በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እየመራ ነፃ የሚያወጣን ማን ነው?

እየመራ ነፃ የሚያወጣን ማን ነው?

ምዕራፍ 9

እየመራ ነፃ የሚያወጣን ማን ነው?

1. (ሀ) ‘ከታላቁ መከራ’ በሕይወት ለማለፍ ከፈለግን ለየትኛው ሥልጣን መገዛት ይኖርብናል? (ለ) አምላክ ሙሴን በተጠቀመበት ጊዜ የነበረው ሁኔታ ለዚህ ምሳሌ የሚሆነን እንዴት ነው?

ከዚህ ክፉ ዓለም ለመዳንና ከሚመጣው “ታላቅ መከራ” በሕይወት ለማለፍ የምንችለው የኢየሱስ ክርስቶስን መሪነት ከተቀበልንና በእርግጥም እርሱን እያዳመጥንና ፈለጉን እየተከተልን መሆኑን አሳማኝ በሆነ መንገድ ካስመሰከርን ብቻ ነው። (ሥራ 4:12) ሥጋዊ እስራኤላውያን በ1513 ከዘአበ ከግብፅ ነፃ በወጡ ጊዜ የተፈጸሙት ሁኔታዎች ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ይሆናሉ። ይሖዋ እስራኤላውያንን ቀይ ባሕርን አሻግሮ ካዳናቸው በኋላ ያሳድዳቸው የነበረውን የግብፅ ሠራዊት ደመሰሰው። በዚህ ጊዜ ሁሉ አምላክ ሕዝቡን ለመምራት የተጠቀመው በሙሴ በኩል ነበር። — ኢያሱ 24:5–7፤ ዘጸአት 3:10

2. (ሀ) ከእስራኤል ጋር ግብፅን ለቀው የወጡት “ብዙ ድብልቅ ሕዝብ” እነማን ነበሩ? (ለ) ከእነዚህ ብዙዎቹን ያለጥርጥር የሳባቸው ነገር ምንድን ነው? (ሐ) ብዙም ሳይቆይ በምን ጉዳይ ላይ ተፈተኑ?

2 እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመጓዝ ከግብፅ ሲወጡ ሌሎች ሰዎችም ከእነርሱ ጋር በመቀላቀል አብረው ወጥተዋል። ሙሴ በኋላ እንደጻፈው “ሌላ ብዙ ድብልቅ ሕዝብ . . . ከእነርሱ ጋር ወጡ።” (ዘጸአት 12:38) እነዚህ ሰዎች እነማን ነበሩ? ዕጣቸውን ከእስራኤል ሕዝብ ጋር ያደረጉ ግብፃውያን ወይም ሌሎች ባዕዳን ነበሩ። ይሖዋ እርሱ ብቻ እውነተኛ አምላክ እንደሆነ፣ የግብፅ አማልክት ግን የማይረቡና የሚያመልኳቸውን ለማዳን የማይችሉ ከንቱ አማልክት መሆናቸውን ለማሳየት ሲል በጨቋኞቹ ግብፃውያን ላይ አስፈሪ መቅሰፍቶችን ሲያወርድ እነዚህ ሰዎች ተመልክተዋል። ከዚህም ሌላ “ማርና ወተት ወደምታፈስ” ምድር እንሄዳለን እያሉ እራኤላውያን ሲያወሩላቸው በነገሩ እንደተማረኩ አያጠራጥርም። (ዘጸአት 3:7, 8፤ 12:12) ይሁን እንጂ አምላክ ሙሴን የሕዝቡ መሪና ነፃ አውጭ አድርጎ እንደሾመው ሙሉ በሙሉ ተቀብለው ነበርን? ይህን ለማረጋገጥ ብዙም ሳይቆይ ተፈትነዋል። — ሥራ 7:34, 35

3. (ሀ) የሙሴን መመሪያዎች መከተሉ በጣም አስፈላጊ የነበረው ለምንድን ነው? (ለ) ‘ወደ ሙሴ ውስጥ የመጠመቁ’ ትርጉም ምን ነበር? (ሐ) ይህስ ለመንፈሳዊ እስራኤላውያን አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው?

