በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ፕላኔቷ ምድራችን ወደፊት ምን ትሆናለች?

ፕላኔቷ ምድራችን ወደፊት ምን ትሆናለች?

ምዕራፍ 1

ፕላኔቷ ምድራችን ወደፊት ምን ትሆናለች?

1. የወደፊቱ ጊዜ ምን ዓይነት ይሆናል ብለህ ታስባለህ? ለምንስ?

በአሁኑ ጊዜ በፕላኔቷ ምድር ላይ ከሚኖሩት በቢልዮን ከሚቆጠሩት ሰዎች አንዱ እንደመሆንህ የወደፊቱ ጊዜ ለአንተ ምን ይዞልሃል? እርስ በርስ ከልብ በሚዋደዱ ሰዎች መካከል እየኖርክ ሰላምና ደኅንነት የምታገኝበት ጊዜ እንዲሆንልህ ትፈልጋለህን? ይህንና ከዚህ የበለጡ ሌሎች ነገሮችን ልታገኝ ትችላለህ። ሆኖም አብዛኞቹ ሰዎች የወደፊቱ ጊዜ እንደዚያ ይሆንልናል ብለው አይጠብቁም። ለምን ይሆን?

2, 3. የኑክሌር ጦርነት ይነሳ ይሆናል የሚለው ስጋት ብዙ ሰዎች ስለ ወደፊቱ ጊዜ ያላቸውን አመለካከት የነካው እንዴት ነው?

2 የኑክሌር ጦርነት ይነሳ ይሆናል የሚለው ስጋት አብዛኛው የሰው ዘር ወደፊት በሕይወት የመኖሩን ጉዳይ ከባድ ጥርጣሬ ላይ ጥሎታል። የአቶም ቦምብ ለመጀመሪያ ጊዜ በ1945 በውጊያ ላይ እንዲውል ሲደረግ ከ70,000 የሚበልጡ ወንዶች፣ ሴቶችና ሕፃናት በቅጽበት እንደ ቅጠል ረግፈዋል። በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎችም በተከታዮቹ ቀኖችና ዓመታት በከባድ ሰቆቃ ሞተዋል። ዛሬ ግን አንዱ የኑክሌር መሣሪያ ብቻ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የተጣሉት ቦምቦች ሁሉ ተዳምረው ከሚያስከትሉት ጉዳት የሚበልጥ የፍንዳታ ኃይል አለው። በቅጽበት ሊተኮሱ የሚችሉ በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠሩ የኑክሌር መሣሪያዎች ተጠምደዋል። ያም ሆኖ ግን ዓለም አሁንም በአንዳንድ ዓመታት ለመሣሪያ እሽቅድምድም በቀን ከ2, 000, 000, 000 የአሜሪካ ዶላር በላይ ታጠፋለች። ብዙ ሰዎች ይህ ይዘገንናቸዋል።

3 ይሁን እንጂ “በተወሰነ አካባቢ ብቻ የኑክሌር ውጊያ” ቢካሄድስ? ውጤቱ አሁንም የሚዘገንን ነው። ካርል ሳጋን የተባሉ አንድ እውቅ ሳይንቲስት በገለጹት መሠረት መንግሥታት ካላቸው የኑክሌር ኃይል ውስጥ በጣም ትንሹን ብቻ እንኳ ቢጠቀሙበት “የዓለማችን ሥልጣኔ ሙሉ በሙሉ እንደሚንኮታኮት ምንም አያጠያይቅም። . . . እንዲያውም የሰው ዘር ጨርሶ መደምሰሱ እርግጠኛ ነገር ይመስላል።” ብዙ ሰዎች እንደዚህ ያለ ነገር ይሆናል ብለው ላለማሰብ ይፈልጋሉ። ይሁን እንጂ ይህ ምኞታቸው የአደጋውን ሥጋት አይቀንሰውም። በርካታ የእልቂት ተራፊዎች ማኅበራት የተቋቋሙ ሲሆን አባላቱም በፍጥነት እየተበራከቱ ነው። ጥቂት ሰዎች በሕይወት ቢተርፉ በሚል ተስፋ በገለልተኛ ስፍራዎች መጠለያዎችን ሠርተዋል፤ በውስጣቸውም ምግብንና መድኃኒቶችን፣ እንዲሁም የማይፈለጉ ሰዎችን ለማባረር የሚያገለግሉ ጠመንጃዎችን እንኳን አከማችተዋል።

4. የአካባቢ ብክለት በጣም አስጊ ሁኔታ ተደርጎ የሚታየው ለምንድን ነው?

