በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 28

“እስከ ምድር ዳር ድረስ”

“እስከ ምድር ዳር ድረስ”

የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. የጀመሩትን ሥራ ዛሬ የይሖዋ ምሥክሮች ተረክበው እየሠሩ ነው

1. የጥንቶቹን ክርስቲያኖችና ዛሬ ያሉትን የይሖዋ ምሥክሮች የሚያመሳስሏቸው ነገሮች ምንድን ናቸው?

 የምሥክርነቱን ሥራ በቅንዓት አከናውነዋል። የመንፈስ ቅዱስን እርዳታና አመራር በትሕትና ተቀብለዋል። ስደት ዝም አላሰኛቸውም። አምላክም በእጅጉ ባርኳቸዋል። እነዚህ ሁሉ የጥንቶቹ ክርስቲያኖች የሚታወቁባቸው ነገሮች ናቸው፤ የዛሬዎቹ የይሖዋ ምሥክሮችም በእነዚሁ ነገሮች ይታወቃሉ።

2, 3. የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍን ልዩ የሚያደርገው ምንድን ነው?

2 ቀልብ የሚስቡ በርካታ ክንውኖችን በሚዘግበው የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ እምነትህ እንደተጠናከረ እንተማመናለን! የጥንቶቹን ክርስቲያኖች ታሪክ የያዘ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ ብቸኛው ዘገባ በመሆኑ በዓይነቱ ልዩ መጽሐፍ ነው።

3 በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ በ32 አገሮች፣ በ54 ከተሞችና በ9 ደሴቶች ውስጥ የሚኖሩ የ95 ግለሰቦች ስም ተጠቅሷል። ተራ ሰዎች፣ ኩሩ ፖለቲከኞች፣ ትዕቢተኛ ሃይማኖተኞች እንዲሁም ጨካኝ አሳዳጆች ያደረጓቸውን ነገሮች የሚያወሳ ቀልብ የሚስብ ዘገባ ይዟል። ከምንም በላይ ግን የመጀመሪያው መቶ ዘመን ወንድሞችህንና እህቶችህን ታሪክ ይዟል፤ የኑሮ ውጣ ውረዶችን እየተጋፈጡም ምሥራቹን በቅንዓት በመስበክ ያከናወኑትን ሥራ ያትታል።

4. ሐዋርያው ጳውሎስንና ጣቢታን ጨምሮ የጥንት ታማኝ ምሥክሮች ቅርባችን ያሉ ያህል የሚሰማን ለምንድን ነው?

4 ቀናተኞቹ ሐዋርያት ጴጥሮስና ጳውሎስ፣ ተወዳጁ ሐኪም ሉቃስ፣ ለጋሱ በርናባስ፣ ደፋሩ እስጢፋኖስ፣ ደጓ ጣቢታ፣ እንግዳ ተቀባይዋ ሊዲያና ሌሎች በርካታ ታማኝ ምሥክሮች አስደናቂ ተግባሮችን አከናውነው ካለፉ 2,000 የሚያህሉ ዓመታት ተቆጥረዋል። ይሁንና ዛሬ ያሉ ያህል ለእኛ ቅርብ ናቸው። ለምን? ለእነሱ የተሰጠው ደቀ መዛሙርት የማድረግ ተልእኮ ለእኛም ስለተሰጠን ነው። (ማቴ. 28:19, 20) በዚህ ሥራ መካፈል መቻላችን እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው!

“እስከ ምድር ዳር ድረስ . . .”—የሐዋርያት ሥራ 1:8

5. የጥንቶቹ የኢየሱስ ተከታዮች የተሰጣቸውን ተልእኮ መፈጸም የጀመሩት ከየት ነው?

5 እስቲ ኢየሱስ ለተከታዮቹ የሰጠውን ተልእኮ መለስ ብለህ አስብ። “መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በሚወርድበት ጊዜ ኃይል ትቀበላላችሁ፤ በኢየሩሳሌም፣ በመላው ይሁዳና በሰማርያ እንዲሁም እስከ ምድር ዳር ድረስ ምሥክሮቼ ትሆናላችሁ” ብሏቸዋል። (ሥራ 1:8) በመጀመሪያ ደቀ መዛሙርቱ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል “በኢየሩሳሌም” ምሥክርነት ሰጡ። (ሥራ 1:1 እስከ 8:3) ቀጥሎም በመንፈስ አመራር “በመላው ይሁዳና በሰማርያ” መሠከሩ። (ሥራ 8:4 እስከ 13:3) ከዚያም ምሥራቹን “እስከ ምድር ዳር ድረስ” መስበክ ጀመሩ።—ሥራ 13:4 እስከ 28:31

6, 7. ከአገልግሎታችን ጋር በተያያዘ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከነበሩ ወንድሞቻችን ይልቅ እኛ ምን የተሻለ አጋጣሚ አለን?

