በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሰውን ልጅ የወደፊት ሁኔታ የሚጠቁሙ አስተማማኝ ጭላንጭሎች

የሰውን ልጅ የወደፊት ሁኔታ የሚጠቁሙ አስተማማኝ ጭላንጭሎች

ምዕራፍ 5

የሰውን ልጅ የወደፊት ሁኔታ የሚጠቁሙ አስተማማኝ ጭላንጭሎች

1. የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ሁልጊዜ በትክክል የሚፈጸመው ለምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ወደፊት ይሆናሉ ብሎ የተናገራቸውን ነገሮች በልበ ሙሉነት ለመቀበል ጥሩ ምክንያቶች አሉን። የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች የነገሮችን አዝማሚያ አጥንተው ወደፊት እንዲህ ይሆናል ብለው በተነበዩ ሰዎች ግምት ላይ የተመሠረቱ አይደሉም። “በመጽሐፍ ያለውን ትንቢት ሁሉ ማንም ለገዛ ራሱ ሊተረጉም አልተፈቀደም፤ ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፣ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ።” (2 ጴጥሮስ 1:20, 21) በዚህ ምክንያት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት በማንኛውም ዝርዝር ጉዳይ በትክክል የሚፈጸም ሆኖ ታይቷል።

2. ስለ ዓለም ጉዳዮች ከተነገሩት ትንቢቶች ውስጥ ምሳሌ ጥቀስ።

2 መጽሐፍ ቅዱስ ባቢሎንን፣ ሜዶፋርስንና ግሪክን የመሳሰሉ የዓለም ኃያል መንግሥታትን በስም በመጥቀስ ስለ አነሳሳቸውና ስለ አወዳደቃቸው አስቀድሞ ተናግሯል። ከሁለት መቶ ዘመናት በፊት ባቢሎን እንዴት እንደምትወድቅና የድል አድራጊዋንም ሰው ስም አስታውቋል። ይህ ትንቢት አንድ በአንድ ተፈጽሟል። የባቢሎን ከተማ በመጨረሻው ማንም ሰው የማይኖርባት ኦና ሆና እንደምትቀር ትንቢቱ አመልክቶ ነበር። ይህ ሁኔታ እስከ ዘመናችን ድረስ ቀጥሏል። (ዳንኤል 8:3–8, 20–22፤ ኢሳይያስ 44:27 እስከ 45:2፤ 13:1, 17–20) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በስም ስላልተጠቀሱ ሌሎች መንግሥታት በቅድሚያ የተሰጠ መግለጫ ያለ ሲሆን እውቀት ያላቸው ሰዎች እነዚህ መንግሥታት እነማን እንደሆኑ ከአገላለጹ በቀላሉ ሊረዱ ይችላሉ።

3. በትንበያ መልክ ያልቀረቡ ትንቢቶች አሉን?

3 ሆኖም የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት አቀራረብ አንድ ዓይነት ብቻ እንዳልሆነ መታወቅ ይኖርበታል። ይህንንም ቀደም ሲል የሰው ዘር በአምላክ መንግሥት ሥር ለሚያገኛቸው ነገሮች ጠቋሚ ድንቆች ሆነው ስለሚያገለግሉት የኢየሱስ ተአምራት በተሰጠው ማብራሪያ ላይ ተመልክተናል። ትንበያ የማይመስሉ የቅዱሳን መጻሕፍት ሌሎች ክፍሎችም ትንቢታዊ ቁምነገሮችን ይዘዋል።

ስሜትን የሚመስጡ ትንቢታዊ ምሳሌዎች

4. የሙሴ ሕግ ትንቢታዊ ትርጉም እንዳለው ማሳሰቢያ ያገኘነው እንዴት ነው?