4 ከኑክሌር ጦርነትም ሌላ በአካባቢ ብክለት ምክንያት ምድር አቀፍ እልቂት ሊደርስ እንደሚችል ሳይንቲስቶች ያስጠነቅቃሉ። የምንተነፍሰው አየር መበከሉ አንዱ አሳሳቢ ጉዳይ ነው። ደኖች በሚያስደነግጥ ፍጥነት እየተጨፈጨፉ ናቸው፤ እነዚህ ደኖች ግን ለምድር የኦክስጅንና የዝናብ ዑደት እንዲሁም ለአፈር ጥበቃ በጣም አስፈላጊ ናቸው። በእውቀት ማነስና በራስ ወዳድነት ሳቢያ እጅግ አስፈላጊ የሆኑ የእርሻ መሬቶች ከጥቅም ውጭ እየሆኑ ነው። የውኃ ምንጮች በአብዛኛው መርዘኛ በሆኑ ኬሚካሎች እየተበከሉ ነው። ነገር ግን እነዚህ የተፈጥሮ ሀብቶች ለሰው ሕይወት የግድ አስፈላጊ ናቸው።

5, 6. የወደፊቱ ጊዜ የሰው ደኅንነት አስተማማኝ የሚሆንበትና ደስታ የሰፈነበት ይሆናል ብለው ሰዎች እንዳይጠብቁ የተጋረጡባቸው ሌሎች ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?

5 ከሁሉም ይበልጥ አሳሳቢ ሆኖ የሚታይህ፣ ዓመፅ ሰዎችን በገዛ ቤታቸው እስረኛ አድርጎ ማስቀመጡ ይሆናል። ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ብጥብጥ የሰውን ሕይወት አደጋ ላይ ጥሎታል። እየተስፋፋ የሄደው ሥራ አጥነትና የገንዘብ ዋጋ ግሽበት ድኅነትና ብስጭት አስከትሏል። የብዙ ሰዎች የቤተሰብ ኑሮ ፈጽሞ የማያረካ ነው። ቤተሰብን አንድ ማድረግ ይችል የነበረው የፍቅር ማሰሪያ በአብዛኛው ቦታ የለም። በየትም ቦታ ያለው የሰዎች ዝንባሌ “ከሁሉ በፊት ለእኔ!” የሚል ነው።

6 ታዲያ አንድ ሰው የመኖር ዋስትና አለኝ በማለት ደፍሮ ለመናገር የሚያበቃው ነገር የት ሊያገኝ ይችላል? ወደፊት በምድር ላይ መኖራችን የተመካው ለእነዚህ ችግሮች መፈጠር ምክንያት የሆኑት ሰዎችና መንግሥታት በሚፈቅዱትና በሚያደርጉት ነገር ላይ ቢሆን ኖሮ ተስፋው ይጨልምብን ነበር። ይሁን እንጂ ሁኔታው እንደዚያ ነውን?

ሊዘነጉ የማይገባቸው ሐቆች

7. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል ለመሆኑ ምን ማስረጃ አለ? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል ሰዎች ማወቃቸው በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

7 ሰዎች ወደፊት ምን እንደሚመጣ አስተያየት ሲሰነዝሩ ብዙውን ጊዜ የምድርንና የሰውን ዘር ፈጣሪ ይዘነጉታል። ይሁንና የእርሱ ዓላማ ምን እንደሆነ እንዴት ለማወቅ እንችላለን? መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። ይህ መጽሐፍ በውስጡ የሰፈረው ሐሳብ ሁሉ መለኮታዊ ምንጭ እንዳለው፣ ማለትም በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት እንደተጻፈ ደጋግሞ ይናገራል። ይህ አባባል እውነት ነውን? እውነት ከሆነ ሕይወትህ የተመካው መጽሐፍ ቅዱስ የሚልህን በመከተልህ ላይ ነው ማለት ነው። ይህ አንገብጋቢ ጉዳይ በመሆኑ መጽሐፍ ቅዱስን በግልህ እንድትመረምረው አጥብቀን እንመክርሃለን። ተወዳዳሪ የሌለው እውቀት የሚሰጡት የወደፊቱን ሁኔታ በዝርዝር የሚገልጹት ብዙዎቹ ትንቢቶች ጎልተው ይታዩሃል። መጽሐፍ ቅዱስ ለዘላቂ ደስታህ የሚጠቅሙህን ጉዳዮች ሲያብራራ ወደር የማይገኝለት ጥበብ ያለው ሆኖ ታገኘዋለህ። አእምሮህን ሰፋ አድርገህ ማስረጃውን ከመረመርከው መጽሐፍ ቅዱስ ከሰው የበለጠ ኃይል ካለው ምንጭ ይኸውም ሰዎችን በእርግጥ ከሚያፈቅር ፈጣሪ የመጣ መሆኑን እንደምትገነዘብ እርግጠኞች ነን። * በሰው ታሪክ ውስጥ በአደገኛነቱ ተወዳዳሪ በሌለው በዚህ ጊዜ ሕይወታችንን ለማትረፍ ምን ማድረግ እንዳለብን የሚገልጹትን መመሪያዎች መጽሐፍ ቅዱስ ይዟል። ስለዚህ ከየትኛውም መጽሐፍ ይበልጥ በምድር ላይ መሰራጨቱ የተገባ ነው። — 2 ጴጥሮስ 1:20, 21​ን፣ 3:11–14​ንና 2 ጢሞቴዎስ 3:1–5, 14–17​ን ተመልከት።