3 እስራኤላውያን ‘ከብዙ ድብልቅ ሕዝብ’ ጋር ሆነው ወደ ቀይ ባሕር ዳርቻ እንደተቃረቡ የግብፅ ንጉሥና የጦር ሠራዊቱ እያሳደዱ ደረሱባቸው፤ ዓላማቸውም እስራኤላውያንን ወደ ባርነት ቀንበር ለመመለስ ነበር። ከእጃቸው ለመዳን ከፈለጉ አንድ ላይ መሆንና የሙሴን መመሪያ መከተል ነበረባቸው፤ ምክንያቱም ይሖዋ በዚህ ጉዞ እንዲመራቸው የተጠቀመው በሙሴ በኩል ነበር። ይሖዋ ውኃውን በሚከፍልበትና የባሕሩን ወለል በሚያደርቅበት ጊዜ ጠላትን በተአምራዊ ደመና ጋርዶ እንዳይንቀሳቀስ ገታው። እስራኤል ሁሉና “ብዙ ድብልቅ ሕዝብ” ከሙሴ ጋር ሆነው ደረቁን የባሕር ወለል ተሻግረው አመለጡ። በግብፃውያን ላይ የደረሰው ግን ከዚህ ተቃራኒ ነበር። (ዘጸአት 14:9, 19–31) ውኃው በግራና በቀኝ እንደ ግድግዳ ቆሞ፣ ከበላያቸው ደግሞ የይሖዋን መገኘት የሚያመለክተው ደመና እያንዣበበ በውስጡ ሲያልፉ አንድ አስደናቂ ነገር ተፈጽሟል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ሁኔታ ጥምቀት ብሎ ይጠራዋል። ይህም ቃል በቃል በውኃ መጠመቅ ማለት ሳይሆን የእነርሱ ነፃ አውጪ ሆኖ ወደተላከው የይሖዋ ነቢይ ወደ ሙሴ ውስጥ የተጠመቁት ምሳሌያዊ ጥምቀት ነው። (1 ቆሮንቶስ 10:1, 2 አዓት) በተመሳሳይም ከዚህ ክፉ ዓለም ጥፋት በሕይወት የሚተርፉት መንፈሳዊ እስራኤላውያን በሙሉ ክርስቶስን እንደ ነፃ አውጪ አድርገው እየተመለከቱ በእርሱ ውስጥ በተመሳሳይ ጥምቀት ማለፍና መሪነቱን መቀበላቸውን በማያሻማ መንገድ ማሳየት አለባቸው። ዘመናዊው “ድብልቅ ሕዝብም” እነርሱን ተከትሎ ማለፍ ይኖርበታል።

4. ይሖዋ ለክርስቶስ ያቀዳጀው ሥልጣን ምን ያህል ታላቅ ነው?

4 ይሖዋ ለልጁ ለኢየሱስ ክርስቶስ ታላቅ ሥልጣን አቀዳጅቶታል። ‘የአሁኑ ክፉ የነገሮች ሥርዓት’ ከሚጠጣው መሪር ጽዋ ተካፋይ እንዳንሆን ሲል ይሖዋ በኢየሱስ በኩል ከሥርዓቱ መዳን የምንችልበትን መንገድ አዘጋጅቶልናል። (ገላትያ 1:3–5 አዓት፤ 1 ተሰሎንቄ 1:9, 10) በሙሴ በኩል ይሖዋ ለእስራኤል የሕዝቡን ዕለታዊ ሕይወት የሚነኩ ሕጎች ሰጥቶ ነበር። እነዚያን ሕጎች በታዛዥነት ሲያከብሩ በጣም ይጠቀሙ ነበር። አንዳንዶቹን ሕጎች መጣስ ግን የሞት ቅጣት ያስከትል ነበር። ከጊዜ በኋላ ኢየሱስ ከሙሴ የሚበልጥ ነቢይ ሆኖ መጣ። የኢየሱስ ትምህርት ሁሉ “የዘላለም ሕይወት ቃል” ነበር። እነዚህን ትእዛዛት ሆን ብሎ ማፍረስ መዳኛ የሌለው ሞት ያመጣል። እንግዲያው እርሱ የሚናገረውን ከልብ አዳምጠን መከተላችን ምን ያህል አስፈላጊ ነው! — ዮሐንስ 6:66–69፤ 3:36፤ ሥራ 3:19–23

5. ለኢየሱስ መገዛትን በጣም አስደሳች የሚያደርገው ነገር ምንድን ነው?

