በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 11

“በደስታና በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ”

“በደስታና በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ”

ጳውሎስ ተቃዋሚዎችንና መልእክቱን የማይቀበሉ ሰዎችን ከያዘበት መንገድ የምናገኘው ትምህርት

በሐዋርያት ሥራ 13:1-52 ላይ የተመሠረተ

1, 2. በርናባስና ሳኦል ሊያደርጉት ያሰቡትን ጉዞ ለየት የሚያደርገው ምንድን ነው? የሚያከናውኑት ሥራስ የሐዋርያት ሥራ 1:8 ፍጻሜውን እንዲያገኝ አስተዋጽኦ የሚያደርገው እንዴት ነው?

 በአንጾኪያ ያለው ጉባኤ እጅግ የተደሰተበት ዕለት ነው። በዚያ ከነበሩት ነቢያትና አስተማሪዎች መካከል በርናባስና ሳኦል በመንፈስ ቅዱስ ተመረጡ፤ ተልእኳቸው ምሥራቹን ራቅ ወዳሉ ቦታዎች ማድረስ ነው። a (ሥራ 13:1, 2) እውነት ነው፣ ከዚያ በፊትም ቢሆን ብቃት ያላቸው ወንዶች ይላኩ ነበር። ይሁን እንጂ ቀደም ሲል ሚስዮናውያን የተላኩት የክርስትናን እምነት የተቀበሉ ሰዎች ወዳሉባቸው አካባቢዎች ነው። (ሥራ 8:14፤ 11:22) በዚህ ጊዜ ግን በርናባስና ሳኦል አብዛኞቹ ሰዎች ምሥራቹን ወዳልሰሙባቸው ቦታዎች ሊላኩ ነው፤ ዮሐንስ ማርቆስም አብሯቸው ይጓዛል፤ በጉዟቸው ላይ እንደ አገልጋይ ሆኖ ይረዳቸዋል።

2 ከ14 ዓመት ገደማ በፊት ኢየሱስ ተከታዮቹን “በኢየሩሳሌም፣ በመላው ይሁዳና በሰማርያ እንዲሁም እስከ ምድር ዳር ድረስ ምሥክሮቼ ትሆናላችሁ” ብሏቸው ነበር። (ሥራ 1:8) በርናባስና ሳኦል ሚስዮናዊ ሆነው እንዲያገለግሉ መሾማቸው ኢየሱስ የተናገረው ትንቢት ፍጻሜውን እንዲያገኝ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል! b

‘ለሥራው የተለዩ’ (የሐዋርያት ሥራ 13:1-12)

3. በመጀመሪያው መቶ ዘመን ረጅም ርቀት መጓዝ አስቸጋሪ የነበረው ለምንድን ነው?

3 እንደ መኪና እና አውሮፕላን ለመሳሰሉት ዘመናዊ መጓጓዣዎች ምስጋና ይግባቸውና በዛሬው ጊዜ በአንድ ወይም በሁለት ሰዓት ውስጥ ረጅም ርቀት መጓዝ ይቻላል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. ግን ሁኔታው ከዚህ የተለየ ነበር። ሰዎች በየብስ ላይ ከቦታ ወደ ቦታ ለመሄድ ብዙውን ጊዜ በእግራቸው መጓዝ ነበረባቸው፤ አብዛኞቹ መንገዶች ደግሞ ለጉዞ ምቹ አልነበሩም። የአንድ ቀን የእግር ጉዞ ከ30 ኪሎ ሜትር እምብዛም አይበልጥም፤ ጉዞውም ሰውነትን የሚያዝል ነው! c በመሆኑም በርናባስና ሳኦል፣ ተልእኳቸው አድካሚና ምቾትን መሥዋዕት ማድረግ የሚጠይቅ እንደሚሆን አይጠፋቸውም፤ ያም ሆኖ ወጥተው ለማገልገል እንደሚጓጉ ጥርጥር የለውም።—ማቴ. 16:24

4. (ሀ) በርናባስና ሳኦል የተመረጡት እንዴት ነው? የእምነት ባልንጀሮቻቸውስ በእነሱ መመረጥ ምን ተሰማቸው? (ለ) ቲኦክራሲያዊ ኃላፊነቶችን ለሚቀበሉ ወንድሞች ድጋፍ መስጠት የምንችለው እንዴት ነው?

