በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 26

“ከእናንተ አንድም ሰው አይጠፋም”

“ከእናንተ አንድም ሰው አይጠፋም”

ጳውሎስ የመርከብ መሰበር አደጋ አጋጠመው፤ ይህ አጋጣሚ የጳውሎስን ጠንካራ እምነትና ለሰዎች ያለውን ፍቅር አሳይቷል

በሐዋርያት ሥራ 27:1 እስከ 28:10 ላይ የተመሠረተ

1, 2. ጳውሎስ የትኛው ጉዞ ይጠብቀዋል? የትኞቹ ጉዳዮችስ አሳስበውት ሊሆን ይችላል?

 ጳውሎስ አገረ ገዢው ፊስጦስ የተናገራቸውን ቃላት በአእምሮው እያውጠነጠነ ነው። “ወደ ቄሳር ትሄዳለህ” ብሎታል፤ ይህ ውሳኔ ቀጣይ ዕጣ ፈንታውን እንደሚወስነው ያውቃል። ጳውሎስ ሁለት ዓመት ሙሉ እስር ቤት ውስጥ አሳልፏል፤ ወደ ሮም የሚያደርገው ረጅም ጉዞ ቢያንስ ለውጥ ይሆንለታል። (ሥራ 25:12) ይሁን እንጂ ጳውሎስ በባሕር ላይ ሲጓዝ ያጋጠሙት በርካታ ነገሮችም ወደ አእምሮው መምጣታቸው አይቀርም፤ ንጹሕ አየር እየተነፈሱና የተንጣለለውን አድማስ እያዩ ከመጓዝ ባለፈ አስቸጋሪ ሁኔታዎችም ሊያጋጥሙት እንደሚችሉ ያውቃል። በመጨረሻም ቄሳር ፊት መቅረብ እንደማይቀርለት ሲያስብ ልቡ መስጋቱ አይቀርም።

2 ጳውሎስ “በባሕር ላይ ለሚያጋጥም አደጋ” እንግዳ አይደለም፤ ሦስት ጊዜ የመርከብ መሰበር አደጋ አጋጥሞታል እንዲሁም አንድ ሌሊትና አንድ ቀን በባሕር ላይ አሳልፏል። (2 ቆሮ. 11:25, 26) ከዚህም ሌላ አሁን የሚያደርገው ጉዞ ነፃ ሰው ሆኖ ካደረጋቸው ሚስዮናዊ ጉዞዎች ፈጽሞ የተለየ ነው። አሁን የሚጓዘው እስረኛ ሆኖ ነው፤ ጉዞው ደግሞ እንዲህ የዋዛ አይደለም። ከቂሳርያ እስከ ሮም ያለው ርቀት ከ3,000 ኪሎ ሜትር በላይ ነው። በሰላም ጉዞውን አጠናቅቆ ካሰበበት ይደርስ ይሆን? እሺ፣ መድረሱንስ ይድረስ፤ እዚያስ ምን ይጠብቀው ይሆን? የሞት ፍርድ? ጳውሎስ ይግባኝ ያለው በወቅቱ በሰይጣን ዓለም ውስጥ ከሁሉ በላይ ኃያል ለሆነው መንግሥት እንደሆነ እናስታውስ።

3. ጳውሎስ ምን ለማድረግ ቆርጦ ነበር? በዚህ ምዕራፍ ላይ ምን እንመለከታለን?

3 ስለ ጳውሎስ እስካሁን ካነበብከው አንጻር ከፊቱ የሚጠብቀውን እያሰበ ተስፋው የሚጨልምበት ወይም በጭንቀት የሚዋጥ ዓይነት ሰው ይመስልሃል? በጭራሽ! እርግጥ ጳውሎስ ከፊቱ መከራ እንደሚጠብቀው ያውቃል፤ ምን ዓይነት ችግሮች የሚለውን ግን በዝርዝር አያውቅም። ታዲያ ከቁጥጥሩ ውጭ ስለሆኑ ጉዳዮች በመጨነቅ ከአገልግሎቱ የሚያገኘውን ደስታ የሚያጣበት ምን ምክንያት አለ? (ማቴ. 6:27, 34) ጳውሎስ የይሖዋ ፈቃድ ምን እንደሆነ ያውቃል፤ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ለሰዎች፣ ለገዢዎችም ጭምር የአምላክን መንግሥት ምሥራች እንዲሰብክ ተልእኮ ተሰጥቶታል። (ሥራ 9:15) የመጣው ቢመጣ የተሰጠውን ተልእኮ ዳር ለማድረስ ቆርጧል። የእኛስ ቁርጥ አቋም ይህ አይደል? እንግዲያው በዚህ ታሪካዊ ጉዞ ላይ ጳውሎስ ምን እንዳጋጠመው እስቲ እንመልከት፤ ከእሱ ምሳሌ ለሕይወታችን የሚጠቅም ምን ትምህርት እናገኝ ይሆን?

