በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የወደፊት ሕይወታችንን የሚወስኑ የአቋም ጥያቄዎች

የወደፊት ሕይወታችንን የሚወስኑ የአቋም ጥያቄዎች

ምዕራፍ 2

የወደፊት ሕይወታችንን የሚወስኑ የአቋም ጥያቄዎች

1. (ሀ) በብዙዎች ሰዎች አእምሮ ውስጥ የሚጉላሉት ወቅታዊ ጥያቄዎች ምንድን ናቸው? ለመፍትሔውስ ወዴት ይመለከታሉ? (ለ) ብዙውን ጊዜ የሚዘነጉት ምንድን ነው?

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የወደፊት ሕይወታችንን የሚመለከቱ አንገብጋቢ ጥያቄዎች በፍጥነት እየተፈራረቁ ከፊታችን ተደቅነዋል። ሁኔታዎቹ በጣም ስለከፉ በየትም ስፍራ የሚገኙ ሰዎች ከችግሮቹ መቼ እንገላገል ይሆን እያሉ ይጨነቃሉ። ምናልባት በአምላክ ያምኑ ይሆናል፤ ቢሆንም በምድር ላይ ያሉት ሁኔታዎች ሊሻሻሉ የሚችሉት በሰው ጥረት ይመስላቸዋል። አንዳንድ ሰዎች በሥልጣን ላይ ባሉት መንግሥታት አማካኝነት ወይም የእነዚህን መንግሥታት ውሳኔ በሕዝባዊ ዓመፅ በመቃወም ይህንን መሻሻል ለማምጣት ይሞክራሉ። ሌሎች ደግሞ ለዚህ አማራጭ የሌለው መፍትሔ አብዮት ነው ብለው ያምናሉ። ሕጎችን መለወጥ፣ መሪዎችን ወይም አንድን መስተዳድር በሌላ መተካት በእርግጥ ሁኔታዎችን ሊለውጥ እንደሚችል ይሰማቸዋል። ይሁን አንጂ ሐቁ ምን ያሳያል? ሰዎች ለብዙ ሺህ ዓመታት ቢዳክሩም ለዜጎቻቸው ሁሉ ፍትሕ፣ እውነተኛ ደኅንነትና ዘላቂ ደስታ ያመጣ አንድም መንግሥት አልፈጠሩም። ለዚህ ምክንያቱ ምንድን ነው?

2. የዓለም ሁኔታዎች ይህን ያህል የከፉት ለምንድን ነው?

2 በሥልጣን ላይ ያሉት ሰዎች የቱንም ያህል በጎ ዓላማ ቢኖራቸውም ሰብዓዊ መንግሥታትን ወደፈለጉት አቅጣጫ የሚያሽከረክሩት እነዚህ ባለሥልጣኖች ሊቆጣጠሯቸው የማይችሏቸው ኃይሎች ናቸው። እነዚህ ኃይሎች እነማን ናቸው? ከሰው የላቀ ኃይል ያላቸው መንፈሳውያን ፍጡራን ይኸውም ሰይጣን ዲያብሎስና አጋንንቱ ናቸው። እውነት ነው፣ ብዙ ሰዎች መንፈሳውያን አካላት አሉ ተብሎ ሲነገራቸው ያፌዛሉ። ኢየሱስ ክርስቶስ ግን እንደዚያ አላደረገም። የሰይጣንን የኋላ ታሪክ ያውቅ ስለ ነበር እርሱን “የዚህ ዓለም ገዥ” ብሎ ጠርቶታል። (ዮሐንስ 12:31) መጽሐፍ ቅዱስ በምሳሌያዊ አነጋገር ምድር አቀፉን የፖለቲካ ሥርዓት በአውሬ በመመሰል “ዘንዶው [ሰይጣን] ኃይሉንና ዙፋኑን ትልቅም ሥልጣን” ለዚህ አውሬ እንደሰጠ ይገልጻል። (ራእይ 13:1, 2፤ ከዳንኤል 7:2–8, 12, 23–26 ጋር አወዳድር።) መጽሐፍ ቅዱስ “ለምድር [ወዮላት] . . . ዲያብሎስ . . . ወደ እናንተ ወርዶአልና” በማለት ወዮ የሚያሰኝ መከራ በዘመናችን እየጨመረ እንደሚሄድ ተናግሯል። (ራእይ 12:12) ሰብዓዊው ኅብረተሰብ በዚህ ዓይነት ብጥብጥ የተናጠው በዚህ ምክንያት ነው ከማለት በስተቀር አርኪ የሆነ ሌላ ምክንያት ማቅረብ አይቻልም። ግን ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? ከዚህስ ለመላቀቅ ምን ማድረግ እንችላለን?

