በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘የአዲስ ሰማይና የአዲስ ምድር’ አጀማመር

‘የአዲስ ሰማይና የአዲስ ምድር’ አጀማመር

ምዕራፍ 14

‘የአዲስ ሰማይና የአዲስ ምድር’ አጀማመር

1. (ሀ) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙ ጊዜ “ሰማያት” ተብሎ የተጠቀሰው ምንድን ነው? (ለ) በአንዳንድ ምንባቦች ላይ “ምድር” የሚለው ቃል ትርጉም ምንድን ነው?

ብዙ ሰዎች ሰማይ ሲባል ትዝ የሚላቸው ጠፈር፣ ጨረቃና ከዋክብት ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ሰማይን’ ከአገዛዝም ጋር ያዛምደዋል። (ሥራ 7:49) አንዳንድ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ “ሰማያት” የሚለውን ቃል በጽንፈ ዓለም ሉዓላዊነቱ አምላክን ለማመልከት ይጠቀምበታል። (ዳንኤል 4:26፤ ማቴዎስ 4:17) የሰዎች መንግሥታትም ከተገዥዎቻቸው ከፍ ያለ ቦታ ስላላቸው “ሰማያት” ተብለው ተጠርተዋል። (2 ጴጥሮስ 3:7) በተመሳሳይም “ምድር” ሲል ብዙውን ጊዜ ግዑዟን መሬት ያመለክታል፤ ይሁን እንጂ ሰብዓዊውን ኅብረተሰብም ሊያመለክት ይችላል። (ዘፍጥረት 11:1፤ መዝሙር 96:1) ይህን አጠቃቀም ማወቅህ ‘አዲሱን ሰማይና አዲሲቱን ምድር’ በሚመለከት የተሰጡት አስደናቂ ተስፋዎች ትርጉማቸው ምን እንደሆነ ይበልጥ ሊገባህ ይችላል። ከእነዚህ ተስፋዎች አንዳንዶቹ በጥንቷ እስራኤል ዘመን የመጀመሪያ ተፈጻሚነት አግኝተዋል።

‘በፈጠርሁት ደስ ይበላችሁ’

2. ይሖዋ እስራኤላውያን ወደ ምርኮ እንዲወሰዱ የፈቀደው ለምንድን ነው? ሆኖም ወደፊት ምን ይሆናል ሲል ተናግሮ ነበር?

2 እስራኤላውያን አምላክን እንደሚታዘዙ በመሐላ በማረጋገጥ ከእርሱ ጋር ቃል ኪዳን ገብተው ነበር። ይሁን እንጂ ከዳተኞች ሆኑ። በዚህም ምክንያት ይሖዋ ጥበቃውን እንደሚያነሳ፣ ኢየሩሳሌም እንድትጠፋና ሕዝቧ ተማርኮ ወደ ባቢሎን እንዲወሰድ የሚፈቅድ መሆኑን አሳወቀ። (ኢሳይያስ 1:2–4፤ 39:5–7) በዚያው ላይ ግን ንስሐ የገቡ ቀሪዎችን እንደገና ወደ አገራቸው እንደሚመልሳቸው በመናገር መሐሪነቱን አሳይቷል። — ኢሳይያስ 43:14, 15፤ 48:20

3. በኢሳይያስ 65:17 ላይ የተሰጠው ተስፋ ምን ትርጉም ነበረው?

3 ይህ የተረጋገጠ ነገር በመሆኑ እነዚህ እስራኤላውያን ወደ አገራቸው የመመለሳቸው ጉዳይ እንደተፈጸመ ያህል በመቁጠር ይሖዋ እንዲህ ብሏል:- “እነሆ፣ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እፈጥራለሁና፤ የቀደሙትም አይታሰቡም፣ ወደ ልብም አይገቡም። ነገር ግን በፈጠርሁት ደስ ይበላችሁ ለዘላለምም ሐሤት አድርጉ፤ እነሆ፣ ኢየሩሳሌምን ለሐሤት፣ ሕዝብዋንም ለደስታ እፈጥራለሁና።” (ኢሳይያስ 65:17, 18) ይህም ንስሐ የገቡት እስራኤላውያን ነፃ ይወጣሉ ማለት ነበር።

4. (ሀ) አስቀድሞ እንደተነገረው ከጭቆና ነፃ የወጡት መቼ ነበር? (ለ) በዚያን ጊዜ “አዲስ ሰማይ” እና “አዲስ ምድር” ምን ነበሩ?

