በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ቆጠራው ዜሮ ሰዓት ላይ ሊደርስ ነው!

ቆጠራው ዜሮ ሰዓት ላይ ሊደርስ ነው!

ምዕራፍ 24

ቆጠራው ዜሮ ሰዓት ላይ ሊደርስ ነው!

1. በታዋቂ ሳይንቲስቶች እምነት መሠረት “የመጥፊያ ቀን” ምን ያህል ቅርብ ነው?

በ1947 ሳይንቲስቶች “የመጥፊያ ቀን ሰዓት” የሚሉትን ነገር ፈጠሩ። የዚህ ሰዓት ምስል ዘ ቡለቲን ኦቭ ሳይንቲስትስ በተባለው መጽሔት ሽፋን ላይ ዘወትር የሚወጣ ሲሆን ሰዓቱ በእነርሱ እምነት ዓለም ወደ ኑክሌር እልቂት ምን ያህል እንደተጠጋች በሥዕል ያሳያል። ይህ “ሰዓት” የዓለም አቀፉ ሁኔታ አደገኛነት ምን ያህል እንደሆነ ለማመልከት አንዳንድ ጊዜ ወደፊት፣ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ወደኋላ እንዲል ተደርጓል። በ1984 መጀመሪያ አካባቢ ሰዓቱ ለእኩለ ሌሊት ሦስት ደቂቃ ጉዳይ ያሳይ ነበር። እኩለ ሌሊት ላይ ቢያመለክት ኖሮ የተፈራው የኑክሌር ጦርነት ጀመረ ማለት ይሆን ነበር።

2. ይሖዋ የጊዜ ቆጠራ የጀመረው መቼ ነው? የቆጠራው ዜሮ ሰዓትስ ምን ማለት ይሆናል?

2 ይሖዋ አምላክ ግን የጊዜ ቆጠራውን የጀመረው ከ6,000 ዓመታት ገደማ በፊት ነው። ይህ ቆጠራ ምንም ነገር ሳያግደው ወደፊት የሚገሰግስ እንጂ ወደኋላ የሚመለስ አይደለም። በዚህ ቆጠራ፣ ዜሮው ሰዓት፣ አምላክ የጽንፈ ዓለሙ ሰላምና ደኅንነት የተመካበትን ሉዓላዊነቱን ለማረጋገጥ እርምጃ የሚወስድበት ጊዜ ነው። ይሖዋ ይህን ዓላማውን ገልጿል፣ ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ የሚጠቁሙ ጊዜያትም ሰጥቶናል። በዔደን፣ ዓመፅ እንደተካሄደ ወዲያው ይሖዋ ‘ከሴቲቱ’ ማለትም ከታማኝ መንፈሳዊ ፍጥረቶቹ ድርጅት ‘የቀድሞውን እባብ’ ይኸውም የሰይጣንን ራስ የሚቀጠቅጥና በመጨረሻም የሚደመስሰው “ዘር” እንደሚያመጣ ቃል ገባ። (ዘፍጥረት 3:15፤ ራእይ 12:9፤ ሮሜ 16:20) ጽድቅ ወዳድ የሆኑ ሁሉ ይህን ጊዜ እንዴት ይናፍቃሉ!

3. (ሀ) መሲሑ የሚመጣበት ጊዜ በጥንቃቄ እንደተወሰነ የሚያሳየው ምንድን ነው? (ለ) በዚያን ጊዜስ ለምን ነገር መሠረት ተጣለ?

3 አምላክ ከረጅም ጊዜ በፊት የወሰነውና አስቀድሞ የተናገረለት ጊዜ ሲደርስ የተስፋው “ዘር” መሲሑ፣ የአምላክ ልጅ፣ በምድር መድረክ ላይ ብቅ አለ። ኢየሱስ እስከ ሞት ድረስ ለአምላክ ያደረ ሆኖ በመጽናት ሰይጣን በዕብሪት ላስነሳው ግድድር አስደናቂ መልስ ሰጥቷል። ኃጢአት የሌለበት ሰው ሆኖ በመሞትም የአዳምን ዘሮች ከኃጢአትና ከሞት ማዳን የሚቻልበትን መንገድ ከፈተ። በዚህ ሁኔታ፣ በመጨረሻ ‘የሰይጣንን ሥራ ለመሻር’ የሚያስችል መሠረት ተጣለ። — 1 ዮሐንስ 3:8፤ ዳንኤል 9:25፤ ገላትያ 4:4, 5

