በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አሁን ያለው ሥርዓት ምን ያህል ይቆያል?

አሁን ያለው ሥርዓት ምን ያህል ይቆያል?

ምዕራፍ 3

አሁን ያለው ሥርዓት ምን ያህል ይቆያል?

1. የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋዎችን በሚመለከት ብዙዎቻችን ከዚህ በፊት ምን ብለን ጠይቀናል?

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሕያው ሆነው የተገለጹትና አርማጌዶን ላይ የሚያበቁት ክንውኖች ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆዩ ለማወቅ መፈለጉ ያለ ነገር ነው። ያሁኑ ክፉ ሥርዓት የሚጠፋው መቼ ነው? ምድር ጽድቅን የሚወዱ ሰዎች የተሟላ ሰላምና ደኅንነት የሚያገኙባት ቦታ ስትሆን ለማየት በሕይወት እንገኝ ይሆን?

2. (ሀ) የኢየሱስ ሐዋርያት ምን ተመሳሳይ ጥያቄዎችን ጠይቀው ነበር? (ለ) የአሁኑ ክፉ ሥርዓት የሚያከትምበትን ጊዜ በትክክል እናውቃለንን? (ሐ) ይሁን እንጂ ኢየሱስ ምን ጠቃሚ መረጃ ሰጥቶናል?

2 ኢየሱስ ክርስቶስ እነዚህን ጥያቄዎች የሚመልሱ ጉልህ መግለጫዎችን በዝርዝር ሰጥቶናል። ይህን ዝርዝር መግለጫ የሰጠው ሐዋርያቱ “የመገኘትህና የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ምልክቱ ምንድን ነው?” ብለው በጠየቁት ጊዜ ነበር። ክፉ ሥርዓት በትክክል መቼ ይጠፋ ይሆን ስለሚለው ጥያቄ ግን ኢየሱስ “ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአባት ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን የሚያውቅ የለም” በማለት በግልጽ ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:3, 36 አዓት ) ይሁን እንጂ ወደ ‘ፍጻሜው [በግሪክኛ ቴሎስ ]’ መዳረሻ የሆነውን ዘመን ወይም “የነገሮችን ሥርዓት መደምደሚያ [በግሪክኛ ሲንቲሊያ ]” ስለሚያየው ትውልድ ብዙ ዝርዝር መግለጫዎችን ሰጥቷል። ይህንን በመጽሐፍ ቅዱስህ ውስጥ በማቴዎስ 24:3 እስከ 25:46 እንዲሁም በማርቆስ 13:4–37 እና በሉቃስ 21:7–36 ላይ ያሉትን ተመሳሳይ ዘገባዎች አንብብ።

3. የኢየሱስ መልስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የሚፈጸሙ ሁኔታዎችን ብቻ የሚገልጽ እንዳልሆነ እንዴት እናውቃለን?

3 እነዚህን ጥቅሶች ስታነብ ኢየሱስ ኢየሩሳሌም ከቤተ መቅደሷ ጋር በ70 እዘአ በምትጠፋበት ጊዜ የሚኖሩትንና ለዚህ ጥፋት መዳረሻ የሚሆኑትን ነገሮች አስመልክቶ የሰጠው መግለጫ የአጠቃላዩ ትንቢት አንዱ ክፍል ብቻ እንደነበረ ትገነዘባለህ። በአእምሮው ከዚህ ሰፋ ያለ ነገር ይዞ እንደነበረ ግልጽ ነው። ለምን እንዲህ ሊባል ይችላል? ምክንያቱም በማቴዎስ 24:21 ላይ “ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ እንግዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናልና” ብሎ ስለተናገረ ነው። የአንዲት ከተማና ማምለጫ አጥተው በውስጧ የታጐሩት ሰዎች መጥፋት ከዚህ መግለጫ ጋር አይተካከልም። እንዲሁም ይደርሳሉ ተብለው የተተነበዩት ሁኔታዎች ለረጅም ዘመን ስትጠበቅ የቆየችውን “የእግዚአብሔር መንግሥት” መምጣት እንደሚጠቁሙ በሉቃስ 21:31 ላይ ተገልጿል። እንግዲያው ኢየሱስ ነቅታችሁ ጠብቁት ብሎ የተናገረለት ጉልህ ‘ምልክት’ ምንድን ነው?

ባለ ብዙ ዘርፍ ምልክት

4. ኢየሱስ የሰጠው ‘ምልክት’ ምንድን ነው?