5 አንዳንድ ሰዎች የአንድን መሪ የበላይነት ተቀብሎ መገዛት ደስ የማይል ነገር መስሎ ይታያቸው ይሆናል። በሥልጣናቸው የሚባልጉ ብዙ ሰዎችን ተመልክተዋል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ልብን የሚያረጋጋ ቃል ተናግሯል። እንዲህ በማለት ሞቅ ያለ ግብዣ አቅርቦልናል:- “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፣ ወደ እኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፣ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፣ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና።” (ማቴዎስ 11:28–30) እንዴት የሚያጓጓ ግብዣ ነው! ልባቸውን በእርሱ ላይ ጥለው ይህንን ሞቅ ያለ ግብዣ የሚቀበሉ ሁሉ የጠበቁትን ነገር አያጡም። (ሮሜ 10:11) በአፍቃሪ እረኛ እንደሚጠበቅ መንጋ ተረጋግተው ይኖራሉ።

እውነተኛው መልካም እረኛ

6. (ሀ) የእስራኤል ሕዝብ በበረት ውስጥ እንዳሉ በጎች የነበሩት እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ ለእነዚህ “በጎች” የሚሾመውን እረኛ በሚመለከት ምን ተስፋ ሰጠ? ይህስ እንዴት ተፈጸመ?

6 የእስራኤል ሕዝብ ልክ የይሖዋ ንብረት እንደሆነ እንደ አንድ የበግ መንጋ ነበር። ይሖዋ እንደ በጎች በረት የሚከላከልላቸውን የሕግ ቃል ኪዳን ሰጥቷቸው ነበር። ይህም ስለ አምላክ ምንም ግድ ከሌላቸው አሕዛብ አኗኗር የሚጠብቃቸው አጥር ሆኖላቸዋል። በተጨማሪም እሺ ባይ ሰዎችን ወደ መሲሑ መርቷቸዋል። (ኤፌሶን 2:14–16፤ ገላትያ 3:24) እረኛና ንጉሥ ስለሚሆነው መሲሕ ይሖዋ “በላያቸውም [በበጎቼ ላይ] አንድ እረኛ አቆማለሁ እርሱም ያሰማራቸዋል፣ እርሱም ባሪያዬ ዳዊት ነው” በማለት ተናግሮ ነበር። (ሕዝቅኤል 34:23, 31) ይህ ማለት ግን ሞቶ የነበረው ዳዊት ራሱ እንደገና በአምላክ ሕዝብ ላይ ንጉሥ ሆኖ ይገዛል ማለት አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ ከዳዊት ንጉሣዊ መሥመር የሕዝቡን ደኅንነት የሚጠብቅ እረኛና ንጉሥ ያስነሳል ማለት ነበር። (ኤርምያስ 23:5, 6) በተለያዩ ጊዜያት ሰዎች መሲሐዊ ነፃ አውጪ ነን ብለው በሐሰት ተነስተው ነበር። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ክርስቶስ ለመሲሕነቱ እውነተኛ ማስረጃዎች ያሉት የአምላክ ልዑክ መሆኑን ለእስራኤል ቤት “በጎች” ለማስተዋወቅ ይሖዋ በ29 እዘአ መጥምቁ ዮሐንስን ተጠቅሞበታል። በዳዊት ንጉሣዊ መሥመር ይወለድ ዘንድ ሕይወቱ ወደ አንዲት አይሁዳዊት ድንግል ማኅፀን እንዲዛወር የተደረገው ሰማያዊ የአምላክ ልጅ ይህ ነበር። ዳዊት የሚለው ስም “የተወደደ” ማለት ነው። ስለዚህ ኢየሱስ በውኃ ከተጠመቀ በኋላ ይሖዋ ከሰማይ “የምወድህ ልጄ አንተ ነህ፣ በአንተ ደስ ይለኛል” የሚል ድምፅ ማሰማቱ ትክክል ነበር። — ማርቆስ 1:11፤ ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።

