በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ታላቅ ጥፋት በተደቀነበት ጊዜ የጥበብ እርምጃ ውሰድ

ታላቅ ጥፋት በተደቀነበት ጊዜ የጥበብ እርምጃ ውሰድ

ምዕራፍ 7

ታላቅ ጥፋት በተደቀነበት ጊዜ የጥበብ እርምጃ ውሰድ

1. (ሀ) ታይታኒክ ስትሰጥም (ለ) በፔሌ ተራራ ላይ እሳተ ጎሞራ ሲፈነዳ ሳያስፈልግ ብዙ ሰዎች የጠፉት ለምንድን ነው?

ታላቅ እልቂት የሚያስከትል አደጋ በመምጣት ላይ እንዳለ ከሚታመን ምንጭ ማስጠንቀቂያ ቢሰጥ ጥበበኛ የሆኑ ሰዎች ሕይወታቸውን ለማትረፍ እርምጃ ይወስዳሉ። (ምሳሌ 22:3) ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሌሎች ሰዎች ግን የተሳሳተ ነገር በማመናቸው ሳያስፈልግ እንደ ቅጠል ረግፈዋል። በ1912 ታይታኒክ የተባለች መርከብ ልትሰጥም ስትል ወደ ሕይወት አድን ጀልባዎች እንዲዛወሩ ማስጠንቀቂያ ቢሰጣቸውም መንገደኞቹ መርከቧ ፈጽሞ አትሰጥምም የሚለውን ቃል በማመናቸው ከመርከቧ ጋር ወደ ውቅያኖሱ ወለል ወርደዋል። በማርቲኒክ ውስጥ የሚገኘው የፔሌ ተራራ በ1902 የእሳተ ጎሞራ ረመጥና ዓለት መትፋት ሲጀምር በአቅራቢያው የምትገኘው የሴንት ፒየር ከተማ ነዋሪዎች ስጋት አድሮባቸው ነበር፤ ይሁን እንጂ አንዳንድ የኅብረተሰቡ ታዋቂ ሰዎች ጉዳዩ የስስት ጥቅማቸውን የሚነካ ስለነበር የአካባቢው የፖለቲካ ሰዎችና የአንድ ጋዜጣ አዘጋጅ ሕዝቡ ከተማይቱን ለቆ እንዳይሄድ በማደፋፈር ሕዝቡን ለማረጋጋት ሽርጉድ ይሉ ነበር። ሆኖም ድንገት ተራራው ፈነዳና 30,000 ሰዎች አለቁ።

2. (ሀ) በጊዜያችን ምን አስቸኳይ ማስጠንቀቂያ እየተነገረ ነው? (ለ) ሁኔታው አሳሳቢ የሆነው ለምንድን ነው?

2 በጊዜያችን ከዚህ ይበልጥ አስቸኳይ የሆነ ማስጠንቀቂያ እየተነገረ ነው። ይህም በአንድ አካባቢ ስለሚደርስ የተፈጥሮ አደጋ ሳይሆን አርማጌዶን ስለሚባል የአምላክ አጠቃላይ ጦርነት መቅረብ የሚያስገነዝብ ማስጠንቀቂያ ነው። (ኢሳይያስ 34:1, 2፤ ኤርምያስ 25:32, 33) የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ በተደጋጋሚ ወደ ሰዎች ቤት እየሄዱ ሕይወታቸውን ለማትረፍ የጥበብ እርምጃ እንዲወስዱ አሳስበዋል። ሳትዘገይ በአስቸኳይ አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ የሚያነሳሳ በቂ የሕይወት ፍቅር አለህን?

‘ዓለም ያልፋል’

3. ለዓለም ያለን ዝንባሌ በሕይወት ለመትረፍ ያለንን ተስፋ የሚነካው ለምንድን ነው?

