በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ተራፊዎች

ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ተራፊዎች

ምዕራፍ 8

ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ተራፊዎች

1. የሰው ዘር ‘ነገዶች በሙሉ’ በአምላክ ተቀባይነትን ለማግኘት የሚያስችል በር እንደሚከፈትላቸው የሚያሳይ ለአብርሃም የተሰጠ ምን የተስፋ ቃል አለ?

ይሖዋ በሁሉም ብሔራትና ጎሣዎች ሕዝብ ላይ ፍቅራዊ ትኩረት አድርጓል። የምድር ነገዶች በሙሉ የእርሱን ሞገስና በረከት አግኝተው በደስታ መኖር የሚችሉበትን ዝግጅት አድርጎላቸዋል። የኖኅ ልጅ የሴም ዘር ለሆነው ለአብራም (ለአብርሃም) ይሖዋ እንዲህ አለው:- “ከአገርህ ከዘመዶችህም ከአባትህም ቤት ተለይተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ውጣ። ታላቅ ሕዝብም አደርግሃለሁ፣ እባርክሃለሁ፣ ስምህንም አከብረዋለሁ፤ ለበረከት ሁን፤ የሚባርኩህንም እባርካለሁ፣ የሚረግሙህንም እረግማለሁ፤ የምድር ነገዶችም ሁሉ በአንተ ይባረካሉ [“ራሳቸውን ይባርካሉ።” አዓት]” (ዘፍጥረት 12:1–3፤ ሥራ 7:2–4) “የምድር ነገዶችም ሁሉ” ሲል ከየትኛውም ብሔር እንወለድ፣ ምንም ዓይነት ቋንቋ እንናገር ዛሬ የምንገኘውን ሁሉ ይጨምራል። — መዝሙር 65:2

2. (ሀ) እንደ አብርሃም ምን ዓይነት ጠባይ እንዲኖረን ያስፈልጋል? (ለ) ዕብራውያን 11:8–10 እንደሚያሳየው አብርሃም ይህ ጥሩ ጠባይ እንደነበረው ያሳየው እንዴት ነው?

2 ይህን የተስፋ ቃል ከይሖዋ የተቀበለው አንድ የእምነት ሰው ነው። እኛም እዚህ ላይ የተገለጹት በረከቶች ተካፋይ ለመሆን እምነት ሊኖረን ያስፈልጋል። (ያዕቆብ 2:23፤ ዕብራውያን 11:6) የአብርሃም እምነት በተግባር የተደገፈ ነበር እንጂ ቀዝቃዛ እምነት አልነበረም። ከመስጴጦምያ ተነስቶ ከዚያ በፊት ዓይቶት ወደማያውቅ ሩቅ አገር እንዲሄድ አነሳስቶታል። እዚያ ከነበሩት የከተማ መንግሥታት ከአንዱም ጋር ትስስር ሳይፈጥር “ለእንግዶች እንደሚሆን በተስፋ ቃል በተሰጠው አገር . . . እንደ መጻተኛ በእምነት ተቀመጠ፤ መሠረት ያላትን፣ እግዚአብሔር የሠራትንና የፈጠራትን ከተማ [የአምላክን መንግሥት] ይጠብቅ ነበርና።” — ዕብራውያን 11:8–10

3. አብርሃም ከይስሐቅ ጋር በተያያዘ ልብን በሚመረምር በምን ፈተና ውስጥ አለፈ?

