በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“መጽናት ያስፈልጋችኋል”

“መጽናት ያስፈልጋችኋል”

ምዕራፍ 23

“መጽናት ያስፈልጋችኋል”

1. (ሀ) የይሖዋ ምሥክሮች በእውነት ደስተኛ ሕዝብ የሆኑት ለምንድን ነው? (ለ) ይሁን እንጂ በዕብራውያን 10:36 ላይ የሚገኝ የትኛው ምክር በሁላችን ላይ ይሠራል?

ዛሬ በምድር ላይ ካሉት ሁሉ ይሖዋን መታመኛቸው ያደረጉትን ሰዎች ያህል እውነተኛ ደስታ ያገኙ ሰዎች የሉም። የሕይወትን ችግሮች ለመቋቋም ወደር የሌለው ምክር የት ሊገኝ እንደሚችል ያውቃሉ። በአምላክ ቃል ውስጥ ነው። የወደፊቱን ጊዜ ሲመለከቱት አይርበተበቱም፤ ምክንያቱም አምላክ ለዚች ምድር ምን ዓላማ እንዳለው ያውቃሉ። (ኤርምያስ 17:7, 8፤ መዝሙር 46:1, 2) ቢሆንም ሐዋርያው ጳውሎስ ለክርስቲያን ወንድሞቹ “የእግዚአብሔርን ፈቃድ አድርጋችሁ የተሰጣችሁን የተስፋ ቃል እንድታገኙ መጽናት ያስፈልጋችኋል” በማለት ጽፎላቸዋል። (ዕብራውያን 10:36) መጽናት አስፈላጊ እንዲሆን ያደረገው ነገር ምንድን ነው?

2. የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት መጽናት የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?

2 ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት ሐዋርያቱ ወደፊት የሚጠብቃቸውን ነገር ለመጠቆምና እንዲነቁ ለማድረግ እንዲህ አላቸው:- “ከዓለምስ ብትሆኑ ዓለም የራሱ የሆነውን ይወድ ነበር፤ ነገር ግን እኔ ከዓለም መረጥኋችሁ እንጂ ከዓለም ስለ አይደላችሁ ስለዚህ ዓለም ይጠላችኋል። ባሪያ ከጌታው አይበልጥም ብዬ የነገርኋችሁን ቃል አስቡ። እኔን አሳደውኝ እንደ ሆኑ እናንተን ደግሞ ያሳድዱአችኋል፤ ቃሌን ጠብቀው እንደ ሆኑ ቃላችሁን ደግሞ ይጠብቃሉ። ዳሩ ግን የላከኝን አያውቁምና ይህን ሁሉ ስለ ስሜ ያደርጉባችኋል።” (ዮሐንስ 15:19–21) ይህ ማስጠንቀቂያ እንዴት በትክክል ተፈጽሟል!

3. (ሀ) ደቀ መዛሙርቱ ‘ስለ ስሙ’ የሚሰደዱት እንዴት ነው? (ለ) አሳዳጆች ኢየሱስን የላከውን አምላክ ‘የማያውቁት’ በምን መንገድ ነው? (ሐ) ቀንደኛው የስደቱ ጠንሳሽ ማን ነው?

3 የኢየሱስ ተከታዮች እውነተኛው ክርስትና የቆመለትን ዓላማ በማይቀበል ዓለም ውስጥ ስለሚኖሩ የተጠሉ ሆነዋል። ክርስቶስ ማለት “የተቀባ” ማለት ነው። ጠቅላላዋን ምድር እንዲገዛ በይሖዋ የተቀባው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ስለዚህ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ‘ስለ ስሙ’ እንደሚሰደዱ በተናገረ ጊዜ እሱን በይሖዋ የተቀባ መሲሐዊ ንጉሥ አድርገው ከጐኑ በመሰለፋቸው፣ ከማንኛውም ምድራዊ መሪ በላይ ክርስቶስን በመታዘዛቸው፣ መንግሥቱን ደግፈው በታማኝነት በመቆማቸውና በሰብዓዊ መንግሥታት ጉዳዩች ውስጥ የማይገቡ በመሆናቸው ይሰደዳሉ ማለቱ ነበር። በዚህ ላይ ኢየሱስ ሌላ ምክንያት ሲጨምር ተቃውሞ የሚመጣው ‘የላከኝን ስለማያውቁ ነው’ በማለት ስለ አሳዳጆች ተናግሯል። ይህም ማለት ይሖዋን የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዥ አድርገው ለመቀበል አሻፈረን ይላሉ ማለት ነው። (ከዘጸአት 5:2 ጋር አወዳድር።) የዚህ ስደት ቀንደኛ ጠንሳሽ ማን ነው? ሰይጣን ዲያብሎስ ነው። — ራእይ 2:10

4. (ሀ) የራእይ 12:17 መፈጸም ሕይወታችንን የሚነካው እንዴት ነው? (ለ) የሰይጣን ግብ ምንድን ነው?