7. (ሀ) ኢየሱስ “መልካም እረኛ” እንደመሆኑ “ለበጎቹ” የጠለቀ ፍቅራዊ አሳቢነቱን ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) ይህስ ከእርሱ በፊት የመጡት ሐሰተኛ መሲሖች ከነበራቸው ሁኔታ በጣም የሚለየው እንዴት ነው?

7 ኢየሱስ ለመሞት አራት ወር የማይሞላ ጊዜ ሲቀረው “መልካም እረኛ እኔ ነኝ። መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ ያኖራል” ሲል ተናግሮ ነበር። (ዮሐንስ 10:11) ኢየሱስ ከእርሱ በፊት የመጡት ሐሰተኛ መሲሖች ከነበራቸው በጣም የተለየ ሚና እንደሚኖረው ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “ወደ በጎች በረት በበሩ የማይገባ በሌላ መንገድ ግን የሚወጣ እርሱ ሌባ ወንበዴም ነው። በበሩ የሚገባ ግን የበጎች እረኛ ነው፤ ለእርሱ በረኛው ይከፍትለታል፤ በጎቹም ድምፁን ይሰሙታል፣ የራሱንም በጎች በየስማቸው ጠርቶ ይወስዳቸዋል። የራሱንም ሁሉ ካወጣቸው በኋላ በፊታቸው ይሄዳል፣ በጎቹም ድምፁን ያውቃሉና ይከተሉታል፤ ከሌላው ግን ይሸሻሉ እንጂ አይከተሉትም፣ የሌሎችን ድምፅ አያውቁምና።” — ዮሐንስ 10:1–5, 8

8. (ሀ) ኢየሱስ የተከተሉትን አይሁዶች ወደየትኛው አዲስ “በረት” መራቸው? (ለ) ወደዚህ በረት ያመጣቸው ሰዎች ስንት ናቸው?

8 በአይሁዳውያኑ የበጎች በረት ውስጥ የነበሩትና የሕጉ ቃል ኪዳን በሚመራቸው አቅጣጫ የሄዱት ሰዎች አጥማቂው ዮሐንስ እንደ ‘በር ጠባቂ’ ሆኖ ኢየሱስን ሲያስተዋውቃቸው እንደ መሲሕ አድርገው ተቀብለውታል። ሰዎቹ የኢየሱስ ‘በጎች’ መሆናቸውን አሳዩ። እርሱም የይሖዋ ንብረት ወደሆነው አዲስ ምሳሌያዊ የበጎች በረት ወይም ጉረኖ መራቸው። ይህ በረት በአምላክ ዘንድ ሞገስ ያለው ዝምድና ማግኘታቸውን የሚያመለክት ሲሆን መሠረቱ አምላክ ከመንፈሳዊ እስራኤል ጋር የገባውና በራሱ በኢየሱስ ደም የጸደቀው አዲሱ ቃል ኪዳን ነው። በዚህ ቃል ኪዳን አማካኝነት እነርሱ ከክርስቶስ ጋር ሰማያዊ ሕይወት ለማግኘት ቻሉ፤ በዚህ ሁኔታ ለምድር አሕዛብ ሁሉ በረከት የሚመጣበት የአብርሃም “ዘር” ይሆናሉ። (ዕብራውያን 8:6፤ 9:24፤ 10:19–22፤ ዘፍጥረት 22:18) አምላክ ከሞት አስነስቶ ወደ ሰማያዊ ሕይወት የመለሰው ኢየሱስ ክርስቶስ የበጎቹ በረት ማለትም የአዲሱ ቃል ኪዳን “በር” ነው። ከአባቱ ዓላማ ጋር በመስማማት የተወሰነ ቁጥር ይኸውም 144,000 ሰዎችን ብቻ በመጀመሪያ ከአይሁድ፣ በኋላም ከሳምራውያንና ከአሕዛብ መካከል ወደዚህ በረት አምጥቷል። ኢየሱስ መልካም እረኛ ስለሆነ እያንዳንዱን በግ በስም ያውቀዋል፤ እንዲሁም ፍቅራዊ እንክብካቤ ያደርግለታል፤ ትኩረትም ይሰጠዋል። — ዮሐንስ 10:7, 9፤ ራእይ 14:1–3