3 ከጥፋት ለመትረፍ ያለህን ተስፋ የሚወስነው አንዱ አንገብጋቢ ጉዳይ ለዓለም ያለህ አቋም ነው። ሰው ሆነህ በሕይወት እስካለህ ድረስ በዓለም ውስጥ መኖርህ ግድ ነው። ይሁን እንጂ የዓለም መጥፎ ምኞቶች ተካፋይ መሆንና ዓለም ስለ አምላክ ምንም ደንታ ሳይኖረው በሚፈጽማቸው ነገሮች ተባባሪ መሆን የለብህም። ትምክህትህን በአምላክና በዓላማው ላይ በመጣል ፈንታ በሰዎችና በሚያቅዷቸው ነገሮች ላይ በመጣል ከዓለም ጋር መለጠፍ አይገባህም። ምርጫ ማድረግ ይኖርብሃል፤ ከሁለቱም ወገን ለመሰለፍ አትችልም። “የዓለም ወዳጅ ሊሆን የሚፈቅድ ሁሉ የእግዚአብሔር ጠላት ሆኖአል።” ለምን? ምክንያቱም የአምላክ ቃል እንደሚነግረን ‘ዓለም በሞላው በክፉው ተይዟል።’ — ያዕቆብ 4:4፤ 1 ዮሐንስ 5:19፤ መዝሙር 146:3–5

4. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስህን በመጠቀም ሰዎች በአምላክ መንግሥት ሥር ሕይወት እንዳያገኙ ዕንቅፋት የሚሆኑባቸውን ድርጊቶችና ዝንባሌዎች ግለጽ። (ለ) እነዚህን ነገሮች ይፈጽም የነበረ ማንኛውም ሰው በፍጥነት ሊተዋቸው የሚገባው ለምንድን ነው?

4 አምላክ ከሚያወግዛቸው ነገሮች ጋር ሙጥኝ ያሉ መሆናቸውን አኗኗራቸው የሚመሰክርባቸውን ሰዎች ይሖዋ ከጥፋቱ አድኖ ወደ አዲሱ የጽድቅ ሥርዓቱ አያስገባቸውም። ምክንያቱም ግልጽ ነው። አምላክ የሚያወግዛቸው አንዳንዶቹ ነገሮች ምንድን ናቸው? ብዙዎቹ ዓለም እንደ ተራ ነገር የሚመለከታቸው እንቅስቃሴዎችና ዝንባሌዎች ናቸው። ይሁን እንጂ ይህ ክፉ ዓለም ሲጠፋ በሕይወት ለመትረፍ የምንፈልግ ከሆነ፣ ሌሎች ሰዎች ያሻቸውን ቢያደርጉ ወይም ቢያስቡ፣ ሴሰኞች፣ አመንዝሮች፣ ግብረ ሰዶም ፈጻሚዎች፣ ምግባረ ብልሹዎችና ነውረኛ ነገር የሚያደርጉ ሰዎች በሕይወት ከሚተርፉት መካከል አይሆኑም ሲል መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ማስጠንቀቂያ ልብ እንላለን። ሌሎች ሰዎች ምንም ያህል ቢዋሹና በስርቆት ቢሳተፉ እኛ እንዲህ ያለውን አኗኗር እንሸሻለን። የጥንቆላ ተግባሮች ተወዳጅነት እያገኙ ቢሆንም እኛ ከእነዚህ ድርጊቶች እንርቃለን። ሌሎች ደግሞ ቀናተኞች፣ ጠበኞችና ግልፍተኞች ቢሆኑ ወይም ከብስጭት ለማምለጥ አደንዛዥ ዕፆችን ወይም ብዙ የአልኮል መጠጥ ቢወስዱም እኛ እነርሱን አንመስልም። እነዚህ ልማዶች ተጠናውተውን ከነበረም ለውጥ የማድረግን አስፈላጊነት መቀበል ይኖርብናል። አንዳንዶቹ ድርጊቶች ባለፉት ጊዜያት “ተራ ነገር” መስለው ይታዩን የነበሩ ቢሆኑም አሁን እርግፍ አድርገን እንተዋቸዋለን። ለምን? ምክንያቱም አምላክን ከልብ እናፈቅራለን፤ ሕይወትንም እንወዳለን። የአምላክ ቃል “እንደዚህ ያሉትን የሚያደርጉ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም” በማለት ያስጠነቅቀናል። — ገላትያ 5:19–21፤ ኤፌሶን 5:3–7፤ 1 ቆሮንቶስ 6:9, 10፤ 2 ቆሮንቶስ 7:1፤ ራእይ 22:15

