በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 8

ጉባኤው “ሰላም አገኘ”

ጉባኤው “ሰላም አገኘ”

ቀንደኛ አሳዳጅ የነበረው ሳኦል ቀናተኛ ሰባኪ ሆነ

በሐዋርያት ሥራ 9:1-43 ላይ የተመሠረተ

1, 2. ሳኦል በደማስቆ ምን ለማድረግ አቅዷል?

 በቁጣ የተሞሉት መንገደኞች ወደ ደማስቆ እየተቃረቡ ነው፤ እዚያ ደርሰው የተላኩበትን ዓላማ እስኪያስፈጽሙ ቸኩለዋል። የክፋት ውጥናቸው ይህ ነው፦ በሕዝቡ ዘንድ የሚጠሉትን የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ከቤታቸው ጎትተው ማውጣት፣ ማሰር፣ ማዋረድ ከዚያም በኢየሩሳሌም ወደሚገኘው የሳንሄድሪን ሸንጎ ወስደው አይቀጡ ቅጣት ማስቀጣት።

2 የቡድኑ መሪ ሳኦል የተባለ ሰው ነው፤ ቀድሞውንም ቢሆን የንጹሕ ሰው ደም እጁ ላይ አለ። a ከጥቂት ጊዜ በፊት፣ በቅናት ያበዱት ባልንጀሮቹ ታማኙን የኢየሱስ ደቀ መዝሙር እስጢፋኖስን በድንጋይ ወግረው ሲገድሉ የድርጊታቸው ተባባሪ ነበር። (ሥራ 7:57 እስከ 8:1) በኋላ ላይ ሳኦል በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን የኢየሱስ ተከታዮች ማሳደድ ጀመረ፤ ሆኖም ይህ ስላላረካው የስደቱን እሳት በሌሎች ቦታዎችም ለማቀጣጠል ቆርጦ ተነሳ፤ የዚህ ዘመቻ ቀንደኛ መሪም ሆነ። ዓላማው፣ ‘የጌታ መንገድ’ ተብሎ የሚጠራውን እንደ መቅሰፍት የሚታይ ኑፋቄ ጠራርጎ ማጥፋት ነው።—ሥራ 9:1, 2፤ “ ሳኦል በደማስቆ የተሰጠው ሥልጣን” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

3, 4. (ሀ) ሳኦል ምን አጋጠመው? (ለ) የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

3 ሳኦል በጉዞ ላይ ሳለ ድንገት በዙሪያው ደማቅ ብርሃን አንጸባረቀ። አብረውት የሚጓዙት ሰዎች ብርሃኑን ሲመለከቱ በድንጋጤ ክው ብለው ቀሩ። ሳኦል ዓይኑ ታውሮ መሬት ላይ ወደቀ። ማየት ቢሳነውም “ሳኦል፣ ሳኦል ለምን ታሳድደኛለህ?” የሚል ድምፅ ከሰማይ ሰማ። በድንጋጤ ተውጦ “ጌታዬ፣ አንተ ማን ነህ?” አለ። በዚህ ጊዜ ሳኦል ጨርሶ ያልጠበቀው መልስ ተሰጠው፦ “እኔ አንተ የምታሳድደኝ ኢየሱስ ነኝ።”—ሥራ 9:3-5፤ 22:9

4 ኢየሱስ መጀመሪያ ላይ ለሳኦል ከተናገረው ሐሳብ ምን እንማራለን? ሳኦል ክርስትናን ከመቀበሉ ጋር በተያያዘ የተከናወኑትን ነገሮች መመርመራችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል? በተጨማሪም ሳኦል ክርስትናን ከተቀበለ በኋላ ጉባኤው ሰላም እንዳገኘ ዘገባው ይገልጻል፤ ታዲያ ጉባኤው በዚህ ሰላም ከተጠቀመበት መንገድ ምን ትምህርት እናገኛለን?

“ለምን ታሳድደኛለህ?” (የሐዋርያት ሥራ 9:1-5)

5, 6. ኢየሱስ ለሳኦል ከተናገረው ሐሳብ ምን እንማራለን?

