ምዕራፍ 20
ተቃውሞ ቢኖርም “የይሖዋ ቃል . . . እየተስፋፋና እያሸነፈ ሄደ”
አጵሎስና ጳውሎስ ምሥራቹ እየተስፋፋ እንዲሄድ አስተዋጽኦ ያደረጉት እንዴት ነው?
በሐዋርያት ሥራ 18:23 እስከ 19:41 ላይ የተመሠረተ
1, 2. (ሀ) ጳውሎስና የጉዞ ጓደኞቹ በኤፌሶን ምን አደገኛ ሁኔታ ገጥሟቸው ነበር? (ለ) በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ምን እንመረምራለን?
በኤፌሶን አውራ ጎዳናዎች ላይ ጫጫታና ሁካታ በዝቷል፤ ሰዎች ወዲያ ወዲህ እየተራወጡ ነው። በቁጣ የተሞላ ሕዝብ ሆ ብሎ ተነስቷል፤ ከፍተኛ የሕዝብ ዓመፅ ሊቀሰቀስ እንደሆነ ያስታውቃል! ሰዎቹ ከሐዋርያው ጳውሎስ የጉዞ ጓደኞች መካከል ሁለቱን ይዘው እየጎተቱ ወሰዷቸው። ሱቆቹ የሚገኙበት ሰፊ ጎዳና ጭር ብሏል፤ በቁጣ የገነፈለው ሕዝብ ንቅል ብሎ በመውጣት ወደ ከተማዋ አምፊቲያትር ግር ብሎ ገባ፤ ግዙፉ አምፊቲያትር 25,000 ተመልካች የማስተናገድ አቅም አለው። አብዛኞቹ ሰዎች ለረብሻ ምክንያት የሆነውን ነገር እንኳ አያውቁም፤ ቤተ መቅደሳቸውንና ተወዳጅ አምላካቸውን አርጤምስን የሚያሰጋ ነገር እንደተፈጠረ ግን ጠርጥረዋል። ስለዚህ “የኤፌሶኗ አርጤምስ ታላቅ ናት!” እያሉ ያለማቋረጥ መጮኹ ጀመሩ።—ሥራ 19:34
2 ሰይጣን አሁንም የሕዝብ ዓመፅ በመቀስቀስ፣ የአምላክ መንግሥት ምሥራች እንዳይስፋፋ ለማገድ እየሞከረ ነው። እርግጥ ነው፣ ሰይጣን ዓላማውን ለማሳካት የሚሞክረው ዓመፅ በማስነሳት ብቻ አይደለም። በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ሰይጣን የተጠቀመባቸውን የተለያዩ ዘዴዎች እንመረምራለን፤ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩትን ክርስቲያኖች ሥራ ለማዳከምና አንድነታቸውን ለማናጋት ከፍተኛ ጥረት አድርጎ ነበር። ደስ የሚለው ግን፣ ቀጥለን እንደምንመለከተው የሰይጣን ዘዴዎች በሙሉ ከሽፈዋል፤ ምክንያቱም “የይሖዋ ቃል በኃይል እየተስፋፋና እያሸነፈ [ሄዷል]።” (ሥራ 19:20) እነዚያ ክርስቲያኖች ድል እንዲያደርጉ የረዳቸው ምንድን ነው? ዛሬም እኛን ለድል ያበቁን ምክንያቶች ናቸው። በእርግጥ ድሉ የእኛ ሳይሆን የይሖዋ ነው። ሆኖም በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበሩት ክርስቲያኖች ሁሉ እኛም የበኩላችንን ማድረግ ይኖርብናል። አገልግሎታችንን ለመፈጸም የሚረዱንን ባሕርያት በይሖዋ መንፈስ እርዳታ ማዳበር እንችላለን። እስቲ በቅድሚያ የአጵሎስን ምሳሌ እንመልከት።
“ቅዱሳን መጻሕፍትን ጠንቅቆ የሚያውቅ ሰው ነበር” (የሐዋርያት ሥራ 18:24-28)
3, 4. አቂላና ጵርስቅላ አጵሎስ ምን እንደጎደለው አስተዋሉ? ምንስ አደረጉ?
