በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ተራፊዎቹን የሚጠብቃቸው ሕይወት

ተራፊዎቹን የሚጠብቃቸው ሕይወት

ምዕራፍ 4

ተራፊዎቹን የሚጠብቃቸው ሕይወት

1. መጪው “የይሖዋ ቀን” ምድርን ሰው የማይኖርባት ፍርስራሽ የማያደርጋት ለምንድን ነው? (ኢሳይያስ 45:18)

መጪው “የይሖዋ ቀን” አስፈሪ ቢሆንም ምድርን ሰው አልባ እስክትሆን ድረስ አያበላሻትም። የኑክሌር ጦርነት ቢደረግ የተፈጥሮን ሚዛን ይገለባብጣል፣ በሕይወት የተረፉትንም ለዓይን በማይታይ መርዛም ጨረር እያሠቃየ ይጨርሳቸዋል ተብሎ የሚፈራ ሲሆን በይሖዋ ቀን ግን እንዲህ ያለ ነገር ከቶ አይሆንም። ፈጣሪያችን ምድርን አበላሽቶ ለመኖሪያነት የማትመች ባዶ ቦታ ከማድረግ ይልቅ “ምድርን የሚያጠፉትን” ያጠፋቸዋል። — ኢዩኤል 2:30, 31 አዓት፤ ራእይ 11:18

2. ይሖዋ የታመኑ አገልጋዮቹን ከታላቁ መከራ እንደሚያድናቸው ትምክህት የሚሰጠን ምንድን ነው?

2 የታመኑ የአምላክ አገልጋዮች ምንም እንኳ በዙሪያቸው የጥፋት ውርጅብኝ ቢወርድም ከዚያ መዓት አምላክ ሊያድናቸው ስለመቻሉ በአእምሯቸው ውስጥ ቅንጣት ያህል ጥርጣሬ የለም። በሥነ ምግባር የተበላሹት ሰዶምና ጎሞራ ‘ከሰማይ በወረደ እሳትና ዲን’ በጠፉ ጊዜ የይሖዋ መላእክት ሎጥንና ሁለቱን ሴቶች ልጆቹን እንዳዳኗቸው ያውቃሉ። (ዘፍጥረት 19:15–17, 24–26) ከዚህም ሌላ በሙሴ ጊዜ የግብፅ በኩራት ሁሉ ሲጠፉ ፍርድ አስፈጻሚው መልአክ በበግ ደም ምልክት የተደረገባቸውን የእስራኤላውያን ቤቶች እንዳለፈ ያስታውሳሉ። (ዘጸአት 12:21–29) በተመሳሳይም የታላቁ መከራ አውዳሚ ዶፍ ሲወርድ ይሖዋ ጥላ ከለላ ያደረጉትን ሰዎች ያድናቸዋል። — መዝሙር 91:1, 2, 14–16፤ ኢሳይያስ 26:20

3. በየቦታው የወደቀው ሬሳ በሕይወት ለሚተርፉት ጤንነት አስጊ የማይሆነው ለምንድን ነው?

3 እውነት ነው፤ በታላቁ እልቂት ሳቢያ ምድር በየቦታው በተዘረሩ ‘የይሖዋ ግዳዮች’ እንደምትሞላ የተረጋገጠ ነው። ሆኖም በሕይወት የተረፉትን ሰዎች ጤንነት ለመጠበቅ ምን ማድረግ እንደሚያስፈልግ ከይሖዋ የተሻለ የሚያውቅ የለም። እርሱም የሰማይ ወፎችንና የምድር አራዊትን ወደ ‘ታላቁ የራት ግብዣው’ እንደሚጠራቸውና የበድኖችን ሥጋ በልተው እንደሚጠግቡ ይነግረናል። (ራእይ 19:17, 18፤ ሕዝቅኤል 39:17–20) ከእነርሱ የተረፈውን አምላክ በሌሎች መንገዶች ሊያስወግደው ይችላል። ከዚያ በኋላ በዔደን ውስጥ የተገለጸው አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ ወደ ፍጻሜው ይገሰግሳል።

የመጀመሪያው የአምላክ ዓላማ የሚጠቁምልን ነገር

4. ይሖዋ የመጀመሪያዎቹን ወንድና ሴት እንዴት ባለ ሁኔታ አስጀምሯቸው ነበር? ይህስ ለእኛ ልዩ ትርጉም ያለው ለምንድን ነው?

