በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዚህ በፊት የጠፋ ዓለም

ከዚህ በፊት የጠፋ ዓለም

ምዕራፍ 6

ከዚህ በፊት የጠፋ ዓለም

1. (ሀ) ከዚህ ቀደም በሰው ልጆች ፊት የዓለም ጥፋት ተደቅኖ ያውቃልን? (ለ) ስለዚህ ጥፋት በተሰጠው ማስጠንቀቂያ ኖኅ ባለማሾፉ አመስጋኝ መሆን የሚገባን ለምንድን ነው?

ከዚህ በፊት በዓለም ላይ ጥፋት የተደቀነበት ዘመን ነበር። ዛሬ በሁሉም ብሔራት ያሉ ሰዎች ከቀድሞ አያቶቻቸው መካከል በዚያን ጊዜ ዓለም አቀፍ የጥፋት ውኃ ይመጣል ሲል አምላክ በሰጠው ማስጠንቀቂያ ያላሾፈ አንድ ሰው በመገኘቱ አመስጋኝ ሊሆኑ ይገባቸዋል። ኖኅ ማስጠንቀቂያውን በመስማቱና በመታዘዙ እርሱና ሚስቱ እንዲሁም ሦስት ወንዶች ልጆቹና ሚስቶቻቸው ከመጥፋት ተርፈዋል። ሁላችንም ከእነርሱ የመጣን ነን። — ዘፍጥረት 10:1, 32

2. አምላክ ያንን ዓለም ለምን አጠፋው?

2 አምላክ ያንን ዓለም ያጠፋው ምድር በዓመፅ መሞላቷን ስላየ ነው። ‘የሰው ክፋት በምድር ላይ በዝቶ ነበር።’ (ዘፍጥረት 6:3, 5, 13) ሁኔታዎቹ የ20ኛውን መቶ ዘመን ሁኔታዎች በእጅጉ የሚመስሉ ነበሩ።

3. ሁኔታው ያን ያህል አሳሳቢ እንዲሆን ያደረገው ምንድን ነው?

3 በኖኅ ዘመን ሁኔታውን በጣም ያባባሰው ነገር ምን ነበር? ዘፍጥረት 6:2 “የእግዚአብሔር ልጆችም የሰውን ሴቶች ልጆች መልካሞች እንደ ሆኑ አዩ፤ ከመረጡአቸውም ሁሉ ሚስቶችን ለራሳቸው ወሰዱ” በማለት አንዱን ዐቢይ ምክንያት ይገልጽልናል። ይሁን እንጂ እንደዚያ ማድረጋቸው ምን ስሕተት ነበረው? እነዚህ ፍጡራን እንዲያው ለማግባት የወሰኑ ሰብዓዊ ፍጡራን የሆኑ ወንዶች አልነበሩም። እነዚህ “የእግዚአብሔር ልጆች” መንፈሳዊ ፍጡራን የሆኑ መላእክት ነበሩ። በምድር ላይ የሴቶችን ቁንጅናና የማግባትን አስደሳችነት ተመልክተው ሰብዓዊ አካል ለበሱ። (ከኢዮብ 1:6 ጋር አወዳድር።) የሰው አካል መልበሳቸውና ማግባታቸው በአምላክ ላይ የእምቢተኝነት ድርጊት ነበር። ‘መኖሪያቸውን መተዋቸውና’ ከሴቶች ጋር መገናኘታቸው ‘ለባሕርያቸው የማይስማማ’ ከተፈጥሮ ውጭ የሆነ ድርጊት እንደሆነ ቅዱሳን ጽሑፎች ያስረዳሉ። (ይሁዳ 6, 7፤ 1 ጴጥሮስ 3:19, 20) የወለዷቸው ዲቃሎች ከመጠን በላይ ግዙፎች ነበሩ። እነዚህ ዲቃሎች ኔፍሊም ወይም ‘አንስተው የሚያፈርጡ’ ተብለው ይጠሩ ነበር፤ ምክንያቱም ትምክሕተኞችና ጉልበተኞች ነበሩ። — ዘፍጥረት 6:4

4. (ሀ) ኖኅ በአምላክ ዘንድ ሞገስ ያገኘው ለምንድን ነው? (ለ) ሕይወትን ለማትረፍ ምን ዝግጅት ተደርጎ ነበር?