4 ኢየሱስ ጦርነት፣ የምግብ እጥረት፣ በስፋት የሚዛመት ቸነፈር፣ ታላላቅ የመሬት መንቀጥቀጦችና በዓመፅ መባባስ ሳቢያ የሚመጣ የፍቅር መቀዝቀዝ እንደሚታይ ተናግሯል። ነገር ግን ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ብቻውን የተሟላ ‘ምልክት’ ሊሆን አይችልም። ሥዕላዊ መግለጫው የተሟላ እንዲሆን በትንቢት የተነገሩት ምልክቶች ሁሉ በአንድ ትውልድ ውስጥ መፈጸም ይኖርባቸዋል። በተጨማሪም ኢየሱስ በላይ በሰማይና በባሕር ላይ በሚከሰቱት ነገሮች ምክንያት “ሰዎችም ከፍርሃትና በዓለም የሚመጣበትን ከመጠበቅ የተነሣ” እንደሚደክሙ ተንብዮአል። (ሉቃስ 21:10, 11, 25–32፤ ማቴዎስ 24:12፤ ከ2 ጢሞቴዎስ 3:1–5 ጋር አወዳድር።) ከዚህ ሁሉ ለየት ያለ፣ ነገር ግን የምልክቱ አንድ ዘርፍ የሆነ ነገር እንደሚከናወንም አስቀድሞ ተነግሯል። ኢየሱስ ተከታዮቹ ዓለም አቀፍ ስደት እየደረሰባቸውም እንኳ የአምላክን መንግሥት ምሥራች በመላዋ ምድር ላይ እንደሚሰብኩ ተንብዮአል። (ማርቆስ 13:9–13) ይህ ብዙ ገጽታዎችን ያካተተው መግለጫ እኛ ለምንኖርበት ዘመን በትክክል ይስማማልን?

5. እነዚህን ሁኔታዎች የታሪክ ድግግሞሽ ከመሆን የበለጡ የሚያደርጋቸው ምንድን ነው?

5 ዘባቾች በሰው ታሪክ ውስጥ ጦርነት፣ ረሀብ፣ የመሬት መንቀጥቀጥና ሌሎች ነገሮችም በተደጋጋሚ ደርሰዋል በማለት በዚህ ያሾፉ ይሆናል። ይሁን እንጂ እንደ እነዚህ ያሉት ሁኔታዎች አለፍ አለፍ እያሉ በአንዳንድ ቦታዎች ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ፣ ከብዙ ጊዜ በፊት አስቀድሞ ከተነገረለት ዓመት ጀምሮ ረዘም ላለ ጊዜ ከታዩ ልዩ ትርጉም ይኖራቸዋል።

6, 7. ከዚህ ባለ ብዙ ዘርፍ ምልክት ጋር በትክክል የሚስማሙት በ20ኛው መቶ ዘመን የተፈጸሙት ምን ሁኔታዎች ናቸው? (መልስህን በምትሰጥበት ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስህ በመጠቀም ኢየሱስ ከተናገረው ትንቢት ውስጥ ስለየትኛው እየተናገርክ እንዳለህ ጠቁም።)

6 እስቲ ቀጥሎ የተጠቀሱትን ሁኔታዎች ግምት ውስጥ አስገባ:- በ1914 የፈነዳው ጦርነት በጣም ከፍተኛ ስለነበር አንደኛው የዓለም ጦርነት በመባል ሊጠራ ችሏል። ከዚያ ወዲህ ምድር ሰላምን መልሳ አላገኘችም። አንደኛውን የዓለም ጦርነት ተከትሎ የሰው ዘር ፈጽሞ ዓይቶት የማያውቅ እጅግ ታላቅ ረሀብ መጣ፤ ዛሬም ቢሆን 40 ሚልዮን የሚያህሉ ሰዎች በየዓመቱ በምግብ እጥረት ምክንያት ይሞታሉ። በ1918 የተከሰተው ስፓኒሽ ፍሉ (የኅዳር በሽታ) በበሽታ ታሪክ ውስጥ ተወዳዳሪ በማይገኝለት ፍጥነት ዓለምን እያሰሰ ብዙ ሰው ረፈረፈ። ብዙ ሳይንሳዊ ምርምር በሚደረግበት ባሁኑ ጊዜም በቢልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በካንሰር፣ በልብ ሕመም፣ በአስጸያፊ የአባለዘር በሽታዎች፣ በወባ፣ በቢልሃርዝያና ሪቨር ብላይንድነስ በሚባል በሽታ እየተጠቁ ናቸው። የትላልቅ የመሬት መንቀጥቀጦች ተደጋጋሚነት ከ1914 በፊት በነበሩት ሁለት ሺህ ዓመታት ውስጥ ከደረሱት በአማካይ በ20 ጊዜ እጥፍ አድጓል። በምድር ዙሪያ ፍርሃትና ጭንቀት በማንኛውም የዕድሜ ክልል የሚገኙትን ሰዎች ያሠቃዩአቸዋል። ከመንስዔዎቹ መካከል የኢኮኖሚ ድቀት፣ የዓመፅ ወንጀሎችና ከሰርጓጅ መርከቦች በሚወነጨፍ ወይም ከሰማይ ተምዘግዝገው በሚመጡ የኑክሌር መሣሪያዎች ታላቅ እልቂት ይመጣል የሚል ፍርሃት ናቸው። ይህም ከ20ኛው መቶ ዘመን በፊት ከቶውንም የማይታሰብ ነገር ነበር።

