በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለአዲሱ የምድር ንጉሥ ታማኝ ነህን?

ለአዲሱ የምድር ንጉሥ ታማኝ ነህን?

ምዕራፍ 18

ለአዲሱ የምድር ንጉሥ ታማኝ ነህን?

1. በ33 እዘአ ኢየሱስ እንደ ንጉሥ ሆኖ በቀረበ ጊዜ ሕዝቡ እንዴት ተቀበለው?

በ33 እዘአ፣ ኒሳን 9 ኢየሱስ ክርስቶስ የአይሁድ ንጉሥ፣ ይመጣል የተባለለት መሲሕ አድርጎ ራሱን ለሕዝቡ አቀረበ። ከደብረ ዘይት ተራራ ወርዶ ወደ ኢየሩሳሌም ሲያመራ ብዛት ያላቸው ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ ባደረጋቸው ታላላቅ ሥራዎች በመደሰት አምላክን ያወድሱ ነበር። (ሉቃስ 19:37, 38፤ ዘካርያስ 9:9) ይሁን እንጂ እንደ ንጉሥ አድርገው በዕልልታ የተቀበሉትን ሰው በታማኝነት ይቆሙለት ይሆን? ታማኝነታቸው ብዙም ሳይቆይ ተፈትኗል።

2. (ሀ) ኢየሱስ አዲሱ የምድር ንጉሥ ሆኗል ለሚለው ማስታወቂያ ዛሬ ብዙ ሰዎች ምን ምላሽ እየሰጡ ነው? (ለ) ይሁን እንጂ በጥሞና ሊታሰብባቸው የሚገቡት የትኞቹ ጥያቄዎች ናቸው?

2 የላቀ ክብር የተቀዳጀው ኢየሱስ ክርስቶስ በ1914 ከሰማይ መግዛት ከጀመረበት ጊዜ አንሥቶ አዲሱ የምድር ንጉሥ ሆኖ ለሁሉም የሰው ዘር ቀርቦላቸዋል። የሰው ልጅ ችግሮች እውነተኛ መፍትሔ አግኝተው፣ በክርስቶስ በምትመራው መስተዳድር ሥር መኖሩ ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ብዙ ሰዎችን በደስታ አስፈንድቋቸዋል። ነገር ግን ታማኝ ይሆኑለታልን? የእያንዳንዳችን የግል ሁኔታ እንዴት ነው?

ንጉሡ ያስመዘገበው የታማኝነት ታሪክ

3. (ሀ) ኢየሱስ ራሱ የይሖዋ “ታማኝ” ተብሎ የተጠራው ለምንድን ነው? (ለ) ታማኝነት ምንድን ነው?

3 ኢየሱስ ክርስቶስ ለአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዥ ለይሖዋ የማይታጠፍ ታማኝነት ያለው መሆኑን በብዙ መንገድ አስመስክሯል። በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የይሖዋ “ታማኝ” የሚል ትክክለኛ መጠሪያ ተሰጥቶታል። (መዝሙር 16:10 አዓት፤ ሥራ 2:24–27 አዓት) እዚህ ላይ የተሠራበት “ታማኝ” የሚለው የዕብራይስጥ ቃል ፍቅራዊ ደግነትን ያካትታል። ታማኝነት ሕግን ወይም ፍትሕን ለማክበር ተብሎ በቀዝቃዛ ስሜት የሚገለጽ ሳይሆን ከፍቅርና ከአድናቆት በመነጨ ስሜት የሚገለጽ ጠባይ ነው። — ከመዝሙር 40:8​ና ከዮሐንስ 14:31 ጋር አወዳድር።

4, 5. (ሀ) ሰይጣን ካመፀ በኋላ በሰማይ የኢየሱስ ታማኝነት የታየው እንዴት ነበር? (ለ) ይኸው ታማኝነት በምድርም ላይ የታየው እንዴት ነው?

4 ሰይጣን ለይሖዋ ብቻ የሚገባውን ክብር ለመውሰድ በሰማይ ውስጥ ብዙ ሲሯሯጥ፣ ሌሎች መላእክትም በሰማያዊው የይሖዋ ድርጅት ውስጥ የነበራቸውን ትክክለኛ ቦታ ትተው ሲሄዱ፣ የአምላክ የበኩር ልጅ የእነርሱን መንፈስ አልተከተለም። በእርሱ ዘንድ ይህ ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር ነበር! ይህ ታማኝ ልጅ ራስን መሥዋዕት ለማድረግ የሚገፋፋ ኃይለኛ ፍቅር ስለነበረው የአባቱን ፈቃድ ለመፈጸም ሲል ሰማያዊ ክብሩን ትቷል፤ ሰው ሆኖአል፤ በመከራ እንጨትም ላይ የሥቃይን ሞት ተቀብሏል። ነገሩ በእርሱ ላይ የተመካ እስከሆነ ድረስ በፍቅር ተገፋፍቶ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ስለ እርሱ የተጻፈው እያንዳንዱ ነገር መፈጸሙን ያረጋግጥ ነበር። — ፊልጵስዩስ 2:5–8፤ ሉቃስ 24:44–48