4 ለምሳሌ ያህል የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የዕብራውያን መጽሐፍ ላይ ላዩን ለሚመለከት አንባቢ እንዲሁ ታሪክ ብቻ የሚመስሉ ነገር ግን ትንቢታዊ ቁም ነገር ያዘሉ ነገሮችን እንድናይ ዓይናችንን ይከፍትልናል። ‘ሕጉ [የሙሴ ሕግ] ሊመጡ ላሉት በጎ ነገሮች ጥላ እንዳለው’ የዕብራውያን መጽሐፍ ያሳየናል። — ዕብራውያን 10:1

5. ግዑዛን ነገሮች የበለጠ ነገር ሊያመለክቱ እንደሚችሉ ምን ማስረጃ አለ?

5 አንዳንድ ጊዜ ግዑዛን ነገሮች ትንቢታዊ ምሳሌ ሆነው አገልግለዋል። ለምሳሌ በይሖዋ መሪነት ሙሴ ስለሠራው ቅዱስ ድንኳን ወይም ስለ መገናኛው ድንኳንና በእርሱ ውስጥ ይከናወን ስለነበረው አገልግሎት በመንፈስ አነሳሽነት የዕብራውያንን መልእክት የጻፈው ጸሐፊ ይህ ድንኳን “ለሰማያዊ ነገር ምሳሌና ጥላ” መሆኑን ገልጿል። ድንኳኑ ቅድስተ ቅዱሳኑ በሰማይ የሚገኘውን የይሖዋን ታላቅ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ያመለክት ነበር። ስለሆነም “ክርስቶስ ይመጣ ዘንድ ላለው መልካም ነገር ሊቀ ካህናት ሆኖ፣ በምትበልጠውና በምትሻለው በእጆችም ባልተሠራች ማለት ለዚህ ፍጥረት ባልሆነች ድንኳን፣ የዘላለም ቤዛነትን አግኝቶ አንድ ጊዜ ፈጽሞ ወደ ቅድስት በገዛ ደሙ ገባ እንጂ በፍየሎችና በጥጆች ደም አይደለም። . . . ክርስቶስ በእጅ ወደ ተሠራች፣ የእውነተኛይቱ ምሳሌ ወደምትሆን ቅድስት አልገባምና፣ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ አሁን ይታይ ዘንድ ወደ እርሷ ወደ ሰማይ ገባ።” (ዕብራውያን 8:1–5፤ 9:1–14, 24–28) እዚህ ላይ የተገለጹት መንፈሳዊ እውነታዎች ለክርስቲያኖች ትልልቅ ጥቅሞች ያመጡላቸዋል። ለእነዚህ ጥቅሞች ያለንን አድናቆት በአኗኗራችን ማንጸባረቅ አለብን። — ዕብራውያን 9:14፤ 10:19–29፤ 13:11–16

6. (ሀ) በገላትያ 4:21–31 (ለ) በማቴዎስ 17:10–13 ላይ ለሰዎች ምን ትንቢታዊ ትርጉም ተሰጥቷል?

6 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ሰዎችም ጭምር ትንቢታዊ አምሳያ ሆነው አገልግለዋል። በገላትያ 4:21–31 ላይ የአብርሃምን ሚስት ሣራን፣ (‘ላይኛይቱ ኢየሩሳሌምን’ እንደምታመለክት የተነገረላት) እና ባሪያዋን አጋርን (‘አሁን ያለችውን ምድራዊት ኢየሩሳሌም’ የምታመለክት ሆና የተገለጸችው) እንዲሁም ልጆቻቸውን በሚመለከት የቀረበው ዝርዝር ማብራሪያ ለዚህ ማስረጃ ይሆናል። በሌላም ጉዳይ ላይ ኢየሱስ ነቢዩ ኤልያስ የመጥምቁ ዮሐንስ አምሳያ መሆኑን ደቀ መዛሙርቱ እንዲያስተውሉ አድርጓል። ዮሐንስ ልክ እንደ ኤልያስ በግብዝነት የሚፈጸሙ ሃይማኖታዊ ድርጊቶችን ያለፍርሃት አጋልጧል። — ማቴዎስ 17:10–13

7. ኢየሱስ ክርስቶስ (ሀ) በሰሎሞን (ለ) በመልከ ጼዴቅ የተመሰለው በምን በምን መንገድ ነው?