4 በሰው አመለካከት የማይቻል ቢመስልም ኃያሏ ባቢሎን በ539 ከዘአበ በሜዶናውያንና በፋርሳውያን ድል ተደረገች። አይሁዳውያን ‘በአዲስ ሰማይ’ ማለትም በአዲስ መስተዳድር ሥር ሆኑ። ታላቁ ቂሮስ ‘በአዲሱ ሰማይ’ ውስጥ ከፍተኛ ሚና ነበረው። ቂሮስ ወደ ይሁዲነት ሃይማኖት ባይለወጥም ያን ሥልጣን እንዲይዝ የፈቀደለት ይሖዋ መሆኑንና የኢየሩሳሌምን ቤተ መቅደስ እንደገና ለመሥራት ይሖዋ እንደወከለው በግልጽ ተናግሯል። (2 ዜና መዋዕል 36:23፤ ኢሳይያስ 44:28⁠ን ተመልከት።) በ537 ከዘአበ በኢየሩሳሌም ውስጥ ገዥው ዘሩባቤልና ሊቀ ካህኑ ኢያሱ በዚያ መስተዳድራዊ “አዲስ ሰማይ” ውስጥ ከፍተኛ ቦታ ነበራቸው፤ ወደ አገራቸው የተመለሱት የአይሁድ ቀሪዎችም “አዲስ ምድር” ማለትም በሀገሪቱ ላይ ንጹሕ አምልኮን እንደገና ያቋቋመ ንጹሕ ኅብረተሰብ ሆነዋል። — ዕዝራ 5:1, 2

5, 6. (ሀ) ሕዝቡ በእርግጥ የተለወጡ መሆናቸውን የሚያረጋግጠው ምን ነበር? (ለ) ይሖዋ ከገሠጻቸው በኋላ ያሳዩት ዝንባሌ ከምርኮው በፊት ከነበራቸው ሁኔታ የተለየው እንዴት ነበር?

5 በአእምሮም ሆነ በልብ የተለወጠ ሕዝብ መሆናቸውን በተጨባጭ ለማሳየት በሕይወታቸው ውስጥ የንጹሕ አምልኮን ጉዳዮች ማስቀደም፣ በእውነት የይሖዋን ሉዓላዊነት ማክበርና የእርሱን ነቢያት ማዳመጥ ያስፈልጋቸው ነበር። ከዚህ ጋር በመስማማት ወደ ይሁዳ ምድር በደረሱ ጊዜ በመጀመሪያ ካደረጓቸው ነገሮቸ መካከል “የእስራኤልን አምላክ መሠዊያ” መሥራትና መሥዋዕት ማቅረብ ነበር። — ዕዝራ 3:1–6

6 የፍቅረ ነዋይ ዝንባሌና የሰው ፍርሃት ቤተ መቅደሱን ሠርተው እንዳይጨርሱ ዕንቅፋት በሆኑባቸው ጊዜ ይሖዋ በነቢያቱ አማካይነት ሕዝቡን ገሠጸ፤ እነርሱም ሰሙት። (ሐጌ 1:2, 7, 8, 12፤ 2:4, 5) ከዚያም ቆየት ብሎ ጋብቻን በሚመለከት ሕጉ የሚጠይቀውን ብቃት ባለማሟላት ትልቅ በደል እንደፈጸሙ በተጠቆመላቸው ጊዜ ሕዝቡ አካሄዳቸውን አስተካክለዋል። (ዕዝራ 10:10–12) በምሳሌያዊ አነጋገር የማያዩ ዓይኖችና የአምላክን ቃል የማይሰሙ ጆሮዎች ይዞ ከመቀመጥ ይልቅ በመንፈሳዊ ተፈወሱና እነዚህን የስሜት ሕዋሳት ከይሖዋ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ ተጠቀሙባቸው። (ኢሳይያስ 6:9, 10​ን ከ35:5, 6 ጋር አወዳድር።) ከዚህም የተነሳ አምላክ በኢሳይያስ 65:20–25 ላይ ከገባው ቃል ጋር በሚስማማ መንገድ አበለጸጋቸው።

