በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 23

“የማቀርበውን የመከላከያ መልስ ስሙ”

“የማቀርበውን የመከላከያ መልስ ስሙ”

ጳውሎስ በቁጣ በተሞላው ሕዝብና በሳንሄድሪን ፊት ለእውነት ተሟገተ

በሐዋርያት ሥራ 21:18 እስከ 23:10 ላይ የተመሠረተ

1, 2. ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም የመጣው ለምንድን ነው? እዚያስ ምን ፈታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሙታል?

 ኢየሩሳሌም! ጳውሎስ ወደዚህች ከተማ ተመልሷል፤ በሰው በተጨናነቁት ጠባብ ጎዳናዎቿ ላይ እየተዘዋወረ ነው። መቼም የኢየሩሳሌምን ያህል በይሖዋ አምልኮ የዘመናት ታሪክ ያስቆጠረ ሌላ ከተማ የለም። አብዛኞቹ ነዋሪዎቿም በከተማቸው የቀድሞ ገናና ታሪክ ይኩራራሉ። በዚያ የሚኖሩ ብዙ ክርስቲያኖችም እንኳ የጥንቱን ወግ ልማድ መተው እንደማይፈልጉ ጳውሎስ ያውቃል፤ ወደፊት እየገሰገሰ ካለው የይሖዋ ዓላማ ጋር እኩል መጓዝ እንደሚከብዳቸው አስተውሏል። ገና በኤፌሶን ሳለ ይህችን ታላቅ ከተማ በድጋሚ መጎብኘት የፈለገው ለዚህ ነው፤ ወንድሞቹ ቁሳዊ እርዳታ ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ እገዛም እንደሚያስፈልጋቸው ተሰምቶታል። (ሥራ 19:21) ጳውሎስ አደጋ ሊያጋጥመው እንደሚችል ቢያውቅም ወደዚህ ለመምጣት ያወጣውን ዕቅድ አልለወጠም።

2 ታዲያ ጳውሎስ በኢየሩሳሌም ምን ያጋጥመው ይሆን? አንዱ ፈተና የሚመጣው ከክርስቶስ ተከታዮች ነው፤ ስለ ጳውሎስ በሰሙት አሉባልታ የተነሳ ቅር ተሰኝተዋል። ከክርስቶስ ጠላቶች ደግሞ ገና ከዚህ የከፉ ፈተናዎች ያጋጥሙታል። እነዚህ ሰዎች የሐሰት ክሶች ይሰነዝሩበታል፣ ይደበድቡታል እንዲሁም እንደሚገድሉት ይዝቱበታል። በጳውሎስ ሕይወት ውስጥ የተፈጠሩት እነዚህ ነውጦች ስለ እምነቱ ለመናገር አጋጣሚ ይከፍቱለታል። ፈተናዎቹን በትሕትና፣ በድፍረትና በእምነት የተወጣበት መንገድ ዛሬ ላሉ ክርስቲያኖች ግሩም ምሳሌ ይሆናል። ከእሱ የምናገኘውን ትምህርት እስቲ እንመልከት።

“አምላክን አመሰገኑ” (የሐዋርያት ሥራ 21:18-20ሀ)

3-5. (ሀ) ጳውሎስ በኢየሩሳሌም በተካሄደው በየትኛው ስብሰባ ላይ ተገኝቷል? በስብሰባው ላይ የተነሳው ጉዳይስ ምን ነበር? (ለ) ጳውሎስ በኢየሩሳሌም ከሚገኙ ሽማግሌዎች ጋር ካደረገው ስብሰባ ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?

3 ጳውሎስና የጉዞ ጓደኞቹ ኢየሩሳሌም በደረሱ ማግስት፣ የጉባኤውን ሽማግሌዎች ለማግኘት ሄዱ። በሕይወት ካሉት ሐዋርያት መካከል የአንዳቸውም ስም በዚህ ዘገባ ላይ አልተጠቀሰም፤ በወቅቱ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ለማገልገል ሄደው ሊሆን ይችላል። የኢየሱስ ወንድም ያዕቆብ ግን አሁንም እዚያ ነው። (ገላ. 2:9) ጳውሎስ ‘ከሽማግሌዎቹ ሁሉ’ ጋር ያደረገውን ስብሰባ የመራው ያዕቆብ ሳይሆን አይቀርም።—ሥራ 21:18

