በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የተለየ የመታዘዝ አመለካከት

የተለየ የመታዘዝ አመለካከት

ምዕራፍ 17

የተለየ የመታዘዝ አመለካከት

1. ይሖዋ ባቢሎናውያን ኢየሩሳሌምን እንዲያጠፉ ለምን ፈቀደ?

ኢየሩሳሌም በባቢሎናውያን ከመጥፋቷ በፊት ይሖዋ አይሁዶችን እየመጣባቸው ስላለው ጥፋትና ይህም ለምን እንደሚመጣ ለብዙ ዓመታት ሲያስጠንቅቃቸው ነበር። እስራኤላውያን ግን አምላክን በመታዘዝ ፈንታ የእልኸኛ ልባቸውን ዝንባሌ ይከተሉ ነበር። — ኤርምያስ 25:8, 9፤ 7:24–28

2. (ሀ) አምላክን በመታዘዝ ላይ የተመረኮዙት ጥቅሞች ምንድን ናቸው? (ለ) እስራኤል ከይሖዋ ጋር የቃል ኪዳን ዝምድና ለመመሥረት የቻለው እንዴት ነው?

2 ይሖዋ ማንንም ሰው እንዲያገለግለው አያስገድድም፤ ሆኖም በእርሱ ዘንድ ተቀባይነትን ለማትረፍና የዚህ ተጓዳኝ የሆኑትን የሕይወት በረከቶች ለማግኘት የሚፈልጉ ሁሉ ታዛዥ እንዲሆኑ ይፈልግባቸዋል። ይህም ምክንያታዊ ነው። ይሖዋ እስራኤልን ከግብፅ ጭቆና ነፃ ካወጣቸው በኋላ “ቃሌን በጥብቅ ብትታዘዙ ቃል ኪዳኔንም በእውነት ብትጠብቁ፣ እናንተ ከሌሎች ሕዝቦች ሁሉ የተመረጣችሁ ልዩ ንብረቴ ትሆናላችሁ መላዋ ምድር የእኔ ናትና። እናንተም ራሳችሁ የካህናት መንግሥትና ቅዱስ ሕዝብ ትሆኑልኛላችሁ” ብሏቸው ነበር። (ዘጸአት 19:5, 6 አዓት) አምላክ ምን እንዲያደርጉ እንደሚፈልግ ከዘረዘረላቸውና “የቃል ኪዳኑ መጽሐፍ” ሲነበብ ካዳመጡ በኋላ ከአምላክ ጋር የሚገቡት ይህ ዝምድና የሚያስከትለውን ኃላፊነት በገዛ ፈቃዳቸው፣ በውዴታ ተቀበሉ።— ዘጸአት 24:7

3. (ሀ) ከዚያ በኋላ እስራኤል ለይሖዋ የዓመፀኝነት መንፈስ ያሳየው በምን መንገዶች ነው? (ለ) እነዚህ ታሪኮች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተመዘገቡት ለምንድን ነበር?

3 ይሁን እንጂ የዓመፀኝነት መንፈስ ብቅ ለማለት ብዙም ጊዜ አልፈጀበትም። የእስራኤል ልጆች በይሖዋ ላይ ያላቸውን እምነት ፊት ለፊት አልካዱም፤ ይሁንና ብዙዎቹ የእርሱን ሕግ በመጣስ የግብፃውያንን ልማዶች ከይሖዋ አምልኮ ጋር ለመቀላቀል ሞክረዋል። (ዘጸአት 32:1–8) ከዚያ ቆየት ብሎም ይሖዋ የሚታዩ ወኪሎቹ አድርጎ የሚጠቀምባቸውን ሰዎች የሚነቅፉ ተነሱ። (ዘኁልቁ 12:1–10፤ 16:1–3, 31–35) በብሔር ደረጃ እስራኤላውያን ሰውን በመፍራት የአምላክን ቃል በሥራ ላይ ሳያውሉ ቀሩና እምነት የለሽ መሆናቸውን አሳዩ። (ዘኁልቁ 13:2, 31–33፤ 14:1–4፤ ዕብራውያን 3:17–19) ሳያስቡት ስህተት የሠሩ ሁሉ ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ንስሐ ከገቡ ይቅርታ ሊያገኙ ይችሉ ነበር። ይሁን እንጂ ለዘጠኝ መቶ ዘመናት ሕዝቡ በመጀመሪያ አንዱን መለኮታዊ ትእዛዝ፣ ከዚያም ሌላውን፣ ከዚያም ብዙዎቹን ትእዛዛት ሆን ብለው ጥሰዋል። እነርሱ ያደረጓቸው ነገሮችና ያስከተሉባቸው ጠንቆች ለእኛ የማስጠንቀቂያ ምሳሌ እንዲሆኑ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበዋል። — 2 ዜና መዋዕል 36:15–17፤ 1 ቆሮንቶስ 10:6–11

