ምዕራፍ 7
“ስለ ኢየሱስ የሚገልጸውን ምሥራች” ማወጅ
ፊልጶስ በወንጌላዊነቱ ሥራ ግሩም ምሳሌ ትቷል
በሐዋርያት ሥራ 8:4-40 ላይ የተመሠረተ
1, 2. በመጀመሪያው መቶ ዘመን የስብከቱን ሥራ ለማስቆም የተደረገው ጥረት ምን ያልተጠበቀ ውጤት አስገኝቷል?
ታላቅ የስደት ማዕበል ተነሳ፤ ሳኦል በጉባኤው ላይ “ከፍተኛ ጥቃት ማድረስ” ጀመረ። “ከፍተኛ ጥቃት” የሚለው አገላለጽ መጀመሪያ በተጻፈበት ቋንቋ አሰቃቂ የጭካኔ ተግባርን ያመለክታል። (ሥራ 8:3) በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደተለያዩ አካባቢዎች ሸሹ፤ ሳኦል ክርስትናን ለማጥፋት የወጠነው ዕቅድ የሰመረለት ይመስል ነበር። ይሁንና ክርስቲያኖች ወደተለያዩ አካባቢዎች መበተናቸው ያልተጠበቀ ውጤት አስገኝቷል። ይህ ውጤት ምንድን ነው?
2 የተበተኑት ክርስቲያኖች ሸሽተው በሄዱበት ቦታ ሁሉ “የአምላክን ቃል ምሥራች [መስበክ]” ጀመሩ። (ሥራ 8:4) እስቲ አስበው! ስደት የምሥራቹን እድገት ይገታዋል ተብሎ ሲታሰብ ጭራሽ ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዲዳረስ ምክንያት ሆነ! አሳዳጆች ደቀ መዛሙርቱ ወደተለያዩ አካባቢዎች እንዲበተኑ ማድረጋቸው ያላሰቡትን ውጤት አስገኝቷል፤ የመንግሥቱ የስብከት ሥራ ያልደረሰባቸው ራቅ ብለው የሚገኙ አካባቢዎች ምሥራቹን ሰሙ። ወደፊት እንደምንመለከተው በዘመናችንም ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ሁኔታ ተከስቷል።
“የተበተኑት ደቀ መዛሙርት” (የሐዋርያት ሥራ 8:4-8)
3. (ሀ) ፊልጶስ ማን ነው? (ለ) የስብከቱ ሥራ በሰማርያ እምብዛም ያልተስፋፋው ለምን ነበር? ይሁንና ኢየሱስ በዚያ አካባቢ ምን እንደሚሆን አስቀድሞ ተናግሯል?
3 ‘ከተበተኑት ደቀ መዛሙርት’ አንዱ ፊልጶስ ነው። a (ሥራ 8:4፤ “ ‘ወንጌላዊው’ ፊልጶስ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) ፊልጶስ የሄደው ወደ ሰማርያ ነው፤ የሰማርያ ከተማ ከስብከቱ ሥራ አንጻር በአብዛኛው ያልተነካ ክልል ነበር። ምክንያቱም በአንድ ወቅት ኢየሱስ ለሐዋርያቱ “ወደ ማንኛውም የሳምራውያን [ከተማ] አትግቡ፤ ከዚህ ይልቅ ከእስራኤል ቤት ወደጠፉት በጎች ብቻ ሂዱ” የሚል መመሪያ ሰጥቷቸው ነበር። (ማቴ. 10:5, 6) ሆኖም ኢየሱስ ከጊዜ በኋላ በሰማርያ ምሥራቹ በሚገባ እንደሚሰበክ ያውቅ ነበር፤ ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት “በኢየሩሳሌም፣ በመላው ይሁዳና በሰማርያ እንዲሁም እስከ ምድር ዳር ድረስ ምሥክሮቼ ትሆናላችሁ” ያለው ለዚህ ነው።—ሥራ 1:8
4. ሳምራውያን ለፊልጶስ ስብከት ምን ምላሽ ሰጡ? እንዲህ ያለ ምላሽ እንዲሰጡ አስተዋጽኦ ያደረገውስ ምን ሊሆን ይችላል?