የሉዓላዊነት ጥያቄ

3. ዘፍጥረት 2:16, 17 የሰው ዘር ከአምላክ ጋር ሊኖረው ስለሚገባ ተገቢ ዝምድና ምን ያሳያል?

3 የመጀመሪያዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ምዕራፎች ይሖዋ አምላክ የመጀመሪያዎቹን ሁለት ሰዎች፣ ማለትም አዳምንና ሔዋንን ከፈጠራቸውና በዔደን ገነት ውስጥ ካስቀመጣቸው በኋላ ከእርሱ ጋር ስለሚኖራቸው ዝምድና መመሪያ እንደሰጣቸው ይነግሩናል። አባታቸውና ደግ መጋቢያቸው እንዲሁም የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዥ ነበር። ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ የሕይወታቸው መቀጠል የተመካው እርሱን በመታዘዛቸው ላይ መሆኑን መቀበል ነበረባቸው። — ዘፍጥረት 2:16, 17፤ ከሥራ 17:24, 25 ጋር አወዳድር።

4. (ሀ) ሰይጣን ከየት መጣ? (ለ) እርሱስ በውስጡ ምን መጥፎ ምኞት እንዲያድግ ፈቀደ?

4 በዚያን ጊዜ ሁሉም ፍጥረት ፍጹም ነበር። መላእክትና ሰዎች የፈቀዱትን የመምረጥ ነፃነት ስለነበራቸው ከእንስሳት የተለዩ ነበሩ። ሆኖም ብዙም ሳይቆይ ከመላእክት አንዱ ይህን ግሩም የሆነ በግል የመወሰን ችሎታ አላግባብ ተጠቀመበትና በይሖዋ ሉዓላዊነት ላይ ዓመፀ። በዚህ ምክንያት ተፃራሪ ወይም እምቢተኛ ሆነ፤ ሰይጣን የሚለው ስም ቀጥተኛ ትርጉሙ ይኸው ነው። (ከያዕቆብ 1:14, 15​ና ከራእይ 12:9 ጋር አወዳድር።) ሰይጣን ትልቅ ደረጃ ላይ ለመድረስ ባለው ምኞት ተነሳስቶ የመጀመሪያዎቹን ሁለት ሰዎች ከይሖዋ ጋር አለያይቶ በቁጥጥሩ ሥር አደረገ። የወደፊቱን ጊዜ አሻግሮ ሲመለከት ምድር በሰው ተሞልታ፣ የሰው ልጆችም እርሱን እንደ አምላክ ቆጥረው ክብር ሲሰጡት ታየው። (ከኢሳይያስ 14:12–14​ና ከሉቃስ 4:5–7 ጋር አወዳድር።) በዔደን ስለተካሄደው ነገር የሚዘግበው ጽሑፍ ተረት አይደለም። ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ እውነተኛ ታሪክ አድርጎ ጠቅሶታል። — ማቴዎስ 19:4, 5

5. (ሀ) በዔደን ምን ጥያቄዎች ተነሱ? (ለ) ጥያቄዎቹስ እነማንን ይነካሉ?