5 ኢየሱስ ወደ ደማስቆ በሚወስደው መንገድ ላይ ሳኦልን ሲያስቆመው “ደቀ መዛሙርቴን ለምን ታሳድዳለህ?” አላለውም። ከዚህ ይልቅ ከላይ እንደተመለከትነው “ለምን ታሳድደኛለህ?” ብሎታል። (ሥራ 9:4) አዎ፣ ኢየሱስ በተከታዮቹ ላይ የሚደርሰው መከራ በራሱ ላይ የደረሰ ያህል ይሰማዋል።—ማቴ. 25:34-40, 45

6 በክርስቶስ በማመንህ የተነሳ መከራ እየደረሰብህ ነው? ከሆነ ይሖዋና ኢየሱስ ያለህበትን ሁኔታ በሚገባ እንደሚያውቁ እርግጠኛ ሁን። (ማቴ. 10:22, 28-31) የሚደርስብህ መከራ ለጊዜው ላይወገድልህ ይችላል። እንደምታስታውሰው፣ ሳኦል በእስጢፋኖስ መገደል ሲተባበር እንዲሁም በኢየሩሳሌም የነበሩትን ታማኝ ደቀ መዛሙርት ከቤታቸው እየጎተተ ሲያወጣ ኢየሱስ ሁኔታውን ይመለከት ነበር። (ሥራ 8:3) ይሁን እንጂ በወቅቱ ጣልቃ ገብቶ እርምጃ አልወሰደም። ያም ሆኖ ይሖዋ ለእስጢፋኖስም ሆነ ለሌሎቹ ደቀ መዛሙርት ያደረገላቸው አንድ ነገር አለ፤ በታማኝነት ለመጽናት የሚያስችላቸውን ብርታት በክርስቶስ አማካኝነት ሰጥቷቸዋል።

7. የሚደርስብህን ስደት በጽናት ለመቋቋም ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

7 አንተም የሚከተሉትን ነገሮች ካደረግክ የሚደርስብህን ስደት በጽናት መቋቋም ትችላለህ፦ (1) ምንም ይምጣ ምን በታማኝነት ለመጽናት ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። (2) ይሖዋ እንዲረዳህ ጠይቅ። (ፊልጵ. 4:6, 7) (3) በቀልን ለይሖዋ ተው። (ሮም 12:17-21) (4) ይሖዋ የሚደርስብህን መከራ እስኪያስወግድልህ ድረስ ለመጽናት የሚያስችል ኃይል እንደሚሰጥህ እምነት ይኑርህ።—ፊልጵ. 4:12, 13

‘ወንድሜ ሳኦል፣ ጌታ ልኮኛል’ (የሐዋርያት ሥራ 9:6-17)

8, 9. ሐናንያ ስለተሰጠው ተልእኮ ምን ተሰምቶት ሊሆን ይችላል?

8 ሳኦል፣ “ጌታዬ፣ አንተ ማን ነህ?” በማለት ላቀረበው ጥያቄ ኢየሱስ መልስ ከሰጠ በኋላ “አሁን ተነስተህ ወደ ከተማዋ ግባ፤ ምን ማድረግ እንዳለብህም ይነገርሃል” አለው። (ሥራ 9:6) ማየት የተሳነውን ሳኦልን በደማስቆ ወደሚገኘው ማረፊያ ቤቱ እየመሩ ወሰዱት፤ በዚያም ለሦስት ቀን ሲጾምና ሲጸልይ ቆየ። ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢየሱስ ሐናንያ ለተባለ ደቀ መዝሙር ተገለጠለትና ስለ ሳኦል ነገረው። ሐናንያ የሚኖረው በዚያው ከተማ ነው፤ በደማስቆ በሚኖሩት “አይሁዳውያን ሁሉ የተመሠከረለት” ሰው ነበር።—ሥራ 22:12

