በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 25

“ወደ ቄሳር ይግባኝ ብያለሁ!”

“ወደ ቄሳር ይግባኝ ብያለሁ!”

ጳውሎስ ለምሥራቹ ጥብቅና በመቆም ምሳሌ ትቷል

በሐዋርያት ሥራ 25:1 እስከ 26:32 ላይ የተመሠረተ

1, 2. (ሀ) ጳውሎስ በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ይገኛል? (ለ) ጳውሎስ ወደ ቄሳር ይግባኝ ማለቱ ምን ጥያቄ ያስነሳል?

 ጳውሎስ አሁንም ቂሳርያ ውስጥ በወታደሮች እየተጠበቀ ነው። ከሁለት ዓመት በፊት ወደ ይሁዳ በተመለሰበት ወቅት አይሁዳውያን እሱን ለመግደል ሞክረው ነበር፤ በጥቂት ቀናት ውስጥ ቢያንስ ሦስት ጊዜ የግድያ ሙከራ ተደርጎበታል። (ሥራ 21:27-36፤ 23:10, 12-15, 27) ጠላቶቹ እስካሁን አልተሳካላቸውም፤ ሆኖም እንዲህ በዋዛ ተስፋ የሚቆርጡ አይደሉም። ጳውሎስ በዚህ አያያዝ በእነሱ እጅ ሊወድቅ እንደሚችል ሲረዳ፣ ሮማዊውን አገረ ገዢ ፊስጦስን “ወደ ቄሳር ይግባኝ ብያለሁ!” አለው።—ሥራ 25:11

2 ይሖዋ፣ ጳውሎስ ለሮም ንጉሠ ነገሥት ይግባኝ ለማለት ያደረገውን ውሳኔ ደግፏል? የዚህን ጥያቄ መልስ ማወቃችን ይጠቅመናል፤ ምክንያቱም እኛም በዚህ የፍጻሜ ዘመን ስለ አምላክ መንግሥት በሚገባ ለመመሥከር እየጣርን ነው። ‘ለምሥራቹ በመሟገትና በሕግ የጸና እንዲሆን በማድረግ’ ረገድ ከጳውሎስ የምናገኘው ትምህርት ሊኖር ይችላል።—ፊልጵ. 1:7

“የፍርድ ወንበር ፊት ቆሜአለሁ” (የሐዋርያት ሥራ 25:1-12)

3, 4. (ሀ) አይሁዳውያኑ ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲመጣ የጠየቁት ለምንድን ነው? ጳውሎስ ከሞት ያመለጠውስ እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ ጳውሎስን እንዳጠነከረው ሁሉ በዚህ ዘመን ያሉ አገልጋዮቹንም የሚያበረታቸው እንዴት ነው?

3 ሮማዊው ፊስጦስ የይሁዳ አገረ ገዢ ከሆነ ከሦስት ቀን በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ። a እዚያም የካህናት አለቆችና የታወቁ አይሁዳውያን በጳውሎስ ላይ ያቀረቧቸውን ከባድ ክሶች አዳመጠ። እነዚህ ሰዎች፣ አዲሱ አገረ ገዢ ከእነሱም ሆነ ከአይሁድ ማኅበረሰብ ጋር ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖረው የበላዮቹ እንደሚጠብቁበት ያውቃሉ። በመሆኑም ፊስጦስን አንድ ውለታ እንዲውልላቸው ጠየቁት፦ ጳውሎስን ወደ ኢየሩሳሌም እንዲያመጣውና በዚያ እንዲዳኘው። ይሁን እንጂ ከጥያቄያቸው በስተ ጀርባ አንድ ስውር ደባ አለ። እነዚህ የጳውሎስ ጠላቶች፣ ሐዋርያው ከቂሳርያ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ መንገድ ላይ አድብተው ሊገድሉት ሴራ ጠንስሰዋል። ፊስጦስ ግን ጥያቄያቸውን አልተቀበለውም፤ “ከእናንተ መካከል ሥልጣን ያላቸው ከእኔ ጋር [ወደ ቂሳርያ] ይውረዱና ሰውየው ያጠፋው ነገር ካለ ይክሰሱት” አላቸው። (ሥራ 25:5) ጳውሎስ አሁንም ከሞት አመለጠ።

