በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 24

“አይዞህ፣ አትፍራ!”

“አይዞህ፣ አትፍራ!”

ጳውሎስ ሕይወቱን ለማጥፋት ከተጠነሰሰው ሴራ አመለጠ፤ በፊሊክስ ፊት የመከላከያ መልስ አቀረበ

በሐዋርያት ሥራ 23:11 እስከ 24:27 ላይ የተመሠረተ

1, 2. ጳውሎስ ኢየሩሳሌም ውስጥ በደረሰበት ስደት ያልተደናገጠው ለምንድን ነው?

 ኢየሩሳሌም ውስጥ በቁጣ ገንፍሎ ከወጣው ሕዝብ ለጥቂት ያመለጠው ጳውሎስ አሁንም እንደታሰረ ነው። ይህ ቀናተኛ ሐዋርያ በኢየሩሳሌም እየደረሰበት ባለው ስደት አልተደናገጠም። በዚህች ከተማ “እስራትና መከራ” እንደሚጠብቀው ተነግሮት ነበር። (ሥራ 20:22, 23) ከዚህ በኋላ ምን እንደሚገጥመው በዝርዝር ባያውቅም ለኢየሱስ ስም ሲል መከራ መቀበሉን እንደሚቀጥል ተገንዝቧል።—ሥራ 9:16

2 ክርስቲያን የሆኑ ነቢያትም እንደሚታሰርና ‘ለአሕዛብ አልፎ’ እንደሚሰጥ ጳውሎስን አስጠንቅቀውታል። (ሥራ 21:4, 10, 11) በቅርቡ በርካታ አይሁዳውያን ሊገድሉት ሞክረው ነበር፤ ያንን አለፍኩ እንዳለ ደግሞ የሳንሄድሪን ሸንጎ አባላት፣ ስለ እሱ ሲሟገቱ ‘ሊገነጣጥሉት’ ተቃርበው ነበር። አሁን በሮማውያን ወታደሮች ቁጥጥር ሥር ነው፤ ገና ብዙ ሙግቶችና ውንጀላዎች ይጠብቁታል። (ሥራ 21:31፤ 23:10) በእርግጥም ሐዋርያው ጳውሎስ ማበረታቻ ያስፈልገዋል!

3. በስብከቱ ሥራችን ለመቀጠል የሚያስችለንን ማበረታቻ የምናገኘው ከየት ነው?

3 በዚህ የፍጻሜ ዘመን “የክርስቶስ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በመሆን ለአምላክ ያደሩ ሆነው መኖር የሚፈልጉ ሁሉ ስደት [እንደሚደርስባቸው]” እናውቃለን። (2 ጢሞ. 3:12) እኛም በስብከቱ ሥራችን እንድንጸና በየጊዜው ማበረታቻ ያስፈልገናል። “ታማኝና ልባም ባሪያ” በሚያዘጋጃቸው ጽሑፎችና ስብሰባዎች አማካኝነት ለምናገኘው ወቅታዊ ማበረታቻ ምንኛ አመስጋኝ ነን! (ማቴ. 24:45) የምሥራቹ ጠላቶች መቼም ቢሆን እንደማይሳካላቸው ይሖዋ ማረጋገጫ ሰጥቶናል። ተቃዋሚዎች የአምላክ አገልጋዮችን በቡድን ደረጃ ማጥፋትም ሆነ የስብከት ሥራቸውን ማስቆም አይችሉም። (ኢሳ. 54:17፤ ኤር. 1:19) ይሁንና እስቲ ሐዋርያው ጳውሎስ ወዳጋጠመው ሁኔታ እንመለስ። ተቃውሞን ተጋፍጦ በሚገባ መመሥከሩን ለመቀጠል የሚያስችል ማበረታቻ አግኝቶ ይሆን? ከሆነ ያገኘው ማበረታቻ ምንድን ነው? እሱስ ምን አደረገ?