5 ኢየሱስ በምድር ሳለ አምላክ ከሰጠው ሥራ እንዲያፈገፍግ፣ ከተቻለም አምላክ ራሱ ልጁን ከልቡ እንዲያወጣው የሚያስገድድ ድርጊት እንዲፈጽም ሰይጣን በኢየሱስ ላይ ከፍተኛ ግፊት አሳድሮበት ነበር። ኢየሱስ ከፍተኛ ሥልጣንና ኃይል ሊያስገኙ የሚችሉ ድርጊቶችን እንዲፈጽም ሰይጣን አጥብቆ ጠየቀው። ይህን ሥልጣን የሚያገኘው በሰይጣን የሚገዛው ዓለም ክፍል በመሆን ነበር። ኢየሱስ ቅዱሳን ጽሑፎችን መመሪያው አድርጎ በመጥቀስ እምቢ አለው። (ማቴዎስ 4:1–10) ኢየሱስ ልዩ ችሎታ ነበረው፤ ደግሞም በደንብ ተጠቅሞበታል፤ ይሁንና ምን ጊዜም ይህን ችሎታ የተጠቀመበት ከአባቱ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ ነበር። ራሱን ሙሉ በሙሉ ያስጠመደው አምላክ እንዲያከናውን በላከው ሥራ ላይ ነበር። (ዮሐንስ 7:16–18፤ 8:28, 29፤ 14:10) እንዴት ያለ ግሩም የታማኝነት ምሳሌ ነው!

6. ለኢየሱስ የተሰጠው ሽልማት፣ ታማኝነት እንድናሳይ የሚጠይቅብን በምን መንገድ ነው?

6 ተፈትኖ በተረጋገጠው ታማኝነቱ ምክንያት ይሖዋ ኢየሱስን ከሞት አስነሳው። “ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው፣ ከስምም ሁሉ በላይ ያለውን ስም ሰጠው፤ ይህም . . . ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ፣ መላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው።” (ፊልጵስዩስ 2:9–11) ኢየሱስ “ከስምም ሁሉ በላይ ያለውን ስም” መቀበሉ የይሖዋን ፈቃድ ለማስፈጸም የሚያስችል ኃይልና ሥልጣን የተሰጠው መሆኑን ያመለክታል። ለኢየሱስ ‘መንበርከክ’ ማለት ቦታውን መቀበልና ለሥልጣኑ መገዛት ማለት ነው። እርሱን እንደ ንጉሥ እየተመለከቱ በታማኝነት ለእርሱ መገዛትን ይጨምራል።

ለይሖዋ ቅቡዓን ታማኝ ፍቅር ማሳየት

7. የኢየሱስ ተከታዮች በየትኞቹ ጉዳዮች ረገድ ታማኝነታቸው ይፈተናል?

7 ኢየሱስ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ በዓይን ሊታይ አለመቻሉ በተከታዮቹ ላይ የልብን ሁኔታ የሚመረምር ልዩ ልዩ ፈተና አምጥቶባቸዋል። እርሱ ያስተማራቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶች እያከበሩ ይኖሩ ይሆን? ከዓለም ፈንጠር ብለው ይቆሙ ይሆን? መንፈስ ቅዱስ የበላይ ተመልካቾች አድርጎ የሾማቸውን ያከብሩ ይሆን? እንዲሠሩት የሰጣቸውን ሥራ በሙሉ ነፍስ ያከናውኑ ይሆን?

8. በዮናታንና በዳዊት መካከል የነበረው ታማኝ ፍቅር የምን ጥላ ነው?