4 ኖኅ በዚያ ብልሹ ዓለም ውስጥ ቢኖርም በይሖዋ ፊት ሞገስ አግኝቷል። ለምን? ምክንያቱም ኖኅ ‘ጻድቅ ሰው’ ነበረ። ኖኅ በዔደን የተነሱትን ዐበይት ጥያቄዎች ያውቅ ነበር። ኖኅ ነቀፋ የሌለበት፣ ‘ንጹሕ አቋሙን ሳያጐድፍ ከአምላክ ጋር የሚጣበቅ ሰው’ መሆኑን አስመሰከረ። (ዘፍጥረት 6:8, 9 ዘ ጀሩሳሌም ባይብል) ይሖዋ ኖኅንና ቤተሰቡን፣ እንዲሁም በምድር የሚኖሩ እንስሳትንና በሰማይ የሚበሩ ወፎችን ዘር ከጥፋቱ ለማዳን ሲል እጅግ ግዙፍ የሆነ የሣጥን ቅርጽ ያለው ተንሳፋፊ መርከብ እንዲሠራ ለኖኅ መመሪያ ሰጠው። አምላክ እንዲህ አለ:- “እኔም እነሆ ከሰማይ በታች አንቀሳቃሽ የሕይወት ኃይል ያለውን ሥጋ ሁሉ ለማጥፋት በምድር ላይ የጥፋት ውኃን አመጣለሁ። በምድር ያለው ነገር ሁሉ ይጠፋል።” (ዘፍጥረት 6:13–17 አዓት) ኖኅ የአምላክን ቃል ሰምቶ በመታዘዝ የጥበብ እርምጃ ወስዷል።

5. የጥፋቱ ውኃ እስከ ምን ድረስ የዘለቀ ነበር?

5 በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በዝርዝር የሰፈረውን የዘመን አቆጣጠር በመመርኮዝ በተደረገው ስሌት መሠረት የጥፋት ውኃው የመጣው በ2370 ከዘአበ ነበር። በሰው ታሪክ ውስጥ እስከ ዘመናችን ድረስ ከታዩት መቅሰፍቶች ሁሉ ተወዳዳሪ የማይገኝለት ታላቅ መቅሰፍት ነበር። መሬት ላይ የወረደው ውኃ እጅግ ብዙ ከመሆኑ የተነሳ ‘ከሰማይ በታች ያሉ ታላላቅ ተራሮች ሁሉ ተሸፈኑ።’ (ዘፍጥረት 7:19) በደረሰው መጥለቅለቅ ምክንያት “ያን ጊዜ የነበረ ዓለም በውኃ ሰጥሞ ጠፋ።” (2 ጴጥሮስ 3:6) ይሁን እንጂ አንድ ሰው ‘ትላልቆቹም ተራሮች በውኃ ተሸፍነው ከነበረ ያ ሁሉ ውኃ የት ሄደ?’ ብሎ ይጠይቅ ይሆናል። እዚሁ ምድር ላይ መኖር እንዳለበት ግልጽ ነው።

6. ከጐርፉ በኋላ ያ ሁሉ ውኃ ወዴት ሄደ?

