በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የዳግም መፈጠር ጊዜ

የዳግም መፈጠር ጊዜ

ምዕራፍ 13

የዳግም መፈጠር ጊዜ

1. (ሀ) ከጥፋት ተርፈው ወደ “አዲስ ምድር” የሚገቡት ምን አስደናቂ አጋጣሚ ይጠብቃቸዋል? (ለ) ይሁን እንጂ ይህ ምን የሚጠይቅ ይሆናል?

ይህ ብልሹ ዓለም በሚጠፋበት ጊዜ በሕይወት መትረፍ ትልቅ መታደል ነው። በዚህ ዓለም ላይ ካለው የፍትሕ መጓደል፣ ስግብግብነትና ዓመፅ ለመገላገል እንናፍቃለን። ነገር ግን ከጥፋቱ መትረፍን ይበልጥ ማራኪ የሚያደርገው ሌላም ነገር አለ። ምን ይሆን? ‘የአዲሲቱ ምድር’ ክፍል የሚሆኑት ሁሉ ከአለፍጽምናቸው፣ ከሕመም፣ በሥቃይ ከተሞላ ኑሮ፣ ከሞትም እንኳን ሳይቀር የመገላገል አጋጣሚ የሚያገኙ መሆናቸው ነው። (ራእይ 21:1–5) ይህ ሁሉ እንዲሆን ግን ኃጢአት ከሥሩ መነቀል ይኖርበታል። ይህስ የሚቻለው እንዴት ነው? ነገሩ ኢየሱስ ክርስቶስ “ዳግም መፈጠር” በማለት ከገለጸው ሁኔታ ጋር የተያያዘ ነው።

2. በማቴዎስ 19:28 ላይ የተጠቀሰው “ዳግም መፈጠር” ምንድን ነው?

2 ኢየሱስ ለሐዋርያቱ “እናንተስ የተከተላችሁኝ፣ በዳግመኛ ልደት [“በዳግም መፈጠር” አዓት] የሰው ልጅ በክብሩ ዙፋን በሚቀመጥበት ጊዜ፣ እናንተ ደግሞ በአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ስትፈርዱ በአሥራ ሁለት ዙፋን ትቀመጣላችሁ” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 19:28) ይህ ‘የዳግም መፈጠር’ ጊዜ፣ ወይም ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች እንደሚገልጹት ሁሉ ነገር ‘የሚታደስበት’፣ ‘ሁሉም አዲስ የሚሆንበት ጊዜ’ ይሆናል። (በሮዘርሃም የተተረጎመው ዘ ኤምፋሳይዝድ ባይብል፣ ዘ ጀሩሳሌም ባይብል ) በዳግም መፈጠር አማካኝነት የሰው ዘር በመጀመሪያው ላይ የነበረው ፍጽምና ይመለስለታል።

3. (ሀ) የአዳም ኃጢአት ምን አስከትሏል? (ለ) ከአዳም ዘሮች ውስጥ አንዳቸውም እንኳን ከወረሱት የኃጢአት ውጤት ለመላቀቅ ያልቻሉት ለምንድን ነው?

3 ከአዳም በተወረሰው ኃጢአት ምክንያት ዘሮቹ ሁሉ መሞት ግድ ሆኖባቸዋል። ብዙዎቹም ወደ ሞት በሚያደርስ ክፉ በሽታ ተሠቃይተዋል። (ሮሜ 5:12) ገንዘብ ከፍሎ ከሞት ነፃ መውጣት የሚቻል ነገር አልሆነም። ፍጽምና የሌለው ማንኛውም ሰው አቅሙ የሚፈቅድለትን ምንም ነገር ቢያደርግ ለራሱም ሆነ ለሌላ ሰው ከኃጢአት እስራት መፈታትን ማስገኘት አይችልም። የሰው ልጆች ለዘላለም የመኖርን አጋጣሚ እንደገና እንዲያገኙ ከተፈለገ አዳም ካጠፋው ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወት ጋር የሚመጣጠን መሥዋዕት እንዲቀርብ መለኮታዊ ፍትሕ ይጠይቃል። ከአዳም ዘሮች ውስጥ አንዳቸውም ቢሆን ለመሥዋዕትነት የሚቀርብ ይህን የመሰለ ሕይወት የለውም። — መዝሙር 49:7–9፤ መክብብ 7:20

4. (ሀ) አስፈላጊው ቤዛ እንዴት ተገኘ? (ለ) ከእርሱስ እንዴት ልንጠቀም እንችላለን?

