በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 1

“ሂዱና . . . ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ”

“ሂዱና . . . ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ”

የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ይዘት እንዲሁም ዘገባው በዘመናችን ካለው ሁኔታ ጋር ያለው ተዛማጅነት

1-6. የይሖዋ ምሥክሮች በተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ እንደሚሰብኩ የሚያሳይ ተሞክሮ ተናገር።

 በጋና የምትኖር ሬቤካ የተባለች ወጣት የይሖዋ ምሥክር ትምህርት ቤቷን የአገልግሎት ክልሏ አድርጋ ትመለከተዋለች። በትምህርት ቤት ቦርሳዋ ውስጥ ምንጊዜም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ትይዛለች። በእረፍት ሰዓት አብረዋት ለሚማሩት ልጆች መመሥከር የምትችልበትን አጋጣሚ ትፈልጋለች። በመሆኑም ሬቤካ ከክፍሏ ተማሪዎች ውስጥ አንዳንዶቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲጀምሩ ማድረግ ችላለች።

2 በአፍሪካ ደቡብ ምሥራቃዊ የባሕር ጠረፍ አጠገብ በምትገኘው በማዳጋስካር ደሴት የሚኖሩ ሁለት አቅኚዎች አሉ፤ ሞቃታማ በሆነው የአየር ጠባይ በየጊዜው 25 ኪሎ ሜትር ገደማ በእግራቸው በመጓዝ ራቅ ብሎ ወደሚገኝ መንደር ይሄዳሉ። በዚያም ፍላጎት ያሳዩ በርካታ ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠናሉ።

3 በፓራጓይ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች፣ ከ15 አገሮች ከመጡ ሌሎች ፈቃደኛ አገልጋዮች ጋር በመሆን አንድ ጀልባ ሠሩ፤ ይህን ያደረጉት በፓራጓይና በፓራና ወንዞች ዳርቻ ለሚኖሩ ሰዎች ለመመሥከር ሲሉ ነው። ክብደቷ 45 ቶን የሆነው ይህች ጀልባ 12 ሰዎችን የመያዝ አቅም አላት። ቀናተኛ የሆኑት የመንግሥቱ ሰባኪዎች በዚህች ጀልባ በመጠቀም በሌላ በምንም መንገድ ሊደረስባቸው በማይችሉ አካባቢዎች ምሥራቹን ማዳረስ ችለዋል።

4 በሰሜናዊው ጫፍ በአላስካ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች፣ ጎብኚዎች ወደዚያ በብዛት የሚመጡበትንና ቅዝቃዜው የሚቀንስበትን ወቅት ለመመሥከር የሚያስችል ግሩም አጋጣሚ አድርገው ይመለከቱታል። የተለያየ አገር ዜግነት ያላቸውን ጎብኚዎች የጫኑት መርከቦች ወደ አካባቢያቸው በሚመጡበት ወቅት በዚያ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች በልዩ ልዩ ቋንቋዎች የተዘጋጁ ማራኪ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ይዘው ወደቡ ላይ ይጠብቋቸዋል። በተጨማሪም ወንድሞች ራቅ ብለው ወደሚገኙ መንደሮች ምሥራቹን ለማድረስ አውሮፕላን መጠቀምን ጥሩ አማራጭ ሆኖ አግኝተውታል፤ በዚህ መንገድ ምሥራቹ በአልዩት፣ በአተባስክን፣ በሲምሺየን እና በክሊንግከት ለሚገኙ ማኅበረሰቦች ሊዳረስ ችሏል።

5 በቴክሳስ፣ ዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘው ላሪ ደግሞ ለየት ያለ የአገልግሎት ክልል አለው፤ የሚኖረው በአረጋውያን መንከባከቢያ ማዕከል ውስጥ ሲሆን በዚያ ለሚገኙ ሰዎች ይሰብካል። ላሪ በደረሰበት አደጋ የተነሳ በተሽከርካሪ ወንበር የሚንቀሳቀስ ቢሆንም ሁልጊዜ በአገልግሎት የተጠመደ ነው። የመንግሥቱን መልእክት ለሌሎች ያውጃል፤ ወደፊት የአምላክ መንግሥት በሚገዛበት ጊዜ ዳግመኛ በእግሩ ቆሞ እንደሚሄድ የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋም ይነግራቸዋል።—ኢሳ. 35:5, 6