9 ሐናንያ የተደበላለቀ ስሜት ተሰምቶት ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም! የጉባኤው ራስ የሆነው ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ክርስቶስ በግል እያነጋገረው ነው፤ ለአንድ ልዩ ተልእኮ እንደተመረጠ ነግሮታል። እንዴት ያለ ክብር ነው! የተሰጠው ተልእኮ ግን የዚያኑ ያህል ከባድ ነበር! ሐናንያ ሳኦልን እንዲያነጋግረው ሲታዘዝ እንዲህ አለ፦ “ጌታ ሆይ፣ ይህ ሰው በኢየሩሳሌም ባሉ ቅዱሳን አገልጋዮችህ ላይ ምን ያህል ጉዳት እንዳደረሰ ከብዙዎች ሰምቻለሁ። ወደዚህ ስፍራ የመጣው ስምህን የሚጠሩትን ሁሉ ለማሰር ከካህናት አለቆች ሥልጣን ተሰጥቶት ነው።”—ሥራ 9:13, 14

10. ኢየሱስ ሐናንያን ከያዘበት መንገድ ምን እንማራለን?

10 ሐናንያ ያሳሰበውን ነገር በመግለጹ ኢየሱስ አልገሠጸውም። ከዚህ ይልቅ ምን ማድረግ እንዳለበት በግልጽ ነግሮታል። በተጨማሪም ይህን ልዩ ተልእኮ እንዲፈጽም የፈለገበትን ምክንያት በመንገር አክብሮታል። ኢየሱስ ሳኦልን አስመልክቶ እንዲህ አለ፦ “ይህ ሰው በአሕዛብ እንዲሁም በነገሥታትና በእስራኤል ልጆች ፊት ስሜን እንዲሸከም ለእኔ የተመረጠ ዕቃ [ነው]። እኔም ስለ ስሜ ሲል ምን ያህል መከራ መቀበል እንዳለበት በግልጽ አሳየዋለሁ።” (ሥራ 9:15, 16) ሐናንያ ኢየሱስ ያለውን ለማድረግ ወዲያውኑ ተነሳ። አሳዳጅ የነበረውን ሳኦልን ፈልጎ ካገኘው በኋላ እንዲህ አለው፦ “ወንድሜ ሳኦል፣ ወደዚህ ስትመጣ መንገድ ላይ የተገለጠልህ ጌታ ኢየሱስ የዓይንህ ብርሃን እንዲመለስልህና በመንፈስ ቅዱስ እንድትሞላ እኔን ልኮኛል።”—ሥራ 9:17

11, 12. ስለ ኢየሱስ፣ ስለ ሐናንያ እና ስለ ሳኦል ከሚገልጸው ዘገባ ምን ቁም ነገሮች እናገኛለን?

11 ስለ ኢየሱስ፣ ስለ ሐናንያ እና ስለ ሳኦል የሚገልጸውን ይህን ዘገባ ስንመረምር በርካታ ቁም ነገሮች እናገኛለን። ለምሳሌ፣ ኢየሱስ የስብከቱን ሥራ በመምራት ረገድ ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት እንማራለን፤ ይህን እንደሚያደርግም አስቀድሞ ቃል ገብቷል። (ማቴ. 28:20) እርግጥ ነው፣ በዘመናችን ኢየሱስ ግለሰቦችን በቀጥታ አያነጋግርም፤ ሆኖም በቤተሰቦቹ ላይ በሾመው ታማኝ ባሪያ አማካኝነት የስብከቱን ሥራ እየመራ ነው። (ማቴ. 24:45-47) የበላይ አካሉ አመራር በመስጠት አስፋፊዎችንና አቅኚዎችን ይልካል፤ እነሱም ስለ ክርስቶስ ይበልጥ የማወቅ ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች ፍለጋ ይሄዳሉ። እንዲህ ያለ ፍላጎት ካላቸው ሰዎች መካከል ብዙዎቹ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር የተገናኙት አምላክ እንዲረዳቸው ከጸለዩ በኋላ ነው፤ ቀደም ባለው ምዕራፍ ላይ ይህን የሚያሳይ ማስረጃ ተመልክተናል።—ሥራ 9:11