4. (ሀ) ሬካባውያን እነማን ነበሩ? (ለ) ኢዮናዳብ ምን ግዴታ ውስጥ አስገብቷቸው ነበር?

4 በኤርምያስ ዘመን የአይሁዳውያን አካሄድ ስለሚያስከትለው አደገኛ ውጤት በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ከተሰጠ በኋላ ይሖዋ ሬካባውያንን እንደ ምሳሌ አድርጎ ጠቀሰላቸው። ሬካባውያን እስራኤላውያን አልነበሩም፤ ነገር ግን ይሖዋን የሚቀናቀን ምንም ነገር አልፈቅድም ሲል ከተናገረው ከኢዩ ጋር የአቋም አንድነት ያሳየው የኢዮናዳብ ዝርያ ናቸው። ይህ ኢዮናዳብ የሬካባውያን ነገድ ሃይማኖታዊ መሪ በመሆን ለዘላለም ከወይን ጠጅ እንዲርቁ፣ እንዲሁም ቤት ሠርተው እንዳይቀመጡና እርሻን እንዳያርሱ፣ ነገር ግን እንደ ዘላን በድንኳን እንዲኖሩ አዟቸው ነበር። በዚህ መንገድ በእስራኤላውያን መካከል እየኖሩ አብረዋቸው ይሖዋን ሲያመልኩ የከተማ ኑሮ ከሚያመጣው መጥፎ ተጽዕኖና ከተድላ ኑሮ ነፃ ሆነው በጭምትነትና በቀላል መንገድ እንዲኖሩ ፈልጎ ነበር።

5. ሬካባውያን በታዛዥነት በኩል ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑት እንዴት ነው?

5 አይሁዶች እንኳ የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዥ የሆነውን ይሖዋን ለማዳመጥ እምቢ ካሉ ሬካባውያን ሰብዓዊ አባታቸውን ይታዘዛሉ ብሎ መጠበቅ ይቻላልን? ሬካባውያን ግን ታዘዋል፤ ያውም ምሳሌነት ባለው መንገድ። የባቢሎናውያንና የሶርያውያን የጦር ኃይል ይሁዳን በወረረ ጊዜ ሬካባውያን በኢየሩሳሌም ከተማ ውስጥ ለመሸሸግ ቢገደዱም የድንኳኑን ኑሮ ቀጥለውበታል። ወይን ጠጅ እንዲጠጡ በተፈቀደላቸው ሕዝብ መሐል እየኖሩ ወይን ጠጅ ላለመጠጣት ምን ያህል ጽኑ አቋም ነበራቸው? ይሖዋ ኤርምያስ ሬካባውያኑን ወደ መቅደሱ የምግብ አዳራሽ እንዲጠራቸውና በፊታቸው የወይን ጠጅ የሚጠጣባቸው ጽዋዎች ደርድሮ እንዲጋብዛቸው አድርጎ ነበር። እነርሱ ግን አንጠጣም አሉ። ለምን? ቅድመ አያታቸው ለይሖዋ የነበረውን የጠበቀ ፍቅር በአድናቆት ይመለከቱ እንደነበረ ግልጽ ነው። ስለ ደኅንነታቸው ፍቅራዊ አሳቢነት እንደነበረውም ተገንዝበው ነበር። ስለዚህም ትእዛዙን ተከተሉ። አይሁዶች ይሖዋን እንደማይታዘዙ ቁልጭ አድርጎ ባሳየው በዚህ ጥሩ የታዛዥነት አርአያ ይሖዋ ተደስቶ ነበር። — ኤርምያስ 35:1–11

6. (ሀ) ዛሬ በሬካባውያን የሚመሰሉት እነማን ናቸው? (ለ) የእምቢተኛዋ እስራኤል አምሳያ ማን ሆና ተገኝታለች?