6 የተወሰኑ የይሖዋ ምሥክሮች በላይኛው ምያንማር በሚደረግ ትልቅ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ከማንዳሌይ ተነስተው በጀልባ የሦስት ቀን መንገድ ተጓዙ። ምሥራቹን ለመስበክ ከፍተኛ ጉጉት ስላላቸው የተለያዩ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ይዘው ነበር፤ ጽሑፎቹን አብረዋቸው ለሚጓዙት ሰዎች አበረከቱላቸው። ጀልባው በአንድ ከተማ ወይም መንደር ላይ በቆመ ቁጥር እነዚህ ቀናተኛ ሰባኪዎች ከጀልባው በመውረድ በፍጥነት ወደ መንደሮቹ ገብተው ጽሑፎች ያበረክቱ ነበር። በዚህ ወቅት ጀልባው አዳዲስ ተሳፋሪዎችን ስለሚጭን አስፋፊዎቹ ከመንደሮቹ ሲመለሱ ጀልባው “አዲስ የአገልግሎት ክልል” ይሆንላቸው ነበር።

7. የይሖዋ አገልጋዮች ስለ አምላክ መንግሥት የሚመሠክሩት በየትኞቹ መንገዶች ነው? ግባቸውስ ምንድን ነው?

7 በእነዚህ ጥቂት ምሳሌዎች ላይ እንደተጠቀሱት ወንድሞችና እህቶች ሁሉ በዓለም ዙሪያ ያሉ ቀናተኛ የይሖዋ አገልጋዮችም “ስለ አምላክ መንግሥት በሚገባ [እየመሠከሩ]” ነው። (ሥራ 28:23) ከቤት ወደ ቤት በመሄድ፣ መንገድ ላይ ሰዎችን በማነጋገር፣ ደብዳቤ በመጻፍና ስልክ በመደወል ይሰብካሉ። በአውቶቡስ ሲጓዙም ሆነ በመናፈሻ ቦታዎች ሲንሸራሸሩ ወይም በሥራ ቦታቸው እረፍት ሰዓት ላይ ሲሆኑ ስለ አምላክ መንግሥት ለመመሥከር የሚያስችሏቸውን አጋጣሚዎች ለማግኘት ጥረት ያደርጋሉ። ለመስበክ የሚጠቀሙበት ዘዴ የተለያየ ቢሆንም ግባቸው አንድ ነው፤ ይኸውም ሰዎች በሚገኙበት ቦታ ሁሉ ምሥራቹን መስበክ ነው።—ማቴ. 10:11

8, 9. (ሀ) የመንግሥቱን ምሥራች የመስበኩ ሥራ እየተስፋፋ መሄዱ እንደ ተአምር ሊቆጠር የሚችለው ለምንድን ነው? (ለ) ምን ጥያቄ ይነሳል? መልሱን ለማግኘትስ ምን ማድረግ ያስፈልገናል?

8 ውድ አንባቢ፣ አንተስ ከ235 በሚበልጡ አገሮች ውስጥ በመስበክ ላይ ከሚገኙት እጅግ ብዙ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች አንዱ ነህ? ከሆንክ ልትደሰት ይገባሃል፤ በአስደናቂ ሁኔታ በመስፋፋት ላይ ለሚገኘው የመንግሥቱ የስብከት ሥራ የበኩልህን ድርሻ እያበረከትክ ነው! በዚህ ረገድ በመላው ዓለም እየተከናወነ ያለው ሥራ እንደ ተአምር የሚቆጠር ነው። መንግሥታት የሚጥሏቸውን እገዳዎች እንዲሁም ቀጥተኛ የሆኑ ስደቶችን ጨምሮ ከባድ እንቅፋቶችና ፈታኝ ሁኔታዎች አሉ፤ ያም ቢሆን የይሖዋ ምሥክሮች ከሁሉም ብሔራት ለተውጣጡ ሰዎች ስለ አምላክ መንግሥት በሚገባ እየመሠከሩ ነው።