4 ጳውሎስ ለሽማግሌዎቹ ሰላምታ ካቀረበ በኋላ “እሱ ባከናወነው አገልግሎት አማካኝነት አምላክ በአሕዛብ መካከል የፈጸማቸውን ነገሮች በዝርዝር ይተርክላቸው ጀመር።” (ሥራ 21:19) ወንድሞች በሰሙት ነገር በጣም ተበረታተው እንደሚሆን መገመት እንችላለን። ዛሬም እኛ በሌሎች አገሮች ከስብከቱ ሥራ ጋር በተያያዘ ስለተገኘው እድገት ስንሰማ እንደሰታለን።—ምሳሌ 25:25

5 ጳውሎስ በንግግሩ መሃል፣ ከአውሮፓ ይዞ ስለመጣው መዋጮ ሳይጠቅስ አይቀርም። ርቀው በሚገኙ አገሮች የሚኖሩ ወንድሞች ስላሳዩት አሳቢነት ሲሰሙ እነዚያ ሽማግሌዎች ልባቸው በደስታ ተሞልቶ መሆን አለበት። ዘገባው የጳውሎስን ሪፖርት ካዳመጡ በኋላ “አምላክን አመሰገኑ” ይላል። (ሥራ 21:20ሀ) ዛሬም በተመሳሳይ አደጋ የደረሰባቸው ወይም በጠና የታመሙ ክርስቲያኖች፣ የእምነት ባልንጀሮቻቸው በሚያስፈልጋቸው ጊዜ ሲረዷቸውና ሲያጽናኗቸው ልባቸው በጥልቅ ይነካል።

ብዙዎች አሁንም “ለሕጉ ቀናተኞች ናቸው” (የሐዋርያት ሥራ 21:20ለ, 21)

6. ጳውሎስ ምን ችግር መከሰቱን ሰማ?

6 ከዚያም ሽማግሌዎቹ ጳውሎስን በቀጥታ የሚመለከት ችግር በይሁዳ መከሰቱን ገለጹለት። እንዲህ አሉት፦ “ወንድም፣ ከአይሁዳውያን መካከል በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ አማኞች እንዳሉ ታውቃለህ፤ ደግሞም ሁሉም ለሕጉ ቀናተኞች ናቸው። እነሱም አንተ በአሕዛብ መካከል ያሉት አይሁዳውያን ሁሉ ልጆቻቸውን እንዳይገርዙም ሆነ የቆየውን ልማድ እንዳይከተሉ በመንገር የሙሴን ሕግ እንዲተዉ ስታስተምር እንደቆየህ ስለ አንተ የሚወራውን ወሬ ሰምተዋል።” aሥራ 21:20ለ, 21

7, 8. (ሀ) በይሁዳ የነበሩ ብዙ ክርስቲያኖች ምን የተሳሳተ አመለካከት ነበራቸው? (ለ) አንዳንድ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች የነበራቸው የተሳሳተ አስተሳሰብ እንደ ክህደት ሊቆጠር የማይችለው ለምንድን ነው?

7 የሙሴ ሕግ ከተሻረ ከ20 ዓመት በላይ አልፎታል፤ ታዲያ አሁንም ለሕጉ የሚቀኑ ብዙ ክርስቲያኖች ሊኖሩ የቻሉት እንዴት ነው? (ቆላ. 2:14) በ49 ዓ.ም. ሐዋርያትና ሽማግሌዎች በኢየሩሳሌም ከተሰበሰቡ በኋላ ለጉባኤዎች ደብዳቤ ልከው ነበር፤ በደብዳቤው ላይም ከአሕዛብ የመጡ አማኞች መገረዝም ሆነ የሙሴን ሕግ መጠበቅ እንደማያስፈልጋቸው ገልጸዋል። (ሥራ 15:23-29) ይሁን እንጂ ደብዳቤው አይሁዳውያን አማኞችን በተመለከተ የሚጠቅሰው ነገር የለም፤ ደግሞም አብዛኞቹ የሙሴ ሕግ እንደተሻረ አልገባቸውም።