4 ይሖዋ ግን በምሕረቱ አስፈላጊውን ዝግጅት አደረገ። አንድያ ልጁ ኢየሱስ ሕይወቱን “ተመጣጣኝ ቤዛ” እንዲሆን ይሖዋ ፍጹም ሰው አድርጎ ወደ ምድር ላከው። (1 ጢሞቴዎስ 2:5, 6 አዓት) ይገባናል የማንለው የአምላክ ደግነትና ለሰው ዘር ያለው ፍቅር እንዴት አስደናቂ በሆነ መንገድ ተገለጸ! በውጤቱ የሚገኘው ሕይወት የድካም ዋጋ ሆኖ የሚከፈለን ሳይሆን ከአምላክ በነፃ የሚታደለን ስጦታ ነው። ይሁን እንጂ ይህ ሕይወት የሚሰጠው ይኸው መለኮታዊ ዝግጅት እንደሚያስፈልጋቸው ከልብ ለተቀበሉ፣ ለሚያምኑበትና ይህንንም እምነት የአምላክን ልጅ በመታዘዝ ለሚያሳዩ ብቻ ነው። (ሮሜ 6:23፤ ዮሐንስ 3:16, 36) ታዲያ የሰው ልጆች የዚህን መሥዋዕት ጥቅሞች የሚያገኙት መቼ ነው?

ከክርስቶስ መሥዋዕት አሁን የሚገኙ ጥቅሞች

5. (ሀ) ከክርስቶስ መሥዋዕት በመጀመሪያ የተጠቀሙት እነማን ነበሩ? (ለ) የትኛው ሌላ ቡድን ተጠቃሚ ሆኗል? በተለይ ከመቼ ጀምሮ?

5 ኢየሱስ ክርስቶስ (የአምላክ ታላቅ ሊቀ ካህናት በመሆን) የመሥዋዕቱን ዋጋ በሰማይ በአምላክ ፊት ባቀረበ ጊዜ የመሥዋዕቱ ጥቅሞች ወዲያው የሰውን ሕይወት መንካት ጀመሩ። በመጀመሪያ ከክርስቶስ ጋር ወራሾች ለመሆን የተጠሩት፣ ከእርሱም ጋር በሰማይ ነገሥታትና ካህናት ሆነው የሚያገለግሉት በ33 እዘአ ከዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት ጀምሮ እነዚህን ጥቅሞች ማግኘት ጀመሩ። (ሥራ 2:32, 33፤ ቆላስይስ 1:13, 14) ከዚያም በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላቸው ሰዎች በተለይ ከ1935 ጀምሮ ወደ መድረኩ ብቅ አሉ። የእነርሱም ተስፋ ሊገኝ የቻለው በክርስቶስ መሥዋዕት አማካኝነት ነው። (1 ዮሐንስ 2:1, 2) በጥንቷ እስራኤል በስርየት ቀን ይከናወኑ የነበሩት ነገሮች የመሥዋዕቱ ዋጋ በዚሁ መንገድ ደረጃ በደረጃ ጥቅም ላይ እንደሚውል ይጠቁሙ ነበር።