6 መጽሐፍ ቅዱስ በኖኅ ዘመን የኤቨረስትን ተራራ ያህል ረጅም ተራራ ነበር ብሎ እንደማይናገር መገንዘብ ይገባል። ሳይንቲስቶች ባለፉት ጊዜያት አብዛኞቹ ተራሮች አሁን ካሉት በጣም ዝቅ ያሉ እንደነበሩና አንዳዶቹም ከባሕር ወለል ተገፍተው የወጡ መሆናቸውን ተናግረዋል። ከዚህም ሌላ ከውቅያኖስ በታች ያሉ ረጃጅም የወንዝ ፈለጎች እንደሚያረጋግጡት ውቅያኖሶች ራሳቸው ካሁኑ ያነሱ የነበሩበትና አህጉሮች ካሁኑ የበለጠ ስፋት የነበራቸው ጊዜ እንደነበረ ይታመናል። አሁን ስላለው ሁኔታ ግን የናሽናል ጂኦግራፊክ መጽሔት በጥር 1945 እትሙ ላይ እንዲህ ብሏል:- “ከባሕር በላይ ያለውን መሬት ከውቅያኖስ ጋር ብናወዳድረው የውኃው መጠን ከአሥር ጊዜ በላይ የሚበልጥ ሆኖ እናገኘዋለን። አፈሩ ተደልድሎ ለጥ ያለ መሬት እንዲሆን ቢደረግ ውኃው መላዋን ምድር በሁለት ኪሎ ሜትር ተኩል ጥልቀት ሊሸፍናት ይችላል።” በዚህም ምክንያት የጥፋት ውኃው ከጎደለ በኋላ፣ ነገር ግን ተራሮች ወደ ላይ ከፍ ብለው ከመውጣታቸውና የባሕሩ ወለል ዝቅ ብሎ ውኃ ከመሬቱ ላይ ጠፈፍ እንዲል ከመደረጉ በፊት፣ እንዲሁም በምድር ዋልቶች ላይ በረዶ ከመከመሩ በፊት መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ‘ትላልቅ ተራራዎችን ሁሉ’ ለመሸፈን የሚችል በቂ ውኃ ነበረ። — ዘፍጥረት 7:17–20፤ 8:1–3፤ ከመዝሙር 104:8, 9 ጋር አወዳድር።

7, 8. ከመጽሐፍ ቅዱስ ሌላ የጥፋት ውኃ ለመድረሱ ምን ማስረጃ አለ?

7 እንደዚህ ያለው ዓለምን ሁሉ የሚያጥለቀልቅ የጥፋት ውኃ በእውን ያዩትን ሰዎች ምን ጊዜም የማይረሳ ትዝታ ጥሎባቸው መሆን አለበት። የኋለኞቹ ትውልዶች ስለዚህ ጉዳይ እንደሚወራላቸው የታወቀ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ሁሉም ሕዝቦች ከጥፋት ውኃ ከተረፈው ከዚሁ ቤተሰብ የመጡ መሆናቸውን ስለሚናገር በየትኛውም የምድር ክፍል የዚያ ታላቅ መቅሰፍት ዝክር መገኘት አለበት ብሎ መጠበቁ ምክንያታዊ ነው። ታዲያ ይህ ይገኛልን? አዎን፣ በእርግጥ ይገኛል!

8 ከጥፋት ውኃው የተረፉት ሰዎች ዘሮቻቸው ራቅ ወዳሉ አካባቢዎች እየፈለሱ ሲሄዱና ጊዜም እያለፈ ሲመጣ የታሪኩ አንዳንድ ዝርዝር ሁኔታዎች ተዛቡ፤ ትረካው ከአካባቢው ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ ጋር እንዲጣጣም በአዲስ መልክ ተቀነባበረ። ይሁን እንጂ በድሮ ዘመን ታላቅ የውኃ መጥለቅለቅ ደርሶ የሰውን ልጆች በሙሉ እንደደመሰሰና ጥቂቶች ብቻ አንድ ላይ ሆነው ከዚያ መትረፋቸውን የሚዘክሩ ጥንታዊ አፈታሪኮች በዓለም ዙሪያ መገኘታቸው እንዲሁ የአጋጣሚ ጉዳይ ሊሆን አይችልም። የዚህ ዝክር በመስጴጦምያና በሌሎች የእስያ ክፍሎች፣ በአውስትራሊያና በፓስፊክ ደሴቶች፣ በሰሜንና በደቡብ አሜሪካ በሚገኙ በብዙ የሕንድ ጎሣዎች ዘንድ፣ በጥንቶቹ የግሪኮችና የሮማውያን አፈታሪኮች፣ በስካንዲኔቪያ አገሮችና በአፍሪካ ልዩ ልዩ ጎሣዎች ዘንድ ይገኛል። ከነዚህ አፈታሪኮች ውስጥ ብዙዎቹ እንስሶች ከሰዎች ጋር መርከብ ውስጥ ገብተው መትረፋቸውን ይጠቅሳሉ። አንዳንዶቹ አፈታሪኮች ውኃው መጉደሉን ለማወቅ ወፎች ተልከው እንደነበረ ይተርካሉ፤ ይህም ከመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ጋር የሚመሳሰል ነው። (ከዘፍጥረት 7:7–10​ና ከ​8:6–12 ጋር አወዳድር።) እንደዚህ ሆኖ በሰፊው የሚዘከር ሌላ ጥንታዊ ታሪክ አይገኝም።

9. በኖኅ የቀን አቆጣጠር “በሁለተኛው ወር” የተፈጸሙትን ነገሮች የሚያስታውሱ ዛሬ ምን ልማዶች አሉ?