8 እነዚህ አይሁዳውያን አማኞች እንዲህ ዓይነት የተሳሳተ አስተሳሰብ ስላላቸው ክርስቲያኖች አይደሉም ማለት ነው? በፍጹም። እነዚህ ሰዎች ከባዕድ አምልኮ የመጣን ሃይማኖታዊ ልማድ መከተላቸውን ለመቀጠል እየሞከሩ አይደለም። እነዚህ አይሁዳውያን አማኞች ከፍ አድርገው የሚመለከቱትን ሕግ ቀድሞውንም ቢሆን የሰጣቸው ይሖዋ ነው። በሕጉ ውስጥ ከአጋንንት ጋር ንክኪ ያለው ወይም የተሳሳተ ነገር የለም። ሆኖም ሕጉ ከተሻረው ቃል ኪዳን ጋር የተያያዘ ነበር፤ ክርስቲያኖች ደግሞ በአዲሱ ቃል ኪዳን ሥር ናቸው። በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ያለው አምልኮ ለማቅረብ የሕጉን ቃል ኪዳን ማክበር አስፈላጊ መሆኑ ቀርቷል። ለሕጉ የሚቀኑት ዕብራውያን አማኞች፣ የክርስቲያን ጉባኤን በተመለከተ ያልገቧቸው ነገሮች ነበሩ፤ ከዚህም ሌላ ይሖዋ ለጉባኤው ባደረገው አዲስ ዝግጅት ላይ እምነት አልነበራቸውም። ደረጃ በደረጃ እየተገለጠ ከሚሄደው እውነት ጋር አስተሳሰባቸውን ማስማማት ያስፈልጋቸው ነበር። bኤር. 31:31-34፤ ሉቃስ 22:20

“የተወራው ሁሉ ከንቱ መሆኑ” ይታወቃል (የሐዋርያት ሥራ 21:22-26)

9. ጳውሎስ የሙሴን ሕግ በተመለከተ ምን አስተምሯል?

9 ጳውሎስ፣ በአሕዛብ መካከል የሚኖሩ አይሁዳውያን “ልጆቻቸውን እንዳይገርዙም ሆነ የቆየውን ልማድ እንዳይከተሉ” እያስተማረ እንደሆነ የተወራበት ነገርስ? ጳውሎስ የአሕዛብ ሐዋርያ ነው፤ አሕዛብ ሕጉን የመጠበቅ ግዴታ እንደሌለባቸው የተላለፈውን ውሳኔ ለእነሱ መንገሩ አይቀርም። ከአሕዛብ የመጡ አማኞች መገረዝና የሙሴን ሕግ ማክበር እንዳለባቸው ለማሳመን የሚሞክሩ ሰዎች ሲያጋጥሙት ደግሞ ስህተታቸውን አጋልጧል። (ገላ. 5:1-7) በሌላ በኩል ደግሞ ጳውሎስ በሄደባቸው ከተሞች ለሚኖሩ አይሁዳውያንም ምሥራቹን ሰብኳል። መልእክቱን ለተቀበሉት አይሁዳውያን የኢየሱስ ሞት ሕጉን እንደሻረውና ሰው የሚጸድቀው በእምነት እንጂ ሕጉን በመጠበቅ እንዳልሆነ አስረድቷቸው መሆን አለበት።—ሮም 2:28, 29፤ 3:21-26

10. ጳውሎስ ከሕጉና ከግርዘት ጋር በተያያዘ ምን ሚዛናዊ አመለካከት ነበረው?

10 አንዳንድ የአይሁዳውያን ልማዶችን ለመከተል ለምሳሌ በሰንበት ሥራ ላለመሥራት ወይም አንዳንድ ምግቦችን ላለመብላት የመረጡ ክርስቲያኖች ነበሩ፤ ጳውሎስ በዚህ አልነቀፋቸውም። (ሮም 14:1-6) ግርዘትን በተመለከተም ያወጣው ደንብ የለም። እንዲያውም ጳውሎስ የጢሞቴዎስ አባት ግሪካዊ ስለሆነ አይሁዳውያን ጢሞቴዎስን በጥርጣሬ እንዳያዩት ሲል ገርዞታል። (ሥራ 16:3) ግርዘት ለግለሰቦች ምርጫ የተተወ ጉዳይ ነበር። ጳውሎስ የገላትያ ክርስቲያኖችን “በፍቅር የሚመራ እምነት እንጂ መገረዝ ወይም አለመገረዝ ፋይዳ የለውም” ብሏቸዋል። (ገላ. 5:6) ይሁንና ሕጉን ለማክበር ብሎ መገረዝ ወይም በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ግርዘት አስፈላጊ እንደሆነ መናገር ስህተት ነው፤ ይህን የሚያደርግ ግለሰብ እምነት ጎድሎታል።

