ወደኋላ የተውከውን አትናፍቅ!
ምዕራፍ 22
ወደኋላ የተውከውን አትናፍቅ!
1. (ሀ) የታመኑት የአምላክ አገልጋዮች ከፊታቸው ምን በረከቶች ይጠብቋቸዋል? (ለ) ይሁን እንጂ አንዳንድ ሰዎች ምን አድርገዋል?
ዛሬ እየተፈጸሙ ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች አምላክ ወዳዘጋጀው ወደ ታላቁ አዲስ የነገሮች ሥርዓት ለመግባት ደጃፉ ላይ እንደቆምን በማያሳስት መንገድ ያሳያሉ። ክፉው ዓለም በቅርቡ ድምጥማጡ ይጠፋል። ዓለም ያመጣው ጭንቀት፣ ብስጭትና ኀዘንም አብሮ ይጠፋል። ምድር ወደ ገነትነት ተለውጣ እውነተኛውን አምላክ የሚያመልኩ ሁሉ ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወት በማግኘት ለዘላለም ደስ ብሏቸው የሚኖሩባት ስፍራ ትሆናለች። ይሖዋ ለሐዋርያው ዮሐንስ “እነዚህ ቃሎች የታመኑና እውነተኛዎች ናቸውና ጻፍ” በማለት የተስፋዎቹን እርግጠኝነት ገልጾለታል። (ራእይ 21:1–5) ይሁንና፣ ነገሩ ግራ የሚያጋባ ቢመስልም፣ ይህንን እውነት ያወቁ አንዳንድ ሰዎች ወደኋላ ዞረው አምላክ አጠፋዋለሁ ብሎ ወደተናገረለት ዓለም የአኗኗር መንገድ ይመለሳሉ። እንዴት ያሳዝናል! ለምን እንደዚህ ያደርጋሉ?
2. (ሀ) አንድ ሰው መጨረሻው ይህ እንዳይሆን እውነትን ካወቀበት ጊዜ ጀምሮ ምን ማድረግ ይኖርበታል? (ለ) ይህን ሳያደርግ ከቀረ አስተሳሰቡን የሚቆጣጠረው ምን ሊሆን ይችላል? ውጤቱስ?
2 ስለ አምላክ መንግሥትና እርሷ ስለምታደርጋቸው ነገሮች የሚገልጸውን ምሥራች በመጀመሪያ ሲሰሙ በደስታ ተቀብለውት ነበር። ይሁን እንጂ ክርስቲያናዊ ጉልምስና ላይ ለመድረስ ወደፊት መግፋት፣ የአምላክን ቃል በጥልቀት መረዳትና ቃሉ የሚናገረውን ተግባራዊ ለማድረግ መጣጣርም አስፈላጊ ነው። (ዕብራውያን 6:1, 11, 12) ማንም ሰው አድናቆት ጎድሎት ይህን ሳያደርግ ከቀረ አምላክን የማገልገሉን መብት እንደ ውድ ነገር አድርጎ መመልከቱን ያቆማል። እንዲህ ያለው ሰው በመንፈሳዊ ማደግ እንደሚያስፈልገውና አምላክ አሁን እንድናከናውነው በሰጠን የስብከትና ደቀ መዛሙርት የማድረግ ሥራ ሙሉ በሙሉ መካፈል እንዳለበት አይታየውም። ከዚህ ይልቅ አምላክ ቃል የገባልን ሥጋዊ በረከቶች ለምን አልመጡም በማለት ትዕግሥት ያጣል። አብዛኛውን ጊዜ የሚያስበው የቁሳዊ ሀብትና የደስታ ፍላጎቱ እንዴት እንደሚሟላለት ነው። መንፈሳዊ ጥቅሞችን በሁለተኛ ደረጃ ያስቀምጣቸዋል። በአንድ ጊዜ ሳይሆን ቀስ በቀስ እየተንሸራተተ ወደ ዓለም ይገባል። — 1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10
3. (ሀ) ይሖዋን የማያመልኩትን ሰዎች ለጓደኝነት መምረጡ አደገኛ የሚሆነው ለምንድን ነው? (ለ) አንድ ሰው እንደነዚህ ካሉት ሰዎች ጋር በተዝናና ሁኔታ በቀላሉ ሊገናኝ የሚችለው መቼ ነው?