7. የኢሳይያስ ትንቢት በሌላም መንገድ ወደፊት መፈጸም እንደነበረበት እንዴት እናውቃለን?

7 ይሁን እንጂ ስለ “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር” የተነገረው ትንቢት በዚህ ብቻ ተፈጽሞ የሚያበቃ ነበርን? በፍጹም አልነበረም። ክርስቲያኑ ሐዋርያው ጴጥሮስ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ትንቢቱ ወደፊት በሌላ መንገድ የሚፈጸምበትን ጊዜ በጉጉት ይጠብቁ እንደነበረ ተናግሯል። (2 ጴጥሮስ 3:13) እነርሱ የጠበቁት ነገር ሲፈጸም ዛሬ በዓይናችን እየተመለከትን ነው። በምን መንገድ? ታላቁ ቂሮስ ማለትም የላቀ ክብር የተቀዳጀው ኢየሱስ ክርስቶስ በዙፋን ላይ ሲቀመጥ ከተከናወኑ ነገሮች ጋር በተያያዘ መንገድ ነው።

8. (ሀ) ይሖዋ ይህ “አዲስ ሰማይ” ወደ ኅልውና እንዲመጣ ያደረገው መቼ ነበር? ከመጀመሪያው የትንቢቱ አፈጻጸም ጋር ሲወዳደር ምን ልዩነት ይታይበታል? (ለ) ‘የአዲሱ ሰማይ’ አባላት መበራከት እየሰፋ የሄደው እንዴት ነው?

8 ቀደም ሲል እንደተመለከትነው ይሖዋ ለልጁ በጠላቶቹ መካከል መግዛት እንዲጀምር ሥልጣን የሰጠው በ1914 ነው። ከረጅም ጊዜ በፊት ሲጠበቅ የኖረው “አዲስ ሰማይ” ከዚያን ጊዜ ወዲህ ኅልውና አገኘ። በዚህ ጊዜ የተፈጸመው ነገር የጥንቶቹ እስራኤላውያን ነፃ ሲወጡ ከተፈጸሙት ነገሮች ይበልጥ አስደናቂ ነበር። (መዝሙር 110:2፤ ዳንኤል 7:13, 14) በ1914 የተወለደው መንግሥት የሚገዛው ከሰማይ ሲሆን አምላክ መላዋን ምድር የመግዛት ሥልጣን ሰጥቶታል። በመንፈስ የተቀቡት (በድሮ ጊዜ የሞቱ) የክርስቶስ ተከታዮች ከጌታቸው ጋር ነገሥታትና ካህናት ለመሆን ከሞት ሲነሱ የመንግሥቱ አባላት ቁጥር ተበራክቷል። የዚህ መንግሥት ክፍል የሆኑ ሌሎች ቅቡዓን ምድራዊ ጉዞአቸውን ሲጨርሱ የአባላት ቁጥሩ እየተበራከተ በሄደው “አዲስ ሰማይ” ላይ ተጨምረዋል። (1 ተሰሎንቄ 4:14–17፤ ራእይ 14:13) እንግዲያው ከክርስቶስ ጋር ወራሽ የሆኑት አብዛኞቹ ቅቡዓን በአሁኑ ጊዜ በዚያች ሰማያዊት መንግሥት ውስጥ በመገኘት ተግተው በመሥራት ላይ ናቸው። ከክርስቶስ ጋር በዚህ መንገድ የተቀላቀሉት በመንፈስ የተወለዱ ክርስቲያኖች አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ሆነዋል። ስለ እርስዋም ይሖዋ “ኢየሩሳሌምን ለሐሤት፣ ሕዝቧንም ለደስታ እፈጥራለሁ” በማለት አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። — ኢሳይያስ 65:18

9. ይሖዋ በ1919 በዚሁ ምድር ላይ ‘ለደስታ ምክንያት’ የሚሆን ምን ነገር ፈጠረ?