7 በዚህ ሁሉ መሐል ኢየሱስ አስቀድሞ እንደተናገረው የመንግሥቱ ምሥራች ታይቶ በማይታወቅ መጠን በስፋት እየተሰበከ ነው። ከ230 በሚበልጡ አገሮችና ደሴቶች ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች በማንኛውም የኑሮ ደረጃ ላሉት ሰዎች በመላው ዓለም እየተፈጸሙ ያሉትን ነገሮች ትርጉም በአምላክ ቃል አማካኝነት ለማስረዳት ያለምንም ክፍያ በየዓመቱ ከአንድ ቢልዮን በላይ የሚሆን ሰዓት ያጠፋሉ። ሰዎች የአምላክ መንግሥት ዜጎች በመሆን “ከታላቁ መከራ” የሚተርፉበትን መንገድ ለማሳየት ምሥክሮቹ ተግተው ይሠራሉ። አንድ የካናዳ የዜና ዘገባ እንዳመለከተው ምሥክሮቹ ይህን ሲያደርጉ “በዓለም ውስጥ ካለ ከማንኛውም ሃይማኖታዊ ቡድን ይልቅ እነርሱ አነስተኛ የሆነ ጥፋት ቢፈጽሙ እንኳ ከሁሉ የከፋ ስደት ይደርስባቸዋል።”

8. በዚህ ትንቢት ውስጥ የተካተተው ዘመን የትኛው ነው?

8 ኢየሱስ የትንቢቱ አንድ ክፍል አድርጎ እንደሚከተለው በማለት የተወሰነው ጊዜ የሚያልቅበትን ወቅት እንደገለጸ ልናስታውስ ይገባናል:- “የተወሰኑት የአሕዛብ ዘመናት እስከሚፈጸሙ ድረስ ኢየሩሳሌም በአሕዛብ የተረገጠች ትሆናለች።” (ሉቃስ 21:24 አዓት) እነዚህ “የተወሰኑት ዘመናት” ተፈጽመዋልን?

“የተወሰኑት የአሕዛብ ዘመናት”

9. (ሀ) በአሕዛብ ‘የተረገጠችው’ “ኢየሩሳሌም” ምንድን ናት? (ለ) ይህ የኢየሩሳሌም ‘መረገጥ’ መቼ ጀመረ?

9 መልሱን በትክክል ለመረዳት ራሷ ኢየሩሳሌም ከምን ነገሮች ጋር ተዛምዶ እንደነበራት መገንዘብ አለብን። ከተማዋ በውስጧ ከሚገኘው የነገሥታት መኖሪያ ከሆነው የጽዮን ተራራ ጋር “የታላቁ ንጉሥ ከተማ . . . የይሖዋ ከተማ” እንደሆነች ተነግሮላታል። (መዝሙር 48:2, 8 አዓት፤ ማቴዎስ 5:34, 35) ከዳዊት መሥመር የተነሱት ነገሥታት “በይሖዋ ዙፋን ላይ” እንደተቀመጡ ተደርጎ ይቆጠር ነበር። በዚህ ምክንያት ኢየሩሳሌም ይሖዋ በምድር ላይ ገዥ ለመሆኑ ምልክት ሆና የቆመች ከተማ ነበረች። (1 ዜና መዋዕል 29:23 አዓት) ስለዚህ የባቢሎን ሠራዊት ኢየሩሳሌምን እንዲያጠፉና ንጉሡን እንዲማርኩ እንዲሁም ምድሪቱን ባድማ እንዲያደርጉ አምላክ በፈቀደላቸው ጊዜ በዳዊት ንጉሣዊ ዘር የምትመራዋን የአምላክ መንግሥት መርገጣቸው ነበር። ይህ ነገር በ607 ከዘአበ በደረሰ ጊዜ “የተወሰኑት የአሕዛብ ዘመናት” በዚያው ዓመት ጀመሩ። ከዚያን ጊዜ ወዲህ የዳዊት ዘር የሆነ ማንም ሰው በኢየሩሳሌም ላይ ንጉሥ ሆኖ አልገዛም።