3 አንድ ሰው በሕይወት ተርፎ ወደ “አዲስ ምድር” ለመግባት እንደሚፈልግ፣ ጽድቅ በሚሰፍንበት ዓለም ውስጥ ለመኖር እንደሚመኝ ይናገር ይሆናል። ይሁን እንጂ የጓደኛ ምርጫው አባባሉን ይደግፋልን? እርግጥ ነው፤ አምላክን ከማያገለግሉ ሰዎች ጋር በየቀኑ በትምህርት ቤት፣ በሥራ ቦታ፣ በገበያ፣ ወይም እቤት መገናኘትን ማስቀረት አይቻልም። ነገር ግን በመሥሪያ ቤት በምሳ ሰዓት፣ ትምህርት ቤት ከመሄዱ በፊትና ከዚያ በኋላ ባለው ጊዜ፣ ለወዳጆቹ ስልክ ሲደውል ወይም እነርሱን ለመጠየቅ ወደ ቤታቸው ሲሄድ እንዲሁም በመዝናኛ ጊዜ ከእነማን ጋር መሆንን ይመርጣል? ምርጫው በእርግጥ ልዩነት ያመጣልን? መጽሐፍ ቅዱስ “አትሳቱ፣ ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን ዓመል ያጠፋል” በማለት ያስጠነቅቃል። (1 ቆሮንቶስ 15:33፤ ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) “ክፉ ባልንጀርነት” ግን ምንድን ነው? አንዳንድ ሰዎች ይሖዋን አለማምለካቸውና እንዲሁ ትክክል መስሎ የታያቸውን ነገር ማድረጋቸው ልዩነት ያመጣልን? አስቀድመን በተመለከትነው መሠረት እንደነዚህ የመሳሰሉት ሰዎች ከጥፋት ተርፈው ወደ ‘አዲሲቱ ምድር’ እንደማይገቡ እናውቃለን። ጓደኛ በሚመርጡበት ጊዜ የይሖዋን የሥነ ምግባር መሥፈርት አቅልለው የሚመለከቱ ሁሉ፣ ብዙም ሳይቆይ፣ ትቼዋለሁ ብለው በተናገሩለት ዓለም ውስጥ ገብተው ይገኛሉ። ይሁን እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተመዘገቡትን የማስጠንቀቂያ ምሳሌዎች ልብ ካልናቸው እንደዚህ ካለ አካሄድ ልንጠበቅ እንችላለን። — 1 ቆሮንቶስ 10:11
‘እኛን ለማስጠንቀቅ ተጻፉ’
4. (ሀ) ዮሴፍ ከሞተ በኋላ እስራኤላውያን በግብፅ ምን ዓይነት ኑሮ ይገፉ ጀመር? (ለ) እስራኤላውያን ከግብፅ ነፃ ሲወጡ “ብዙ ድብልቅ ሕዝብ” አብሯቸው የወጣው ለምን ነበር? (ሐ) ይህ ትንቢታዊ ድራማ በጊዜያችን የተፈጸመው እንዴት ነው?
4 ይሖዋ እስራኤልን ከግብፅ ባርነት ነፃ ባወጣቸው ጊዜ ይህ እንዴት ያለ እፎይታ ሰጥቷቸው መሆን አለበት! ከዮሴፍ ሞት በኋላ ባጋጠማቸው የሚያንገፈግፍ ጭቆና ምክንያት ግብፅ መውጫ የሌላት እቶነ እሳት ሆነችባቸው። (ዘጸአት 1:13, 14፤ ዘዳግም 4:20) በኋላ ግን ይሖዋ በግብፅ ላይ አሥር መቅሰፍቶች አመጣ። በእውነተኛው አምላክና በግብፅ አማልክት መካከል ያለው ሰፊ ልዩነት ግልጽ ሆነ። ስለዚህ እስራኤላውያን አገሩን ለቀው ሲወጡ፣ ልክ በዛሬው ጊዜ “እጅግ ብዙ ሰዎች” ከዓለም ተለይተው ከመንፈሳዊ እስራኤል ቀሪዎች ጋር እንደተቀላቀሉት፣ ያን ጊዜም እስራኤላውያን ያልሆኑ “ብዙ ድብልቅ ሕዝብ” ከእነርሱ ጋር ወጡ። (ዘጸአት 12:38) ነገር ግን ከወጡ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በሰፈሩ ምን ተከሰተ?