4 ጳውሎስ ለፍርድ በቀረበባቸው ጊዜያት ሁሉ ይሖዋ በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ኃይል ሰጥቶታል። ኢየሱስ በራእይ ተገልጦለት “አይዞህ፣ አትፍራ!” ብሎት እንደነበር አስታውስ። (ሥራ 23:11) በዛሬው ጊዜ ያሉ የአምላክ አገልጋዮችም እንቅፋቶች ያጋጥሟቸዋል፤ ዛቻም ይሰነዘርባቸዋል። ይሖዋ ከእያንዳንዱ ችግር አይጋርደንም፤ ነገር ግን በጽናት ለመቀጠል የሚያስችለንን ጥበብና ብርታት ይሰጠናል። አፍቃሪው አምላካችን “ከሰብዓዊ ኃይል በላይ [የሆነ] ኃይል” እንደሚሰጠን ምንጊዜም መተማመን እንችላለን።—2 ቆሮ. 4:7

5. ፊስጦስ የጳውሎስን ጉዳይ የያዘው እንዴት ነበር?

5 ከተወሰኑ ቀናት በኋላ ፊስጦስ በቂሳርያ ‘በፍርድ ወንበር ላይ ተቀመጠ።’ b ጳውሎስና ከሳሾቹ ፊቱ ቆመዋል። ጳውሎስ ለቀረበበት መሠረተ ቢስ ክስ እንዲህ ሲል መልስ ሰጠ፦ “እኔ በአይሁዳውያን ሕግ ላይም ሆነ በቤተ መቅደሱ ወይም በቄሳር ላይ ምንም የፈጸምኩት በደል የለም።” ሐዋርያው ንጹሕ ሰው በመሆኑ በነፃ መለቀቅ ይገባዋል። ፊስጦስ ምን ውሳኔ ያስተላልፍ ይሆን? በአይሁዳውያን ዘንድ መወደድ ስለፈለገ ጳውሎስን “ወደ ኢየሩሳሌም ወጥተህ ስለዚህ ጉዳይ እዚያ እኔ ባለሁበት መዳኘት ትፈልጋለህ?” ሲል ጠየቀው። (ሥራ 25:6-9) እንዴት ያለ ፌዝ ነው! ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም ከተመለሰ ከሳሾቹ ሊዳኙት ነው፤ ይህ ከሆነ ደግሞ እንደሚገደል የታወቀ ነው። በዚህ ወቅት ፊስጦስ የፍትሕ ነገር ያሳሰበው አይመስልም፤ ለፖለቲካው የሚጠቅመውን ነገር ማድረግ የፈለገ ይመስላል። ከዓመታት በፊት፣ አገረ ገዢው ጳንጥዮስ ጲላጦስም ተመሳሳይ ፍርደ ገምድልነት ታይቶበታል፤ ያኔ ግን ይህን ግፍ የሠራው ከጳውሎስ በላይ ትልቅ ቦታ በሚሰጠው እስረኛ ላይ ነበር። (ዮሐ. 19:12-16) በዛሬው ጊዜ ያሉ ዳኞችም በፖለቲካዊ ጫና ሊሸነፉ ይችላሉ። በመሆኑም ፍርድ ቤቶች የአምላክን ሕዝቦች የሚመለከቱ ጉዳዮችን በሚያዩበት ጊዜ ማስረጃዎችን ያላገናዘበ ውሳኔ ቢያስተላልፉ መገረም አይኖርብንም።

6, 7. ጳውሎስ ወደ ቄሳር ይግባኝ ያለው ለምንድን ነው? በዚህ ረገድስ ዛሬ ላሉ እውነተኛ ክርስቲያኖች ምን አርዓያ ትቶላቸዋል?