12 ሐናንያ የተሰጠውን ተልእኮ በታዛዥነት በመቀበሉ ተባርኳል። የተጣለብህ ኃላፊነት አስጨናቂ በሚሆንበት ጊዜም እንኳ በሚገባ እንድትመሠክር የተሰጠህን ትእዛዝ ተግባራዊ ታደርጋለህ? ለምሳሌ አንዳንዶች፣ ከቤት ወደ ቤት ሄደው የማያውቁትን ሰው ማነጋገር ያስጨንቃቸዋል። ሌሎች ደግሞ በንግድ ቦታዎች፣ መንገድ ላይ፣ በስልክ ወይም በደብዳቤ መመሥከር በጣም ከባድ ሆኖ ይታያቸዋል። ሐናንያ የተሰማውን ፍርሃት አሸንፏል፤ በውጤቱም ሳኦል መንፈስ ቅዱስን እንዲቀበል የመርዳት ልዩ መብት አግኝቷል። b ሐናንያ በኢየሱስ በመታመኑና ሳኦልን እንደ ወንድሙ አድርጎ በመቁጠሩ ስኬታማ ሊሆን ችሏል። እኛም ልክ እንደ ሐናንያ ፍርሃታችንን ማሸነፍ ከፈለግን ኢየሱስ የስብከቱን ሥራ እየመራ እንዳለ እንተማመን፤ ለሰዎች አዘኔታ ይኑረን፤ እንዲሁም አስፈሪ የሚመስሉ ሰዎችም እንኳ ወደፊት ወንድሞቻችን ሊሆኑ እንደሚችሉ እናስብ።—ማቴ. 9:36

“ስለ ኢየሱስ . . . መስበክ ጀመረ” (የሐዋርያት ሥራ 9:18-30)

13, 14. ገና ያልተጠመቅክ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ከሆንክ ከሳኦል ምሳሌ ምን ትምህርት ማግኘት ትችላለህ?

13 ሳኦል የተማረውን ነገር ወዲያውኑ ተግባራዊ አድርጓል። ከተፈወሰ በኋላ ተጠመቀ፤ በደማስቆ ካሉት ደቀ መዛሙርት ጋርም ተቀራርቦ መሥራት ጀመረ። ይሁንና ይህ ብቻ አይደለም። ወዲያው “ስለ ኢየሱስ እሱ የአምላክ ልጅ እንደሆነ በምኩራቦቹ ውስጥ መስበክ ጀመረ።”—ሥራ 9:20

14 አንተስ ገና ያልተጠመቅክ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ነህ? ታዲያ እንደ ሳኦል ከተማርከው ነገር ጋር የሚስማማ ቆራጥ እርምጃ መውሰድ ትችል ይሆን? በእርግጥ ሳኦል፣ ክርስቶስ የፈጸመውን ተአምር በዓይኑ የማየት አጋጣሚ አግኝቷል፤ ይህም ለተግባር እንዳነሳሳው ጥርጥር የለውም። ሆኖም ኢየሱስ የፈጸማቸውን ተአምራት ያዩ ሌሎች ሰዎችም ነበሩ። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ የፈሪሳውያን ቡድን ኢየሱስ እጁ የሰለለበትን ሰው ሲፈውስ ተመልክቷል፤ ብዙ አይሁዳውያን ደግሞ ኢየሱስ አልዓዛርን ከሞት እንዳስነሳው ያውቃሉ። ይሁንና ብዙዎቹ ግድ የለሾች አልፎ ተርፎም ተቃዋሚዎች ነበሩ። (ማር. 3:1-6፤ ዮሐ. 12:9, 10) ከዚህ በተቃራኒ ሳኦል በሕይወቱ ላይ ለውጥ አድርጓል። የኢየሱስን ተአምራት ከተመለከቱት ከእነዚያ ሰዎች በተቃራኒ ሳኦል ጥሩ ምላሽ የሰጠው ለምንድን ነው? ከሰው ይልቅ አምላክን ይፈራ ስለነበር ነው፤ ደግሞም ክርስቶስ ላሳየው ምሕረት ከፍተኛ አድናቆት ነበረው። (ፊልጵ. 3:8) አንተም እንዲህ ዓይነት አመለካከት ካለህ አገልግሎት ለመጀመር ምንም ነገር እንዲያግድህ አትፈቅድም፤ ለመጠመቅ ብቁ የሚያደርጉህን እርምጃዎች ከመውሰድም ወደኋላ አትልም።