9 አሁን የሚነሳው ጥያቄ ይህ ነው፦ ‘ማንኛውም እንቅፋት ሌላው ቀርቶ የሰይጣን ተቃውሞ እንኳ የመንግሥቱን የስብከት ሥራ ሊገታው ያልቻለው ለምንድን ነው?’ የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረውን ሁኔታ መለስ ብለን መቃኘት ያስፈልገናል። ደግሞም በዛሬው ጊዜ ያለነው የይሖዋ ምሥክሮች የምናከናውነው በዚያ ዘመን የተጀመረውን ሥራ ነው።

መጠነ ሰፊ ተልእኮ

10. ኢየሱስ በምን ሥራ ተጠምዶ ነበር? ይህን ሥራ በተመለከተስ ምን የሚያውቀው ነገር ነበር?

10 የክርስቲያን ጉባኤ መሥራች የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ የአምላክን መንግሥት ምሥራች በመስበኩ ሥራ ሙሉ በሙሉ ተጠምዶ ነበር። በአንድ ወቅት ኢየሱስ “ለሌሎች ከተሞችም የአምላክን መንግሥት ምሥራች ማወጅ አለብኝ፤ ምክንያቱም የተላክሁት ለዚህ ዓላማ ነው” ብሎ ነበር። (ሉቃስ 4:43) እርግጥ ነው፣ ኢየሱስ ያስጀመረውን ሥራ እሱ ብቻውን ከፍጻሜው ሊያደርሰው እንደማይችል ያውቅ ነበር። ኢየሱስ ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ የመንግሥቱ መልእክት “ለብሔራት ሁሉ” እንደሚሰበክ ትንቢት ተናግሯል። (ማር. 13:10) ይሁን እንጂ ይህ ሥራ የሚከናወነው እንዴት ነው? የሚያከናውኑትስ እነማን ናቸው?

“ሂዱና . . . ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ።”—ማቴዎስ 28:19

11. ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ምን ከባድ ተልእኮ ሰጥቷቸዋል? ይህን ተልእኮ ለመወጣት የሚያስችል ምን ድጋፍ አላቸው?

11 ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ ተገልጦላቸው የሚከተለውን ከባድ ተልእኮ ሰጣቸው፦ “ስለዚህ ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ፤ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፣ ያዘዝኳችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው። እነሆም እኔ እስከ ሥርዓቱ መደምደሚያ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።” (ማቴ. 28:19, 20) “ከእናንተ ጋር ነኝ” የሚለው ሐሳብ ደቀ መዛሙርቱ የስብከቱንና ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ ሲያከናውኑ የእሱ ድጋፍ እንደማይለያቸው የሚጠቁም ነው። ደግሞም ኢየሱስ “በሕዝቦች ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ” በማለት አስቀድሞ ስለተናገረ እንዲህ ዓይነቱ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል። (ማቴ. 24:9) ደቀ መዛሙርቱ ከሌላም አቅጣጫ ድጋፍ እንደሚያገኙ መተማመን ይችሉ ነበር። ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት “እስከ ምድር ዳር ድረስ” ምሥክሮቹ እንዲሆኑ መንፈስ ቅዱስ ኃይል እንደሚሰጣቸው ነግሯቸዋል።—ሥራ 1:8

12. ምን ወሳኝ ጥያቄዎች ይነሳሉ? የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ማግኘታችን እጅግ አስፈላጊ የሆነውስ ለምንድን ነው?