5. (ሀ) ሕይወት ለእኛ ክቡር ነገር ከሆነ ምን ማድረግን መማር ይገባናል? (ለ) በዚህ አንቀጽ መጨረሻ ባሉት ጥቅሶች ውስጥ ምን ግሩም ባሕርያት ተጠቅሰዋል? እነርሱስ ምን ያህል አስፈላጊ ናቸው? እነዚህን ባሕርያት እንዴት ማፍራት እንችላለን?

5 ለዘላለም በደስታ የመኖርን አጋጣሚ ትልቅ ግምት የምንሰጠው ከሆነ ሕይወት ሰጪ የሆነውን አምላክ ይሖዋን እንዴት እንደምናስደስት መማር ያስፈልገናል። (ሥራ 17:24–28፤ ራእይ 4:11) በማንኛውም የሕይወታችን ዘርፍ የእርሱን ቃል ደረጃ በደረጃ በሥራ ላይ ማዋል ይገባናል። ይህንን ስናደርግ ስለ ራሳችንና ስለ ሌሎች ሰዎች ያለንን አመለካከትና ስለ ግል ንብረቶችና ግቦች ያለንን ዝንባሌ በቁም ነገር እናስብበታለን፤ ይህ ዝንባሌአችን በአምላክ ፊት የሚኖረንን አቋም እንዴት እንደሚነካውም እናጤናለን። በዙሪያችን ያሉት ሰዎች ራሳቸውን፣ ጎሣቸውን፣ ዘራቸውን ወይም ብሔራቸውን ከመጠን በላይ ከፍ አድርገው ይመለከቱ ይሆናል። እኛ ግን “እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፣ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል” የሚለውን ጥቅስ በጥሞና እናስብበታለን። — ያዕቆብ 4:6፤ ሶፎንያስ 2:2, 3፤ መዝሙር 149:4

6, 7. የራሳችንን ሕይወት ከ1 ዮሐንስ 2:15–17 አንፃር መመርመር የሚገባን ለምንድን ነው?

6 ሌሎች ሰዎች በፍቅረ ነዋይ የተያዘው ኅብረተሰብ ለሚቀሰቅሳቸው ምኞቶች እንደ ባሪያ ሆነው ቢገዙም ወይም ታዋቂ የመሆን ምኞት ቢነዳቸውም እኛ የራሳችንን ሕይወት 1 ዮሐንስ 2:15–17 ከሚናገረው አንፃር እንመረምራለን። ጥቅሱ እንዲህ ይላል:- “ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለ ሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ፣ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም። ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል።” ለውጥ ማድረግ የሚያስፈልገን ከሆነ ጊዜው አሁን ነው።

7 ይህ ዓለምም ሆነ የአኗኗር ዘይቤው ለዘላለም አይቀጥሉም። ዓለም “የማትሰጥም” መርከብ አይደለችም። የዚህ ዓለም ሰዎች በተከታዮቻቸው ላይ ዓለምን በጥረት ማሻሻል ይቻላል የሚል እምነት በማሳደር ከእጃቸው እንዳያመልጡ አጥብቀው ሊይዟቸው ይሞክሩ ይሆናል። ይሁን እንጂ ከፊታችን ከተጋረጠው መዓት በሕይወት መትረፍ የሚቻልበት ብቸኛው መንገድ የአምላክን ማስጠንቀቂያ መስማት ነው። በዚህ ረገድ በነቢዩ ዮናስ ጊዜ የነበሩት የነነዌ ሰዎች ልብ ልንለው የሚገባንን አርዓያ ትተውልናል።

‘በዮናስ ስብከት ንስሐ ገቡ’

8. የነነዌ ሰዎች ዮናስ የአምላክን ማስጠንቀቂያ ሲነግራቸው ጥበብ ያሳዩት እንዴት ነበር? ከምንስ ውጤት ጋር?