6 ዛሬም ሬካባውያንን የሚመስሉ ሰዎች አሉ። እነርሱም የጌታ “ሌሎች በጎች” ናቸው። ዛሬ ጥያቄው ወይን ጠጅ ይጠጣሉ ወይስ አይጠጡም የሚል አይደለም። (ከ1 ጢሞቴዎስ 5:23 ጋር አወዳድር።) ልማደኛ ጠጪዎች ወይም ሰካራሞች እስካልሆኑ ድረስ ይህ በግል የሚወሰን ጉዳይ ነው። (ምሳሌ 23:20፤ 1 ቆሮንቶስ 6:9, 10) ይሁን እንጂ አምላክን መታዘዝ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው። የከሐዲዋ እስራኤል አምሳያ ከሆነችው ከሕዝበ ክርስትና አንፃር ሲታዩ የዘመናችን ሬካባውያን አምላክን ለመታዘዙ ጉዳይ ትልቅ ዋጋ እንደሰጡት ተግባራቸው ይመሰክራል። ይህስ የሚጠቅማቸው እንዴት ነው?

7. (ሀ) ይሖዋ ለሬካባውያን ምን የሚያበረታታ ተስፋ ሰጥቷቸው ነበር? (ለ) ይህስ ለዘመናዊው የሬካባውያን ክፍል ምን ተስፋ ይዞላቸዋል?

7 ሬካባውያን ላሳዩት የአቋም ጽናት “የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል:- ለአባታችሁ ለኢዮናዳብ ትእዛዝ ታዛችኋልና፣ ትእዛዙንም ሁሉ ጠብቃችኋልና፣ ያዘዛችሁንም ሁሉ ፈጽማችኋልና ስለዚህ በፊቴ የሚቆም ሰው ከሬካብ ልጅ ከኢዮናዳብ ወገን ለዘላለም አይታጣም” በማለት ይሖዋ ለዘመናችን የሚሠራ ትልቅ ትንቢታዊ ትርጉም ያለው የተስፋ ቃል ሰጣቸው። (ኤርምያስ 35:18, 19) በ607 ከዘአበ ኢየሩሳሌም ስትጠፋ በሕይወት ከተረፉት መካከል እነርሱም ነበሩበት። ሬካባውያን ጥላ የሆኑለት ቡድንም በሕዝበ ክርስትናና የይሖዋን ሉዓላዊነት ለመቀበል አሻፈረኝ ብሎ በራሱ መንገድ በሚሄደው በቀረው የዓለም ክፍል ሁሉ ላይ ከሚመጣው እልቂት ይተርፋል።

መታዘዝ ቀላል የማይሆንበት ምክንያት

8. ብዙ ሰዎች መታዘዝ ከባድ የሚሆንባቸው ለምንድን ነው?

8 ብዙ ሰዎች መታዘዝን መማሩ ይከብዳቸዋል። ያደጉት ሁሉም ሰው ‘ባሻው መንገድ’ እንዲሄድ በሚፈቅድ ዓለም ውስጥ ነው። በአምላክ መንግሥት ሥር ስለሚኖረው ሕይወት ሲሰሙ ደስ ይላቸው ይሆናል፤ ነገር ግን ኩራት አስተሳሰባቸውን ካጨለመው አምላክ እንዲያሟሉ በሚጠይቃቸው አንዳንድ ብቃቶች ላይ ያንጐራጉሩ ይሆናል ወይም እነዚህ ትእዛዞች የተሰጡበትን መንገድ ይነቅፉ ይሆናል። (ምሳሌ 8:13፤ 16:18) በነቢዩ ኤልሳዕ ዘመን የሶሪያ ሠራዊት አለቃ የነበረው ንዕማን ይህ ችግር ነበረበት።

9. (ሀ) ንዕማን እንዴት ወደ ኤልሳዕ ሊሄድ ቻለ? (ለ) ምን ጠብቆ ነበር? ይሁን እንጂ ምን አጋጠመው?