4 ፊልጶስ በሰማርያ “አዝመራው እንደነጣ” ተመልክቶ ነበር። (ዮሐ. 4:35) እሱ የሚሰብከው መልእክት ለነዋሪዎቹ መንፈስን እንደሚያድስ ንጹሕ አየር ሆኖላቸዋል፤ ይህ የሆነበትን ምክንያትም መረዳት አያስቸግርም። አይሁዳውያን ከሳምራውያን ጋር ምንም ግንኙነት እንዲኖራቸው አይፈልጉም፤ እንዲያውም ብዙ አይሁዳውያን ይንቋቸው ነበር። ከዚህ በተቃራኒ የምሥራቹ መልእክት እንዲህ ዓይነት የመደብ ልዩነት አያደርግም፤ ሳምራውያንም ይህን አስተውለዋል፤ ከፈሪሳውያን ጠባብ አስተሳሰብ ፈጽሞ የተለየ እንደሆነ ገብቷቸዋል። ፊልጶስም ለሳምራውያን በቅንዓትና ያለአድልዎ ምሥራቹን ሰብኳል፤ ሳምራውያንን ዝቅ አድርገው የሚመለከቷቸው ሰዎች ጭፍን ጥላቻ በአመለካከቱ ላይ ተጽዕኖ እንዳላሳደረ አሳይቷል። በመሆኑም በርካታ ሳምራውያን ፊልጶስን “በአንድ ልብ” ያዳመጡት መሆኑ አያስገርምም።—ሥራ 8:6
5-7. ክርስቲያኖች ወደተለያዩ ቦታዎች መበተናቸው ለምሥራቹ መስፋፋት በር መክፈቱን የሚያሳዩ ምሳሌዎችን ተናገር።
5 በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደሆነው ሁሉ ዛሬም ስደት የአምላክ ሕዝቦች ምሥራቹን ከመስበክ ወደኋላ እንዲሉ አላደረገም። በተደጋጋሚ እንደታየው፣ ክርስቲያኖችን ማሳደድ ያስገኘው ውጤት ቢኖር ምሥራቹ ይበልጥ እንዲዳረስ ማድረግ ነው፤ ክርስቲያኖች እስር ቤት ቢጣሉም ሆነ በስደት ምክንያት ወደ ሌላ አገር ቢሄዱ፣ ምሥራቹን በየሄዱበት መስበካቸው አይቀርም። ለምሳሌ ያህል፣ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የይሖዋ ምሥክሮች በናዚ ማጎሪያ ካምፖች ውስጥ አስደናቂ ምሥክርነት መስጠት ችለዋል። ማጎሪያ ካምፕ ውስጥ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር የተገናኘ አንድ አይሁዳዊ እንደሚከተለው ብሏል፦ “የይሖዋ ምሥክር የሆኑ እስረኞች ያላቸውን ጥንካሬ ሳይ እምነታቸው በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ የተመሠረተ እንደሆነ አመንኩ፤ እኔ ራሴም የይሖዋ ምሥክር ሆንኩ።”
6 አንዳንድ ጊዜ የይሖዋን ሕዝቦች ሲያሳድዱ የነበሩ ሰዎች እንኳ ምሥራቹን ተቀብለው ጥሩ ምላሽ ይሰጣሉ። አንድ ምሳሌ እንመልከት፦ ፍራንዝ ደሽ የተባለ አንድ የይሖዋ ምሥክር፣ ኦስትሪያ ወደሚገኘው ጉዘን ማጎሪያ ካምፕ በተዛወረበት ወቅት አንድን የኤስ ኤስ ወታደር መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናት ችሎ ነበር። እነዚህ ሰዎች ከዓመታት በኋላ በአንድ ትልቅ የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ ሁለቱም የምሥራቹ ሰባኪዎች ሆነው ዳግመኛ ሲገናኙ ምን ያህል እንደተደሰቱ አስብ!