6 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት የእምነት ባልንጀሮችህ፣ በምሥክርነቱ ሥራ የሚጠቀሙበት ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ አልነበራቸውም። የማቴዎስ ወንጌል ቢያንስ እስከ 41 ዓ.ም. ድረስ አልተዘጋጀም ነበር። የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ በ61 ዓ.ም. ተጽፎ ከመጠናቀቁ በፊት የተጻፉት የጳውሎስ ደብዳቤዎችም የተወሰኑ ናቸው። በመሆኑም የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ የያዘ የግል ቅጂ ወይም ፍላጎት ላሳዩ ሰዎች የሚሰጧቸው ጽሑፎች አልነበሯቸውም። አይሁዳውያን ክርስቲያኖች፣ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ከመሆናቸው በፊት የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ምኩራብ ውስጥ ሲነበቡ የመስማት አጋጣሚ ነበራቸው። (2 ቆሮ. 3:14-16) ያም ሆኖ እነሱም ትጉ ተማሪዎች መሆን ይጠበቅባቸው ነበር፤ ምክንያቱም ጥቅሶችን በቃላቸው መጥቀስ ሊያስፈልጋቸው ይችላል።

7 ዛሬ አብዛኞቻችን የግላችን መጽሐፍ ቅዱስና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ እጅግ በርካታ ጽሑፎች አሉን። በ240 አገሮች ውስጥ በብዙ ቋንቋዎች ምሥራቹን በማወጅ ደቀ መዛሙርት እያደረግን ነው።

ከመንፈስ ቅዱስ ኃይል ማግኘት

8, 9. (ሀ) መንፈስ ቅዱስ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ምን እንዲያደርጉ አስችሏቸዋል? (ለ) ታማኙ ባሪያ በአምላክ መንፈስ እርዳታ ምን እያዘጋጀ ነው?

8 ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የስብከት ተልእኮ ሲሰጣቸው “መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በሚወርድበት ጊዜ ኃይል ትቀበላላችሁ” ብሏቸው ነበር። የኢየሱስ ተከታዮች የአምላክ መንፈስ ወይም ኃይል ስለሚመራቸው ውሎ አድሮ በመላው ምድር ምሥክርነት ይሰጣሉ። ጴጥሮስና ጳውሎስ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት በሽተኞችን ፈውሰዋል፣ አጋንንትን አስወጥተዋል አልፎ ተርፎም የሞቱትን አስነስተዋል! ይሁን እንጂ መንፈስ ቅዱስ ኃይል የሚሰጣቸው ከዚህም ለላቀ ዓላማ ነው። ይህም የዘላለም ሕይወት የሚያስገኘውን ትክክለኛ እውቀት ለሰዎች ማካፈል ነው፤ ሐዋርያትና ሌሎች ደቀ መዛሙርት ይህን ዓላማ ማሳካት የቻሉት በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ነው።—ዮሐ. 17:3

9 በ33 ዓ.ም. በተከበረው የጴንጤቆስጤ በዓል ላይ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት “[መንፈስ] እንዲናገሩ ባስቻላቸው መሠረት በተለያዩ ቋንቋዎች ይናገሩ ጀመር።” በውጤቱም “ስለ አምላክ ታላቅ ሥራ” ምሥክርነት መስጠት ችለዋል። (ሥራ 2:1-4, 11) በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ ቋንቋዎች የመናገር ተአምራዊ ችሎታ የለንም። ይሁን እንጂ ታማኙ ባሪያ በአምላክ መንፈስ እርዳታ በብዙ ቋንቋዎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን እያዘጋጀ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ በየወሩ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔት ቅጂዎች ይታተማሉ፤ jw.org በተሰኘው ድረ ገጻችን ላይ ደግሞ ከ1,000 በሚበልጡ ቋንቋዎች የተዘጋጁ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችና ቪዲዮዎች ይገኛሉ። እነዚህ ሁሉ ጽሑፎች “ስለ አምላክ ታላቅ ሥራ” ለሁሉም ብሔራት፣ ነገዶችና ቋንቋዎች እንድናውጅ ያስችሉናል።—ራእይ 7:9

10. ከ1989 ወዲህ ከመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ጋር በተያያዘ ምን ተከናውኗል?