3 አብርሃም 100 ዓመት ሲሆነው፣ ሚስቱ ሣራም 90 ዓመት ሲሞላት ይሖዋ በተአምር ወንድ ልጅ፣ ይኸውም ይስሐቅን በመስጠት ባረካቸው። ከዚህ ልጅ ጋር በተያያዘ መንገድ አብርሃም ለአምላክ ያለውን እምነትና ታዛዥነት የሚመረምር ፈተና ደርሶበታል። አብርሃም በዚህ ጊዜ ጎልማሳ የሆነውን ይስሐቅን ይዞ ወደ ሞሪያ ምድር እንዲሄድና እዚያ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ እንዲያቀርበው ይሖዋ አዘዘው። አምላክ የልጁን ሕይወት በትንሣኤ ለመመለስ እንደሚችል በመተማመን አብርሃም ትእዛዙን ለመፈጸም ተነሳ። (ዕብራውያን 11:17–19) ይስሐቅ ለአባቱ ፈቃድ ተገዥ በመሆን እጅና እግሩ ታስሮ በመሠዊያው ላይ ተጋድሟል። በዚህ ጊዜ አብርሃም ልጁን ለማረድ እጁን ሲያነሳ የይሖዋ መልአክ አስቆመው። አብርሃም ምንም ነገር ለአምላክ ከመስጠት ወደኋላ እንደማይል ፈተናው በበቂ ሁኔታ አረጋግጦ ነበር። በዚህ ምክንያት መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚከተለው በማለት እንደሚናገረው አምላክ ከአብርሃም ጋር ቃል ኪዳኑን አጸና:-

4. በዚያ ወቅት የሁሉንም ብሔራት ሕዝቦች በተመለከተ አምላክ ምን ትልቅ ተስፋ ሰጠ?

4 “እግዚአብሔር:- በራሴ ማልሁ ይላል፤ ይህን ነገር አድርገሃልና፣ አንድ ልጅህንም አልከለከልህምና በእውነት በረከትን እባርክሃለሁ፣ ዘርህንም እንደ ሰማይ ከዋክብትና በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ አበዛዋለሁ፤ ዘርህም የጠላቶችን ደጅ ይወርሳል፤ የምድር አሕዛብ ሁሉም በዘርህ ይባረካሉ፣ [“ራሳቸውን ይባርካሉ” አዓት ] ቃሌን ሰምተሃልና።” — ዘፍጥረት 22:15–18

5. (ሀ) አብርሃም ይስሐቅን ለመሠዋት ያደረገው ሙከራ ወደፊት ለሚፈጸም ለምን ነገር ጥላ ነበር? (ለ) በዘፍጥረት 12:3 ላይ ያለው ቃል ይፈጸም ዘንድ ሰዎች ታላቁ አብርሃምን ‘የሚረግሙት’ እንዴት ነው? በውጤቱስ ምን ይሆናሉ? (ሐ) እንዴትስ ‘ልንባርከው’ እንችላለን?

5 ታላቁ አብርሃም ይሖዋ መሆኑንና ይስሐቅም የኢየሱስ ክርስቶስ ጥላ እንደሆነ ከተገነዘብን እነዚህ ክንውኖች ለእኛ በግላችን እንዴት አስፈላጊ እንደሆኑ ማስተዋል እንጀምራለን። እንደ እውነቱ ከሆነ የወደፊት ሕይወታችንን የሚወስነው ለይሖዋ አምላክ በምናሳየው ዝንባሌ ነው። የዘላለም ሕይወት ተስፋ ማግኘት የቻልነው አምላክ አንድያ ልጁን ለኃጢአታችን መሥዋዕት አድርጎ በማቅረቡ ነው። አብርሃም ልጁን ይስሐቅን ለመሠዋት መቃጣቱ ለዚህ ምሳሌ ነበር። (ዮሐንስ 3:16) ይሖዋን ‘መራገሙን’ የቀጠለ፣ ለእርሱ ንቀት የሚያሳይና ፍቅራዊ ዓላማዎቹን የሚያንኳስስ ማንኛውም ሰው በእርግማን ሥር ይሆናል፤ ይህም ዘላለማዊ ጥፋት ያስከትልበታል። (ከ1 ሳሙኤል 3:12–14፤ 2:12 ጋር አወዳድር።) የተደረገልንን የምናደንቅ ከሆን ግን ታላቁ አብርሃምን ‘እንባርካለን።’ እንዴት? መልካም ነገሮች ሁሉ፣ በልጁ አማካይነት የምናገኘው ይገባናል የማንለው የሕይወት ስጦታም ጭምር፣ ከይሖዋ የሚመጡ መሆናቸውን በግልጽ አምነን በመቀበል ነው። በተጨማሪም ስለ ይሖዋ ጥሩነትና ስለ ንግሥናው አስደናቂ ባሕርያት ለሌሎች እንናገራለን። (ያዕቆብ 1:17፤ መዝሙር 145:7–13) በዚህ መንገድ ከእርሱ ዘላለማዊ በረከቶችን ለመቀበል ከተሰለፉት መካከል እንሆናለን።