15, 16. ሳኦል በምኩራቦቹ ውስጥ ምን ያደርግ ነበር? በደማስቆ የሚኖሩት አይሁዳውያንስ ምን ምላሽ ሰጡ?

15 አሁን ሳኦል በየምኩራቦቹ ስለ ኢየሱስ መስበክ ጀምሯል፤ እዚያ የተሰበሰቡት ሰዎች ይህን ሲያዩ ምን ሊሰማቸው እንደሚችል አስበው፤ አንዳንዶቹ ሲደነቁና ሲገረሙ፣ ሌሎቹ ደግሞ በንዴት ሲበግኑ ይታይህ! “ይህ ሰው በኢየሩሳሌም ይህን ስም የሚጠሩትን ሲያጠፋ የነበረው አይደለም?” ይሉ ነበር። (ሥራ 9:21) ሳኦል ስለ ኢየሱስ የነበረው አመለካከት እንዲለወጥ ያደረገው ምን እንደሆነ አብራርቷል፤ ኢየሱስ “እሱ ክርስቶስ እንደሆነ አሳማኝ ማስረጃ” አቀረበላቸው። (ሥራ 9:22) ይሁንና አሳማኝ ማስረጃ ቀርቦላቸውም አመለካከታቸውን የማይቀይሩ ሰዎች ይኖራሉ። በወግ የተተበተበ አእምሮ ወይም በኩራት የተሞላ ልብ በአሳማኝ ማስረጃ አይሸነፍም። ያም ሆኖ ሳኦል ተስፋ አልቆረጠም።

16 በደማስቆ የሚገኙት አይሁዳውያን ከሦስት ዓመት በኋላም ሳኦልን መቃወማቸውን አላቆሙም። በመጨረሻም ሊገድሉት አሰቡ። (ሥራ 9:23፤ 2 ቆሮ. 11:32, 33፤ ገላ. 1:13-18) ሳኦልም የወጠኑትን ሴራ ሲያውቅ በስውር ከተማዋን ለቆ ለመሄድ አሰበ፤ በከተማዋ ግንብ ላይ ባለ መስኮት በኩል በቅርጫት አወረዱትና አመለጠ። በዚያ ምሽት ሳኦልን በቅርጫት ያወረዱት “የእሱ [የሳኦል] ደቀ መዛሙርት” እንደሆኑ ሉቃስ ዘግቧል። (ሥራ 9:25) ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው ሳኦል በደማስቆ ሲሰብክ ከሰሙት ሰዎች መካከል ቢያንስ የተወሰኑት አዎንታዊ ምላሽ በመስጠት የክርስቶስ ተከታዮች ሆነዋል።

17. (ሀ) ሰዎች ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ምን ምላሽ ይሰጣሉ? (ለ) ምን ማድረጋችንን መቀጠል አለብን? ለምንስ?

17 የተማርከውን ነገር ለቤተሰቦችህ፣ ለጓደኞችህና ለሌሎች መናገር በጀመርክበት ጊዜ ሰው ሁሉ አሳማኝ የሆነውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት እንደሚቀበል ጠብቀህ ሊሆን ይችላል። እርግጥ ነው፣ አንዳንዶች ተቀብለው ይሆናል፤ ብዙዎቹ ግን አይቀበሉም። እንዲያውም የገዛ ቤተሰቦችህ እንደ ጠላት አይተውህ ሊሆን ይችላል። (ማቴ. 10:32-38) ይሁንና ከቅዱሳን መጻሕፍት እየጠቀስክ የማስረዳት ችሎታህን ለማሻሻል ጥረት አድርግ፤ እንዲሁም ምንጊዜም ክርስቲያናዊ ባሕርያትን አንጸባርቅ፤ ይህን ሲያዩ የሚቃወሙህ ሰዎች እንኳ ውሎ አድሮ የአመለካከት ለውጥ ሊያደርጉ ይችላሉ።—ሥራ 17:2፤ 1 ጴጥ. 2:12፤ 3:1, 2, 7