4 ከታላቁ መከራ በሕይወት ለሚተርፉት ሰዎች የወደፊቱ ጊዜ ምን እንደያዘላቸው ይሖዋ በዔደን ውስጥ ለሰብዓዊ ቤተሰብ የሰጠው ጅምር ጥሩ ጥቆማ ያደርጋል። ፈጣሪያችን ምድርን ለሰው ዘር መኖሪያ እንድትሆን ሲያዘጋጃት ዓይነታቸውና ብዛታቸው ተቆጥሮ የማይዘለቅ አትክልቶች፣ ዓሦች፣ ወፎችና የመሬት እንስሳት ፈጥሯል። “እግዚአብሔር አምላክም በምሥራቅ በዔድን ገነትን ተከለ የፈጠረውንም ሰው ከዚያው አኖረው።” (ዘፍጥረት 2:8) ይሁን እንጂ አምላክ መላዋን ምድር ገነት አድርጎ በማዘጋጀት ክብካቤ ብቻ የሚያሻት መናፈሻ አላደረጋትም። በዚህ ፋንታ ይሖዋ የመጀመሪያዎቹን ወንድና ሴት በጥሩ ሁኔታ አስጀመረ፣ ባረካቸው እንዲሁም የሚያከናውኑትን ሥራ ሰጣቸው። ችሎታቸውን ሙሉ በሙሉ እንዲጠቀሙበት አጋጣሚ የሚከፍትና የወጠኑትን ዳር በማድረስ እርካታ የሚያስገኝ ሥራ ነበር። ይህም ሕይወታቸውን ትርጉም ያለው ሊያደርግላቸው ይችል ነበር። ልጆችን መለኮታዊ ባሕርያት የሚያንጸባርቁ አድርጎ ማሳደግ፣ ገነት ጠቅላላውን ምድር እስክትሸፍን ድረስ በሁሉም ማዕዘናት ማስፋፋት፣ ምድርን በጥንቃቄ መያዝና በላይዋ የሚንቀሳቀሱትን ሕያዋን ፍጥረታት ሁሉ መንከባከብ እንዴት ያለ አስደሳች ሥራ ነበር! አዳምና ሔዋን የይሖዋን ሉዓላዊነት ማክበራቸውን እስካላቆሙ ድረስ ፈጽሞ አይሞቱም ነበር። አስደሳችና ፍጹም የሆነ ሕይወት አግኝተው በምድር ላይ ለዘላለም መኖር ይችሉ ነበር። — ዘፍጥረት 1:26–28፤ 2:16, 17

5. ስለዚህ ከታላቁ መከራ ለሚተርፉት ከፊታቸው ምን ዓይነት አጋጣሚዎች ይከፈቱላቸዋል?

5 እርግጥ፣ ከታላቁ መከራ በኋላ ሁኔታዎቹ በቅጽበት ተለውጠው ልክ በዔደን ገነት እንደነበረው አይሆኑም። ነገር ግን አምላክ ለምድርና ለሰው ልጅ የነበረው የመጀመሪያ ዓላማው አይለወጥም። ገነት ምድርን ትሸፍናለች፣ የሰው ልጆች ተንከባካቢዎቿ ይሆናሉ፣ ሁሉም ሰው እውነተኛውን አምላክ በአንድነት ያመልካል። የአምላክ ልጆች ብቻ የሚያገኙት ዓይነት ነፃነት በማግኘት ለዘላለም የመኖር ዕድል ከፊታቸው ይዘረጋላቸዋል። — ሉቃስ 23:42, 43፤ ራእይ 21:3, 4፤ ሮሜ 8:20, 21

6. (ሀ) ሳይጠፋ የቀረ የጦር መሣሪያ ካለ ምን ይሆናል? (ለ) ማንም ሰው እንደገና እየተራበ ለመኖር የማይገደደው ለምንድን ነው?

