በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 6

‘ጸጋና ኃይል የተሞላው እስጢፋኖስ’

‘ጸጋና ኃይል የተሞላው እስጢፋኖስ’

እስጢፋኖስ በሳንሄድሪን ሸንጎ ፊት በድፍረት ከሰጠው ምሥክርነት የምናገኘው ትምህርት

በሐዋርያት ሥራ 6:8 እስከ 8:3 ላይ የተመሠረተ

1-3. (ሀ) እስጢፋኖስ ምን አስፈሪ ሁኔታ ከፊቱ ተጋርጧል? እሱስ በዚህ ወቅት የነበረው ሁኔታ ምን ይመስል ነበር? (ለ) የትኞቹን ጥያቄዎች እንመለከታለን?

 እስጢፋኖስ ሸንጎው ፊት ቀርቧል። ሸንጎው የተሰየመበት አዳራሽ ራሱ ፍርሃት የሚያሳድር ነው፤ ቦታው ኢየሩሳሌም ባለው ቤተ መቅደስ አቅራቢያ ሳይሆን አይቀርም። አዳራሹ ውስጥ 71 ዳኞች ግማሽ ክብ ሠርተው ተቀምጠዋል፤ ይህ የሳንሄድሪን ሸንጎ ዛሬ የተሰየመው የእስጢፋኖስን ጉዳይ ለማየት ነው። ዳኞቹ ከፍተኛ ሥልጣንና ተደማጭነት ያላቸው ሰዎች ናቸው፤ አብዛኞቹም የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ለሆነው ለዚህ ሰው ንቀት ይታይባቸዋል። እንዲያውም ሸንጎውን የጠራው ሊቀ ካህናቱ ቀያፋ፣ ከጥቂት ወራት በፊት የሳንሄድሪን ሸንጎ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ሞት በፈረደበት ጊዜ የሸንጎው ሊቀ መንበር ነበር። ታዲያ እስጢፋኖስ በፍርሃት ርዶ ይሆን?

2 በዚህ ወቅት በእስጢፋኖስ ፊት ላይ አንድ አስደናቂ ነገር ይታይ ነበር። ዳኞቹ ትኩር ብለው ሲያዩት “ፊቱ እንደ መልአክ ፊት ሆኖ ታያቸው።” (ሥራ 6:15) መላእክት የይሖዋን መልእክት የሚያደርሱ መልእክተኞች ናቸው፤ ስለዚህ ድፍረትና የመረጋጋት ስሜት የሚታይባቸው መሆኑ አያስገርምም። በእስጢፋኖስ ላይ የሚታየው ሁኔታም ተመሳሳይ ነው፤ ሌላው ቀርቶ በጥላቻ የተሞሉት ዳኞች እንኳ ይህን ማስተዋል ችለዋል። እስጢፋኖስ እንዲህ ሊረጋጋ የቻለው ለምንድን ነው?

3 በዛሬው ጊዜ ያለን ክርስቲያኖች ከዚህ ጥያቄ መልስ ብዙ ትምህርት ማግኘት እንችላለን። በተጨማሪም እስጢፋኖስን ለዚህ አስጨናቂ ሁኔታ የዳረገው ምን እንደሆነ ማወቅ ያስፈልገናል። እስጢፋኖስ ከዚያ ቀደም ብሎም ለእምነቱ ጥብቅና ይቆም የነበረው እንዴት ነው? እኛስ የእሱን ምሳሌ መከተል የምንችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው?

‘ሕዝቡን ቀሰቀሱ’ (የሐዋርያት ሥራ 6:8-15)

4, 5. (ሀ) እስጢፋኖስ ለጉባኤው ትልቅ ሀብት ነበር የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) እስጢፋኖስ ‘ጸጋና ኃይል የተሞላ’ ሰው የነበረው በምን መንገድ ነው?

4 እስጢፋኖስ አዲስ ለተቋቋመው የክርስቲያን ጉባኤ ትልቅ ሀብት እንደነበር ከዚህ በፊት አይተናል። በዚህ መጽሐፍ ቀደም ባለው ምዕራፍ ላይ እንደተመለከትነው፣ ሐዋርያቱን እንዲያግዙ ተጠይቀው ፈቃደኛ ከሆኑት ሰባት ትሑት ወንድሞች አንዱ እስጢፋኖስ ነው። አምላክ ምን ዓይነት ስጦታዎች በመስጠት ባርኮት እንደነበር ስናውቅ የዚህ ሰው ትሕትና ይበልጥ ሊያስገርመን ይችላል። የሐዋርያት ሥራ 6:8 እንደሚናገረው አንዳንዶቹ ሐዋርያት እንዳደረጉት ሁሉ እሱም “ታላላቅ ድንቅ ነገሮችና ተአምራዊ ምልክቶች ይፈጽም ነበር።” በተጨማሪም ‘ጸጋና ኃይል የተሞላ’ እንደነበር ተገልጿል። ይህ ምን ማለት ነው?