4 በተለይ መሲሐዊቷ የይሖዋ መንግሥት በ1914 ተወልዳ ሰይጣን ከሰማይ ከተባረረ በኋላ በእውነተኛ ክርስቲያኖች ላይ የሚደርሰው ተጽዕኖ ተካሯል። አቅልለህ አትመልከተው። በኢየሱስ ክርስቶስ በምትመራዋ የአምላክ መንግሥት ደጋፊዎች ሁሉ ላይ ሰይጣንና አጋንንቱ በሁሉም አቅጣጫ ጦርነት ከፍተዋል። ይህንን በሚመለከት ራእይ 12:17 እንዲህ ይላል:- “ዘንዶውም [ሰይጣን ዲያብሎስ] በሴቲቱ [በአምላክ ሰማያዊት ሚስት መሰል ድርጅት] ላይ ተቆጥቶ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጠብቁትን የኢየሱስ ምስክር ያላቸውን ከዘርዋ የቀሩትን [በምድር ያሉትን በመንፈስ የተቀቡ የኢየሱስ ተከታዮች] ሊዋጋ ሄደ” በማለት ይናገራል። ‘ሌሎች በጎችም’ እንደዚሁ በተፋፋመ ፍልሚያ ውስጥ ገብተዋል። ሰይጣን አታሎ አለዚያም ኃይል ተጠቅሞ የአምላክን ትእዛዛት መከተላቸውን ለማስቆም ተንኮል ይሸርባል። መንፈሳዊነታቸውን ለማዳከም፣ ብሎም ቦጫጭቆ ለማጥፋት ይፈልጋል። ግቡም ኢየሱስ የይሖዋ መሲሐዊ ንጉሥ ሆኗል የሚለውን አዋጅ ጸጥ ለማሰኘት ነው። ይሁን እንጂ በዚህ መንፈሳዊ ፍልሚያ የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች በድል አድራጊነት እየተወጡ ነው።

ክርስቲያኖች ምን ማድረግ ይገባቸዋል?

5. መንግሥታት በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ምን እርምጃ ወስደዋል?

5 በርካታ የመንግሥት ባለሥልጣኖች የይሖዋ ምሥክሮች ሕግ አክባሪ እንደሆኑና በኅብተረሰቡም ውስጥ በጎ ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩ ያምናሉ። ይሁንና ሁሉም ሰብዓዊ መንግሥታት ሰይጣን በጠቅላላው ዓለም የዘረጋው የነገሮች ሥርዓት ክፍል መሆናቸው አልቀረም። (1 ዮሐንስ 5:19፤ ራእይ 13:2) ስለሆነም አንዳንድ መንግሥታት እውነተኛውን አምላክ የሚያመልኩ ሰዎችን እንዳይሰበሰቡ መከልከላቸው፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎቻቸውን ማገዳቸው፣ ስለ አምላክ መንግሥት አትስበኩ ማለታቸውና ማሰራቸው ወይም መደብደባቸው የሚያስደንቅ አይሆንም። አንተ ራስህ እንደዚህ ያለ ተጽዕኖ ቢደርስብህ ምን ታደርጋለህ?

6. (ሀ) ለመንግሥት ባለሥልጣኖች ምን ዝንባሌ ሊኖረን ይገባል? (ለ) ይሁን እንጂ ምን ለማድረግ ቆርጠናል? (ሐ) ብንሰደድም እንኳን ደስተኞች ሆነን ለመቀጠል የምንችለው እንዴት ነው?