10 ከ1989 ወዲህ ታማኙ ባሪያ፣ አዲስ ዓለም ትርጉም በበርካታ ቋንቋዎች እንዲዘጋጅ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው። ይህ መጽሐፍ ቅዱስ እስካሁን ድረስ ከ200 በሚበልጡ ቋንቋዎች ተተርጉሟል፤ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ቅጂዎች ታትመዋል፤ ወደፊት ደግሞ ከዚህም በላይ እንደሚሆን ይጠበቃል። እነዚህ ጥረቶች ሊሳኩ የቻሉት በአምላክና በቅዱስ መንፈሱ እርዳታ ብቻ ነው።

11. የይሖዋ ምሥክሮች ከሚያከናውኑት የትርጉም ሥራ ጋር በተያያዘ ምን ተከናውኗል?

11 ከ150 በሚበልጡ አገሮች ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ክርስቲያን ፈቃደኛ ሠራተኞች የትርጉም ሥራ እያከናወኑ ነው። ይህ ሊያስገርመን አይገባም፤ ምክንያቱም በመንፈስ ቅዱስ እየተመራ ስለ ይሖዋ አምላክ፣ ስለ መሲሐዊው ንጉሥና በሰማይ ስለተቋቋመው መንግሥት በዓለም ዙሪያ ‘በሚገባ የሚመሠክር’ ሌላ ድርጅት በምድር ላይ የለም።—ሥራ 28:23

12. ጳውሎስም ሆነ ሌሎች ክርስቲያኖች የምሥክርነቱን ሥራ ማከናወን የቻሉት እንዴት ነው?

12 ጳውሎስ በጵስድያ በምትገኘው በአንጾኪያ ለአይሁዳውያንም ሆነ ለአሕዛብ በመሠከረ ጊዜ “ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው ሁሉ አማኞች [ሆነዋል]።” (ሥራ 13:48) በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ መደምደሚያ ላይ ከጳውሎስ ጋር የምንሰነባበተው “ያለምንም እንቅፋት በታላቅ የመናገር ነፃነት ስለ አምላክ መንግሥት [እየሰበከ]” ነው። (ሥራ 28:31) ሐዋርያው የሰበከው የት ነው? የዓለም ኃያል መንግሥት ዋና ከተማ በሆነችው በሮም ነዋ! አዎ፣ የጥንቶቹ የኢየሱስ ተከታዮች ንግግር በማቅረብም ይሁን በሌላ መንገድ የተሟላ ምሥክርነት መስጠት የቻሉት በመንፈስ ቅዱስ እርዳታና አመራር ነው።

ስደት እያለም መጽናት

13. ስደት ሲያጋጥመን መጸለይ የሚኖርብን ለምንድን ነው?

13 የጥንቶቹ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ስደት ሲደርስባቸው ድፍረት እንዲሰጣቸው ይሖዋን ተማጽነዋል። ውጤቱስ ምን ነበር? በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ፤ የአምላክን ቃል በድፍረት ለመናገርም ኃይል አገኙ። (ሥራ 4:18-31) እኛም በስደት ጊዜ መመሥከራችንን ለመቀጠል የሚያስችለን ጥበብና ጥንካሬ ለማግኘት እንጸልያለን። (ያዕ. 1:2-8) የአምላክ በረከትና የመንፈሱ እርዳታ ስለማይለየን መንግሥቱን ማወጃችንን እንቀጥላለን። ከባድ ተቃውሞም ሆነ መራራ ስደት የስብከቱን ሥራ ሊያስቆመው አይችልም። ስደት ሲደርስብን ምሥራቹን ማወጃችንን ለመቀጠል የሚያስችለንን መንፈስ ቅዱስ፣ ጥበብና ድፍረት እንድናገኝ መጸለይ ይኖርብናል።—ሉቃስ 11:13

14, 15. (ሀ) “ከእስጢፋኖስ ሞት በኋላ በተቀሰቀሰው ስደት” ሳቢያ ምን ተከስቷል? (ለ) በእኛ ዘመን በሳይቤሪያ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች እውነትን የሰሙት እንዴት ነው?