9 ከጥፋት ውኃው ጋር የተያያዙ የታሪኩ ዝርዝር ጉዳዮች እስከ ጊዜያችን ድረስ ልዩ ልዩ ልማዶችን ነክተዋል። እንዴት? መጽሐፍ ቅዱስ የጥፋት ውኃው የጀመረው “በሁለተኛው ወር ከወሩም በአሥራ ሰባተኛው ዕለት” እንደነበረ ይገልጻል። ይህ ‘ሁለተኛ ወር’ በዛሬው የቀን አቆጣጠራችን የጥቅምት አጋማሽ ይሆናል። (ዘፍጥረት 7:11) ስለዚህ በምድር ዙሪያ ብዙ ሰዎች በዚህ የዓመቱ ክፍል ሙታንን ወይም ቅድመ አያቶችን የሚዘክር በዓል ማክበራቸው ልብ ልንለው የሚገባ ነው። በዓሉ ለምን በዚህ ጊዜ ላይ ይደረጋል? ምክንያቱም እነዚህ ልማዶች የውኃውን ጥፋት ዝክር ስለሚያንጸባርቁ ነው። *

10. መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጥፋት ውኃ የሚናገረው ታሪክ በጣም አስተማማኝና በግልም በጣም ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?

10 ይሁን እንጂ ስለደረሰው ሁኔታ ያልተዛባ ማብራሪያ የያዘው መጽሐፍ ቅዱስ ነው። ኖኅ ያየውና ያጋጠመው ነገር ከጊዜ በኋላ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንዲሰፍር ተደርጓል። ከብዙ መቶ ዘመናት በኋላ አምላክ ራሱ በኢሳይያስ በኩል ሲናገር ስለ “ኖኅ ውኃ” ጠቅሷል። (ኢሳይያስ 54:9) የአምላክ የበኩር ልጅ በኖኅ ዘመን የደረሱትን ሁኔታዎች ተመልክቷል። በኋላም ይኸው ልጅ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ የጥፋትን ውኃ እንደ እውነተኛ ታሪክ አድርጎ ጠቅሶታል፤ በተጨማሪም በዚያን ጊዜ ብዙዎቹ የሞቱበትን ምክንያት ገልጿል።

‘አላስተዋሉም ነበር’

11. እነዚያ ሁሉ ሰዎች በጥፋት ውኃ የተደመሰሱት ለምንድን ነው?

11 ኢየሱስ ከኖኅ ቤተሰብ ውጭ ሁሉም ሰው የዓመፅ ወንጀል ይሠራ ነበር አላለም። ከዚህ ይልቅ “በዚያች ወራት ከጥፋት ውኃ በፊት፣ ኖኅ ወደ መርከብ እስከገባበት ቀን ድረስ፣ ሲበሉና ሲጠጡ ሲያገቡና ሲጋቡም እንደ ነበሩ፣ የጥፋት ውኃም መጥቶ ሁሉን እስከ ወሰደ ድረስ እንዳላወቁ፣ [“እንዳላስተዋሉ” አዓት ] የሰው ልጅ [የኢየሱስ ክርስቶስ] መምጣት ደግሞ እንዲሁ ይሆናል” በማለት ተናግሯል።— ማቴዎስ 24:37–39

12. ‘አለማስተዋላቸው’ ያን ያህል ከባድ ጉዳይ የነበረው ለምንድን ነው?