5. (ሀ) ነፃ በወጡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ‘ወደ ግብፅ የተመለሱት’ እንዴት ነበር? (ለ) ይህስ ለምን ሆነ?
5 ክርስቲያኑ ደቀ መዝሙር እስጢፋኖስ “በልባቸውም ወደ ግብፅ ተመለሱ” በማለት የተፈጸመውን ነገር ገልጿል። ይህ የሆነው ከግብፅ ነፃ ወጥተው ጥቂት ወራት ብቻ ካለፉ በኋላ ነበር። (ሥራ 7:39, 40) በልባቸው ወደ ግብፅ እንደተመለሱ የሚያሳይ ምን ነገር ተፈጸመ? የወርቅ ጥጃ ሠሩና (በግብፅ ሳሉ ሁልጊዜ የሚያዩት ነገር ነው) ‘ለእግዚአብሔር በዓል እናደርጋለን’ ብለው አወጁ። ሆኖም የግብፃውያንን ልማድ መቅዳታቸው ነበር። (ዘጸአት 32:1–6) ይሖዋ በአድራጎታቸው በጣም አዘነ። ያደረጉት ነገር በሲና ተራራ ለሙሴ ከተሰጠው ሕግ ጋር በቀጥታ ይጋጫል። በሺህ የሚቆጠሩ ሕይወታቸውን አጡ። ይህ ለምን ደረሰ? የይሖዋን ትእዛዛት ቢያውቁም ለትእዛዛቱም ሆነ እነርሱን እየመራ ያለው እውነተኛው አምላክ ለመሆኑ ጉዳይ ልባዊ ግንዛቤና አድናቆት አልኮተኮቱም ነበር።
6. (ሀ) ይሖዋ በምድረ በዳ ምን ምን ነገር ሰጥቷቸው ነበር? (1 ቆሮንቶስ 10:3, 4) (ለ) አንዳንዶቹ የግብፅ ኑሯቸውን መናፈቅ የጀመሩት ለምንድን ነው?
6 እስራኤላውያንም ሆኑ አብሯቸው የተጓዘው ድብልቅ ሕዝብ ከግብፅ ሲወጡ፣ ያደረጉት ነገር ትክክል መሆኑን አውቀው ነበር። በኋላ ግን አንድ ዓመት ሲያልፍ ወደ ተስፋይቱ ምድር ገና አልገቡም። ‘ወተትና ማር በምታፈሰው ምድር’ ውስጥ መኖሪያ ቤት ገና አላገኙም። በሥጋዊ በኩል በቂ ምግብ ነበራቸው፤ በተለይ ደግሞ በመንፈሳዊ ነገሮች ተንበሽብሸዋል። እየመራቸው ያለው ይሖዋ ለመሆኑ የደመናውና የእሳቱ ዓምድ ቋሚ ምልክት ነበር። በቀይ ባሕርና በሲና ተራራ የይሖዋን አስፈሪ ክንድ የሚያሳይ ነገር አይተው ነበር። የሕጉ ቃል ኪዳን መንፈሳዊ ምግብና የመንፈስ እረፍት ሰጥቷቸዋል። በተጨማሪም ጠባያቸው፣ አስተሳሰባቸውና የልባቸው ዓላማ ይሖዋን ያስደስት ዘንድ የት ላይ ማስተካከል እንደሚያስፈልጋቸው ለማወቅ በግላቸው የሚያደርጉትን ብዙ ነገር አቅርቦላቸው ነበር። ይሁን እንጂ ይሖዋ ያደርግላቸው የነበረውን ሁሉ በማድነቅ ፋንታ በግብፅ የተዉአቸውን ነገሮች መናፈቅ ጀመሩ። የራስ ወዳድነት ምኞት ብዙዎቹን ለጥፋት ዳረጋቸው። —7. (ሀ) ሰላዮቹ ሪፖርታቸውን ይዘው ከመጡ በኋላ ሕዝቡ ወደ ግብፅ እንመለስ ብሎ የተናገረው ለምንድን ነው? (ለ) ውጤቱስ ምን ነበር? (ዕብራውያን 3:17, 19)