6 በመጀመሪያ ያሮጌው ሥርዓት ፍርስራሽ መጠረግ እንደሚያስፈልገው አያጠራጥርም። ገና ያልጠፋ የጦር መሣሪያ ካለ ተለውጦ ለሰላማዊ አገልግሎት እንዲውል ይደረጋል። (ሕዝቅኤል 39:8–10፤ ከሚክያስ 4:3 ጋር አወዳድር።) ከጥፋቱ የሚተርፉት ሰዎች የሚበሉት ምግብ እንዲያገኙ በየማሳው ያለ አዝመራ እንደሚሰበሰብ አያጠራጥርም። ከዚያ በኋላ እህል እየተዘራ አዲሱ መከር ሲሰበሰብ “ምድር ፍሬዋን ሰጠች፤ እግዚአብሔር አምላካችንም ይባርከናል” የሚለው ትንቢት ይፈጸማል። (መዝሙር 67:6፤ ከዘዳግም 28:8 ጋር አወዳድር።) ራስ ወዳድ የሆኑትና ሰውን እየከፋፈሉ የሚያጋጩት የአሮጌው ዓለም ኃይሎች ከተወገዱ በኋላ ጦሙን የሚያድር ሰው በፍጹም አይኖርም። — መዝሙር 72:16 አዓት

7. ይሖዋ ለምድር አዲስ ንጉሥ ሲሾም አመራረጡ ጥበቡንና ፍቅሩን የሚያንጸባርቀው እንዴት ነው?

7 ያ ዓለም የይሖዋ መመሪያና በረከት አስፈላጊነት በግልጽ በሚታያቸው ሕዝቦች የተሞላ ይሆናል። መመሪያዎቹና በረከቶቹም የራሱን የአምላክን ጥበብና ፍቅር በሚያንጸባርቅ መንገድ መስጠታቸው አይቀርም። ይሖዋ ለምድር አዲስ ንጉሥ አድርጎ የሾመው የገዛ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ነው። አምላክ ምድርንና በእርሷ ላይ ያሉትን የተለያዩ ሕያዋን ፍጥረታት የሠራው በእርሱ አማካኝነት መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። (ቆላስይስ 1:15–17) የአምላክ ልጅ በምድር ላይ ሕይወት ለሁልጊዜው እንዲቀጥል ምን እንደሚያስፈልግ በሚገባ ያውቃል፤ እንዲሁም ከሰው ልጆች ጋር ለተያያዙ ነገሮች ሁሉ ልዩ ፍቅር አለው። — ምሳሌ 8:30, 31

8. ክርስቶስ ምድራዊ ተገዢዎቹ ለይሖዋ አጽናፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት ምን አቋም እንዲኮተኩቱ ይረዳቸዋል?

8 ከሁሉ በላይ ደግሞ ልጁ የይሖዋን ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ በታማኝነት ይሠራል። ኢየሱስን በሚመለከት “የእግዚአብሔር መንፈስ፣ የጥበብና የማስተዋል መንፈስ፣ የምክርና የኃይል መንፈስ፣ የእውቀትና እግዚአብሔርን የመፍራት መንፈስ ያርፍበታል። እግዚአብሔርንም በመፍራት ደስታውን ያያል” ተብሎ ተተንብዮአል። (ኢሳይያስ 11:2, 3) ምድራዊ ተገዥዎቹ አኗኗራቸውን ከይሖዋ መንገዶች ጋር በማስማማት እሱ ያገኘውን ዓይነት ደስታ እንዲያገኙ ይረዳቸዋል። የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ዔደን መኖሪያቸው እንድትሆን በተሰጠቻቸው ጊዜ አምላክ አስቦላቸው የነበረው ዓይነት ሕይወት ኢየሱስ ንጉሥ ሆኖ ሲገዛ ከታላቁ መከራ በሕይወት ለተረፉት ይመለስላቸዋል።

የኢየሱስ አገልግሎት የሚጠቁመው ነገር

9. (ሀ) የተወረሰው ኃጢአት ያስከተላቸው አንዳንድ አስከፊ ውጤቶች ምንድን ናቸው? (ለ) ኢየሱስ የሠራቸው ተአምራት ምን ተስፋ የሚያሳድሩ ናቸው?