4 ይሁን እንጂ መንፈስ ቅዱስ ‘ለአንድ ሥራ እንዲለዩ’ ከሌሎቹ ሁሉ በርናባስንና ሳኦልን የመረጠው ለምንድን ነው? (ሥራ 13:2) መጽሐፍ ቅዱስ ምክንያቱን አይገልጽም። የምናውቀው ነገር ቢኖር እነዚህ ሰዎች የተመረጡት መንፈስ ቅዱስ በሰጠው መመሪያ መሠረት መሆኑን ነው። በአንጾኪያ የነበሩት ነቢያትና አስተማሪዎች ውሳኔውን ለመቀበል አንገራግረው እንደነበር የሚጠቁም ምንም ነገር አናገኝም። ከዚህ ይልቅ የእነሱን መመረጥ ሙሉ በሙሉ ደግፈዋል። ዘገባው “ከጾሙና ከጸለዩ በኋላ እጃቸውን ጫኑባቸው፤ ከዚያም አሰናበቷቸው” ይላል፤ በርናባስና ሳኦል መንፈሳዊ ወንድሞቻቸው ምንም የቅናት ስሜት ሳያድርባቸው ሲያሰናብቷቸው ምን ያህል ተበረታተው እንደሚሆን አስብ። (ሥራ 13:3) እኛም ቲኦክራሲያዊ ኃላፊነቶች የሚሰጣቸውን ሁሉ ልንደግፋቸው ይገባል፤ ይህም የጉባኤ የበላይ ተመልካች ሆነው የሚሾሙትን ወንድሞች ይጨምራል። እንዲህ ዓይነት መብቶች ባገኙ ወንድሞች ከመቅናት ይልቅ “በሚያከናውኑት ሥራ የተነሳ በፍቅር ለየት ያለ አሳቢነት” ልናሳያቸው ይገባል።—1 ተሰ. 5:13

5. በርናባስና ሳኦል በቆጵሮስ ደሴት የሰበኩት እንዴት ነው?

5 በርናባስና ሳኦል በአንጾኪያ አቅራቢያ ወደምትገኘው ወደ ሴሌውቅያ ወደብ በእግራቸው ተጓዙ፤ ከዚያም መርከብ ተሳፍረው 200 ኪሎ ሜትር ርቃ ወደምትገኘው የቆጵሮስ ደሴት አቀኑ። d በርናባስ የቆጵሮስ ተወላጅ እንደመሆኑ መጠን ለአገሩ ሰዎች ምሥራቹን ለመንገር ጓጉቶ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። በመጨረሻም በደሴቲቱ ምሥራቃዊ ጠረፍ ወደምትገኘው ስልማና ከተማ ደረሱ፤ ጊዜ ሳያጠፉም “የአምላክን ቃል በአይሁዳውያን ምኩራቦች ማወጅ ጀመሩ።” e (ሥራ 13:5) ከዚህኛው የቆጵሮስ ጫፍ ተነስተው ደግሞ እስከ ሌላኛው ጫፍ ድረስ ተጓዙ፤ እግረ መንገዳቸውን ደሴቲቱ ላይ ባሉ ዋና ዋና ከተሞች ውስጥ ምሥራቹን ሰብከው መሆን አለበት። እነዚህ ሚስዮናውያን የትኛውን መንገድ ይዘው እንደተጓዙ ባናውቅም በጥቅሉ 160 ኪሎ ሜትር ገደማ ሳይጓዙ አልቀሩም!

6, 7. (ሀ) ሰርግዮስ ጳውሎስ ማን ነው? በርያሱስ ይህ ሰው ምሥራቹን እንዳይሰማ ሊያከላክል የሞከረውስ ለምንድን ነው? (ለ) ሳኦል፣ በርያሱስ ላስነሳው ተቃውሞ ምላሽ የሰጠው እንዴት ነው?