“ሴራ ለመፈጸም የተማማሉት ሰዎች” ዕቅድ ከሸፈ (የሐዋርያት ሥራ 23:11-34)

4, 5. ጳውሎስ ምን ማበረታቻ አግኝቷል? ማበረታቻውስ ወቅታዊ ነበር የምንለው ለምንድን ነው?

4 ሐዋርያው ጳውሎስ በሳንሄድሪን ሸንጎ ከአደጋ ካመለጠ በኋላ ማበረታቻ በጣም ያስፈልገው ነበር፤ ደግሞም በዚያኑ ሌሊት ማበረታቻ አግኝቷል። በመንፈስ መሪነት የተጻፈው ዘገባ እንዲህ ይላል፦ “ጌታ በጳውሎስ አጠገብ ቆሞ እንዲህ አለው፦ ‘አይዞህ፣ አትፍራ! ምክንያቱም በኢየሩሳሌም ስለ እኔ በሚገባ እንደመሠከርክ ሁሉ በሮምም ልትመሠክርልኝ ይገባል።’” (ሥራ 23:11) ኢየሱስ የሰጠው ይህ ማበረታቻ ጳውሎስ በሕይወት እንደሚተርፍ አረጋግጦለታል። ወደ ሮም ሄዶ ስለ ኢየሱስ እንደሚመሠክር ስለተነገረው እዚያ በሰላም እንደሚደርስ ገብቶታል።

“ከመካከላቸው ከ40 በላይ የሚሆኑ ሰዎች አድብተው በእሱ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር እየጠበቁ ነው።”—የሐዋርያት ሥራ 23:21

5 ጳውሎስ ማበረታቻ ያገኘው ልክ በሚያስፈልገው ወቅት ነው። በሚቀጥለው ቀን ከ40 በላይ አይሁዳውያን ወንዶች “በጳውሎስ ላይ በማሴር እሱን እስኪገድሉ ድረስ እህል ውኃ ላለመቅመስ ተማማሉ።” እነዚህ አይሁዳውያን ‘ይህን ሴራ ለመፈጸም መማማላቸው’ ሐዋርያውን ለመግደል ምን ያህል እንደቆረጡ ያሳያል። ሴራቸውን ተግባራዊ ማድረግ ካቃታቸው እርግማን ወይም ክፉ ነገር እንደሚደርስባቸው አምነዋል። (ሥራ 23:12-15) የሰዎቹ ዕቅድ፣ የጳውሎስን ጉዳይ ይበልጥ ማጣራት የፈለጉ በማስመሰል ለተጨማሪ ምርመራ በድጋሚ ወደ ሳንሄድሪን እንዲመጣ ማስደረግ ነበር፤ ይህ ዕቅዳቸውም የካህናት አለቆቹንና የሽማግሌዎቹን ይሁንታ አግኝቷል። የሴራው ጠንሳሾች፣ ጳውሎስ ሳንሄድሪን ከመድረሱ በፊት መንገድ ላይ አድፍጠው ጥቃት ሊሰነዝሩበት አቀዱ።

6. ጳውሎስን ለመግደል የተጠነሰሰው ሴራ የተጋለጠው እንዴት ነው? በዛሬው ጊዜ ያሉ ወጣቶች ከዚህ ዘገባ ምን ትምህርት ማግኘት ይችላሉ?

6 ይሁን እንጂ የጳውሎስ እህት ልጅ ስለዚህ ሴራ ሰማ፤ ጉዳዩንም ለጳውሎስ ነገረው። ጳውሎስ ደግሞ ወጣቱ፣ ሁኔታውን ለሮማዊው ሻለቃ ለቀላውዴዎስ ሉስዮስ እንዲነግረው አደረገ። (ሥራ 23:16-22) ዛሬም በስም እንዳልተጠቀሰው የጳውሎስ እህት ልጅ ያሉ ብዙ ደፋር ወጣቶች አሉ፤ ከራሳቸው ይልቅ የአምላክን ሕዝቦች ደህንነት የሚያስቀድሙ ከመሆኑም ሌላ የአምላክን መንግሥት ለመደገፍ የሚችሉትን ሁሉ ያደርጋሉ፤ ይሖዋ እነዚህን ወጣቶች እንደሚወዳቸው ምንም ጥርጥር የለውም።

7, 8. ቀላውዴዎስ ሉስዮስ ጳውሎስን ከአደጋ ለመጠበቅ ምን ዝግጅት አደረገ?