18, 19. (ሀ) በርናባስ ለሳኦል ዋስ መሆኑ ምን ውጤት አስገኘ? (ለ) በርናባስና ሳኦል የተዉትን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?

18 ሳኦል ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ፈሩት፤ ደቀ መዝሙር መሆኑን ቢነግራቸውም ጥርጣሬ አደረባቸው፤ በእርግጥ ይህ መሆኑ ምንም አያስገርምም። ሆኖም በርናባስ ለሳኦል ዋስ በመሆን ደቀ መዝሙርነቱን ሲያረጋግጥላቸው ሐዋርያቱ ተቀበሉት፤ ለተወሰነ ጊዜም አብሯቸው ቆየ። (ሥራ 9:26-28) ሳኦል አገልግሎቱን የሚያከናውነው በጥንቃቄ ነበር፤ ይህ ሲባል ግን በምሥራቹ ያፍር ነበር ማለት አይደለም። (ሮም 1:16) በኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ላይ የስደት ዘመቻውን በጀመረበት በዚያው ከተማ በድፍረት እየሰበከ ነው። በኢየሩሳሌም ያሉት አይሁዳውያን፣ ‘ክርስቲያኖችን ልክ ያስገባልናል’ ብለው ያሰቡት ሰው ራሱ ክርስቲያን መሆኑን ሲመለከቱ ምን ያህል ደንግጠው ይሆን! በመሆኑም ይህን ሰው ሊገድሉት አሰቡ። “ወንድሞች ይህን ሲያውቁ [ሳኦልን] ወደ ቂሳርያ ይዘውት ወረዱ፤ ከዚያም ወደ ጠርሴስ ላኩት።” (ሥራ 9:30) ሳኦል፣ ኢየሱስ በጉባኤው አማካኝነት የሰጠውን መመሪያ ታዟል። ይህን በማድረጉም እሱም ሆነ ጉባኤው ተጠቅመዋል።

19 በርናባስ ሳኦልን ለመርዳት ቅድሚያውን እንደወሰደ ልብ በል። ይህ ደግነት በእነዚህ ቀናተኛ የይሖዋ አገልጋዮች መካከል የጠበቀ ወዳጅነት እንዲመሠረት ምክንያት እንደሆነ ጥርጥር የለውም። አንተስ እንደ በርናባስ በጉባኤህ ያሉ አዳዲስ ክርስቲያኖችን ለማገዝ ፈቃደኛ ነህ? አብረሃቸው በማገልገልና መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ በመርዳት ታግዛቸዋለህ? እንዲህ የምታደርግ ከሆነ ብዙ በረከት ታገኛለህ። አዲስ የምሥራቹ አስፋፊ ከሆንክ ደግሞ እንደ ሳኦል ሌሎች የሚሰጡህን እርዳታ ትቀበላለህ? ተሞክሮ ካካበቱ አስፋፊዎች ጋር የምታገለግል ከሆነ ለአገልግሎት የሚጠቅሙ ክህሎቶችን ታዳብራለህ፣ ደስታህ ይጨምራል እንዲሁም ከክርስቲያን ባልንጀሮችህ ጋር ዘላቂና የጠበቀ ወዳጅነት ትመሠርታለህ።

‘ብዙዎች አመኑ’ (የሐዋርያት ሥራ 9:31-43)

20, 21. ጥንትም ሆነ ዛሬ የአምላክ አገልጋዮች ‘ያገኙትን ሰላም’ የተጠቀሙበት እንዴት ነው?