6 በመጀመሪያው መቶ ዘመን ቆጵሮስ የሐሰት አምልኮ መናኸሪያ ነበረች። በርናባስና ሳኦል በደሴቲቱ ምዕራባዊ ዳርቻ ወደምትገኘው ወደ ጳፎስ በደረሱ ጊዜ ያጋጠማቸው ሁኔታ ይህን በግልጽ የሚያሳይ ነው። በዚያ “በርያሱስ የተባለ . . . ጠንቋይና ሐሰተኛ ነቢይ” አገኙ። እሱም “ሰርግዮስ ጳውሎስ ከተባለው አስተዋይ የሮም አገረ ገዢ ጋር ነበር።” f በመጀመሪያው መቶ ዘመን የሠለጠኑ ናቸው የሚባሉ በርካታ ሮማውያን ትላልቅ ውሳኔዎች ሲያደርጉ ጠንቋዮችን ወይም ኮከብ ቆጣሪዎችን የማማከር ልማድ ነበራቸው፤ እንደ ሰርግዮስ ጳውሎስ ያሉ “አስተዋይ” ሰዎችም እንኳ ይህን ያደርጉ ነበር። ይሁንና ሰርግዮስ ጳውሎስ የመንግሥቱን ምሥራች ሲሰማ ደስ አለው፤ “የአምላክን ቃል ለመስማት [ጓጓ]።” ይህ ግን በርያሱስን አላስደሰተውም፤ በርያሱስ ‘ኤልማስ’ በመባልም ይታወቅ የነበረ ሲሆን ትርጉሙ “ጠንቋይ” ማለት ነው።—ሥራ 13:6-8

7 በርያሱስ የመንግሥቱን መልእክት ይቃወም ጀመር። ደግሞም የሰርግዮስ ጳውሎስ አማካሪ በመሆን ያገኘውን ከፍተኛ ሥልጣን ጠብቆ ማቆየት የሚችለው “አገረ ገዢው ይህን እምነት እንዳይቀበል” ማደናቀፍ ከቻለ ብቻ ነው። (ሥራ 13:8) ሆኖም ሳኦል፣ ይህ ጠንቋይ ለሰርግዮስ ጳውሎስ እንቅፋት እንዲሆን አልፈለገም። ታዲያ ምን አደረገ? ዘገባው እንዲህ ይላል፦ “ጳውሎስ ተብሎ የሚጠራው ሳኦል በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ትኩር ብሎ ተመለከተው፤ ከዚያም እንዲህ አለው፦ ‘አንተ ተንኮልና ክፋት ሁሉ የሞላብህ፣ የዲያብሎስ ልጅ፣ የጽድቅም ሁሉ ጠላት! ቀና የሆነውን የይሖዋን መንገድ ማጣመምህን አትተውም? እነሆ፣ የይሖዋ እጅ በአንተ ላይ ነው፤ ዓይነ ስውር ትሆናለህ፤ ለተወሰነ ጊዜም የፀሐይ ብርሃን አታይም።’ ወዲያውኑም ጭጋግና ጨለማ ዓይኑን ጋረደው፤ እጁን ይዞ የሚመራው ሰው ለማግኘትም ዙሪያውን መፈለግ ጀመረ።” g ታዲያ ይህ ተአምራዊ ክንውን ምን ውጤት አስገኘ? አገረ ገዢው “ስለ ይሖዋ በተማረው ነገር ተደንቆ ስለነበር ይህን ባየ ጊዜ አማኝ ሆነ።”—ሥራ 13:9-12

ልክ እንደ ጳውሎስ፣ ተቃውሞ በሚኖርበት ጊዜም እንኳ በድፍረት ለእውነት ጥብቅና እንቆማለን

8. ጳውሎስ ድፍረት በማሳየት ረገድ የተወውን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?