10. (ሀ) ‘የመረገጧ’ ማብቃት ምን ማለት ይሆናል? (ለ) ከዚያ በኋላ ኢየሱስ የሚገዛው በየትኛዋ “ኢየሩሳሌም” ተቀምጦ ነው? ለምንስ?

10 እንግዲያው ‘የኢየሩሳሌም መረገጥ’ አበቃ ሲባል ምን ማለት ይሆናል? ይሖዋ ራሱ የመረጠውንና ከዳዊት ዘር የሆነውን ንጉሥ በዙፋን ላይ ማስቀመጡን የሚያመለክት ሲሆን ይህ ንጉሥ በአይሁዳውያን ላይ ብቻ ሳይሆን በጠቅላላው የሰው ዘር ጉዳዮች ላይ ሥልጣን ይኖረዋል። እርሱም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። (ሉቃስ 1:30–33) ነገር ግን እርሱ የሚገዛው የት ሆኖ ነው? በምድራዊቷ የኢየሩሳሌም ከተማ ላይ ተቀምጦ ይሆን? ከአምላክ መንግሥት ጋር የተያያዙ መብቶች ከሥጋዊ እስራኤላውያን የሚወሰዱ መሆናቸውን ኢየሱስ በግልጽ አመልክቶ ነበር። (ማቴዎስ 21:43፤ በተጨማሪም 23:37, 38⁠ን ተመልከት።) ከዚያን ጊዜ ወዲህ እውነተኛውን አምላክ የሚያመልኩ ሰዎች “ሰማያዊቷን ኢየሩሳሌም” ማለትም የአምላክን መንፈሳዊ ፍጥረታት ሰማያዊት ድርጅት እንደ እናታቸው አድርገው ተመልክተዋል። (ገላትያ 4:26) ኢየሱስ ምድርን ለመግዛት በዙፋኑ ላይ የሚቀመጠው በዚህች ሰማያዊት ኢየሩሳሌም ላይ መሆን ይኖርበታል። (መዝሙር 110:1, 2) ይህ የሚሆነው “የተወሰኑት የአሕዛብ ዘመናት” ሲያልቁ ነው። ታዲያ ይህ ነገር መቼ ተፈጸመ?

11 እና ሰንጠረዡ (ገጽ 27) (ሀ) ‘የተወሰኑት ዘመናት’ ማብቂያ የሚሰላው እንዴት ነው? (ለ) ስለዚህ እነዚህ ‘የተወሰኑት ዘመናት’ ሲፈጸሙ ምን ጀመረ? (ሐ) የታሪክ ምሁራን 1914⁠ን የሚመለከቱት እንዴት ነው? (ገጽ 29⁠ን ተመልከት።)

11 ይህ የሚፈጸመው በዳንኤል 4:10–17 ላይ የተጠቀሱት “ሰባት ዘመናት” በሚያበቁበት በ1914 ላይ እንደሚሆን ከአሥርተ ዓመታት በፊት ታውቆ ነበር። * ሆኖም ሙሉ ግንዛቤ የተገኘው በቀጣዮቹ ዓመታት ቀስ እያለ ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ኢየሱስ በመንግሥታዊ ሥልጣኑ በሰማይ መገኘቱን ያመለክታሉ ብሎ የተናገረላቸው ብዙ ነገሮችን አጣምሮ የያዘ ባለ ብዙ ዘርፍ ምልክት ደረጃ በደረጃ ሲፈጸም ተመልክተዋል። እነርሱ ወደ “ነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ” ውስጥ እንደገቡና ክርስቶስ በ1914 ንጉሥ ሆኖ መግዛት እንደጀመረ እንዲሁም እነዚህን ነገሮች ገና ሲጀምሩ ባየው ትውልድ ውስጥ የዚህ ክፉ ዓለም ፍጻሜ እንደሚመጣ ግልጽ ሆነላቸው።

የምትጠብቃቸው ነገሮች ምን ያህል ትክክል ናቸው?