20 ሳኦል ክርስትናን ከተቀበለ እንዲሁም ጉዳት ሳይደርስበት ከኢየሩሳሌም ካመለጠ በኋላ የነበረው ሁኔታ ምን ይመስላል? ዘገባው “በይሁዳ፣ በገሊላና በሰማርያ ያለው ጉባኤ ሁሉ ሰላም አገኘ” ይላል። (ሥራ 9:31) ታዲያ ደቀ መዛሙርቱ ይህን ‘አመቺ የሆነ ጊዜ’ እንዴት ተጠቀሙበት? (2 ጢሞ. 4:2) መጽሐፍ ቅዱስ ‘በእምነት እየጠነከሩ እንደሄዱ’ ይገልጻል። ሐዋርያትና ኃላፊነት ያላቸው ሌሎች ወንድሞች የደቀ መዛሙርቱን እምነት አጠናከሩ፤ ደግሞም በእነሱ አመራር ሥር ጉባኤው “ይሖዋን በመፍራትና መንፈስ ቅዱስ ከሚሰጠው ማጽናኛ ጋር በመስማማት ይኖር [ነበር]።” ለምሳሌ ጴጥሮስ በሳሮን ሜዳ ወደምትገኘው ወደ ልዳ ከተማ ሄዶ ነበር፤ ይህን የሰላም ወቅት በዚያ የሚኖሩትን ደቀ መዛሙርት እምነት ለማጠናከር ተጠቅሞበታል። ጴጥሮስ ያደረገው ጥረት በዚህ አካባቢ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች ‘በጌታ እንዲያምኑ’ አስተዋጽኦ አድርጓል። (ሥራ 9:32-35) ደቀ መዛሙርቱ በሌሎች ጉዳዮች ትኩረታቸው አልተከፋፈለም፤ ከዚህ ይልቅ አንዳቸው ሌላውን በማበረታታትና ምሥራቹን በመስበኩ ሥራ ተጠምደው ነበር። በውጤቱም ጉባኤው “በቁጥር እየበዛ ሄደ።”

21 በተመሳሳይም በብዙ አገሮች የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች በ20ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ አካባቢ ‘ሰላም አግኝተው’ ነበር። የአምላክን ሕዝቦች ለአሥርተ ዓመታት ሲጨቁኑ የነበሩ አገዛዞች በድንገት ተገረሰሱ፤ በተጨማሪም በአንዳንድ አካባቢዎች በስብከቱ ሥራ ላይ ተጥለው የነበሩ እገዳዎች በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ ተነሱ። በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች ይህን አጋጣሚ ምሥራቹን በይፋ ለማወጅ ተጠቅመውበታል፤ ይህም አስደናቂ ውጤት አስገኝቷል።

22. ያለህን ነፃነት በተሻለ ሁኔታ ልትጠቀምበት የምትችለው እንዴት ነው?

22 አንተስ አሁን ያለህን ነፃነት በአግባቡ እየተጠቀምክበት ነው? የምትኖረው የሃይማኖት ነፃነት ባለበት አገር ከሆነ ሰይጣን የአምላክን መንግሥት ከማስቀደም ይልቅ ቁሳዊ ነገሮችን እንድታሳድድ በማድረግ ሊያታልልህ መሞከሩ አይቀርም። (ማቴ. 13:22) ስለዚህ ትኩረትህ እንዲከፋፈል አትፍቀድ። አሁን ያለህን አንጻራዊ ሰላም በተቻለ መጠን በጥሩ ሁኔታ ተጠቀምበት። ይህን ወቅት በሚገባ ለመመሥከርና ጉባኤውን ለማነጽ የሚያስችል አጋጣሚ አድርገህ ተመልከተው። ያለህበት ሁኔታ ድንገት ሊለወጥ እንደሚችል አስታውስ።

23, 24. (ሀ) ስለ ጣቢታ ከሚናገረው ዘገባ ምን ቁም ነገሮችን እንማራለን? (ለ) ቁርጥ ውሳኔያችንስ ምን መሆን አለበት?