11. ሽማግሌዎቹ ለጳውሎስ ምን ምክር ሰጡት? ሆኖም ጳውሎስ ለማድረግ ፈቃደኛ የሚሆናቸው ወይም የማይሆናቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)

11 በጳውሎስ ላይ የተወራው ነገር ትክክል ባይሆንም አይሁዳውያን ክርስቲያኖች በሰሙት ነገር ተረብሸዋል። በመሆኑም ሽማግሌዎቹ እንዲህ የሚል ምክር ሰጡት፦ “ስእለት ያለባቸው አራት ሰዎች በእኛ ዘንድ አሉ። እነዚህን ሰዎች ይዘህ በመሄድ ከእነሱ ጋር የመንጻት ሥርዓት ፈጽም፤ ራሳቸውንም እንዲላጩ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ክፈልላቸው። ይህን ካደረግክ በአንተ ላይ የተወራው ሁሉ ከንቱ መሆኑንና አንተም ሕጉን እያከበርክ በሥርዓት እንደምትኖር ሁሉም ሰው ያውቃል።” cሥራ 21:23, 24

12. ጳውሎስ የኢየሩሳሌም ሽማግሌዎች ምክር ሲሰጡት እሺ ባይና ተባባሪ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?

12 ጳውሎስ የችግሩ ዋና መንስኤ ስለ እሱ የተወራው አሉባልታ ሳይሆን አይሁዳውያን አማኞች ለሙሴ ሕግ ያላቸው ቅንዓት እንደሆነ በመግለጽ መቃወም ይችል ነበር። ይሁን እንጂ አምላክ ያወጣቸው መሠረታዊ ሥርዓቶች እስካልተጣሱ ድረስ ሽማግሌዎቹ ያሉትን ለማድረግ ፈቃደኛ ሆኗል። ቀደም ሲል “እኔ ራሴ በሕግ ሥር ባልሆንም እንኳ በሕግ ሥር ያሉትን እማርክ ዘንድ በሕግ ሥር ላሉት በሕግ ሥር እንዳለሁ ሆንኩ” በማለት ጽፎ ነበር። (1 ቆሮ. 9:20) በዚህ ወቅት ጳውሎስ ከኢየሩሳሌም ሽማግሌዎች ጋር በመተባበር “በሕግ ሥር” እንዳለ ሆኗል። ከሽማግሌዎች ጋር በመተባበርና እኔ ያልኩት ካልሆነ ብሎ ድርቅ ከማለት በመቆጠብ ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል።—ዕብ. 13:17

ጳውሎስ ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች እስካልተጣሱ ድረስ የሌሎችን ሐሳብ ይቀበል ነበር። አንተስ?

“ይህ ሰው መኖር የማይገባው” ነው! (የሐዋርያት ሥራ 21:27 እስከ 22:30)

13. (ሀ) አንዳንድ አይሁዳውያን ቤተ መቅደሱ ውስጥ ሁከት ያስነሱት ለምንድን ነው? (ለ) ጳውሎስ ከሞት ሊተርፍ የቻለው እንዴት ነው?