6. በስርየት ቀን ምን ይከናወን እንደነበር በአጭሩ ግለጽ።

6 በቅዱሱ የእስራኤል የመገናኛ ድንኳን፣ በኋላም በቤተ መቅደሱ ውስጥ ዋነኛ ባለሥልጣን ሆኖ የሚያገለግለው ከሌዊ ነገድ፣ ከአሮን ቤት የሆነ ሊቀ ካህን ነበር። የአሮን ዘር የሆኑት ሌሎቹ ወንዶች የበታች ካህናት ሲሆኑ የሌዊ ነገድ ተወላጅ የሆኑት ወንዶች ደግሞ በሥራ ያግዙ ነበር። ኃጢአት ለማስተሰረይ ሊቀ ካህኑ ሁለት እንስሳት ይሠዋል፤ በኋላም የእያንዳንዱ እንስሳ ደም ይሖዋ በሰጠው መመሪያ መሠረት ለየብቻው በቅድስተ ቅዱሳኑ ይቀርባል። በመጀመሪያ የአሮን ተወላጅ የሆነው ሊቀ ካህን “ለራሱም ለቤተ ሰቡም” [ጠቅላላውን የሌዊ ነገድ ይጨምራል] የወይፈን መሥዋዕት ያቀርብ ነበር። (ዘሌዋውያን 16:11, 14) ቀጥሎም ‘ለሕዝቡ’ ይኸውም ለቀሪዎቹ አሥራ ሁለት ነገዶች አንድ ፍየል የኃጢአት መሥዋዕት ሆኖ ይቀርባል። (ዘሌዋውያን 16:15) በተጨማሪም ሊቀ ካህናቱ የእስራኤልን ኃጢአት ሁሉ ሕያው በሆነ ሌላ ፍየል ራስ ላይ ከተናዘዘ በኋላ ፍየሉ ወደ ምድረ በዳ ተወስዶ ይለቀቅ ነበር። (ዘሌዋውያን 16:21, 22) ይህ ሁሉ ምን ትርጉም ነበረው?

7. (ሀ) በዚህ ላይ የተከናወነው ነገር ለየትኛው አንድ መሥዋዕት ጥላ ይሆናል? (ለ) ከአንድ በላይ እንስሳት መሥዋዕት ሆነው እንዲቀርቡ ያስፈለገው ለምን ነበር?

7 ሐዋርያው ጳውሎስ የዚህ ሁሉ ፍጻሜ በአንዱ የኢየሱስ ክርስቶስ መሥዋዕት ላይ የሚያተኩር መሆኑን ገልጿል። “ክርስቶስ በእጅ ወደ ተሠራች፣ የእውነተኛይቱ ምሳሌ ወደምትሆን ቅድስት አልገባምና፣ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ አሁን ይታይ ዘንድ ወደ እርስዋ ወደ ሰማይ ገባ። . . . ራሱን በመሠዋት ኃጢአትን ሊሽር አንድ ጊዜ ተገልጦአል።” (ዕብራውያን 9:24–26) ታዲያ በእስራኤል የስርየት ቀን ከአንድ እንስሳ ደም በላይ በቅድስተ ቅዱሳኑ ይቀርብ የነበረው ለምንድን ነው? ይህ የተደረገው የኢየሱስ ፍጹም ሰብዓዊ መሥዋዕት የሚያከናውነውን ነገር የተለያዩ ገጽታዎች ለመጠቆም ነው። ሕያው በሆነ ፍየል ራስ ላይ የሕዝቡን ኃጢአት ተናዞ ፍየሉን በምድረ በዳ መልቀቁ አጉልቶ የሚያሳየው ሌላም ገጽታ ነበር።

8. (ሀ) በስርየት ቀን በቅደም ተከተል የሚከናወኑት ነገሮች ከክርስቶስ መሥዋዕት እነማን በመጀመሪያ እንደሚጠቀሙ ያመለከቱት እንዴት ነው? (ለ) ‘ለሕዝቡ’ የሚቀርበው የኃጢአት መሥዋዕት፣ የኢየሱስ መሥዋዕት እንዴት በሥራ ላይ እንደሚውል ያመለክታል? (ሐ) አንድ ፍየል ወደ ምድረ በዳ ተወስዶ መለቀቁ የምን ተጨማሪ ምሳሌ ነው?