7 ቀላውዴዎስ ሉስዮስ 1,000 ወታደሮችን የሚያዝዝ ሻለቃ ነው፤ በጳውሎስ ላይ የተጠነሰሰውን ሴራ እንደሰማ 470 ወታደሮች፣ ፈረሰኞችና ባለጦር ወታደሮች እንዲዘጋጁ አዘዘ፤ በዚያው ምሽት ከኢየሩሳሌም በመነሳት ጳውሎስን አጅበው ወደ ቂሳርያ እንዲያደርሱት ትእዛዝ አስተላለፈ። ጳውሎስ እዚያ እንደደረሰ ለአገረ ገዢው ለፊሊክስ ይሰጣል። a ይሁዳን የሚያስተዳድረው የሮም ባለሥልጣን የሚገዛው ከቂሳርያ ሆኖ ነው፤ በቂሳርያ ብዙ አይሁዳውያን ቢኖሩም አብዛኞቹ ነዋሪዎች ግን አሕዛብ ናቸው። በቂሳርያ ያለው ሁኔታ ሥርዓታማና ሰላማዊ ነበር፤ በአንጻሩ ግን ኢየሩሳሌም ሃይማኖታዊ ጽንፈኝነት የገነነባትና ሕዝባዊ ዓመፅ በተደጋጋሚ የሚነሳባት ከተማ ነች። ከዚህም ሌላ ቂሳርያ፣ በይሁዳ የሰፈረው ሠራዊት ጠቅላይ መምሪያ የሚገኝባት ከተማ ነች።

8 የሮማውያን ሕግ በሚያዘው መሠረት ሉስዮስ ጉዳዩን የሚያስረዳ ደብዳቤ ለፊሊክስ ላከ። ሉስዮስ፣ አይሁዳውያን ጳውሎስን “ሊገድሉት” እንደነበር፣ ሮማዊ መሆኑን ሲሰማ ግን ከእጃቸው እንዳዳነው ደብዳቤው ላይ ጠቅሷል። “ለሞት ወይም ለእስር የሚያበቃ” አንድም ጥፋት እንዳላገኘበት፣ ሴራ እንደተጠነሰሰበት ሲያውቅ ግን ወደ እሱ እንደላከው ለፊሊክስ ጻፈለት። አገረ ገዢው ፊሊክስ፣ ከሳሾቹ የሚያቀርቡትን ክስ ሰምቶ በጉዳዩ ላይ ፍርድ እንዲሰጥ ማሰቡንም ሉስዮስ ገልጿል።—ሥራ 23:25-30

9. (ሀ) ጳውሎስ ሮማዊ መሆኑ ያስገኘለት መብት የተጣሰው እንዴት ነው? (ለ) የዜግነት መብታችንን መጠቀም የሚያስፈልገን ምን ዓይነት ሁኔታዎች ሲፈጠሩ ነው?