5 ‘ጸጋ’ ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል “ሞገስ ያለው” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው እስጢፋኖስ፣ ደግና ለስላሳ ባሕርይ ያለው በመሆኑ ሰዎች በቀላሉ የሚቀርቡት ሰው ነበር። አነጋገሩ የአድማጮቹን ልብ የሚገዛ ነው፤ ምክንያቱም የሚያስተምረውን ነገር ከልቡ እንደሚያምንበት በሚያሳይ መንገድ ይናገር ነበር፤ በተጨማሪም የሚያስተምራቸው እውነቶች አድማጮቹን እንደሚጠቅሟቸው የማሳመን ችሎታ ነበረው። እስጢፋኖስ ኃይል የተሞላ ነበር፤ ይህ የሆነውም ለይሖዋ መንፈስ አመራር በትሕትና በመገዛት መንፈሱ በውስጡ እንዲሠራ ስለፈቀደ ነው። ባሉት ስጦታዎችና ችሎታዎች ከመኩራራት ይልቅ ክብሩ ሁሉ ለይሖዋ እንዲሰጥ አድርጓል፤ ለሚያስተምራቸው ሰዎችም ፍቅራዊ አሳቢነት እንዳለው አሳይቷል። በመሆኑም ተቃዋሚዎቹ እሱን በተመለከተ ስጋት ቢያድርባቸው ምንም አያስገርምም!

6-8. (ሀ) የእስጢፋኖስ ተቃዋሚዎች በእሱ ላይ ምን ሁለት ክሶችን መሠረቱ? ለምንስ? (ለ) እስጢፋኖስ የተወው ምሳሌ በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖችን የሚጠቅማቸው እንዴት ነው?

6 አንዳንድ ሰዎች ተነስተው ከእስጢፋኖስ ጋር ተከራክረው ነበር፤ ሆኖም “ይናገርበት የነበረውን ጥበብና መንፈስ መቋቋም አልቻሉም።” a በዚህ ስለተበሳጩ፣ ንጹሕ በሆነው በዚህ የክርስቶስ ተከታይ ላይ የሐሰት ክስ የሚሰነዝሩ ሰዎችን “በድብቅ አግባቡ።” በተጨማሪም ሽማግሌዎችንና ጸሐፍትን ጨምሮ ‘ሕዝቡን ቀሰቀሱ’፤ እስጢፋኖስንም አስገድደው ሳንሄድሪን ሸንጎ ፊት አቀረቡት። (ሥራ 6:9-12) ተቃዋሚዎቹ ‘አምላክንና ሙሴን ተሳድቧል’ የሚሉ ሁለት ክሶችን መሠረቱበት። ሆኖም የክሶቹ መነሻ ምንድን ነው?

7 እነዚያ የሐሰት ምሥክሮች፣ እስጢፋኖስ “ይህን ቅዱስ ስፍራ” ማለትም በኢየሩሳሌም የሚገኘውን ቤተ መቅደስ የሚቃወም ቃል ተናግሯል አሉ፤ ይህን ሲሉም አምላክን እንደተሳደበ መክሰሳቸው ነው። (ሥራ 6:13) በተጨማሪም ሙሴ ያስተላለፈውን ወግና ልማድ በመለወጥ ሕጉን የሚቃወም ነገር እንደተናገረና በዚህም ሙሴን እንደተሳደበ በመግለጽ ከሰሱት። እነዚህ ክሶች በቀላሉ የሚታዩ አልነበሩም፤ ምክንያቱም በወቅቱ የነበሩት አይሁዳውያን ለቤተ መቅደሱ፣ በሙሴ ሕግ ላይ ለሰፈሩት ዝርዝር ነገሮችና በሕጉ ላይ ለጨመሯቸው በቃል የሚተላለፉ በርካታ ወጎች ትልቅ ቦታ ይሰጡ ነበር። በሌላ አነጋገር እነዚህ ሰዎች እስጢፋኖስ፣ ሞት የሚገባው አደገኛ ሰው ነው ማለታቸው ነበር!