8 ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ በመጀመሪያ የሚወሰደው ለአሮን ቤተሰብ የተሠዋው ወይፈን ደም እንደነበረ ሁሉ፣ የኢየሱስ መሥዋዕት ጥቅሞችም በመጀመሪያ ሥራ ላይ የዋሉት ከክርስቶስ ጋር በሰማያዊ ክህነት ለሚካፈሉት ሰዎች ጥቅም ነው። ይህም ከ33 እዘአ ጀምሮ በሥራ ላይ ውሏል። ኢየሱስ ክርስቶስ ምንም ኃጢአት ስላልነበረው እንደ አሮን የኃጢአት ሥርየት አላስፈለገውም። የእርሱ የበታች ካህናት ሆነው የሚያገለግሉት ግን የኃጢአት ሥርየት ያስፈልጋቸዋል። የሌዊ ነገድ የእነርሱ አምሳያ ነበር። (1 ጴጥሮስ 2:4, 5) ለመሥዋዕትነት ከተዘጋጀው ከሁለተኛው ፍየል የተወሰደው ደም ስለ “ሕዝቡ” መቅረቡ ከሰማያዊ ክፍል ቀጥሎ ሌሎች የሰው ዘሮችም የኢየሱስ መሥዋዕት ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ያመለክታል። እነርሱም ምድር እንደገና ገነት ስትሆን ሕይወት የሚያገኙ ሰዎች ናቸው። ከክህነቱ ውጭ የነበሩት “አሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች” በስርየት ቀን ከነበራቸው ሁኔታ አኳያ የእነዚህ ሰዎች አምሳያ ነበሩ። (ማቴዎስ 19:28፤ መዝሙር 37:29) ኢየሱስ ስለ እነዚህ ሁሉ ከመሞቱም በተጨማሪ መሥዋዕት ሆኖ የሞተላቸውን ሰዎች ሁሉ ኃጢአት በመሸከም ያሳርፋቸዋል። በመጨረሻ የእስራኤል ኃጢአት በሕያው ፍየል ራስ ላይ ከተነበነበ በኋላ ፍየሉ ዳግም ላይታይ ወደ ምድረ በዳ ተወስዶ መለቀቁ ይህን ያመለክታል። — መዝሙር 103:12፤ ኢሳይያስ 53:4–6

9. (ሀ) በክርስቶስ መሥዋዕት የሚያምኑ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ ምን አስደሳች በረከቶች አግኝተዋል? (ለ) ወደፊትስ ምን ተጨማሪ ጥቅሞች ይመጣሉ?

9 ይሖዋ በክርስቶስ አማካኝነት ባደረገው ፍቅራዊ ዝግጅት ላይ እምነት ያላቸው ሁሉ በአሁኑ ጊዜ እውነተኛ የኃጢአት ይቅርታና በአምላክ ፊት ንጹሕ አቋም ለማግኘት ይችላሉ። ፊተኛው አኗኗራቸው ምንም ዓይነት ቢሆን ይህን ከማግኘት አያግዳቸውም። ንጹሕ ሕሊና ይዘው አምላክን በማገልገል እጅግ ከፍተኛ በረከት ሊያገኙ ይችላሉ። (1 ቆሮንቶስ 6:9–11፤ ዕብራውያን 9:13, 14) እንዲህ ሲባል ግን በአሁኑ ጊዜ ኃጢአት ካስከተላቸው ውጤቶች ሁሉ ነፃ የሆነ ሕይወት ይኖራቸዋል ማለት አይደለም። (1 ዮሐንስ 1:8–10፤ ሮሜ 7:21–25) ከክርስቶስ ጋር በሰማይ ገዥ የሚሆኑት ሰዎች እንደዚህ ያለውን ሕይወት የሚያገኙት ምድራዊ ጉዞአቸውን ከፈጸሙ በኋላ እስከ መቼም የማይጠፋ ሕይወት ለብሰው ከሞት ሲነሱና ወደ ሰማይ ሲሄዱ ብቻ ነው። ሌሎቹ የሰው ዘሮች ከኃጢአት ሙሉ በሙሉ የሚላቀቁት በዳግም መፈጠር ጊዜ ይሆናል።

“በዳግም መፈጠር ጊዜ”

10. (ሀ) ዳግም መፈጠር የጀመረው መቼ ነው? (ለ) ኢየሱስ የገባው ቃል ይፈጸም ዘንድ ዙፋን የተሰጣቸው ሰዎች አሉን?