9 ሉስዮስ የጻፈው ነገር እውነት ነው? ሙሉ በሙሉ እውነት ነው ማለት አይቻልም። አገረ ገዢው ስለ እሱ ጥሩ አመለካከት እንዲኖረው ለማድረግ እየጣረ የነበረ ይመስላል። ሉስዮስ፣ ጳውሎስን ለማዳን የመጣው ሮማዊ መሆኑን ስላወቀ አልነበረም። በተጨማሪም ጳውሎስ “በሁለት ሰንሰለት እንዲታሰር” አድርጎ እንደነበር ከዚያም “እየተገረፈ እንዲመረመር” እንዳዘዘ አልጠቀሰም። (ሥራ 21:30-34፤ 22:24-29) ሉስዮስ፣ ጳውሎስ ሮማዊ መሆኑ ያስገኘለትን መብት ሳያከብርለት ቀርቷል። በዛሬው ጊዜም ሰይጣን ጽንፈኛ ሃይማኖተኞችን በመጠቀም ስደት ያስነሳል፤ በዚህም ምክንያት የዜግነት መብቶቻችን ይጣሱ ይሆናል። ሆኖም ጳውሎስ እንዳደረገው ሁሉ የአምላክ ሕዝቦችም የዜግነት መብታቸውን በመጠቀም የሕግ ከለላ ለማግኘት ጥረት ያደርጋሉ።

“ስለ ራሴ የመከላከያ መልስ የማቀርበው በደስታ ነው” (የሐዋርያት ሥራ 23:35 እስከ 24:21)

10. በጳውሎስ ላይ የትኞቹ ከባድ ክሶች ተሰነዘሩ?

10 ጳውሎስ ከሳሾቹ ከኢየሩሳሌም እስኪመጡ ድረስ በቂሳርያ “[በሄሮድስ] ቤተ መንግሥት ውስጥ በጥበቃ ሥር ሆኖ እንዲቆይ” ተደረገ። (ሥራ 23:35) ከአምስት ቀን በኋላ ሊቀ ካህናቱ ሐናንያ፣ ጠርጡለስ የሚባል ጠበቃና የተወሰኑ ሽማግሌዎች መጡ። ጠርጡለስ በመጀመሪያ፣ ፊሊክስ ለአይሁዳውያን እያደረገ ስላለው ነገር ምስጋና አቀረበ፤ ይህን ያደረገው እሱን ለመሸንገልና በእሱ ለመወደድ ብሎ እንደሆነ ግልጽ ነው። b ከዚያም ጠርጡለስ ወደ ጉዳዩ በመግባት ጳውሎስን እንዲህ ሲል ወነጀለው፦ “ይህ ሰው መቅሰፍት ሆኖብናል፤ በዓለም ባሉት አይሁዳውያን ሁሉ መካከል ዓመፅ ያነሳሳል፤ ከዚህም ሌላ የናዝሬታውያን ኑፋቄ ቀንደኛ መሪ ነው። በዚህ ላይ ደግሞ ቤተ መቅደሱን ለማርከስ ሲሞክር ስላገኘነው ያዝነው።” የተቀሩት አይሁዳውያንም “የተባለው ነገር ሁሉ እውነት መሆኑን በመግለጽ በክሱ ተባበሩ።” (ሥራ 24:5, 6, 9) ዓመፅ ማነሳሳት፣ የአደገኛ ኑፋቄ ቀንደኛ መሪ መሆንና ቤተ መቅደሱን ማርከስ በሞት ሊያስቀጡ የሚችሉ ከባድ ክሶች ናቸው።

11, 12. ጳውሎስ የቀረቡበት ክሶች ትክክል አለመሆናቸውን ያስረዳው እንዴት ነው?

11 አሁን ጳውሎስ እንዲናገር ተፈቀደለት። “ስለ ራሴ የመከላከያ መልስ የማቀርበው በደስታ ነው” በማለት ንግግሩን ጀመረ። ጳውሎስ የቀረቡበት ክሶች በሙሉ ትክክል እንዳልሆኑ ተናገረ። ቤተ መቅደሱን አላረከሰም፤ ዓመፅ ለማነሳሳትም አልሞከረም። እንዲያውም ወደ ኢየሩሳሌም የመጣው “ከብዙ ዓመታት በኋላ” እንደሆነ ገለጸ፤ የመጣውም “ምጽዋት” ለመስጠት እንደሆነ ተናገረ፤ ይህ ምጽዋት በረሃብና በስደት የተነሳ ድህነት ላይ ለወደቁት ክርስቲያኖች የተዋጣ ገንዘብ ነው። ጳውሎስ ወደ ቤተ መቅደሱ ከመግባቱ በፊት “የመንጻት ሥርዓት” እንደፈጸመና “በአምላክም ሆነ በሰው ፊት ንጹሕ ሕሊና [ይዞ] ለመኖር” ሁልጊዜ ጥረት እንደሚያደርግም አስረግጦ ተናገረ።—ሥራ 24:10-13, 16-18