9 ይሁን እንጂ ይህን ዓይነት ሕይወት አግኝተን እንድንደሰት ከተፈለገ በመጀመሪያ ኃጢአት ካስከተላቸው አሳዛኝ ውጤቶች መላቀቅ ያስፈልገናል። ሁላችንም የይሖዋን ሉዓላዊነት ቸል በማለት በማመፁ ፍጽምናውን ካጣው ከአዳም ኃጢአትን ወርሰናል። ኃጢአት የሚያስከትለው ጠንቅ በተለያዩ መንገዶች ይታያል። በሽታንና የአካል ጉድለትን፤ እንዲሁም በመጥፎ ዓላማ ተነሳስቶ የማሰብ፣ የመናገርና የማድረግ ዝንባሌን አስከትሏል። በመጨረሻም ሞትን ያመጣል። (ሮሜ 5:12፤ 6:23) ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት ወደፊት የአምላክን መንግሥት ዜጎች ከዚህ ሁሉ ለማሳረፍ ምን እንደሚያደርግ የሚጠቁሙ ብዙ ተአምራት ሠርቷል።

10. ኢየሱስ ሳይንቲስቶች ሊሠሯቸው የማይችሏቸውን ተአምራት ለመሥራት መቻሉ ምክንያተ ቢስ ያልሆነው ለምንድን ነው?

10 ሆኖም አንዳንድ ሰዎች ኢየሱስ ስለፈጸማቸው እጅግ አስደሳች ተአምራት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሲያነቡ ይጠራጠራሉ። ለምን? ምክንያቱም ተጠራጣሪነት የተለመደ በሆነበት ዓለም ውስጥ ስለምንኖር ነው። ተጠራጣሪዎቹ እነዚህ ተአምራት እንዲታመኑ ከተፈለገ ዛሬ ያሉት ሳይንቲስቶች ሊሠሯቸው ወይም ማብራሪያ ሊሰጡባቸው መቻል አለባቸው ብለው ያስባሉ። ይሁን እንጂ ሳይንቲስቶች እስከ ዛሬ ድረስ ለምርምር ብዙ ጊዜና ገንዘብ የሚያጠፉት ለምንድን ነው? ምክንያቱም ያልደረሱበት ገና ብዙ ነገር ስላለ ነው። ለኢየሱስ አገልግሎት ያለንን ዝንባሌ በተመለከተ የሚነሳው ዋናው ጥያቄ አምላክ በሰው ልጆች ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ ገብቶ አንዳንድ ነገሮችን እንደሚያደርግ ለመቀበል ፈቃደኛ ነን ወይስ አይደለንም የሚለው ነው።

11. በሥራ 2:22 የኢየሱስ ተአምራት በምን ቃላት ተገልጸዋል? እነዚህስ ቃላት ምን ያመለክታሉ?

11 በ33 እዘአ በኢየሩሳሌም ተሰብስቦ ለነበረው ሕዝብ ሐዋርያው ጴጥሮስ “አምላክ በእርሱ በኩል ባደረጋቸው ኃያል ሥራዎችና ጠቋሚ ድንቆች እንዲሁም በምልክቶች አማካይነት አምላክ ለእናንተ በይፋ ያሳየው ሰው” ነው በማለት ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ተናግሯል። (ሥራ 2:22 አዓት) ተአምራቶቹ እዚህ ላይ ጴጥሮስ እንዳመለከተው ‘ኃያል ሥራዎች’ ነበሩ። ሌሎች ሰዎች ሊሠሯቸው ወይም ምንነታቸውን መግለጽ የማይችሏቸው፣ ነገር ግን የአምላክ ኃይል በኢየሱስ በኩል ይሠራ እንደነበረ የሚያረጋግጡ ነበሩ። ኢየሱስ መሲህ የሆነ የአምላክ ልጅ መሆኑን የሚያስረዱ “ምልክቶች” ነበሩ። ወደፊት ወደሚመጡ ልብን በደስታ የሚያሞቁ ተስፋዎች የሚያመለክቱ “ጠቋሚ ድንቆች” ነበሩ።

12. (ሀ) ለምጽ የነበረባቸው ሰዎች ስለ መንጻታቸው የሚናገረውን ዘገባ የሚያጽናና ሆኖ ያገኘኸው ለምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ ሽባውን ሲፈውስ በተለይ ትኩረታችንን የሚስብ ምን ቃል ተናግሯል?