8 ጳውሎስ በርያሱስን አልፈራውም። እኛም ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን እምነት ለማዳከም የሚሞክሩ ተቃዋሚዎችን መፍራት የለብንም። እርግጥ ነው፣ ንግግራችን “ምንጊዜም በጨው የተቀመመ ያህል ለዛ ያለው” መሆን ይኖርበታል። (ቆላ. 4:6) ይሁን እንጂ ከሌሎች ጋር ላለመጋጨት ስንል ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን ከመርዳት መቆጠብ የለብንም። ወይም የሐሰት ሃይማኖቶች የሚፈጽሙትን መጥፎ ድርጊት ከማጋለጥ ወደኋላ አንልም፤ ምክንያቱም እነሱም እንደ በርያሱስ “ቀና የሆነውን የይሖዋን መንገድ” ያጣምማሉ። (ሥራ 13:10) ጳውሎስ እንዳደረገው ሁሉ እኛም እውነትን በድፍረት እናውጅ፤ ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች ከመርዳትም ወደኋላ አንበል። እርግጥ ነው፣ በጳውሎስ ጊዜ እንደሆነው፣ አምላክ የሚሰጠን ድጋፍ በግልጽ አይታይ ይሆናል፤ ሆኖም ይሖዋ የሚገባቸውን ሰዎች ወደ እውነት ለመሳብ ቅዱስ መንፈሱን እንደሚጠቀም እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ዮሐ. 6:44

‘የሚያበረታታ ቃል’ (የሐዋርያት ሥራ 13:13-43)

9. ጳውሎስና በርናባስ በዛሬው ጊዜ ጉባኤውን ግንባር ቀደም ሆነው ለሚመሩ ወንድሞች ግሩም ምሳሌ የሚሆኑት እንዴት ነው?

9 እነዚህ ሰዎች ከጳፎስ ተነስተው ባሕር ላይ በመጓዝ ጴርጌ ደረሱ፤ በትንሿ እስያ የባሕር ዳርቻ ላይ የምትገኘው ጴርጌ ከጳፎስ 250 ኪሎ ሜትር ትርቃለች። በዚህ ጊዜ አንድ ለውጥ የተደረገ ይመስላል። ምክንያቱም በሐዋርያት ሥራ 13:13 ላይ ዘገባው “ጳውሎስና ባልደረቦቹ” ይላል። ይህ አባባል ጳውሎስ ቡድኑን በግንባር ቀደምትነት መምራት እንደጀመረ ይጠቁማል። ሆኖም በርናባስ በጳውሎስ እንደቀና የሚጠቁም ምንም ነገር አናገኝም። ከዚህ በተቃራኒ እነዚህ ሁለት ሰዎች የአምላክን ፈቃድ ለመፈጸም ተባብረው መሥራታቸውን ቀጥለዋል። ጳውሎስና በርናባስ በዛሬው ጊዜ ጉባኤውን ግንባር ቀደም ሆነው ለሚመሩ ወንድሞች ግሩም ምሳሌ ይሆናሉ። ክርስቲያኖች፣ አንዳቸው ከሌላው ልቀው ለመታየት ከመሞከር ይልቅ ኢየሱስ “እናንተ ሁላችሁም ወንድማማቾች ናችሁ” በማለት የተናገረውን ሐሳብ ማስታወስ ይኖርባቸዋል። ኢየሱስ አክሎም “ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ዝቅ ይደረጋል፤ ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ሁሉ ደግሞ ከፍ ይደረጋል” ብሏል።—ማቴ. 23:8, 12

10. ጳውሎስና በርናባስ ከጴርጌ ወደ ጵስድያዋ አንጾኪያ ያደረጉትን ጉዞ ግለጽ።

10 ጴርጌ ሲደርሱ ዮሐንስ ማርቆስ ትቷቸው ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ። ዮሐንስ ማርቆስ ድንገት የተመለሰበት ምክንያት አልተገለጸም። ጳውሎስና በርናባስ ጉዟቸውን ቀጠሉ፤ ከጴርጌ ተነስተው ወደ ጵስድያዋ አንጾኪያ ሄዱ፤ አንጾኪያ በገላትያ አውራጃ የምትገኝ ከተማ ነች። ጉዞው ቀላል አልነበረም፤ ምክንያቱም የጵስድያዋ አንጾኪያ የምትገኘው ከባሕር ጠለል በላይ 1,100 ሜትር ከፍታ ላይ ነው። ተራሮችን አቋርጠው የሚያልፉት አሳቻ መንገዶች ሽፍቶች የበዙባቸው ነበሩ። ይህ ሁሉ እንዳይበቃ ደግሞ በዚህ ወቅት ጳውሎስ የጤና እክል ሳያጋጥመው አልቀረም። h