8 የሚያሳዝነው፣ ሃይማኖተኛ ነን የሚሉ ሰዎች በአምላክ አገልጋዮች ላይ ችግር ለመፍጠር እንዲህ ዓይነት ዘዴዎችን መጠቀማቸው እንግዳ ነገር አይደለም። በዛሬው ጊዜም ሃይማኖተኛ ነን የሚሉ ተቃዋሚዎች በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ስደት እንዲያደርሱ ባለሥልጣናትን ይቆሰቁሳሉ። ታዲያ የሐሰት ክስ ሲሰነዘርብን ምን ምላሽ መስጠት ይኖርብናል? ከእስጢፋኖስ ብዙ የምንማረው ነገር ይኖራል።

ስለ “ክብር አምላክ” በድፍረት መመሥከር (የሐዋርያት ሥራ 7:1-53)

9, 10. አንዳንድ ተቺዎች እስጢፋኖስ በሳንሄድሪን ፊት ያቀረበውን ንግግር አስመልክተው ምን ሐሳብ ይሰነዝራሉ? ምን ነገር ማስታወስ ይኖርብናል?

9 በመግቢያው ላይ እንደተገለጸው እስጢፋኖስ የተሰነዘረበትን ክስ ባዳመጠበት ወቅት ፊቱ እንደ መልአክ ፊት የመረጋጋት ስሜት ይታይበት ነበር። በዚህ ጊዜ ቀያፋ ወደ እሱ ዞር በማለት “ይህ የተባለው ነገር ልክ ነው?” አለው። (ሥራ 7:1) አሁን ተራው የእስጢፋኖስ ነው። እሱም መናገር ጀመረ።

10 አንዳንድ ተቺዎች እስጢፋኖስ ረጅም ንግግር ቢያቀርብም ለተሰነዘረበት ክስ መልስ አልሰጠም የሚል ተቃውሞ ይሰነዝራሉ። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን በምሥራቹ ላይ ለሚሰነዘረው ክስ ‘መልስ መስጠት’ የሚቻልበትን መንገድ በተመለከተ እስጢፋኖስ ግሩም ምሳሌ ይሆነናል። (1 ጴጥ. 3:15) እስጢፋኖስ ‘ቤተ መቅደሱን በማቃለል አምላክን ተሳድቧል’ እንዲሁም ‘ሕጉን የሚቃወም ነገር በመናገር ሙሴን ተሳድቧል’ የሚል ክስ እንደተሰነዘረበት አስታውስ። እስጢፋኖስ የሰጠው መልስ፣ የእስራኤላውያንን ታሪክ በሦስት ምዕራፍ ከፍሎ በአጭሩ ይዳስሳል፤ ይህን ሲያደርግ አንዳንድ ነጥቦችን በዘዴ ያጎላ ነበር። እስቲ እነዚህን ሦስት የታሪክ ምዕራፎች አንድ በአንድ እንመልከት።

11, 12. (ሀ) እስጢፋኖስ የአብርሃምን ታሪክ ውጤታማ በሆነ መንገድ የተጠቀመበት እንዴት ነው? (ለ) እስጢፋኖስ በንግግሩ ላይ ዮሴፍን የጠቀሰው ለምንድን ነው?

11 የጥንት አባቶች ዘመን። (ሥራ 7:1-16) እስጢፋኖስ ንግግሩን የጀመረው አይሁዳውያን በእምነቱ የሚያከብሩትን አብርሃምን በመጥቀስ ነው፤ ይህ ሁሉም በጋራ የሚስማሙበት አስፈላጊ ነጥብ ነው። ከዚያም እስጢፋኖስ “የክብር አምላክ” የሆነው ይሖዋ ለመጀመሪያ ጊዜ ለአብርሃም የተገለጠለት በሜሶጶጣሚያ ሳለ እንደነበር ጎላ አድርጎ ተናገረ። (ሥራ 7:2) እንዲያውም አብርሃም በተስፋይቱ ምድር የኖረው በመጻተኝነት ነበር። አብርሃም ቤተ መቅደስም ሆነ የሙሴ ሕግ አልነበረውም። ታዲያ ለአምላክ ታማኝ ሆኖ ለመገኘት እነዚህ ነገሮች የግድ ያስፈልጋሉ ብሎ ሊከራከር የሚችል ሰው ይኖራል?