“ነፋሱ ከፊት ለፊታችን ይነፍስ” ነበር (የሐዋርያት ሥራ 27:1-7ሀ)

4. ጳውሎስ ጉዞ የጀመረው በምን ዓይነት መርከብ ነው? እነማንስ አብረውት ነበሩ?

4 ጳውሎስና የተወሰኑ እስረኞች ዩልዮስ በሚባል የጦር መኮንን ኃላፊነት እንዲጓዙ ተወሰነ፤ እሱም ወደ ቂሳርያ በመጣ የንግድ መርከብ ለመሳፈር አሰበ። መርከቡ የመጣው በትንሿ እስያ ምዕራባዊ የባሕር ዳርቻ ላይ ካለው የአድራሚጢስ ወደብ ነው፤ አድራሚጢስ በሌዝቮስ ደሴት ላይ ካለችው የሚጢሊኒ ከተማ ማዶ የሚገኝ ወደብ ነው። መርከቡ በመጀመሪያ ወደ ሰሜን አቅጣጫ ከዚያም ወደ ምዕራብ የሚጓዝ ሲሆን ዕቃ ለማራገፍና ለመጫን አንዳንድ ቦታዎች ላይ ይቆማል። እንዲህ ዓይነቶቹ መርከቦች የመንገደኞችን ምቾት ለመጠበቅ ታስበው የተሠሩ አይደሉም፤ በተለይ ደግሞ ለእስረኞች ፈጽሞ አይመቹም። (“ የባሕር ጉዞና የንግድ መስመሮች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) ጥሩነቱ፣ በመንገደኞቹ መካከል ያለው ክርስቲያን ጳውሎስ ብቻ አይደለም። ቢያንስ ሁለት የእምነት ባልንጀሮቹ አብረውት ስላሉ ብቻውን ከወንጀለኞች ጋር ለመጓዝ አልተገደደም፤ አርስጥሮኮስና ሉቃስ ከጎኑ ነበሩ። እንደሚታወቀው፣ ይህን ዘገባ የጻፈው ሉቃስ ነው። እነዚህ ሁለት ታማኝ ወዳጆቹ የጉዟቸውን ወጪ የሸፈኑት ራሳቸው ናቸው? ወይስ እንደ ጳውሎስ አገልጋዮች ተቆጥረው በነፃ ተጓዙ? ዘገባው የሚገልጸው ነገር የለም።—ሥራ 27:1, 2

5. ጳውሎስ በሲዶና ከእነማን ጋር የመገናኘት አጋጣሚ አግኝቷል? ከዚህስ ምን ትምህርት እናገኛለን?

5 በስተ ሰሜን 110 ኪሎ ሜትር ያህል ከተጓዙ በኋላ በማግስቱ መርከቡ በሶርያ የባሕር ዳርቻ የምትገኘው ሲዶና ላይ ቆመ። ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው ዩልዮስ ጳውሎስን የያዘው ከሌሎቹ ወንጀለኞች በተለየ መንገድ ነው፤ ይህን ያደረገው ጳውሎስ፣ ጥፋተኛ መሆኑ ያልተረጋገጠ የሮም ዜጋ ስለሆነ ይመስላል። (ሥራ 22:27, 28፤ 26:31, 32) ጳውሎስ ከመርከብ ወርዶ ክርስቲያን ባልንጀሮቹ ጋ እንዲሄድ ዩልዮስ ፈቀደለት። እነዚህ ወንድሞችና እህቶች ለረጅም ጊዜ የታሰረውን ይህን ሐዋርያ የመንከባከብ አጋጣሚ በማግኘታቸው ምንኛ ተደስተው ይሆን! አንተስ እንደዚህ ዓይነት እንግዳ ተቀባይነት ማሳየት የምትችልበት አጋጣሚ ይኖር ይሆን? በዚህ መንገድ ፍቅር ስታሳይ አንተም በምላሹ ትታነጻለህ።—ሥራ 27:3

6-8. ከሲዶና እስከ ቀኒዶስ ያለው የጳውሎስ ጉዞ ምን ይመስል ነበር? መስበክ የሚችልባቸው ምን አጋጣሚዎችስ ተከፍተውለት ነበር?