3 ጳውሎስ በሦስተኛው ሚስዮናዊ ጉዞው ወቅት ወደ ኤፌሶን ለመሄድ ተነስቷል፤ በዚሁ ጊዜ ላይ አጵሎስ የተባለ አይሁዳዊ ወደዚህች ከተማ መጣ። አጵሎስ ታዋቂ የሆነችው የግብጿ እስክንድርያ ተወላጅ ነው። ይህ ሰው በርካታ ግሩም ባሕርያት አሉት። ጥሩ የመናገር ችሎታ አለው። አንደበተ ርቱዕ ከመሆኑም ሌላ “ቅዱሳን መጻሕፍትን ጠንቅቆ የሚያውቅ ሰው ነበር።” በተጨማሪም “በመንፈስ እየተቃጠለ . . . ያስተምር ነበር።” በቅንዓት የተሞላው አጵሎስ በምኩራብ ለተሰበሰቡት አይሁዳውያን በድፍረት ይናገር ነበር።—ሥራ 18:24, 25
4 አጵሎስ በዚህ መንገድ ሲናገር አቂላና ጵርስቅላ ሰሙት። “ኢየሱስን ስለሚመለከቱ ጉዳዮች በትክክል [ሲያስተምር]” በመስማታቸው በጣም ተደስተው እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። አጵሎስ ስለ ኢየሱስ የተናገረው ነገር ምንም ስህተት የለውም። ብዙም ሳይቆይ ግን እነዚህ ክርስቲያን ባልና ሚስት አንድ ነገር አስተዋሉ፤ አጵሎስ ያልተረዳው አንድ በጣም አስፈላጊ ነገር አለ። “እሱ የሚያውቀው ዮሐንስ ይሰብከው ስለነበረው ጥምቀት ብቻ ነበር።” ድንኳን በመሥራት ሙያ የሚተዳደሩት እነዚህ ባልና ሚስት የአጵሎስን የመናገር ችሎታ ወይም የትምህርት ደረጃ በማየት ተሸማቅቀው ወደኋላ አላሉም። ከዚህ ይልቅ “ይዘውት በመሄድ የአምላክን መንገድ ይበልጥ በትክክል አብራሩለት።” (ሥራ 18:25, 26) ታዲያ አንደበተ ርቱዕና ምሁር የሆነው ይህ ሰው ምን ምላሽ ሰጠ? ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው፣ እንደ ክርስቲያን መጠን እጅግ አስፈላጊ ከሆኑት ባሕርያት አንዱን ይኸውም ትሕትናን አሳይቷል።
5, 6. አጵሎስን ይበልጥ ውጤታማ የይሖዋ አገልጋይ እንዲሆን ያስቻለው ምንድን ነው? እኛስ እሱ ከተወው ምሳሌ ምን እንማራለን?
5 አጵሎስ፣ አቂላና ጵርስቅላ ያደረጉለትን እርዳታ በመቀበሉ ይበልጥ ውጤታማ የሆነ የይሖዋ አገልጋይ መሆን ችሏል። ወደ አካይያ በመጓዝ በዚያ ያሉትን አማኞች “በእጅጉ ረዳቸው።” በተጨማሪም ‘አስቀድሞ የተነገረለት መሲሕ ኢየሱስ አይደለም’ ብለው ለሚከራከሩት በዚያ ክልል የነበሩ አይሁዳውያን ጥሩ ምሥክርነት ሰጥቷል። ሉቃስ እንዲህ ሲል ዘግቧል፦ “ከአይሁዳውያን ጋር በይፋ በመወያየት ከቅዱሳን መጻሕፍት ላይ እያሳያቸው ኢየሱስ እሱ ክርስቶስ እንደሆነ በመግለጽ ትክክል እንዳልሆኑ በጋለ ስሜት ያስረዳቸው ነበር።” (ሥራ 18:27, 28) አጵሎስ ለክርስቲያን ጉባኤ እንዴት ያለ በረከት ነበር! እሱ ያከናወነው አገልግሎት “የይሖዋ ቃል” እያሸነፈ እንዲሄድ አስተዋጽኦ አበርክቷል። አጵሎስ ከተወው ምሳሌ ምን እንማራለን?
6 ትሕትና ሁሉም ክርስቲያኖች ሊያዳብሩት የሚገባ ባሕርይ ነው። እያንዳንዳችን በተፈጥሮ ወይም በትምህርት ያገኘናቸው አሊያም በተሞክሮ ያዳበርናቸው የተለያዩ ስጦታዎች አሉን። ሆኖም ካሉን ስጦታዎች ይልቅ ጎልቶ መታየት ያለበት ትሕትናችን ነው። አለዚያ ጥሩ ጎናችን ደካማ ጎን ሊሆንብን ይችላል። አደገኛ የሆነው የትዕቢት ባሕርይ በውስጣችን እንዲያቆጠቁጥ ምቹ ሁኔታ ልንፈጥርለት እንችላለን። (1 ቆሮ. 4:7፤ ያዕ. 4:6) ከልባችን ትሑቶች ከሆንን ሌሎች ከእኛ እንደሚበልጡ ለማሰብ እንጥራለን። (ፊልጵ. 2:3) ሌሎች እርማት ሲሰጡንም ሆነ ሲያስተምሩን በደስታ እንቀበላለን። አመለካከታችን መንፈስ ቅዱስ በወቅቱ ከሚሰጠው አመራር ጋር እንደማይጣጣም ከተገነዘብን ለውጥ ለማድረግ እንጥራለን፤ በያዝነው አቋም ድርቅ በማለት የኩራት ዝንባሌ አናሳይም። ይሖዋም ሆነ ልጁ የሚጠቀሙብን ምንጊዜም ትሑቶች ከሆንን ነው።—ሉቃስ 1:51, 52
7. ጳውሎስና አጵሎስ ምን የትሕትና ምሳሌ ትተዋል?