12. ይህንን ድምዳሜ ለመቀበል ለአንዳንዶች ከባድ የሚሆንባቸው ምን የተሳሳተ ነገር ስለሚጠብቁ ነው? (ማቴዎስ 24:26, 27፤ ዮሐንስ 14:3, 19)

12 የኢየሱስን ትንቢት የሚፈጽሙትን እነዚህን ተጨባጭ ነገሮች የሚያውቁ አንዳንድ ሰዎች ምልክቶቹ የሚጠቁሙትን መደምደሚያ ለመቀበል አስቸጋሪ ሆኖባቸዋል። ለምን? ምክንያቱም ሌላ ነገር ስለሚጠብቁ ነው። የክርስቶስ ዳግመኛ መምጣት በዓይን የሚታይ እንደሚሆንና የሰው ልጆች የቀድሞ ሃይማኖታቸውን እየተዉ ወደ ክርስትና እየጐረፉ እንደሚገቡ ተነግሯቸዋል። የመጀመሪያው መቶ ዘመን አይሁዶችም በተመሳሳይ የጠበቋቸው ነገሮች ሳይፈጸሙ ቀርተዋል። መሲሑ እነርሱን ከሮም አገዛዘ ነፃ ለማውጣት የኃይል እርምጃ ሲወስድ እንመለከታለን ብለው ተስፋ አድርገው ነበር። የራሳቸውን የተሳሳተ ግምት የሙጥኝ ብለው በመያዝ የአምላክን አንድያ ልጅ ሳይቀበሉት ቀሩ። ክርስቶስ በንጉሣዊ ሥልጣኑ ላይ በሚገኝበት በአሁኑ ጊዜ ያንን ስህተት መድገሙ እንዴት ያለ ሞኝነት ነው! ከዚህ ይልቅ ቅዱሳን ጽሑፎች ራሳቸው ምን እንደሚሉ መመርመሩ ምንኛ የተሻለ ነው!

13. መጽሐፍ ቅዱስ ከክርስቶስ መገኘት ጋር የሚያያይዛቸው ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?

13 መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቶስ መግዛት የሚጀምረው በጠላቶቹ መካከል እንደሚሆን ያሳያል። (መዝሙር 110:1, 2) ክርስቶስ ንጉሣዊ ሥልጣን ከተሰጠው በኋላ ሰይጣንና አጋንንቱ ወደ ምድር አካባቢ እንደሚጣሉ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። በዚህም ምክንያት በምድር እየጨመረ የሚሄድ ወዮታ የሚሆንበት ወቅት ይሆናል። (ራእይ 12:7–12) በዚያም ወቅት ሰዎች ሕይወታቸውን ለማትረፍ እርምጃ እንዲወስዱ አጋጣሚ ለመስጠት የመንግሥቱ መልእክት በተጧጧፈ ሁኔታ እንደሚሰበክ ተገልጿል። (ማቴዎስ 24:14፤ ራእይ 12:17) ይሁን እንጂ በዚህ ስብከት ምክንያት ጠቅላላው ዓለም ወደ ክርስትና ይለወጣልን? ከዚህ በተቃራኒ መጽሐፍ ቅዱስ የስብከቱ ሥራ እንዳበቃ በሰው ታሪክ ውስጥ ወደር የሌለው እልቂት እንደሚመጣ ያሳያል። ሰዎች የላቀ ክብር የተጎናጸፈውን ኢየሱስ ክርስቶስን በሥጋዊ ዓይናቸው በጭራሽ የማያዩት ቢሆንም የክርስቶስ ንጉሣዊ መገኘት እውን እንደሆነ ለመቀበል ያልፈለጉ ሁሉ በትንቢት እንደተነገረው በእነርሱ ላይ የጥፋት እርምጃ እየወሰደ ያለው እርሱ መሆኑን ‘ለማየት’ ይገደዳሉ። — ራእይ 1:7፤ ማቴዎስ 24:30፤ ከ1 ጢሞቴዎስ 6:15, 16​ና ከዮሐንስ 14:19 ጋር አወዳድር።

14, 15. ከ1914 ወዲህ ብዙ ዓመታት ማለፋቸው በእርግጥም ‘በመጨረሻዎቹ ቀኖች’ ውስጥ ስለ መኖራችን እንድንጠራጠር ሊያደርገን የማይገባው ለምንድን ነው?