12 የመጽሐፍ ቅዱስን የወንጌል ዘገባዎች በምታነብበት ጊዜ ኢየሱስ የሠራቸው ተአምራት በአምላክ መሲሐዊት መንግሥት ጊዜ እርሱ ለሰው ልጆች ለሚያደርግላቸው ነገሮች መቅድም እንደሆኑ አድርገህ ተመልከታቸው። ኢየሱስ በ33 እዘአ ወደ ኢየሩሳሌም ሲያልፍ አሥር ለምጻሞችን እንዳነጻ ሁሉ በዚያን ጊዜም እንደ ሥጋ ደዌ በመሳሰሉ የሰውነትን ቅርጽ በሚያበለሻሹ በሽታዎች የሚሠቃዩ ሰዎች እፎይ ይላሉ። ኢየሱስ እንደነዚህ ያሉትን ሰዎች ሊረዳቸው እንደሚችልና በእርግጥም ሊያደርግ እንደሚፈልግ አሳይቷል። (ሉቃስ 17:11–19፤ ማርቆስ 1:40–42) ብዙ ሰዎች ሽባ በሚያደርግ በሽታ ተጠቅተዋል። ኢየሱስ የአልጋ ቁራኛ የሆነውን አንድ ሽባ ኃጢአቱን ይቅር በማለት እንደፈወሰው ለእነርሱም ቢሆን ፈውስ ይመጣላቸዋል። — ማርቆስ 2:1–12

13. (ሀ) ማየት ለተሳናቸው (ለ) መስማት ወይም መናገር ለተሳናቸው (ሐ) በብዙ ሐኪሞች ተረድተው መዳን ላልቻሉ ሰዎች ተስፋ የሚሰጡትን የኢየሱስ ተአምራት ጥቀስ። (መ) ኢየሱስ ሁሉንም ዓይነት በሽታና ደዌ ለማዳን እንደሚችል እንዴት ታውቃለህ?

13 በመጀመሪያው መቶ ዘመን ኢየሱስ በገሊላና በአሥሩ ከተሞች ለነበሩት ሰዎች እንዳደረገው ሁሉ በዚያን ጊዜም የታወሩ ዓይኖች ይበራሉ፣ የማይሰሙ ጆሮዎች ይከፈታሉ፣ የተለጐሙ ምላሶች ይፈታሉ። (ማቴዎስ 9:27–30፤ ማርቆስ 7:31–37) ዛሬ ሐኪሞች ብዙ ሰዎችን ከበሽታቸው ሊፈውሱ አልቻሉም። በቅፍርናሆም ትኖር የነበረች አንዲት ሴት ይህን በመሰለ ሁኔታ ላይ ትገኝ ነበር። “ከብዙ ባለ መድኃኒቶችም ብዙ ተሣቀየች፤ ገንዘብዋንም ሁሉ ከስራ ባሰባት እንጂ ምንም አልተጠቀመችም።” ኢየሱስ ግን ፈወሳት፤ እንደ እርሷ ያሉ ብዙ ሰዎችንም ወደፊት ይፈውሳል። (ማርቆስ 5:25–29) በገሊላ አገልግሎቱ ወቅት “በሕዝብ ያለውን ደዌና ሕማም ሁሉ” በፈወሰ ጊዜ እንደታየው ካንሰር፣ የልብ በሽታ፣ ወባ፣ ቢልሃርዝያና የመሳሰሉት በሽታዎች ከአቅሙ በላይ አይሆኑበትም። — ማቴዎስ 9:35

14. ኢየሱስ ሙታንን ስለማስነሳቱ የሚናገሩት ዘገባዎች ለታላቁ መከራ ተራፊዎች ትንሣኤ ምን ማለት እንደሚሆን የሚጠቁሙት እንዴት ነው?