6 ፊስጦስ አይሁዳውያኑን ለማስደሰት ያለው ፍላጎት የጳውሎስን ሕይወት አደጋ ላይ ጥሎታል። ስለዚህ ጳውሎስ የሮም ዜጋ መሆኑ ባስገኘለት መብት ለመጠቀም መረጠ። ፊስጦስን እንዲህ አለው፦ “እኔ ልዳኝበት በሚገባኝ በቄሳር የፍርድ ወንበር ፊት ቆሜአለሁ። አንተ ራስህ በሚገባ እንደተገነዘብከው በአይሁዳውያን ላይ የፈጸምኩት ምንም በደል የለም። . . . ወደ ቄሳር ይግባኝ ብያለሁ!” አንዴ ይግባኝ ከተባለ ደግሞ በአብዛኛው ሐሳብን መቀየር አይቻልም። ፊስጦስ “ወደ ቄሳር ይግባኝ ስላልክ ወደ ቄሳር ትሄዳለህ” የሚል መልስ መስጠቱ ይህን ያሳያል። (ሥራ 25:10-12) ጳውሎስ የበላይ ለሆነው የሕግ አካል ይግባኝ ማለቱ ዛሬ ላሉ እውነተኛ ክርስቲያኖችም አርዓያ የሚሆን ነው። ተቃዋሚዎች “በሕግ ስም ችግር ለመፍጠር” ጥረት በሚያደርጉበት ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች የሕግ አማራጮችን በመጠቀም ለምሥራቹ ጥብቅና ይቆማሉ። cመዝ. 94:20

7 ጳውሎስ ባልፈጸመው ወንጀል ከሁለት ዓመት በላይ በእስር ቆይቷል፤ አሁን ግን ጉዳዩ በሮም እንዲታይለት ለማድረግ አጋጣሚ ተሰጠው። ወደዚያ ከማቅናቱ በፊት ግን አንድ ሌላ ገዢ እሱን ማግኘት ፈለገ።

አግባብ ያልሆነ ፍርድ ሲፈረድብን ይግባኝ እንላለን

“አልታዘዝም አላልኩም” (የሐዋርያት ሥራ 25:13 እስከ 26:23)

8, 9. ንጉሥ አግሪጳ ወደ ቂሳርያ የመጣው ለምንድን ነው?

8 ጳውሎስ ፊስጦስ ፊት ቀርቦ ወደ ቄሳር ይግባኝ ካለ የተወሰኑ ቀናት አልፈዋል፤ ይህ በእንዲህ እያለ፣ ንጉሥ አግሪጳና እህቱ በርኒቄ ለአዲሱ አገረ ገዢ “ክብር ይፋዊ ጉብኝት” አደረጉ። d በሮማውያን ዘመን ባለሥልጣናት አዲስ ለተሾመ አገረ ገዢ እንዲህ ዓይነት ጉብኝት የማድረግ ልማድ ነበራቸው። አግሪጳ፣ ፊስጦስ ላገኘው ሹመት ደስታውን በመግለጽ ጥሩ ግንኙነት እንዲኖራቸው ለማድረግ የሞከረው ወዳጅነቱ ወደፊት የሚያስገኘውን ፖለቲካዊ ጥቅም በማሰብ ሊሆን ይችላል።—ሥራ 25:13

9 ፊስጦስ የጳውሎስን ጉዳይ ለንጉሥ አግሪጳ አነሳለት፤ በመሆኑም ንጉሡ ስለ እሱ ለማወቅ ጓጓ። በማግስቱ ሁለቱ ገዢዎች በፍርድ ወንበር ላይ ተቀመጡ። አግሪጳና ፊስጦስ ከፍተኛ ሥልጣን እንዳላቸው የታወቀ ነው፤ ወደ ቦታው የሄዱትም በታላቅ ክብር ደምቀው ነበር፤ ከዚህ ሁሉ ይበልጥ የሚያስደምመው ግን በፊታቸው የቆመው እስረኛ የተናገረው ነገር ነው።—ሥራ 25:22-27

10, 11. ጳውሎስ ለአግሪጳ አክብሮት ያሳየው እንዴት ነው? ሐዋርያው የቀድሞ ሕይወቱን በተመለከተ ለንጉሡ ምን ነገረው?