6 መርከቡ ከሲዶና ተነስቶ ጉዞውን በመቀጠል ኪልቅያን አልፎ ሄደ፤ ኪልቅያ የምትገኘው ጳውሎስ ባደገባት በጠርሴስ አቅራቢያ ነው። ሉቃስ ሌላ ቦታ ላይ እንደቆሙ አልጠቀሰም፤ በእርግጥ “ነፋሱ ከፊት ለፊታችን ይነፍስ [ነበር]” ማለቱ አደገኛ ሁኔታ አጋጥሟቸው እንደነበር ይጠቁማል። (ሥራ 27:4, 5) እንዲህ ያለ ሁኔታ ቢኖርም ጳውሎስ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ምሥራቹን ይሰብክ እንደነበር መገመት እንችላለን። ለመርከበኞቹ፣ ለወታደሮቹ እንዲሁም እንደ እሱ እስረኛ ለሆኑትም ሆነ ለሌሎቹ ተሳፋሪዎች መሥክሮላቸው እንደሚሆን ጥያቄ የለውም፤ መርከቡ በቆመባቸው ወደቦች ላይ ለሚያገኛቸውም ቢሆን መስበኩ አይቀርም። እኛስ ለመስበክ የሚያስችሉንን አጋጣሚዎች በሚገባ እንጠቀምባቸዋለን?

7 ከተወሰነ ጊዜ በኋላ መርከቡ በትንሿ እስያ ደቡባዊ የባሕር ዳርቻ ላይ ወደሚገኘው የሚራ ወደብ ደረሰ። በዚያም ጳውሎስና ሌሎቹ ሰዎች ወደ ጉዟቸው መጨረሻ ይኸውም ወደ ሮም የሚያደርሳቸው ሌላ መርከብ መቀየር ያስፈልጋቸው ነበር። (ሥራ 27:6) በዚያ ዘመን ለሮም አብዛኛውን ስንዴ የምታቀርበው ግብፅ ነበረች፤ እህል የጫኑ የግብፅ መርከቦች ሚራ ወደብ ላይ ይቆሙ ነበር። ዩልዮስ እንዲህ ዓይነት መርከብ አገኘና ወታደሮቹና እስረኞቹ እንዲሳፈሩ አደረገ። ይህ መርከብ ከመጀመሪያው በጣም የሚተልቅ ሳይሆን አይቀርም። መርከቡ ብዙ ዋጋ የሚያወጣ ስንዴ ጭኗል፤ በዚያ ላይ ደግሞ መርከበኞቹን፣ ወታደሮቹን፣ እስረኞቹንና ወደ ሮም የሚሄዱ ሌሎች ሰዎችን ጨምሮ በድምሩ 276 ሰዎችን አሳፍሯል። መርከብ ሲቀይሩ የጳውሎስ የአገልግሎት ክልል እንደሰፋ ግልጽ ነው፤ ደግሞም ጳውሎስ ይህ ሁኔታ የፈጠረውን አጋጣሚ እንደሚጠቀምበት የታወቀ ነው።

8 ቀጥሎ የቆሙት፣ በትንሿ እስያ ደቡብ ምዕራብ ጫፍ ላይ በምትገኘው በቀኒዶስ ነው። ነፋሱ ለጉዞ ተስማሚ ቢሆን ኖሮ ይህ የአንድ ቀን ጉዞ ነበር። ይሁንና ሉቃስ “ለብዙ ቀናት በዝግታ ተጉዘን በስንት ችግር ቀኒዶስ ደረስን” ሲል ጽፏል። (ሥራ 27:7ሀ) የአየሩ ሁኔታ ለጉዞ አስቸጋሪ እየሆነባቸው መጣ። (“ አስቸጋሪ የሆነው የሜድትራንያን ነፋስ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) ኃይለኛው ነፋስና ማዕበሉ መርከቡን ከዚያም ከዚህም ሲያላጋው ተሳፋሪዎቹ እንዴት እንደሚንገላቱ አስበው።

‘አውሎ ነፋሱ ክፉኛ አንገላታን’ (የሐዋርያት ሥራ 27:7ለ-26)

9, 10. በቀርጤስ አካባቢ ምን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ተፈጠሩ?