9 ይሖዋ ‘ለደስታ ምክንያት’ የሚሆን ነገር [አዓት ] የፈጠረው በሰማይ ብቻ አይደለም፤ በምድርም ጭምር ነው። የመንግሥቱ ወራሽ የሆኑ ቀሪዎች አሁንም በምድር ላይ ይገኛሉ። በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት ጦርነቱ በፈጠረው ውዥንብር ተጠቅመው እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በሐሰት አስከስሰዋል፤ በአስተዳደር አካል አባላትም ላይ የረጅም ዘመን እስራት አስፈርደው ነበር። ይሁን እንጂ በታላቂቱ ባቢሎን ቁስቆሳ ከደረሰባቸው ከዚህ እስራት በ1919 በነፃ ተለቀቁ። በይሖዋ መንፈስ እየታገዙ ለንጹሕ አምልኮና ለአምላክ መንግሥት ጉዳዮች ያደረ ሕዝብ በመሆን እንደገና ተደራጁ።

10. (ሀ) በ537 ከዘአበ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የተደረጉት አይሁዶች በተስፋ የጠበቋቸው ነገሮች እነዚህ መንፈሳዊ እስራኤላውያን ከጠበቋቸው ነገሮች የተለዩ የነበሩት እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ ምን ሥራ ሰጣቸው? (ሐ) ገና በምድር ላይ እያሉ በብዙ የባረካቸው እንዴት ነው? ምዕራፍና ቁጥራቸው ብቻ የተሰጡት ጥቅሶች እነርሱ የሚገኙባቸውን አስደሳች ሁኔታዎች የሚገልጹትስ እንዴት ነው?

10 ይሁን እንጂ እነርሱ በተስፋ የሚጠብቋቸው ነገሮች በ537 ከዘአበ ወደ አገራቸው የተመለሱት አይሁዶች ከጠበቋቸው ነገሮች የተለዩ ነበሩ። የመንፈሳዊ እስራኤል አባሎች ‘በሰማይ የተጠበቀላቸውን’ ውርሻ በተስፋ ይጠብቁ ነበር። (1 ጴጥሮስ 1:3–5 አዓት) ሆኖም ያንን ሽልማት ከማግኘታቸው በፊት ይሖዋ እንዲሠሩት የፈለገው ሥራ ነበር። ይህን በማስመልከት “ሰማያትን እዘረጋ ዘንድ ምድርንም እመሠርት ዘንድ፣ ጽዮንንም:- አንቺ ሕዝቤ ነሽ እል ዘንድ ቃሌን በአፍህ አድርጌአለሁ፣ በእጄም ጥላ ጋርጄሃለሁ” በማለት ይሖዋ ትንቢት አስነግሮ ነበር። (ኢሳይያስ 51:16) ‘ቃሉን’ ማለትም መልእክቱን በመላው ምድር ላይ እንዲያውጁ በአገልጋዮቹ አፍ ላይ አስቀመጠ። አምላክ ‘አዲሱን ሰማይ’ በሰዎችም ሆነ በአጋንንት ሊነቀል እንደማይችል አድርጎ የተከለው መሆኑን በልበ ሙሉነት ማወጅ ጀመሩ። ይሖዋ ለሰማያዊቷ ጽዮን ተወካዮች ያደረገው ነገር ማንነታቸውን በግልጽ አሳይቷል። በመንፈሳዊና በሥነ ምግባር ባድማ ከሆነው የዓለም ሁኔታ ጋር ሲነፃፀር መንፈሳዊ እስራኤል የሚኖርበት “ምድር” ማለትም የእንቅስቃሴአቸው መስክ መንፈሳዊ ባሕርያትና የሥራ እንቅስቃሴዎች ሊያብቡ የሚችሉበት ሥፍራ ሆኖአል። ይህ መንፈሳዊ ገነት ነው! (ኢሳይያስ 32:1–4፤ 35:1–7፤ 65:13, 14፤ መዝሙር 85:1, 8–13) እንግዲያው በኢሳይያስ 65:17 ላይ ትንቢት የተነገረላት “አዲስ ምድር” ምንድን ነች?