7 ክርስቲያኖች በስደት ምክንያት ከአንዱ አገር ወደ ሌላው በሸሹበት ጊዜም ተመሳሳይ ነገር ተከስቷል። ለምሳሌ ያህል፣ በ1970ዎቹ ዓመታት የማላዊ የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ሞዛምቢክ ለመሸሽ በተገደዱበት ወቅት በዚያ ታላቅ ምሥክርነት መስጠት ችለዋል። ከጊዜ በኋላ በሞዛምቢክ ተቃውሞ ቢነሳም እንኳ የስብከቱ ሥራ አልተገታም። ፍራንሲስኮ ኮዋና እንዲህ ብሏል፦ “እርግጥ ነው፣ አንዳንዶቻችን በስብከቱ ሥራችን የተነሳ በተደጋጋሚ ጊዜ እንያዝና እንታሰር ነበር። ያም ሆኖ ብዙዎች ለመንግሥቱ መልእክት ጥሩ ምላሽ ሲሰጡ ስንመለከት አምላክ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖችን እንደረዳቸው ሁሉ እኛንም እየረዳን እንዳለ እርግጠኞች ሆንን” ብሏል።
8. ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች በስብከቱ ሥራ ላይ ምን በጎ ተጽዕኖ አሳድረዋል?
8 እውነት ነው፣ የክርስትና እምነት በሌሎች አካባቢዎች እንዲስፋፋ ምክንያት የሆነው ስደት ብቻ አይደለም። ባለፉት አሥርተ ዓመታት የተከሰቱት ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች፣ የመንግሥቱ መልእክት የተለያየ ቋንቋ ለሚናገሩ ሰዎችና ለልዩ ልዩ ብሔራት እንዲዳረስ አጋጣሚዎችን ከፍተዋል። አንዳንዶች በጦርነት ከሚታመሱና የኢኮኖሚ ችግር ካለባቸው አካባቢዎች በመሸሽ የተረጋጋ ሁኔታ ወዳለባቸው አገሮች ሄደዋል፤ በዚያ በሄዱበት አገርም መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀምረዋል። በርካታ ስደተኞች ወደተለያዩ አገሮች መጉረፋቸው የውጭ አገር ቋንቋ ክልሎች እንዲከፈቱ ምክንያት ሆኗል። ታዲያ አንተስ በአካባቢህ “ከሁሉም ብሔራት፣ ነገዶች፣ ሕዝቦችና ቋንቋዎች” ለተውጣጡ ሰዎች ለመስበክ ጥረት እያደረግክ ነው?—ራእይ 7:9
“ይህን ሥልጣን ለእኔም ስጡኝ” (የሐዋርያት ሥራ 8:9-25)
9. ስምዖን ማን ነበር? በፊልጶስ የተደነቀውስ ለምንድን ነው?
9 ፊልጶስ በሰማርያ በርካታ ተአምራትን ፈጽሟል። ለምሳሌ የአካል ጉዳተኞችን ፈውሷል፤ አልፎ ተርፎም ርኩሳን መናፍስትን አስወጥቷል። (ሥራ 8:6-8) በተለይ አንድ ሰው ፊልጶስ ባለው ተአምራዊ ስጦታ እጅግ ተደንቆ ነበር። ይህ ሰው ስምዖን የተባለ አስማተኛ ነው፤ ሰዎች ለእሱ ካላቸው ከፍተኛ አክብሮት የተነሳ “ይህ ሰው . . . ‘የአምላክ ኃይል’ ነው” ይሉ ነበር። ይሁንና ስምዖን፣ ፊልጶስ በፈጸማቸው ተአምራት ላይ የተገለጠውን እውነተኛውን የአምላክ ኃይል በገዛ ዓይኑ ተመለከተ፤ በዚህም የተነሳ አማኝ ሆነ። (ሥራ 8:9-13) ቆየት ብሎ ግን የስምዖን የውስጥ ዝንባሌ ተፈተነ። እንዴት?
10. (ሀ) ጴጥሮስና ዮሐንስ በሰማርያ ምን አደረጉ? (ለ) ጴጥሮስና ዮሐንስ እጃቸውን የጫኑባቸው አዳዲስ ደቀ መዛሙርት መንፈስ ቅዱስን ሲቀበሉ ሲያይ ስምዖን ምን አደረገ?