14 እስጢፋኖስ በጠላቶቹ እጅ ከመገደሉ በፊት ድፍረት የተሞላበት ምሥክርነት ሰጥቷል። (ሥራ 6:5፤ 7:54-60) እሱ መገደሉን ተከትሎ በተከሰተው “ከባድ ስደት” የተነሳ ከሐዋርያት በስተቀር ሁሉም ደቀ መዛሙርት በመላው ይሁዳና በሰማርያ ተበታተኑ። ይሁን እንጂ ስደቱ የምሥክርነቱን ሥራ አላስቆመውም። ፊልጶስ ወደ ሰማርያ ሄዶ “ስለ ክርስቶስ ይሰብክላቸው ጀመር”፤ ይህም ጥሩ ውጤት አስገኝቷል። (ሥራ 8:1-8, 14, 15, 25) በተጨማሪም ዘገባው እንዲህ ይላል፦ “ከእስጢፋኖስ ሞት በኋላ በተቀሰቀሰው ስደት የተነሳ የተበተኑት ደቀ መዛሙርት እስከ ፊንቄ፣ ቆጵሮስና አንጾኪያ ድረስ ሄዱ፤ ቃሉን ይናገሩ የነበረው ግን ለአይሁዳውያን ብቻ ነበር። ይሁን እንጂ ከእነሱ መካከል የቆጵሮስና የቀሬና ሰዎች የሆኑ አንዳንዶች ወደ አንጾኪያ መጥተው ግሪክኛ ተናጋሪ የሆኑ ሰዎችን በማነጋገር የጌታ ኢየሱስን ምሥራች ይሰብኩላቸው ጀመር።” (ሥራ 11:19, 20) አዎ፣ በዚያን ጊዜ የተነሳው ስደት የመንግሥቱ መልእክት እንዲዳረስ ምክንያት ሆኗል።

15 በእኛ ዘመንም በቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት ውስጥ ተመሳሳይ ነገር ተከስቷል። በተለይ በ1950ዎቹ ዓመታት በሺዎች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች በግዞት ወደ ሳይቤሪያ ተወስደው ነበር። ምሥክሮቹ በተለያዩ ቦታዎች እንዲሰፍሩ ስለተደረገ ምሥራቹ በዚያ ሰፊ ምድር ሊዳረስ ችሏል። ይህን ያህል ብዛት ያላቸው የይሖዋ ምሥክሮች በራሳቸው እስከ 10,000 ኪሎ ሜትር ርቀት ተጉዘው ምሥራቹን እንስበክ ቢሉ ለዚህ ሁሉ የሚበቃ ገንዘብ ከየት ያገኙ ነበር? አሁን ግን መንግሥት በራሱ ወጪ ልኳቸዋል። አንድ ወንድም እንዳለው “በሳይቤሪያ የሚኖሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ልበ ቅን ሰዎች እውነትን እንዲያውቁ ያደረጉት ራሳቸው ባለሥልጣናቱ ናቸው።”

ይሖዋ አብዝቶ ባርኳቸዋል

16, 17. የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ምሥክርነት የመስጠቱን ሥራ ይሖዋ እንደባረከው የሚያሳይ ምን ማስረጃ ይዟል?

16 ይሖዋ የጥንቶቹን ክርስቲያኖች እንደባረካቸው ምንም ጥያቄ የለውም። ጳውሎስና ሌሎች ክርስቲያኖች ተክለዋል፣ አጠጥተዋል፤ “ያሳደገው ግን አምላክ ነው።” (1 ቆሮ. 3:5, 6) በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ሪፖርት የተደረገው እድገት ይሖዋ የምሥክርነቱን ሥራ እንደባረከው ያረጋግጣል። ለአብነት ያህል፣ “የአምላክ ቃል መስፋፋቱን ቀጠለ፤ በኢየሩሳሌምም የደቀ መዛሙርቱ ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ ሄደ” ይላል። (ሥራ 6:7) የምሥክርነቱ ሥራ እየተስፋፋ ሲሄድ “በይሁዳ፣ በገሊላና በሰማርያ ያለው ጉባኤ ሁሉ ሰላም አገኘ፤ በእምነትም እየጠነከረ ሄደ፤ መላው ጉባኤ ይሖዋን በመፍራትና መንፈስ ቅዱስ ከሚሰጠው ማጽናኛ ጋር በመስማማት ይኖር ስለነበር በቁጥር እየበዛ ሄደ።”—ሥራ 9:31