8 በዘጠነኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ይሖዋ ነቢዩ ዮናስን የአሦር ዋና ከተማ ወደሆነችው ወደ ነነዌ በመላክ በክፋታቸው ምክንያት ነነዌ የምትደመሰስ መሆኗን እንዲያውጅ አዘዘው። ዮናስ በ40 ቀን ውስጥ ትጠፋላችሁ እያለ ባስጠነቀቀ ጊዜ ምን አደረጉ? በማፌዝ ፋንታ “የእግዚአብሔርን ቃል አመኑ፤ ጾምም ዐወጁ፤ . . . ማቅ ለበሱ።” ንጉሡ ራሱ ከሕዝቡ ጋር ተባበረ፤ እንዲሁም አምላክን እንዲማጸኑና ከመጥፎ መንገዳቸውና ከዓመፅ ድርጊታቸው እንዲመለሱ አጥብቆ አሳሰባቸው። ሕዝቡን ለማግባባት “ምናልባት እግዚአብሔር ራርቶልን ቁጣውን ይመልስ ይሆናል፤ እኛም ከጥፋት እንድናለን” ብሎ ተናገራቸው። ከመጥፎ መንገዳቸው ስለተመለሱም ይሖዋ ምሕረት አደረገላቸው። ሕይወታቸው ከጥፋት ተረፈ። — ዮናስ 3:2–101980 ትርጉም።

9, 10. (ሀ) የነነዌ ሰዎች በምን በኩል ጥሩ ምሳሌ ሊሆኑን እንደሚችሉ ነው ኢየሱስ የተናገረው? (ለ) በዛሬው ጊዜ እንደ እነዚያ የነነዌ ሰዎች የሆኑት እነማን ናቸው?

9 ኢየሱስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ ይኖሩ ለነበሩት እምነተቢስ አይሁዶች ያንን ታሪክ በመጥቀስ ወቅሷቸዋል፤ እንዲህ አለ:- “የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥተው ይፈርዱበታል፤ በዮናስ ስብከት ንስሐ ገብተዋልና፣ እነሆም፣ ከዮናስ የሚበልጥ ከዚህ አለ።” — ማቴዎስ 12:41

10 ስለ ዘመናችንስ ምን ሊባል ይቻላል? ይህን የመሰለ ንስሐ የሚያሳዩ ሰዎች አሉን? አዎን፣ ልክ እንደ ነነዌ ሰዎች ከዚህ ቀደም የመጽሐፍ ቅዱስን አምላክ የማያመልኩ የነበሩ አሁን ግን የይሖዋን የማስጠንቀቂያ መልእክት ሰምተው እርምጃ የሚወስዱ በዓለም ዙሪያ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አሉ። በዚህ ዓለም ላይ ጥፋት ለምን እንደሚመጣ ሲነገራቸው የአምላክን ምሕረት ለማግኘት ይጥራሉ። የቀድሞ አኗኗራቸውን እርግፍ አድርገው በመተው እውነተኛ የአእምሮና የልብ ለውጥ አሳይተዋል፤ በአሁኑ ጊዜም “ለንስሐ የሚገባ ነገር እያደረጉ” ነው። (ሥራ 26:20፤ በተጨማሪም ሮሜ 2:4⁠ን ተመልከት።) ከእነርሱ አንዱ ለመሆን ትፈልጋለህን? የምትፈልግ ከሆነ አትዘግይ።

በአስቸኳይ እርቅ ለምኑ

11. (ሀ) የገባዖናውያን የቀድሞ ሁኔታ ምን ነበር? (ለ) ከእስራኤላውያን ጋር የሰላም ውል ለማድረግ የጠየቁት ለምን ነበር?