12 በልክ ቢበሉና ቢጠጡ ወይም ክብር ባለው መንገድ ቢያገቡ ስህተት አልነበረውም። ነገር ግን ዓለም አቀፍ ጥፋት እንደሚመጣ ማስጠንቀቂያ ሲሰጣቸው ሕይወታቸው እንደነዚህ ባሉት ሰብዓዊ ፍላጎቶች ላይ ማተኮሩ ኖኅንም ሆነ የማስጠንቀቂያው ምንጭ የሆነውን ይሖዋ አምላክን እንዳላመኑ ያሳያል። ቢያምኑ ኖሮ እንዴት መዳን እንደሚቻል በቁም ነገር ጠይቀው ያንን ብቃት ለማሟላት ፈጣን እርምጃ በወሰዱ ነበር። አንዳንድ ሰዎች በወቅቱ የተስፋፋውን ዓመፅ ለማቆም አንድ ነገር መደረግ እንዳለበት ተስማምተው ይሆናል። ዓለም አቀፍ የውኃ መጥለቅለቅ የመምጣቱ ጉዳይ ግን የማይመስል ነገር እንደሆነባቸው አያጠራጥርም። ስለዚህ ኢየሱስ እንደተናገረው ‘ውኃው መጥቶ ሁሉንም እስከ ወሰደ ድረስ [በኖኅ አማካኝነት የተላለፈውን የአምላክ መልእክት] አላስተዋሉም ነበር።’ ይህ ጉዳይ ተመዝግቦ የቆየው ለእኛ የማስጠንቀቂያ ምሳሌ እንዲሆን ነው።

13. (ሀ) በቅድሚያ እንደተገለጸው ዛሬ ብዙ ሰዎች ክርስቶስ በማይታይ ሁኔታ ተገኝቷል ተብሎ ሲነገራቸው ምን ይላሉ? ለምንስ? (ለ) ጴጥሮስ እነርሱ ምን ነገር እንደዘነጉ ተናግሯል?

13 በመንፈስ አነሳሽነት የጻፈው ሐዋርያው ጴጥሮስም በተመሳሳይ “በመጨረሻው ዘመን [አሁን እኛ ባለንበት ዘመን] እንደ ራሳቸው ምኞት የሚመላለሱ ዘባቾች በመዘበት እንዲመጡ ይህን በፊት እወቁ፤ እነርሱም:- የመምጣቱ የተስፋ ቃል ወዴት ነው? አባቶች ከሞቱባት ጊዜ፣ ከፍጥረት መጀመሪያ ይዞ ሁሉ እንዳለ ይኖራልና ይላሉ” ሲል አስጠንቅቋል። እንደነዚህ ያሉት ሰዎች በማንም ተጠያቂ እንደሆኑ እንዲሰማቸው አይፈልጉም፤ ይህም በመሆኑ ስለ ክርስቶስ መገኘትና ለአምላክ ደንታቢስ ሆኖ መኖር ስለሚያስከትለው ጠንቅ ለማሰብ አይፈልጉም። ይሁን እንጂ ጴጥሮስ በመቀጠል እንዲህ ብሏል:- “ሰማያት ከጥንት ጀምረው ምድርም በእግዚአብሔር ቃል ከውኃ ተጋጥማ በውኃ መካከል እንደ ነበሩ ወደው አያስተውሉምና፤ በዚህም ምክንያት ያን ጊዜ የነበረ ዓለም በውኃ ሰጥሞ ጠፋ፤ አሁን ያሉት ሰማያትና ምድር ግን እግዚአብሔርን የማያመልኩት ሰዎች እስከሚጠፉበት እስከ ፍርድ ቀን ድረስ ተጠብቀው በዚያ ቃል ለእሳት ቀርተዋል።”— 2 ጴጥሮስ 3:3–7

14. በፍጥረት ጊዜና በኖኅ ዘመን ‘የአምላክ ቃል’ መፈጸሙ ዛሬ በጣም ሊያሳስበን የሚገባው ለምንድን ነው?

14 ዘባቾቹ ‘የአምላክ ቃል’ ሳይፈጸም የሚቀር አለመሆኑን ዘንግተዋል። አመለካከታቸውን ውድቅ ለማድረግ ሐዋርያው ጴጥሮስ ወደ ፍጥረት ጊዜ መለስ ብለን እንድናስብ አሳስቦናል። በዚያን ጊዜ አምላክ “በውኆች መካከል ጠፈር ይሁን፣ በውኃና በውኃ መካከልም ይክፈል አለ።” ይህን ቃል ከተናገረ በኋላ “እግዚአብሔርም ጠፈርን አደረገ፣ ከጠፈር በታችና ከጠፈር በላይ ያሉትንም ውኆች ለየ።” በዚህ ሁኔታ “የእግዚአብሔር ቃል” ይኸውም ስለ ዓላማው የተናገረው ቃል ተፈጸመ። (ዘፍጥረት 1:6, 7) ይሖዋ በኖኅ ዘመን ዓለም አቀፍ የውኃ መጥለቅለቅ እንዲመጣ ሲያዝና የወረደውን ውኃ ‘በዚያን ጊዜ የነበረውን ዓለም’ ለማጥፋት ሲጠቀምበት ቃሉ ተፈጽሟል። ዛሬም ለአምላክ ምንም ግድ በሌለው ሥርዓት ላይ ጥፋት የሚመጣው በዚያው በማይታጠፈው የአምላክ ቃል መሠረት ይሆናል።