11, 12. ጳውሎስ በጵስድያዋ አንጾኪያ በሚገኝ ምኩራብ ውስጥ ንግግር ባቀረበበት ጊዜ የአድማጮቹን ፍላጎት መቀስቀስ የቻለው እንዴት ነው?

11 ጳውሎስና በርናባስ በጵስድያዋ አንጾኪያ በሰንበት ቀን ወደ ምኩራብ ገቡ። ዘገባው እንዲህ ይላል፦ “የሕጉና የነቢያት መጻሕፍት በሕዝቡ ፊት ከተነበበ በኋላ የምኩራቡ አለቆች ‘ወንድሞች ሆይ፣ ሕዝቡን የሚያበረታታ የምትናገሩት ቃል ካላችሁ ተናገሩ’ የሚል መልእክት ላኩባቸው።” (ሥራ 13:15) በዚህ ጊዜ ጳውሎስ ሊናገር ተነሳ።

12 ጳውሎስ ንግግሩን የጀመረው “የእስራኤል ሰዎችም ሆናችሁ አምላክን የምትፈሩ ሌሎች ሰዎች ሁሉ” ብሎ ነው። (ሥራ 13:16) ጳውሎስን ያዳምጡት የነበሩት ሰዎች አይሁዳውያንና ወደ ይሁዲነት የተለወጡ አሕዛብ ነበሩ። አድማጮቹ ኢየሱስ በአምላክ ዓላማ ውስጥ የሚጫወተውን ሚና አያውቁም፤ ታዲያ ጳውሎስ ትኩረታቸውን ለመሳብ ምን አደረገ? በመጀመሪያ የአይሁድ ብሔርን ታሪክ በአጭሩ ተረከላቸው። ይሖዋ “በግብፅ ምድር ባዕዳን ሆነው ይኖሩ በነበረበት ጊዜ . . . ሕዝቡን ከፍ ከፍ [እንዳደረጋቸው]” ገለጸ፤ ነፃ ከወጡ በኋላ ደግሞ ‘ለ40 ዓመት ያህል በምድረ በዳ እንዴት እንደታገሣቸው’ አብራራላቸው። በተጨማሪም ጳውሎስ እስራኤላውያን ተስፋይቱን ምድር መውረስ የቻሉት እንዲሁም ይሖዋ “ምድራቸውን ርስት አድርጎ [የሰጣቸው]” እንዴት እንደሆነ ገለጸ። (ሥራ 13:17-19) አንዳንዶች እንደሚሉት ከሆነ፣ ጳውሎስ የጠቀሳቸው ነጥቦች የተወሰዱት አድማጮቹ በዚያ የሰንበት ዕለት ጥቂት ቀደም ብሎ ከሰሙት የቅዱሳን መጻሕፍት ንባብ ሳይሆን አይቀርም። እውነታው እንዲህ ከሆነ፣ ጳውሎስ “ለሁሉም ዓይነት ሰዎች ሁሉንም ነገር” ለመሆን የሚያደርገውን ጥረት የሚያሳይ ተጨማሪ ማስረጃ ነው።—1 ቆሮ. 9:22

13. የአድማጮቻችንን ልብ መማረክ የምንችለው እንዴት ነው?