9 ንዕማን በለምጽ በሽታ ተይዞ ነበር። ይሁን እንጂ ምርኮኛ የሆነች አንዲት ወጣት እስራኤላዊት እርሱ ወደ ይሖዋ ነቢይ ወደ ኤልሳዕ ቢሄድ እንደሚፈወስ ያላትን እምነት በድፍረት በመግለጿ ንዕማን ወደ እስራኤል ሄደ። በፈረሶችና በጦር ሠረገሎች ታጅቦ ወደ ኤልሳዕ ቤት ደረሰ። ንዕማን ባለ ከፍተኛ ማዕርግ ስለነበረ ኤልሳዕ ወደ እርሱ መጥቶ እንደሚቀበለውና በታመመው አካሉ ላይ እጁን ወዲያና ወዲህ እያወዛወዘ እስኪድን ድረስ ወደ ይሖዋ በመጮኽ የሆነ ሥነ ሥርዓት ይፈጽማል ብሎ ጠብቆ ነበር። በዚህ ፈንታ ግን ኤልሳዕ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ እንዲሄድና ሰባት ጊዜ እንዲነከር ብቻ እንዲነግረው አገልጋዩን ላከበት። — 2 ነገሥት 5:1–12

10. (ሀ) ንዕማን እንዲህ ዓይነት ነገር ሲያጋጥመው ምን ተሰማው? (ለ) በመጨረሻ እንዲታዘዝ የገፋፋው ምን ነበር? (ሐ) ውጤቱስ ምን ሆነ?

10 ንዕማን ኩራቱ መጣበት። ተናዶ ወደ ቤቱ መመለስ ጀመረ። በኋላ ግን አገልጋዮቹ አግባቡትና በእምነት ራሱን ዝቅ አደረገ። “ወረደም፣ የእግዚአብሔርም ሰው እንደ ተናገረው በዮርዳኖስ ሰባት ጊዜ ብቅ ጥልቅ አለ፤ ሥጋውም እንደ ገና እንደ ትንሽ ብላቴና ሥጋ ሆኖ ተመለሰ፣ ንጹሕም ሆነ።” ንዕማን ይሖዋ ብቻውን እውነተኛ አምላክ እንደሆነ አመነ፤ በመጀመሪያ ተቆጥቶ የነበረ ቢሆንም ኤልሳዕ የሰጠው መመሪያ በእርግጥ ከአምላክ የመጣ መሆኑን ተገነዘበ። — 2 ነገሥት 5:13–15

11. (ሀ) “ሌሎች በጎች” በንዕማን የተመሰሉት በምን መንገዶች ነው? (ለ) ሁላችንም ከዚህ ምን ትልቅ ትምህርት ማግኘት አለብን?

11 ምናልባት የንዕማንን አንዳንድ ጠባዮች በራስህ ላይ ትመለከታለህን? እምነት እንዳሳዩት እስራኤላውያን ያልሆኑ ሌሎች ሰዎች ሁሉ ንዕማንም በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ከእውነተኛው አምልኮ ጋር ለሚተባበሩት “ሌሎች በጎች” አምሳያ ነው። እነዚህ ሁሉ በኃጢኣት የተወለዱ በመሆናቸው በመንፈሳዊ ሕመምተኞች የነበሩበት ጊዜ ነበር። ሁሉም የይሖዋ የቅቡዓን አገልጋዮች ክፍል እርዳታ አስፈልጓቸው ነበር። ይህ “ባሪያ” ከአምላክ ቃል ያስተማራቸውንም ነገሮች በታዛዥነት መፈጸም ነበረባቸው። (ማቴዎስ 24:45) አንዳንዶቹ በተሰጣቸው ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ሁሉ ያልተደሰቱበት ጊዜ አለ። ለምሳሌ አዘውትሮ በጉባኤ ስብሰባዎች የመገኘት፣ ከዓለም የመለየት ወይም የክርስቲያናዊ የውኃ ጥምቀት አስፈላጊነት አልታያቸውም ነበር። ምናልባትም ‘ራሳቸውን ክደው’ የክርስቶስ ተከታይ እንዳይሆኑ ልባቸው ስለከለከላቸው ራሳቸውን ከመወሰንና ከመጠመቅ ወደኋላ ብለው ይሆናል። አንዳንድ ጊዜም በጉባኤው ውስጥ ኃላፊነት ያላቸው ሰዎች ምክር ሲሰጧቸው የምክር አሰጣጡን መንገድ ነቅፈው ይሆናል። ውሎ አድሮ ግን እውነተኞቹ የጌታ “ሌሎች በጎች” ሁሉ ትሕትናንና ፍቅራዊ ታዛዥነትን የግድ መማር እንዳለባቸው ተገንዝበዋል። — ያዕቆብ 4:6፤ ማቴዎስ 16:24

