በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 27

“በሚገባ . . . መመሥከር”

“በሚገባ . . . መመሥከር”

ጳውሎስ በሮም ታስሮ እያለም መስበኩን አላቆመም

በሐዋርያት ሥራ 28:11-31 ላይ የተመሠረተ

1. ጳውሎስና አብረውት ያሉት ክርስቲያኖች ስለ ምን ነገር እርግጠኞች ናቸው? ለምንስ?

 ጊዜው 59 ዓ.ም. ገደማ ነው። አንድ ትልቅ መርከብ በሜድትራንያን ባሕር ላይ ጉዞ ጀምሯል፤ መነሻው የማልታ ደሴት፣ መድረሻው ደግሞ ጣሊያን ነው፤ መርከቡ እህል የጫነ ሳይሆን አይቀርም። የመርከቡ ዓርማ “የዙስ ልጆች” የሚል ነው። እስረኛው ሐዋርያው ጳውሎስና ጠባቂው እንዲሁም ክርስቲያን ባልንጀሮቹ ሉቃስና አርስጥሮኮስ በዚህ መርከብ ላይ ተሳፍረዋል። (ሥራ 27:2) መርከበኞቹ፣ ካስተርና ፖለክስ ከተባሉት የዙስ መንትያ ልጆች ጥበቃ ማግኘት ይፈልጋሉ፤ ወንጌላውያኑ ግን የግሪካውያኑ አማልክት ጥበቃ አላስፈለጋቸውም። (የ⁠ሥራ 28:11⁠ን ለጥናት የሚረዳ መረጃ ተመልከት፣ nwtsty-E) ጳውሎስና የጉዞ ጓደኞቹ፣ የይሖዋ አገልጋዮች ናቸው፤ ይሖዋ ደግሞ በሮም ስለ እውነት እንደሚመሠክርና በቄሳር ፊት እንደሚቆም ለጳውሎስ ነግሮታል።—ሥራ 23:11፤ 27:24

2, 3. ጳውሎስ የተሳፈረበት መርከብ የተጓዘው በየት በኩል ነው? ጳውሎስ ከመጀመሪያው አንስቶ የማን ድጋፍ አልተለየውም?

2 መርከቡ ማረፊያውን በውቧ የሲሲሊ ከተማ በስራኩስ አደረገ፤ ስራኩስ ከአቴንስና ከሮም ጋር የምትፎካከር ከተማ ናት። ከሦስት ቀናት ቆይታ በኋላ መርከቡ በደቡባዊ ጣሊያን ጫፍ ወደምትገኘው ወደ ሬጊዩም አመራ። ቀጥሎ ደግሞ 320 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘው ፑቲዮሉስ አቀና፤ ከደቡብ በኩል በሚመጣ ነፋስ እየታገዘ ገና በሁለተኛው ቀን እዚያ ደረሰ፤ ፑቲዮሉስ የጣሊያን የወደብ ከተማ ስትሆን በዛሬዋ ኔፕልስ አጠገብ ትገኛለች።—ሥራ 28:12, 13

3 ጳውሎስ በንጉሠ ነገሥት ኔሮ ፊት ለመቅረብ ወደ ሮም የሚያደርገውን ጉዞ እያገባደደ ነው። “የመጽናናት ሁሉ አምላክ” ጉዞው ተጀምሮ እስኪያልቅ ድረስ ከጳውሎስ ጋር ነበር። (2 ቆሮ. 1:3) ቀጥሎ እንደምንመለከተው ይሖዋ ለጳውሎስ ድጋፍ መስጠቱን አያቋርጥም፤ ጳውሎስም ቢሆን የሚስዮናዊነት ቅንዓቱ አይበርድም።

“ጳውሎስ . . . አምላክን አመሰገነ፤ እንዲሁም ተበረታታ” (የሐዋርያት ሥራ 28:14, 15)

4, 5. (ሀ) ጳውሎስና ጓደኞቹ ፑቲዮሉስ ሲደርሱ ምን ዓይነት መስተንግዶ ተደረገላቸው? ጳውሎስ ይህን ያህል ነፃነት ያገኘው ለምን ሊሆን ይችላል? (ለ) ክርስቲያኖች እስር ቤት እያሉም እንኳ መልካም ባሕርይ ማሳየታቸው እንዴት ሊጠቅማቸው ይችላል?