‘ለአዲሲቱ ምድር’ መዘጋጀት

11. (ሀ) ይሖዋ ‘የአዲሲቱን ምድር’ እጩ አባላት በተለይ ከመቼ ጀምሮ እያዘጋጃቸው ነው? (ለ) የጥንቷን ባቢሎን ለቀው የወጡ የትኞቹ ሕዝቦች የእነርሱ ጥላ ናቸው?

11 በተለይ ከ1935 ጀምሮ ይሖዋ የመንፈሳዊ እስራኤልን አባላት ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት የሚጠባበቁ እጅግ ብዙ ሰዎች የሚሰበሰቡበት ሰዓት እንደ ደረሰ እንዲያስተውሉ አድርጓቸዋል። የመንግሥቱ ወራሽ ከሆኑት “ታናሽ መንጋ” ጋር ሲወዳደሩ በእርግጥም እጅግ ብዙ ሰዎች ሆነዋል። (ራእይ 7:9, 10) እነርሱም ጭምር ወደ መንፈሳዊ ገነት እንዲገቡ ተደርገዋል። በ537 ከዘአበ እና ከዚያ ቆየት ብሎ ከአይሁድ ጋር ከባቢሎን የወጡት እስራኤላውያን ያልነበሩ ሰዎች የእነርሱ ጥላ ነበሩ። (ዕዝራ 2:58, 64, 65፤ 8:17, 20) ምድራዊ ተስፋ ያላቸው እነዚህ እጅግ ብዙ ሰዎች የሆኑ ዘመናዊ የይሖዋ ምሥክሮች ‘የአዲሲቱ ምድር’ የወደፊት አባላት ናቸው።

12. ሰዎች ‘ለአዲሲቱ ምድር’ ጥሩ መሠረት መሆን እንዲችሉ በአሁኑ ጊዜ አምላክ እያዘጋጃቸው ያለው እንዴት ነው?

12 ከታላቁ መከራ በሕይወት የሚተርፉና ከፊታቸው ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወት የሚጠብቃቸው ሁሉ ‘የአዲሲቱ ምድር’ መሠረት ወይም የመጀመሪያ አባላት ይሆናሉ። መሠረቱ ጥሩ መሆን ይኖርበታል። ስለዚህ ከአሁኑ ጀምሮ በይሖዋ መንገዶች እንዲጓዙ በደንብ እየሠለጠኑ ነው። በጽንፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት ላይ ስለተነሳው ጥያቄ ልብን የሚነካ ግንዛቤ እንዲያገኙ እየተደረገ ነው። “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፣ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ” የሚለውን ምክር መከተሉ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ እየተማሩ ነው። (ምሳሌ 3:5, 6) ‘ይህን የመንግሥት ምሥራች’ በመስበኩ ሥራ ሙሉ ተሳትፎ በማድረግ የአምላክ መንግሥት ቀናተኛና ታማኝ ደጋፊ መሆናቸውን ለማስመስከር አጋጣሚ አግኝተዋል። (ማቴዎስ 24:14) ከሁሉም ብሔራት፣ ቋንቋዎችና ዘሮች የተውጣጡ ሰዎች በፍቅር በወንድምነት እየተያዩ እንደ አንድ ሆነው የሚሠሩበት ዓለም አቀፍ ኅብረተሰብ ክፍል መሆን ምን ማለት እንደሆነ ከራሳቸው ተሞክሮ እያዩት ነው። (ዮሐንስ 13:35፤ ሥራ 10:34, 35) አንተስ ከዚህ የትምህርት መርሐ ግብር ሙሉ በሙሉ ለመጠቀም በግልህ ትጣጣራለህን? እንዲህ የሚያደርጉ ሁሉ ከፊታቸው ግሩም ሕይወት ይጠብቃቸዋል።