17 በሶርያ በምትገኘው አንጾኪያ፣ ደፋር ምሥክሮች ለአይሁዳውያንም ሆነ ለግሪክኛ ተናጋሪዎች እውነትን ሰብከዋል። “የይሖዋም እጅ ከእነሱ ጋር ነበር፤ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎችም አማኝ በመሆን ጌታን መከተል ጀመሩ” ሲል ዘገባው ይገልጻል። (ሥራ 11:21) በዚች ከተማ የታየውን ተጨማሪ እድገት በተመለከተ ደግሞ “የይሖዋ ቃል . . . እየተስፋፋ ሄደ፤ ብዙ ሰዎችም አማኞች ሆኑ” የሚል ዘገባ እናነባለን። (ሥራ 12:24) በተጨማሪም ጳውሎስና ሌሎች ክርስቲያኖች በአሕዛብ መካከል የስብከቱን ሥራ ሲያጧጡፉት “የይሖዋ ቃል በኃይል እየተስፋፋና እያሸነፈ ሄደ።”—ሥራ 19:20

18, 19. (ሀ) “የይሖዋ እጅ” ከእኛ ጋር መሆኑን እንዴት እናውቃለን? (ለ) ይሖዋ ሕዝቡን እንደሚደግፍ የሚያሳይ ምሳሌ ተናገር።

18 ዛሬም “የይሖዋ እጅ” ከእኛ ጋር እንደሆነ ምንም ጥያቄ የለውም። በዚህም ምክንያት ብዙዎች አማኞች እየሆኑና ራሳቸውን ለአምላክ መወሰናቸውን በጥምቀት እያሳዩ ነው። በተጨማሪም ጠንካራ ተቃውሞ አንዳንድ ጊዜም ኃይለኛ ስደት እያለም እንደ ጳውሎስና እንደ ሌሎቹ የጥንት ክርስቲያኖች አገልግሎታችንን በተሳካ መንገድ ማከናወን የቻልነው የአምላክ እርዳታና በረከት ስላልተለየን ብቻ ነው። (ሥራ 14:19-21) ይሖዋ አምላክ እኛን ለመርዳት ሁልጊዜ ዝግጁ ነው። “ዘላለማዊ ክንዶቹ” ምንም ዓይነት መከራ ቢያጋጥመን ምንጊዜም ይደግፉናል። (ዘዳ. 33:27) ደግሞም ይሖዋ ለታላቅ ስሙ ሲል ሕዝቡን ፈጽሞ እንደማይጥል እናስታውስ።—1 ሳሙ. 12:22፤ መዝ. 94:14

19 አንድ ምሳሌ እናንሳ፤ ወንድም ሃራልት አፕት መመሥከሩን በመቀጠሉ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ናዚዎች ወደ ዛክሰንሃውዘን ማጎሪያ ካምፕ ላኩት። ግንቦት 1942 ጌስታፖዎች ባለቤቱ ኤልዛ ወደምትኖርበት ቤት ሄደው ትንሿን ልጃቸውን ቀምተው ወሰዱ፤ ኤልዛን ደግሞ አሰሯት። ከዚያ በኋላ በተለያዩ ካምፖች ውስጥ አስረዋታል። እህት ኤልዛ እንዲህ ብላለች፦ “በጀርመን ባሉ ማጎሪያ ካምፖች በቆየሁባቸው ዓመታት አንድ ትልቅ ትምህርት አግኝቻለሁ። ይህም አንድ ሰው በከባድ ፈተና ውስጥ ሲያልፍ የይሖዋ መንፈስ በእጅጉ እንደሚያጠናክረው ነው! ከመታሰሬ በፊት አንዲት እህት የጻፈችውን ደብዳቤ አንብቤ ነበር፤ ‘እጅግ ከባድ በሆነ ፈተና ውስጥ የይሖዋ መንፈስ የመረጋጋት ስሜት እንዲያድርባችሁ ያደርጋል’ ብላ ነበር። በወቅቱ ትንሽ ሳታጋንን አትቀርም ብዬ አስቤ ነበር። ሆኖም እኔ ራሴ በተለያዩ መከራዎች ውስጥ ሳልፍ የተናገረችው ነገር እውነት መሆኑን ተገነዘብኩ። በእርግጥም የሚሰማችሁ እንዲህ ነው። እንዲህ ያለ ሁኔታ ካላጋጠማችሁ በስተቀር ይህን መረዳት ይከብዳችኋል። ይሁንና እኔ ራሴ የተሰማኝ እንዲሁ ነበር።”

በሚገባ መመሥከራችሁን ቀጥሉ!