13 እኛም ምሥራቹን ማራኪ በሆነ መንገድ ለማቅረብ መጣር ይኖርብናል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ሰው ሃይማኖቱ ምን እንደሆነ ማወቃችን ትኩረቱን የሚስቡ ርዕሰ ጉዳዮችን ለመምረጥ ያግዘናል። በተጨማሪም ግለሰቡ ከሚያውቃቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ላይ ልንጠቅስለት እንችላለን። ሰውየው ጥቅሱን ከራሱ መጽሐፍ ቅዱስ አውጥቶ እንዲያነብ ማድረግም ይበልጥ ውጤታማ የሚሆንበት ጊዜ አለ። እንግዲያው የአድማጮችህን ልብ መማረክ የምትችልባቸውን መንገዶች ፈልግ።

14. (ሀ) ጳውሎስ ስለ ኢየሱስ የሚገልጸውን ምሥራች ለአድማጮቹ ያስተዋወቀው እንዴት ነው? ምን ማስጠንቀቂያስ ሰጠ? (ለ) አድማጮቹ ለጳውሎስ ንግግር ምን ምላሽ ሰጡ?

14 ጳውሎስ በመቀጠል ‘አዳኝ የሆነው ኢየሱስ’ በእስራኤል የነገሥታት መስመር እንደመጣ አብራራ፤ መጥምቁ ዮሐንስ ለኢየሱስ መንገድ ጠራጊ እንደነበረም ተናገረ። ከዚያም ኢየሱስ እንዴት እንደተገደለና ከሞት እንደተነሳ ገለጸ። (ሥራ 13:20-37) አክሎም እንዲህ አለ፦ “በእሱ በኩል የሚገኘው የኃጢአት ይቅርታ አሁን እየታወጀላችሁ እንዳለ እወቁ፤ በኢየሱስ የሚያምን ማንኛውም ሰው፣ በእሱ አማካኝነት ‘ከበደል ነፃ ነህ’ ሊባል ይችላል።” ከዚያም ለአድማጮቹ እንዲህ የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጣቸው፦ “በነቢያት መጻሕፍት እንዲህ ተብሎ የተነገረው ነገር በእናንተ ላይ እንዳይደርስ ተጠንቀቁ፦ ‘እናንተ ፌዘኞች፣ ተመልከቱ፣ ተደነቁ፣ ጥፉም፤ ማንም በዝርዝር ቢነግራችሁ እንኳ ፈጽሞ የማታምኑትን ሥራ በእናንተ ዘመን እያከናወንኩ ነውና።’” አድማጮቹ ለጳውሎስ ንግግር የሰጡት ምላሽ አስደናቂ ነበር። ዘገባው እንደሚናገረው “ሰዎቹ ስለዚሁ ጉዳይ በሚቀጥለው ሰንበትም እንዲነግሯቸው ለመኗቸው።” በተጨማሪም በምኩራቡ የተደረገው ስብሰባ ከተበተነ በኋላ “ከአይሁዳውያንና ወደ ይሁዲነት ተለውጠው አምላክን ከሚያመልኩት መካከል ብዙዎች ጳውሎስንና በርናባስን ተከተሏቸው።”—ሥራ 13:38-43

“ለአሕዛብ እንሰብካለን” (የሐዋርያት ሥራ 13:44-52)

15. ጳውሎስ ንግግር ባቀረበ በቀጣዩ ሰንበት ምን ነገር ተከሰተ?

15 በቀጣዩ ሰንበት “የከተማዋ ሕዝብ ሁሉ ማለት ይቻላል” ጳውሎስን ለመስማት አንድ ላይ ተሰበሰበ። ይህ ሁኔታ ያላስደሰታቸው አንዳንድ አይሁዳውያን “ጳውሎስ የተናገረውን ቃል በመቃወም ይሳደቡ ጀመር።” በዚህ ጊዜ ጳውሎስና በርናባስ በድፍረት እንዲህ አሏቸው፦ “የአምላክ ቃል በመጀመሪያ ለእናንተ መነገሩ አስፈላጊ ነበር። እናንተ ግን ወደ ጎን ገሸሽ እያደረጋችሁትና የዘላለም ሕይወት እንደማይገባችሁ በራሳችሁ ላይ እየፈረዳችሁ ስለሆነ እኛም ለአሕዛብ እንሰብካለን። ይሖዋ ‘እስከ ምድር ዳር ድረስ መዳንን እንድታመጣ ለብሔራት ብርሃን አድርጌ ሾሜሃለሁ’ በማለት ትእዛዝ ሰጥቶናልና።”—ሥራ 13:44-47፤ ኢሳ. 49:6