7 በጥበቡ፣ በብልጽግናውና በግዛቱ ሰላማዊነት በጣም የታወቀው ሰሎሞንም ለኢየሱስ ክርስቶስ ትክክለኛ አምሳያ ነበር። (1 ነገሥት 3:28፤ 4:25፤ ሉቃስ 11:31፤ ቆላስይስ 2:3) አብርሃም ከመልከ ጼዴቅ ጋር ተገናኝቶ ስለመነጋገሩ በዘፍጥረት መጽሐፍ ላይ የቀረበው ዘገባ አጭር ቢሆንም ብዙ ቁም ነገር እንደያዘ መዝሙር 110:1–4 ይጠቁመናል። ይህ የሆነበት ምክንያት መሲሑ “እንደ መልከ ጼዴቅ ሥርዓት . . . ለዘላለም ካህን” ስለሚሆን ነው። ይህም ማለት የሊቀ ካህንነቱን ሹመት የሚያገኘው በቀጥታ ከአምላክ በመቀበል እንጂ በትውልድ ከቤተሰብ በመጣ ውርሻ ምክንያት አይደለም ማለት ነው። ከዚያም ቆየት ብሎ ለዕብራውያን የተላከው ደብዳቤ ይህን ጉዳይ ይበልጥ አስፋፍቶታል። መልእክቱ እንደነዚህ ላሉት እውነቶች የምናሳየውን አድናቆት አምላክን ለማስደሰት የሚፈልጉ ሁሉ ሊደርሱበት ከሚገባቸው ከክርስቲያናዊ ጉልምስና ጋር አዛምዶታል። — ዕብራውያን 5:10–14፤ 7:1–17

8. (ሀ) በሕይወት ዘመን የሚያጋጥሙ ነገሮች ትንቢታዊ ሊሆኑ እንደሚችሉ የትኛው ምሳሌ ያሳያል? (ለ) እነዚህን የመሰሉ ገጠመኞች በጥቃቅን ነገሮችም ጭምር አምሳያ ይኖራቸዋልን?

8 ትንቢታዊ አምሳያነት ያለው የሰዎቹ የሥልጣን ደረጃ ወይም ቦታ ብቻ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ሰዎቹ በሕይወት ዘመናቸው ያጋጠማቸውም ነገር እንደዚሁ አምሳያነት ሊኖረው ይችላል። በአንድ ወቅት የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ለማመን እምቢ ባሉ ጊዜ ኢየሱስ “ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል፣ ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም። ዮናስ በዓሣ አንባሪ ሆድ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ነበረ፣ እንዲሁ የሰው ልጅ በምድር ልብ ውስጥ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል” ብሏቸዋል። (ማቴዎስ 12:38–40፤ ዮናስ 1:17፤ 2:10) ይሁን እንጂ ኢየሱስ በዮናስ ሕይወት ውስጥ የደረሰው እያንዳንዱ ነገር እርሱ ለሚደርስበት ነገር ጥላ ይሆናል ብሎ አልተናገረም። ዮናስ ይሖዋ ሥራ ሲሰጠው ወደ ተርሴስ ለመሸሽ ሞክሯል፤ ኢየሱስ ግን እንደዚያ አላደረገም። ነገር ግን ኢየሱስ እንዳመለከተው ዮናስ በትልቅ ዓሣ ሆድ ውስጥ እንደቆየ የሚገልጸው ዘገባ ስለ ኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ ትንቢታዊ ዝርዝር ሁኔታዎችን ስለሚገልጽ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲሰፍር ተደርጓል። — ማቴዎስ 16:4, 21

9. (ሀ) ኢየሱስ በሁለት የታሪክ ጊዜያት ከተፈጸሙት ውስጥ የትኞቹ ሁኔታዎች ትንቢታዊ ትርጉም እንዳላቸው ጠቀሰ? (ለ) ጴጥሮስ በመንፈስ አነሳሽነት ምን ተጨማሪ ዝርዝር ሁኔታዎችን ጠቅሷል?