‘አዲሲቱ ምድር’ እውን ስትሆን

13. የይሖዋ የተስፋ ቃል በ537 ከዘአበ ከታዩት ሁኔታዎች ይልቅ ወደፊት በምትመጣው “አዲስ ምድር” ላይ በላቀ መንገድ የሚፈጸመው እንዴት ነው?

13 ይሖዋ “አዲስ ምድር” ለማምጣት የገባው ቃል በ537 ከዘአበ ከተፈጸመበት ሁኔታ ይልቅ የመጨረሻው አፈጻጸሙ እጅግ የላቀና የተሟላ ይሆናል። የ“አዲስ ምድር” መሥራች የሚሆኑት ከታላቂቱ ባቢሎን ነፃ የወጡ ሰዎች ከመሆናቸውም ሌላ በዓለም ላይ የተንሰራፋው ጠቅላላው የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ለዘላለም ይደመሰሳል። (ራእይ 18:21) የኢሳይያስ ትንቢት መጀመሪያ ሲፈጸም ከነበረው ሁኔታ በተለየ መልኩ፣ ይህ “አዲስ ምድር” ይኸውም ጻድቅ የሆነ ሰብዓዊ ኅብረተሰብ ይሖዋን በሚሰድቡና አገልጋዮቹን በሚያሳድዱ ብሔራት የተከበበ አይሆንም። ሰብዓዊ መንግሥታት በሙሉ ለይሖዋ ሉዓላዊነት ለመገዛት እምቢ ስላሉ ድምጥማጣቸው እንዲጠፋ ይደረጋል፤ አሁን ያለው ክፉ ሰብዓዊ ኅብረተሰብም ከምድረ ገጽ ይጠፋል። (ዳንኤል 2:44፤ ምሳሌ 2:21, 22) ጽድቅ የሚሰፍንበት አዲሱ የአምላክ ሥርዓት ሲጀምር በፕላኔቷ ምድር ላይ በሕይወት የሚገኙት ይሖዋን የሚያከብሩና በመንገዶቹ መሄድ የሚያስደስታቸው ሰዎች ብቻ ይሆናሉ። — መዝሙር 37:4, 9

14. (ሀ) 2 ጴጥሮስ 3:13 እና ራእይ 21:1 የሚፈጸሙት መቼ ነው? (ለ) ‘አዲሱ ሰማይ’ በዚያን ጊዜ ሥራውን ሲያካሄድ ሁኔታዎቹን የተለዩ የሚያደርጋቸው ምንድን ነው? (ሐ) ‘በአዲሲቱ ምድር’ አባልነት ውስጥ እነማን ይጨመራሉ?