12 እስጢፋኖስን ያዳምጡት የነበሩት ሰዎች የአብርሃም ዘር ለሆነው ለዮሴፍም ከፍተኛ አክብሮት ነበራቸው፤ ሆኖም የእስራኤል ነገዶች አባቶች የሆኑት የዮሴፍ ወንድሞች ይህን ጻድቅ ሰው እንዳሳደዱትና ለባርነት እንደሸጡት እስጢፋኖስ አስታወሳቸው። ያም ሆኖ ዮሴፍ እስራኤላውያንን ከረሃብ ለመታደግ የአምላክ መሣሪያ ሆኖ አገልግሏል። በመሆኑም በዮሴፍና በኢየሱስ ክርስቶስ መካከል ያለውን ተመሳሳይነት በግልጽ ማየት ይቻላል፤ እስጢፋኖስም ይህን እንደሚያስተውል ምንም ጥርጥር የለውም። ሆኖም አድማጮቹ ጆሮ እንዳይነፍጉት ሲል ይህን ጉዳይ ከማብራራት ተቆጥቧል።

13. እስጢፋኖስ ሙሴን አስመልክቶ የሰጠው ማብራሪያ ለተሰነዘረበት ክስ መልስ የሚሆነው እንዴት ነው? ይህስ የትኛው ቁልፍ ነጥብ ጎልቶ እንዲወጣ አድርጓል?

13 የሙሴ ዘመን። (ሥራ 7:17-43) እስጢፋኖስ ስለ ሙሴ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጠ። ከሳንሄድሪን ሸንጎ አባላት ብዙዎቹ ሰዱቃውያን ስለነበሩ እንዲህ ማድረጉ ብልህነት ነው፤ ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች ሙሴ ከጻፋቸው መጻሕፍት በስተቀር ሌሎቹን የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት አይቀበሉም ነበር። እስጢፋኖስ ሙሴን ተሳድቧል ተብሎ እንደተከሰሰም አስታውስ። የእስጢፋኖስ ንግግር ለሙሴና ለሕጉ ከፍተኛ አክብሮት እንዳለው የሚያሳይ ስለነበር ለተሰነዘረበት ክስ ቀጥተኛ መልስ ሰጥቷል። (ሥራ 7:38) እስጢፋኖስ ሙሴም ቢሆን ወገኖቹን ሊያድናቸው በሞከረበት ወቅት ተቀባይነት እንዳላገኘ ጠቀሰ። እነዚህ ሰዎች ሙሴን ያልተቀበሉት የ40 ዓመት ሰው ሳለ ነው። ይህ ከሆነ ከ40 ዓመታት በኋላም በተደጋጋሚ ዓምፀውበታል። b እስጢፋኖስ ቀስ በቀስ አንድ ቁልፍ ነጥብ ጎልቶ እንዲወጣ እያደረገ ነበር፤ የአምላክ ሕዝቦች ይሖዋ እነሱን እንዲመሩ የሾማቸውን ሰዎች በተደጋጋሚ ጊዜያት እንዳልተቀበሏቸው እየጠቆማቸው ነበር።

14. እስጢፋኖስ የሙሴን ታሪክ ተጠቅሞ የትኞቹን ነጥቦች አስጨበጠ?

14 እስጢፋኖስ፣ ሙሴ ከእስራኤላውያን መካከል እንደ እሱ ያለ ነቢይ እንደሚነሳ መናገሩን ለአድማጮቹ አስታወሳቸው። ይህ ነቢይ ማን ነው? ሰዎችስ እንዴት ይቀበሉታል? እስጢፋኖስ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ የሰጠው በንግግሩ መደምደሚያ ላይ ነው። እስጢፋኖስ አሁንም ሌላ ቁልፍ ነጥብ ጠቀሰ፤ ይሖዋ የትኛውንም ቦታ ቅዱስ ሊያደርግ እንደሚችል ጠቆመ። ምክንያቱም ሙሴ በሚነደው ቁጥቋጦ ዙሪያ ከይሖዋ ጋር በተነጋገረበት ወቅት መሬቱ ቅዱስ እንደሆነ ተነግሮት ነበር። ታዲያ ለይሖዋ የሚቀርበው አምልኮ በኢየሩሳሌም እንደሚገኘው ቤተ መቅደስ ባለ አንድ ሕንፃ ውስጥ ብቻ ሊገደብ ይችላል? እስቲ እንመልከት።

15, 16. (ሀ) እስጢፋኖስ የማደሪያ ድንኳኑን መጥቀሱ ላቀረበው የመከራከሪያ ሐሳብ ወሳኝ የነበረው ለምንድን ነው? (ለ) እስጢፋኖስ ባቀረበው ንግግር ላይ የሰለሞንን ቤተ መቅደስ የጠቀሰው የትኛውን ነጥብ ለማስጨበጥ ነው?