4. (ሀ) ኢየሱስ በምድር ላይ ሳለ የትኛውን ቡድን መሰብሰብ ጀመረ? (ለ) ከአምላክ የጊዜ ሰሌዳ ጋር በመስማማት ክርስቶስ ንጉሥ ሆኖ መግዛት የጀመረው መቼ ነው? (ሐ) መጀመሪያ ከወሰዳቸው እርምጃዎች አንዱ ምን ነበር?

4 ኢየሱስ ገና ምድር ላይ እያለ፣ ወደፊት አብረውት በሰማያዊቷ መንግሥት ወራሽ የሚሆኑትን ወንዶችና ሴቶች መሰብሰብ ጀምሮ ነበር። በዚህ ውስጥ የሚካተቱት የተመረጡ፣ የተፈተኑና ታማኝነታቸውን ያረጋገጡ 144,000 ብቻ ናቸው። የዚህ ቡድን የመጨረሻ አባላት የሚሰበሰቡበት ጊዜ እንደደረሰ፣ ኢየሱስ በሰማይ “ግዛትና ክብር መንግሥትም” ተሰጠው። (ዳንኤል 7:13, 14) ፕሮግራሙን ጠብቆ ልክ በ1914 ንጉሥ ሆኖ በመግዛት እርምጃ መውሰድ ጀመረ። ወዲያው ሰይጣንና አጋንንቱ ከሰማይ ተባረሩ። ይህም የመንግሥቱን መቀመጫ የሚያጸዳ እርምጃ ነበር። (ራእይ 12:7–12) አሁን ያለው የዓለም ሥርዓት ያን ጊዜ ወደ መጨረሻ ቀኖቹ ገባ።

5. የይሖዋ ሉዓላዊነት ሲረጋገጥ በሕይወት ቆይተው የሚያዩት እነማን ይሆናሉ?

5 ለስድስት ሺህ ዓመታት ያህል የቀጠለው የጊዜ ቆጠራ ዜሮ ሰዓት ላይ ለመድረስ ተቃርቧል። ሰዓቱ በጣም ቅርብ ከመሆኑ የተነሳ በ1914 በሕይወት የነበሩና አሁን በዕድሜ የገፉ ሰዎች የይሖዋን ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ የሚወሰዱትን ታላላቅ እርምጃዎች ሳያዩ ሞተው አያልቁም። — ማርቆስ 13:30

6, 7. (ሀ) ታላቁ መከራ በጣም ቅርብ እንደሆነ የሚያሳዩ “እጅግ ብዙ ሰዎች” የተባሉትን የሚያመለክቱ ምን ሁኔታዎች ናቸው? (ለ) የወደፊቱን ሁኔታ በታላቅ ጉጉት የሚጠብቁት ለምንድን ነው?

6 የታላቁን ቀን ክንውኖች በዓይን የሚያዩ ሌሎች ታማኝ የአምላክ አገልጋዮችም ይኖራሉ። “እጅግ ብዙ ሰዎች” የተባሉት እነማን እንደሆኑ ከታወቀበት ከ1935 ወዲህ፣ ይህን ቀን የሚያዩ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ተሰብስበዋል። በመጀመሪያ በመቶ የሚቆጠሩ ነበሩ፤ ቆይቶም በሺህ የሚቆጠሩ ሆኑ፤ አሁን ደግሞ በመላው ዓለም ላይ የተሰራጩ በሚልዮን የሚቆጠሩ አሉ። መሬት የማይወድቀው የአምላክ ቃል የዚህ ቡድን አባላት ‘ከታላቁ መከራ በሕይወት እንደሚተርፉ፣’ ወደ አዲሱ የአምላክ ሥርዓት እንደሚገቡና ወደፊት ጨርሶ እንደማይሞቱ ይገልጻል። (ራእይ 7:9, 10, 14፤ ዮሐንስ 11:26) የዚህ ቡድን የመጀመሪያ አባላት በአሁኑ ጊዜ በ70 ወይም በ80 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ ይገኛሉ፤ ከዚያ በላይ የሆናቸውም አሉ። ይሖዋ የዚህ ቡድን አባላት አለጊዜው ቶሎ መሰብሰብ እንዲጀምሩ አልፈቀደም። “እጅግ ብዙ ሰዎች” (የመጀመሪያዎቹን አባላት ጨምሮ) ከጥፋት በሕይወት ተርፈው ወደ “አዲስ ምድር” ይገባሉ።