5 ኢየሱስ “እርሱ . . . በእውነት አልቆመም። . . . ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነውና” በማለት ስለ ሰይጣን ተናግሯል። (ዮሐንስ 8:44) በጽሑፍ ተመዝግቦ የሚገኘው የመጀመሪያው የሰይጣን ውሸት የአምላክ እውነተኝነት አጠያያቂ ነው በማለት ለሔዋን የነገራት ቃል ነው። የአምላክን ሕግ እንዳይቀበሉ ገፋፋቸው፤ እያንዳንዱ ፍጡር በሕይወቱ ውስጥ የራሱን የአቋም መስፈርት ቢያወጣ ጠቃሚ ነው ብሎ ተከራከረ። (ዘፍጥረት 3:1–5፤ ከኤርምያስ 10:23 ጋር አወዳድር።) በዚህ መንገድ የይሖዋ ሉዓላዊነት በዔደን ውስጥ ግድድር ተነሳበት። በኋላ የተፈጸሙ ነገሮች እንደሚያሳዩት የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጥረታት በሙሉ አቋማቸውን ሳያጐድፉ ከአምላክ ጋር የመጣበቃቸው ጉዳይ ጥያቄ ላይ ወድቋል። አምላክን የሚያገለግሉት በእርግጥ ስለወደዱት ነው ወይስ እነርሱን ከእርሱ እንዲያፈነግጡ ማድረግ ይቻላል? (ኢዮብ 1:7–12፤ 2:3–5፤ ሉቃስ 22:31) እነዚህ የአቋም ጥያቄዎች በሰማይና በምድር ያሉትን ፍጥረታት ሁሉ ይነካሉ። ታዲያ የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዥ ምን እርምጃ ወሰደ?

6. ይሖዋ ዓመፀኞቹን ለምን ወዲያው አላጠፋቸውም?

6 ይሖዋ ዓመፀኞቹን ወዲያውኑ በማጥፋት ፈንታ የአቋም ጥያቄዎቹ ለአንዴና ለመጨረሻ እልባት የሚያገኙበትን የተወሰነ ጊዜ በመፍቀድ ነገሩን በጥበብ ይዞታል። አምላክ ይህን ያደረገው ለራሱ አንዳች ነገር ለማረጋገጥ ብሎ ሳይሆን የፈቀዱትን የማድረግ ነፃነት ያላቸው ፍጡሮቹ በእርሱ አገዛዝ ላይ ማመፅ የሚያመጣውን መጥፎ ፍሬ ራሳቸው እንዲያዩና በእነዚህ ከፍተኛ ጥያቄዎች ላይ በየትኛው ወገን መቆም እንደሚፈልጉ እንዲያሳዩ ዕድል ለመስጠት ነው። ጥያቄዎቹ አንድ ጊዜ እልባት ካገኙ ወደፊት ማንም ቢሆን ሰላምን እንደገና እንዲያደፈርስ በጭራሽ አይፈቀድለትም።

7. (ሀ) ሰብዓዊ መንግሥታት እንዴት ተጀመሩ? (ለ) ምን ዓይነት ታሪክስ አስመዝግበዋል?

7 ይሖዋ አምላክ የሰዎች ፈጣሪ እንደመሆኑ መጠን ገዥያቸው ለመሆን የማይገሰስ መብት አለው። (ራእይ 4:11) ይሁን አንጂ ከጊዜ በኋላ ሰይጣንና አጋንንቱ ሰዎች ምን ነገር መጥፎ ወይም ጥሩ እንደሆነ የሚወስኑበትን የአቋም መስፈርት ራሳቸው ለማውጣትና መሰሎቻቸው የሆኑትን ሰዎች ለመግዛት በውስጣቸው ፍላጎት አሳደሩባቸው። ራሱን ንጉሥ አድርጎ የሾመው የመጀመሪያው ሰው ናምሩድ ነበር። እርሱም በመስጴጦምያ ባሉት ከተሞች መግዛት ጀመረ። ናምሩድ “ይሖዋን በመቃወም [የእንስሳትና የሰዎች ጭምር] ታላቅ አዳኝ ነበር።” (ዘፍጥረት 10:8–12 አዓት) ከናምሩድ ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ሁሉም የመስተዳድር ዓይነት ተሞክሯል። ይሁን እንጂ ታሪክን ያጠና ማንኛውም ሰው እንደሚያውቀው አጠቃላዩ የታሪክ መዝገብ በሥልጣን መባለግና በደም ማፍሰስ የተሞላ ነው። — መክብብ 8:9

8. ኢየሱስ በዓለም የፖለቲካ ሥርዓት እጁን ለማስገባት እምቢ ያለው ለምንድን ነው?