10 ጳውሎስ፣ የመከላከያ ሐሳቡን በፊቱ እንዲያቀርብ ስለፈቀደለት ለንጉሥ አግሪጳ በአክብሮት ምስጋና አቀረበ፤ ንጉሡ የአይሁዳውያንን ልማዶችና በመካከላቸው ያሉትን ክርክሮች ጠንቅቆ ስለሚያውቅም ይህ ጥሩ አጋጣሚ መሆኑን ጠቀሰ። ከዚያም ጳውሎስ ስለ ቀድሞ ሕይወቱ ተናገረ፤ “በሃይማኖታችን ውስጥ ወግ አጥባቂ የሆነውን ቡድን በመከተል ፈሪሳዊ ሆኜ [ኖሬአለሁ]” አለ። (ሥራ 26:5) ጳውሎስ ፈሪሳዊ ሳለ የመሲሑን መምጣት በተስፋ ይጠባበቅ ነበር። ክርስቲያን ከሆነ በኋላ ደግሞ ለረጅም ዘመን ሲጠበቅ የነበረው መሲሕ ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን በድፍረት እየገለጸ ነው። ጳውሎስ በዚህ ዕለት ለፍርድ የቀረበው፣ እሱም ሆነ ከሳሾቹ በሚያምኑበት ጉዳይ የተነሳ ነው፤ ይህም አምላክ ለአባቶቻቸው የገባው ቃል እንደሚፈጸም ያለው ተስፋ ነው። አግሪጳ ይህን ሲሰማ የማወቅ ጉጉቱ ጨመረ። e

11 ጳውሎስ ከዚህ ቀደም በክርስቲያኖች ላይ የፈጸመውን የጭካኔ ድርጊት በማስታወስ እንዲህ አለ፦ “እኔ ራሴ የናዝሬቱ ኢየሱስን ስም በተቻለኝ መጠን መቃወም እንዳለብኝ አምን ነበር። . . . [በክርስቶስ ተከታዮች] ላይ እጅግ ተቆጥቼ በሌሎች ከተሞች ያሉትን እንኳ ሳይቀር እስከ ማሳደድ ደርሻለሁ።” (ሥራ 26:9-11) ጳውሎስ እንዲህ ሲል እያጋነነ አልነበረም። በክርስቲያኖች ላይ ያደረሰውን ከባድ ስደት ብዙዎች ያውቃሉ። (ገላ. 1:13, 23) አግሪጳ ‘ታዲያ ይህ ሰው እንዲለወጥ ያደረገው ምንድን ነው?’ ብሎ ሳይገረም አይቀርም።

12, 13. (ሀ) ጳውሎስ እምነቱን የቀየረበትን መንገድ የገለጸው እንዴት ነው? (ለ) ጳውሎስ ‘መውጊያውን ይቃወም’ የነበረው እንዴት ነው?

12 ጳውሎስ ቀጥሎ የተናገረው ሐሳብ መልሱን ይዟል፦ “ከካህናት አለቆች ሥልጣንና ተልእኮ ተቀብዬ ወደ ደማስቆ እየተጓዝኩ ሳለ ንጉሥ ሆይ፣ እኩለ ቀን ሲሆን በመንገድ ላይ ከፀሐይ ብርሃን የበለጠ ድምቀት ያለው ከሰማይ የመጣ ብርሃን በእኔና አብረውኝ በሚጓዙት ሰዎች ዙሪያ ሲያበራ አየሁ። ሁላችንም መሬት ላይ በወደቅን ጊዜ አንድ ድምፅ በዕብራይስጥ ቋንቋ ‘ሳኦል፣ ሳኦል ለምን ታሳድደኛለህ? መውጊያውን መቃወምህን ከቀጠልክ ለአንተው የባሰ ይሆንብሃል’ ሲለኝ ሰማሁ። እኔም ‘ጌታዬ፣ አንተ ማን ነህ?’ አልኩ። ጌታም እንዲህ አለኝ፦ ‘እኔ አንተ የምታሳድደኝ ኢየሱስ ነኝ።’” fሥራ 26:12-15