14 ሐዋርያው ጴጥሮስ በመንፈስ አነሳሽነት በጻፈው በሁለተኛው መልእክቱ ላይ የጠቀሰው ይህን ታላቅ ጊዜ ነው። (2 ጴጥሮስ 3:13) ሐዋርያው ዮሐንስም ከአምላክ የመጣለትን ራእይ ሲገልጽ “አዲስ ሰማይንና አዲስ ምድርንም አየሁ፣ ፊተኛው ሰማይና ፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና” በማለት ተመሳሳይ ወደሆነ አስደናቂ ተስፋ አመልክቷል። (ራእይ 21:1) ታላቁ መከራ አልፎ ሰይጣንና አጋንንቱ ሲታሰሩ አዲስ ዘመን ተከፈተ ማለት ነው። የሰይጣንና የአጋንንቱ መገኘት አሳድሮት የነበረው እኩይ ተጽዕኖ ይወገዳል። እርሱ የገነባው ሥርዓት በጠቅላላ ይንኮታኮታል። ከዚያ በኋላ የይሖዋን ሉዓላዊነት ችላ የሚሉ መንግሥታት ጣልቃ ገብነት ሳይኖር ‘አዲስ ሰማይ’ ይሖዋ ለፍጥረቶቹ ያለው ፍቅራዊ ዓላማ እንዲፈጸም ያደርጋሉ። በዚያ “አዲስ ሰማይ” ሥር ‘እጅግ ብዙ በሆኑ ሰዎች’ የተገነባች በእውነት ‘አዲስ የሆነች ምድር’ ትኖራለች። ለእነዚህ “እጅግ ብዙ ሰዎች” አምላክ ውብ በሆነች፣ ሁሉ ነገር በሚትረፈረፍባት፣ ደስታና ሰላም በሰፈነባት ምድራዊት ገነት ላይ ፍጻሜ የሌለው ሕይወት የማግኘት አጋጣሚ ይሰጣቸዋል። ሙታን የሚነሱበት አምላክ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ እነርሱም ጭምር የዚህች ጽድቅ የሚኖርባት “አዲስ ምድር” ክፍል የመሆን አጋጣሚ ያገኛሉ። — ራእይ 20:12, 13

15. በራእይ 21:3, 4 ላይ ያለውን ተስፋ ትልቅ ቦታ የምትሰጠው ለምንድን ነው?

15 ሐዋርያው ዮሐንስ አምላክ በዚያን ጊዜ ለሰው ልጆች ምን እንደሚያደርግላቸው የሚገልጽ የሚከተለውን ማስታወቂያ ከሰማይ ሰምቶ ነበር:- “እነሆ፣ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው ከእነርሱም ጋር ያድራል፣ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፤ እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና ብሎ ሲናገር ሰማሁ።” (ራእይ 21:3, 4) በዚያን ጊዜ ሕይወት እንዴት አስደሳች ይሆናል!

16. (ሀ) በኢሳይያስ 11:6–9 (ለ) በኢሳይያስ 35:1–7 (ሐ) በኢሳይያስ 65:20–25 ላይ የሚገኙት ተስፋዎች ምን እንድንጠብቅ ይቀሰቅሱናል? (መ) እነዚህን አስደሳች ተስፋዎች ያስገኘልን ማን ነው?

16 በዔደን የነበሩት ሁኔታዎችና ኢየሱስ ያደረጋቸው ተአምራት ‘በአዲሲቱ ምድር’ ውስጥ የሰው ሕይወት ምን እንደሚመስል አስደሳች ፍንጭ ይሰጣሉ። በተጨማሪም የኢሳይያስ 11:6–9፤ 35:1–7 እና 65:20–25 ትንቢቶች በዚያን ጊዜ በሥጋዊ መንገድ የሚፈጸሙ አንዳንድ ገጽታዎችን ይዘዋል። ይህም ለታዛዥ የሰው ልጆች ታላቅ በረከት ይሆናል። በሁሉም መልኩ ገነት በሆነችው ምድር ላይ ለመንፈሳዊ ጤንነትና ብልጽግና በጣም አስፈላጊ የሆኑት ነገሮች ከአካልና ከአእምሮ ፍጽምና ጋር ተዳምረው ሲሰጡን መንፈሳችን እንዴት ይረካ ይሆን! ከፊታችን እንደዚህ ያለ ዕፁብ ድንቅ የሆነ ተስፋ ተዘርግቷል። ታዲያ የዚህ ሁሉ ነገር ታላቅ ፈጣሪ ለሆነው ለይሖዋ ድምፃችንን ከፍ አድርገን ምስጋና ከማሰማት እንዴት መቆጠብ እንችላለን!

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]