7 የሰውን ዘር በሙሉ ይደመስሳል ተብሎ የሚፈራው የኑክሌር ፍንዳታ ለ“እጅግ ብዙ ሰዎች” የተሰጠውን ተስፋ እንዲያጨናግፍ አይፈቀድለትም። ብሩህ አመለካከት እንዲኖራቸውና ደፋሮች እንዲሆኑ የሚያበቃ ምክንያት አላቸው። የመጨረሻዎቹ ቀኖች ክንውኖች ተጠቅልሎ እንደነበረ ወረቀት እየተዘረጉ ሲሄዱ “ነፃ የምትወጡበት ጊዜ ቀርቧልና ቀጥ ብላችሁ ቁሙ፤ ራሳችሁንም ቀና አድርጉ” የሚለውን የኢየሱስ ምክር በመከተል ወደፊት የሚሆነውን በጉጉት ይጠብቃሉ። (ሉቃስ 21:28 አዓት) ሆኖም ያ ነፃነት ከመምጣቱ በፊት ዓለምን የሚያናጉ ተጨማሪ ነገሮች መከሰት አለባቸው።

ገና ያልተፈጸሙ ነገሮች

8. (ሀ) በ1 ተሰሎንቄ 5:3 ላይ በቅድሚያ የተገለጸ ምን ከፍተኛ ትርጉም ያለው ነገር ገና ወደፊት ይፈጸማል? (ለ) ከብዙ ዓመታት በፊት መድረኩ ለዚህ የተመቻቸው እንዴት ነው? (ሐ) በቅርብ ዓመታት የዓለምን ሰላም ለማረጋገጥ ምን ታላቅ ተጽዕኖ ተደርጓል?

8 ከእነዚህ አንዱን በመጠቆም ሐዋርያው ጳውሎስ “ሰላምና ደኅንነት ነው ሲሉ፣ ያን ጊዜ ምጥ እርጉዝን እንደሚይዛት ጥፋት በድንገት ይመጣባቸዋል። ከቶም አያመልጡም” በማለት ጽፎአል። (1 ተሰሎንቄ 5:3) ይህ ልፈፋ ምን መልክ እንደሚኖረው ገና ወደፊት የሚታይ ነው። ይሁን እንጂ ዓለም ወደ ‘መጨረሻ ቀኖችዋ’ ስትገባ ወዲያው መድረኩ ለልፈፋው እንደተመቻቸ ሊስተዋል የሚገባው ነው። በ1919 የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር ዓላማ “ሰላምና ደኅንነት” ማስጠበቅ እንደሆነ ይፋ ተደርጎ ነበር። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ላይም የተባበሩት መንግሥታት ዋነኛ ግብ “ሰላምና ደኅንነት” ማምጣት እንደሆነ በቻርተሩ ላይ ሰፍሯል። ድርጅቱ ግቡን አልመታም። በቅርብ ዓመታት ግን በሁሉም የኑሮ መስክ ያሉ ሕዝቦች በብዙ አገሮች ታላላቅ ሰላማዊ ሰልፎችን በማድረግ የዓለም መሪዎች የኑክሌር መሣሪያን በምንም መንገድ ማምረትን፣ መፈተሽንና በየቦታው መትከልን እንዲያቆሙ አጥብቀው አሳስበዋል። የዓለም ሰላም እንደሚጠበቅ ዋስትና እንዲሰጣቸው ይፈልጋሉ። የዚህን ተቃራኒ አማራጭ እጅግ ይፈሩታል።

9. በቅድሚያ የተገለጸውን “ሰላምና ደኅንነት” መጣ የሚለውን ልፈፋ በሚያራምዱ ላይ ድንገተኛ ጥፋት የሚመጣው ለምንድን ነው?