የአብርሃም የተስፋ “ዘር”

6. (ሀ) ዋነኛው የአብርሃም “ዘር” ማን ነው? (ለ) በእርሱ በኩል የሚመጣውን በረከት ልናገኝ የምንችለው እንዴት ነው?

6 ይሖዋ ጽድቅ የሰፈነበት የሰማይ መስተዳድር ለማቋቋም ዓላማ ነበረው። ይህም የሰውን ዘር ለመባረክ ያደረገው ዝግጅት አንዱ ክፍል ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ የአብርሃም “ዘር” ሆኖ ተወለደ። ከዘሮቹ ሁሉ እርሱ ብልጫ ነበረው፤ ይሖዋም የንግሥናውን ሥልጣን የሰጠው ለእርሱ ነው። (ገላትያ 3:16፤ ማቴዎስ 1:1) ስለዚህ አምላክ ለአብርሃም በመሃላ እንዳረጋገጠለት የምድር አሕዛብ ሁሉ የሚባረኩት በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ነው። ያን በረከት ለማግኘት የሚያስፈልገውን ብቃት እያሟላህ ነውን? ለምሳሌ አኗኗርህ የኢየሱስ መሥዋዕት ለአንተ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ እንደምትገነዘብ ያሳያልን? ለንጉሣዊ ሥልጣኑ በእርግጥ እየተገዛህ ነውን? — ዮሐንስ 3:36፤ ሥራ 4:12

7. (ሀ) “የአብርሃም ዘር” እነማንን ይጨምራል? (ለ) አምላክን በታማኝነት ያገለገለ ሁሉ ወደ ሰማይ እንደማይሄድ እንዴት እናውቃለን?

7 ሐዋርያው ዮሐንስ ወደፊት በሰማይ የሚፈጸሙ ነገሮችን የሚያመለክት ትንቢታዊ ራእይ ተቀብሏል። በዚህ ራእይ ውስጥ በሰማያዊው የጽዮን ተራራ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ቆመው የነበሩ ሌሎችን ተመልክቷል። እነርሱም ጭምር “የአብርሃም ዘር” ክፍል ናቸው። በራእይ 14:1–5 ላይ እንደተገለጸው “ከምድር የተዋጁ” ሲሆን ቁጥራቸው 144,000 ነው። (ገላትያ 3:26–29) እነዚህ እነማን ናቸው? አምላክ የጽድቅ ዝንባሌ ያላቸውን በሙሉ ወደ ሰማይ ለመውሰድ ፈጽሞ አስቦ እንደማያውቅ መጽሐፍ ቅዱስ በጣም ግልጽ ያደርግልናል። (ማቴዎስ 11:11፤ ሥራ 2:34፤ መዝሙር 37:29) በሰማያዊቷ መንግሥት ከክርስቶስ ጋር የመቀመጥን ታላቅ መብት የሚያገኙት ለሺህ ዓመት አብረውት ነገሥታትና ካህናት የሚሆኑት ‘የታናሹ መንጋ’ አባላት ብቻ ናቸው። — ሉቃስ 12:32፤ ራእይ 5:9, 10፤ 20:6

8. ‘ታናሹን መንጋ’ የመምረጡ ሂደት የተጀመረው መቼ ነው? ለምን ያህል ጊዜስ ይቀጥላል?