13 ቤተ መቅደሱ ውስጥ ነገሮች እንደታሰበው በሰላም አልተከናወኑም። ስእለቱ የሚፈጸምባቸው ቀናት ሊጠናቀቁ ሲቃረቡ ከእስያ የመጡ አይሁዳውያን ጳውሎስን አዩት፤ ‘ከአሕዛብ ወገን የሆኑ ሰዎችን ወደ ቤተ መቅደሱ አምጥቷል’ የሚል የሐሰት ክስ በመሰንዘር ሁከት አስነሱ። ሮማዊው ሻለቃ ጣልቃ ባይገባ ኖሮ ጳውሎስን ደብድበው ይገድሉት ነበር። ሻለቃው ጳውሎስን በቁጥጥር ሥር አዋለው። ጳውሎስ በዚህ ወቅት የተነጠቀውን ነፃነት መልሶ የሚያገኘው ከአራት ዓመት በኋላ ነው። የተጋረጠበት አደጋም በዚሁ ቢያበቃ አንድ ነገር ነበር፤ ግን ይህ አልሆነም። ሻለቃው በጳውሎስ ላይ ጥቃት የሰነዘሩት ለምን እንደሆነ ሲጠይቃቸው አይሁዳውያኑ የተለያዩ ክሶች አቀረቡ። ሻለቃው ከጫጫታው የተነሳ ምንም የተጨበጠ ነገር ማግኘት አልቻለም። ውጥረቱ እየተባባሰ ሲመጣ ወታደሮቹ ጳውሎስን ተሸክመው ወሰዱት። ጳውሎስና ሮማውያኑ ወታደሮች ወደ ጦር ሰፈሩ ሲቃረቡ ጳውሎስ ሻለቃውን “ለሕዝቡ እናገር ዘንድ እንድትፈቅድልኝ እለምንሃለሁ” አለው። (ሥራ 21:39) ሻለቃው በሐሳቡ በተስማማ ጊዜ ጳውሎስ በድፍረት ለእምነቱ የመከላከያ ሐሳብ ማቅረብ ጀመረ።

14, 15. (ሀ) ጳውሎስ ለአይሁዳውያኑ ምን አስረዳቸው? (ለ) ሮማዊው ሻለቃ አይሁዳውያኑ የተቆጡበትን ምክንያት ለማወቅ ምን እርምጃዎች ወሰደ?

14 ጳውሎስ ንግግሩን የጀመረው “የማቀርበውን የመከላከያ መልስ ስሙ” በማለት ነው። (ሥራ 22:1) በዕብራይስጥ ቋንቋ ሲናገር ሕዝቡ ጸጥ ብለው ማዳመጥ ጀመሩ። ጳውሎስ፣ የክርስቶስ ተከታይ የሆነው ለምን እንደሆነ በግልጽ አስረዳቸው። አይሁዳውያኑ ከፈለጉ ሊያረጋግጧቸው የሚችሉ አንዳንድ ነጥቦችን በዘዴ ጠቀሰ። የተማረው ገማልያል በተባለ ስመ ጥር መምህር እግር ሥር ተቀምጦ ነው፤ የክርስቶስን ተከታዮች ያሳድድም ነበር፤ በዚያ ከተገኙት ሰዎች አንዳንዶቹ ይህን ሳያውቁ አይቀሩም። ይሁን እንጂ ወደ ደማስቆ እየተጓዘ ሳለ፣ ከሞት የተነሳው ክርስቶስ በራእይ ተገልጦለት አናገረው። ከጳውሎስ ጋር የሚጓዙት ሰዎች ኃይለኛ ብርሃን አይተዋል፣ ድምፅም ሰምተዋል፤ ምን እንደተባለ ግን አላስተዋሉም። (ሥራ 9:7፤ 22:9 የግርጌ ማስታወሻ) ጳውሎስ ከዚያ በኋላ ማየት ስለተሳነው አብረውት የነበሩት ሰዎች እየመሩ ወደ ደማስቆ ወሰዱት። እዚያ ሲደርስ ሐናንያ የተባለ በአካባቢው ባሉ አይሁዳውያን ዘንድ የታወቀ ሰው በተአምር የጳውሎስን ዓይን አበራለት።