9 የመርከቡ አዛዥ ከቀኒዶስ ተነስቶ ወደ ምዕራብ አቅጣጫ ጉዞውን ለመቀጠል አቅዶ ነበር፤ ይሁንና በቦታው የነበረው ሉቃስ እንደዘገበው ‘ነፋሱ እንደ ልብ ለመጓዝ አልፈቀደላቸውም።’ (ሥራ 27:7ለ) መርከቡ ከየብስ እየራቀ ሲሄድ በባሕሩ ዳርቻ ካለው ለጉዞ ተስማሚ ሞገድ ራቀ፤ ከሰሜን ምዕራብ የመጣው ኃይለኛ ነፋስ ወደ ደቡብ አቅጣጫ ገፋው፤ ምናልባትም በፍጥነት እየነዳ ወስዶት ሊሆን ይችላል። እንደምታስታውሰው፣ ቀደም ሲል የተሳፈሩበት መርከብ ኃይለኛውን ነፋስ ያለፈው የቆጵሮስ ደሴትን ተገን አድርጎ ነው፤ አሁን ደግሞ ለዚህኛው መርከብ የቀርጤስ ደሴት ተገን ሆነለት። መርከቡ በቀርጤስ ምሥራቃዊ ዳርቻ የምትገኘውን ስልሞናን ካለፈ በኋላ ሁኔታው በመጠኑ ተሻሻለ። ምን ተገኘ? መርከቡ ከደሴቱ በስተ ደቡብ በኩል ስላለ የብሱ ኃይለኛውን ነፋስ አበረደለት። ተሳፋሪዎቹ በዚህ ጊዜ የተሰማቸውን እፎይታ መገመት ይቻላል! መርከበኞቹ ግን ባሕር ላይ እስካሉ ድረስ መረጋጋት እንደማይችሉ ያውቃሉ፤ ክረምት እየቀረበ በመሆኑ ከፊታቸው አሳሳቢ ሁኔታ ተደቅኗል።

10 ሉቃስ “[የቀርጤስን የባሕር] ዳርቻ ይዘን በብዙ ችግር በመጓዝ . . . ‘መልካም ወደብ’ ወደተባለ ስፍራ ደረስን” ሲል ዘግቧል። ደሴቱ ከለላ ሆኖላቸውም እንኳ መርከቡን መቆጣጠር በጣም አዳጋች ነበር። በመጨረሻ ግን መልሕቃቸውን መጣል የሚችሉበት ቦታ አገኙ፤ ይህ ወደብ የባሕሩ ዳርቻ ወደ ሰሜን እጥፍ የሚልበት ቦታ ላይ እንደሚገኝ ይገመታል። ለመሆኑ በዚህ ቦታ ምን ያህል ጊዜ ቆዩ? ሉቃስ “ረጅም ጊዜ” መቆየታቸውን ገልጿል፤ ሆኖም ለጉዞ አመቺ የሆነው ጊዜ እየተሟጠጠባቸው ነው። በመስከረም/በጥቅምት ወር በባሕር ላይ መጓዝ የባሰ አደገኛ ይሆናል።—ሥራ 27:8, 9

11. ጳውሎስ አብረውት ለሚጓዙት ሰዎች ምን ምክር ሰጠ? ይሁንና ሰዎቹ ምን ለማድረግ ወሰኑ?

11 ጳውሎስ በሜድትራንያን ባሕር ላይ የመጓዝ ልምድ ስላለው አንዳንድ መንገደኞች ምክር ጠይቀውት ሊሆን ይችላል። እሱም መርከቡ ጉዞ መቀጠል እንደሌለበት ሐሳብ አቀረበ። ጉዞ ከቀጠለ ግን “ከፍተኛ ጉዳትና ጥፋት” ሊደርስ ምናልባትም የሰው ሕይወት ሊጠፋ ይችላል። ይሁን እንጂ የመርከቡ መሪና የመርከቡ ባለቤት ጉዟቸውን መቀጠል ፈለጉ፤ ምናልባትም ይበልጥ አስተማማኝ ቦታ በአፋጣኝ ማግኘት እንዳለባቸው ተሰምቷቸው ይሆናል። ሰዎቹ ዩልዮስን አሳመኑት፤ አብዛኞቹ መንገደኞችም እንደ ምንም ብለው ፊንቄ ወደብ ለመድረስ መረጡ። አሁን ካሉበት ራቅ ብላ በቀርጤስ የባሕር ዳርቻ ላይ የምትገኘው ፊንቄ ክረምቱን ማሳለፍ የሚችሉበት ትልቅና የተሻለ ወደብ ሳይኖራት አይቀርም። ለጉዞ ተስማሚ የሚመስል የደቡብ ነፋስ በቀስታ ሲነፍስ ደግሞ ተነስተው ጉዞ ጀመሩ።—ሥራ 27:10-13

12. መርከቡ ቀርጤስን ለቆ ከሄደ በኋላ ምን አደጋዎች አጋጠሙት? መርከበኞቹ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስባቸው ምን አደረጉ?