8 የዚህ “ታናሽ መንጋ” አባላት የተመረጡት እንዴት ነው? የሰማያዊቷ መንግሥት ተካፋይ እንዲሆኑ በቸርነት ጥሪ የቀረበላቸው በመጀመሪያ ሥጋዊ እስራኤላውያን ነበሩ። ይሁን እንጂ ባለማመናቸው ምክንያት 144,000 የሚያክሉ አባላት ከእነርሱ ሊገኙ አልቻሉም። ስለዚህ በመጀመሪያ ሳምራውያን፣ ቆይቶም የሁሉም ብሔራት ሕዝቦች ተጋበዙ። (ሥራ 1:8) ከክርስቶስ ጋር ወራሾች የሆኑት የመጀመሪያዎቹ አባላት በ33 እዘአ በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት በመንፈስ ቅዱስ ተቀቡ። አምላክ ብቁ ሆናችኋል ብሎ የሚያትምባቸው 144,000 ሰዎች እስኪሞሉ ድረስ የዚህን ቡድን አባላት የመምረጡ ሂደት ቀጥሎ ነበር። ከዚያ በኋላ የሰማያዊቷ መንግሥት አመስጋኝ ተገዥዎች በመሆን በምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎችን የመሰብሰቡ ሥራ ተጀመረ።

9. (ሀ) ይህን ሰማያዊ ክፍል ለማመልከት የሚሠራባቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ስያሜዎች የትኞቹ ናቸው? (ለ) ሥጋዊ እስራኤላውያን ጥላ የሆኑት ለማን ነበር?

9 ከክርስቶስ ጋር በሰማያዊቷ መንግሥት ወራሽ የሚሆኑት ሰዎች በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ‘የተመረጡ፣’ “ቅዱሳን፣” ‘በአምላክ የተቀቡ’ ተብለው ተጠርተዋል። (2 ጢሞቴዎስ 2:10፤ 1 ቆሮንቶስ 6:1, 2፤ 2 ቆሮንቶስ 1:21) በጥቅል ደግሞ የክርስቶስ “ሙሽራ” ተብለዋል። (ራእይ 21:2, 9፤ ኤፌሶን 5:22–32) ከሌላ አንፃር ሲታዩም የክርስቶስ “ወንድሞች፣” ‘ከክርስቶስ ጋር ወራሽ የሆኑ’ እና የአምላክ “ልጆች” ተብለው ተጠርተዋል። (ዕብራውያን 2:10, 11፤ ሮሜ 8:15–17፤ ኤፌሶን 1:5) ከየትኛውም ብሔር የመጡ ቢሆኑ በመንፈሳዊ አመለካከት “የእግዚአብሔር እስራኤል” ናቸው። (ገላትያ 6:16፤ ሮሜ 2:28, 29፤ 9:6–8) ይሖዋ ከሥጋዊ እስራኤል ጋር የገባውን የሕግ ቃል ኪዳን ካቋረጠ በኋላ ከመንፈሳዊ እስራኤል ጋር አዲስ ቃል ኪዳን አድርጓል። ሆኖም ሥጋዊ እስራኤላውያን በሕጉ ሥር በነበሩበት ጊዜ አምላክ ከእነርሱ ጋር በነበረው ግንኙነት የፈጸማቸው ነገሮች ወደፊት ለሚመጡት ነገሮች ምሳሌ ሆነው አገልግለዋል። (ዕብራውያን 10:1) ታዲያ “ለርስቱ የተለየ ወገን” በመሆን በአምላክ የተመረጠውና የሥጋዊ እስራኤል ሕዝብ ጥላ የሆነለት ብሔር የትኛው ነው? ማስረጃዎቹ አምላክ ከክርስቶስ ጋር በሰማይ እንዲገዙ ወደመረጣቸው ወደ መንፈሳዊ እስራኤል ያመለክታሉ። (ዘጸአት 19:5, 6⁠ን ከ1 ጴጥሮስ 1:3, 4 እና 2:9 ጋር አወዳድር።) ታዛዥ የሆኑ ሌሎች የሰው ልጆች በረከት የሚወርድላቸው በእነርሱና በክርስቶስ በኩል ይሆናል። ይህን ሐቅ መቀበሉ መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት ቁልፍ የሆነ ነገር ነው።

‘በዘሩ’ አማካይነት የሚባረኩት ሰዎች

10. እስራኤላውያን ባልነበሩት የይሖዋ አምላኪዎች የተመሰሉት እነማን ናቸው?