10 ኢየሱስ እንደተናገረው ዳግም መፈጠር የሚካሄደው “የሰው ልጅ [ኢየሱስ ክርስቶስ] በክብሩ ዙፋን በሚቀመጥበት ጊዜ” ነው። (ማቴዎስ 19:28) እርግጥ ነው፣ እርሱ ዙፋኑ ላይ እንደተቀመጠ ወዲያው ሁሉም ነገር አልተፈጸመም። በ1914 እዘአ ኢየሱስ ከነገሠ በኋላ ሰይጣንንና አጋንንቱን ከሰማይ በማባረር በመጀመሪያ ሰማይን አጸዳ። ከዚያ በኋላ ቅቡዓን ተከታዮቹን ከሞት በማስነሳት ወደ ሰማያዊ ክብር መውሰድ ጀመረ። (ራእይ 12:5, 7–12፤ 1 ተሰሎንቄ 4:15–17) የታመኑት የክርስቶስ ሐዋርያት እርሱ ቃል የገባላቸውን “አሥራ ሁለት ዙፋኖች” ከማግኘታቸውም ሌላ የቀሩት 144,000ዎች በሙሉ ከሙታን እየተነሱ ደረጃ በደረጃ በሰማይ ዙፋናቸውን እንዲይዙ እየተደረገ ነው። — ራእይ 3:21

11. “ሌሎች በጎች” የዳግም መፈጠሩ ውጤቶች አሁንም እየተሰሟቸው ያለው በምን መንገድ ነው?

11 የሰማያዊ ክፍል አባላት የሚሆኑትን የመምረጡ ሂደት ሲያበቃ፣ ‘የሌሎች በጎች’ ክፍል የሆኑ እጅግ ብዙ ሰዎች በተለይ ከ1935 ወዲህ በመሰብሰብ ላይ ናቸው። ‘ልብሳቸውን በበጉ ደም አጥበው ነጭ በማድረግ’ እነርሱም ጭምር ከክርስቶስ መሥዋዕታዊ ጥቅሞች ተካፋይ ሆነዋል። “በእውነተኛ ጽድቅና ታማኝነት እንደ አምላክ ፈቃድ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው” እንዲለብሱ እገዛ እየተደረገላቸው ነው። (ራእይ 7:9, 10, 14፤ ኤፌሶን 4:20–24 አዓት) ቁጥራቸው በየጊዜው እየጨመረ ሲሆን አምላክ በክርስቶስ በኩል ያደረገው ዝግጅት ተጠቃሚ በመሆን ምድር እንደገና ገነት ስትሆን በእርስዋ ላይ ለዘላለም ወደመኖር ሊያደርሳቸው ይችላል። — ራእይ 7:17፤ 22:17

12. (ሀ) ኢየሱስ እዚህ ላይ የጠቀሳቸው “አሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች” ለእነማን ምሳሌ ሆነው የቆሙ ናቸው? (ለ) ከጥፋቱ ተራፊዎች በተጨማሪ ከዳግም መፈጠሩ የሚጠቀሙት እነማን ናቸው?

12 ክፉው ዓለም በቅርብ ጊዜ ይደመሰሳል። ሰይጣንና አጋንንቱ ወደ ጥልቁ ይጣላሉ። የሰው ዘር የሚዳኝበት የሺህ ዓመት ጊዜ ይጀምራል። ኢየሱስ ክርስቶስ ዋነኛው ፈራጅ ይሆናል። እርሱም ሁሉ ሰው የይሖዋን የጽድቅ መንገዶች እንዲማርና አካሄዱን ከእነዚህ መንገዶች ጋር ለማስማማት በቂ እገዛ እንዲያገኝ ያደርጋል። አቋማቸውን እስከ ሞት ድረስ ሳያጐድፉ በንጽሕና የጠበቁ የክርስቶስ ቅቡዓን ተከታዮች ‘በአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ላይ በመፍረዱ’ ሥራ ከእርሱ ጋር ተካፋይ ይሆናሉ። (ሉቃስ 22:28–30፤ ራእይ 20:4, 6) ይህ ማለት ግን በሥጋዊ የእስራኤል ዘሮች ላይ ብቻ ይፈርዳሉ ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ከክህነት ውጭ የነበሩት “አሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች” በሥርየት ቀን ከነበራቸው ሁኔታ አኳያ ምሳሌ የሆኑላቸው የሰው ልጆች ሁሉ በእነርሱ ይዳኛሉ። ይህም የተቤዡትን የሰው ልጆች በሙሉ ይጨምራል። (1 ቆሮንቶስ 6:2) የሰውን ዘር አቋም ከፍ ለማድረግ ከሚዘረጋው ከዚህ ፕሮግራም በመጀመሪያ ተጠቃሚ የሚሆኑት የታላቁ መከራ ተራፊዎች ይሆናሉ። ይሁን እንጂ በቢልዮን የሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎችም ተካፋይ ይሆናሉ፤ ምክንያቱም ‘ሕያዋንና ሙታን’ ለፍርድ ይቀርባሉ ተብሏል። (2 ጢሞቴዎስ 4:1፤ ሥራ 24:15) ኃጢአታቸው በክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት የሚሰረይላቸው ሙታን ተመልሰው ሲመጡ እንዴት የሚያስደስት ይሆናል! የሚዋደዱ ቤተሰቦች እንደገና ሲገናኙ ፊታቸው በደስታ እንባ ምን ያህል ይርስ ይሆን!