20. ጳውሎስ የቁም እስረኛ ሳለ ምን ያደርግ ነበር? ይህስ ለአንዳንድ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ምን ማበረታቻ ይዟል?

20 የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ የሚደመደመው ጳውሎስ በቅንዓት “ስለ አምላክ መንግሥት ይሰብክ” እንደነበር በመግለጽ ነው። (ሥራ 28:31) በወቅቱ የቁም እስረኛ ስለነበር ሮም ውስጥ ከቤት ወደ ቤት እየሄደ የመመሥከር ነፃነት አልነበረውም። ይሁንና ወደ እሱ ለሚመጡ ሰዎች ሁሉ ይመሠክር ነበር። በዛሬው ጊዜ አንዳንድ ውድ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ከቤት መውጣት አይችሉም፤ በዕድሜ መግፋት፣ በበሽታ ወይም በአካል ጉዳት የተነሳ የአልጋ ቁራኛ ናቸው አሊያም የሚኖሩት እንክብካቤ በሚሰጥባቸው ተቋማት ውስጥ ነው። ሆኖም ለአምላክ ያላቸው ፍቅርና ምሥክርነት ለመስጠት ያላቸው ፍላጎት እንደ ወትሮው ጠንካራ ነው። እነዚህን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በጸሎታችን እናስባቸው፤ የሰማዩ አባታችን ስለ እሱና ስለ ዓላማዎቹ ለማወቅ ከሚጓጉ ሰዎች ጋር እንዲያገናኛቸው እንለምነው።

21. የምሥክርነቱን ሥራ በጥድፊያ ስሜት ማከናወን ያለብን ለምንድን ነው?

21 አብዛኞቻችን ከቤት ወደ ቤት ማገልገል እንዲሁም ደቀ መዛሙርት ማድረግ በሚቻልባቸው ሌሎች የአገልግሎት ዘርፎች መካፈል እንችላለን። እንግዲያው ሁላችንም የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች እንድንሆን የተሰጠንን ተልእኮ ለመወጣት እንጣር፤ “እስከ ምድር ዳር ድረስ” በሚከናወነው የምሥክርነት ሥራ የበኩላችንን ድርሻ ለማበርከት የምንችለውን ሁሉ እናድርግ። ይህን ሥራ በጥድፊያ ስሜት ማከናወን ይኖርብናል፤ ምክንያቱም የክርስቶስን መገኘት የሚያሳየው “ምልክት” በግልጽ እየታየ ነው። (ማቴ. 24:3-14) ጊዜያችንን ማባከን አይኖርብንም። አሁን ‘የጌታ ሥራ የበዛልን’ ጊዜ ነው።—1 ቆሮ. 15:58

22. የይሖዋን ቀን በምንጠባበቅበት ጊዜ ቁርጥ ውሳኔያችን ምን መሆን ይኖርበታል?

22 “ታላቁና የሚያስፈራው የይሖዋ ቀን ከመምጣቱ በፊት” በድፍረትና በታማኝነት መመሥከራችንን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። (ኢዩ. 2:31) “ቃሉን በታላቅ ጉጉት ተቀበሉ” እንደተባለላቸው የቤርያ ሰዎች ያሉ ገና ብዙ ቅኖች አሉ። (ሥራ 17:10, 11) እንግዲያው ሥራው እስኪጠናቀቅ ድረስ መመሥከራችንን እንቀጥል፤ ያን ጊዜ “ጎበዝ፣ አንተ ጥሩና ታማኝ ባሪያ!” የሚባልልን ዓይነት ሰዎች እንሆናለን። (ማቴ. 25:23) ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ በቅንዓት የበኩላችንን ከተወጣንና ለይሖዋ ታማኝ ከሆንን፣ ስለ አምላክ መንግሥት ‘በሚገባ የመመሥከር’ ታላቅ ክብር በማግኘታችን ለዘላለም እንደሰታለን!