4 ጳውሎስና ጓደኞቹ ፑቲዮሉስ ሲደርሱ ምን አጋጠማቸው? ዘገባው “በዚያም ወንድሞችን አገኘን፤ እነሱም ሰባት ቀን አብረናቸው እንድንቆይ ለመኑን” ይላል። (ሥራ 28:14) እንዴት ያለ ግሩም የእንግዳ ተቀባይነት ምሳሌ ነው! እነዚህ ደግ ወንድሞች ከጳውሎስና ከጓደኞቹ መንፈሳዊ ማበረታቻ በማግኘታቸው በብዙ እጥፍ እንደተካሱ ምንም ጥያቄ የለውም። ይሁንና በጥበቃ ሥር ያለ አንድ እስረኛ ይህን ያህል ነፃነት ሊያገኝ የቻለው እንዴት ነው? ሐዋርያው ይህን መብት ያገኘው የሮማውያን ጠባቂዎቹን እምነት ስላተረፈ ይሆናል።

5 በዘመናችንም በተደጋጋሚ እንደታየው የይሖዋ አገልጋዮች በእስር ቤቶችና በማጎሪያ ካምፖች ውስጥ ለየት ያለ ነፃነት ተሰጥቷቸዋል፤ ይህ የሆነው በክርስቲያናዊ ባሕርያቸው የተነሳ ነው። አንድ ምሳሌ እንመልከት፤ ሩማኒያ ውስጥ በዝርፊያ ወንጀል 75 ዓመት ተፈርዶበት የታሰረ አንድ ሰው የአምላክን ቃል ማጥናት ከጀመረ በኋላ በባሕርዩ ላይ ከፍተኛ ለውጥ አደረገ። በዚህም የተነሳ የእስር ቤቱ ኃላፊዎች፣ ያለምንም አጃቢ ከተማ ሄዶ ለእስር ቤቱ የሚያስፈልጉትን ዕቃዎች ገዝቶ እንዲመጣ ይልኩት ጀመር! እርግጥ ነው፣ የምናሳየው መልካም ባሕርይ ከሁሉ በላይ የሚያስከብረው ይሖዋን ነው።—1 ጴጥ. 2:12

6, 7. የሮም ወንድሞች ልዩ ፍቅር ያሳዩት እንዴት ነው?

6 ጳውሎስና ጓደኞቹ ከዚህ ቀጥሎ ወደ ካፑዋ በእግር የተጓዙ ይመስላል፤ ከፑቲዮሉስ 50 ኪሎ ሜትር ያህል ርቀት ላይ ያለችው ካፑዋ በአፒያን ጎዳና ላይ ትገኛለች። ወደ ሮም የሚያመራው ይህ ታዋቂ አውራ ጎዳና ትላልቅና ጠፍጣፋ የእሳተ ገሞራ ድንጋዮች ተነጥፈውበታል፤ በዚህ መንገድ ላይ የሚጓዝ ሰው ውቡን የጣሊያን ገጠራማ አካባቢ፣ አለፍ አለፍ እያለ ደግሞ የሜድትራንያንን ባሕር መቃኘት ይችላል። ፖንታይን ማርሽስ የተባለውን ረግረጋማ ቦታም አቋርጦ ያልፋል፤ ይህ ቦታ የሚገኘው ለሮም 60 ኪሎ ሜትር ገደማ ሲቀረው ነው፤ የአፍዩስ የገበያ ስፍራም ያለው እዚሁ ነው። ሉቃስ እንደዘገበው የሮም ወንድሞች ‘ስለ እነሱ በሰሙ ጊዜ’ አንዳንዶቹ እስከ ገበያ ስፍራው ድረስ መጡ፤ ሌሎቹ ደግሞ ሦስት ማደሪያ የሚባለው ቦታ ላይ ጠበቋቸው፤ ይህ ማረፊያ ቦታ ያለው ከሮም 50 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቆ ነው። እንዴት ያለ ልዩ ፍቅር ነው!—ሥራ 28:15