9 አንዳንድ የታሪክ ጊዜያትም ትኩረታችንን የሚስብ ትንቢታዊ ጭላንጭል ይሰጡናል። ኢየሱስ ንጉሣዊ ሥልጣን ይዞ ለሚገለጥበት ጊዜ መዳረሻ ስለሚሆነው ዘመን ሲናገር በክፉ ሰዎች ላይ መለኮታዊ ፍርድ የተፈጸመባቸው ሁለት ወቅቶች ለዚህ አምሳያ እንደሆኑ አመልክቷል። ስለ “ኖኅ ዘመን” እና ስለ “ሎጥ ዘመን” በመናገር በተለይ በዚያን ጊዜ የነበሩት ሰዎች በዕለታዊ የኑሮ ጉዳዮች ተጠምደው እንደነበር ጎላ አድርጓል። አጣዳፊ እርምጃ እንድንወስድ፣ እንደ ሎጥ ሚስት ወደኋላ መለስ ብለን የተውናቸውን ነገሮች እንዳንናፍቅ አጥብቆ አሳስቦናል። (ሉቃስ 17:26–32) ሐዋርያው ጴጥሮስም በመንፈስ አነሳሽነት በጻፈው ሁለተኛ መልእክቱ ላይ ትርጉም ያላቸው ተጨማሪ ዝርዘር ሁኔታዎች ጠቅሷል። ከጥፋት ውኃ በፊት የመላእክት አለመታዘዝ፣ የኖኅ የስብከት እንቅስቃሴ፣ በሰዶም ሰዎች የተጨማለቀ የሴሰኝነት ኑሮ ምክንያት ሎጥ ያደረበት ጭንቀት፣ አምላክ በወሰነው ጊዜ ክፉዎችን ማጥፋቱ ወደፊት ለሚደረጉት ነገሮች ምሳሌ እንደሆነ፣ እንዲሁም ይሖዋ የታመኑ አገልጋዮቹን ከመከራ ሊያድናቸው እንደሚችልና በእርግጥም እንደሚያድናቸው የሚያሳይ ማስረጃ ከእነዚህ አንዳንዶቹ ናቸው። — 2 ጴጥሮስ 2:4–9

10. ኤርምያስን ከራእይ ጋር በማስተያየት አስቀድሞ የተፈጸሙ ትንቢቶች ተጨማሪ ትርጉም ሊኖራቸው እንደሚችል አሳይ።

10 ትንቢቶች ከተፈጸሙ በኋላ ታሪካዊ ጠቀሜታ ብቻ የሚሰጡ ሆነው ይቀራሉ ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ስለሚደርሰው ነገር በቅድሚያ የተሰጠው ማስጠንቀቂያም ሆነ የትንቢቱ አፈጻጸም ብዙውን ጊዜ የበለጠ ለውጥ የሚያመጡ ወደፊት የሚሆኑ ነገሮች ትንቢታዊ አምሳያ አላቸው። ሃይማኖት የጐላ ባሕሪዋ የነበረውና ተጽዕኖዋም እስከ ዘመናችን ድረስ በምድር ዙሪያ እየተንጸባረቀ ያለችው የጥንቷ ባቢሎንን የሚመለከተው የታሪክ መዝገብ ለዚህ ዓይነተኛ ማስረጃ ነው። ባቢሎን በ539 ከዘአበ በሜዶንና በፋርስ ሠራዊት የተገረሰሰች ብትሆንም በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ መጨረሻ አካባቢ በተጻፈው የራእይ መጽሐፍ ላይ የነቢዩን የኤርምያስን አነጋገር በቀጥታ በመጠቀም እነዚያ ትንቢቶች የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ከሆነችው ከታላቂቱ ባቢሎን ጋር በተያያዘ ሁኔታ ገና ወደፊትም እንደሚፈጸሙ ተገልጿል። ለዚህ ምሳሌ ይሆን ዘንድ ራእይ 18:4⁠ን ከኤርምያስ 51:6, 45 ጋር፤ ራእይ 17:1, 15 እና 16:12⁠ን ከኤርምያስ 51:13​ና 50:38 ጋር፤ ራእይ 18:21⁠ን ከኤርምያስ 51:63, 64 ጋር አወዳድር።