7 ይህ በሆነ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሙሴ የተስፋይቱን ምድር የሚሰልሉ ሰዎች ላከ። እነርሱም ሲመለሱ ምድሪቱ በእርግጥም ‘ወተትና ማር የምታፈስስ’ ለመሆንዋ በአንድ ድምፅ ተሰማምተው ነበር። አሥሩ ሰላዮች ግን ከአገሩ ሰዎችና ከተመሸጉት ከተሞቻቸው የተነሳ ፈርተውና ደንግጠው ነበር። በሙሉ ልባቸው በይሖዋ አልታመኑም። የሌሎቹንም ልብ በፍርሃት አቀለጡት። አሁንም እንደገና በሐሳባቸው ወደ ግብፅ ተመለሱ። የሚመለሱበትንም ዕቅድ አወጡ። እምነት ባለማሳየታቸው 20 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆናቸው በዚያ ትውልድ የነበሩት ሰዎች በጠቅላላ ቀስ በቀስ በምድረ በዳ ሞተው አለቁ። ወደ ተስፋይቱ ምድር ፈጽሞ አልገቡም። — ዘኁልቁ 13:27–33፤ 14:1–4, 29
8. (ሀ) ሰዶም ስትጠፋ ሎጥና ቤተሰቡ ሕይወታቸውን ለማትረፍ ምን ማድረግ ነበረባቸው? (ለ) የሎጥ ሚስት የጨው ዓምድ ሆና የተለወጠችው ለምንድን ነው? (ሐ) ይህስ ለእኛ ምን የማስጠንቀቂያ መልእክት ይዟል?
ዘፍጥረት 19:12–26፤ ሉቃስ 17:31, 32) እስራኤላውያንና የሎጥ ሚስት የተያዙበት ወጥመድ እኛንም እንዳይዘን ምን ሊጠብቀን ይችላል?
8 ከ400 ዓመት በላይ ቀደም ብሎ ይኸው ትምህርት በሌላ ትዕይንት ላይ ጎላ ብሎ ታይቷል። የአብርሃም የወንድም ልጅ ሎጥ፣ በሥነ ምግባር ብልሹ፣ በሥጋዊ ግን ሀብታም በሆነችው የሰዶም ከተማ ይኖር ነበር። ሰዶምና በዙሪያዋ ያለው አውራጃ በብልግና ማጥ ውስጥ ገብተው ስለነበር ይሖዋ ከተማዋን ዳግም እንዳታንሰራራ አድርጎ ለማጥፋት ወሰነ። ሎጥንና ቤተሰቡን ለማዳን መላእክት ተላኩ። ሎጥ ልጆቹን ያጩትን ሰዎች ሲያስጠነቅቃቸው “የሚያፌዝባቸው መሰላቸው።” ነገሩ ግን ፌዝ አልነበረም። ጎህ ሲቀድ መላእክቱ ሎጥንና ቤተሱን አስቸኩለው ከከተማይቱ አወጧቸውና ወደኋላ ዘወር ብለው ሳይመለከቱ እንዲሸሹ ነገሯቸው። ሕይወታቸው በመታዘዝ ላይ የተመካ ነበር። ሎጥና ሁለቱ ሴቶች ልጆቹ የታዘዙትን አደረጉ። በዚህም ምክንያት ሕይወታቸው ሊተርፍ ቻለ። የሎጥ ሚስት ግን ወደኋላ ከተወቻቸው ሥጋዊ ነገሮች በሐሳብ ለመላቀቅ ልቧ አልጨክን አለ። ወደኋላ ዞር አለች፤ ሕይወቷንም አጣችና የጨው ዓምድ ሆና ተተክላ ቀረች። ቁም ነገሩ ወደ ልባችን ገብቷልን? ኢየሱስ ነጥቡን እንዳንስተው ሲል በዘመናችን ካለው አሮጌ ሥርዓት ባስቸኳይ ስለመሸሽ በሰጠው ማስጠንቀቂያ ውስጥ በድጋሚ ጠቅሶታል። ኢየሱስ ስለ ሥጋዊ ንብረት ከመጠን በላይ መጨነቅ እንደማይገባ ባስጠነቀቀ ጊዜ ባጭሩ “የሎጥን ሚስት አስቡአት” አለ። (‘የተሻለ ስፍራ መጠበቅ’
9. እምነት ምንድን ነው? እንዴትስ ልናዳብረው እንችላለን?