7 የአፍዩስ የገበያ ስፍራ፣ ከአድካሚው ጉዞ አረፍ ማለት ለሚፈልግ መንገደኛ የሚመች ቦታ አይደለም። ሮማዊው ባለቅኔ ሆራስ እንደገለጸው የገበያ ስፍራው “በመርከበኞችና ሥነ ሥርዓት በሌላቸው የማረፊያ ቤት ባለቤቶች የተጨናነቀ” ነው። በተጨማሪም “ውኃው በጣም ያስጠላል” ሲል ጽፏል። ሆራስ በዚያ ምግብ ለመብላት እንኳ አልፈለገም! ከሮም የመጡት ወንድሞች ግን ጳውሎስንና ጓደኞቹን የጠበቁት እንዲህ ባለ መጥፎ ቦታ ሆነው ነው፤ ወንድሞችን ለመቀበልና ሮም ድረስ አጅበው ለመሄድ ሲሉ ምቾት የሚነሳ ብዙ ነገር ተቋቁመዋል።

8. ጳውሎስ ወንድሞቹን “ባያቸው ጊዜ” አምላክን ያመሰገነው ለምንድን ነው?

8 ዘገባው፣ ጳውሎስ ወንድሞቹን “ባያቸው ጊዜ አምላክን አመሰገነ፤ እንዲሁም ተበረታታ” ይላል። (ሥራ 28:15) አዎ፣ ሐዋርያው እነዚህን ውድ ወንድሞች በማየቱ ብቻ እንኳ ተበረታቷል እንዲሁም ተጽናንቷል፤ ምናልባትም ከመካከላቸው አንዳንዶቹን በቅርበት ያውቃቸው ይሆናል። ታዲያ ጳውሎስ አምላክን ያመሰገነው ለምንድን ነው? ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር የመንፈስ ፍሬ ገጽታ እንደሆነ ስለሚያውቅ ነው። (ገላ. 5:22) በዛሬው ጊዜም ክርስቲያኖች ለራሳቸው ቅንጣት ሳይሳሱ ወንድሞቻቸውን የሚረዱትና የሚያጽናኑት በመንፈስ ቅዱስ ተነሳስተው ነው።—1 ተሰ. 5:11, 14

9. ጳውሎስን የተቀበሉት ወንድሞች ያሳዩት ዓይነት መንፈስ ማንጸባረቅ የምንችለው እንዴት ነው?

9 ለምሳሌ ያህል፣ መንፈስ ቅዱስ ለጋስ የሆኑ ወንድሞች ለወረዳ የበላይ ተመልካቾች፣ ለሚስዮናውያንና ለሌሎች የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ እንዲያሳዩ ይገፋፋቸዋል፤ እነዚህ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች በይሖዋ አገልግሎት ተጨማሪ ለማድረግ ሲሉ ብዙ መሥዋዕት ከፍለዋል። እንግዲያው ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘የወረዳ የበላይ ተመልካቹን ጉብኝት ለመደገፍ ማድረግ የምችለው ተጨማሪ ነገር ይኖራል? እሱንም ሆነ ያገባ ከሆነ ሚስቱን በእንግድነት መቀበል እችላለሁ? አብሬያቸው ለማገልገል ሁኔታዎቼን ማመቻቸት እችላለሁ?’ እንዲህ የምታደርግ ከሆነ ብዙ በረከት ታገኛለህ። በሮም ያሉት ወንድሞች ጳውሎስና ጓደኞቹ ያገኟቸውን የሚያንጹ ተሞክሮዎች ሲሰሙ ምን ያህል ተደስተው እንደሚሆን አስበው።—ሥራ 15:3, 4

‘በየቦታው መጥፎ ነገር ይወራበታል’ (የሐዋርያት ሥራ 28:16-22)

10. ጳውሎስ ሮም ውስጥ የነበረበት ሁኔታ ምን ይመስላል? ሐዋርያው እዚያ ከደረሰ ብዙም ሳይቆይ ምን አደረገ?