15 የማደሪያ ድንኳኑና ቤተ መቅደሱ። (ሥራ 7:44-50) እስጢፋኖስ በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ከመገንባቱ በፊት አምላክ ሙሴን የማደሪያ ድንኳን እንዲሠራ አዞት እንደነበር ገለጸ፤ ይህም አምልኮ ለማቅረብ የሚያገለግል ከቦታ ወደ ቦታ የሚንቀሳቀስ ድንኳን ነው። ታዲያ ይህ የማደሪያ ድንኳን ከቤተ መቅደሱ ያነሰ ነው ብሎ ለመከራከር የሚደፍር ይኖራል? ሙሴ ራሱ አምልኮውን ያከናውን የነበረው በማደሪያ ድንኳኑ አልነበረም እንዴ?

16 ከጊዜ በኋላ ሰለሞን በኢየሩሳሌም የሚገኘውን ቤተ መቅደስ ገነባ፤ በወቅቱ ባቀረበው ጸሎት ላይም በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ አንድ ትልቅ ቁም ነገር ተናግሯል። እስጢፋኖስ ይህን የሰለሞን አባባል በመዋስ “ልዑሉ አምላክ የሰው እጅ በሠራው ቤት አይኖርም” አለ። (ሥራ 7:48፤ 2 ዜና 6:18) እርግጥ ነው፣ ይሖዋ ዓላማውን ለማራመድ ቤተ መቅደስን ሊጠቀም ይችላል፤ ሆኖም ቤተ መቅደስ ባይኖርም ዓላማውን ማስፈጸም ይችላል። ታዲያ እሱን የሚያመልኩ ሰዎች፣ ንጹሑ አምልኮ የተመካው የሰው እጅ በሠራው ሕንፃ ላይ እንደሆነ ሊሰማቸው ይገባል? እስጢፋኖስ የሚከተለውን ሐሳብ ከኢሳይያስ መጽሐፍ ላይ በመጥቀስ ይህን የመከራከሪያ ነጥብ በጥሩ ሁኔታ ደምድሞታል፦ “ሰማይ ዙፋኔ ነው፤ ምድር ደግሞ የእግሬ ማሳረፊያ ናት። ለእኔ የምትሠሩልኝ ምን ዓይነት ቤት ነው? ይላል ይሖዋ። ወይስ የማርፍበት ቦታ ምን ዓይነት ነው? እነዚህን ነገሮች ሁሉ የሠራው እጄ አይደለም?”—ሥራ 7:49, 50፤ ኢሳ. 66:1, 2

17. የእስጢፋኖስ ንግግር (ሀ) የአድማጮቹን የተሳሳተ አመለካከት ያጋለጠው እንዴት ነው? (ለ) በእሱ ላይ ለተሰነዘሩት ክሶች ጥሩ ምላሽ የሚሆነውስ እንዴት ነው?

17 እስጢፋኖስ በሳንሄድሪን ሸንጎ ፊት ያቀረበውን ንግግር እስካሁን እንደቃኘነው የከሳሾቹን የተሳሳተ አመለካከት በዘዴ አጋልጧል ቢባል አትስማማም? እስጢፋኖስ በግልጽ እንዳስረዳው የይሖዋ ዓላማ በወጎችም ሆነ በሁኔታዎች የተገደበ ወይም ድርቅ ያለ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ተራማጅና እንደአስፈላጊነቱ አዳዲስ ሁኔታዎችን የሚያካትት ነው። በኢየሩሳሌም ለሚገኘው የሚያምር ሕንፃ እንዲሁም የሙሴን ሕግ መሠረት በማድረግ ለተፈጠሩት ወጎችና ልማዶች ከፍተኛ አክብሮት የነበራቸው ሰዎች የሕጉና የቤተ መቅደሱ ዓላማ ምን እንደሆነ ማስተዋል ተስኗቸዋል! የእስጢፋኖስ ንግግር በተዘዋዋሪ መንገድ የሚከተለው ወሳኝ ጥያቄ እንዲነሳ ያደርጋል፦ አንድ ሰው ሕጉንና ቤተ መቅደሱን እንደሚያከብር ማሳየት የሚችልበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ ይሖዋን መታዘዝ አይደለም? በእርግጥም የእስጢፋኖስ ንግግር የተሰነዘረበትን ክስ ውድቅ የሚያደርግ ግሩም የመከላከያ ሐሳብ ነበር፤ ይሖዋን ለመታዘዝ አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ አድርጓል።

18. እስጢፋኖስ የተወውን ምሳሌ መከተል የምንችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው?