14 ይሁን እንጂ ከ1914 ወዲህ ከ80 ዓመታት በላይ ማለፋቸው ከዚያች ዓመት ጀምሮ ‘በመጨረሻዎቹ ቀኖች’ ውስጥ ስለመኖራችንና ክርስቶስ ፍርድ አስፈጻሚ ሆኖ የሚመጣበት ጊዜ ቅርብ ስለመሆኑ አንድ ዓይነት አጠራጣሪ ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል አያመለክትምን? በጭራሽ አያመለክትም! “ምልክቱ” መታየት ከጀመረበት ከ1914 አንስቶ የምልክቱን መፈጸም ስለሚያዩት ሰዎች ሲናገር ኢየሱስ “ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም” ብሏል። (ማርቆስ 13:30) የዚያ ትውልድ ክፍል የሆኑ ሰዎች ምንም እንኳን ቁጥራቸው በፍጥነት እያሽቆለቆለ ቢሆንም እስከ አሁን ድረስ በሕይወት አሉ።

15 በአሁኑ ጊዜ በመላው ዓለም የሰዎች አማካይ ዕድሜ 60 ዓመት መሆኑን የሚያመለክት ስታትስቲክስ ቢኖርም በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከዚህ ዕድሜ በላይ ይኖራሉ። በተገኙት መረጃዎቸ መሠረት በ1914 በሕይወት ከነበሩት ሰዎች መካከል በግምት ወደ 250,000,000 የሚሆኑት በ1980 ገና በሕይወት እንደነበሩ ተረጋግጦ ነበር። ያ ትውልድ ገና አላለፈም። በ1900 ወይም ከዚያ በፊት ከተወለዱት ውስጥ በ1980 በሕይወት የነበሩት ሰዎች 35,316,000 ብቻ እንደሆኑ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተመዘገበው አኀዝ ያሳያል። ስለዚህ ሰዎች ወደ ሰባዎቹና ሰማንያዎቹ ዓመታት ሲደርሱ ቁጥራቸው በፍጥነት ዝቅ እያለ ይሄዳል። እነዚህ ማስረጃዎች ከኢየሱስ ትንቢታዊ ምልክት ዝርዝር ሁኔታዎች ሁሉ ጋር ተዳምረው መጨረሻው በጣም ቅርብ እንደሆነ ያመለክታሉ። — ሉቃስ 21:28

16. ስለዚህ አቋማችን ምን መሆን ይኖርበታል?

16 አሁን ዳተኞች የምንሆንበት ጊዜ አይደለም። በአፋጣኝ እርምጃ የሚወሰድበት ጊዜ ነው! ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንዳስጠነቀቃቸው “እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፣ የሰው ልጅ [ኢየሱስ ክርስቶስ] በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና።” — ማቴዎስ 24:44

[የግርጌ ማስታወሻ]

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የታሪክ ምሁራን 1914ን እንዴት ይመለከቱታል?

በ1914 የተጀመረው ጦርነት “ታላቁ ጦርነት“ እና “አንደኛው የዓለም ጦርነት“ ተብሎ ተጠርቷል። ለዚህ ስያሜ መነሻ የሆነ ጥሩ ምክንያት አለ። ይህን ያህል እልቂት የታየበት ጦርነት ከዚያ በፊት ተደርጎ አያውቅም። ከዚያን ጊዜ ወዲህ የተደረጉት ጦርነቶች ሁሉ በ1914 የተጀመረው ጦርነት ቅጣይ ናቸው። ይህ ልዩ ዓመት ስላስከተላቸው ውጤቶች የተሰነዘሩትን የሚከተሉትን አስተያየቶች ተመልከት፦

● “ጦርነቱ የአውሮፓን ካርታ ከመለወጡና በንጉሥ የሚገዙ ሦስት ታላላቅ ግዛቶችን በአብዮታዊ እንቅስቃሴ ከማውደሙም ሌላ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በማንኛውም መስክ ለውጥ አስከትሏል። ከጦርነቱ በኋላ የፖለቲካ ሰዎችና ሌሎችም የለውጡን ሂደት ለመግታት ወይም ለማቆምና ነገሮችን ከ1914 በፊት ወደነበረው ’ደህና’ ሁኔታ ለመመለስ ሞክረዋል። ይህ ግን የማይቻል ሆነ። ነውጡ ብርቱና ለረጅም ጊዜ የቆየ ስለነበረ አሮጌው ዓለም እስከመሠረቱ ድረስ ተንዶ ነበር። ዓለምን ቀድሞ እንደነበረበት አድርጎ ከማኅበራዊ ሥርዓቶቹና ከሥነ ምግባር ደንቦቹ ጋር መልሶ ለመገንባት የቻለ ሰው አልነበረም።”