12 ይሁን እንጂ ጳውሎስ፣ ‘እነሱ “ኑፋቄ” ብለው በሚጠሩት መንገድ’ ለአባቶቹ አምላክ ቅዱስ አገልግሎት እንደሚያቀርብ አልካደም። ሆኖም “በሕጉና በነቢያት የተጻፉትን ነገሮች ሁሉ” እንደሚያምን ጠበቅ አድርጎ ተናገረ። ደግሞም ልክ እንደ ከሳሾቹ እሱም “ጻድቃንም ሆኑ ጻድቃን ያልሆኑ ሰዎች ከሞት እንደሚነሱ” ተስፋ እንደሚያደርግ ገለጸ። ከዚያም ጳውሎስ ከሳሾቹን እንዲህ ሲል ተሟገታቸው፦ “እዚህ ያሉት ሰዎች በሳንሄድሪን ሸንጎ ፊት በቀረብኩበት ጊዜ ያገኙብኝ ጥፋት ካለ እነሱ ራሳቸው ይናገሩ፤ በመካከላቸው ቆሜ በነበረበት ጊዜ ድምፄን ከፍ አድርጌ ‘ዛሬ በፊታችሁ ለፍርድ የቀረብኩት በሙታን ትንሣኤ በማመኔ ነው!’ ብዬ ከመናገር በቀር ያደረግኩት ነገር የለም።”—ሥራ 24:14, 15, 20, 21

13-15. በመንግሥት ባለሥልጣናት ፊት በድፍረት በመመሥከር ረገድ ጳውሎስ ምን ምሳሌ ትቶልናል?

13 እኛም በአምልኳችን ምክንያት የመንግሥት ባለሥልጣናት ፊት የምንቀርብበት ጊዜ አለ፤ ረብሻ ፈጣሪዎች፣ ዓመፅ ቆስቋሾች ወይም “የአደገኛ ኑፋቄ” አባላት እንደሆንን በሐሰት ሊከሱን ይችላሉ፤ በዚህ ጊዜ የጳውሎስን ግሩም ምሳሌ መከተል ይጠቅመናል። ጳውሎስ፣ ጠርጡለስ እንዳደረገው ልወደድ ብሎ የሽንገላ ቃላት አልተናገረም። ሐሳቡን የገለጸው በተረጋጋ ሁኔታና በአክብሮት ነው። በዘዴ ሆኖም በሐቀኝነት እውነታውን መሥክሯል። ‘ቤተ መቅደሱን አርክሷል’ ብለው የከሰሱት “ከእስያ አውራጃ የመጡ . . . አይሁዳውያን” እዚህ ችሎት ላይ እንደሌሉ ተናገረ፤ በሕጉ መሠረት ግን እነሱ ራሳቸው እዚያ ተገኝተው ፊት ለፊት ሊከሱት ይገባ እንደነበር ጠቀሰ።—ሥራ 24:18, 19