10 መንገደኞቹ በመጨረሻ ሮም ደረሱ፤ በዚያም “ጳውሎስ አንድ ወታደር እየጠበቀው ብቻውን እንዲኖር ተፈቀደለት።” (ሥራ 28:16) የቁም እስረኛ የሆነ ሰው እንዳያመልጥ በአብዛኛው ከጠባቂው ጋር በሰንሰለት እንዲቆራኝ ይደረግ ነበር። ጳውሎስ ግን ቀናተኛ ሰባኪ ነው፤ በሰንሰለት መታሰሩ ስለ መንግሥቱ ከመስበክ አያግደውም። በመሆኑም ከጉዞው ድካም ለሦስት ቀን ብቻ ካረፈ በኋላ በሮም ያሉትን የአይሁዳውያን ታላላቅ ሰዎች ጠራ፤ ይህን ያደረገው ራሱን ለማስተዋወቅና ለእነዚህ ሰዎች ምሥራቹን ለመንገር ነው።

11, 12. ጳውሎስ አይሁዳውያን ወገኖቹን ሲያነጋግር ስለ እሱ የሚኖራቸውን የተሳሳተ አመለካከት ለማስወገድ ጥረት ያደረገው እንዴት ነው?

11 ጳውሎስ እንዲህ አለ፦ “ወንድሞች፣ ምንም እንኳ ሕዝቡን ወይም የአባቶቻችንን ልማድ የሚጻረር ነገር ያልፈጸምኩ ቢሆንም በኢየሩሳሌም አስረው ለሮማውያን አሳልፈው ሰጥተውኛል። እነሱም ከመረመሩኝ በኋላ ለሞት የሚያበቃ ምንም ጥፋት ስላላገኙብኝ ሊፈቱኝ ፈልገው ነበር። ሆኖም አይሁዳውያን ይህን በተቃወሙ ጊዜ ለቄሳር ይግባኝ ለማለት ተገደድኩ፤ ይህን ያደረግኩት ግን ሕዝቤን የምከስበት ነገር ኖሮኝ አይደለም።”—ሥራ 28:17-19

12 ጳውሎስ አይሁዳውያን አድማጮቹን “ወንድሞች” ብሎ በመጥራት ከእነሱ ጋር ለመግባባት የሚያስችል መሠረት ጥሏል፤ ስለ እሱ የተሳሳተ አመለካከት ከነበራቸውም ይህን ማለቱ ሁኔታውን ለማለዘብ ይረዳል። (1 ቆሮ. 9:20) በተጨማሪም ወደ ሮም የመጣው ወገኖቹ የሆኑትን አይሁዳውያን ለመክሰስ ሳይሆን ለቄሳር ይግባኝ ለማለት እንደሆነ በግልጽ ተናገረ። ይሁን እንጂ በዚያ የሚኖሩት አይሁዳውያን ጳውሎስ ይግባኝ ስለመጠየቁ የሰሙት ነገር የለም። (ሥራ 28:21) በይሁዳ ከሚኖሩት አይሁዳውያን ይህ መረጃ ያልደረሳቸው ለምንድን ነው? አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ እንዲህ ይላል፦ “ጳውሎስ የተሳፈረበት መርከብ፣ ከክረምቱ በኋላ መጀመሪያ ጣሊያን ከደረሱት መርከቦች መካከል ሳይሆን አይቀርም፤ በመሆኑም በኢየሩሳሌም ከሚገኙት አይሁዳውያን ባለሥልጣኖች የተላኩ ሰዎችም ሆኑ ጉዳዩን በተመለከተ የተጻፈ ደብዳቤ ከዚህ ቀድሞ ሮም ሊደርስ አይችልም።”

13, 14. ጳውሎስ ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገረውን ጭብጥ ያስተዋወቀው እንዴት ነው? የእሱን ምሳሌ መኮረጅ የምንችለውስ በምን መንገድ ነው?