12 አሁን የሚነሱት ጥያቄዎች፦ የኢየሱስ ሐዋርያትም ሆኑ ሌሎቹ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ደቀ መዛሙርት የተሰጣቸውን ተልእኮ በቁም ነገር ተመልክተውት ነበር? በአንጻራዊ ሁኔታ ጥቂት የነበሩት እነዚህ ክርስቲያኖች ከባድ ስደት እያለም ስለ አምላክ መንግሥት በሚገባ መመሥከር ችለው ነበር? ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራቸው በእርግጥ የይሖዋን፣ የክርስቶስንና የመላእክትን ድጋፍ እንዲሁም የመንፈስ ቅዱስን እገዛ አግኝተዋል? የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ለእነዚህና ከእነዚህ ጋር ተዛማጅነት ላላቸው ሌሎች ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል። የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ማግኘታችን እጅግ አስፈላጊ ነው። ለምን? ኢየሱስ ተከታዮቹ እንዲሠሩት ያዘዘው ሥራ “እስከ ሥርዓቱ መደምደሚያ ድረስ” እንደሚቀጥል ተናግሯል። በመሆኑም ይህ ሥራ በዚህ የመጨረሻ ዘመን የምንኖረውን እኛን ጨምሮ ሁሉንም እውነተኛ ክርስቲያኖች ይመለከታል። ስለዚህ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘውን ታሪካዊ ዘገባ በቁም ነገር ልንመረምረው ይገባል።

የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ጠቅለል ያለ ይዘት

13, 14. (ሀ) የሐዋርያት ሥራን የጻፈው ማን ነው? ጸሐፊውስ መረጃዎቹን ያገኘው ከየት ነው? (ለ) የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ይዘት ምን ይመስላል?

13 የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍን የጻፈው ማን ነው? መጽሐፉ ራሱ ጸሐፊው ማን እንደሆነ አይገልጽም፤ ይሁንና በመግቢያው ላይ ያለው ሐሳብ የሐዋርያት ሥራን የጻፈው የሉቃስ ወንጌል ጸሐፊ እንደሆነ ይጠቁማል። (ሉቃስ 1:1-4፤ ሥራ 1:1, 2) በመሆኑም የሐዋርያት ሥራን የጻፈው ‘የተወደደ ሐኪም’ እና ጠንቃቃ ታሪክ ጸሐፊ የሆነው ሉቃስ መሆኑ ከጥንት ዘመን ጀምሮ ተቀባይነት ያገኘ ጉዳይ ነው። (ቆላ. 4:14) መጽሐፉ ኢየሱስ ወደ ሰማይ ካረገበት ከ33 ዓ.ም. አንስቶ ሐዋርያው ጳውሎስ ሮም ውስጥ እስከታሰረበት እስከ 61 ዓ.ም. ገደማ ድረስ ያሉትን ወደ 28 የሚጠጉ ዓመታት ይሸፍናል። ሉቃስ በዘገባው ላይ ‘እነሱ’ ሲል ቆይቶ በኋላ ላይ ‘እኛ’ እያለ መጻፍ መጀመሩ፣ የጠቀሳቸው ብዙዎቹ ክንውኖች በተፈጸሙበት ወቅት በቦታው እንደነበር የሚጠቁም ነው። (ሥራ 16:8-10፤ 20:5፤ 27:1) በጥንቃቄ ምርምር ያደርግ የነበረው ሉቃስ መረጃዎቹን ከጳውሎስ፣ ከበርናባስ፣ ከፊልጶስና በዘገባው ውስጥ ከጠቀሳቸው ሌሎች ሰዎች በቀጥታ እንዳገኘ ምንም ጥርጥር የለውም።

14 የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ይዘት ምን ይመስላል? ሉቃስ ቀደም ሲል በወንጌሉ ላይ ኢየሱስ ስለተናገራቸውና ስላደረጋቸው ነገሮች ዘግቧል። በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ የጻፈው ግን የኢየሱስ ተከታዮች ስለተናገሯቸውና ስላደረጓቸው ነገሮች ነው። በመሆኑም የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ አስደናቂ ነገሮችን ስላከናወኑ ሰዎች የሚዘግብ መጽሐፍ ነው፤ ከእነዚህ ሰዎች መካከል ብዙዎቹ በዘመኑ በነበሩት ሰዎች ዘንድ “ያልተማሩና ተራ ሰዎች” ተደርገው ይታዩ ነበር። (ሥራ 4:13) በአጭር አነጋገር፣ በመንፈስ መሪነት የተጻፈው ይህ ዘገባ የክርስቲያን ጉባኤ የተቋቋመውና እያደገ የሄደው እንዴት እንደሆነ የሚገልጽ ነው። የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች እንዴት እንደሰበኩ ማለትም ዘዴዎቻቸውንና ለሥራው የነበራቸውን አመለካከት ያወሳል። (ሥራ 4:31፤ 5:42) መንፈስ ቅዱስ ምሥራቹ እንዲስፋፋ በማድረግ ረገድ ስለተጫወተው ሚና ጎላ አድርጎ ይገልጻል። (ሥራ 8:29, 39, 40፤ 13:1-3፤ 16:6፤ 18:24, 25) የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ በክርስቶስ በሚመራው የአምላክ መንግሥት አማካኝነት የአምላክ ስም እንዴት እንደሚቀደስ የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጭብጥ ጎላ አድርጎ ይገልጻል፤ በተጨማሪም ከባድ ተቃውሞ ቢኖርም የመንግሥቱ መልእክት እንቅፋቶችን ድል በማድረግ ይበልጥ እየተስፋፋ የሄደው እንዴት እንደሆነ ይናገራል።—ሥራ 8:12፤ 19:8፤ 28:30, 31

15. የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍን መመርመራችን በየትኞቹ መንገዶች ይጠቅመናል?

15 በእርግጥም የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍን መመርመር አስደሳችና እምነት የሚያጠነክር ነው! ቀደም ሲል የነበሩት የክርስቶስ ተከታዮች በተዉት የድፍረትና የቅንዓት ምሳሌ ላይ የምናሰላስል ከሆነ ልባችን በጥልቅ ይነካል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩትን የእምነት ባልንጀሮቻችንን በእምነታቸው ለመምሰል እንነሳሳለን። ይህም “ሂዱና . . . ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ” የሚለውን ተልእኳችንን ለመወጣት በተሻለ ሁኔታ ያስታጥቀናል። እያነበብከው ያለኸው መጽሐፍ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍን በጥልቀት ለማጥናት እንዲረዳህ ታስቦ የተዘጋጀ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዳ መጽሐፍ

16. የዚህ መጽሐፍ ሦስት ዓላማዎች ምንድን ናቸው?

16 የዚህ መጽሐፍ ዋና ዓላማ ምንድን ነው? የዚህ መጽሐፍ ሦስት ዓላማዎች የሚከተሉት ናቸው፦ (1) ይሖዋ የመንግሥቱን ምሥራች የመስበኩንና ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት እንደሚደግፈው ያለንን እምነት ማጠናከር፣ (2) የመጀመሪያው መቶ ዘመን የክርስቶስ ተከታዮች የተዉትን ምሳሌ በመመርመር ለአገልግሎቱ ያለንን ቅንዓት ማቀጣጠል እንዲሁም (3) ለይሖዋ ድርጅት ብሎም በስብከቱ ሥራና ጉባኤዎችን በመምራት ግንባር ቀደም ለሆኑት ወንድሞች ያለን አክብሮት እንዲጨምር ማድረግ።

17, 18. ይህ ጽሑፍ የተዘጋጀው በምን መልኩ ነው? የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በምታደርግበት ወቅት የሚረዱህ ምን ገጽታዎችስ አሉት?

17 ይህ ጽሑፍ የተዘጋጀው በምን መልኩ ነው? መጽሐፉ ስምንት ክፍሎች አሉት፤ እያንዳንዱ ክፍል ከሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ የተወሰኑ ምዕራፎችን ይሸፍናል። ይሁንና በእያንዳንዱ ክፍል ውስጥ ያሉት ምዕራፎች ዓላማ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍን ቁጥር በቁጥር ማብራራት አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ በመጽሐፉ ውስጥ ከሰፈሩት ዘገባዎች ትምህርት እንድናገኝና የተማርነውን ነገር እንዴት በሥራ ላይ ማዋል እንደምንችል እንድንገነዘብ መርዳት ነው። በእያንዳንዱ ምዕራፍ መጀመሪያ ላይ የሚገኘው አጭር መግለጫ ምዕራፉ የሚያተኩርበትን ዋና ሐሳብ ይገልጻል፤ ጥቅሱ ደግሞ ከሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ የትኛው ክፍል እንደሚብራራ ይጠቁማል።