8 ጊዜው ሲደርስ “ሌሎች በጎች” መሰብሰብና የሰማያዊቷ መንግሥት ወራሽ ከሆኑት የ“ታናሽ መንጋ” አባላት ጋር መቀላቀል ነበረባቸው። ታዲያ ሁለቱም ወገኖች ክርስቶስን በንጉሥነቱ፣ እርስ በርሳቸውም በተመደበላቸው ቦታ አንፃር እየተመለከቱ ቦታቸውን በእርግጥ አድንቀው ይቀበሉ ይሆን? በኢየሱስ ክርስቶስ ሥር ያለው “አንድ መንጋ” ክፍል የሆኑ ሁሉ በመካከላቸው እውነተኛ ፍቅር እንዳለ ማስረጃዎቹ ያሳያሉ። የንጉሥ ሳኦል ልጅ፣ ዮናታን፣ ለዳዊት የነበረው የማይበጠስና የማይከስም ፍቅር ለዚህ ጥላ ነበር። ዳዊት ለይሖዋ የነበረውን ኃይለኛ ፍቅርና በይሖዋ ተመክቶ ግዙፉን ጎልያድን ለመግደል እንዴት ቆርጦ እንደተነሳ ሲመለከት ዮናታን ልቡ በጥልቅ ተነካና “የዮናታን ነፍስ በዳዊት ነፍስ ታሰረች፣ ዮናታንም እንደ ነፍሱ ወደደው።” ይሖዋ ንግሥናውን ለዳዊት እንጂ ለዮናታን እንደማያስተላልፍ ግልጽ በሆነ ጊዜም ፍቅሩ አልቀነሰም። እንዲያውም ዮናታን ለዳዊት ሲል ብዙ ጊዜ ሕይወቱን አደጋ ላይ ጥሏል። — 1 ሳሙኤል 17:45–47፤ 18:1፤ 23:16, 17

9. በዳዊት ሠራዊት ውስጥ ያገለግሉ የነበሩ እስራኤላውያን ያልሆኑ ሰዎች ተመሳሳይ ታማኝነት ያሳዩት እንዴት ነው?

9 ከዮናታን በተጨማሪ ከዳዊት ጋር በፍቅር የተጣበቁ እስራኤላውያን ያልሆኑ ሌሎች ሰዎችም ነበሩ። እነዚህ ሰዎች ቅጥረኛ ወታደሮች አልነበሩም፤ ከዚህ ይልቅ ዳዊት የይሖዋ ቅቡዕ መሆኑን ተመልክተው ለእርሱ ኃይለኛ ፍቅር ያደረባቸው ጀግኖች ነበሩ። ከሊታውያንና ፈሊታውያን፣ እንዲሁም የቀድሞዋ የጌት ከተማ ነዋሪዎች የሆኑ ፍልስጥኤማውያን ከእነርሱ መካከል ነበሩ። የዳዊት ልጅ አቤሴሎም በተንኮል የእስራኤልን ልብ ለመስረቅ ሲጥር እነርሱ ከዳዊት ጋር በታማኝነት ተጣብቀዋል። አቤሴሎም የቱንም ያህል ታዋቂና ተንኮለኛ ቢሆንም በእርሱ አፈጮሌነት ወደ ክህደት አላዘነበሉም። — 2 ሳሙኤል 15:6, 10, 18–22

10. (ሀ) በክርስቶስ፣ በቅቡዓን ቀሪዎችና ‘በሌሎች በጎች’ መካከል ያለው የጠበቀ ትስስር በመዝሙር 45 ላይ ሕያው ሆኖ የተገለጸው እንዴት ነው? (ለ) ‘ደናግል ባልንጀሮቿ ወደ ንጉሡ እልፍኝ’ የሚገቡት በምን መንገድ ነው?

10 በክርስቶስ፣ በቅቡዓን ቀሪዎችና ‘በሌሎች በጎች’ መካከል ስላለው ትስስር ልብን የሚነካው ሌላው አስደሳች መግለጫ በመዝሙር 45 ውስጥ ይገኛል። ይህ እንዲሁ ውብ የሆነ ግጥም አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ስለ መሲሐዊቷ መንግሥት የተጻፈ ትንቢት ነው። የመንግሥቲቱ ‘ዙፋን’ ማለትም የኢየሱስ ንግሥና መሠረትና ድጋፍ አምላክ ራሱ ነው። (መዝሙር 45:1–7 አዓት፤ ዕብራውያን 1:8, 9 አዓት ) መዝሙራዊው የ“ንጉሥ ሴት ልጅ” ማለትም የክርስቶስን ሙሽራ በሠርጉ ቀን ወደ ንጉሡ ሲያቀርቧት የሚኖረውን ሁኔታ ገልጿል። “ደናግል . . . ባልንጀሮቿ” አጅበዋታል። እነዚህ እነማን ናቸው? ወደፊት የአምላክ መንግሥት ምድራዊ ዜጎች ለመሆን የሚጠብቁ ሰዎች ናቸው። “የሙሽራይቱ” ክፍል የሆነ የመጨረሻው አባል በሰማይ ከክርስቶስ ጋር ለመቀላቀል እስኪሄድ ድረስ “በደስታና በሐሴት” ያጅቧቸዋል። ከእነርሱ ጋር ሆነው “ወደ ንጉሥ እልፍኝ” ይገባሉ። የሚገቡት ግን ወደ ሰማይ በማረግ ሳይሆን ራሳቸውን ለንጉሡ አገልግሎት በማቅረብ ነው። የዚህ ደስተኛ አጀብ አካል ሆነሃልን? — መዝሙር 45:13–15

ታማኝነት ምን እንድናደርግ ይጠይቅብናል?