ለእኛ ጠቃሚ የሆኑ ትእዛዞች

12, 13. (ሀ) የይሖዋን ትእዛዞች ማክበር የሚጠቅመን ለምንድን ነው? (ለ) ይህንን እንዴት በምሳሌ ማስረዳት ይቻላል?

12 ይሖዋንና መንገዶቹን እያወቅን ስንሄድ “እኔ ይሖዋ ራስህን እንድትጠቅም የማስተምርህ፣ መሄድ በሚገባህም መንገድ እንድትራመድ የማደርግህ አምላክህ ነኝ። ምነው ትእዛዞቼን ብቻ በጠበቅህ ኖሮ!” በማለት በቀድሞ ዘመን ለአገልጋዮቹ የተናገራቸው ቃላት ምን ያህል እውነት እንደ ነበሩ ለመገንዘብ እንችላለን። (ኢሳይያስ 48:17, 18 አዓት) የይሖዋ ጽኑ ምኞት ሕዝቦቹ ትእዛዛቱን በመከተል ከጉዳት እንዲጠበቁና ሕይወት አግኝተው በደስታ እንዲኖሩ ነው። አፈጣጠራችንንና እውነተኛ ደስታ የሚያመጣልን ነገር ምን እንደሆነ ያውቃል። ወራዳ ከሆነ ወይም ከሌሎች ጋር ያለንን ዝምድና ከሚያበላሽብን ተግባር እንድንርቅ ያስጠነቅቀናል።

13 ስለ ዝሙትና ስለ ምንዝር ይሖዋ የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ሰምተው የታዘዙት ሁሉ እነዚህ ድርጊቶች ከሚያስከትሉት የስሜት መረበሽ፣ ከበሽታና ዲቃላ ከመውለድ ድነዋል። (1 ቆሮንቶስ 6:18፤ ዕብራውያን 13:4) በ2 ቆሮንቶስ 7:1 ላይ እንደሚገኘው ያሉትን ምክሮች በሥራ ላይ በማዋል ጤንነትን ከሚጎዱና በሞት መቀጨትን ከሚያስከትሉ የትምባሆና የሌሎች አደንዛዥ ዕፆች ሱሰኛ ከመሆን ተገላግለዋል። ‘ከደም ራቁ’ ሲል የሰጣቸው ትእዛዝ አገልጋዮቹ ወደፊት በሕይወት የመኖር ተስፋቸው በእርሱ ላይ የተመካ እንደሆነ ያላቸውን እምነት ለማጠንከር የረዳቸው ሲሆን ደም በመውሰድ ሊተላለፉ ከሚችሉ አስፈሪ በሽታዎችም ጠብቋቸዋል። — ሥራ 15:28, 29

14. ሳያስፈልግ ከዓለም ጋር ከመጠላላፍ ይልቅ አስቀድመን መንግሥቱን በመፈለጋችን የምንጠቀመው እንዴት ነው?