10 ሐዋርያት በሰማርያ ስለተገኘው እድገት ሲሰሙ ጴጥሮስንና ዮሐንስን ወደዚያ ላኳቸው። (“ ጴጥሮስ ‘የመንግሥቱን ቁልፎች’ ተጠቀመ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) ሁለቱ ሐዋርያት እዚያ በደረሱ ጊዜ በአዲሶቹ ደቀ መዛሙርት ላይ እጃቸውን ጫኑባቸው፤ እያንዳንዳቸውም መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ። b ስምዖን ይህን ሲያይ ትኩረቱ ተሳበ። በመሆኑም ሐዋርያቱን “እጄን የምጭንበት ሰው ሁሉ መንፈስ ቅዱስን እንዲቀበል ይህን ሥልጣን ለእኔም ስጡኝ” አላቸው። አልፎ ተርፎም ይህን ቅዱስ መብት ለመግዛት በማሰብ ገንዘብ እንደሚሰጣቸው ቃል ገባላቸው!—ሥራ 8:14-19
11. ጴጥሮስ ለስምዖን ምን ተግሣጽ ሰጠው? ስምዖንስ ምን ምላሽ ሰጠ?
11 ጴጥሮስ ለስምዖን ጠንከር ያለ ተግሣጽ ሰጠው። እንዲህ አለው፦ “የአምላክን ነፃ ስጦታ በገንዘብ ማግኘት እንደምትችል ስላሰብክ የብር ገንዘብህ ከአንተ ጋር ይጥፋ። ልብህ በአምላክ ፊት ቀና ስላልሆነ በዚህ አገልግሎት ምንም ዓይነት ድርሻም ሆነ ዕድል ፋንታ የለህም።” ከዚያም ንስሐ እንዲገባ እንዲሁም ይቅርታ ለማግኘት እንዲጸልይ ነገረው። ጴጥሮስ “ምናልባት የልብህ ክፉ ሐሳብ ይቅር ይባልልህ እንደሆነ ይሖዋን ተማጸን” አለው። ስምዖን ክፉ ሰው እንዳልነበር ግልጽ ነው፤ ትክክል የሆነውን ማድረግ ይፈልጋል፤ ሆኖም ለጊዜው የተሳሳተ አስተሳሰብ አድሮበት ነበር። በመሆኑም ሐዋርያቱን “ከተናገራችሁት ነገር አንዱም እንዳይደርስብኝ እባካችሁ ይሖዋን ማልዱልኝ” በማለት ተማጸናቸው።—ሥራ 8:20-24
12. ሲሞናዊነት ምንድን ነው? በሕዝበ ክርስትና ውስጥስ ምን ያህል የተለመደ ነው?
12 ጴጥሮስ ለስምዖን የሰጠው ተግሣጽ በዛሬው ጊዜ ላሉ ክርስቲያኖችም ማስጠንቀቂያ ይሆናል። እንዲያውም ይህ ዘገባ “ሳይመኒ” የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል። “ሳይመኒ” ወይም ሲሞናዊነት የሚለው ቃል ሹመትን በገንዘብ መግዛትን ወይም መሸጥን ያመለክታል፤ በተለይም ሃይማኖታዊ ሹመትን። የከሃዲዋ ሕዝበ ክርስትና ታሪክ በዚህ ዓይነቱ ድርጊት የተሞላ ነው። ዚ ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ (1878) ዘጠነኛው እትም እንደሚከተለው ይላል፦ “ሊቀ ጳጳሱ ስለሚመረጥባቸው ዝግ ስብሰባዎች የሚገልጹ ታሪኮችን የሚያጠና ተማሪ፣ ከሲሞናዊነት ጋር ያልተነካካ አንድም ሹመት እንዳልነበረ መረዳቱ አይቀርም፤ እንዲያውም በዝግ ስብሰባዎቹ ላይ የሚፈጸመው ሲሞናዊነት አብዛኛውን ጊዜ በዓይነቱ እጅግ የከፋ፣ በጣም አሳፋሪና ዓይን ያወጣ ነበር።”
13. ክርስቲያኖች ራሳቸውን ከሲሞናዊነት የሚጠብቁት በየትኞቹ መንገዶች ነው?