23 ጣቢታ ወይም ዶርቃ የተባለችውን ደቀ መዝሙር ሁኔታ ተመልከት። ጣቢታ የምትኖረው በልዳ አቅራቢያ ባለችው በኢዮጴ ከተማ ነው። ይህች ታማኝ እህት “መልካም በማድረግና ምጽዋት በመስጠት” ጊዜዋንና ጥሪቷን በጥበብ ተጠቅማበታለች። ይሁንና ጣቢታ ታመመችና ድንገት ሞተች። c በኢዮጴ የሚኖሩት ደቀ መዛሙርት፣ በተለይም ደግነቷን የቀመሱት መበለቶች በእሷ ሞት እጅግ አዘኑ። ጴጥሮስ አስከሬኗን ለቀብር እያዘጋጁ ወዳሉበት ቤት መጣ፤ ከኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት መካከል ማንም አድርጎ የማያውቀውን ተአምርም ፈጸመ። ከጸለየ በኋላ ጣቢታን ከሞት አስነሳት! ጴጥሮስ መበለቶቹንና ሌሎቹን ደቀ መዛሙርት ጠርቶ ሕያው መሆኗን አሳያቸው፤ በዚህ ጊዜ ምን ያህል ተደስተው ሊሆን እንደሚችል አስበው! እነዚህ ክንውኖች ወደፊት የሚጠብቋቸውን መከራዎች ለመቋቋም ብርታት ሰጥተዋቸው መሆን አለበት! ደግሞም እንደሚጠበቀው፣ ይህ ተአምር “በመላው ኢዮጴ ታወቀ፤ ብዙዎችም በጌታ አመኑ።”—ሥራ 9:36-42

የጣቢታን ምሳሌ መከተል የምትችለው እንዴት ነው?

24 ስለ ጣቢታ ከሚናገረው ከዚህ አስደሳች ዘገባ ሁለት ቁም ነገሮችን እንማራለን። (1) ሕይወት አላፊ ነው። በአምላክ ዘንድ መልካም ስም ማትረፍ የምንችልበትን አጋጣሚ ጥሩ አድርገን መጠቀማችን ምንኛ አስፈላጊ ነው! (መክ. 7:1) (2) የትንሣኤ ተስፋ የተረጋገጠ ነው። ይሖዋ ጣቢታ ያከናወነቻቸውን በርካታ የደግነት ተግባራት ተመልክቷል፤ ለዚህ ድርጊቷም ክሷታል። እኛም በትጋት የምናከናውነውን ሥራ ፈጽሞ አይረሳም፤ ከአርማጌዶን በፊት ብንሞት እንኳ ወደፊት ያስነሳናል። (ዕብ. 6:10) እንግዲያው “በአስቸጋሪ” ጊዜም ሆነ ‘በሰላሙ’ ጊዜ ስለ ክርስቶስ በሚገባ መመሥከራችንን እንቀጥል።—2 ጢሞ. 4:2

a ፈሪሳዊው ሳኦል” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

b በመሠረቱ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎችን ለሌሎች የመስጠት ሥልጣን የነበራቸው ሐዋርያት ናቸው። በዚህ ጊዜ ግን ኢየሱስ ይህን ሥልጣን ለሐናንያ የሰጠው ይመስላል፤ በመሆኑም በዚህ ለየት ያለ ሁኔታ ሳኦል የመንፈስ ቅዱስን ስጦታዎች የተቀበለው ከሐናንያ ነው። ሳኦል ክርስትናን ከተቀበለ በኋላ ረዘም ላለ ጊዜ ከ12ቱ ሐዋርያት ጋር አልተገናኘም። ይሁንና በእነዚህ ጊዜያት ሁሉ የስብከቱን ሥራ በትጋት ሲያከናውን እንደቆየ ግልጽ ነው። በመሆኑም ኢየሱስ፣ ሳኦል የስብከት ተልእኮውን በጽናት ለመወጣት የሚያስችለውን ኃይል እንዲያገኝ ፈልጎ እንደነበር መረዳት ይቻላል።

c ጣቢታ—‘መልካም በማድረግ የምትታወቅ’ ሴት” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።