11. ‘የዓለም ክፍል’ መሆን አለመሆናችንን የትኞቹ ሁኔታዎች ይፈትኑናል?

11 በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥሙን ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሁኔታዎች ምን ዓይነት ሰዎች መሆናችንን ያሳያሉ። በይሖዋ መሲሐዊት መንግሥት በእርግጥ እናምናለንን? እውን ሆና ትታየናለችን? ኢየሱስ እውነተኛ ተከታዮቹ ‘የዓለም ክፍል’ እንደማይሆኑ ተናግሯል። ያንተ አቋም ልክ እንደዚህ ነውን? — ዮሐንስ 17:15, 16

12. ፍጽምና ባይኖረንም ታማኝ መሆናችንን በምን ተጨማሪ መንገዶች ማረጋገጥ እንችላለን?

12 ታማኝነት ፍጽምና ከሌላቸው ሰዎች ዘንድ ፍጹም መሆንን አይጠይቅም። ይሁን እንጂ ሌሎች ሰዎች አዩንም አላዩን፣ ሆን ብለን የመጽሐፍ ቅዱስን ትእዛዛት እንዳንጥስ ይከለክለናል። ወደ ዓለም መንገዶች ምን ያህል መጠጋት እንደምንችል ለማየት ከመሞከር ይልቅ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች አሟልተን ሥራ ላይ ለማዋል እንድንጥር ያንቀሳቅሰናል። መጥፎ ለሆነው ነገር እውነተኛ ጥላቻ እንድንኮተኩት ያደርገናል። — መዝሙር 97:10

13. ታማኝነት ከከሐዲዎች አፈጮሌነት የሚጠብቀን እንዴት ነው?

13 መጥፎውን ነገር በእውነት የምንጠላ ከሆነ፣ አንድን ሁኔታ ለማወቅ በመጓጓት ክፉ ወደሆነው ነገር ለመሳብ ልባችን አይታለልም። የፆታ ብልግና የሚፈጽሙ ሰዎችን ሕይወት ለማወቅ መጓጓት ወደ ውድቀት ሊያደርስ ይችላል። (ምሳሌ 7:6–23) ይሖዋንና ድርጅቱን ከተዉ በኋላ የቀድሞ ጓደኞቻቸውን በቃላት ‘የሚማቱ’ ከሐዲዎች ለጻፉት ጽሑፍ ጉጉት አድሮባቸው የሚገዙትና የሚያነቡትም እንደዚሁ መንፈሳዊነታቸው ሊናድ ይችላል። (ማቴዎስ 24:48–51) “ዝንጉ [“ከሐዲ” አዓት] ሰው በአፉ ባልንጀራውን ያጠፋል” በማለት ምሳሌ 11:9 ያስጠነቅቃል። ታማኝነት ግን በአፈ ጮሌነታቸው እንዳንሳሳት ይጠብቀናል። — 2 ዮሐንስ 8–11

14. (ሀ) ክርስቶስን እንደ ንጉሥ አድርገን በመቀበል ታማኝነታችንን ለእርሱ ለማሳየት ከምንችልባቸው ዋና ዋና መንገዶች አንዱ ምንድን ነው? (ለ) ይህ ሥራ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

14 ታማኝነት ማሳየት ከምንችልባቸው ዋና ዋና መንገዶች አንዱ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ እንዲሠሩት ባስተማራቸው ሥራ በሙሉ ነፍስ መሳተፋችን ነው። ኢየሱስ ራሱ ከከተማ ወደ ከተማ፣ ከመንደር ወደ መንደር እየሄደ የአምላክን መንግሥት ምሥራች በመስበክ ምሳሌውን ትቶልናል። (ሉቃስ 8:1) ኢየሱስ “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል” በማለት እውነተኛ ክርስቲያኖች ዛሬ ምን እንደሚያደርጉ አስቀድሞ ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:14) በየትም ቦታ የሚገኙ ሰዎች መንግሥቲቱን በሚመለከተው ጥያቄ ላይ የግል ውሳኔ ማድረግ እንዲችሉ ጥያቄው ለእነርሱ የሚቀርበው በዚህ የምሥራቹ ስብከት አማካኝነት ነው። እጅግ ብዙ ሰዎች የሚያደርጉት ውሳኔ በመጨረሻው ከታላቁ መከራ በሕይወት ለመትረፍ ያበቃቸዋል። (ራእይ 7:9, 10) አንተስ በዚህ አጣዳፊ ሥራ በታማኝነት እየተሳተፍክ ነውን?