14 በዓለም እስካለን ድረስ አስፈላጊ ለሆኑ ጉዳዮች ከዓለም ጋር በመጠኑ መገናኘታችን የማይቀር ነው። ይሁን እንጂ ይሖዋ ተስፋችንን ሁሉ በዓለም ላይ እንዳንጥልና የዓለም ክፍል እንዳንሆን አስጠንቅቆናል። ዓለም ወደፊት ምን እንደሚጠብቀው ይሖዋ ያውቃል። ሕይወታችንን አምላክ ወደፊት የሚያፈርሰውን ነገር በመገንባት ላይ ብናባክነው እንዴት ያለ ሞኝነት ይሆናል! ከዚህ የሚብሰው ግን እንደዚያ የሚያደርጉ ሰዎች ሕይወታቸውን ሙሉ የደከሙለት ዓለም የሚደርስበት ዕጣ ተካፋይ መሆናቸው ነው። እንግዲያው ‘የአምላክን መንግሥት ፈልጉ፤ በሕይወታችሁም አንደኛ ቦታ ስጡት!’ በማለት የአምላክ ልጅ የሰጠን ምክር እንዴት ጠቃሚ ነው!— 1 ዮሐንስ 2:17፤ ማቴዎስ 6:33

15. (ሀ) አዳም ያመለጠውን ዕድል እንደገና ከሚያገኙት መካከል ለመሆን ምን ማድረግን መማር ይኖርብናል? (ለ) በሺው ዓመት ግዛት ውስጥ ይሖዋ የሚያነጋግረን እንዴት ይሆናል?

15 ይሖዋ የሚያስፈልጉንን ነገሮች ሁሉ ግንዛቤው ውስጥ በማስገባት እርሱ በሚያመጣው ጽድቅ በሚሰፍንበት የነገሮች ሥርዓት ውስጥ በሕይወት እንድንኖር እያዘጋጀን ነው። የአዳም አለመታዘዝ ሰብዓዊ አለፍጽምናን፣ የዘላለም ሕይወት ማጣትንና ከገነት መውጣትን አስከትሏል። አዳም ያጣውን ዕድል ከሚያገኙት መካከል ለመሆን አምላክ ሲናገር የምናዳምጥ መሆናችንን ማረጋገጥ ይኖርብናል። በመጪው የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት የሰው ልጅ ወደ ፍጽምና የሚያደርሰውን ጉዞ ሲያያዘው አምላክ እኛን የሚያነጋግረን እንዴት ነው? በመሲሐዊቷ መንግሥት በኩል ነው። ያቺስ መንግሥት የሚታዩ ምድራዊ ተወካዮች ይኖሯታልን? አዎን፣ ይኖሯታል። ንጉሡ “በምድር ሁሉ ላይ መሳፍንት” ሆነው የሚያገለግሉ ሰዎች ይኖሩታል። (መዝሙር 45:16 አዓት ከኢሳይያስ 32:1, 2 ጋር አወዳድር።) የሰው ልጆች ለእነዚህ መሳፍንት ፍቅራዊ ታዛዥነትን በማሳየት ለሰማያዊ ንጉሣቸው ተገዢ መሆናቸውን ያረጋግጣሉ።

16. ሽማግሌዎችን መታዘዙ በአሁኑ ጊዜ ጥበቃ የሚሆነን ለምንድን ነው? ይህስ በአዲሱ የአምላክ ሥርዓት ውስጥ ለምናገኘው ሕይወት በደንብ የሚያዘጋጀን እንዴት ነው?