13 ይህ አስደናቂ ተአምር ከመፈጸሙ በፊት ጳውሎስ በምሳሌያዊ አነጋገር ‘መውጊያውን እየተቃወመ’ ነበር። አንድ የጭነት እንስሳ፣ የሚመራውን ሹል ጫፍ ያለው ዘንግ ቢራገጥ የሚጎዳው ራሱን ነው፤ ጳውሎስም የአምላክን ፈቃድ በመቃወም በራሱ ላይ መንፈሳዊ ጉዳት አድርሷል። ይህ ልበ ቅን ሰው፣ የተሳሳተ አካሄድ እየተከተለ ነበር፤ ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ወደ ደማስቆ በሚወስደው መንገድ ላይ ለጳውሎስ በመገለጥ አስተሳሰቡን እንዲለውጥ ረድቶታል።—ዮሐ. 16:1, 2

14, 15. ጳውሎስ በሕይወቱ ውስጥ ያደረጋቸውን ለውጦች በተመለከተ ምን ብሏል?

14 በእርግጥም ጳውሎስ በሕይወቱ ውስጥ ሥር ነቀል ለውጦች አድርጓል። አግሪጳን እንዲህ ብሎታል፦ “ከሰማይ ለተገለጠልኝ ራእይ አልታዘዝም አላልኩም፤ ከዚህ ይልቅ በመጀመሪያ በደማስቆ ላሉ ቀጥሎም በኢየሩሳሌምና በመላው የይሁዳ አገር ሁሉ ለሚገኙ ከዚያም ለአሕዛብ ንስሐ እንዲገቡና ለንስሐ የሚገባ ሥራ በመሥራት ወደ አምላክ እንዲመለሱ የሚያሳስበውን መልእክት ማዳረሴን ቀጠልኩ።” (ሥራ 26:19, 20) ጳውሎስ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ እኩለ ቀን ላይ በራእይ በተገለጠለት ዕለት የሰጠውን ተልእኮ ለበርካታ ዓመታት ሲፈጽም ቆይቷል። ታዲያ ምን ውጤት አግኝቷል? ጳውሎስ የሰበከውን ምሥራች የተቀበሉ ሰዎች ሥነ ምግባር የጎደለው ብልሹ አኗኗራቸውን ትተው ወደ አምላክ ተመልሰዋል። ሕግ አክባሪና ሰላማዊ ዜጎች ሆነዋል።

15 ሆኖም እነዚህ መልካም ውጤቶች ጳውሎስን ለሚቃወሙት አይሁዳውያን ምንም ማለት አልነበሩም። ጳውሎስ እንዲህ ብሏል፦ “አይሁዳውያኑ በቤተ መቅደሱ ውስጥ የያዙኝና ሊገድሉኝ የሞከሩት በዚህ የተነሳ ነው። ይሁን እንጂ ከአምላክ እርዳታ በማግኘቴ እስከዚህ ቀን ድረስ ለትንሹም ሆነ ለትልቁ መመሥከሬን ቀጥያለሁ።”—ሥራ 26:21, 22

16. ለዳኞችና ለገዢዎች ስለ እምነታችን ስናስረዳ የጳውሎስን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?