8. መጽሐፍ ቅዱስ የፕላኔታችንን ፈጣሪ በምን ስም ይጠራዋል?

8 የመጽሐፍ ቅዱስ የመክፈቻ ጥቅስ “እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ” የሚለውን መሠረታዊ ሐቅ ያስቀምጣል። (ዘፍጥረት 1:1) * አንዳንድ ሰዎች አምላክን ያለ ስም ለማስቀረት ቢመርጡም መጽሐፍ ቅዱስ እንደዚያ አያደርግም። ዘፍጥረት 2:4 (አዓት) ፈጣሪያችን ማን መሆኑን በስም ሲገልጽ “ይሖዋ አምላክ ሰማይንና ምድርን ፈጠረ” ይላል። (በተጨማሪም ዘፍጥረት 14:22 አዓት፤ ዘጸአት 6:3 የ1879 እትም፤ 20:11 አዓት ተመልከት።) አብዛኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በመጀመሪያ የተጻፈው በዕብራይስጥ ቋንቋ ሲሆን በዕብራይስጡ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የአምላክ የግል ስም 7,000 ጊዜ ያህል እንደ ቅዱስ በሚቆጠሩ አራት ፊደላት (יהוה) ተጽፎ ይገኛል። አንዳንድ ተርጓሚዎች ስሙን ያህዌህ ብለው ሲጽፉት በእንግሊዝኛ በይበልጥ የታወቀው አጠራር ግን ጅሆቫ፣ በአማርኛም ይሖዋ ነው።

9. (ሀ) ይህ የአምላክ ስም ከየት የተገኘ ነው? (ለ) የአምላክ ስም ለእኛ የቱን ያህል አስፈላጊ ነው? (ኢዩኤል 2:32፤ ሚክያስ 4:5)

9 ይህ ስም ለአምላክ ባደሩ ሰዎች የተፈለሰፈ አይደለም። ፈጣሪ ራሱ የመረጠው ስም ነው። (ዘጸአት 3:13–15፤ ኢሳይያስ 42:8 አዓት) ስሙ ቡድሃ፣ ብራህማ፣ አላህ ወይም ኢየሱስ ከሚሉት ስሞች ጋር በአማራጭነት የሚሠራበት ስም አይደለም። ነቢዩ ሙሴ ለጥንቱ የእስራኤል ሕዝብ “እንግዲህ እግዚአብሔር [“ይሖዋ” አዓት፣ በዕብራይስጥ “יהוה”] በላይ በሰማይ በታችም በምድር አምላክ እንደ ሆነ፣ ሌላም እንደሌለ ዛሬ እወቅ፣ በልብህም ያዝ” በማለት ተገቢ ማሳሰቢያ ሰጥቷል። (ዘዳግም 4:39) ኢየሱስ ክርስቶስ የጸለየው ወደዚህ አምላክ ነው፤ “ብቻህን እውነተኛ አምላክ የሆንከው” በማለት የጠራውም ይህን አምላክ ነው። በዛሬው ጊዜ ትክክለኛ እውቀት አግኝተው እርሱን የሚያመልኩ ከሕዝብ ሁሉ የተውጣጡ ሰዎች አሉ። — ዮሐንስ 17:3 የ1980 ትርጉም፤ ማቴዎስ 4:8–10፤ 26:39፤ ሮሜ 3:29

10. የኑክሌር ጦርነትና የአካባቢ ብክለት ስጋት አምላክ ለምድር ያለውን ዓላማ ለምን አያደናቅፈውም?