9 ወደኋላ እንድናይ የሚገፋፋ ተጽዕኖ እንዳያሸንፈን ወደፊት ስለሚሆኑት ነገሮች ያለንን እምነት እየኮተኮትን ማሳደግ ይኖርብናል። ዕብራውያን 11:1 (አዓት ) እምነትን “ተስፋ የተሰጠባቸውን ነገሮች በእርግጠኝነት መጠበቅ፣ በእርግጥ ያሉ ነገሮች በዓይን ባይታዩም መኖራቸውን በተጨባጭ ነገሮች የሚያስረዳ” በማለት ይገልጸዋል። እምነት የርስት ባለቤትነትን እንደሚያረጋግጥ ደብተር ነው፤ አምላክ ቃል የገባልንን ነገር ለመውረሳችን ማረጋገጫ ወይም ዋስትና ይሆነናል። እምነት በተጨባጭ ነገሮች ላይ የተመሠረተ ነው። በዚህም ምክንያት በሰብዓዊ ዓይን ሊታዩ ያልቻሉትን ነገሮች ለማመን ጠንካራ ምክንያቶች አሉን። እምነት ተላላነት ወይም አንድ ነገር ጥሩ መስሎ ስለታየ ብቻ በቀላሉ መቀበል ማለት አይደለም። እውነተኛ እምነት እንዲኖረን ከፈለግን ለእምነቱ መሠረት የሆነውን ማስረጃ ራሳችን ለማየት በጥንቃቄ መመርመር ያስፈልገናል። በተጨማሪም የምንማረው ነገር ከሕይወታችን ጋር እንዴት እንደሚዛመድ በጥንቃቄ ማሰብና ለእርሱም ልባዊ፣ እውነተኛ የሆነ አድናቆት መኮትኮት ይገባናል።
10. (ሀ) አብርሃም እምነቱን በተጨባጭ ያሳየው እንዴት ነበር? ለምንስ ያህል ጊዜ? (ለ) እርሱ ያደረገው ነገር ትክክል እንደነበር እንዴት እናውቃለን?