14 የሚያስገርመው ደግሞ፣ ጳውሎስ ስለሚያምንባቸው ነገሮች ከመመሥከር ወደኋላ አላለም። በትንሣኤ ላይ ስላለው እምነት በድጋሚ በድፍረት ተናግሯል፤ ይሁንና ያኔ ሳንሄድሪን ፊት በቀረበበት ወቅትም ከፍተኛ ሁከት የተነሳው ስለ ትንሣኤ ከጠቀሰ በኋላ እንደሆነ ይታወሳል። (ሥራ 23:6-10) ጳውሎስ የመከላከያ መልስ ሲሰጥ የትንሣኤን ተስፋ ጎላ አድርጎ ገልጿል። ለምን? ስለ ኢየሱስና ስለ ትንሣኤው እየመሠከረ ስለነበረ ነው፤ ይህ ተቃዋሚዎቹ የማይቀበሉት ጉዳይ ነው። (ሥራ 26:6-8, 22, 23) ለነገሩ ውዝግቡ የተነሳውና ለፍርድ የቀረበውም በትንሣኤ በተለይ ደግሞ በኢየሱስና በትንሣኤው በማመኑ ነው።

15 እንደ ጳውሎስ ሁሉ እኛም በድፍረት መመሥከር እንችላለን፤ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የተናገረው የሚከተለው ሐሳብ ለእኛም ብርታት ይሆነናል፦ “በስሜ የተነሳም ሰዎች ሁሉ ይጠሏችኋል። እስከ መጨረሻው የጸና ግን ይድናል” ብሏል። ታዲያ ምን ብለን እንደምንናገር መጨነቅ ይኖርብናል? በጭራሽ! ኢየሱስ እንዲህ የሚል ዋስትና ሰጥቶናል፦ “አሳልፈው ለመስጠት በሚወስዷችሁ ጊዜም ምን እንላለን በማለት አስቀድማችሁ አትጨነቁ፤ ከዚህ ይልቅ በዚያች ሰዓት የሚሰጣችሁን ተናገሩ፤ የሚናገረው መንፈስ ቅዱስ እንጂ እናንተ አይደላችሁምና።”—ማር. 13:9-13

‘ፊሊክስ ፈራ’ (የሐዋርያት ሥራ 24:22-27)

16, 17. (ሀ) ፊሊክስ የጳውሎስን ጉዳይ የያዘው እንዴት ነው? (ለ) ፊሊክስ የፈራው ለምን ሊሆን ይችላል? ይሁንና ጳውሎስን በተደጋጋሚ ያናግረው የነበረው ለምንድን ነው?

16 አገረ ገዢው ፊሊክስ ስለ ክርስትና እምነት ሲሰማ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ዘገባው እንዲህ ይላል፦ “ፊሊክስ ስለ ጌታ መንገድ በሚገባ ያውቅ ስለነበረ ‘የሠራዊቱ ሻለቃ ሉስዮስ ሲመጣ ለጉዳያችሁ ውሳኔ እሰጣለሁ’ በማለት ያቀረቡትን ክስ ለሌላ ጊዜ አስተላለፈው። ከዚያም ጳውሎስ በቁጥጥር ሥር እንዲቆይ፣ ይሁንና መጠነኛ ነፃነት እንዲሰጠው መኮንኑን አዘዘው፤ ደግሞም ወዳጆቹ የሚያስፈልገውን ነገር ለማድረግ ሲመጡ እንዲፈቅድላቸው መመሪያ ሰጠው።”—ሥራ 24:22, 23

17 ከተወሰኑ ቀናት በኋላ ፊሊክስ ከአይሁዳዊት ሚስቱ ከድሩሲላ ጋር ሆኖ ጳውሎስን አስጠራው፤ ከዚያም “በክርስቶስ ኢየሱስ ስለ ማመን ሲናገር አዳመጠው።” (ሥራ 24:24) “ጳውሎስ ስለ ጽድቅ፣ ራስን ስለ መግዛትና ስለሚመጣው ፍርድ ሲናገር ግን ፊሊክስ [ፈራ]”፤ ይህ የሆነው በሕይወቱ ውስጥ ስለፈጸማቸው መጥፎ ነገሮች ሲያስብ ሕሊናው ስለረበሸው ሊሆን ይችላል። በመሆኑም “ለአሁኑ ይበቃል፤ አጋጣሚ ሳገኝ ግን እንደገና አስጠራሃለሁ” በማለት ጳውሎስን አሰናበተው። ከዚያ በኋላም ፊሊክስ ጳውሎስን ብዙ ጊዜ አነጋግሮታል፤ እንዲህ ያደረገው ግን እውነትን መማር ፈልጎ ሳይሆን “ጳውሎስ ጉቦ ይሰጠኛል” ብሎ ተስፋ ስላደረገ ነበር።—ሥራ 24:25, 26