13 ጳውሎስ የአይሁዳውያን እንግዶቹን ጉጉት በሚቀሰቅስ መንገድ የመልእክቱን ጭብጥ አስተዋወቀ፤ ስለ አምላክ መንግሥት አንድ ሐሳብ ጣል አደረገ። “[እናንተን] ለማየትና ለማነጋገር ጥያቄ ያቀረብኩት ለዚህ ነው፤ በዚህ ሰንሰለት የታሰርኩትም ለእስራኤል በተሰጠው ተስፋ ምክንያት ነው” አላቸው። (ሥራ 28:20) የክርስቲያን ጉባኤ የሚያውጀው ይህ ተስፋ ከመሲሑና ከእሱ መንግሥት ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው። አይሁዳውያኑ ሽማግሌዎችም “ስለዚህ ኑፋቄ በየቦታው መጥፎ ነገር እንደሚወራ ስለምናውቅ የአንተን ሐሳብ ደግሞ መስማት ተገቢ ይመስለናል” አሉት።—ሥራ 28:22

14 እኛም ምሥራቹን የምንሰብክበት አጋጣሚ ስናገኝ ጳውሎስ እንዳደረገው ትኩረት የሚስቡ ሐሳቦችንና ጥያቄዎችን በማንሳት የአድማጮቻችንን ፍላጎት ማነሳሳት እንችላለን። ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሱ ማመራመር፣ በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም እንዲሁም ለማንበብ እና ለማስተማር የተቻለህን ሁሉ ጥረት አድርግ የተባሉት ጽሑፎች ላይ ግሩም ሐሳቦች ማግኘት ይቻላል። መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት በሚረዱት በእነዚህ መሣሪያዎች በሚገባ እየተጠቀምክ ነው?

“በሚገባ በመመሥከር” ግሩም አርዓያ ትቶልናል (የሐዋርያት ሥራ 28:23-29)

15. ጳውሎስ ከሰጠው ምሥክርነት የምናገኛቸው አራት ቁም ነገሮች ምንድን ናቸው?

15 የተቀጠረው ቀን ሲደርስ፣ አይሁዳውያኑ ጳውሎስ ወደሚኖርበት ስፍራ “ብዙ ሆነው” መጡ። ጳውሎስ “በኢየሱስ እንዲያምኑ ለማድረግ ከሙሴ ሕግና ከነቢያት እየጠቀሰ ከጠዋት ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ ስለ አምላክ መንግሥት በሚገባ በመመሥከር ጉዳዩን አብራራላቸው።” (ሥራ 28:23) ጳውሎስ ምሥክርነት ከሰጠበት መንገድ የምናገኛቸው አራት ቁም ነገሮች አሉ። አንደኛ፣ ትኩረት ያደረገው በአምላክ መንግሥት ላይ ነው። ሁለተኛ፣ የአድማጮቹን ልብ ለመንካት የጣረው አሳማኝ ማስረጃ በማቅረብ ነው። ሦስተኛ፣ ከቅዱሳን መጻሕፍት እየጠቀሰ ያስረዳ ነበር። አራተኛ፣ “ከጠዋት ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ” በመመሥከር የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ አሳይቷል። በእርግጥም ልንከተለው የሚገባ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው! ውጤቱስ ምን ነበር? “አንዳንዶቹ የተናገረውን ነገር ሲያምኑ ሌሎቹ ግን አላመኑም።” ሉቃስ እንደዘገበው በመካከላቸው ክፍፍል ስለተፈጠረ “ለመሄድ ተነሱ።”—ሥራ 28:24, 25ሀ

16-18. በሮም የሚኖሩ አይሁዳውያን አሉታዊ ምላሽ መስጠታቸው ጳውሎስን ያላስገረመው ለምንድን ነው? ሰዎች መልእክታችንን ለመቀበል ፈቃደኛ ባይሆኑ ምን ሊሰማን አይገባም?