6 የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት የመንግሥት ባለሥልጣኖችን የሚያከብሩ ሰዎች ነበሩ። ሲሰደዱ የአጸፋ እርምጃ አልወሰዱም። አምላክ ያዘዘውን አታድርጉ በተባሉ ጊዜ ግን “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል” በማለት ቁርጥ ያለ መልስ ሰጥተዋል። (ሥራ 5:29፤ ሮሜ 12:19፤ 1 ጴጥሮስ 3:15) ትገደላላችሁ የሚል ዛቻ በተሰጣቸውም ጊዜ የሞት ፍርሃት አቋማቸውን አላስለወጣቸውም። ‘ሙታንን የሚያስነሳውን አምላክ’ እያገለገሉ እንዳሉ ያውቁ ነበር። (2 ቆሮንቶስ 1:9፤ ዕብራውያን 2:14, 15) ቢሰደዱም ደስተኞች ነበሩ። የተደሰቱትም አምላክን እያስደሰቱ እንዳሉ በማወቃቸው ነው። ስሙን ለማስከበር በሚደረገው ሥራ ተካፋይ በመሆናቸውና እርሱ ለቀባው ንጉሥ ያላቸውን ታማኝነት ለማሳየት ዕድል በማግኘታቸው ደስተኞች ናቸው። (ሥራ 5:41, 42፤ ማቴዎስ 5:11, 12) አንተ የዚህ ዓይነት ሰው ነህን? እንደነዚህ ያሉ ነገሮች ከሚደርሱባቸው ሰዎች ጋር የአቋም አድንነት እንዳለህ በይፋ ታሳያለህን? አቤሜሌክ ይህን ለማድረግ ፍርሃት ያልገታው ሰው ነበር። ለመሆኑ እርሱ ማን ነበር?

7. (ሀ) አቤሜሌክ ማን ነበር? እርሱስ ዛሬ የእኛን ትኩረት የሚስበው ለምንድን ነው? (ለ) ኤርምያስ በጭቃ በተሞላ ጉድጓድ ውስጥ እንደተጣለ በሰማ ጊዜ አቤሜሌክ ምን እርምጃ ወሰደ? ለምንስ?

7 አቤሜሌክ ኢየሩሳሌም በባቢሎናውያን እስከጠፋችበት ጊዜ ድረስ በከተማዋ ይኖር የነበረ ፈሪሃ አምላክ ያደረበት ኢትዮጵያዊ ነበር። በንጉሥ ሴዴቅያስ ቤት ተቀጥሮ ይሠራ ነበር። በዚያን ጊዜ ኤርምያስ ለይሁዳ መንግሥትና በዙሪያው ለነበሩት ብሔራት የይሖዋ ነቢይ ሆኖ ያገለግል ነበር። የማያወላውል አቋም ይዞ የይሖዋን የማስጠንቀቂያ መልእክት ለሕዝብ ያሰማ ስለነበር ከባድ ስደት ደረሰበት። በኢየሩሳሌም የነበሩ አንዳንድ መሳፍንት በፈጠሩት ሴራ በጭቃ ተውጦ እንዲሞት ወደ ጉድጓድ ተጣለ። አቤሜሌክ እስራኤላዊ ባይሆንም ኤርምያስን የይሖዋ ነቢይ አድርጎ ይመለከተው ነበር። የተደረገውን በሰማ ጊዜ አቤሜሌክ ወዲያው ንጉሡን ፍለጋ ሄደና በከተማው በር ሲያገኘው የኤርምያስን ሕይወት እንዲያድን ተማጸነው። በንጉሡ ትእዛዝ 30 ሰዎችን እንዲሁም ገመድና አሮጌ ጨርቅ ወስዶ ሄደ። ብብቱ በገመድ እንዳይላላጥ ጨርቁን እንዲጎዘጉዝ ለኤርምያስ ነገረው፤ ነቢዩንም ከጉድጓድ ውስጥ ጎትተው አወጡት። — ኤርምያስ 38:4–13

8. ይሖዋ ለአቤሜሌክ ምን ልብን የሚያረጋጋ መልእክት ላከበት? ለምንስ?