18 እስጢፋኖስ ካቀረበው ንግግር ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን? ቅዱሳን መጻሕፍትን ጠንቅቆ ያውቅ ነበር። እኛም “የእውነትን ቃል በአግባቡ በመጠቀም” ረገድ የተዋጣልን መሆን ከፈለግን የአምላክን ቃል በትጋት ማጥናት አለብን። (2 ጢሞ. 2:15) አነጋገራችን ጸጋ የተሞላና ዘዴኛነት የሚንጸባረቅበት እንዲሆን በማድረግ ረገድም ከእስጢፋኖስ የምንማረው ነገር አለ። ያዳምጡት የነበሩት ሰዎች ለእሱ ከፍተኛ ጥላቻ ነበራቸው! ሆኖም ሰዎቹ ከፍ አድርገው የሚመለከቷቸውን ነገሮች በመጥቀስ ሁኔታው እስከፈቀደለት ድረስ በጋራ በሚያስማሟቸው ነጥቦች ላይ ትኩረት አድርጓል። በተጨማሪም “አባቶች” ብሎ በመጥራት ለእነሱ አክብሮት እንዳለው አሳይቷል። (ሥራ 7:2) እኛም በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን እውነት “በገርነት መንፈስና በጥልቅ አክብሮት” መናገር ይኖርብናል።—1 ጴጥ. 3:15

19. እስጢፋኖስ የይሖዋን የፍርድ መልእክት በሳንሄድሪን ሸንጎ ፊት በድፍረት የተናገረው እንዴት ነው?

19 ይህ ሲባል ግን ሰዎችን እንዳናስቀይም በመፍራት በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን እውነት ከመናገር ወደኋላ እንላለን ማለት አይደለም፤ የይሖዋን የፍርድ መልእክት ለማለዘብም አንሞክርም። በዚህ ረገድ እስጢፋኖስ ጥሩ ምሳሌ ይሆነናል። በሳንሄድሪን ሸንጎ ፊት ያቀረባቸው ማስረጃዎች፣ ልበ ደንዳና በሆኑት ዳኞች ላይ ምንም ለውጥ እንዳላመጡ ሳያስተውል አልቀረም። በመሆኑም ንግግሩን የደመደመው በመንፈስ ቅዱስ ተገፋፍቶ ሐቁን በድፍረት በመናገር ነው፤ አድማጮቹ ዮሴፍን፣ ሙሴንና ሌሎች ነቢያትን አንቀበልም ካሉት አባቶቻቸው ምንም እንደማይለዩ በግልጽ ነገራቸው። (ሥራ 7:51-53) እንዲያውም እነዚህ የሳንሄድሪን ዳኞች፣ ሙሴም ሆነ ሌሎቹ ነቢያት ይመጣል ብለው አስቀድመው የተናገሩለትን መሲሕ ገድለውታል። በእርግጥም ከእነሱ የከፋ የሙሴን ሕግ የተላለፈ የለም!

“ጌታ ኢየሱስ ሆይ፣ መንፈሴን ተቀበል” (የሐዋርያት ሥራ 7:54 እስከ 8:3)

“እነሱም ይህን ሲሰሙ ልባቸው በንዴት በገነ፤ ጥርሳቸውንም ያፋጩበት ጀመር።”—የሐዋርያት ሥራ 7:54

20, 21. የሳንሄድሪን ሸንጎ እስጢፋኖስ የተናገረውን ሲሰማ ምን አደረገ? ይሖዋስ እስጢፋኖስን ያበረታታው እንዴት ነው?