16 የሰዎቹ ምላሽ ጳውሎስን አላስገረመውም፤ ምላሻቸው መጽሐፍ ቅዱስ አስቀድሞ ከተናገረው ትንቢት ጋር የሚስማማ ነው፤ እሱ ራሱም እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሞት ያውቃል። (ሥራ 13:42-47፤ 18:5, 6፤ 19:8, 9) በመሆኑም ጳውሎስ መልእክቱን መቀበል ያልፈለጉት ሰዎች ተነስተው ሲወጡ እንዲህ አላቸው፦ “መንፈስ ቅዱስ በነቢዩ ኢሳይያስ በኩል ለአባቶቻችሁ እንዲህ ሲል የተናገረው ቃል ትክክል ነበር፦ ‘ወደዚህ ሕዝብ ሄደህ እንዲህ በላቸው፦ “መስማቱን ትሰማላችሁ፤ ግን በፍጹም አታስተውሉም፤ ማየቱን ታያላችሁ፤ ግን በፍጹም ልብ አትሉም። ምክንያቱም . . . የዚህ ሕዝብ ልብ ደንድኗል።”’” (ሥራ 28:25ለ-27) “ደንድኗል” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “የወፈረ” ወይም “የሰባ” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል፤ በመሆኑም የመንግሥቱ መልእክት ወደ ልባቸው ጠልቆ እንዳይገባ ስቡ አግዶታል ማለት ነው። እንዴት ያለ አሳዛኝ ሁኔታ ነው!

17 ጳውሎስ ንግግሩን ሲደመድም፣ ከእነዚህ አይሁዳውያን በተለየ “[አሕዛብ] በእርግጥ ይሰሙታል” ብሏል። (ሥራ 28:28፤ መዝ. 67:2፤ ኢሳ. 11:10) ሐዋርያው ስለዚህ ጉዳይ አፉን ሞልቶ መናገር ይችላል! ምክንያቱም በርካታ አሕዛብ የመንግሥቱን መልእክት ሲቀበሉ በገዛ ዓይኑ ተመልክቷል።—ሥራ 13:48፤ 14:27

18 ሰዎች ምሥራቹን ለመቀበል ፈቃደኛ በማይሆኑበት ጊዜ ቅር ባለመሰኘት የጳውሎስን ምሳሌ መከተል እንችላለን። ደግሞም ወደ ሕይወት የሚወስደውን መንገድ የሚያገኙት በአንጻራዊ ሁኔታ ጥቂቶች እንደሆኑ እናውቃለን። (ማቴ. 7:13, 14) ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች ከእውነተኛው አምልኮ ጎን ሲቆሙ ደግሞ ልንደሰትና ልባችንን ከፍተን ልንቀበላቸው ይገባል።—ሉቃስ 15:7

‘ስለ አምላክ መንግሥት መስበክ’ (የሐዋርያት ሥራ 28:30, 31)

19. ጳውሎስ የነበረበትን ሁኔታ ጥሩ አድርጎ የተጠቀመበት እንዴት ነው?

19 ሉቃስ ዘገባውን የሚደመድመው አዎንታዊና አስደሳች በሆነ መንገድ ነው፤ እንዲህ ብሏል፦ “ጳውሎስም በተከራየው ቤት ሁለት ዓመት ሙሉ ኖረ፤ ወደ እሱ የሚመጡትንም ሁሉ በደግነት ያስተናግዳቸው ነበር፤ ያለምንም እንቅፋት በታላቅ የመናገር ነፃነት ስለ አምላክ መንግሥት ይሰብክላቸው የነበረ ከመሆኑም በላይ ስለ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተምራቸው ነበር።” (ሥራ 28:30, 31) በእርግጥም በእንግዳ ተቀባይነት፣ በእምነትና በቅንዓት ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቷል!