“. . . ለሥነ ምግባር በሚሰጠው ዋጋ በኩል የተደረገው ለውጥም በትንሹ የሚገመት አይደለም። በብዙ መስኮች አዲስ የአቋም መስፈርት መጣ። . . . አረመኔያዊ ግፍ የተፈጸመባቸውና ስለ ሰው ንብረት ደንታ ቢስ የሆኑት በጦር ግንባሩ የተፋለሙት ወታደሮች ብቻ አልነበሩም። ሰዎች ያለሟቸው ብዙ ግቦች፣ የዘር ጥላቻና ዋጋቢስ የሆኑ የሥነ ምግባር ግምቶች ብቻ ሳይሆኑ ብዙ ባሕላዊ የኑሮ ዘይቤዎችና የኅብረተሰብ ጠባዮችም ጭምር እንዳልነበሩ ሆነዋል። ለሥነ ምግባር ይሰጥ የነበረው ዋጋ ተለውጧል። ከዚያ በኋላ ሁሉም ነገር ጥልቅ መሠረት እንደሌለው ያህል ከቦታው እየሸሸ የሚሄድ ይመስላል። ገንዘብ ነክ የሆነው ሥርዓት፣ የፆታ ሥነ ምግባር፣ ፖለቲካዊ መርሆዎችና የሥነ ጥበብ ሕጎች ተናግተዋል።. . . .”

“የጊዜው ልዩ ባሕርይ የሆነው ሥር የሰደደ ያለመረጋጋት ሁኔታ በተለይ በኢኮኖሚው መስክ ጎልቶ ይታይ ነበር። እዚህ ላይ ጦርነቱ ውስብስብ የሆነውን ጥብቅ ሕጎችና በቀላሉ የማይፈርሱ የሥነ ምግባር አቋሞች የነበረውን፣ ያልታሰቡ ሁኔታዎችን እንደ ልብ ማስተናገድ የሚችለውን ሚዛናዊ ሥርዓት ያለ ምንም ርኅራኄ ደምስሶታል። . . . በዚህም መስክ ቢሆን ወደ ቀድሞው “ተፈጥሯዊ“ ሁኔታው ለመመለስ አልተቻለም።“​—ቫልድሺስቶሪያ—ፎከንስ ሊቭ ኦቭ ኩልተር (ስቶክሆልም፤ 1958) ጥራዝ 7፣ ገጽ 421, 422

● “ግማሽ መቶ ዘመን ቢያልፍም የታላቁ ጦርነት አሠቃቂነት በመንግሥታት አካልና ነፍስ ላይ ትቶት ያለፈው ጠባሳ አልሻረም። . . . መከራ ያጠላበት ይህ ዘመን የነበረው አካላዊና ሥነ ምግባራዊ ስፋት እጅግ ታላቅ ከመሆኑ የተነሳ ምንም ነገር እንደድሮው ሊሆን አልቻለም። ኅብረተሰብ በአጠቃላይ መልኩ ይኸውም የመስተዳድር ሥርዓቶች፣ ብሔራዊ ድንበሮች፣ ሕጎች፣ የጦር ኃይሎች፣ የመንግሥታት ግንኙነቶች ብቻ ሳይሆኑ ርዕዮተ ዓለም፣ የቤተሰብ ኑሮ፣ ሀብት፣ ሥልጣን፣ የሰዎች ግንኙነቶች፣ ማንኛውም ነገር ከላይ እስከ ታች ድረስ ተለውጧል። . . . በመጨረሻም የሰው ዘር ሚዛኑን ወደሚስትበት ደረጃ ደርሶ እስከ ዛሬ ድረስ ሊያገግም አልቻለም።”​—ጄኔራል ቻርልስ ደ ጎል በ1968 ከተናገሩት (ለ ሞንድ፣ ኅዳር 12, 1968)

● “የዓለምን አካሄድ ያስተዋሉ ሰዎች በተለይ ከ1914 ወዲህ በሚታየው የማይቀር ዕጣ የተወሰነለት በሚመስለው የጥፋት ጉዞ በጥልቅ ተረብሸዋል። ነገሩን በቁም ነገር የሚመለከቱ ብዙ ሰዎች ወደ ጥፋት አዘቅት እንዳንገባ የሚያግድ ምንም ነገር እንደሌለ እየተሰማቸው መጥቷል። እነዚህ ሰዎች የሰውን ዘር በተቆጡ አማልክት እንደሚነዳና የራሱን ዕድል ለመወሰን ምንም አጋጣሚ እንደሌለው በግሪኮች አሳዛኝ ልብ ወለድ ታሪክ ውስጥ እንዳለ አንድ ጀግና አድርገው ይመለከቱታል።”​—በርትራንድ ራስል፣ የኒው ዮርክ ታይምስ መጽሔት፣ መስከረም 27, 1953.