7 ትሕትና ለፉክክር መንፈስም ፍቱን መድኃኒት ነው። ሰይጣን በጥንቶቹ ክርስቲያኖች መካከል ክፍፍል ለመፍጠር ምን ያህል ቋምጦ እንደነበር አስበው። አጵሎስም ሆነ ሐዋርያው ጳውሎስ የተጨበጨበላቸው አስተማሪዎች ናቸው፤ ቅናት በልባቸው አድሮ በጉባኤ ውስጥ የበላይ ለመሆን መፎካከር ቢጀምሩ ሰይጣን የልቡ ደረሰ ማለት ነው! ደግሞም እንዲፎካከሩ ሊያደርጋቸው የሚችል ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር። በቆሮንቶስ ያሉ አንዳንድ ክርስቲያኖች “እኔ የጳውሎስ ነኝ” ሲሉ ሌሎቹ ደግሞ “እኔ ግን የአጵሎስ ነኝ” ይሉ ነበር። ጳውሎስና አጵሎስ እንዲህ ያለውን የሚከፋፍል አመለካከት ለማስተናገድ ፈቃደኞች ነበሩ? በፍጹም! አጵሎስ ለሥራው ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳበረከተ ጳውሎስ በትሕትና አምኖ ተቀብሏል፤ እንዲያውም ተጨማሪ የአገልግሎት መብት ሰጥቶታል። አጵሎስም ቢሆን ጳውሎስ የሰጠውን መመሪያ ተግባራዊ አድርጓል። (1 ቆሮ. 1:10-12፤ 3:6, 9፤ ቲቶ 3:12, 13) በትሕትና ተባብሮ በመሥራት ረገድ ጥሩ ምሳሌ ይሆኑናል!
“ስለ አምላክ መንግሥት አሳማኝ በሆነ መንገድ . . . ማስረዳት” (የሐዋርያት ሥራ 18:23፤ 19:1-10)
8. ጳውሎስ ወደ ኤፌሶን የተመለሰው በየት አድርጎ ነው? ለምንስ?
8 ጳውሎስ ወደ ኤፌሶን ተመልሶ እንደሚመጣ ቃል ገብቶ ነበር፤ ቃሉንም ጠብቋል። a (ሥራ 18:20, 21) ይሁንና ወደ ኤፌሶን የተመለሰው እንዴት ነበር? ጉዞውን የጀመረው ከሶርያዋ አንጾኪያ ነው። ወደ ኤፌሶን ለመሄድ አጭሩ መንገድ በአቅራቢያው ወዳለችው ሴሌውቅያ መጓዝ፣ ከዚያም መርከብ ተሳፍሮ በቀጥታ መሄድ ነው። ጳውሎስ ግን “በመሃል አገር አቋርጦ” ተጓዘ። በሐዋርያት ሥራ 18:23 እና 19:1 ላይ የተገለጸው የጳውሎስ ጉዞ በግምት አንድ ሺህ ስድስት መቶ ኪሎ ሜትር ገደማ ይሆናል! ጳውሎስ እንዲህ ያለ አድካሚ ጉዞ ለማድረግ የመረጠው ለምንድን ነው? ‘ደቀ መዛሙርቱን ሁሉ ማበረታታት’ ስለፈለገ ነው። (ሥራ 18:23) ሦስተኛው ሚስዮናዊ ጉዞው እንደ ቀድሞዎቹ ሁለት ጉዞዎች ሁሉ አድካሚ መሆኑ አይቀርም፤ ለወንድሞቹ ሲል ግን ምንም ያህል ቢደክም አይቆጨውም። በዛሬው ጊዜም የወረዳ የበላይ ተመልካቾችና ሚስቶቻቸው ተመሳሳይ መንፈስ አላቸው። የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት በማድረግ የሚያሳዩትን ፍቅር እናደንቃለን!
9. አንዳንድ ደቀ መዛሙርት እንደገና መጠመቅ ያስፈለጋቸው ለምንድን ነው? ከእነሱስ ምን እንማራለን?