9 በዚህ ምክንያትም ይሁን በሌላ ግፊት፣ ሰብዓዊ መሪዎች “ሰላምና ደኅንነት” ሆኗል! ብለው ልዩ ትኩረት በሚስብ መልክ ያስታውቃሉ። ሆኖም ሰላምና ደኅንነቱ የቀለም ቅብ ብቻ ይሆናል። አራማጆቹ ግን የአምላክ መንግሥት እርዳታ ሳያስፈልጋቸው በራሳቸው ዘዴ ግባቸው ላይ እንደደረሱ በይፋ ያስታውቃሉ። የይሖዋን ሉዓላዊነት በዚህ ሁኔታ አጥላልተው ገሸሽ ሲያደርጉት “ጥፋት በድንገት ይመጣባቸዋል።”

10. ለታላቂቱ ባቢሎን መጥፋት ሁኔታው አሁንም እንኳን እየተመቻቸ ያለው እንዴት ነው?

10 ነገሮች በፍጥነት ይገሰግሳሉ። ታላቂቱ ባቢሎን፣ ይኸውም በዓለም ዙሪያ የተንሰራፋችው የሐሰት ሃይማኖት ግዛት በቀድሞ ፖለቲካዊ ወዳጆቿ ትጨፈለቃለች። ሃይማኖት በዓለም ዙሪያ ጥላቻ፣ ደም መፋሰስና ጦርነት የሚያነሳሳ ኃይል መሆኑ አሁንም እንኳ መሪዎችን የሚያንገበግብ ጉዳይ ነው። የፖለቲካ ሰዎች የቄሶች ተጽዕኖ አንገሽግሿቸዋል። በብዙ የዓለም ክፍሎች በአምልኮ ስፍራዎች የሚታየው የተሰብሳቢ ቁጥር አሽቆልቁሏል። በይፋ የሚታወቅም ይሁን በድብቅ የተያዘ፣ አምላክ የለም የሚል አቋም የብዙ ሰዎችን አእምሮ ይቆጣጠራል። ከዚህም ሌላ የተባበሩት መንግሥታት ብዙ አባል አገሮች ጠንካራ ፀረ ሃይማኖት ፖሊሲ አላቸው። ይሖዋ ፍርድ ለማስፈጸም ሰዓቱ ሲደርስ የፖለቲካ መሪዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ በመንቀሳቀስ በታላቂቱ ባቢሎን ላይ እንዲዘምቱና ድምጥማጧን እንዲያጠፉ ይፈቅድላቸዋል። — ራእይ 17:15, 16፤ 19:1, 2

11. (ሀ) ቀጥሎ ብሔራት ፊታቸውን በማን ላይ ያዞራሉ? (ለ) ይህስ ወደ ምን ሌሎች ክስተቶች ይመራል?

11 ከዚያ ቀጥሎ፣ ብሔራት ባገኙት ድል ሰክረውና በማይታየው ገዥያቸው በሰይጣን ዲያብሎስ ተነድተው በምድር ዙሪያ የሚገኙትን የይሖዋ ታማኝ ምሥክሮች ማጥቃት ይጀምራሉ። (ሕዝቅኤል 38:14–16) ሰላማዊና ሕግ አክባሪ መሆናቸው፣ በፖለቲካ ጣልቃ አለመግባታቸውና ለየትኛውም ጦርነት ተጠያቂ አለመሆናቸው ግምት ውስጥ አይገባም። መንግሥታት ሙሉ ድጋፍ እንዲሰጣቸው፣ የፖለቲካው ሥርዓት እንዲመለክ ያስገድዳሉ። የሚታየውን የይሖዋ ድርጅት ለመጨፍለቅ ሲንቀሳቀሱ ግን አምላክ ታማኝ አገልጋዮቹን ለማዳን ወሳኝ እርምጃ ይወስዳል። የሚታየው የሰይጣን ድርጅት ምንም ምልክት እስከማይቀርለት ድረስ የሰማይ ሠራዊት ይደመስሱታል፤ ሙጥኝ ብለው የያዙትንም ሁሉ ያወድማሉ። ከዚያ በኋላ ቀንደኛው ጠላት ሰይጣን ዲያብሎስ ራሱ ተይዞ ለሺህ ዓመት ተሽመድምዶ እንዲቀመጥ ይደረጋል። እኩይ ተጽዕኖው ይወገዳል፤ ምድርም ወደ ገነትነት ትለወጣለች። በኋላም፣ ወደ ፍጽምና ደረጃ የደረሰውን የሰው ዘር ለመፈተን ሰይጣን ለአጭር ጊዜ ይለቀቃል። እርሱን ለመከተል የሚመርጡ ሰዎች ሁሉ ከሰይጣንና ከአጋንንቱ ጋር ይደመሰሳሉ። — ራእይ 19:19–21፤ 20:1–3, 7–10