11 በኢያሱ ዘመን የነበሩት ገባዖናውያንም ሕይወታቸውን ለማትረፍ የጥበብ እርምጃ ወስደዋል። የገባዖን ሰዎች አኗኗራቸው በብልግና የተበላሸ፣ በፍቅረ ነዋይ ላይ ያተኮረ፣ በጣዖት አምልኮ የተሞላና አጋንንታዊ በመሆኑ ይሖዋ እንዲጠፉ የወሰነባቸው ከነዓናውያን ክፍል ነበሩ። ከ40 ዓመታት በፊት ይሖዋ እስራኤላውያንን ከግብፅ እንዴት ነፃ እንዳወጣቸውና ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተምሥራቅ የነበሩት ኃያላን አሞራውያን ነገሥታት በፊታቸው ሊቆሙ እንዳልቻሉ ሰምተዋል። ግዙፎቹ የኢያሪኮ ግንቦች ያለ መቆፈሪያ በፊታቸው እንደተናዱና የጋይ ከተማም የፍርስራሽ ክምር እንደሆነች ሁሉም ሰው ያውቅ ነበር። (ኢያሱ 9:3, 9, 10) የገባዖን ከተማ ነዋሪዎች በሕይወት ለመኖር ፈለጉ፤ ነገር ግን ከእስራኤል አምላክ ጋር ተዋግተው ማሸነፍ እንደማይችሉ ያውቃሉ። በፍጥነት አንድ ነገር መደረግ ነበረበት። ምን? የሰላም ውል እናድርግ ብለው እስራኤላውያንን ማስገደድ አይችሉም። ግን ለምን አንሞክርም ብለው አሰቡ። እንዴት?

12. (ሀ) በማታለል ዘዴ ቢጠቀሙም ገባዖናውያን ከጥፋት እንዲድኑ የተደረገው ለምንድን ነው? (ለ) ምን ለውጦችን ማድረግ ነበረባቸው? ምን ሥራስ ተሰጣቸው?

12 ገባዖናውያን አንድ ብልሃት ፈጠሩ። ከሩቅ አገር እንደመጡ የሚያስመስል ቁመና ያላቸውን ሰዎች ወደ ኢያሱ ለመላክ ወሰኑ። እነርሱም ወደ ኢያሱ ቀርበው ከሩቅ አገር እንደመጡ፣ ይሖዋ ያደረጋቸውን ታላላቅ ነገሮች እንደሰሙና አገልጋዮቻቸው ለመሆን ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን ለማድረግ ጥያቄ እንዲያቀርቡ ሕዝባቸው ወክሎ የላካቸው መሆኑን ተናገሩ። ኢያሱና የእስራኤል አለቆች በዚህ ተስማሙ። ከዚያ በኋላ እንዳታለሉ ሲደረስበት ገባዖናውያኑ ለሕይወታቸው ፈርተው ይህንን እንዳደረጉ በትሕትና እውነቱን በመግለጽ የታዘዙትን ማንኛውንም ነገር ለመፈጸም ፈቃደኞች መሆናቸውን አሳዩ። (ኢያሱ 9:4–25) ይሖዋ ነገሩን ከመጀመሪያው አንስቶ ይመለከተው ነበር። እርሱ አልተታለለም። ከዚያ በፊት ሞዓባውያን እንዳደረጉት ገባዖናውያን የሕዝቡን ሥነ ምግባር የማበላሸት ዓላማ አልነበራቸውም። በሕይወት ለመኖር የነበራቸውን ጽኑ ፍላጎትም አድንቆታል። በዚህም ምክንያት ከሌዋውያን ሥር በቅዱሱ ድንኳን እንጨት ሰባሪዎችና ውኃ ቀጂዎች ሆነው እንዲያገለግሉ፣ በዚህም ለይሖዋ አምልኮ ድጋፍ እንዲሰጡ ፈቀደላቸው። እርግጥ ለእንደዚህ ዓይነቱ አገልግሎት አምላክ እንዲቀበላቸው የቀድሞ ርኩስ ተግባራቸውን ጨርሶ መተው ነበረባቸው። — ኢያሱ 9:27፤ ዘሌዋውያን 18:26–30

13. (ሀ) ገባዖናውያንን ከሚመለከተው ከዚህ ትንቢታዊ ድራማ ልንጠቀም የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) ዛሬ ያሉት ሰዎች ታላቁ ኢያሱ ከጥፋት እንዲያድናቸው ከፈለጉ ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል?