20 እስጢፋኖስ የተናገረው የማይታበል ሐቅ ዳኞቹ በቁጣ እንዲሞሉ አደረጋቸው። በመሆኑም ራሳቸውን መቆጣጠር ተስኗቸው በእስጢፋኖስ ላይ ጥርሳቸውን ያፋጩበት ጀመር። ይህ ታማኝ ሰው፣ ልክ እንደ ጌታው እንደ ኢየሱስ ሁሉ እሱም ምንም ምሕረት እንደማይደረግለት ሳይገነዘብ አይቀርም።

21 እስጢፋኖስ ከፊቱ የሚጠብቀውን ነገር ለመጋፈጥ ድፍረት ያስፈልገው ነበር፤ ይሖዋ በደግነት ተነሳስቶ ያሳየው ራእይ ብርታት እንደሰጠው ግልጽ ነው። እስጢፋኖስ የአምላክን ክብር እንዲሁም ኢየሱስን በይሖዋ ቀኝ ቆሞ ተመልክቷል! ስላየው ራእይ እየተናገረ ሳለ ዳኞቹ ጆሯቸውን በእጃቸው ደፈኑ። ለምን? ከዚህ በፊት ኢየሱስ ለዚሁ ሸንጎ፣ መሲሕ እንደሆነና ብዙም ሳይቆይ በአባቱ ቀኝ እንደሚቀመጥ ተናግሮ ነበር። (ማር. 14:62) እስጢፋኖስ ያየው ራእይ ኢየሱስ የተናገረው ነገር እውነት መሆኑን አረጋግጧል። አዎ፣ የሳንሄድሪን ሸንጎ አሳልፎ የሰጠውና ያስገደለው ራሱን መሲሑን ነው! በዚህ ጊዜ ሁሉም በአንድነት ተነስተው እስጢፋኖስን እያጣደፉ ይዘውት ሄዱ፤ በድንጋይ አስወግረውም ገደሉት። c

22, 23. የእስጢፋኖስ ሞት ከጌታው ከኢየሱስ ሞት ጋር የሚመሳሰለው በየትኞቹ መንገዶች ነው? በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖችስ ልክ እንደ እስጢፋኖስ ልበ ሙሉ እንዲሆኑ የሚያስችላቸው ምንድን ነው?

22 እስጢፋኖስ ሲሞት የነበረው ሁኔታ ከጌታው ጋር በጣም ይመሳሰላል፤ እሱም እንደ ኢየሱስ የተረጋጋ መንፈስ እንዲሁም በይሖዋ ላይ ሙሉ እምነት ነበረው፤ ለገዳዮቹም ምሕረትን ተመኝቷል። “ጌታ ኢየሱስ ሆይ፣ መንፈሴን ተቀበል” ብሏል፤ ምናልባትም ይህን የተናገረው አሁንም ኢየሱስን በይሖዋ ቀኝ ቆሞ እያየው ስለነበር ይሆናል። ኢየሱስ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ” በማለት የተናገራቸውን አጽናኝ የሆኑ ቃላት ያውቅ እንደነበር ጥርጥር የለውም። (ዮሐ. 11:25) በመጨረሻም እስጢፋኖስ ድምፁን ከፍ አድርጎ “ይሖዋ ሆይ፣ ይህን ኃጢአት አትቁጠርባቸው” በማለት ወደ አምላክ ጸለየ። ይህን ከተናገረ በኋላም በሞት አንቀላፋ።—ሥራ 7:59, 60

23 በመሆኑም እስጢፋኖስ ከክርስቶስ ተከታዮች መካከል ሰማዕት ሆኖ እንደሞተ የተጠቀሰ የመጀመሪያው ሰው ነው። (“ ‘ሰማዕት’ የተባለው ከምን አንጻር ነው?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) የሚያሳዝነው ግን እንዲህ ዓይነቱ አሟሟት በእሱ አላበቃም። ባለፉት ዘመናትም ሆነ በጊዜያችን አንዳንድ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች በሃይማኖታዊ አክራሪዎች፣ በፖለቲካ ጽንፈኞችና በሌሎች ጨካኝ ተቃዋሚዎች እጅ ተገድለዋል። ይሁንና እኛም እንደ እስጢፋኖስ ልበ ሙሉ የምንሆንበት በቂ ምክንያት አለን። በአሁኑ ጊዜ ኢየሱስ ንጉሥ ሆኗል፤ አባቱ የሰጠውን ታላቅ ሥልጣንም ይጠቀምበታል። ታማኝ ተከታዮቹን ከሞት እንዳያስነሳ ሊያግደው የሚችል ምንም ነገር የለም።—ዮሐ. 5:28, 29

24. ሳኦል በእስጢፋኖስ መገደል የተባበረው በምን መንገድ ነው? የዚህ ታማኝ ሰው ሞትስ ዘላቂ የሆኑ ምን በጎ ውጤቶች አስገኝቷል?