14 ይህ ጊዜ ባለፉት ብዙ መቶ ዘመናት ውስጥ ለሞቱት በቢልዮን ለሚቆጠሩ ሙታን (እርግጥ በታላቁ መከራ ወቅት አምላክ ያጠፋቸው ሙታን ይህን ዕድል አያገኙም) እንደገና የመኖርና ከዚያ በፊት በፍጹም አግኝተዋቸው የማውቋቸውን ተስፋዎች የመጨበጥ አጋጣሚ የሚያገኙበት ጊዜ ይሆናል። ለታላቁ መከራ ተራፊዎች ይህ ምን ማለት ይሆናል? ናይን በምትባል መንደር አጠገብ ኢየሱስ አንድያ ልጅዋን ወደ ሕይወት በመመለስ የመበለቲቱን የሐዘን እንባ አድርቋል። በቅፍርናሆም አንዲትን ልጅ ከሞት በማስነሳት ወላጆቿን በታላቅ ደስታ አስፈንድቋል። (ሉቃስ 7:11–16፤ ማርቆስ 5:35–42) የምታፈቅራቸው ሰዎች ከሙታን ሲነሱ በሕይወት ለመገኘት ትፈልጋለህን? ከመጪው ታላቅ መከራ በሕይወት ተርፈው ወደ “አዲስ ምድር” የሚገቡ ሁሉ አስደሳች ዕጣቸው ይህ ይሆናል።

15. (ሀ) የኢየሱስ ትምህርቶች በዚያን ጊዜ በምድር ላይ ምን ዓይነት ሰዎች እንደሚኖሩ የሚያመለክቱት እንዴት ነው? (ለ) በዚያን ጊዜ የምናገኘውን ዓይነት ሕይወት ዛሬ በትንሹ መቅመስ የምንችለው በምን መንገድ ነው?

15 በዚያን ጊዜ የሚኖረው ሕይወት ዛሬ እንዳለው ብዙ ጊዜ ተስፋ አስቆራጭና ሐዘን የተቆራኘው ዓይነት ከባድ ኑሮ አይሆንም። በሕይወት ተርፈው ወደ “አዲስ ምድር” የሚገቡት የኢየሱስ እውነተኛ ደቀ መዛሙርት ብቻ ስለሚሆኑ ይህ ነገር ኢየሱስ በሠራቸው ተአምራት ብቻ ሳይሆን በሰጠውም ትምህርት ጭምር ታይቷል። (ዮሐንስ 3:36) ኢየሱስ ተከታዮቹ ቁሳዊ ሀብት ከማሳደድ ይልቅ ለመንፈሳዊ ነገሮች የበለጠ ዋጋ እንዲሰጡ፣ በይሖዋ እንዲመኩ መመሪያ ለማግኘትም ወደ እርሱ እንዲመለከቱና የእርሱን በረከቶች እንዲያደንቁ አስተምሯቸዋል። በቃልና በምሳሌ ኢየሱስ የፍቅርንና የትሕትናን አስፈላጊነት፣ ስለ ሌሎች ችግር በጥልቅ ስለማሰብና የራስን ጉልበትና ጊዜ ለእነርሱ የመሠዋትን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ አሳይቷል። የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት የሆኑ ሁሉ አሁንም እንኳ እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ላይ ሲያውሉ ለነፍሳቸው ታላቅ እረፍት አግኝተዋል፤ በተራቸው ደግሞ ለሌሎች የመንፈስ እረፍትን አምጥተውላቸዋል። (ማቴዎስ 11:28, 29፤ ዮሐንስ 13:34, 35) ይህ ሁሉ የዛሬው ፍቅር የለሽ ዓለም በሚያልፍበት ጊዜ በሕይወት የሚተርፉት ለሚያገኙት አስደሳች ሕይወት መቅድም የሚሆን ትንሽ ቅምሻ ብቻ ነው። በአሁኑ ጊዜ የጥበብ እርምጃ ከወሰድክ ይህን የመሰለ ሕይወት ትጨብጣለህ።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 33 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

አምላክ ለሰው ልጆች የነበረው የመጀመሪያው ዓላማ

ምድርን አምላካዊ ባሕርያት በሚያንጸባርቁ ሰዎች መሙላት

ገነት ምድርን እስክትሸፍን ድረስ ማስፋፋትና ምድርንና እንስሳትን መንከባከብ

እየተደሰቱ በምድር ላይ ለዘላለም መኖር