9 ጳውሎስ ኤፌሶን ሲደርስ የአጥማቂው ዮሐንስ ደቀ መዛሙርት የሆኑ አሥራ ሁለት ገደማ ሰዎች አገኘ። እነዚህ ሰዎች የዮሐንስን ጥምቀት ተጠምቀው ነበር፤ ሆኖም ይህ ጥምቀት በወቅቱ ተቀባይነት አልነበረውም። ከዚህም ሌላ ስለ መንፈስ ቅዱስ እምብዛም የሚያውቁት ነገር አልነበረም። ስለዚህ ጳውሎስ ግንዛቤያቸውን ወቅታዊ እንዲያደርጉ ረዳቸው፤ ልክ እንደ አጵሎስ እነሱም ትሑቶችና ለመማር ፈቃደኞች መሆናቸውን አሳይተዋል። በኢየሱስ ስም ከተጠመቁ በኋላ መንፈስ ቅዱስንና አንዳንድ ተአምራዊ ስጦታዎችን ተቀብለዋል። በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ወደፊት እየገሰገሰ ካለው የይሖዋ ቲኦክራሲያዊ ድርጅት ጋር እኩል መራመድ በረከት ያስገኛል።—ሥራ 19:1-7
10. ጳውሎስ ከምኩራቡ ወጥቶ ወደ አንድ የትምህርት ቤት አዳራሽ የሄደው ለምንድን ነው? እኛስ በአገልግሎታችን እሱን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው?
10 ብዙም ሳይቆይ ሌላ ነገር ደግሞ ተከናወነ። ጳውሎስ ምኩራብ ውስጥ ለሦስት ወር በድፍረት ሰበከ። “ስለ አምላክ መንግሥት አሳማኝ በሆነ መንገድ” ቢያስረዳም አንዳንዶች ልባቸውን በማደንደን ኃይለኛ ተቃዋሚዎች ሆኑ። ጳውሎስ ‘የጌታን መንገድ ከሚያጥላሉ’ ሰዎች ጋር ጊዜውን ማጥፋት አልፈለገም፤ በመሆኑም በአንድ የትምህርት ቤት አዳራሽ ንግግር ለመስጠት ዝግጅት አደረገ። (ሥራ 19:8, 9) መንፈሳዊ እድገት ማድረግ የሚፈልጉ ሁሉ ከምኩራቡ ወጥተው ወደ ትምህርት ቤቱ አዳራሽ መሄድ ነበረባቸው። ጳውሎስ እንዳደረገው ሁሉ እኛም የምናነጋግረው ሰው ለመስማት ፈቃደኛ እንዳልሆነ ወይም እንዲሁ መከራከር ብቻ እንደሚፈልግ ከተገነዘብን ትተነው መሄድ እንችላለን። የምንሰብከውን የሚያጽናና መልእክት መስማት የሚያስፈልጋቸው ብዙ በግ መሰል ሰዎች አሉ!
11, 12. (ሀ) ጳውሎስ በትጋት በመሥራትና እንደ ሁኔታው ማስተካከያ በማድረግ ረገድ ምን ምሳሌ ትቷል? (ለ) የይሖዋ ምሥክሮች በአገልግሎታቸው በትጋት ለመሥራትና እንደ ሁኔታው ማስተካከያ ለማድረግ የሚጥሩት እንዴት ነው?
11 ጳውሎስ በዚያ የትምህርት ቤት አዳራሽ ውስጥ በየዕለቱ ያስተምር ነበር፤ ምናልባትም ይህን የሚያደርገው ከቀኑ 5:00 እስከ 10:00 ሳይሆን አይቀርም። (ለሥራ 19:9 የተዘጋጀውን ለጥናት የሚረዳ መረጃ ተመልከት፣ nwtsty-E) ይህ ሰዓት ከተማው ጭር የሚልበትና ሙቀቱ የሚያይልበት ጊዜ ነው፤ ብዙዎች ሥራቸውን አቁመው ምግብ የሚበሉበትና የሚያርፉበት ሰዓት ነው። ጳውሎስ ሁለት ዓመት ሙሉ ይህን ፕሮግራም ተከትሎ ከነበረ በማስተማር ሥራው ከ3,000 ሰዓት በላይ አሳልፏል ማለት ነው። b የይሖዋ ቃል እየተስፋፋና እያሸነፈ የሄደበት ሌላው ምክንያት ይህ ነው። ጳውሎስ ትጉና እንደ ሁኔታው ማስተካከያ የሚያደርግ ሰው ነበር። ብዙ ሰዎችን ለማግኘት ሲል ፕሮግራሙን እንደ ሁኔታው አስተካክሏል። ይህ ምን ውጤት አስገኝቷል? “በእስያ አውራጃ የሚኖሩ አይሁዳውያንና ግሪካውያን ሁሉ የጌታን ቃል ሰሙ።” (ሥራ 19:10) በእርግጥም ጳውሎስ በሚገባ መሥክሯል!