13 ክርስቲያኖች ራሳቸውን ከሲሞናዊነት መጠበቅ ይኖርባቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በጉባኤ ውስጥ መብት ሊሰጡ ይችላሉ ተብለው ለሚታሰቡ ወንድሞች ስጦታዎችን በማዥጎድጎድ ወይም እነሱን በማሞጋገስ አንዳንድ ጥቅሞችን ለማግኘት መሞከር የለባቸውም። በሌላ በኩል ደግሞ በኃላፊነት ላይ ያሉ ወንድሞች፣ የተሻለ ኑሮ ላላቸው ክርስቲያኖች እንዳያደሉ መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል። ሁለቱም ቢሆኑ እንደ ሲሞናዊነት ይቆጠራሉ። አዎ፣ ሁሉም የአምላክ አገልጋዮች ራሳቸውን ‘ከሁሉ እንደሚያንሱ አድርገው ሊቆጥሩ’ ይገባል፤ ለኃላፊነት የሚሾሙ ወንድሞችን የይሖዋ መንፈስ እንዲመርጥ መፍቀድ አለባቸው። (ሉቃስ 9:48) ‘የራሳቸውን ክብር የሚሹ’ ሰዎች በአምላክ ድርጅት ውስጥ ቦታ የላቸውም።—ምሳሌ 25:27
“ለመሆኑ የምታነበውን ትረዳዋለህ?” (የሐዋርያት ሥራ 8:26-40)
14, 15. (ሀ) ‘ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ’ ማን ነው? ፊልጶስ ከእሱ ጋር ሊገናኝ የቻለውስ እንዴት ነው? (ለ) ጃንደረባው ፊልጶስ ለነገረው መልእክት ምን ምላሽ ሰጠ? ይህ ሰው የተጠመቀው እንዲሁ በስሜት ተነሳስቶ አልነበረም የምንለውስ ለምንድን ነው? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)
14 አሁን የይሖዋ መልአክ ፊልጶስን ከኢየሩሳሌም ወደ ጋዛ በሚወስደው መንገድ እንዲሄድ አዘዘው። ፊልጶስ፣ እዚያ ስለሚሄድበት ምክንያት ጥያቄ ተፈጥሮበት ከነበረ ብዙም ሳይቆይ መልሱን ያገኛል፤ በመንገዱ ላይ አንድ ኢትዮጵያዊ ጃንደረባ “የነቢዩ ኢሳይያስን መጽሐፍ ድምፁን ከፍ አድርጎ [እያነበበ]” አየ። (“ ‘ጃንደረባ’ የተባለው ከምን አንጻር ነው?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ፊልጶስን ሰውየው ወደተቀመጠበት ሠረገላ እንዲቀርብ ገፋፋው። ፊልጶስ ከሠረገላው ጎን እየሮጠ ጃንደረባውን “ለመሆኑ የምታነበውን ትረዳዋለህ?” ሲል ጠየቀው። እሱም “የሚመራኝ ሰው ሳይኖር እንዴት ልረዳው እችላለሁ?” በማለት መለሰ።—ሥራ 8:26-31
15 ጃንደረባው፣ ሠረገላው ላይ ወጥቶ አብሮት እንዲቀመጥ ፊልጶስን ለመነው። ከዚያ በኋላ ምን ዓይነት አስደሳች ውይይት አድርገው እንደሚሆን መገመት አያዳግትም! በኢሳይያስ ትንቢት ላይ “በግ” ወይም “አገልጋዬ” የተባለው ማን እንደሆነ ለብዙ ዘመናት ሚስጥር ሆኖ ቆይቷል። (ኢሳ. 53:1-12) ሆኖም እየተጓዙ ሳለ ፊልጶስ ይህ ትንቢት በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ፍጻሜውን እንዳገኘ ለኢትዮጵያዊው ጃንደረባ አብራራለት። ይህ ጃንደረባ ወደ ይሁዲነት የተለወጠ ሰው ነው፤ በ33 ዓ.ም. በዋለው የጴንጤቆስጤ ዕለት እንደተጠመቁት ሰዎች ሁሉ እሱም ምን እርምጃ መውሰድ እንዳለበት ወዲያውኑ ተገነዘበ። ፊልጶስን “ውኃ ይኸውና፤ እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምን ነገር አለ?” አለው። ፊልጶስም ጃንደረባውን ወዲያውኑ አጠመቀው! c (“ ‘ውኃ’ ውስጥ ገብቶ መጠመቅ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) ከዚያም ፊልጶስ ወደ አሽዶድ እንዲሄድ አዲስ ተልእኮ ተሰጠው፤ በዚያም ምሥራቹን መስበኩን ቀጠለ።—ሥራ 8:32-40
16, 17. በዛሬው ጊዜ መላእክት በስብከቱ ሥራ እየተካፈሉ ያሉት እንዴት ነው?