ዕፁብ ድንቅ ክብር ወደተላበሰችው “አዲስ ምድር” መግባት

12. (ሀ) “እጅግ ብዙ ሰዎች” ነፃ አውጪአቸው ማን እንደሆነ ይናገራሉ? (ለ) አምላክን በማወደሱ ተግባር እነማን ይተባበሯቸዋል?

12 በሕይወት ለመትረፍ የታደሉት የምድር ነዋሪዎች ሁሉ የአሁኑ ዓለም ሲወድም የተፈጸሙትን አስፈሪ ሁኔታዎች ከኋላቸው አድርገው የክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ከፊታቸው ወለል ብሎ ሲዘረጋ እጅግ በጋለ የምስጋና ስሜት ተሞልተው ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አምላክን ያወድሳሉ። “እጅግ ብዙ ሰዎች” ጥልቅ በሆነ ልባዊ ስሜት በመመሰጥ “በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለአምላካችንና [ለይሖዋና] ለበጉ [ለኢየሱስ ክርስቶስ] ማዳን ነው” በማለት ከፍተኛ የዕልልታ ድምፅ ያሰማሉ። የአምላክ ሰማያዊ ድርጅት ታማኝ አባላትም የእነዚህን ክንዋኔዎች ታላቅ ትርጉም በመገንዘብ “አሜን፣ በረከትና ክብር ጥበብም ምሥጋናም ውዳሴም ኃይልም ብርታትም ለዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ለአምላካችን ይሁን፤ አሜን” እያሉ ከእነርሱ ጋር በዚህ ስግደት ይካፈላሉ። — ራእይ 7:10–12

13. የሰውን ልጆች በሕይወት ለማቆምና ለመፈወስ የተደረገውን ዝግጅት መጽሐፍ ቅዱስ እንዴት ይገልጸዋል?

13 በመጨረሻም የሰው ልጆች በሙሉ እውነተኛውን አምላክ የሚያከብር አንድ ሰብዓዊ ኅብረተሰብ ይሆናሉ፤ በሌላ አነጋገር ‘በአዲስ ሰማይ’ ሥር የሚተዳደር የይሖዋን ፍቅራዊ ሉዓላዊነት የሚያንጸባርቅ “አዲስ ምድር” ይሆናሉ። የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የመጨረሻው መጽሐፍ አስደሳች በሆኑ ምሳሌያዊ አነጋገሮች በመጠቀም በዚያን ጊዜ ለሰው ልጆች የሚወርዱትን አስደናቂ ጥቅሞች በሰማያዊቱ ኢየሩሳሌም ሰፊ ጎዳናዎች መካከል እንደሚፈስ ‘ከአምላክና ከበጉ ዙፋን እንደሚወጣ እንደ ብርሌ የሚያንጸባርቅ የሕይወት ውኃ’ አስመስሎ ይገልጻቸዋል። በዚህ ወንዝ ዳርቻዎች ላይ፣ የተመጋቢዎቹን ሰዎች ሕይወት ለማቆም የሚችል ፍሬ የሚያፈሩ፣ ለአሕዛብም መፈወሻ የሚሆኑ ቅጠሎችን የሚያወጡ ‘የሕይወት ዛፎች’ ይኖራሉ። ይህ ሁሉ፣ የሚያምንና ታዛዥ የሆነውን የሰው ዘር ለመፈወስና በሕይወት ለማኖር፣ እንዲሁም በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ ለማስቻል አምላክ ያሰናዳውን ጠቅላላ ዝግጅት የሚያመለክት ነው። — ራእይ 21:1, 2፤ 22:1, 2

14. ‘በአዲሲቱ ምድር’ ውስጥ የሚኖሩት ሁኔታዎች ዛሬ ባለው ዓለም ላይ ካሉት ሁኔታዎች በምን መንገዶች የተለዩ ይሆናሉ?