18 ይህ ጽሑፍ ለግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን የሚረዱ ሌሎች ገጽታዎችም አሉት። በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ የተገለጹትን አስደናቂ ታሪኮች የሚያሳዩ ማራኪ የሆኑ ሥዕሎች አሉ፤ በዘገባዎቹ ላይ ስታሰላስል በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ይረዱሃል። ብዙዎቹ ምዕራፎች ጠቃሚ የሆኑ ተጨማሪ መረጃዎችን የያዙ ሣጥኖች አሏቸው። አንዳንዶቹ ሣጥኖች በእምነታቸው ልንመስላቸው የሚገቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ባለታሪኮችን አጭር ታሪክ ይዘዋል። ሌሎቹ ደግሞ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ ስለተጠቀሱ አንዳንድ ቦታዎች፣ ክንውኖች፣ ልማዶች ወይም ሌሎች ሰዎች ተጨማሪ ማብራሪያ ይሰጣሉ።

የተሰጠህን የአገልግሎት ክልል በጥድፊያ ስሜት ሸፍን

19. በየጊዜው ራሳችንን ምን እያልን መመርመር አለብን?

19 ይህ ጽሑፍ ራስህን በሐቀኝነት እንድትመረምር ይረዳሃል። የመንግሥቱ አስፋፊ ሆነህ የቱንም ያህል ረጅም ዓመት ያገለገልክ ብትሆንም፣ በሕይወትህ ውስጥ ቅድሚያ እየሰጠሃቸው ያሉትን ነገሮችና ለክርስቲያናዊ አገልግሎት ያለህን አመለካከት በየጊዜው መመርመርህ ተገቢ ነው። (2 ቆሮ. 13:5) እንግዲያው ራስህን እንደሚከተለው እያልክ ጠይቅ፦ ‘አገልግሎቴን አሁንም በጥድፊያ ስሜት እያከናወንኩ ነው? (1 ቆሮ. 7:29-31) ምሥራቹን በጠንካራ እምነትና በቅንዓት እየሰበክሁ ነው? (1 ተሰ. 1:5, 6) በስብከቱና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ የተቻለኝን ያህል የተሟላ ተሳትፎ ለማድረግ እጥራለሁ?’—ቆላ. 3:23

20, 21. የተሰጠን ተልእኮ በጣም አጣዳፊ የሆነው ለምንድን ነው? ቁርጥ ውሳኔያችንስ ምን መሆን ይኖርበታል?

20 አንድ አስፈላጊ ሥራ የማከናወን ይኸውም የመስበክና ደቀ መዛሙርት የማድረግ ተልእኮ እንደተሰጠን መዘንጋት የለብንም። እያንዳንዱ ቀን ባለፈ ቁጥር የዚህ ተልእኮ አጣዳፊነት የዚያኑ ያህል እየጨመረ ይሄዳል። የዚህ ሥርዓት ፍጻሜ በፍጥነት እየቀረበ ነው። ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ዛሬ የብዙ ሰዎች ሕይወት አደጋ ላይ ወድቋል። ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸውና መልእክታችንን የሚቀበሉ ምን ያህል ሰዎች እንደቀሩ የምናውቀው ነገር የለም። (ሥራ 13:48) ሆኖም ጊዜው ከማለቁ በፊት እነዚህን ሰዎች የመርዳት ኃላፊነት ያለብን እኛ ነን።—1 ጢሞ. 4:16

21 በመሆኑም በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ቀናተኛ የመንግሥቱ ሰባኪዎች የተዉትን ምሳሌ መከተላችን አስፈላጊ ነው። ይህን ጽሑፍ በጥንቃቄ ማጥናትህ ከምንጊዜውም ይበልጥ በከፍተኛ ቅንዓትና ድፍረት ለመስበክ እንዲያነሳሳህ እንመኛለን። እንዲሁም “ስለ አምላክ መንግሥት በሚገባ [ለመመሥከር]” ያደረግከውን ቁርጥ ውሳኔ ይበልጥ እንደሚያጠናክርልህ ተስፋ እናደርጋለን።—ሥራ 28:23