12 ብዙም ሳይቆይ ግን ሌላ ጣጣ መጣ፦ ከሰሜን ምሥራቅ አቅጣጫ “ኃይለኛ አውሎ ነፋስ” መጣባቸው። ከመልካም ወደብ 65 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ የምትገኝ ‘ቄዳ የተባለች ትንሽ ደሴት’ ለተወሰነ ጊዜ ተገን ሆነችላቸው። አውሎ ነፋሱ ግን አሁንም መርከቡን ወደ ደቡብ አቅጣጫ ገፍቶ ሊወስደው ይችላል፤ መርከቡ በአፍሪካ የባሕር ዳርቻ አቅራቢያ ከሚገኝ የአሸዋ ቁልል ጋር የመላተም አደጋ ተደቅኖበት ነበር። መርከበኞቹ ይህ እንዳይደርስባቸው ስለፈሩ መርከቡ ከኋላ የሚጎትታትን ትንሽ ጀልባ ስበው ወደ መርከቡ አስገቧት። ጀልባዋ በውኃ ስለተሞላች ሳይሆን አይቀርም ይህ የሆነላቸው በስንት መከራ ነው። ከዚያም መርከቡ የተሠራባቸው ጣውላዎች እንዳይበታተኑ ከሥር በኩል ዙሪያውን በገመድ ወይም በሰንሰለት በማሰር አጠናከሩት። ገመዶቹን በመፍታት ሸራውን ዝቅ ካደረጉ በኋላ ነፋሱን ፊት ለፊት በመጋፈጥ ማዕበሉን ሰንጥቆ እንዲያልፍ ለማድረግ ይታገሉ ጀመር። ሁኔታው ምን ያህል አስፈሪ እንደሚሆን አስበው! ይህ ሁሉ ተደርጎም ጉዞው የዋዛ አልነበረም፤ ሉቃስ “አውሎ ነፋሱ ክፉኛ እያንገላታን [ነበር]” ብሏል። በሦስተኛው ቀን ለመርከቡ የሚያገለግሉትን ዕቃዎች ወደ ባሕሩ ወረወሩ፤ እንዲህ ያደረጉት መርከቡ መንሳፈፍ እንዲቀለው ብለው ሳይሆን አይቀርም።—ሥራ 27:14-19

13. ጳውሎስ በተሳፈረበት መርከብ ላይ ሁኔታው ምን ይመስል ነበር?

13 ተሳፋሪዎቹ በፍርሃት ተውጠው መሆን አለበት። ጳውሎስና ጓደኞቹ ግን አልተሸበሩም። ቀደም ሲል ጌታ፣ በሮም እንደሚመሠክርለት ለጳውሎስ ማረጋገጫ ሰጥቶታል፤ (ሥራ 19:21፤ 23:11) በኋላ ደግሞ አንድ መልአክ ይህንኑ ተስፋ ደግሞለታል። ይሁንና ኃይለኛው ውሽንፍር ለሁለት ሳምንት ሌት ተቀን አንገላታቸው። ዝናቡ ሊያባራ አልቻለም፤ ደመናው ደግሞ ጥቅጥቅ ከማለቱ የተነሳ ፀሐይና ከዋክብት አልታይ አሉ፤ በመሆኑም የመርከቡ መሪ የት ቦታ እንዳሉ ወይም ወዴት እያመሩ እንደሆነ የሚጠቁሙ ነገሮች ማየት አልቻለም። በዚህ ሁሉ መሃል እህል መቅመስ ጨርሶ የማይታሰብ ነው። ብርዱ፣ ዝናቡ፣ ባሕሩ የሚፈጥረው የማጥወልወል ስሜት፣ በዚያ ላይ ፍርሃት ቀስፎ ይዞት ምግብ የሚያሰኘው ሰው ይኖራል?

14, 15. (ሀ) ጳውሎስ አብረውት ለሚጓዙት ሰዎች ቀደም ሲል የሰጣቸውን ማስጠንቀቂያ የጠቀሰው ለምንድን ነው? (ለ) ጳውሎስ ሕይወታቸው እንደሚተርፍ ከተናገረው የተስፋ መልእክት ምን ትምህርት እናገኛለን?