9. ኢየሱስ የጠቀሳቸው “ሌሎች በጎች” እነማን ናቸው? እነርሱስ የሚሰበሰቡት መቼ ነው?

9 ይሁን እንጂ ኢየሱስ እረኛ የሚሆነው ሰማያዊ ሕይወት ለሚያገኘው ለዚህ “ታናሽ መንጋ” ብቻ አይደለም። (ሉቃስ 12:32) “ከዚህ በረት ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱን ደግሞ ላመጣ ይገባኛል ድምፄንም ይሰማሉ፣ አንድም መንጋ ይሆናሉ እረኛውም አንድ” በማለት ኢየሱስ ተናግሯል። (ዮሐንስ 10:16) እነዚህ እነማን ናቸው? በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ ያልገቡ፣ መንፈሳዊ እስራኤላውያንም ያልሆኑ ሰዎች ናቸው። የኢየሱስ መሥዋዕት ዋጋ እንዳለው በማመናቸው ምክንያት በምድር ላይ በሚኖረው የዘላለማዊ ሕይወት ዝግጅት ተካፋይ እንዲሆኑ በመሰብሰብ ላይ ያሉ ሰዎች ናቸው። የመንፈሣዊ እስራኤል አባላት እዚህ ምድር ላይ እያሉ የ“ሌሎች በጎች” ክፍል የሆኑ ብዙ ሰዎች ወደ እነርሱ በመምጣት የቅርብ ግንኙነት ፈጥረዋል። ከቅቡዓኑ ጋር ሆነው ክርስቶስን እንደ መልካም እረኛ አድርገው ይመለከቱታል። በራእይ 7:9, 10, 14 ላይ የተጠቀሱት ታላቁን መከራ በሕይወት የሚሻገሩት “እጅግ ብዙ ሰዎች” አሁን በምድር ላይ በሕይወት ያሉና ወደ መድረኩ ብቅ ያሉት የ“የሌሎች በጎች” ክፍል የሆኑት ሰዎች ናቸው።

10. ከእነዚህ “ሌሎች በጎች” አንዱ ለመሆን ምን ያስፈልጋል?

10 መጽሐፍ ቅዱስ በመልካሙ እረኛ ስለሚጠበቁትና ከጥፋት ስለሚድኑት “ሌሎች በጎች” ከሚሰጠው መግለጫ ጋር የሚስማማ ሁኔታ እንዲኖረው የፈለገ ሰው የኢየሱስን ድምፅ ‘መስማትና’ እውነተኛዎቹን የሰማይ መንግሥት ወራሾች የሚጨምረው “አንድ መንጋ” ክፍል መሆኑን ማስመስከር ይኖርበታል። አንተስ ይህን እያደረግህ ነውን? ድምፁን ምን ያህል በጥንቃቄ ታዳምጣለህ?

11. ኢየሱስ በዮሐንስ 15:12 ላይ የተናገረውን በእርግጥ ‘እንደሰማን’ የሚመሰክረው ምንድን ነው?

11 ኢየሱስ “እኔ እንደ ወደድኋችሁ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትእዛዜ ይህች ናት” ብሎ መናገሩን እንደምታውቅ አያጠራጥርም። (ዮሐንስ 15:12) ይህ ትእዛዝ ሕይወትህን የነካው እንዴት ነው? አንተ የምታሳየው ፍቅር ኢየሱስ በተግባር ያሳየው ዓይነት ፍቅር ነውን? ፍቅርህ የራስህን ጥቅም ለመሠዋት የሚገፋፋ ነውን? ድርጊትህና ስሜትህ በጉባኤ ውስጥ ላሉት ሁሉና ለቤተሰብህ ሁሉ እንደዚህ ዓይነቱ ፍቅር እንዳለህ ያረጋግጣልን?