8 ኢየሱስ ክርስቶስ ምድር ላይ ሳለ ሰይጣን እርሱንም ጭምር እጁ ውስጥ ለማስገባት ሞክሮ ነበር። አንድ ጊዜ ብቻ ወድቆ ቢሰግድለት “የዓለምን መንግሥታት ሁሉ” እንደሚሰጠው ቃል ገባለት። ኢየሱስ ግን እምቢ አለ። (ሉቃስ 4:1–13) ቆይቶም ሕዝቡ ሊያነግሡት ፈለጉ፤ ኢየሱስ ግን ጥሏቸው ሄደ። (ዮሐንስ 6:15) የዓለም የፖለቲካ ሥርዓት ምን እንደሆነ ያውቅ ስለነበር ይህን ሥርዓት ለማሻሻል እንዲሞክር የአምላክ ፈቃድ አለመሆኑን ተገንዘቦ ነበር።

9. (ሀ) የሰውን ዘር ችግሮች ለመፍታት የአምላክ መንግሥት ብቻ ማድረግ የምትችላቸው ምን ነገሮች መደረግ አለባቸው? (ለ) ይህች መንግሥት ምንድን ናት?

9 ኢየሱስ አምላኩና አባቱ ለሆነው ለይሖዋ ፍጹም ታማኝ መሆኑን አሳይቷል። የአባቱን መንገዶች ይወድ ነበር፤ ምን ጊዜም ይሖዋን ደስ የሚያሰኘውን ያደርግ ነበር። (ዮሐንስ 8:29) ለሰው ችግሮች መፍትሔ የሚመጣው እውን መስተዳድር ከሆነችው በሰማይ ሆና ከምትገዛውና ለሰው ዘር የሚያስፈልገውን ጽድቃዊና ፍቅራዊ መመሪያ ከምትሰጠው የአምላክ መንግሥት እንደሆነ ያውቅ ነበር። የሰይጣንንና የአጋንንቱን ተፅዕኖ ልታስወግድ የምትችለው ይህች መንግሥት ብቻ ነች። ከሁሉም ዘሮችና ብሔራት የተውጣጡ ሕዝቦችን አስተባብራ በሰላም የሚኖር አንድ ዓለም አቀፋዊ ቤተሰብ ለማድረግ የምትችል እርሷ ብቻ ነች። የሰውን ዘር ከኃጢአትና ከሞት ባርነት ነፃ ልታወጣ የምትችል እርሷ ብቻ ነች። ለሰው ዘር ዘላቂ ደስታ ልታመጣ የምትችለው እርሷ ብቻ ነች። ይህች መንግሥት በፖለቲከኞች ቀያሽነትና በቄሶች ቡራኬ የተቋቋመች መንግሥት አይደለችም። የእርሷን ጉዳዮች ለማራመድ እውነተኛ ክርስቲያኖች ብረት አንስተው እንዲዋጉላት የሚያስፈልጋት መንግሥት አይደለችም። አምላክ ራሱ በዙፋን ላይ ያስቀመጠው ፍጹም የሆነ ሰማያዊ ንጉሥ ያላት የአምላክ የራሱ መስተዳድር ነች። ኢየሱስ የሰበከውና ተከታዮቹ መንግሥትህ ትምጣ ብለው እንዲጸልዩ ያስተማረው ስለዚች መንግሥት ነው። — ዳንኤል 2:44፤ ራእይ 20:1, 2፤ 21:3, 4

የትኛውን ወገን ትመርጣለህ?

10. (ሀ) እያንዳንዳችን መልስ ልንሰጥበት የሚገባ ትልቁ የአቋም ጥያቄ ምንድን ነው? (ለ) ያንንስ በሚመለከት ምን እያደረግን መሆን አለብን?