18. ጳውሎስ ለፊሊክስና ለሚስቱ “ስለ ጽድቅ፣ ራስን ስለ መግዛትና ስለሚመጣው ፍርድ” የነገራቸው ለምንድን ነው?

18 ጳውሎስ ለፊሊክስና ለሚስቱ “ስለ ጽድቅ፣ ራስን ስለ መግዛትና ስለሚመጣው ፍርድ” የነገራቸው ለምንድን ነው? እንደምታስታውሰው፣ እነዚህ ሰዎች ‘በክርስቶስ ኢየሱስ ማመን’ ምን እንደሚጠይቅ ማወቅ ፈልገው ነበር። ፊሊክስና ሚስቱ ሥነ ምግባር የጎደለው ሕይወት እንደሚመሩ እንዲሁም ጭካኔና ግፍ እንደሚፈጽሙ ጳውሎስ ያውቃል፤ ስለዚህ የኢየሱስ ተከታዮች ከሚሆኑ ሰዎች ሁሉ ምን እንደሚጠበቅ በግልጽ እያስረዳቸው ነበር። ጳውሎስ የተናገረው ነገር፣ የፊሊክስና የሚስቱ አኗኗር ከአምላክ የጽድቅ መሥፈርቶች ምን ያህል የራቀ እንደሆነ ጠቁሟቸዋል። የሰው ልጅ ለሚያስበው፣ ለሚናገረውና ለሚያደርገው ነገር በአምላክ ፊት ተጠያቂ መሆኑን እንዲገነዘቡ አድርጓቸው መሆን አለበት፤ ፊሊክስ በጳውሎስ ላይ ከሚያስተላልፈው ፍርድ ይልቅ አምላክ በእነሱ ላይ የሚያስተላልፈው ፍርድ ይበልጥ አሳሳቢ መሆኑን እንዲያስተውሉ ሳያደርጋቸው አልቀረም። በእርግጥም ፊሊክስ ‘መፍራቱ’ አያስገርምም!

19, 20. (ሀ) በአገልግሎታችን ላይ ፍላጎት ያላቸው የሚመስሉ ሆኖም የራስ ወዳድነት አካሄዳቸውን መተው የማይፈልጉ ሰዎች ሲያጋጥሙን ምን ማድረግ ይኖርብናል? (ለ) ፊሊክስ ለጳውሎስ የሚያስብ ሰው እንዳልሆነ በምን ማወቅ እንችላለን?

19 እኛም በአገልግሎት ላይ እንደ ፊሊክስ ያሉ ሰዎች ሊያጋጥሙን ይችላሉ። መጀመሪያ ላይ ለእውነት ፍላጎት ያላቸው ይመስሉ ይሆናል፤ ይሁንና ራስ ወዳድነት የሚንጸባረቅበት አካሄዳቸውን መለወጥ አይፈልጉም። እንዲህ ያሉ ሰዎችን ለመርዳት ስንሞክር ጠንቃቃ መሆን ይኖርብናል። ይሁንና ጳውሎስ እንዳደረገው ሁሉ፣ ስለ አምላክ የጽድቅ መሥፈርቶች በዘዴ ልንነግራቸው እንችላለን። ምናልባት እውነት ልባቸውን ሊነካው ይችላል። የኃጢአት መንገዳቸውን የመተው ሐሳብ እንደሌላቸው በግልጽ ካሳዩ ግን እንተዋቸዋለን፤ እውነትን የማወቅ ልባዊ ፍላጎት ያላቸው ሌሎችን ለመፈለግ ጊዜያችንን እንጠቀምበታለን።