15. (ሀ) 2 ጴጥሮስ 3:7 ፕላኔቷ ምድር ትቃጠላለች ብሎ አልተነበየም የምንለው ለምንድን ነው? (ለ)ታዲያ ‘ለእሳት ተጠብቀው’ የቀሩት “ሰማያትና ምድር” ምንድን ናቸው?

15 በጥፋት ውኃ ጊዜ የደረሰው ነገር ወደፊት ለሚመጡት ነገሮች ምሳሌ ነው። በዚያን ጊዜ ለአምላክ ግድ የሌላቸው ሰዎች ጠፉ እንጂ ምድሪቱ አልጠፋችም። ታዲያ “አሁን ያሉ ሰማያትና ምድር ግን . . . ተጠብቀው . . . ለእሳት ቀርተዋል” ሲል ምን ማለቱ ነው? (2 ጴጥሮስ 3:7፤ 2:5) ከፍተኛ ቃጠሎ ባላቸው ፀሐይና ከዋክብት ላይ ቃል በቃል እሳት ቢረጭ ምን ለውጥ ሊያመጣ ይችላል? ቃል በቃል ምድርን ማቃጠሉስ አምላክ እርሷን ገነት ለማድረግ ካለው ዓላማ ጋር እንዴት ሊጣጣም ይችላል? እንግዲያው “አሁን ያሉ ሰማያትና ምድር” የሚለው አባባል ምሳሌያዊ መሆን ይኖርበታል። (ከዘፍጥረት 11:1፤ ከ1 ነገሥት 2:1, 2​ና ከ1 ዜና መዋዕል 16:31 ጋር አወዳድር።) “ሰማያት” ከሰው በላይ ከፍ ብለው የሚታዩትን መንግሥታዊ ኃይሎች ሲወክሉ “ምድር” ደግሞ ለአምላክ ምንም ግድ የሌለውን ሰብዓዊ ኅብረተሰብ ይወክላል። በታላቁ የይሖዋ ቀን በእሳት እንደተቃጠሉ ያህል ፈጽሞ ይወድማሉ። በዚህ መለኮታዊ ማስጠንቀቂያ ላይ ማሾፋቸውን የሚቀጥሉ ሁሉ ሕይወታቸውን ከፍተኛ አደጋ ላይ ይጥላሉ።

ለአምላክ ያደሩ ሰዎች ከመከራ ይድናሉ

16. በ2 ጴጥሮስ 2:9 ላይ እንደተጠቀሰው ለመዳን ቁልፉ ምንድን ነው?

16 የጥፋት ውኃው ታሪክ፣ ዛሬ ልብ ማለት የሚያስፈልገንን አንድ ነጥብ ሕያው አድርጎ ያስረዳል። ነጥቡ ምንድን ነው? ሐዋርያው ጴጥሮስ አምላክ በኖኅ ዘመን ያደረገውን ከጠቀሰ በኋላ “ይሖዋ ለአምላክ ምንም ግድ የሌላቸውን ለፍርድ ቀን እንዴት እንደሚጠብቅ፣ ለአምላክ ያደሩትን ሰዎች ደግሞ ከመከራ እንዴት እንደሚያድን ያውቃል” በማለት ይደመድማል። (2 ጴጥሮስ 2:9 አዓት) እንግዲያው ከመከራ ለመዳን ቁልፉ ለአምላክ ያደሩ መሆን ነው።

17. ኖኅ ለአምላክ ያደረ መሆኑን ያስመሰከረው እንዴት ነው?