20, 21. ጳውሎስ በሮም ካከናወነው አገልግሎት የተጠቀሙ አንዳንድ ሰዎችን ጥቀስ።

20 ጳውሎስ በደግነት ካስተናገዳቸው መካከል ከቆላስይስ ኮብልሎ የመጣ አናሲሞስ የተባለ ባሪያ ይገኝበታል። ጳውሎስ አናሲሞስን ወደ ክርስትና አምጥቶታል፤ አናሲሞስ ደግሞ ለጳውሎስ ‘ታማኝና የተወደደ ወንድም’ ሆኖለታል። እንዲያውም ጳውሎስ ስለ እሱ ሲናገር “እንደ አባት የሆንኩለትን ልጄን” የሚል መግለጫ ተጠቅሟል። (ቆላ. 4:9፤ ፊልሞና 10-12) አናሲሞስ ለጳውሎስ ምንኛ የብርታት ምንጭ ሆኖለት ይሆን! a

21 ጳውሎስ ከተወው ግሩም ምሳሌ ሌሎችም ተጠቅመዋል። ሐዋርያው ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “እኔ ያጋጠመኝ ሁኔታ ምሥራቹ ይበልጥ እንዲስፋፋ አስተዋጽኦ [አድርጓል]፤ የታሰርኩት የክርስቶስ አገልጋይ በመሆኔ የተነሳ እንደሆነ በንጉሠ ነገሥቱ የክብር ዘብ ሁሉና በሌሎች ሰዎች ሁሉ ዘንድ በይፋ ታውቋል። ጌታን የሚያገለግሉ አብዛኞቹ ወንድሞች በእኔ መታሰር ምክንያት የልበ ሙሉነት ስሜት አድሮባቸው የአምላክን ቃል ያለፍርሃት ለመናገር ከቀድሞው የበለጠ ድፍረት እያሳዩ ነው።”—ፊልጵ. 1:12-14

22. ጳውሎስ በሮም ታስሮ ያሳለፈውን ጊዜ በጥሩ ሁኔታ የተጠቀመበት እንዴት ነው?

22 ጳውሎስ በሮም ታስሮ ያሳለፈውን ጊዜ፣ አሁን የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ክፍል የሆኑትን ጠቃሚ ደብዳቤዎች ለመጻፍ ተጠቅሞበታል። b እነዚህ ደብዳቤዎች የተላኩላቸው የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች እንደተጠቀሙ ጥያቄ የለውም። እኛም ብንሆን ከጳውሎስ ደብዳቤዎች እንጠቀማለን፤ ምክንያቱም በመንፈስ መሪነት የጻፈው ምክር እንደ ያኔው ሁሉ ዛሬም አስፈላጊ ነው።—2 ጢሞ. 3:16, 17

23, 24. በዛሬው ጊዜ ያሉ በርካታ ክርስቲያኖች በግፍ ቢታሰሩም እንኳ እንደ ጳውሎስ አዎንታዊ አመለካከት ያሳዩት እንዴት ነው?

23 የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ጳውሎስ መቼ እንደተፈታ ባይናገርም ነፃነቱን ለማግኘት አራት ዓመት ገደማ ወስዶበታል፤ በቂሳርያ ሁለት ዓመት፣ በሮምም ሁለት ዓመት ታስሮ ነበር። c (ሥራ 23:35፤ 24:27) ያም ቢሆን በአምላክ አገልግሎት የሚችለውን ሁሉ እያደረገ አዎንታዊ አመለካከት ይዞ ቀጥሏል። ዛሬ ያሉ በርካታ የይሖዋ ምሥክሮችም በእምነታቸው ምክንያት በግፍ ቢታሰሩም ደስታቸውን አላጡም፤ መስበካቸውንም ቀጥለዋል። በክርስቲያናዊ ገለልተኝነቱ ምክንያት በስፔን ታስሮ የነበረውን አዶልፎን እንደ ምሳሌ እንመልከት። አንድ መኮንን እንዲህ ብሎት ነበር፦ “በጣም ነው የምታስገርመን። ሕይወት እንዲመርህ ያላደረግነው ነገር አልነበረም፤ እኛ ስናከብድብህ አንተ ፈገግታ አይለይህም፤ ደግ ቃል እንጂ ክፉ አይወጣህም።”