24 ይህ ሁሉ ሲከናወን ሳኦል የተባለ አንድ ወጣት ይመለከት ነበር። ሳኦል በእስጢፋኖስ መገደል ተስማምቶ ነበር፤ እንዲያውም እስጢፋኖስን የሚወግሩትን ሰዎች ልብስ ይጠብቅ ነበር። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ይህ ወጣት በክርስቲያኖች ላይ ጭካኔ የተሞላበት የስደት ዘመቻ አስጀመረ። ሆኖም የእስጢፋኖስ ሞት ዘላቂ የሆኑ በጎ ውጤቶችም ነበሩት። የእሱ ምሳሌ ሌሎች ክርስቲያኖች በታማኝነት እንዲጸኑና እነሱም የሚደርስባቸውን ስደት በድል እንዲወጡ አበረታቷቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ በኋላ ላይ ጳውሎስ ተብሎ በተጠራው በሳኦል ሕይወት ላይ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል፤ ጳውሎስ በእስጢፋኖስ መገደል ተባባሪ በመሆኑ የኋላ ኋላ እጅግ ተጸጽቷል። (ሥራ 22:20) ጳውሎስ፣ እስጢፋኖስ ሲገደል ድጋፍ ሰጥቷል፤ ቆየት ብሎ ግን “አምላክን የምሳደብ፣ አሳዳጅና እብሪተኛ [ነበርኩ]” ሲል ተናግሯል። (1 ጢሞ. 1:13) ጳውሎስ እስጢፋኖስንም ሆነ ያን ቀን ያቀረበውን ኃይለኛ ንግግር እንዳልረሳው ግልጽ ነው። እንዲያውም ከጳውሎስ ንግግሮችና መልእክቶች አንዳንዶቹ እስጢፋኖስ በንግግሩ ላይ ከጠቀሳቸው ነጥቦች ጋር የተያያዙ ናቸው። (ሥራ 7:48፤ 17:24፤ ዕብ. 9:24) ከጊዜ በኋላ ጳውሎስ፣ ‘ጸጋና ኃይል የተሞላው’ እስጢፋኖስ እምነትና ድፍረት በማሳየት ረገድ የተወውን ምሳሌ ሙሉ በሙሉ ተከትሏል። አሁን የሚነሳው ትልቁ ጥያቄ ‘እኛስ?’ የሚል ነው።

a ከተቃዋሚዎቹ መካከል አንዳንዶቹ “ነፃ የወጡ ሰዎች ምኩራብ” ተብሎ የሚጠራው ቡድን አባላት ነበሩ። እነዚህ ሰዎች በአንድ ወቅት በሮማውያን ተማርከው በኋላ ላይ ነፃ የወጡ ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ፤ ወይም ደግሞ ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ነፃ የወጡ ባሮች ይሆናሉ። እንደ ጠርሴሱ ሳኦል ሁሉ አንዳንዶቹ ከኪልቅያ የመጡ ነበሩ። ሳኦል፣ እስጢፋኖስን መቋቋም ካልቻሉት የኪልቅያ ሰዎች መካከል ይኑር አይኑር ዘገባው የሚገልጸው ነገር የለም።

b እስጢፋኖስ የሰጠው ንግግር፣ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሌላ የትም ቦታ የማናገኛቸውን መረጃዎች ይዟል፤ ለምሳሌ ያህል፣ ሙሴ የግብፃውያንን ትምህርት እንደቀሰመ፣ ከግብፅ ሸሽቶ በወጣበት ጊዜ ዕድሜው ስንት እንደነበርና በምድያም ምድር ምን ያህል ጊዜ እንደቆየ ገልጿል።

c በሮማውያን ሕግ መሠረት የሳንሄድሪን ሸንጎ የሞት ቅጣት የማስተላለፍ ሥልጣን ያለው አይመስልም። (ዮሐ. 18:31) ያም ሆነ ይህ እስጢፋኖስ የተገደለው ቁጣቸውን መቆጣጠር በተሳናቸው ሰዎች እንጂ ሸንጎው ደንቡን ጠብቆ ባስተላለፈው የፍርድ ውሳኔ አይደለም።