10 አምላክ ከእስራኤል ሕዝብ ጋር ልዩ ግንኙነት በነበረው ወቅት የዚህ ብሔር አባል ያልሆኑትን፣ ነገር ግን ከእስራኤላውያን ጋር በእውነተኛ አምልኮ ለመካፈል ልባቸው ያንቀሳቀሳቸውን ሰዎች ለመርዳት ፍቅራዊ ዝግጅት አድርጎ ነበር። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጎላ ተደርገው ተጠቅሰዋል። እነርሱስ ዘመናዊ አምሳያ ይኖራቸው ይሆን? አዎን፣ አላቸው። ከመንፈሳዊ እስራኤል ያልሆኑትን፣ ነገር ግን የአምላክ መንግሥት ምድራዊ ተገዥዎች በመሆን አስደናቂውን የዘላለም ሕይወት ተስፋ በደስታ የተቀበሉትን ሰዎች በብዙ መንገድ ይመስላሉ። አምላክ ለአብርሃም “የምድር አሕዛብ ሁሉ በዘርህ ራሳቸውን ይባርካሉ” በማለት የተናገረላቸው ሰዎች እነርሱ ናቸው። — ዘፍጥረት 22:18 አዓት፤ ዘዳግም 32:43

11. (ሀ) በሰሎሞን ቤተ መቅደስ ምረቃ ላይ ስለዚህኛው ወገን ምን ተብሎ ነበር? (ለ) በኢሳይያስ 56:6, 7 ላይ እንደ ተተነበየው በዘመናችን “መጻተኞች” ‘ወደ ይሖዋ እየተጠጉ’ ያሉት እንዴት ነው?

11 ሁሉም የሰው ልጆች በእውነተኛው አምልኮ ተጠቃለው አንድ እንዲሆኑ ምን ጊዜም የነበረ የአምላክ ዓላማ ነው። ስለሆነም ሰሎሞን በኢየሩሳሌም ያሠራው ቤተ መቅደስ ሲመረቅ ከእስራኤላውያን ጋር በመተባበር ተቀባይነት ያለው አምልኮ ለማቅረብ የሚፈልጉ ሌሎች ሕዝቦች የሚያቀርቡትን ጸሎት ይሖዋ እንዲያዳምጥ ንጉሡ መለመኑ የተገባ ነበር። (2 ዜና መዋዕል 6:32, 33) ከዚህም ሌላ በኢሳይያስ 56:6, 7 ላይ አምላክ “ያገለግሉት ዘንድ የእግዚአብሔርንም [“የይሖዋንም” አዓት ] ስም ይወድዱ ዘንድ ባሪያዎቹም ይሆኑ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር የሚጠጉትንም መጻተኞች . . . ሁሉ፣ ወደ ተቀደሰ ተራራዬ አመጣቸዋለሁ፣ በጸሎቴም ቤት ደስ አሰኛቸዋለሁ፤ ቤቴ ለአሕዛብ ሁሉ የሚሆን የጸሎት ቤት ይባላልና” በማለት ቃል ገብቷል። ይህ አነጋገር የሚያስተላልፈውን መንፈስ በማንጸባረቅ የዛሬው ዘመን “መጻተኞች” በመሰብሰብ ላይ ናቸው። የሚሰበሰቡትም ለዘብተኛ ተመልካቾች በመምሰል ሳይሆን ‘ወደ ይሖዋ የሚጠጉ’ ሕዝብ በመሆን ነው። ይህንንም የሚያደርጉት ሕይወታቸውን ለይሖዋ በመወሰንና ይህን ውስንነታቸው በውኃ ጥምቀት በማረጋገጥ፤ እንዲሁም ‘ለይሖዋ ስም’ እና ይህ ስም ለሚወክላቸው ነገሮች ሁሉ ያላቸውን ፍቅር በሚያሳይ መንገድ በማገልገል ነው። — ማቴዎስ 28:19, 20