● “አሁን ባለንበት ሁኔታ ላይ ሆነን ያለፈውን ጊዜ ወደኋላ መለስ ብለን ስንቃኝ አንደኛው የዓለም ጦርነት መፈንዳቱ እንደ እንግሊዛዊው ታሪክ ጸሐፊ እንደ አርኖልድ ቶይንቢ አባባል ሥልጣኔአችንን ሊወጣ ወደማይችልበት የሃያኛው መቶ ዘመን ’የችግር ጊዜ’ ውስጥ ይዞት እንደገባ ልንገነዘብ እንችላለን። ሥልጣኔአችን ከተዘፈቀበት ከዚህ አዘቅት ፈጽሞ ሊወጣ አልቻለም። ያለፈው ግማሽ መቶ ዘመን ከፍተኛ ነውጦች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከ1914 የመነጩ ናቸው።”​—ዘ ፎል ኦቭ ዘ ዳይናስቲስ፦ ዘ ኮላፕስ ኦቭ ዘ ኦልድ ኦርደር (የሥርወ መንግሥታት መውደቅ፦ የአሮጌው ሥርዓት መንኮታኮት)(በኒው ዮርክ፣ 1963) በኤድመንድ ቴይለር የተጻፈ፣ ገጽ 16

ሁኔታዎች ዓለምን የሚያናጉ ሆነው የተለወጡበት ምክንያት ምንድን ነው?

የሚያረካ መልስ የሚሰጠን መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው።

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሠንጠረዥ]

1914​—የመጽሐፍ ቅዱስ የዘመናት ስሌትና የዓለም ሁኔታዎች ያነጣጠሩበት ዓመት

የዘመናት ስሌት

→ “ሰባት ዘመናት“ እንደሚኖሩና እነዚህም ዘመናት

ካለቁ በኋላ አምላክ ዓለምን የመግዛት ሥልጣን

ለመረጠው እንደሚሰጥ መጽሐፍ ቅዱስ አስቀድሞ ተናግሯል

(ዳንኤል 4:3-17)

→ “ሰባት ዘመናት” = 2,520 ዓመታት

(ከራእይ 11:2, 3፤ ከ​12:6, 14 እና

ከሕዝቅኤል 4:6 ጋር አወዳድር።)

→ ’ሰባቱ ዘመናት’ የጀመሩት፦ በ607 ከዘአበ

(ሕዝቅኤል 21:25-27፤ ሉቃስ 21:24)

→ ’ሰባቱ ዘመናት’ ያበቁት፦ በ1914 እዘአ

በዚህ ዓመት ኢየሱስ ክርስቶስ በሰማይ ዙፋን ላይ

ተቀመጠ፤ በጠላቶቹ መካከል መግዛት ጀመረ

(መዝሙር 110:1, 2)

ሰይጣን ከሰማይ ተባረረ፤ ለሰው ልጆች ወዮታ ወረደባቸው

ራእይ 12:7-12)

የመጨረሻ ቀኖች ጀመሩ (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5)

የመጨረሻ ቀኖች ምልክት ይሆናሉ የተባሉ ነገሮች

→ ጦርነት (በ1914 የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ጀመረ፤

ከዚያ በኋላ ሰላም ፈጽሞ አልተመለሰም)

→ ረሃብ (ባሁኑ ጊዜ በየዓመቱ 40 ሚልዮን

የሚያክሉ ሰዎችን ሕይወት ይቀጥፋል)

→ የበሽታ ወረርሽኝ (በሳይንሳዊ ምርምር ምጥቀት

በታየበት ዘመን)

→ የመሬት መንቀጥቀጥ (ከ1914 ወዲህ

በየዓመቱ በአማካይ ከ20 በላይ

ታላላቅ የመሬት መንቀጥቀጦች ደርሰዋል)

→ ፍርሃት (የወንጀል፣ የኢኮኖሚ ውድቀት፣

የኑክሌር እልቂት)

1914ን ያየው ትውልድ ከማለፉ በፊት አምላክ የአሁኑን ክፉ ትውልድ ይደመስሰዋል (ማቴዎስ 24:3-34፤ ሉቃስ 21:7-32)