16 እኛም እውነተኛ ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ለእምነታችን “መልስ ለመስጠት ዘወትር ዝግጁ” መሆን አለብን። (1 ጴጥ. 3:15) ለዳኞችና ለገዢዎች ስለ እምነታችን ስንናገር ጳውሎስ ለንጉሥ አግሪጳና ለፊስጦስ ሲናገር የተጠቀመበትን ዘዴ መከተል እንችላለን። የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የራሳችንንም ሆነ መልእክታችንን የተቀበሉ ሰዎችን ሕይወት እንዴት እንደቀየረው በአክብሮት ብንነግራቸው የባለሥልጣናቱን ልብ መንካት እንችል ይሆናል።

“አሳምነህ ክርስቲያን ልታደርገኝ እኮ ምንም አልቀረህም” (የሐዋርያት ሥራ 26:24-32)

17. ፊስጦስ፣ ጳውሎስ ላቀረበው የመከላከያ መልስ ምን ምላሽ ሰጠ? ዛሬስ ምን ተመሳሳይ አመለካከት ሰፍኖ ይታያል?

17 የጳውሎስ አሳማኝ ምሥክርነት በሁለቱ ገዢዎች ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩ አልቀረም። ቀጥሎ ምን እንደተከሰተ ተመልከት፦ “ጳውሎስ የመከላከያ መልሱን እየሰጠ ሳለ ፊስጦስ ጮክ ብሎ ‘ጳውሎስ አሁንስ አእምሮህን ልትስት ነው! ብዙ መማር አእምሮህን እያሳተህ ነው!’ አለ።” (ሥራ 26:24) የፊስጦስ ምላሽ ዛሬም በብዙዎች አመለካከት ላይ ይታያል። ብዙዎች፣ ትክክለኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የሚያስተምሩ ሰዎችን አክራሪ አድርገው ይመለከቷቸዋል። ዓለም የተማሩ የሚላቸው ሰዎች ብዙውን ጊዜ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሙታን ትንሣኤ የሚያስተምረውን ትምህርት መቀበል ይከብዳቸዋል።

18. ጳውሎስ፣ ፊስጦስ ለሰነዘረው ሐሳብ ምን ምላሽ ሰጠ? አግሪጳስ ምን አለ?

18 ይሁንና ጳውሎስ ለአገረ ገዢው የሚሰጠው መልስ አለው፦ “ክቡር ፊስጦስ ሆይ፣ አእምሮዬን እየሳትኩ አይደለም፤ እኔ እየተናገርኩ ያለሁት እውነተኛ እንዲሁም ከጤናማ አእምሮ የሚመነጭ ቃል ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ በነፃነት እያናገርኩት ያለሁት ንጉሥ ስለ እነዚህ ነገሮች በሚገባ ያውቃል፤ . . . ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፣ በነቢያት ታምናለህ? እንደምታምን አውቃለሁ።” በዚህ ጊዜ አግሪጳ “በአጭር ጊዜ ውስጥ አሳምነህ ክርስቲያን ልታደርገኝ እኮ ምንም አልቀረህም” ሲል መለሰለት። (ሥራ 26:25-28) ንጉሡ ይህን የተናገረው ከልቡ ይሁንም አይሁን፣ ጳውሎስ የሰጠው ምሥክርነት ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሮበት እንደነበር ያሳያል።

19. ፊስጦስና አግሪጳ ጳውሎስን በተመለከተ ምን መደምደሚያ ላይ ደረሱ?

19 ከዚህ በኋላ አግሪጳና ፊስጦስ ተነሱ፤ ይህም ስብሰባው ማብቃቱን የሚጠቁም ነበር። “እየወጡ ሳሉም እርስ በርሳቸው ‘ይህ ሰው ለሞት ወይም ለእስራት የሚያበቃ ምንም ነገር አላደረገም’ ተባባሉ።” ከዚያም አግሪጳ ፊስጦስን “ይህ ሰው ወደ ቄሳር ይግባኝ ባይል ኖሮ ሊፈታ ይችል ነበር” አለው። (ሥራ 26:31, 32) ፊታቸው የቀረበው ሰው ምንም ጥፋት እንደሌለበት ተገንዝበዋል። ምናልባት ይህ አጋጣሚ ወደፊት ለክርስቲያኖች የተሻለ ቀና አመለካከት እንዲኖራቸው ያደርግ ይሆናል።

20. ጳውሎስ ለከፍተኛ ባለሥልጣናት መመሥከሩ ምን ውጤት አስገኝቷል?