12. የአምላክ መንግሥት ምድራዊ ተገዥዎች ለመሆን ተስፋ የሚያደርጉም ጭምር ለመንፈሳዊ እስራኤል የሚሠሩትን ከፍተኛ የሥነ ምግባር መስፈርቶች ማሟላት እንደሚገባቸው የሙሴ ሕግ የሚያመለክተው እንዴት ነው?

12 ከእነርሱ የሚጠበቀው ታማኝነት በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች ማሟላት ከሚኖርባቸው የታማኝነት ደረጃ ያነሰ አይደለም። እስራኤላውያን በሙሴ ሕግ ሥር ሳሉ፣ እውነተኛውን አምልኮ የተቀበሉ “መጻተኞች” በእስራኤላውያን ላይ የሚሠራውን ሕግ ሁሉ እንዲጠብቁ ይፈለግባቸው ነበር። (ዘኁልቁ 15:15, 16) በመካከላቸው የነበረው ግንኙነት ተቻችሎ የመኖር ጉዳይ ሳይሆን ከእውነተኛ ፍቅር የመነጨ መሆን ነበረበት። (ዘሌዋውያን 19:34) በተመሳሳይም መጻተኞቹ ጥላ የሆኑላቸው ሰዎች አኗኗራቸውን ከይሖዋ ብቃቶች ጋር ለማስማማት ይጥራሉ፤ እንዲሁም ከመንፈሳዊ እስራኤል ቀሪዎች ጋር በፍቅራዊ አንድነት ተሳስረው ማገልገል ይገባቸዋል። — ኢሳይያስ 61:5

13. ከመጪው ጥፋት በሕይወት ተርፈን ወደ “አዲስ ምድር” ለመግባት ከፈለግን የትኞቹን የኢሳይያስ 2:1–4 ዝርዝር ጉዳዮች ልብ ልንላቸው ያስፈልጋል?

13 ይሖዋ ከአሕዛብ ሁሉ ተውጣጥተው ወደ ጽንፈ ዓለማዊው የአምልኮ ቤቱ በጋለ ስሜት እየጐረፉ ያሉትን ‘ከአሕዛብ ሁሉ’ የተውጣጡ ሰዎች ሁኔታ በነቢዩ ኢሳይያስ አማካይነት እንደሚከተለው ገልጾታል:- “ብዙዎች አሕዛብ ሄደው:- ኑ፣ ወደ እግዚአብሔር ተራራ፣ ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንውጣ፤ እርሱም መንገዱን ያስተምረናል፣ በጎዳናውም እንሄዳለን ይላሉ።” ‘ሠይፋቸውን ማረሻ ለማድረግ መቀጥቀጣቸውና’ ውጊያ ባናጋው በዚህ ዓለም ውስጥ ‘ጦርነት መማርን’ ማቆማቸው የዚህ ውጤት ነው። (ኢሳይያስ 2:1–4) ወደዚህ ደስተኛ ሕዝብ ተቀላቅለሃልን? እንደ እነርሱ አንተም የይሖዋን ትእዛዛት ለማወቅ ምኞት አለህን? እነዚህንስ ትእዛዛት በሕይወትህ ውስጥ ትሠራባቸዋለህን? በጦር መሣሪያ መመካትን አቁመሃልን? አምላክ በዚህ ሁኔታ የሚመላለሱ እጅግ ብዙ ሰዎች “ከታላቁ መከራ” በሕይወት ተርፈው እርሱ ወዳቋቋመው ሰላማዊ “አዲስ ምድር” እንደሚገቡ ይሖዋ ቃል ገብቷል። — ራእይ 7:9, 10, 14፤ መዝሙር 46:8, 9

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]