12 በዘመናችን ያሉ የይሖዋ ምሥክሮችም በትጋት ይሠራሉ እንዲሁም ሰዎችን ለመርዳት ሲሉ እንደ ሁኔታው ማስተካከያ ያደርጋሉ። ሰዎች ሊገኙ በሚችሉበት ቦታና ጊዜ ሁሉ ምሥራቹን ለመስበክ እንጥራለን። በመንገድ ላይ፣ በገበያ ቦታዎችና በመኪና ማቆሚያ ስፍራዎች እንሰብካለን። በስልክም ሆነ በደብዳቤ ለሰዎች እንመሠክራለን። ከቤት ወደ ቤት በምናገለግልበት ጊዜም ሰዎችን ቤታቸው ልናገኛቸው በምንችልበት ሰዓት ላይ ለመሄድ ጥረት እናደርጋለን።
የርኩሳን መናፍስት ተጽዕኖ ቢኖርም “የይሖዋ ቃል . . . እየተስፋፋና እያሸነፈ ሄደ” (የሐዋርያት ሥራ 19:11-22)
13, 14. (ሀ) ይሖዋ ጳውሎስን ምን እንዲፈጽም አስችሎታል? (ለ) የአስቄዋ ልጆች ምን ስህተት ሠሩ? በዛሬው ጊዜስ በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ያሉ ብዙዎች ተመሳሳይ ስህተት የሚሠሩት እንዴት ነው?
13 ቀጣዩ የሉቃስ ዘገባ፣ ጳውሎስ በይሖዋ ኃይል “በጣም አስደናቂ የሆኑ ነገሮችን” እንደፈጸመ ይገልጻል። ሰዎች የጳውሎስን ጨርቆችና ሽርጦች እንኳ ወደ ሕመምተኞች በመውሰድ እንዲፈወሱ ያደርጉ ነበር። ርኩሳን መናፍስትም በዚሁ መንገድ ይወጡ ነበር። c (ሥራ 19:11, 12) በሰይጣን ኃይሎች ላይ የተገኘው ይህ አስደናቂ ድል የብዙዎችን ትኩረት ሳበ፤ በዚህ የተደሰተው ግን ሁሉም ሰው አይደለም።
14 “እየዞሩ አጋንንትን ያስወጡ ከነበሩት አይሁዳውያን አንዳንዶቹ” ጳውሎስ የፈጸማቸውን ተአምራት ለማስመሰል ሞከሩ። ከእነዚህ አንዳንዶቹ የኢየሱስንና የጳውሎስን ስም በመጥራት አጋንንትን ለማስወጣት ተነሱ። የሉቃስ ዘገባ የካህናት ቤተሰብ የሆነው የአስቄዋ ሰባት ወንዶች ልጆችም ይህን ለማድረግ ሞክረው እንደነበር ይገልጻል። ጋኔኑ “ኢየሱስን አውቀዋለሁ፤ ጳውሎስንም አውቀዋለሁ፤ እናንተ ደግሞ ማን ናችሁ?” አላቸው። ከዚያም ክፉው መንፈስ ያደረበት ሰው እነዚህ አስመሳዮች ላይ እንደ አውሬ ዘሎ ጉብ አለባቸው፤ ስለዚህ ቆሳስለው ራቁታቸውን ሸሹ። (ሥራ 19:13-16) ጳውሎስ የተሰጠው ታላቅ ኃይል የእነዚያን የሐሰት ሃይማኖት ተከታዮች አቅመ ቢስነት አጋለጠ፤ በዚህም “የይሖዋ ቃል” አስደናቂ ድል አገኘ። በዛሬው ጊዜም የኢየሱስን ስም መጥራት ወይም “ክርስቲያን” ተብሎ መጠራት ብቻ በቂ እንደሆነ የሚያስቡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች አሉ። ሆኖም ኢየሱስ እንደተናገረው እውነተኛ የወደፊት ተስፋ ያላቸው የአባቱን ፈቃድ የሚያደርጉ ብቻ ናቸው።—ማቴ. 7:21-23
15. መናፍስታዊ ድርጊትንና ከዚህ ልማድ ጋር ንክኪ ያላቸውን ነገሮች በተመለከተ የኤፌሶን ነዋሪዎች ምን ምሳሌ ትተውልናል?