11. ይሖዋ ከከሐዲዋ እስራኤልና እምነት አጉዳይ በነበረችበት ጊዜ ከይሁዳ ጋር የነበረው ግንኙነት ምን ትንቢታዊ ትርጉም አለው? ለምንስ?

11 በተመሳሳይም ይሖዋ ከከሐዲው የአሥሩ ነገድ የእስራኤል መንግሥትና ከሁለቱ የይሁዳ ነገድ መንግሥት እምነት አጉዳይ ነገሥታትና ካህናት ጋር የነበረው ግንኙነትም ትንቢታዊ ነው። በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙት በእነዚያ የጥንት መንግሥታት ላይ የደረሱት ትንቢቶችና አፈጻጸማቸው የመጽሐፍ ቅዱስን አምላክ አመልካለሁ እያለች የጽድቅ ትእዛዞቹን ያለምንም እፍረት የምታፈርሰውን ዘመናዊቷን ሕዝበ ክርስትና ምን እንደሚያደርጋት ጉልህ በሆነ ሥዕላዊ መግለጫ ያመለክታሉ።

12. እኛ በግላችን ከእነዚህ ታሪኮች የምንጠቀመው እንዴት ነው?

12 እንግዲያው እነዚህ ሁሉ ታሪኮች ለዛሬው ጊዜ ትርጉም አላቸው። አምላክ በጊዜያችን ያሉትን ሁኔታዎች እንዴት እንደሚመለከታቸውና እኛም በበኩላችን ከመጪው ታላቅ መከራ በሕይወት ለመትረፍ ምን ማድረግ እንደሚገባን እንድናስተውል ይረዱናል። በዚህ መንገድ “[ቅዱሳን መጻሕፍት] ሁሉ . . . ለትምህርት ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር” እንደሚጠቅሙ የበለጠ ለማስተዋል ችለናል። — 2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17

ይህ ሁሉ በዕቅድ የተቀነባበረ ነውን?

13. አምላክ ትንቢታዊ አምሳያዎችን ለማስገኘት ሲል ሰዎች ኃጢአት እንዲፈጽሙ እንዳልገፋፋ እንዴት እናውቃለን?

13 ከዚህ ሁሉ የምንረዳው፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙት ሰዎችና መንግሥታት የፈጸሟቸው ነገሮች ትንቢታዊ ትርጉም እንዲኖራቸው ተብሎ በቅድሚያ በአምላክ የተቀነባበሩ መሆናቸውን ነውን? አምላክ ወደፊት ለማምጣት ያሰባቸውን የተሻሉ ነገሮች ለማመልከት ሲል ባለፉት ጊዜያት ከአገልጋዮቹ ጋር ለየት ያለ ግንኙነት አድርጎ እንደነበር ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ ሰዎቹ ስላደረጉትስ ምን ለማለት ይቻላል? አንዳንዶቹ ከባድ ኃጢአቶችን ፈጽመዋል። አምላክ የመጽሐፍ ቅዱስን ታሪክ ለማሟላት ብሎ ይህንን እንዲፈጽሙ ገፋፍቷቸው ነበርን? ክርስቲያኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ ያዕቆብ “እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንምና፣ እርሱ ራሱስ ማንንም አይፈትንም” በማለት ይመልሳል። (ያዕቆብ 1:13) ትንቢታዊ አምሳያዎች እንዲሆኑ ብሎ አምላክ ስህተት እንዲሠሩ አላደረጋቸውም።

14. (ሀ) ሰዎች ወይም ሰይጣን ወደፊት ምን እንደሚያደርጉ ይሖዋ ለማወቅ የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ ስለ ራሱና ስለ ዓላማው ያለው እውቀት በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ውስጥ የሚገቡት በምን መንገዶች ነው?