12. (ሀ) በእርግጥ ‘ከኢየሱስ የምንማር’ ከሆነ ትምህርቱ በውስጣችን ምን ያህል ለውጥ ያመጣል? (ለ) ስለዚህ ከመጽሐፍ ቅዱስ የተማርናቸውን ነገሮች በተመለከተ ምን እያደረግን መሆን አለብን?

12 ሐዋርያው ጳውሎስ ኢየሱስን በእርግጥ ‘የምንሰማ’ እና ‘ከእርሱም የምንማር’ ከሆነ ጠቅላላው ባሕርያችን እንደሚለወጥ ተናግሯል። ከቀድሞ አኗኗራችን ጋር የሚስማማውን ሰውነት በመፋቅ የይሖዋን መልካም ባሕርያት የሚያንጸባርቀውን “አዲሱን ሰውነት” እንለብሳለን። (ኤፌሶን 4:17–24፤ ቆላስይስ 3:8–14) መጽሐፍ ቅዱስን ስታጠና አምላክን ለማስደሰት በግልህ ልታስተካክላቸው ስለሚገቡህ ጉዳዮች አጥብቀህ ታስባለህን? እንደነዚህ ያሉትን ለውጦች ለማድረግ ትጠነቀቃለህን? ኢየሱስ በጊዜያችን እንዲሠራ ያዘዘውን የሞትና የሕይወት ጉዳይ የሆነ ሥራ ይኸውም የተቋቋመችውን የአምላክ መንግሥት ምሥራች መስበኩን ከልብ ተቀብለኸዋልን? በዚህስ ሥራ ለመካፈል መንገድ ትፈላልጋለህን? አምላክ ላሳየህ ይገባኛል የማትለው ደግነት ያለህ አድናቆት ይህንን እንድታደርግ ልባዊ ምኞት ያሳድርብሃልን? — ማቴዎስ 24:14

13. (ሀ) ካልተጠነቀቅን ልባችን ሊያታልለን የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) እንግዲያው የኢየሱስን ፈለግ እስከ ምን ድረስ መከተል ይገባናል?

13 ልባችን እንዳያስተን መጠንቀቅ አለብን። በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በኢየሱስ ክርስቶስ እናምናለን ይላሉ። ምናልባትም እርሱ ያስተማራቸውን አንዳንድ ነገሮች ይጠቅሱ ይሆናል። ሆኖም በሥራ ላይ የሚያውሉት ለእነሱ የሚስማማቸውን ብቻ እየመረጡ ነው። አንዳንዶቹ ከባድ ኃጢአት ነው ብለው የሚያምኑትን ነገር ከመፈጸም ይቆጠቡ ይሆናል። በአምላክ መንግሥት ሥር ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የመኖሩ ተስፋ ይማርካቸው ይሆናል፤ እንዲሁም በአሁኑ ጊዜ የክርስትና መሠረታዊ ሥርዓቶች በሕይወታቸው ውስጥ ለመተግበር ከሚጥሩት ክርስቲያኖች ጋር መሰብሰቡ ያስደስታቸው ይሆናል። ነገር ግን ከጥፋቱ በሕይወት ተርፈን ወደ “አዲስ ምድር” ከሚገቡት ሰዎች መካከል ለመሆን ከፈለግን ኢየሱስ የተናገረውን እያንዳንዱን ነገር በጥንቃቄ ማዳመጥ ይኖርብናል። እርምጃችንን በራሳችን ለማቅናት አለመቻላችንን ማወቁ በጣም አስፈላጊ ነው። ይሖዋ የሕዝቦቹ ነፃ አውጪ አድርጎ የሾመው ልጁ የሚናገረውን መስማትና በጥንቃቄ ፍለጋውንም መከተል ይገባናል። — ኤርምያስ 10:23፤ ማቴዎስ 7:21–27፤ 1 ጴጥሮስ 2:21

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]