13. የሺው ዓመት የፍርድ ቀን የሚያመጣቸው ውጤቶች በእርግጥ ዳግም መፈጠር ማለት የሚሆኑት እንዴት ነው?

13 ይህ ጊዜ የሰው ልጆች፣ ኃጢአት ካስከተላቸው የአካልና የአእምሮ ቀውሶች ለመላቀቅ ለብዙ ዘመናት በናፍቆት ሲጠብቁት የነበረው ጊዜ ይሆናል። ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ሽባዎችን፣ ዓይነ ስውራንን፣ መስማት የተሳናቸውን፣ ዲዳዎችን፣ የአካላቸው ቅርጽ የተበላሸባቸውንና በሽታ ያመነመናቸውን ፈውሷል። እነዚህ ድንቅ ሥራዎች በሺህ ዓመት ግዛቱ ወቅት ኢየሱስ ለሁሉም የሰው ልጅ ለሚያደርጋቸው ነገሮች የቅድሚያ ቅምሻ ብቻ ናቸው። ማንም ሰው እንዲህ ያሉትን የይሖዋ ደግነት አስደናቂ መግለጫዎች በሌሎች ወይም በራሱ ላይ ሲፈጸሙ ካየ በኋላ የይሖዋን ሉዓላዊነት ቢያቃልል ለዘላለም ይደመሰሳል። ለሚወሰደው እርምጃ ጥሩ ምክንያት ይኖራል። ልባዊ እምነትና ታዛዥነት የሚያሳዩ ሁሉ ስለ ይሖዋ የጽድቅ መንገዶች ትምህርት ሲሰጣቸው አስተሳሰባቸውና የልባቸው ዓላማ በየጊዜው እየተሻሻለ ሄዶ ሙሉ ፍጽምና ላይ ይደርሳሉ። እንደነዚህ ያሉት ይሖዋን የሚወዱ ሰዎች በእውነት ዳግም ይወለዳሉ፤ ዳግም ይፈጠራሉ። የዘላለም አባት የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ አዲስ አባት ሆኖላቸው አዲስ ሕይወት፣ አዲስ ጅምር እንዳገኙ ያህል ይሆናል። — ኢሳይያስ 26:9፤ 9:6

14. የመጨረሻውን ፈተና የሚያልፉት ሁሉ የትኛውን ውድ ዝምድና የማግኘት ልዩ መብት ይኖራቸዋል?

14 ከዚያም በሺው ዓመት ፍጻሜ ላይ የመጨረሻውን ፈተና ካለፉ በኋላ ይሖዋ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የራሱ ልጆችና የፍጹሙ አጽናፈ ዓለማዊ ቤተሰቡ ክፍል አድርጎ ይቀበላቸዋል። ለታላቁ መከራ ተራፊዎች ብቻ ሳይሆን ገነት በምትሆነው ምድር ላይ አስደሳች ሕይወት ለማግኘት ከሞት ለሚነሱትም ጭምር ይህ እንዴት ያለ የሚያጽናና ተስፋ ነው! — ሮሜ 8:20, 21

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]