“በጳውሎስና በበርናባስ ላይ ስደት አስነሱ፤ . . . ደቀ መዛሙርቱም በደስታና በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ።”—የሐዋርያት ሥራ 13:50-52

16. አይሁዳውያኑ የጳውሎስንና የበርናባስን ጠንከር ያለ ንግግር ሲሰሙ ምን ምላሽ ሰጡ? ጳውሎስና በርናባስስ ተቃውሞ ሲነሳባቸው ምን አደረጉ?

16 ንግግሩን ያዳመጡት ከአሕዛብ ወገን የሆኑ ሰዎች እጅግ ተደሰቱ፤ “ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው ሁሉ አማኞች ሆኑ።” (ሥራ 13:48) ብዙም ሳይቆይ የይሖዋ ቃል በመላ አገሪቱ እየተስፋፋ ሄደ። የአይሁዳውያኑ ምላሽ ግን ከዚህ ፈጽሞ የተለየ ነበር። ጳውሎስና በርናባስ እንዳሉት የአምላክ ቃል በመጀመሪያ የተነገረው ለአይሁዳውያኑ ቢሆንም መሲሑን አንቀበልም ብለዋል፤ በዚህም የተነሳ የአምላክ ፍርድ እንደማይቀርላቸው ጳውሎስና በርናባስ በግልጽ ነግረዋቸዋል። አይሁዳውያኑ፣ በከተማዋ የሚኖሩትን የተከበሩ ሴቶችና ታላላቅ ወንዶች በመቀስቀስ “በጳውሎስና በበርናባስ ላይ ስደት አስነሱ፤ ከክልላቸውም አስወጧቸው።” በዚህ ጊዜ ጳውሎስና በርናባስ ምን አደረጉ? “የእግራቸውን አቧራ አራግፈው ወደ ኢቆንዮን ሄዱ።” ታዲያ የክርስትና እምነት በጵስድያዋ አንጾኪያ አከተመለት ማለት ነው? በፍጹም! ዘገባው በዚያ ስለቀሩት ደቀ መዛሙርት ሲናገር “በደስታና በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ” ይላል።—ሥራ 13:50-52

17-19. ጳውሎስና በርናባስ የተዉትን ግሩም ምሳሌ መከተል የምንችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው? እንዲህ ማድረጋችንስ ለደስታችን አስተዋጽኦ የሚያደርገው እንዴት ነው?

17 እነዚህ ታማኝ ሰዎች ተቃውሞ በተነሳባቸው ጊዜ ካደረጉት ነገር ጠቃሚ ትምህርት እናገኛለን። በዓለም ላይ ትልቅ ቦታ ያላቸው ሰዎች መልእክቱን እንዳናውጅ ቢከለክሉን እንኳ መስበካችንን አናቆምም። ጳውሎስና በርናባስ፣ የአንጾኪያ ሰዎች መልእክቱን አንቀበልም ባሉ ጊዜ “የእግራቸውን አቧራ አራግፈው [እንደሄዱ]” ልብ በል፤ ይህ በሁኔታው እንደተቆጡ የሚያሳይ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ኃላፊነታቸውን እንደተወጡና በሕዝቡ ላይ ለሚደርሰው ነገር ተጠያቂ አለመሆናቸውን የሚጠቁም ምልክት ነው። እነዚህ ሚስዮናውያን፣ ሰዎች ምሥራቹን እንዲቀበሉ ማስገደድ እንደማይችሉ ተገንዝበው ነበር። ማድረግ የሚችሉት ነገር ቢኖር መስበካቸውን መቀጠል ነው። ደግሞም ያደረጉት ይህንኑ ነው፤ ወደ ኢቆንዮን ሄደው መስበካቸውን ቀጠሉ!