16 ለዚያ ዘመን ቅድመ ዝግጅት ለማድረግ ሲል ይሖዋ በአሁኑ ጊዜ በሚታየው ቲኦክራሲያዊ ድርጅቱ አማካኝነት ማሠልጠኛ እየሰጠ ነው። በጉባኤዎች ውስጥ በመንፈሳዊ የጎለመሱ ወንዶችን ወይም ሽማግሌዎችን አስነስቷል። እነርሱም የጉባኤ ስብሰባዎችን በተቀናጀ መልኩ ያካሄዳሉ፤ እንዲሁም የመንግሥቱን ምሥራች ለመስበክ መሪ ሆነው ይሠማራሉ። ይሖዋን ለማገልገል የሚፈልጉ ሁሉ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች እንዴት ሊሠሩባቸው እንደሚችሉ እንዲያስተውሉ ይረዷቸዋል፤ ከአምላክ ጋር ያላቸውን ዝምድና ሊያበላሹ ከሚችሉ ወጥመዶችም እንዲጠበቁ በፍቅር ያስጠነቅቃሉ። በዓለም ዙሪያ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች በተለይ አውሎ ነፋስ አዘል የባሕር ማዕበል ሲነሳ፣ የመሬት መንቀጥቀጥ ሲደርስና መሣሪያ በታጠቁ ሰዎች ብጥብጥ በሚፈጠርባቸው ጊዜያት የሽማግሌዎቹን መመሪያ መከተሉ ሕይወታቸውን እንዳዳነላቸው ተመልክተዋል። ጉባኤው የሽማግሌዎቹ ሳይሆን የይሖዋ ንብረት ነው። ሽማግሌዎቹ መንፈስ የገለጠልንን ነው የምንነግራችሁ አይሉም። ይሁን እንጂ ቅዱሳን ጽሑፎች እንደሚያሳዩት አምላክ መሪ አድርጎ ይጠቀምባቸዋል። እነርሱን መታዘዝ ማለት ይሖዋ አገልጋዮቹ ከመጪው ጥፋት በሕይወት ተርፈው ወደ አዲስ ሥርዓት እንዲገቡ እነርሱን ለማሰናዳት ለሚጠቀምበት ዝግጅት አክብሮት ማሳየት ማለት ነው። — ሥራ 20:28፤ ዕብራውያን 13:17

17. ታዛዥ እንድንሆን ሊገፋፋን የሚገባው ምንድን ነው?

17 ይሁን እንጂ እንዲህ ያለ የታዛዥነት መንፈስ እንዲያሳዩ የሚገፋፋቸው ከመጪው የዓለም ጥፋት በሕይወት ለመትረፍ ያላቸው ፍላጎት ብቻ አይደለም። ከዚህ የላቀ ምክንያትም አለ። ምን? ለሕይወትና ሕይወታችን እንዲቀጥል አምላክ ላዘጋጀው ነገር ሁሉ ያላቸው አድናቆት ነው። ሕይወታችን ትርጉም ያለው እንዲሆን የሚረዳ የማመዛዘን ችሎታ፣ ውበትንና መንፈሳዊ ነገሮችን የማድነቅ ችሎታ እንዲሁም ፈጣሪያችንን ለማወቅና ለማምለክ የሚያበቃ ችሎታ አለን። ለዘላለም የመኖር ዕድል እንድናገኝ ሲል የገዛ ልጁ ሕይወቱን አሳልፎ እንዲሰጥልን ያንቀሳቀሰውን ታላቅ ፍቅሩን ማወቃችንም ሌላው ምክንያት ነው።

18. አምላክን በደንብ ስናውቀው እርሱንና ድርጅቱን መታዘዝን እንዴት እንመለከተዋለን?

18 አምላክን በደንብ ያወቁ ሰዎች፣ ታዛዥነትን አስከፊ ግዴታ አድርገው አይመለከቱትም። የአምላክን ዓላማዎችና ብቃቶች በትክክል መረዳታቸውና እነርሱንም በሥራ ላይ በማዋል ጥሩ ውጤቶችን ማየታቸው ነገሮችን አምላክ በሚፈልገው መንገድ ማድረጉ አማራጭ የሌለው ምክንያታዊና ጠቃሚ ጎዳና ስለመሆኑ ምንም ጥርጣሬ እንዳያድርባቸው አድርጓል። ይህም ከመጥፎ ውጤት እንደሚጠብቅ ይገነዘባሉ። እንዲሁም ለአምላክ ያላቸውን ፍቅር የሚያሳዩበት አንዱ መንገድ ይህ ነው። አምላክን በመታዘዛቸው ታላቅ ደስታ ያገኛሉ። — 1 ዮሐንስ 5:3፤ መዝሙር 119:129

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 135 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

አንዳንዶች እንደ ለምጻሙ ንዕማን ኩራታቸውን ማሸነፍ አስፈልጓቸዋል