15 ቀጥሎም ጳውሎስ፣ ወደ ኢየሩሳሌም ከተመለሰ በኋላ ኢየሱስ ቤተ መቅደሱ ውስጥ እንደተገለጠለት ተናገረ። አይሁዳውያኑ ይህን ሲሰሙ በጣም ተናደው “ይህ ሰው መኖር የማይገባው ስለሆነ ከምድር ገጽ ይወገድ!” ብለው ጮኹ። (ሥራ 22:22) ሻለቃው የጳውሎስን ሕይወት ለማትረፍ ሲል ወደ ጦር ሰፈሩ እንዲያስገቡት አደረገ። አይሁዳውያኑ በጳውሎስ ላይ ይህን ያህል ያስቆጣቸው ምን እንደሆነ ማወቅ ስለፈለገም እየተገረፈ እንዲመረመር አዘዘ። ይሁንና ጳውሎስ ሕጋዊ ከለላ ማግኘት የሚችልበትን እርምጃ ወሰደ፤ የሮም ዜጋ መሆኑን አሳወቀ። በዛሬው ጊዜ ያሉ የይሖዋ አገልጋዮችም የሕግ ከለላ ለማግኘት በሚያስችሏቸው ዝግጅቶች በመጠቀም ለእምነታቸው ጥብቅና ይቆማሉ። (“ የሮም ሕግና የሮም ዜጎች” የሚለውን ሣጥን እንዲሁም “ በዘመናችን የተደረጉ የሕግ ፍልሚያዎች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) ሻለቃው፣ ጳውሎስ ሮማዊ መሆኑን ሲሰማ ስለ እሱ መረጃ ለማግኘት ሌላ መንገድ መጠቀም እንዳለበት ተገነዘበ። በነጋታው የአይሁዳውያን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሆነው የሳንሄድሪን ሸንጎ እንዲሰበሰብ አዘዘ፤ ጳውሎስንም ፊታቸው አቀረበው።

“ፈሪሳዊ ነኝ” (የሐዋርያት ሥራ 23:1-10)

16, 17. (ሀ) ጳውሎስ በሳንሄድሪን ሸንጎ ፊት ሲናገር ምን እንደተከሰተ ግለጽ። (ለ) ጳውሎስ በጥፊ በተመታበት ወቅት ትሕትና ያሳየው እንዴት ነው?

16 ጳውሎስ በሳንሄድሪን ሸንጎ ፊት ያቀረበውን የመከላከያ ሐሳብ የጀመረው እንዲህ በማለት ነው፦ “ወንድሞች፣ እኔ እስከዚህ ቀን ድረስ በአምላክ ፊት ሙሉ በሙሉ ንጹሕ ሕሊና ይዤ ተመላልሻለሁ።” (ሥራ 23:1) ሆኖም ንግግሩን ከዚያ በላይ መቀጠል አልቻለም። ዘገባው አክሎ እንደሚናገረው “ሊቀ ካህናቱ ሐናንያ፣ ጳውሎስ አጠገብ የቆሙት ሰዎች አፉን እንዲመቱት አዘዘ።” (ሥራ 23:2) እንዴት ያለ ንቀት ነው! ደግሞስ እንዴት ያለ ፍርደ ገምድልነት ነው! የመከላከያ ሐሳብ ለማቅረብ እንኳ ዕድል ሳይሰጠው ውሸታም ያለው ያህል ነው! ጳውሎስ የሚከተለውን ምላሽ መስጠቱ ምንም አያስደንቅም፦ “አንተ በኖራ የተለሰንክ ግድግዳ! አምላክ አንተን ይመታሃል። በሕጉ መሠረት በእኔ ላይ ለመፍረድ ተቀምጠህ ሳለ አንተ ራስህ ሕጉን በመጣስ እንድመታ ታዛለህ?”—ሥራ 23:3

17 በዚህ ጊዜ በቦታው ከቆሙት መካከል አንዳንዶቹ ደነገጡ! የደነገጡት ግን ጳውሎስ በመመታቱ ሳይሆን በሰጠው መልስ ነበር። “የአምላክን ሊቀ ካህናት ትሳደባለህ?” አሉት። በዚህ ጊዜ ጳውሎስ፣ የሰጠው መልስ በትሕትናና ለሕጉ አክብሮት በማሳየት ረገድ ጥሩ ትምህርት የሚሆናቸው ነው። “ወንድሞች፣ እኔ እኮ ሊቀ ካህናት መሆኑን አላወቅኩም። ምክንያቱም ‘በሕዝብህ ገዢ ላይ ክፉ ቃል አትናገር’ ተብሎ ተጽፏል” አላቸው። d (ሥራ 23:4, 5፤ ዘፀ. 22:28) አሁን ጳውሎስ ለየት ያለ ዘዴ ተጠቀመ። የሳንሄድሪን አባላት ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን መሆናቸውን ስላወቀ እንዲህ አላቸው፦ “ወንድሞች፣ እኔ ከፈሪሳውያን የተወለድኩ ፈሪሳዊ ነኝ። ለፍርድ የቀረብኩት በሙታን ትንሣኤ ተስፋ በማመኔ ነው።”—ሥራ 23:6