15 በአስቄዋ ልጆች ላይ የደረሰው ውርደት ብዙዎች አምላክን እንዲፈሩ አደረገ፤ በዚህም የተነሳ መናፍስታዊ ድርጊታቸውን እርግፍ አድርገው በመተው አማኞች ሆኑ። በኤፌሶን አስማታዊ ድርጊቶች ተስፋፍተው ነበር። መተት መሥራትና ክታብ ማሰር የተለመዱ ነገሮች ነበሩ፤ ድግምትም እንዲሁ፤ ብዙ የድግምት መጻሕፍትም ነበሩ። በአምላክ ያመኑ ብዙ የኤፌሶን ነዋሪዎች ለአስማታዊ ድርጊቶች የሚጠቀሙባቸውን መጻሕፍት አምጥተው በሕዝብ ፊት አቃጠሉ፤ እነዚህ መጻሕፍት አሁን ባለው የዋጋ ተመን መሠረት በአሥር ሺዎች የሚቆጠር ዶላር ሳያወጡ አይቀሩም። d ሉቃስ “በዚህ መንገድ የይሖዋ ቃል በኃይል እየተስፋፋና እያሸነፈ ሄደ” በማለት ዘግቧል። (ሥራ 19:17-20) አዎ፣ እውነት በሐሰት ትምህርትና በአጋንንታዊ ድርጊት ላይ ታላቅ ድል ተቀዳጀ! እነዚያ ታማኝ ሰዎች ለእኛ ጥሩ ምሳሌ ይሆኑናል። እኛም የምንኖረው በመናፍስታዊ ድርጊት በተሞላ ዓለም ውስጥ ነው። ከመናፍስታዊ ድርጊት ጋር ንክኪ ያለው ነገር ካለን የኤፌሶን ነዋሪዎች እንዳደረጉት ወዲያውኑ ማስወገድ ይኖርብናል! ምንም ያህል ከፍተኛ ዋጋ የሚያስከፍለን ቢሆን እንዲህ ካለው አስጸያፊ ድርጊት መራቅ አለብን።
“ታላቅ ሁከት ተፈጠረ” (የሐዋርያት ሥራ 19:23-41)
16, 17. (ሀ) ድሜጥሮስ በኤፌሶን ረብሻ እንዲቀሰቀስ ያደረገው እንዴት ነው? (ለ) የኤፌሶን ነዋሪዎች ጽንፈኛ መሆናቸውን ያሳዩት እንዴት ነው?
16 አሁን ደግሞ ሰይጣን የተጠቀመበትን ሌላ ዘዴ እንመልከት፤ ሉቃስ “የጌታን መንገድ በተመለከተ ታላቅ ሁከት ተፈጠረ” ብሏል። ሉቃስ ይህን ሲል እያጋነነ አልነበረም። e (ሥራ 19:23) ሁከቱን የቀሰቀሰው ድሜጥሮስ የተባለ የብር አንጥረኛ ነው። በመጀመሪያ፣ የሙያ ባልደረቦቹን ትኩረት ለመሳብ ብልጽግናቸው የተመካው የጣዖት ምስሎችን በመሸጥ ላይ እንደሆነ ጠቀሰላቸው። ቀጥሎም ክርስቲያኖች ጣዖታትን ስለማያመልኩ ጳውሎስ የሚሰብከው መልእክት የገቢ ምንጫቸውን እንደሚያደርቅባቸው ገለጸ። ከዚያም የአገር ፍቅር ስሜታቸውን ለመቀስቀስ ሞከረ፤ ድሜጥሮስ፣ የኤፌሶን ሰዎች በከተማቸውና በዜግነታቸው እንደሚኮሩ ያውቃል፤ በመሆኑም አምላካቸው አርጤምስም ሆነች በዓለም ሁሉ ከፍተኛ ዝናን ያተረፈው ቤተ መቅደሷ ‘ዋጋ ቢስ ሆነው እንደሚቀሩ’ በመግለጽ ክብራቸው እንደተነካ እንዲሰማቸው አደረገ።—ሥራ 19:24-27
17 ድሜጥሮስ የተናገረው ነገር የፈለገውን ውጤት አስገኝቶለታል። የብር አንጥረኞቹ “የኤፌሶኗ አርጤምስ ታላቅ ናት!” እያሉ ይጮኹ ጀመር፤ በዚህም ምክንያት ከተማዋ በረብሻ ተናወጠች፤ በዚህ ምዕራፍ መግቢያ ላይ ለተገለጸው የሕዝብ ዓመፅ ምክንያት የሆነው ይህ ነበር። f ለወንድሞቹ ሲል ራሱን አሳልፎ የሚሰጠው ጳውሎስ ወደ ጨዋታ ማሳያው ስፍራ ገብቶ ሕዝቡን ማነጋገር ፈለገ፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን አደጋ እንዳይደርስበት ስለፈሩ ወደዚያ እንዳይሄድ ከለከሉት። እስክንድር የሚባል ሰው ሕዝቡ ፊት ቆሞ ሊናገር ሞከረ። ይህ ሰው አይሁዳዊ ስለሆነ በአይሁዳውያንና በእነዚህ ክርስቲያኖች መካከል ያለውን ልዩነት ሊያብራራ ፈልጎ ሊሆን ይችላል። እንዲህ ዓይነቱ ማብራሪያ ግን ለእነዚህ ሰዎች ምንም ፋይዳ አልነበረውም። አይሁዳዊ መሆኑን ሲያውቁ ጩኸታቸውን ቀጠሉ፤ “የኤፌሶኗ አርጤምስ ታላቅ ናት!” እያሉ ለሁለት ሰዓት ያህል ጮኹ። ሃይማኖታዊ ጽንፈኝነት ዛሬም ተመሳሳይ ባሕርይ አለው። ሰዎች ጨርሶ እንዳያመዛዝኑ ያደርጋል።—ሥራ 19:28-34
