ከመሬት በታች ባለው ዓለም ውስጥ ስለሚገኙት ነፍሳት ያላቸው አመለካከት

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሶቅራጥስ ነፍስ አትሞትም ሲል ተከራክሯል