8 አቤሜሌክ የመሳፍንቱን ሴራ ስላከሸፈ ምን ያደርጉብኝ ይሆን የሚል ስጋት ተሰማው፤ ስጋቱም አለምክንያት የተፈጠረ አልነበረም። ይሁን እንጂ ለይሖዋ ነቢይ የነበረው አክብሮትና ራሱ በይሖዋ ላይ የነበረው እምነት ከጭንቀቱ በለጠበት። በዚህ ምክንያት ይሖዋ ለአቤሜሌክ በኤርምያስ በኩል እንዲህ ሲል አረጋገጠለት:- “እነሆ፣ ለበጎነት ሳይሆን ለክፋት ቃሌን በዚህች ከተማ ላይ አመጣለሁ፤ በዚያም ቀን በፊትህ ይፈጸማል። በዚያ ቀን አድንሃለሁ፣ ይላል እግዚአብሔር፤ በምትፈራቸው ሰዎች እጅ አልሰጥህም። ፈጽሜ አድንሃለሁ ነፍስህም እንደ ምርኮ ትሆንልሃለች እንጂ በሰይፍ አትወድቅም፣ በእኔም ታምነሃልና፣ ይላል እግዚአብሔር።” — ኤርምያስ 39:16–18

9. (ሀ) “ሌሎች በጎች” እንደ አቤሜሌክ የሆኑት እንዴት ነው? (ለ) ስለዚህ ይሖዋ ለአቤሜሌክ የገባለት ቃል ዛሬ ላሉት “ሌሎች በጎች” ምን ትርጉም አለው?

9 ይህ የተስፋ ቃል ዛሬ ላሉት የይሖዋ አገልጋዮች እንዴት ያለ ክቡር ተስፋ ነው! እንደ አቤሜሌክ ሁሉ ‘ሌሎች በጎችም፣’ በዘመናዊው የኤርምያስ ክፍል፣ በቅቡዓን ቀሪዎች ላይ የሚፈጸመውን ግፍና የይሖዋን መንግሥት እንዳይሰብኩ ለማስቆም የሚደረግባቸውን ሴራ ይመለከታሉ። የቅቡዓኑን ክፍል ከመከራ ለመጠበቅና ማንኛውንም የድጋፍ እርምጃ ለመውሰድ ወደኋላ አላሉም። ስለዚህ ይሖዋ ለአቤሜሌክ የገባለት የተስፋ ቃል እነርሱንም የሚያጠነክር መሆኑ የተገባ ነው። ተቃዋሚዎች እነርሱን ለማጥፋት አምላክ እንደማይፈቅድላቸው፣ ከዚህ ይልቅ ከመጪው የዓለም ጥፋት በቡድን መልክ በሕይወት አትርፎ ጽድቅ ወደሚሰፍንበት “አዲስ ምድር” እንደሚያስገባቸው ያላቸው ትምክህት በዚህ የተስፋ ቃል ይጎለብታል።

10. ክርስቲያኖች ስደት የሚደርስባቸው በየትኞቹ የኑሮ ዘርፎች ነው?

10 የኢየሱስ ክርስቶስን ፈለግ የሚከተሉ ሁሉ ይታሰራሉ ማለት አይደለም። ነገር ግን በዚያም ሆነ በዚህ ሁሉም ስደት ይደርስባቸዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:12) በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ክርስቲያን ሚስቶችና ባሎች በገዛ ቤታቸው ውስጥ ለብዙ ዓመታት ከባድ ተቃውሞ ደርሶባቸው በታማኝነት ጸንተዋል። ልጆችም ይሖዋን ለማገልገል ስለፈለጉ ወላጆቻቸው ክደዋቸዋል። (ማቴዎስ 10:36–38) በተጨማሪም ክርስቲያን ወጣቶች በትምህርት ቤት፣ ጎልማሶችም በሥራ ቦታ ስደት ያጋጥማቸዋል። ሁሉም የይሖዋ ምሥክሮች ስለ አምላክ መንግሥት ለሕዝብ በሚመሰክሩበት ጊዜ በተለያየ መንገድ ስደት ይቀምሳሉ። “በመታገሣችሁም [“በመጽናታችሁም” አዓት] ነፍሳችሁን ታገኛላችሁ” ሲል ኢየሱስ የተናገራቸው ቃላት እንደነዚህ ባሉት ሁሉ ላይ ይፈጸማሉ። — ሉቃስ 21:19

11. (ሀ) ለብዙዎቹ ከባድ ፈተና የሚያመጡባቸው ሌሎች ሁኔታዎች ምንድን ናቸው? (ለ) እነዚህ ነገሮች የደረሱበት ሌላ ሰው ማን ነበር? ለምንስ?