14 በዚህ ሁኔታ ላይ እያሉ ጳውሎስ ተነስቶ በመካከላቸው ቆመ። ቀደም ሲል ምን ብሏቸው እንደነበር ጠቀሰ፤ እርግጥ እንዲህ ያለው ‘እኔ’ኮ ነግሬያችሁ ነበር’ በሚል መንፈስ አይደለም። ይልቁንም የደረሰባቸው ነገር፣ እሱ የተናገረው ሐሳብ ጥበብ ያዘለ እንደነበረ በግልጽ ያሳያል። በመቀጠል እንዲህ አለ፦ “አሁንም ቢሆን አይዟችሁ! ምክንያቱም መርከቡ ብቻ እንጂ ከእናንተ አንድም ሰው አይጠፋም።” (ሥራ 27:21, 22) ሰዎቹ ይህን ሲሰሙ ምንኛ ተጽናንተው ይሆን! ጳውሎስም ቢሆን ለሰዎቹ የሚናገረው ይህን የመሰለ የተስፋ መልእክት ከይሖዋ በማግኘቱ እጅግ ተደስቶ መሆን አለበት። ይሖዋ የእያንዳንዱ ሰው ሕይወት እንደሚያሳስበው ፈጽሞ መዘንጋት አይኖርብንም። ሁሉም ሰው በእሱ ዘንድ ትልቅ ቦታ አለው። ሐዋርያው ጴጥሮስ “ይሖዋ . . . ሁሉ ለንስሐ እንዲበቃ እንጂ ማንም እንዲጠፋ [አይፈልግም]” ሲል ጽፏል። (2 ጴጥ. 3:9) እንግዲያው እኛም የይሖዋን የተስፋ መልእክት በተቻለ መጠን ለብዙዎች ለማድረስ ጥረት ማድረጋችን ምንኛ አጣዳፊ ነው! ክቡር የሆነው የሰው ልጅ ሕይወት አደጋ ላይ ነው።

15 ጳውሎስ በመርከቡ ላይ ለነበሩ በርካታ ሰዎች ‘አምላክ ስለሰጠው ተስፋ’ ሳይመሠክርላቸው አልቀረም። (ሥራ 26:6፤ ቆላ. 1:5) የመርከብ መሰበር አደጋ ተደቅኖባቸው ባለበት በዚህ ወቅት ደግሞ ዛሬን የመትረፍ ተስፋቸውን የሚያለመልምላቸው አሳማኝ ማስረጃ ሊነግራቸው ነው። ሐዋርያው እንዲህ አለ፦ “ንብረቱ የሆንኩለት አምላክ የላከው መልአክ ትናንት ሌሊት አጠገቤ ቆሞ ‘ጳውሎስ ሆይ፣ አትፍራ። ቄሳር ፊት መቅረብ ይገባሃል፤ አምላክ ለአንተ ሲል ከአንተ ጋር የሚጓዙት ሰዎች ሁሉ እንዲተርፉ ያደርጋል’ ብሎኛል።” ከዚያም እንዲህ ሲል አሳሰባቸው፦ “ስለዚህ እናንተ ሰዎች፣ አይዟችሁ! ምክንያቱም ይህ የተነገረኝ ነገር በትክክል እንደሚፈጸም በአምላክ ላይ እምነት አለኝ። ይሁን እንጂ ከአንዲት ደሴት ዳርቻ ጋር መላተማችን የግድ ነው።”—ሥራ 27:23-26

“ሁሉም በደህና ወደ የብስ ደረሱ” (የሐዋርያት ሥራ 27:27-44)

“በሁሉ ፊት አምላክን አመሰገነ።”—የሐዋርያት ሥራ 27:35

16, 17. (ሀ) ጳውሎስ የጸለየው የትኛውን አጋጣሚ ተጠቅሞ ነው? ይህስ ምን ውጤት አስገኘ? (ለ) ጳውሎስ የተናገረው ነገር የተፈጸመው እንዴት ነው?

16 መርከቡ አስፈሪ በሆኑት ሁለት ሳምንታት ውስጥ 870 ኪሎ ሜትር ገደማ በነፋስ እየተገፋ ሄዷል፤ አሁን ግን መርከበኞቹ የሆነ ለውጥ አስተዋሉ፤ ምናልባትም ውኃ ከመሬት ጋር ሲላተም የሚፈጥረውን ድምፅ ሰምተው ሊሆን ይችላል። ከፊት ለፊታቸው የብስ ካለም ወደዚያ ለማምራት አሰቡ፤ ስለዚህ ከኋላ ያሉትን መልሕቆች በመጣል መርከቡ ካሉበት ቦታ እየተገፋ እንዳይሄድ፣ የፊተኛው ክፍልም ወደ የብሱ አቅጣጫ እንዲሆን ለማድረግ ሞከሩ። በዚህ ጊዜ መርከበኞቹ መርከቡን ጥለው ለማምለጥ ሞክረው ነበር፤ ወታደሮቹ ግን እንዳይሄዱ ከለከሏቸው። ጳውሎስ መኮንኑንና ወታደሮቹን “እነዚህ ሰዎች መርከቡን ጥለው ከሄዱ ልትድኑ አትችሉም” አላቸው። መርከቡ ትንሽ ከተረጋጋ በኋላ ጳውሎስ ምግብ እንዲበሉ አበረታታቸው፤ ሁሉም እንደሚተርፉም በድጋሚ ነገራቸው። ከዚያም “በሁሉ ፊት አምላክን አመሰገነ።” (ሥራ 27:31, 35) ጳውሎስ ያቀረበው ይህ የምስጋና ጸሎት ለሉቃስም ሆነ ለአርስጥሮኮስ እንዲሁም ዛሬ ላሉ ክርስቲያኖች ግሩም ምሳሌ ይሆናል። አንተስ በሌሎች ሰዎች ፊት የምታቀርበው ጸሎት ሰሚዎቹን የሚያበረታታና የሚያጽናና ነው?