14 በዚያን ጊዜ በምድር ላይ የሚኖረው ሁኔታ አሮጌው ዓለም ያፈራው ምንም ነገር የማይተካከለው፣ ልዩና መንፈስን የሚያድስ ይሆናል። ታዛዥ የሰው ልጆች፣ የክርስቶስ መሥዋዕት ያስገኘው ጥቅም በእነርሱ ላይ እንዲሠራ ሲደረግና ስለ አምላክ ፈቃድ ትምህርት ሲሰጣቸው፣ እነርሱም ሆኑ ከሙታን የሚነሱት፣ ማንኛውም የኃጢአት ምልክት ይራገፍላቸዋል። እንዲሁም በአካል፣ በአእምሮ፣ በስሜትና በመንፈሳዊነት ወደ ፍጽምና እስኪደርሱ ድረስ እየተሻሻሉ እንዲሄዱ ይደረጋል። ማንኛውም ሰው አንዱን ከአንዱ የሚከፋፍሉ “የሥጋ ሥራዎች” ከማፍራት ይልቅ እንደ ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ደግነት፣ ጥሩነት፣ እምነት፣ የዋህነትና ራስን መግዛት የመሳሰሉ የመንፈስ ፍሬዎችን በብዛት ያፈራል። (ገላትያ 5:19–23) እንደዚህ ያለ መንፈስ በሰለጠነበት ዓለም ላይ፣ ምድር የምታፈራቸው ነገሮች የሰውን ልጆች ፍላጎት ለማሟላት በገፍ ይታደላሉ። የሰው ልጆች፣ ፈጣሪያቸው ለምድርና ለነዋሪዎቿ የነበረውን የመጀመሪያ ዓላማ ለመፈጸም በኅብረት ሲሠሩ ሕይወት ከምን ጊዜውም የበለጠ ጣፋጭና ትርጉም ያለው ይሆናል።

15. (ሀ) አሁንም ቢሆን ለሰው ልጆች ሁሉ ምን ማራኪ ጥሪ እየቀረበ ነው? (ለ) እንግዲያው በግላችን ምን እያደረግን መሆን አለብን?

15 ይህን ሁሉ በከፍተኛ ደስታ በመጠበቅ፣ የአምላክ መንፈስና የክርስቶስ ሙሽራ በአሁኑ ጊዜ በየትም ቦታ ለሚገኙ ሰዎች “ና . . . የሚሰማም ሁሉ ና ይበል። የተጠማም ይምጣ፣ የወደደም የሕይወትን ውኃ እንዲያው ይውሰድ” የሚል ልባዊ ግብዣ ያቀርባሉ። (ራእይ 22:17) እንግዲያው አሁን፣ የይሖዋ የጊዜ ቆጠራ በታላቁ መከራ ላይ ወደ ዜሮ ሰዓቱ እስኪደርስ ድረስ ቁጭ ብለን፣ እጅና እግራችንን አጣጥፈን የምንጠብቅበት ጊዜ አይደለም። “የሕይወትን ውኃ እንዲያው ይውሰድ” የሚለውን የቸርነት ጥሪ ተቀብለሃል፤ እንግዲህ አንተም በተራህ ያንን ጥሪ ለሌሎች እንድታሰማ መብት ተሰጥቶሃል። ከመጪው ታላቅ መከራ በሕይወት ተርፈው ዕፁብ ድንቅ ክብር ወደምትላበሰው የአምላክ “አዲስ ምድር” ለመግባት የሚጓጉ ሁሉ በቅንዓት የሚንቀሳቀሱበት ጊዜ ነው።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]