20 በዚህ ዘገባ ላይ የተጠቀሱት ሁለቱም ኃያል ገዢዎች የአምላክን መንግሥት ምሥራች የተቀበሉ አይመስልም። ታዲያ ሐዋርያው ጳውሎስ እነዚህ ሰዎች ፊት መቅረቡ ያስገኘው ጥቅም አለ? አዎ፣ አለ። ጳውሎስ በይሁዳ ‘ነገሥታትና ገዢዎች ፊት መቅረቡ’ ምናልባትም በሌላ በማንኛውም መንገድ ምሥራቹን የመስማት አጋጣሚ ላልነበራቸው ሮማውያን ባለሥልጣናት ለመመሥከር አስችሎታል። (ሉቃስ 21:12, 13) በተጨማሪም ተሞክሮውና በፈተና ወቅት ያሳየው ታማኝነት የእምነት ባልንጀሮቹን አበረታቷቸዋል።—ፊልጵ. 1:12-14

21. የመንግሥቱን ምሥራች መስበካችንን መቀጠላችን ምን ጥሩ ውጤቶች ያስገኛል?

21 ዛሬም ሁኔታው ከዚህ የተለየ አይደለም። ፈተናና ተቃውሞ እያለም የመንግሥቱን ምሥራች መስበካችንን መቀጠላችን በርካታ አበረታች ውጤቶች ያስገኛል። በቀላሉ ለማይገኙ ባለሥልጣናት የመመሥከር አጋጣሚ ልናገኝ እንችላለን። በተጨማሪም በታማኝነት መጽናታችን ለክርስቲያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የብርታት ምንጭ ይሆናል፤ ስለ አምላክ መንግሥት በሚገባ ለመመሥከር በሚያደርጉት ጥረት ድፍረት ይጨምርላቸዋል።

a ጶርቅዮስ ፊስጦስየይሁዳ አገረ ገዢ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

b እዚህ ላይ የተጠቀሰው ‘የፍርድ ወንበር’ መድረክ ላይ የሚቀመጥ ወንበር ነው። ወንበሩ ከፍ ያለ ስፍራ ላይ መቀመጡ ዳኛው ለሚያስተላልፈው ውሳኔ ክብደት ይጨምራል፤ ውሳኔው የማያዳግም ተደርጎ እንዲታይም ያደርጋል። ጲላጦስ በኢየሱስ ላይ የቀረቡትን ክሶች የተመለከተው በፍርድ ወንበር ላይ ተቀምጦ ነበር።

d ዳግማዊ ሄሮድስ አግሪጳ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

e ጳውሎስ ክርስቲያን እንደመሆኑ መጠን የኢየሱስን መሲሕነት ተቀብሏል። ኢየሱስን ያልተቀበሉት አይሁዳውያን ግን ጳውሎስን እንደ ከሃዲ ቆጥረውታል።—ሥራ 21:21, 27, 28

f ጳውሎስ “እኩለ ቀን” ላይ እየተጓዘ እንደነበር የተናገረውን ሐሳብ በተመለከተ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር እንዲህ ብለዋል፦ “አንድ መንገደኛ በጣም አጣዳፊ ጉዳይ ካላጋጠመው በስተቀር እኩለ ቀን ላይ አረፍ ይላል እንጂ በጠራራ ፀሐይ አይጓዝም። ጳውሎስ ክርስቲያኖችን እንዲያሳድድ ለተሰጠው ተልእኮ ምን ያህል ራሱን እንደሰጠ ከዚህ ማየት እንችላለን።”