18 በአንጾኪያ የቀሩት ደቀ መዛሙርትስ ምን አደረጉ? የሚሰብኩበት ክልል ተቃዋሚዎች የበዙበት እንደሆነ አይካድም። ሆኖም ደስታቸው የተመካው ሰዎች በሚሰጡት በጎ ምላሽ ላይ አልነበረም። ኢየሱስ “የአምላክን ቃል ሰምተው የሚጠብቁት [ደስተኞች] ናቸው!” ብሏል። (ሉቃስ 11:28) በጵስድያዋ አንጾኪያ ያሉት ደቀ መዛሙርትም ይህንኑ ለማድረግ ቆርጠው ነበር።

19 ልክ እንደ ጳውሎስና እንደ በርናባስ ሁሉ እኛም ኃላፊነታችን ምሥራቹን መስበክ እንደሆነ ማስታወስ ይኖርብናል። መልእክቱን መቀበል ወይም አለመቀበል የምንሰብክላቸው ሰዎች ውሳኔ ነው። ሰዎች መልእክቱን ለመቀበል ፈቃደኛ በማይሆኑበት ጊዜ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩትን ደቀ መዛሙርት ምሳሌ እንከተል። እውነትን የምናደንቅና የመንፈስ ቅዱስን አመራር የምንቀበል ከሆነ ተቃውሞ ደስታችንን ሊያጠፋው አይችልም።—ገላ. 5:18, 22

a በርናባስ—‘የመጽናናት ልጅ’” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

b በዚህ ወቅት በሶርያዋ አንጾኪያ ሳይቀር ጉባኤዎች ተቋቁመው ነበር፤ ይህች ከተማ የምትገኘው ከኢየሩሳሌም በስተ ሰሜን 550 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቃ ነው።

c በመንገድ ላይ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

d በመጀመሪያው መቶ ዘመን፣ አንድ መርከብ የነፋሱ ሁኔታ ጥሩ ከሆነ በቀን 160 ኪሎ ሜትር ገደማ ይጓዝ ነበር። የአየሩ ሁኔታ አመቺ በማይሆንበት ጊዜ ደግሞ ጉዞው ረዘም ያለ ጊዜ ሊወስድ ይችላል።

e በአይሁዳውያን ምኩራቦች ውስጥ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

f ቆጵሮስ በሮም አገዛዝ ሥር ነበረች። ደሴቲቱን የሚያስተዳድረው አገረ ገዢው ሲሆን በሮም የተሾመ የአካባቢው ባለሥልጣን ነበር።

g ሳኦል ከዚህ ጊዜ አንስቶ ጳውሎስ ተብሎ መጠራት ጀመረ። አንዳንዶች ሳኦል በሮማዊ ስሙ መጠራት የጀመረው ለሰርግዮስ ጳውሎስ ክብር ሲል እንደሆነ ይናገራሉ። ይሁን እንጂ ቆጵሮስን ለቅቆ ከሄደ በኋላም በዚህ ስም መጠራቱን መቀጠሉ ከዚህ የተለየ ምክንያት እንዳለ የሚጠቁም ነው፤ አዎ፣ ጳውሎስ “ለአሕዛብ [የተላከ] ሐዋርያ” ስለሆነ በሮማዊ ስሙ ለመጠራት መርጧል። ምናልባት ሌላው ምክንያት ደግሞ ሳኦል ከሚለው የዕብራይስጥ ስሙ ጋር የተያያዘ ይሆናል፤ የዚህ ስም ግሪክኛ አጠራር መጥፎ መልእክት ከሚያስተላልፍ አንድ የግሪክኛ ቃል ጋር በጣም ይመሳሰላል።—ሮም 11:13

h ጳውሎስ ለገላትያ ሰዎች የላከውን ደብዳቤ የጻፈው ይህ ከሆነ ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ነበር። ጳውሎስ በደብዳቤው ላይ “ለመጀመሪያ ጊዜ ለእናንተ ምሥራቹን ለመስበክ አጋጣሚ ያገኘሁት በመታመሜ የተነሳ እንደነበር ታውቃላችሁ” በማለት ጽፏል።—ገላ. 4:13