13 እኛም ‘በመጨረሻዎቹ ቀኖች’ ማለቂያ ላይ የምንገኝ እንደመሆናችን መጠን ከጥፋት ለመትረፍ የሚፈልጉ ሁሉ ሳይዘገዩ በፍጹም ቅንነት እርምጃ መውሰድ ይኖርባቸዋል። ዛሬ የይሖዋ ፍርድ አስፈጻሚ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ኢያሱ ሊታለል አይችልም። እንደዚህ ያሉት ሰዎች ከጥፋቱ እንዲያድናቸው ከኢየሱስ ጋር መስማማት የሚችሉበት ብቸኛው መንገድ ይሖዋን እንደ እውነተኛ አምላክ አድርገው ማመናቸውን በሕዝብ ፊት ማሳወቅ ነው። (ከሥራ 2:17–21 ጋር አወዳድር።) ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ ክርስቶስን አምላክ እንዲጫወተው ከመደበለት ሚና አንፃር መቀበልና ከዚያ ወዲያም የዚህን የተወገዘ ዓለም አኗኗር የሚጠሉ ሆነው መኖር አለባቸው። ቀጥሎም ከአምላክ ሕዝብ ጉባኤ ጋር በመተባበር ቅዱስ አገልግሎት እያቀረቡ ትሑታን የአምላክ አገልጋዩች መሆን ይገባቸዋል። — ዮሐንስ 17:16፤ ራእይ 7:14, 15

14. ይሖዋ ገባዖናውያንን ከጠላቶቻቸው እጅ ማዳኑ ለእኛ ልዩ ትርጉም የሚኖረው ለምንድን ነው?

14 ገባዖናውያን ከይሖዋ ሕዝብ ጎን ለመቆም እንደወሰኑ ወዲያው ታላቅ ተጽዕኖ መጣባቸው። እንደገና የእስራኤል ባላጋራ እንዲሆኑና ከእነርሱ ጎን እንዲሰለፉ ለማስገደድ አምስት የአሞራውያን ነገሥታት ገባዖንን ከበቡ። ገባዖናውያኑ ባስቸኳይ ወደ ኢያሱ ሰዎችን በመላክ እንዲደርስላቸውና ከጠላት እንዲያስጥላቸው ተማጸኑት። እነርሱ የዳኑበት ሁኔታ በታሪክ ሁሉ ታይቶ የማያውቅ እጅግ በጣም አስገራሚ ትርዒት ነበር። ይሖዋ ጠላቶቻቸው ግራ እንዲጋቡ አደረገ፣ ታላላቅ የበረዶ ድንጋይ ከሰማይ አወረደ፣ እንዲሁም እስራኤላውያን ጠላቶቻቸውን እስኪደመስሱ ድረስ ቀኑን በተአምር አራዘመው። (ኢያሱ 10:1–14) የገባዖናውያኑ መዳን ወደፊት በሚደረገው አጠቃላይ የአርማጌዶን ጦርነት ወቅት እውነተኛውን አምላክ የሚያመልኩ እጅግ ብዙ ሰዎች ለሚያገኙት ይበልጥ አስገራሚ ለሆነ መዳን ትንቢታዊ ምሳሌ ነው። በየትኛውም ብሔር ያሉ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ የጥበብ እርምጃ ከወሰዱ ከዚያ ጥፋት የመዳን አጋጣሚ ይኖራቸዋል። አንተስ ዛሬ ለዚህ አጋጣሚ ራስህን አዘጋጅተሃልን? — ራእይ 7:9, 10

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]