10 ይሖዋ የምድር ፈጣሪ በመሆኑ መላዋ ፕላኔት የእርሱ ንብረት ናት፤ ወደፊት ምን እንደምትሆን መወሰንም በእጁ ላይ ያለ ነገር ነው። (ዘዳግም 10:14፤ መዝሙር 89:11) የሰው ዘር ችግሮች አምላክ ሊፈታቸው የማይችሉ አይደሉም። የኑክሌር ጦርነት ሊነሳ የሚችል መሆኑ ሰዎችን በጣም ያስጨንቃል። ይሁን እንጂ ስፍር ቁጥር በሌላቸው ከዋክብት ውስጥ ለግምት በሚያዳግት መጠን የሚካሄዱትን የኑክሌር ፍንዳታዎች የሚቆጣጠሩት የማን ሕጎች ናቸው? አምላክ በፕላኔቷ ምድር ላይ ያለውን ሕይወት ለመጠበቅ እውቀቱም ሆነ ኃይሉ የለውምን? በተመሳሳይም ሰዎች በእውቀት ማነስና በራስ ወዳድነት ምክንያት አካባቢያቸውን መበከላቸው ያስከተለው መዘዝ ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ ዓላማ አያጨናግፍም። ምድርንና በእርሷ ላይ ያሉትን ልዩ ልዩ ሕያዋን ነገሮች ለመፍጠር አስፈላጊው ጥበብና ኃይል የነበረው አምላክ የእርሱ ፈቃድ ከሆነ ለፍጡሮቹ ሁሉንም ነገር እንደገና ንጹሕ አድርጎ ሊያስጀምርላቸው ይችላል። (ኢሳይያስ 40:26፤ መዝሙር 104:24) ታዲያ ፕላኔቷ መኖሪያችንን በተመለከተ የይሖዋ ዓላማ ምንድን ነው?

ምድር ለምን ያህል ጊዜ ትኖራለች?

11. (ሀ) አንዳንድ ሳይንቲስቶች መሬት በመጨረሻው ምን ትሆናለች ብለው ያምናሉ? (ለ) ስለነዚህ ጉዳዮች ከእነርሱ ይበልጥ የሚያውቀው ማን ነው? ለምንስ?

11 አምላክ ምድርንና በላይዋ የሚገኙትን ሕያዋን ፍጥረታት ለማጥፋት ዓላማ አለውን? አንዳንድ የከዋክብት ተመራማሪዎች ፀሐያችን ወደፊት በፍንዳታ ትሰፋና ምድራችንን ትውጣለች የሚል ንድፈ ሐሳብ አላቸው። ግዑዙ አጽናፈ ዓለም ካለው ተፈጥሯዊ ባሕርይ የተነሳ ፀሐይ ማብራቷን የምታቆምበት ምድርም ሕይወትን ማኖር የማትችልበት ጊዜ ይመጣል ብለው የሚናገሩ ሌሎችም አሉ። ይሁን እንጂ ትክክል ናቸውን? ኃይልንና ቁስ አካልን ወደ መኖር ያመጣና የሕይወታችን መሠረት የሆኑትን ሕጎች ያመነጨው ፈጣሪ ምን ያላል? — ኢዮብ 38:1–6, 21፤ መዝሙር 146:3–6

12. የመክብብ 1:4 ቃላት ትክክል እንደሆኑ የተረጋገጠው እንዴት ነው?

12 ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን የሰው ዕድሜ ርዝማኔ ምድር ከምትኖርበት ዘመን ጋር ሲነጻጸር ምን ያህል እንደሆነ እንዲጽፍ ይሖዋ በመንፈስ መርቶታል። ሰሎሞን በመክብብ 1:4 “ትውልድ ይሄዳል፣ ትውልድም ይመጣል፤ ምድር ግን ለዘላለም [“ላልተወሰነ ጊዜ” አዓት ] ነው” በማለት ጽፏል። ለዚህ አባባል እውነተኛነት የሰው ታሪክ ይመሰክራል። አንዱ ትውልድ አልፎ በሌላው ቢተካም የምንኖርባት ምድር አለች። ግን ለምን ያህል ጊዜ ትኖራለች? የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ጥቅሱን ቃል በቃል ተርጉሞ ባስቀመጠው መሠረት “ላልተወሰነ ጊዜ” ትኖራለች። ይህ ምን ማለት ነው?