ከእኛ የተለየ ሃይማኖታዊ አመለካከት ካላቸው ሰዎች ጋር ስንወያይ እንደ ጳውሎስ በጋራ የሚያስማሙንን ነጥቦች እናነሳለን

18. ጳውሎስ ፈሪሳዊ ነኝ ያለው ለምንድን ነው? እኛስ ከሰዎች ጋር ስንወያይ ተመሳሳይ ዘዴ ልንጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?

18 ጳውሎስ ፈሪሳዊ ነኝ ያለው ለምንድን ነው? ‘ከፈሪሳውያን ስለተወለደ’ ማለትም የፈሪሳውያን ሃይማኖታዊ ቡድን አባል ከሆነ ቤተሰብ ስለመጣ ነው። ከዚህ የተነሳ ብዙዎች አሁንም የሚያዩት እንደ ፈሪሳዊ ነው። e ይሁን እንጂ ጳውሎስ ይህን ሲል ፈሪሳውያን ስለ ትንሣኤ ያላቸውን አመለካከት ይቀበላል ማለት ነው? ፈሪሳውያን፣ ሰው ሲሞት ነፍሱ እንደማትሞት እንዲሁም የጻድቅ ነፍስ እንደገና ሥጋዊ አካል ለብሳ እንደምትኖር ያምናሉ። ጳውሎስ እንዲህ ያለ አመለካከት አልነበረውም። እሱ የሚያምነው ኢየሱስ ያስተማረውን ትንሣኤ ነው። (ዮሐ. 5:25-29) ይሁንና ጳውሎስ ከፈሪሳውያን ጋር የሚያስማማው ነገር አለ፤ ከሰዱቃውያን በተቃራኒ ከሞት ባሻገር የመኖር ተስፋ እንዳለ ያምናል። እኛም የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶችን ከሚከተሉ ሰዎች ጋር ስንወያይ ተመሳሳይ ዘዴ መጠቀም እንችላለን። ልክ እንደ እነሱ እኛም በአምላክ እንደምናምን ልንገልጽላቸው እንችላለን። እርግጥ እነሱ የሚያምኑት በሥላሴ ሊሆን ይችላል፤ እኛ ደግሞ የምናምነው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተጠቀሰው አምላክ ነው። ይሁንና እነሱም እኛም በአምላክ ማመናችን ያመሳስለናል።

19. የሳንሄድሪን ሸንጎ በትርምስ የተበተነው ለምንድን ነው?

19 ጳውሎስ የተናገረው ሐሳብ በሳንሄድሪን ሸንጎ መካከል ክፍፍል ፈጠረ። ዘገባው እንዲህ ይላል፦ “ከፍተኛ ሁከት ተፈጠረ፤ ከፈሪሳውያን ወገን የሆኑ አንዳንድ ጸሐፍት ተነስተው እንዲህ ሲሉ አጥብቀው ተከራከሩ፦ ‘በዚህ ሰው ላይ ምንም ጥፋት አላገኘንም፤ መንፈስ ወይም መልአክ አናግሮት ከሆነ ግን . . . ።’” (ሥራ 23:9) ጳውሎስን መልአክ አናግሮት ይሆናል የሚለው ሐሳብ በራሱ ሰዱቃውያንን የሚያስቆጣ ነው! ምክንያቱም በመላእክት አያምኑም። (“ ሰዱቃውያንና ፈሪሳውያን” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) ውዝግቡ እየከረረ ሲሄድ ሮማዊው ሻለቃ በድጋሚ ጣልቃ በመግባት ሐዋርያውን ታደገው። (ሥራ 23:10) ይሁንና ጳውሎስ አሁንም ቢሆን አደጋ አጥልቶበታል። ከዚህ በኋላስ ምን ያጋጥመው ይሆን? ይህን በሚቀጥለው ምዕራፍ እንመለከታለን።