17 ጳውሎስ ከጸለየ በኋላ “ሁሉም ተበረታተው ምግብ እየወሰዱ ይበሉ ጀመር።” (ሥራ 27:36) ከዚያም የተጫነውን ስንዴ ወደ ባሕሩ በመጣል መርከቡ ቀለል እንዲል አደረጉ፤ ይህም ወደ ባሕሩ ዳርቻ እየተጠጋ ሲመጣ መሬት ሳይነካ ከፍ ብሎ ለመንሳፈፍ ያስችለዋል። ጎህ ሲቀድ መርከበኞቹ መልሕቆቹን ቆርጠው ጣሉ፣ ከበስተ ኋላ ያሉትን መቅዘፊያዎች ገመዶች ፈቱ እንዲሁም የፊተኛውን ሸራ ከፍ አደረጉ፤ እንዲህ ያደረጉት መርከቡን ባሕሩ ዳር በሚያቆሙበት ጊዜ እንቅስቃሴውን ለመቆጣጠር እንዲያመቻቸው ነው። ወደ ዳርቻው እያመሩ ሳለ ግን የመርከቡ ፊተኛ ክፍል የአሸዋ ቁልል ውስጥ ተቀረቀረ፤ ኃይለኛው ማዕበል ደግሞ የኋለኛውን ክፍል እየመታ ይሰባብረው ጀመር። አንዳንዶቹ ወታደሮች እስረኞቹ እንዳያመልጡ ሲሉ ሁሉንም ለመግደል አሰቡ፤ ዩልዮስ ግን ይህን እንዳያደርጉ ከለከላቸው። ሁሉም እየዋኙ ወይም በሆነ ነገር ላይ ተንሳፈው ወደ ባሕሩ ዳርቻ እንዲሄዱ አዘዘ። በመጨረሻ ጳውሎስ የተናገረው ነገር ተፈጸመ፤ 276ቱም መንገደኞች በሕይወት ተረፉ። አዎ፣ “ሁሉም በደህና ወደ የብስ ደረሱ።” ሆኖም የት ነው ያሉት?—ሥራ 27:44

“የተለየ ደግነት” (የሐዋርያት ሥራ 28:1-10)

18-20. የማልታ ነዋሪዎች “የተለየ ደግነት” ያሳዩት እንዴት ነው? አምላክ በጳውሎስ አማካኝነት ምን ተአምር ፈጸመ?

18 ከአደጋው የተረፉት ሰዎች ከሲሲሊ በስተ ደቡብ ማልታ በተባለች ደሴት ላይ እንደሚገኙ ተገነዘቡ። (“ ማልታ የምትገኘው የት ነው?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) ባዕድ ቋንቋ የሚናገሩት የደሴቲቱ ነዋሪዎች “የተለየ ደግነት” አሳዩአቸው። (ሥራ 28:2) የማልታ ሰዎች በውኃ ርሰውና በብርድ እየተንቀጠቀጡ ለመጡት እንግዶች እሳት አነደዱላቸው። ብርዱና ዝናቡ ባያቆምም እሳቱ ሞቅ አደረጋቸው። በተጨማሪም አንድ ተአምር እንዲፈጸም ምክንያት ሆነ።

19 ጳውሎስ ሰዎቹን ለማገዝ ሲል ጭራሮ ሰብስቦ እሳቱ ውስጥ ጨመረው። በዚህ ጊዜ አንዲት መርዛማ እፉኝት እጁ ላይ ተጣበቀችና ነደፈችው። የማልታ ሰዎች ይህ ነገር መለኮታዊ ቅጣት እንደሆነ ተሰምቷቸው ነበር። a