17 ይህስ ምን ማለት ነው? በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ኖኅ ለአምላክ ያደረ ሰው ነበር። “ኖኅ አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ።” (ዘፍጥረት 6:9) ይሖዋ ለፍጡሮቹ ከገለጸው ፈቃዱ ጋር የሚስማማ የሕይወት ጎዳና ይከተል ነበር። ከአምላክ ጋር የቀረበ የግል ዝምድና መሥርቷል። መርከቡን መሥራቱና የወፎችንና የእንስሳትን ልዩ ልዩ ዘሮች መሰብሰቡ ትልቅ ሥራ ነበር። ‘እስቲ ልቆይና ልይ’ የሚል አቋም አልነበረውም። እምነት ነበረው። “ኖኅም እንዲሁ አደረገ፤ እግዚአብሔር እንዳዘዘው ሁሉ እንዲሁ አደረገ።” (ዘፍጥረት 6:22፤ ዕብራውያን 11:7) ሰዎች ስለ አምላክ የጽድቅ መንገዶች የሚያሳስባቸውና ለአምላክ ምንም ግድ በሌላቸው ሰዎች ላይ ስለሚመጣው ጥፋት የሚያስጠነቅቃቸው ሰው ያስፈልጋቸው ነበር። ኖኅ ‘የጽድቅ ሰባኪ’ ስለነበረ ይህንንም አድርጓል። — 2 ጴጥሮስ 2:5

18. ከጥፋት ውኃው በሕይወት የተረፈው እያንዳንዱ ሰው ልክ እንደ ኖኅ ለአምላክ ያደረ ኖሮ መሆን አለበት የምንለው ለምንድን ነው?

18 የኖኅ ሚስት፣ ወንዶች ልጆቹና ሚስቶቻቸውስ እንዴት ነበሩ? ምን እንዲያደርጉ ይፈለግባቸው ነበር? ኖኅ የቤተሰብ ራስ በመሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ የሚያተኩረው በእርሱ ላይ ነው፤ ይሁን እንጂ የተቀሩትም ቢሆኑ ለአምላክ ያደሩ ሰዎች ኖረው መሆን አለበት። ለምን? የኖኅን ልጆች ጉዳይ በሌላ ጊዜ ይሖዋ ለነቢዩ ሕዝቅኤል አውስቶለታል። ኖኅ በዚያን ጊዜ በእስራኤል ቢኖር ኖሮ ልጆቹ በአባታቸው ጽድቅ ምክንያት እንድናለን ብለው እንደማይጠብቁ ይሖዋ ገልጾለታል። ለመታዘዝም ሆነ ላለመታዘዝ ዕድሜያቸው ይፈቅድ ስለነበረ ለይሖዋና ለጽድቅ መንገዶቹ ያደሩ መሆናቸውን በግል አኗኗሯቸው ማረጋገጥ ነበረባቸው። — ሕዝቅኤል 14:19, 20

19. ስለዚህ አሁን ምን እያደረግን መሆን ይኖርብናል? እንዴትስ?

19 የዓለም ጥፋት በላያችን እያንዣበበ ስለሆነ ይህንን ቀን አቅርበን እንድንመለከተውና እኛም ለአምላክ ያደርን መሆናችንን እንድናስመሰክር መጽሐፍ ቅዱስ አጥብቆ ይመክረናል። (2 ጴጥሮስ 3:11–13) ዛሬ በተለያዩ የምድር ክፍሎች ያንን ጥበብ አዘል ምክር የሚሰሙና በሕይወት ተርፈው ወደ “አዲስ ምድር” የሚገቡ የኖኅ ዝርያዎች አሉ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.9 ዘ ወርሺፕ ኦቭ ዘ ዴድ (የሙታን አምልኮ) (ለንደን፤ 1904) በኮሎኔል ጄ ጋርኒየር የተጻፈ፣ ገጽ 3–8፤ ላይፍ ኤንድ ወርክ አት ዘ ግሬት ፒራሚድ (በታላቁ ፒራሚድ አካባቢ የነበረው ሕይወትና ሥራ) (ኤዲንበርግ፤ 1867) ጥራዝ 2፣ በፕሮፌሰር ሲ ፒያሲ ስሚዝ የተጻፈ፣ ገጽ 371–424

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]