10 መልስ እንድትሰጥበት የሚያስፈልግህ ጥያቄ አለ:- የአጽናፈ ዓለም ፈጣሪ የሆነው ይሖዋ አምላክ የዚህ አጽናፈ ዓለም ሉዓላዊ ገዥ ለመሆን የማይገሰስ መብት እንዳለውና፣ የሥልጣን ቁንጮ መሆኑን ትቀበላለህን? በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተገለጹትን ዓላማዎቹና ከአንተ የሚፈለጉትን ብቃቶች ለማወቅ ጊዜ መድበህ አጥንተሃልን? ለይሖዋ የበላይነት ካለህ አክብሮትና ለመንገዶቹ ካለህ አድናቆት የተነሳ አምላክን በፍቅር የምትታዘዝ መሆንህን ታሳያለህን? — መዝሙር 24:1, 10፤ ዮሐንስ 17:3፤ 1 ዮሐንስ 5:3

11. ከዚያ የተለየ ጎዳና መምረጥ ለምን ደስታ አያስገኝም?

11 ከዚህ የተለየ መንገድ የመረጡ ሰዎች የላቀ ደስታ አግኝተዋልን? ሰይጣን የሰው ዘሮች አምላክን ከመስማት ይልቅ በራሳቸው ሐሳብ ቢመሩ ሊጠቀሙ ይችላሉ ሲል ያስነሳው ክርክር ውጤቱ ምን ሆኖአል? አምላክ የምድር ባለቤት መሆኑን፣ የሰው ዘሮችም ከመጀመሪያዎቹ ሁለት ሰዎች የመጡ ወንድማማች መሆናቸውን አለመቀበሉ በዚህ መቶ ዘመን ውስጥ ብቻ ከ100 ሚልዮን የሚበልጡ ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች በጦርነት እሳት እንዲበሉ ምክንያት ሆኖአል። የመጽሐፍ ቅዱስን የሥነ ምግባር ደረጃ አለመጠበቅ የቤተሰብ መፍረስን፣ እንደ ወረርሽኝ የተዛመተውን የአባለዘር በሽታ፣ አደንዛዥ ዕፅ እየወሰዱ ጤናን ማቃወስንና የዓመፅ ወንጀልን አስከትሏል። በዓመፅ ከመሞት ያመለጡ ሰዎችም ቢሆኑ ከአዳም በተወረሰ ኃጢአት ምክንያት የሚመጣው ሞት አሳዶ ይደርስባቸዋል። ሰዎች የፈጣሪያቸውን ጥበባዊና ፍቅራዊ ሕጎች ቸል በማለታቸው ራሳቸውንም ሆነ አጠገባቸው ያሉትን እንደሚጎዱ ማስረጃዎቹ ሁሉ ይመሰክራሉ። (ሮሜ 5:12፤ ከኢሳይያስ 48:17, 18 ጋር አወዳድር።) የምትፈልገው የዚህ ዓይነት ሕይወት እንዳልሆነ የተረጋገጠ ነው። ከዚህ በጣም የሚሻል ነገር ለመምረጥ ትችላለህ።

12. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ ምን ሞቅ ያለ ግብዣ ያቀርብልናል? (ለ) ደረጃ በደረጃ የአምላክን ቃል በሕይወታችን ውስጥ በሥራ ላይ ስናውል ምን እናያለን?