24 ከጊዜ በኋላ ጠባቂዎቹ አዶልፎን በጣም ስለተማመኑበት የታሰረበትን ክፍል ክፍት ይተዉት ጀመር። ወታደሮችም እየመጡ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ይጠይቁት ነበር። እንዲያውም ከጠባቂዎቹ አንዱ መጽሐፍ ቅዱስ ለማንበብ ወደ አዶልፎ ክፍል ይገባ ነበር፤ በዚህ ጊዜ ሰው እንዳያየው አዶልፎ አካባቢውን ይቃኝለታል። እስረኛው የጠባቂው “ጠባቂ” ሆነ! እንዲህ ያሉ ታማኝ ምሥክሮች የተዉት ግሩም ምሳሌ እኛም በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥም እንኳ “የአምላክን ቃል ያለፍርሃት ለመናገር ከቀድሞው የበለጠ ድፍረት” እንድናሳይ ያነሳሳናል።

25, 26. ጳውሎስ 30 ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የትኛው አስደናቂ ትንቢት ሲፈጸም ተመልክቷል? ይህስ በዘመናችን ካለው ሁኔታ ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው?

25 የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ፣ ምሥራቹን ለመስበክ አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ ስላደረጉ ክርስቲያኖች የሚገልጹ አስገራሚ ዘገባዎችን ይዟል፤ መጽሐፉ የሚደመደመውም እስረኛ የሆነው የክርስቶስ ሐዋርያ ሊጠይቁት ለመጡ ሁሉ “ስለ አምላክ መንግሥት ይሰብክላቸው” እንደነበር በሚገልጽ የሚያበረታታ ሐሳብ ነው! በመጀመሪያው ምዕራፍ ላይ ኢየሱስ ለተከታዮቹ የሰጣቸውን ተልእኮ እናነባለን፤ እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በሚወርድበት ጊዜ ኃይል ትቀበላላችሁ፤ በኢየሩሳሌም፣ በመላው ይሁዳና በሰማርያ እንዲሁም እስከ ምድር ዳር ድረስ ምሥክሮቼ ትሆናላችሁ።” (ሥራ 1:8) ይህን ከተናገረ 30 ዓመት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ የመንግሥቱ መልእክት “ከሰማይ በታች ላለ ፍጥረት ሁሉ ተሰብኳል።” d (ቆላ. 1:23) የአምላክ መንፈስ ያለውን ኃይል የሚያሳይ እንዴት ያለ ማስረጃ ነው!—ዘካ. 4:6

26 ዛሬም ቅቡዓን ቀሪዎችና “ሌሎች በጎች” “ስለ አምላክ መንግሥት በሚገባ [እንዲመሠክሩ]” ኃይል እየሰጣቸው ያለው ይኸው መንፈስ ነው፤ ምሥራቹን ከ240 በሚበልጡ አገሮች ውስጥ ይሰብካሉ! (ዮሐ. 10:16፤ ሥራ 28:23) አንተስ በዚህ ሥራ የተሟላ ተሳትፎ እያደረግክ ነው?

a ጳውሎስ፣ አናሲሞስን እሱ ጋር ሊያስቀረው ፈልጎ ነበር። ይሁን እንጂ እንዲህ ቢያደርግ የሮምን ሕግ መጣስ ይሆንበታል፤ የአናሲሞስ ጌታ የሆነውን ፊልሞና የተባለውን ክርስቲያን መብትም ይጋፋል። በመሆኑም አናሲሞስ፣ ጳውሎስ ለፊልሞና የጻፈውን ደብዳቤ ይዞ ወደ ጌታው ተመልሷል፤ ጳውሎስ በደብዳቤው ላይ ፊልሞና፣ ባሪያውን እንደ መንፈሳዊ ወንድም ቆጥሮ በደግነት እንዲቀበለው አበረታቶታል።—ፊልሞና 13-19

c የጳውሎስ ሕይወት ከ61 ዓ.ም. በኋላ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

d ምሥራቹ ‘ለፍጥረት ሁሉ ተሰብኳል’” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።