13. (ሀ) “ላልተወሰነ ጊዜ” ሲባል ምን ማለት ሊሆን ይችላል? (ለ) ታዲያ ምድር ለዘላለም ጸንታ እንደምትኖር እንዴት እርግጠኞች ለመሆን እንችላለን?

13 እዚህ ላይ በአዲሲቱ ዓለም ትርጉም “ላልተወሰነ ጊዜ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል ኦህላም ሲሆን በመሠረቱ አሁን ካለው ጊዜ አንጻር ሲታይ ያልተወሰነ ወይም ከዕይታ የተሰወረ ረጅም ዘመንን ያመለክታል። ይህም ዘላለም ማለት ሊሆን ይችላል። ታዲያ እዚህ ጥቅስ ላይ እንደዚያ ማለት ነውን? ወይስ ይህ አገላለጽ አሁን ለዕይታችን ስውር ከሆነ ያልተወሰነ ጊዜ በኋላ የምድር ፍጻሜ ይሆናል ማለት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “ላልተወሰነ ጊዜ” ይቀጥላሉ ያላቸው አንዳንድ ነገሮች በመጨረሻው ወደ ፍጻሜያቸው ደርሰዋል። (ከዘኁልቁ 25:13 አዓት እና ከዕብራውያን 7:12 ጋር አወዳድር።) ሆኖም ቅዱሳን ጽሑፎች ኦህላም የሚለውን ቃል ዘላለማዊ ከሆኑ ነገሮችም ጋር ያዛምዱታል። ለምሳሌ የፈጣሪን ሁኔታ ለመግለጽ ይጠቀሙበታል። (መዝሙር 90:2⁠ን ከ1 ጢሞቴዎስ 1:17 አዓት ጋር አወዳድር።) ምድርን በተመለከተ ቃሉ በየትኛው ትርጉሙ እንደገባ የሚያጠራጥር ነገር አይደለም። በመዝሙር 104:5 ላይ “ለዘላለም [“ላልተወሰነ ጊዜ” አዓት] እንዳትናወጥ ምድርን በመሠረቷ ላይ መሠረታት” የሚል ቃል ተጽፎልናል። * (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) — በተጨማሪም መዝሙር 119:90⁠ን ተመልከት።

14. ሉል የሆነችው መኖሪያችን አንድ ቀን ኦና እንደማትሆን እንዴት እናውቃለን?

14 ለዘላለም የምትኖረው ፍሬ የማትሰጥ ባድማ የሆነች ሉል አይደለችም። በኤርምያስ 10:10–12 (አዓት ) ላይ “ይሖዋ ግን እውነተኛ አምላክ ነው። . . . ምድርን በኃይሉ የሠራ ፍሬ የምትሰጠውን ምድር በጥበቡ አጽንቶ የመሠረተ ሰማያትንም በማስተዋሉ የዘረጋ እርሱ ነው” ተብሎ ተገልጿል። ጥቅሱ አምላክ “ምድርን” እንደሠራት ብቻ ሳይሆን ፍሬ የምትሰጠውን ምድር አጽንቶ እንደመሠረተ መናገሩን አስተውል። “ፍሬ የምትሰጠውን ምድር” በሚለው ሐረግ ቦታ ብዙ ተርጓሚዎች ቴቬል የሚለውን የዕብራይስጥ ቃል “ዓለም” ብቻ በማለት ተርጉመውታል። ይሁን እንጂ በዊልያም ዊልሰን የተዘጋጀው ኦልድ ቴስታመንት ወርድ ስተዲስ (የብሉይ ኪዳን ቃላት ጥናት) የተሰኘው መጽሐፍ በተናገረው መሠረት ቴቬል ማለት “ምድር፣ ለምና የሰው መኖሪያ የሆነው ክፍል፣ የሰው መኖሪያ ሊሆን የሚችለውን መሬት፣ ዓለም” ማለት ነው። ይሖዋ ለዚች ለምና መኖሪያ ለሆነችው ምድር ስላለው ዓላማ ሲናገር መዝሙር 96:10 (አዓት ) “ይሖዋ ነገሠ ፍሬ የምትሰጠዋንም ምድር እንዳትናወጥ አጥብቆ መሠረታት” በማለት ያረጋግጥልናል። — በተጨማሪም ኢሳይያስ 45:18⁠ን ተመልከት።

15. እነዚህ ሐቆች ኢየሱስ ለተከታዮቹ ካስተማረው ጸሎት ጋር የሚስማሙት እንዴት ነው?