11 በሌሎች ሁኔታዎች የሚፈተኑም ቁጥራቸው ትንሽ አይደለም። አንዳንዶች ደስ እያላቸው እንዳይኖሩ ከባድ ሕመም ዕንቅፋት ይሆንባቸው ይሆናል። ወይም ደግሞ በጣም አስቸጋሪ በሆነ የኢኮኖሚ አጣብቂኝ ውስጥ ገብተው ይሆናል። አንዳንድ ጊዜም የቅርብ ጓደኞቻቸው የሚሰነዝሩት ቃል አግባብነትና ደግነት የጐደለው ይሆናል። በድሮ ዘመን የነበረው ኢዮብ ንጹሕ አቋሙን እንዲያበላሽ ለመገፋፋት ሰይጣን በነዚህ ዘዴዎች ሁሉ ተጠቅሟል። እኛስ ተመሳሳይ ሁኔታዎች ቢደርሱብን ምን እናደርጋለን? — ያዕቆብ 5:11

12. (ሀ) በተለይ ኖኅ በአገልግሎቱ ጽናት ያስፈለገው ለምንድን ነው? (ለ) ሁኔታው በዘመናችንም ተመሳሳይ የሆነው እንዴት ነው?

12 በሌላም በኩል ስለ ይሖዋ ዓላማዎች ስንመሰክር ብዙ ተቀባይ ባናገኝስ? ይህም ቢሆን ጽናት ይጠይቃል። ከጥፋት ውኃ በፊት ኖኅ በእነዚያ ሁሉ ዓመታት ሲሰብክ ይሖዋን ለማገልገል የተባበሩት ሚስቱ፣ ወንዶች ልጆቹና ሚስቶቻቸው ብቻ እንደነበሩ አስታውስ። የቀሩት የሰው ልጆች ሁሉ ‘አላስተዋሉም ነበር።’ (ማቴዎስ 24:39) ዛሬም በተመሳሳይ አብዛኞቹ ሰዎች ‘አያስተውሉም።’ እምብዛም ተቀባይ ባልነበራቸው አንዳንድ ቦታዎች ግን በአሁኑ ጊዜ እውነተኛውን አምላክ የሚያመልኩ እጅግ ብዙ ሰዎች ተገኝተዋል። ሰዎቹ ችላ ይሉ የነበሩባቸውን ወይም ቀጥተኛ ተቃውሞ ያደረሱባቸውን እነዚያን ዓመታት ጸንተው የተቋቋሙና አሁን በሚካሄደው አጨዳ የሚካፈሉ ሁሉ እንዴት ደስ ይላቸው!

‘ጽናታቸውን የሚገፉበት ደስተኞች ናቸው’

13. (ሀ) ጸንተን ለመቀጠል በምን ነገር ላይ ማተኮር ይገባናል? (ለ) ስለ ሰይጣን ዘዴዎች ምን እውነታ ማወቅ ያስፈልገናል?

13 ‘በአዲሲቱ ምድር’ ውስጥ የሚገኘው በሕይወት የመኖር አጋጣሚ እንዳያመልጠን በሁሉም ፍጥረታት ፊት የተደቀነው ታላቅ ጥያቄ ምን ጊዜም ቁልጭ ብሎ እንዲታየን እናድርግ። ጥያቄው አጽናፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነትን የሚመለከት ነው። ታዲያ የማያወላውል አቋም ይዘን ከይሖዋ ጎን ቆመናልን? ሁለት አማራጭ አቋሞች ብቻ እንዳሉ፣ መሐል ላይ መቆም ግን እንደማይቻል ሙሉ በሙሉ ተቀብለናልን? በዚህ ጦርነት ውስጥ ተወግተው ከሚወድቁት መካከል እንዳንሆን ሰይጣን ንጹሕ አቋማችንን ለማጉደፍ፣ አምላክን መታዘዝን እንድናቆም፣ ስለ መሲሐዊቷ መንግሥት እንዳንመሰክር ለማድረግ የሚጠቀምባቸው ሁለት ዘዴዎች፣ በሰው እንድንጠላ ማድረግና መደለያ ማቅረብ መሆናቸውን ማወቃችን አንገብጋቢ ጉዳይ ነው። — 1 ጴጥሮስ 5:8, 9፤ ማርቆስ 4:17–19

14. (ሀ) ምን ዓይነት ዝምድና መኮትኮት ያስፈልገናል? ከማንስ ጋር? (ለ) እርሱስ እንዴት ይረዳናል?