18, 19. (ሀ) የከተማዋ ዋና ጸሐፊ በኤፌሶን የተቀሰቀሰውን የሕዝብ ረብሻ ጸጥ ያሰኘው እንዴት ነው? (ለ) አንዳንድ ባለሥልጣናት ለይሖዋ ሕዝቦች ከለላ የሆኑት እንዴት ነው? እኛስ በዚህ ረገድ ምን ሚና መጫወት እንችላለን?
18 በመጨረሻ የከተማዋ ዋና ጸሐፊ ሕዝቡን ጸጥ አሰኘ። ይህ ባለሥልጣን ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ ያለውና ምክንያታዊ ሰው ነው፤ ክርስቲያኖች፣ በቤተ መቅደሳቸውም ሆነ በአምላካቸው ላይ የሚያስከትሉት አደጋ እንደሌለ በመግለጽ ሕዝቡን አረጋጋ፤ ጳውሎስና ባልደረቦቹ በአርጤምስ ቤተ መቅደስ ላይ ምንም ወንጀል እንዳልፈጸሙም ገለጸ። የሚያቀርቡት ክስ ካላቸው ደግሞ ጉዳዩ የሚታይበት የራሱ የሆነ ሥርዓት እንዳለ ተናገረ። ከዚያ ግን ሕገወጥነትና ሥርዓት አልበኝነት በሚንጸባረቅበት ሁኔታ መሰባሰባቸው በሮም ሕግ ሊያስጠይቃቸው እንደሚችል አስታወሳቸው፤ ሰዎቹ አደብ እንዲገዙ ያደረጋቸው ይህ አባባሉ ሳይሆን አይቀርም። ይህን ከተናገረ በኋላ ሕዝቡ እንዲበተን አደረገ። በድንገት የገነፈለው የሕዝቡ ቁጣ በዋና ጸሐፊው ምክንያታዊና አሳማኝ ቃላት የተነሳ ወዲያውኑ በረደ።—ሥራ 19:35-41
19 ረጋ ያለና አስተዋይ ባለሥልጣን፣ የኢየሱስን ተከታዮች ከአደጋ ለመጠበቅ እርምጃ ሲወስድ ይህ የመጀመሪያም ሆነ የመጨረሻ አይደለም። እንዲያውም ሐዋርያው ዮሐንስ፣ በእነዚህ የመጨረሻ ቀኖች ይህ እንደሚሆን በራእይ ተመልክቶ ነበር፤ ምድሪቱ ሰይጣን በኢየሱስ ተከታዮች ላይ የለቀቀውን የስደት ጎርፍ ስትውጥ አይቷል፤ በምድሪቱ የተመሰሉት የተሻለ ምክንያታዊነት ያላቸው የዚህ ዓለም ክፍሎች ለአምላክ ሕዝቦች እንደሚደርሱላቸው ራእዩ ይጠቁማል። (ራእይ 12:15, 16) የሆነውም ይህ ነው። ፍትሐዊ አመለካከት ያላቸው ዳኞች፣ የይሖዋ ምሥክሮች ለአምልኮ የመሰብሰብና ምሥራቹን የመስበክ መብታቸው እንዲከበር ያደረጉባቸው አጋጣሚዎች ጥቂት አይደሉም። እርግጥ ነው፣ እኛ የምናሳየው ምግባርም ለእነዚህ ድሎች የበኩሉን ሚና ሊጫወት ይችላል። ጳውሎስ ያሳየው ምግባር በኤፌሶን የሚገኙ አንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናትን አክብሮት ሳያተርፍለት አልቀረም፤ በመሆኑም እነዚህ ሰዎች አደጋ እንዳይደርስበት ለማድረግ ጥረዋል። (ሥራ 19:31) እኛም ሐቀኛና ሰው አክባሪ መሆናችን በሌሎች ዘንድ ጥሩ ስም እንዲያተርፍልን እንመኛለን። ይህ ምግባራችን የኋላ ኋላ ምን በጎ ውጤት እንደሚያስገኝ አናውቅም።
20. (ሀ) በመጀመሪያው መቶ ዘመንም ሆነ በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ቃል በኃይል እያሸነፈ መሄዱን ስታስብ ምን ይሰማሃል? (ለ) በዘመናችን ይሖዋ እየተቀዳጀ ካለው ድል ጋር በተያያዘ ቁርጥ ውሳኔህ ምንድን ነው?