20 የፊሊክስን ሁኔታ ከወሰድን እውነተኛ የልብ ዝንባሌው ምን እንደሆነ ከሚከተለው ሐሳብ መረዳት እንችላለን፦ “ሁለት ዓመት ካለፈ በኋላ ፊሊክስ በጶርቅዮስ ፊስጦስ ተተካ፤ በዚህ ጊዜ ፊሊክስ በአይሁዳውያን ዘንድ ተወዳጅነት ማትረፍ ስለፈለገ ጳውሎስን እንደታሰረ ተወው።” (ሥራ 24:27) ፊሊክስ ለጳውሎስ የሚያስብ ሰው አልነበረም። ፊሊክስ “የጌታን መንገድ” የሚከተሉ አማኞች ዓመፅ ወይም አብዮት እንደማይቀሰቅሱ ያውቃል። (ሥራ 19:23) በተጨማሪም ጳውሎስ የሮምን ሕግ በምንም መልኩ አለመጣሱን ተገንዝቧል። ይሁንና “በአይሁዳውያን ዘንድ ተወዳጅነት ማትረፍ ስለፈለገ [ሐዋርያውን] እንደታሰረ ተወው።”

21. ጶርቅዮስ ፊስጦስ አገረ ገዢ ከሆነ በኋላ ጳውሎስ ምን አጋጠመው? እስከ መጨረሻው እንዲጸና የረዳውስ ምን መሆን አለበት?

21 የሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 24 የመጨረሻው ቁጥር እንደሚያሳየው ጶርቅዮስ ፊስጦስ፣ ፊሊክስን ተክቶ አገረ ገዢ በሆነ ጊዜም ጳውሎስ እንደታሰረ ነበር። ከዚህ በኋላ ጳውሎስ በተለያዩ ባለሥልጣናት ፊት መቅረብ አስፈልጎታል። ይህ ደፋር ሐዋርያ “በነገሥታትና በገዢዎች ፊት” ቀርቧል። (ሉቃስ 21:12) ወደፊት እንደምናየው፣ በዘመኑ ለነበረው ከፍተኛ ባለሥልጣን ጭምር ምሥክርነት የሚሰጥበት ጊዜ ይመጣል። በዚህ ሁሉ ግን ጳውሎስ እምነቱ ፈጽሞ አልዋዠቀም። ኢየሱስ “አይዞህ፣ አትፍራ!” ሲል የሰጠው ማበረታቻ እስከ መጨረሻው እንዳጸናው ምንም ጥያቄ የለውም።

a ፊሊክስ—የይሁዳ አገረ ገዢ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

b ጠርጡለስ፣ ለሕዝቡ “ብዙ ሰላም” በማምጣቱ ፊሊክስን አመስግኖታል። ይሁን እንጂ የፊሊክስን የግዛት ዘመን ያህል ሰላም የጠፋበት የሮም አገረ ገዢዎች ዘመን የለም፤ ከፊሊክስ ዘመን የከፋ ብጥብጥ የታየው በሮም ላይ ዓመፅ በተነሳበት ጊዜ ብቻ ነው። ጠርጡለስ፣ ፊሊክስ ላስገኘው መሻሻል አይሁዳውያን “ታላቅ ምስጋና” እንዳቀረቡ መናገሩም ዓይን ያወጣ ውሸት ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ፣ አብዛኞቹ አይሁዳውያን ፊሊክስን ይጠሉት ነበር፤ ፊሊክስ ጨቋኝ ገዢ ከመሆኑም ሌላ ዓመፅን ለማስቆም የሚወስደው እርምጃ ጭካኔ የተሞላበት ነበር።—ሥራ 24:2, 3