12 መጽሐፍ ቅዱስ “ይሖዋ ጥሩ እንደሆነ ቅመሱ፣ እዩም፣ እርሱን መጠለያው የሚያደርግ ሰው ደስተኛ ነው” በማለት ሞቅ ያለ ጥሪ ያቀርባል። (መዝሙር 34:8 አዓት) ይህን ለማድረግ በመጀመሪያ ይሖዋን ማወቅና ምክሩን በሥራ ላይ ማዋል ያስፈልግሃል። ይህን ስታደርግ ሕይወትህ ትርጉም ያለው ይሆንልሃል። ለጊዜው ችግርህን ለመርሳት የሚያስችሉ በኋላ ግን ሐዘን የሚያስከትሉ ደስታዎችን ለአንድ አፍታ በመጨበጥ ፋንታ የኑሮን ችግሮች ታግለህ ለማሸነፍና ለሁልጊዜው የሚጸና ደስታ እንዴት ማግኘት እንደምትችል ትማራለህ። (ምሳሌ 3:5, 6፤ 4:10–13፤ 1:30–33) በተጨማሪም በአምላክ መንግሥት አማካኝነት በሚመጡት ግሩም የሆኑ በረከቶች የመካፈል አጋጣሚ ይኖርሃል። የምትናፍቀው የዚህን ዓይነት ሕይወት ከሆነ አሁንኑ እርምጃ መውሰድህ በጣም አስፈላጊ ጉዳይ ነው። ለምን?

ሁሉም ብሔራት ወደ አርማጌዶን እየገሰገሱ ነው

13. በአሁኑ ጊዜ ከይሖዋ ጎን ለመቆም ጽኑ አቋም መውሰድ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

13 እያወቁም ይሁን በግድ የለሽነት የሰይጣንን አመራር የሚከተሉትን ሰዎችና ድርጅቶች ይሖዋ ለዘላለም አይታገሳቸውም። የምድርን መልክ እያጠፉ፣ የሌሎችን ሕይወት እያበላሹና የአምላክን ሕግ እየጣሱ ለሁልጊዜ እንዲቀጥሉ አይፈቀድላቸውም። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ታላቁ የይሖዋ ቀን’ ብሎ የሚጠራው ጊዜ ሲደርስ ለአድራጎታቸው ሁሉ መልስ ይሰጣሉ። — ሶፎንያስ 1:2, 3, 14–18

14. አሁን ሁሉም ብሔራት ወዴት እየገሰገሱ ነው?

14 ኢየሱስ ክርስቶስ በአሁኑ የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ቀናት ውስጥ ስለሚደርሱት ነገሮች በላከው ራእይ ላይ ‘የአጋንንት መናፍስት ሁሉን ወደሚችለው የአምላክ ታላቅ የጦርነት ቀን ለማስከተት ወደ ምድር ነገሥታት ሁሉ እንደሚወጡ’ ገልጾ ነበር። ራእዩ እንደገለጸው “በዕብራይስጥም ሐርማጌዶን [ወይም አርማጌዶን] ወደሚባል ሥፍራ አስከተቷቸው።” በአሁኑ ጊዜ የነገሥታቱ ክተት እየተካሄደ ነው! — ራእይ 16:14, 16 ኦቶራይዝድ ቨርሽን

15, 16. (ሀ) አርማጌዶን ምንድን ነው? (ለ) ለምንስ አስፈላጊ ሆነ?

15 መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገርለት አርማጌዶን የኑክሌር መሣሪያ እንዳይመረት እገዳ ቢደረግ ሊቀር የሚችል አይደለም። ብሔራት በውይይት ሊያስቀሩት አይችሉም። ስሙ ከጥንቷ የመጊዶ ከተማ የተወሰደ ቢመስልም በመካከለኛው ምሥራቅ ከሚገኝ ቦታ የበለጠ ነገርን ያመለክታል። ምንም እንኳን የተለያየ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ቢኖራቸውም ሁሉም መንግሥታት በማይታየው “የዚህ ዓለም ገዥ” እየተነዱ የይሖዋ ተቃዋሚ መሆናቸውን ወደሚያሳዩበት ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ ለመድረስ ጉዞውን ተያይዘውታል። “የምድር ሁሉ ነገሥታት” ከተከታዮቻቸው ሁሉ ጋር አቋማቸውን እንዲያሳዩ እየተደረጉ ነው። አርማጌዶን ልክ ሊጀምር ሲል ለአምላክ መንግሥትና ስለ እርሷ ለሚያውጁ ሰዎች ያላቸው ተቃውሞ በምድር ዙሪያ የከረረ ይሆናል። የሰይጣንን መኖር ቢቀበሉም ባይቀበሉም የአምላክ ቃል እንደሚገልጸው ‘ዓለም በሞላው በክፉው ተይዟል።’ ጠቅላላው ክፉ ዓለምና ልባቸውን የሚጥሉበት ሁሉ አዎን፣ የዓለምን መንገዶች የሚከተሉ ሁሉ መወገድ አለባቸው። — 1 ዮሐንስ 5:19፤ 2:15–17