20 በመጀመሪያው መቶ ዘመን “የይሖዋ ቃል . . . እየተስፋፋና እያሸነፈ” የሄደው እንዴት እንደሆነ መለስ ብለን መቃኘታችን በእርግጥም የሚያስደስት ነው! በዘመናችን ይሖዋ ተመሳሳይ ድሎች እንዲገኙ ያደረገበትን መንገድ ስናስብም ተመሳሳይ ስሜት ይሰማናል። ለዚህ ድል ትንሽም እንኳ ቢሆን አስተዋጽኦ የማድረግ መብት ማግኘት ትፈልጋለህ? እንግዲያው ከላይ የተጠቀሱት ሰዎች የተዉትን ምሳሌ ተከተል። ምንጊዜም ትሑት ሁን፤ ወደፊት እየገሰገሰ ካለው የይሖዋ ድርጅት እኩል ተራመድ፤ በትጋት መሥራትህን ቀጥል፤ ከመናፍስታዊ ድርጊቶች ራቅ እንዲሁም ሐቀኛ በመሆንና የሚያስከብር ምግባር በማሳየት ጥሩ ምሥክርነት ለመስጠት የተቻለህን አድርግ።
a “ ኤፌሶን—የእስያ ዋና ከተማ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
b ጳውሎስ 1 ቆሮንቶስን የጻፈውም በኤፌሶን ሳለ ነበር።
c እዚህ ላይ የተጠቀሱት ጨርቆች ጳውሎስ ላቡ ዓይኑ ውስጥ እንዳይገባ ግንባሩ ላይ የሚያስራቸው መሐረቦች ሊሆኑ ይችላሉ። በተጨማሪም ስለ ሽርጦቹ ከሚገልጸው ሐሳብ እንደምንረዳው ጳውሎስ በወቅቱ ነፃ በሚሆንበት ሰዓት ምናልባትም ማለዳ ላይ ድንኳን ይሠራ የነበረ ይመስላል።—ሥራ 20:34, 35
d ሉቃስ እነዚህ መጻሕፍት 50,000 የብር ሳንቲሞች እንደሚያወጡ ጠቅሷል። እነዚህ የብር ሳንቲሞች ዲናር ከሆኑ ዋጋቸው በጣም ብዙ ነው፤ በዚያ ዘመን አንድ ሠራተኛ ይህን የሚያህል ገንዘብ ለማግኘት በሳምንት ሰባቱንም ቀን ቢሠራ እንኳ 50,000 ቀናት ማለትም 137 ዓመታት ገደማ ይፈጅበታል።
e አንዳንዶች፣ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች ሲጽፍ “በሕይወት የመትረፍ ተስፋችን እንኳ ተሟጦ ነበር” ያለው ይህን ገጠመኝ አስቦ እንደሆነ ይናገራሉ። (2 ቆሮ. 1:8) ይሁን እንጂ ከዚህም የከፋ አደገኛ ሁኔታ ያጋጠመውን ጊዜ መጥቀሱ ሊሆን ይችላል። ጳውሎስ “በኤፌሶን ከአውሬዎች ጋር [እንደታገለ]” ሲጽፍ በመወዳደሪያ ቦታዎች ከጨካኝ አራዊት ጋር መታገሉን መግለጹ ሊሆን ይችላል፤ አሊያም ደግሞ ከሰዎች ኃይለኛ ተቃውሞ እንዳጋጠመው እየተናገረ ይሆናል። (1 ቆሮ. 15:32) ሐሳቡ ቃል በቃል አሊያም ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ሊወሰድ ይችላል።
f እንዲህ ያሉ የእጅ ሙያ ማኅበራት ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳደር ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ከመቶ ዓመት ገደማ በኋላ የዳቦ ጋጋሪዎች ማኅበር በኤፌሶን ተመሳሳይ ዓመፅ አስነስቶ ነበር።