14 ይሖዋ የሰው ልጆች ፈጣሪ መሆኑን አትርሳ። አፈጣጠራችንንና ሰዎች ከሚያደርጓቸው ነገሮች በስተጀርባ ያሉትን ሁኔታዎች ያውቃል። (ዘፍጥረት 6:5፤ ዘዳግም 31:21) ከጽድቅ ሥርዓቶቹ ጋር ተስማምተው የሚኖሩ ሁሉ በመጨረሻው ምን እንደሚያገኙና የአምላክን አስፈላጊነት የማይቀበሉ ወይም መንገዶቹን የሚያጣምሙ ሁሉ በመጨረሻው ምን እንደሚደርስባቸው አስቀድሞ በትክክል ሊያስታውቅ ይችላል። (ገላትያ 6:7, 8) ዲያብሎስ ባለፉት ጊዜያት የተጠቀመባቸውን ዘዴዎች ወደፊትም እንደሚጠቀምባቸው ያውቃል። ከዚህም ሌላ ይሖዋ ራሱ በአንዳንድ የተወሰኑ ሁኔታዎች ምን እንደሚያደርግ፣ ሁልጊዜ ከሚያሳያቸው የፍትሕ፣ አድልዎ ያለማድረግ፣ የፍቅርና የምሕረት ጠባዮቹ ጋር የሚስማማ ነገር እንደሚያደርግ ያውቃል። (ሚልክያስ 3:6) የይሖዋ ዓላማዎች መፈጸማቸው የተረጋገጠ ነገር ስለሆነ የእነዚህን ውጤትና እነርሱን ለማከናወን የሚወስዳቸውን እርምጃዎች አስቀድሞ ለማስታወቅ ይችላል። (ኢሳይያስ 14:24, 27) በዚህም ምክንያት የወደፊቱ ጊዜ ምን እንደሚያመጣ ለመጠቆም ከግለሰቦችና ከብሔራት ታሪክ ውስጥ መርጦ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲጨመር አድርጓል።

15. የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ታሪክ ብቻ እንዳልሆኑ ሐዋርያው ጳውሎስ ያጎላው እንዴት ነው?

15 ሐዋርያው ጳውሎስ የእስራኤልን ሕዝብ ታሪክ ከገለጸ በኋላ ለክርስቲያን ጓደኞቹ “ይህም ሁሉ እንደ ምሳሌ ሆነባቸው፣ እኛንም የዘመናት መጨረሻ የደረሰብንን ሊገሥጸን ተጻፈ” በማለት በትክክል ነግሯቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 10:11) ሮም ለነበረው የክርስቲያን ጉባኤም ሲጽፍ “በመጽናትና መጻሕፍት በሚሰጡት መጽናናት ተስፋ ይሆንልን ዘንድ አስቀድሞ የተጻፈው ሁሉ ለትምህርታችን ተጽፎአልና” ብሏል። (ሮሜ 15:4) እንግዲያው የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች እንዲሁ ትረካ ብቻ አለመሆናቸውን ከተገነዘብን ታሪኮቹ የያዟቸውን የሰውን ልጅ የወደፊት ሁኔታ የሚጠቁሙ ጭላንጭሎች መረዳት ልንጀምር እንችላለን።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 41 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ትንቢታዊ አምሳያዎች—ምን ያመለክታሉ?

የኖኅ ዘመን

የመገናኛው ድንኳን

ንጉሥ ሰሎሞን

ዮናስ በዓሣ ሆድ ውስጥ ሦስት ቀን መቆየቱ

የባቢሎን መውደቅ