16 ይህ ዓለም ከላይ እስከ ታች ነቅዟል። የወጣላቸው ወንጀለኞች ብቻ ሳይሆኑ ተራ ዜጎችም ጭምር ለሕግ፣ ለሰው ሕይወትና ንብረት የግድ የለሽነት ጠባይ ያሳያሉ። ከዚህ የባሰ ደግሞ አምላክ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚናገረውን ለመስማት አሻፈረን ብለዋል። ሉዓላዊነቱን ኣያከብሩም። አምላክ በስሙ ላይ የመጣውን ስድብ ለማስወገድና ጽድቅ አፍቃሪዎች እውነተኛ ሰላምና ደኅንነት የሚያገኙባትን ገነት የሆነች ምድር ለማዘጋጀት ሲል እርምጃ መውሰድ ያስፈልገዋል።

17. (ሀ) የጥፋት እርምጃው ስፋት ምን ያህል ይሆናል? (ለ) የተፈለገው ውጤት እንዲገኝ የሚከታተለው ማን ነው?

17 የጥፋት እርምጃ በሚወሰድበት ጊዜ ይህ የመጣው ከይሖዋ እንደሆነ ምንም የማያጠራጥር ይሆናል። ምድር ዙሪያዋን በጥፋት ማዕበል ትጥለቀለቃለች። ፍርድ አስፈጻሚ ኃይሎች ሥራቸውን ሲጀምሩ ይሖዋ እርምጃ እየወሰደ እንደሆነ ብሔራት ይታወቃቸዋል። የመንግሥት ሥልጣን ተዳክሞ ሁሉም ነገር ከቁጥጥር ውጭ ሲሆን የሰው ሁሉ እጅ በወንድሙ ላይ ይሆናል። የአምላክ ልጅ በሰማይ ሆኖ የእርምጃው ውጤት እርሱ እንደሚፈልገው እንዲሆን ያደርጋል። — ራእይ 6:16, 17፤ 19:11–13፤ ዘካርያስ 14:13

18. ከዚያ በሕይወት የሚተርፉት እነማን ይሆናሉ?

18 የኑክሌር ጦርነት ቢደረግ ማንንም ሳይመርጥ ሁሉንም ያወድማል፤ ይህ ጥፋት ግን እንደዚያ አይሆንም። ታዲያ እነማን በሕይወት ይተርፋሉ? ሃይማኖት አለን የሚሉ ሁሉ ወይም ምናልባት ክርስቲያን ነን የሚሉ ሁሉ ከጥፋቱ ይተርፉ ይሆን? ኢየሱስ እንደነዚህ ያሉትን “ብዙዎች” “ዓመፀኞች” ብሏቸዋል። (ማቴዎስ 7:21–23) በሕይወት ተርፈው ወደ “አዲስ ምድር” የሚገቡት ከይሖዋና ከነገሠው ልጁ ከኢየሱስ ጋር የጠበቀ ዝምድና የመሠረቱት ብቻ ይሆናሉ። እነዚህ ሰዎች በአኗኗራቸውና ስለ መንግሥቱ በሚሰጡት ምሥክርነት በእርግጥ ‘አምላክን እንደሚያውቁና ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል እንደሚታዘዙ’ ያረጋገጡ ይሆናሉ። ታዲያ አንተ እንደዚህ ዓይነት ሰው ለመሆን እየጣርክ ነውን? — 2 ተሰሎንቄ 1:8፤ ዮሐንስ 17:3፤ ሶፎንያስ 2:2, 3

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]