15. (ሀ) መዝሙር 145:10–13 የይሖዋ ታማኞች ስለምን ነገሮች ይናገራሉ ይላል? (ለ) ይህስ ለእኛ የሚሠራው እንዴት ነው?

15 ከብዙ ጊዜ በፊት መዝሙራዊው ዳዊት “አቤቱ፣ ሥራህ ሁሉ ያመሰግኑሃል፣ ቅዱሳንህም [“ታማኞችህም” አዓት] ይባርኩሃል። የመንግሥትህን ክብር ይናገራሉ፣ ኃይልህንም ይነጋገራሉ፣ ለሰው ልጆች ኃይልህን የመንግሥትህንም ግርማ ክብር ያስታውቁ ዘንድ። መንግሥትህ የዘላለም መንግሥት ናት፣ ግዛትህም ለልጅ ልጅ ነው” በማለት ጽፏል። (መዝሙር 145:10–13) ይህ ንግሥና በአሁኑ ጊዜ የኢየሱስ ክርስቶስ ታማኝ እጆች በጨበጧት መሲሐዊት መንግሥት በኩል እየተገለጸ ነው። እኛም ስለ እርሷ በጋለ ስሜትና ያለፍርሃት በመናገር ለአምላክና ለክርስቶስ ያለንን ታማኝነት በተጨባጭ እናሳያለን።

16. ታማኝነት፣ በመንግሥቱ ስብከት ያለንን ተሳትፎ መጠንና ለዚህ ተሳትፎ የሚያነሳሳንን ዓላማ እንዴት ሊለውጠው ይገባል?

16 ስለ መንግሥቲቱ ለመመሥከር ለሚደረገው ለዚህ ሥራ በሕይወትህ ውስጥ ምን ቦታ ሰጥተኸዋል? ከሌሎች ጉዳዮች በእርግጥ ታስቀድመዋለህን? አንተ በግልህ የምታደርገው ነገር ሌሎች ከሚያደርጉት ሊበልጥ ወይም ሊያንስ ይችላል። የግለሰቦች ሁኔታ ይለያያል። ሆኖም ሁላችንም ከዚህ በታች ያሉትን ጥያቄዎች ለራሳችን ብንጠይቅ ልንጠቀም እንችላለን:- ‘ተሳትፎዬ እንዲያው አድርጓል እንድባል ለስሙ ያህል ብቻ የሚደረግ ነውን? ከጥፋት ለመትረፍ ብቻ እንደሚያስፈልግ ብቃት አድርጌ እመለከተዋለሁን? ወይስ ለይሖዋ ካለኝ ፍቅር፣ ለመሲሐዊው ንጉሥ ታማኝ ከመሆኔና እንደኔ ላሉት ሰዎች ካለኝ እውነተኛ አሳቢነት የተነሳ ሌሎቹን የኑሮ ጉዳዮች ወደኋላ በማድረግ የመጀመሪያውን ቦታ እንድሰጠው ተገፋፍቻለሁ?’ ታማኝነት፣ ይህ ሥራ ለንጉሣችን በጣም አስፈላጊ ጉዳይ የነበረውን ያህል ለእኛም በጣም አስፈላጊ ሆኖ እንደሚታየን የምናረጋግጥበትን መንገድ እንድንፈላልግ ያነሳሳናል።

17. ኢየሱስ ክፉዎችን በሚያጠፋበት ጊዜ ‘ሰላም የሚናገረው’ ለእነማን ነው?

17 በ33 እዘአ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ ደቀ መዛሙርቱ እንደ ንጉሥ የደመቀ አቀባበል ያደረጉለት ክርስቶስ፣ በይሖዋ መሲሐዊ ንጉሥ የተወከለውን የይሖዋን ሉዓላዊነት የሚቃወሙትን ሁሉ በቅርቡ ያጠፋቸዋል። ነገር ግን የእርሱን የታማኝነት ምሳሌ ለተከተሉት ከየብሔሩ ለተውጣጡት “እጅግ ብዙ ሰዎች” “ሰላምን ይናገራል።” ከእነርሱ መካከል ትገኛለህን? — ዘካርያስ 9:10፤ ኤፌሶን 4:20–24

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]