10 አብርሃም እንዲህ ያለ እምነት ነበረው። በዚህም ምክንያት በይሖዋ ትእዛዝ ዑር የተባለችውን የበለጸገች የከለዳውያን ከተማ ትቶ ከዚያ በፊት በፍጹም አይቶት ወደማያውቀው ሩቅ አገር ወደ ከነዓን ሄደ። እዚያም ጥላ ከለላ እንዲሆንለት ከየትኛውም የከተማ መንግሥት ጋር ሳይጣበቅ ለብቻው መጻተኛ ሆኖ ኖረ። “መሠረት ያላትን፣ እግዚአብሔር የሠራትንና የፈጠራትን ከተማ [የይሖዋን መሲሐዊት መንግሥት] ይጠብቅ ነበርና።” በከለዳውያን አገር የነበረውን ኑሮ ቢናፍቅ ኖሮ መንገዱ ያለጥርጥር ጨርቅ ይሆንለት ነበር። ከዚህ ይልቅ ‘የተሻለ ስፍራ፣ ይኸውም ሰማያዊ አገር ጠበቀ።’ (ዕብራውያን 11:8–16) አብርሃም ‘የተሻለውን ስፍራ የጠበቀው’ ለጥቂት ዓመታት ወይም ለአሥርና ለሃያ ዓመት አልነበረም። እስከሞተበት ጊዜ ድረስ ማለትም ዑርን ለቆ ከወጣ ለ100 ዓመታት ወይም ከዚያ ለሚበልጥ ጊዜ ሲጠብቅ ነበር። እምነት እንዳለው በአፉ ብቻ አልተናገረም፤ በተግባርም አሳይቶታል። በዚህም ምክንያት ሽልማቱን ማግኘቱ የተረጋገጠ ነው። ከሞት የመነሳቱ ጉዳይ እርግጠኛ ነገር በመሆኑ ኢየሱስ ‘በአምላክ ፊት አብርሃም ሕያው ነው’ ብሏል። — ሉቃስ 20:37, 38፤ ያዕቆብ 2:18
11. ይስሐቅና ያዕቆብም እምነት እንደነበራቸው ያሳዩት እንዴት ነው?
11 ይሁን እንጂ የአብርሃም ልጅ ይስሐቅና የይስሐቅ ልጅ ያዕቆብስ እንዴት ነበሩ? የከለዳውያንን ኑሮ አይተው አያውቁም። ሆኖም በዚህ አሳበው ‘እስቲ ምን እንደሚመስል እንየው’ ለማለት አልከጀሉም። ወላጆቻቸው ይሖዋ ስለገባላቸው ቃል ሲነግሯቸው ይህን በልባቸው አኖሩት። አብርሃም የነበረው ዓይነት እምነት አዳበሩ። እነርሱም ጭምር ‘የተሻለውን ስፍራ ይጠብቁ ነበር።’ አምላክ አላፈረባቸውም። — ዕብራውያን 11:9, 16, 20, 21፤ ዘፍጥረት 26:24, 25፤ 28:20–22
12. ዔሳውንና ዲናን ወደ ከባድ ችግሮች ያስገባቸው ምንድን ነው?
12 በሌላው በኩል ግን የያዕቆብ ወንድም ዔሳው ለመንፈሳዊ ነገሮች አድናቆት አልነበረውም። ይሖዋን የማያመልኩ ሴቶች አገባ። ቅዱሳን ነገሮችን በእንክባካቤ በመጠበቅ ፋንታ ብኩርናውን ለአንድ መብል ሸጠ። (ዘፍጥረት 25:29–34፤ 26:34, 35፤ ዕብራውያን 12:14–17) አሁንኑ በልቼ ልሙት የሚል ሰው ነበር። የያዕቆብ ልጅ ዲናም ወደ ከባድ ችግር ገብታለች። ለምን? አረማውያን ከሆኑት “የዚያ አገር ሴቶች ልጆች” ጋር መዋል ያስደስታት ስለነበር ነው። — ዘፍጥረት 34:1, 2
13. (ሀ) ዛሬ ያለው ዓለም ክፍል የሆኑ ሰዎች ሕይወታቸው ምን ይመስላል? (ለ) እንደገና ወደ ዓለም ተስበን እንዳንሄድ የሚጠብቀን ምንድን ነው?
13 እንግዲህ አንተም እንደ አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብ ‘የተሻለ ስፍራ’ ማለትም በመሲሐዊቷ የይሖዋ መንግሥት ውስጥ የሚገኘውን ሕይወት እየጠበቅህ ከሆነ ዓለም ጎትቶ እጁ ውስጥ እንዳያስገባህ ጠንቀቅ በል። ዓለም ዘላቂ የሆነ ምንም ነገር ሊያቀርብልህ እንደማይችል አስታውስ። “የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል።” ይህም እንዴት ያለ አርኪ ሕይወት ይሆናል! — 1 ዮሐንስ 2:17
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 172 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የሎጥን ሚስት አስቧት!