20 ጳውሎስ ሲነደፍ ያዩት የአካባቢው ነዋሪዎች “ሰውነቱ ያብጣል” ብለው አስበው ነበር። አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ እንደገለጸው እዚህ ቦታ ላይ የገባው ግሪክኛ ቃል “የሕክምና ቃል” ነው። ጸሐፊው “የተወደደው ሐኪም ሉቃስ” በመሆኑ እንዲህ ዓይነት ቃል መጠቀሙ አያስገርምም። (ሥራ 28:6፤ ቆላ. 4:14) ያም ሆነ ይህ ጳውሎስ መርዛማዋን እባብ ከእጁ ላይ አራገፋት፤ አንዳች ጉዳትም አልደረሰበትም።

21. (ሀ) ሉቃስ ባሰፈረው በዚህ ዘገባ ላይ ሙያዊ ትክክለኛነትን የሚጠይቁ ምን ነገሮች ገልጿል? (ለ) ጳውሎስ ምን ተአምራት ፈጽሟል? ይህስ በማልታ ነዋሪዎች ላይ ምን ስሜት አሳድሯል?

21 ፑፕልዮስ የሚባል ሀብታም ባለርስት በዚህ አካባቢ ይኖር ነበር። በሮም የተሾመው የማልታ ዋና አስተዳዳሪ እሱ ሳይሆን አይቀርም። ሉቃስ ይህን ግለሰብ “የደሴቲቱ አስተዳዳሪ” ብሎታል፤ በማልታ ቋንቋ በተቀረጹ ሁለት ጽሑፎች ላይ ይኸው የማዕረግ ስም ተገኝቷል። ፑፕልዮስ ጳውሎስንና ጓደኞቹን ለሦስት ቀናት በእንግድነት ተቀበላቸው። ይሁንና የፑፕልዮስ አባት ታሞ ነበር። በዚህ ጊዜም ቢሆን ሉቃስ በሽታውን በትክክል ገልጾታል። ሰውየው “ትኩሳትና ተቅማጥ ይዞት ተኝቶ ነበር” በማለት የበሽታውን ምልክቶች በትክክለኛው የሕክምና አገላለጽ አስፍሮታል። ጳውሎስ ከጸለየለትና እጁን ከጫነበት በኋላ ሰውየው ተፈወሰ። የአካባቢው ነዋሪዎች በዚህ ተአምር በጣም ስለተደነቁ ጳውሎስ እንዲፈውሳቸው ሌሎች በሽተኞችን ይዘው መጡ፤ ከዚህም ሌላ ጳውሎስንና ጓደኞቹን በሚያስፈልጓቸው ነገሮች ለማገዝ ስጦታ አመጡላቸው።—ሥራ 28:7-10

22. (ሀ) አንድ ፕሮፌሰር፣ ወደ ሮም የተደረገውን ጉዞ በተመለከተ ሉቃስ ስለጻፈው ዘገባ ምን ብለዋል? (ለ) በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ ምን እንመለከታለን?

22 ጳውሎስ ስላደረገው ጉዞ እስካሁን የተመለከትነው ዘገባ ሐቁን በትክክል አስፍሯል። አንድ ፕሮፌሰር እንዲህ ብለዋል፦ “መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሉቃስ ዘገባን ያህል . . . ምስል ከሳች የአጻጻፍ ስልት የተንጸባረቀባቸው ዘገባዎች ብዙ አይደሉም። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ስለነበረው የባሕር ጉዞም ሆነ በምሥራቃዊው የሜድትራንያን ባሕር ላይ ስላለው ሁኔታ በዝርዝር የጻፋቸው ነገሮች በጣም ትክክለኛ ናቸው”፤ ከዚህ አንጻር ዘገባዎቹ የተመሠረቱት በዕለት ውሎ ማስታወሻዎች ላይ ነው ብሎ መደምደም ይቻላል። ሉቃስ ከሐዋርያው ጋር በሚጓዝበት ወቅት እንዲህ ዓይነት ማስታወሻዎችን ይዞ ሊሆን ይችላል። በቀጣዩ ጉዟቸው ላይ ደግሞ ገና ብዙ የሚጽፈው ነገር ያገኛል። በመጨረሻ ሮም ሲደርሱ ጳውሎስ ምን ያጋጥመው ይሆን? እስቲ እንመልከት።

a ነዋሪዎቹ እፉኝቷን ማወቃቸው በዚያን ጊዜ ደሴቲቱ ላይ እንዲህ ዓይነት እባቦች እንደነበሩ ይጠቁማል። ዛሬ በማልታ ደሴት ላይ እፉኝት አይገኝም። ለዚህ አንዱ ምክንያት ባለፉት በርካታ ዘመናት በአካባቢው ሥነ ምህዳር ላይ የተከሰተው ለውጥ ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ ደሴቲቱ ላይ የሕዝብ ብዛት እየጨመረ መሄዱ እፉኝቶች እንዲጠፉ አድርጎ ይሆናል።