14 በተጨማሪም በይሖዋ ላይ ሙሉ ትምክህት መጣልን ኮትኩተን ማሳደግ ይገባናል። ከሰው በላይ ኃይል ያለው ጠላት ያጠመዳቸውን መሠሪ ወጥመዶች በራሳችን ኃይል ብቻ ለማክሸፍ መሞከር እንዴት ሞኝነት ነው! ነገር ግን በሙሉ ልባችን በይሖዋ ላይ ከተመካን፣ ችግር ሲደርስብንና ፈተና ሲያጋጥመን ወደ እርሱ ይበልጥ እንቀርባለን። (ኤፌሶን 6:10, 11፤ ምሳሌ 3:5, 6) ይሖዋ እኛን አስገድዶ በፈለገው አቅጣጫ እንድንሄድ አያደርግም። ከፈቃዳችንም ውጭ ምንም ነገር እንድናደርግ አያስገድደንም። ነገር ግን መመሪያ ለማግኘት ወደ ቃሉ ዘወር ካልን፣ ብርታት ለማግኘት ወደ እርሱ ከጸለይንና ድርጅቱን ተጠግተን ከኖርን እምርጃዎቻችንን ያቀናልናል። ምን ጊዜም አለኝታችን የሆነውን ፍቅሩን የሚያረጋግጥ አዲስ ነገር በማሳየት ብርታት ይሰጠናል። — ሮሜ 8:38, 39

15. (ሀ) በሕይወታችን ውስጥ አንደኛውን ቦታ መያዝ የሚገባው ማን ነው? (ለ) እምነታችንን የሚፈታተኑ ሁኔታዎችን እንዴት መመልከት ይገባናል?

15 የሚያጋጥሙህ መከራዎችና አሳች መስህቦች ማንነትህን ይፈታተናሉ። በሕይወትህ ውስጥ በአንደኛ ደረጃ የምታስቀምጠው ማንን ነው? ሰይጣን ሁላችንንም የሚያስጨንቀን ዋናው ነገር የራሳችን ጥቅም ነው ባይ ነው። አብዛኞቹ ሰዎች እንደዚያ ናቸው። ኢየሱስ ክርስቶስ ግን የተለየ ነበር። አንተስ እንደ እርሱ ነህን? የይሖዋን ስም ለማሳወቅ የሚደረገውን ሥራ ማስቀደምን ተምረሃልን? እንደዚህ ከሆነ እምነትህን የሚፈትኑ ሁኔታዎች ሲመጡ በመሸሽ ፋንታ እርሱን ለማክበር እንድትጠቀምባቸው ጥበብ እንዲሰጥህ ወደ ይሖዋ እየጸለይክ ፊት ለፊት ልትጋጠማቸው ትችላለህ። የምትቀበለው መከራ ጽናትን እንድታዳብር ያስችልሃል። ለይሖዋ ባለህ ፍቅር የተነሳ የምታሳየው ጽናት ደግሞ የእርሱን ሞገስ ያስገኝልሃል። “በፈተና የሚጸና ሰው ደስተኛ ነው፤ ከተፈተነ በኋላ ይሖዋ እርሱን በመውደድ ለሚቀጥሉት እሰጣለሁ ብሎ ቃል የገባውን የሕይወት አክሊል ይቀበላልና።” — ያዕቆብ 1:2–4, 12 አዓትሮሜ 5:3, 4

16. የትኛው ግብ ላይ ለመድረስ መጣጣር አለብን?

16 የይሖዋን አገልግሎት መጀመሩ ወይም ለአጭር ጊዜ ብቻ መጽናቱ በቂ አይሆንም። በሩጫ ውድድር ላይ ነን፤ ሽልማቱ የሚሰጠው የሩጫው ማለቂያ ምልክት የሆነውን መሥመር ለሚያልፉት ነው። ይህ አሮጌ ሥርዓት በሚንኮታኮትበት ጊዜ ዓይናቸውን በሽልማቱ ላይ ተክለው ወደፊት የሚገፉ ሁሉ ደስተኞች ናቸው! ከዚያ በኋላ እንዴት ያለ አስደናቂ ዘመን ይከፈትላቸዋል! — ዕብራውያን 12:1–3፤ ማቴዎስ 24:13

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]