a በወቅቱ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ነበሩ፤ የሁሉንም መንፈሳዊ ፍላጎት ለማሟላት በግል መኖሪያ ቤቶች የሚሰበሰቡ በርካታ ጉባኤዎች ማቋቋም ሳያስፈልግ አልቀረም።

b ሐዋርያው ጳውሎስ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች ደብዳቤ ጻፈ፤ በደብዳቤው ላይ የአዲሱን ቃል ኪዳን ብልጫ አስረግጦ ተናግሯል። አዲሱ ቃል ኪዳን አሮጌውን የሚተካ እንደሆነ በግልጽ አስረድቷል። ጳውሎስ፣ እነዚያ ክርስቲያኖች ለአይሁዳውያን ተቃዋሚዎቻቸው መልስ ለመስጠት የሚያስችሏቸው አሳማኝ ማስረጃዎች አቅርቧል፤ ከዚህም ሌላ ጳውሎስ ያቀረባቸው ጠንካራ ነጥቦች ለሙሴ ሕግ አላስፈላጊ ትኩረት የሚሰጡ ክርስቲያኖችን እምነት አጠናክረው መሆን አለበት።—ዕብ. 8:7-13

c አንዳንድ ምሁራን፣ እነዚህ ሰዎች የናዝራዊነት ስእለት እንደነበረባቸው ይናገራሉ። (ዘኁ. 6:1-21) እርግጥ ነው፣ ይህን ስእለት የሚያካትተው የሙሴ ሕግ አሁን ተሽሯል። ይሁንና እነዚህ ሰዎች የተሳሉት ለይሖዋ በመሆኑ ጳውሎስ ስእለቱን መፈጸማቸው ስህተት እንዳልሆነ አስቦ ሊሆን ይችላል። በመሆኑም የሰዎቹን ወጪ መክፈሉና አብሯቸው መሄዱ ምንም ስህተት የለውም። ሰዎቹ የተሳሉት ምን ዓይነት ስእለት እንደሆነ በእርግጠኝነት ማወቅ አንችልም። ይሁንና ብዙውን ጊዜ ናዝራውያን ከኃጢአት ለመንጻት የእንስሳት መሥዋዕት ያቀርቡ እንደነበር ይታወቃል፤ የሰዎቹ ስእለት ምንም ዓይነት ይሁን፣ ጳውሎስ እንዲህ ያለውን መሥዋዕት ለማቅረብ እንደማይስማማ ጥያቄ የለውም። ፍጹም የሆነው የክርስቶስ መሥዋዕት ከቀረበ ወዲህ የእንስሳት መሥዋዕቶች ኃጢአትን ማስተሰረይ አይችሉም። ጳውሎስ ያደረገው ነገር ምንም ይሁን ምን፣ ሕሊናውን የሚያስጥስ ነገር ለማድረግ እንደማይስማማ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።

d አንዳንዶች እንደሚሉት ከሆነ ጳውሎስ ሊቀ ካህናቱን ያላወቀው አጥርቶ የማየት ችግር ስለነበረበት ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ ለረጅም ጊዜ በኢየሩሳሌም ስላልነበረ በወቅቱ ያለው ሊቀ ካህናት ማን እንደሆነ አላወቀ ይሆናል። አሊያም ብዙ ሰው ስለነበር እንዲመታ ትእዛዝ የሰጠው ማን እንደሆነ መለየት ስላቃተው ሊሆን ይችላል።

e በ49 ዓ.ም. ሐዋርያትና ሽማግሌዎች፣ ‘አሕዛብ የሙሴን ሕግ ማክበር አለባቸው ወይም የለባቸውም’ በሚለው ጉዳይ ላይ ተወያይተው ነበር፤ ከመካከላቸው አንዳንዶቹ “ከፈሪሳውያን ሃይማኖታዊ ቡድን መካከል አማኞች የሆኑ” ተብለዋል። (ሥራ 15:5) እንዲህ የተባለው እነዚህ አማኞች ከዚህ ቀደም ፈሪሳዊ ስለነበሩ ሊሆን ይችላል።