15 ይህም በመሆኑ ኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮቹ “መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን ” ብለው እንዲጸልዩ ባስተማራቸው ጊዜ አሁን ስለምንኖርባት ፕላኔት፣ ስለ ምድር መናገሩ ነበር። — ማቴዎስ 6:9, 10፤ ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።

16. (ሀ) በዚያን ጊዜ በምድር ላይ ምን ዓይነት ሰዎች ይኖራሉ? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገርላት “አዲስ ምድር” ምንድን ነች?

16 ይሖዋ ለምድር ያለው ፈቃድ ስለ ባለቤቷ ምንም ደንታ በሌላቸውና እርስ በርሳቸውም በማይዋደዱ ሰዎች እንድትሞላ አይደለም። ከብዙ ጊዜ በፊት “ክፉ አድራጊዎች ይጠፋሉና፤ እግዚአብሔርን ተስፋ የሚያደርጉ ግን እነርሱ ምድርን ይወርሳሉ። ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፣ በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ” በማለት አምላክ ቃል ገብቷል። (መዝሙር 37:9, 29) መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገርላት ‘ወደፊት የምትመጣዋ ምድር’ አምላክን በሚፈሩና መሰል ሰብዓዊ ፍጡሮችን ከልብ በሚወዱ ሰዎች ትሞላለች። (ዕብራውያን 2:5 አዓት፤ ከሉቃስ 10:25–28 ጋር አወዳድር።) በአምላክ ሰማያዊት መንግሥት ሥር የሚመጡት ለውጦች እጅግ ታላቅ ከመሆናቸው የተነሳ መጽሐፍ ቅዱስ “አዲስ ምድር” ትመጣለች ብሎ ይናገራል። ሌላ ሉል ይፈጠራል ማለቱ ሳይሆን የሰው ልጆች ሠሪ ምድራዊ ፍጥረቱን ሲጀምር አስቦት በነበረው ገነታዊ ሁኔታ ውስጥ የሚኖረውን አዲስ ኅብረተሰብ ማመልከቱ ነው። — ራእይ 21:1–5፤ ዘፍጥረት 2:7–9, 15

17. በሕይወት ለመትረፍ አምላክ ያወጣቸውን መስፈርቶች ማወቃችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

17 ከ“አዲስ ምድር” ምሥረታ በፊት ግን የግድ ታላቅ ጥፋት መምጣት ይኖርበታል። እርሱም የሰው ዘር ዓይቶት የማያውቅ ታላቅ እልቂት ይሆናል። አምላክ ለምድሪቱ በማሰብና ፈጣሪያቸውን ከልብ ለሚያመሰግኑ ሰዎች ደህንነት ሲል ‘ምድርን የሚያጠፉትን ያጠፋል።’ (ራእይ 11:17, 18) አምላክ ይህን የሚያደርግበት ጊዜ በጣም ቅርብ ነው! የጥፋት እርምጃው ካበቃ በኋላ በሕይወት ከሚተርፉት መካከል ትገኝ ይሆን? — 1 ዮሐንስ 2:17፤ ምሳሌ 2:21, 22

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.7 ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና የትራክት ማኅበር የታተመውን መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል ነው ወይስ የሰው? የተባለውን የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ተመልከት።

^ አን.8 ሌላ መግለጫ ካልተሰጠ በስተቀር በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሱት ጥቅሶች ከ1954 የአማርኛ የመጽሐፍ ቅዱስ እትም የተወሰዱ ናቸው። ከጥቅስ ቀጥሎ “አዓት” ሲባል ጥቅሱ የተወሰደው በእንግሊዝኛ ከተዘጋጀው የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም የ1984 እትም መሆኑን ያመለክታል።

^ አን.13 አንዳንድ የመዝገበ ቃላት አዘጋጆች ኦህላም በመክብብ 1:4 አገባቡ ላይ “ለዘላለም” ማለት እንደሆነ አድርገው ይረዱታል። የሚከተሉት የእንግሊዝኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችም በዚያ መንገድ አስቀምጠውታል። ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል፣ ሪቫይዝድ ስታንዳርድ ቨርሽን፣ ዘ ጀሩሳሌም ባይብል፣ ዘ ባይብል ኢን ሊቪንግ ኢንግሊሽ፣ ኪንግ ጄምስ ቨርሽን እና ሌሎች።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ባለ ሙሉ ገጽ ሥዕል]