16 ዛሬ ያሉ ክርስቲያኖችም ፊልጶስ ይሠራው በነበረው ዓይነት ሥራ የመካፈል መብት አላቸው። ብዙውን ጊዜ የመንግሥቱን ምሥራች የሚሰብኩት በተለያዩ አጋጣሚዎች ለሚያገኟቸው ሰዎች ነው፤ ለምሳሌ በጉዞ ላይ ለሚያገኟቸው ሰዎች ይመሠክራሉ። አንዳንድ ጊዜ ግን ቅን ልብ ካላቸው ሰዎች ጋር የሚገናኙበት መንገድ እንዲሁ የአጋጣሚ ነገር አይመስልም። ይህ መሆኑም የሚጠበቅ ነው፤ ምክንያቱም የመንግሥቱ ምሥራች “በምድር ላይ ለሚኖር ብሔር፣ ነገድ፣ ቋንቋና ሕዝብ ሁሉ” ይዳረስ ዘንድ መላእክት የስብከቱን ሥራ እንደሚመሩ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ራእይ 14:6) የስብከቱ ሥራ የመላእክት አመራር እንደሚኖረው ኢየሱስም ከረጅም ጊዜ በፊት በግልጽ ተናግሯል። ስለ ስንዴውና ስለ እንክርዳዱ በተናገረው ምሳሌ ላይ በመከር ወቅት ይኸውም በዚህ ሥርዓት መደምደሚያ ላይ ‘አጫጆቹ መላእክት’ እንደሚሆኑ ገልጿል። እነዚህ መንፈሳዊ ፍጥረታት “እንቅፋት የሚፈጥሩትን ነገሮች ሁሉና ዓመፅ የሚፈጽሙትን ሰዎች ከመንግሥቱ ይለቅማሉ” በማለትም አክሎ ተናግሯል። (ማቴ. 13:37-41) ከዚሁ ጎን ለጎን መላእክቱ፣ ይሖዋ ወደ ድርጅቱ ሊስባቸው የሚፈልጋቸውን ሰዎች ይሰበስባሉ፤ ይህን ሥራ የጀመሩት በሰማይ የመንግሥቱ ወራሽ የመሆን ተስፋ ያላቸውን ሰዎች በመሰብሰብ ነው፤ በመቀጠል ደግሞ ‘የሌሎች በጎች’ ክፍል የሆነውን “እጅግ ብዙ ሕዝብ” መሰብሰብ ጀመሩ።—ራእይ 7:9፤ ዮሐ. 6:44, 65፤ 10:16
17 በአገልግሎት ላይ የምናገኛቸው አንዳንድ ሰዎች የአምላክን እርዳታ ለማግኘት ሲጸልዩ እንደነበር መናገራቸው መላእክት በዚህ ሥራ እንደሚሳተፉ ማስረጃ ይሆናል። ለአብነት ያህል፣ አንድ ተሞክሮ እናንሳ፤ ሁለት የመንግሥቱ አስፋፊዎች ከአንድ ትንሽ ልጅ ጋር ሆነው እያገለገሉ ነበር። እነዚህ ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች አገልግሎታቸውን ሊያበቁ ሲሉ ልጁ የሚቀጥለውን ቤት ካላንኳኳሁ ብሎ አስቸገራቸው። እንዲያውም እሱ ራሱ ሄዶ በሩን አንኳኳ! አንዲት ወጣት በሩን ስትከፍት ሁለቱ የይሖዋ ምሥክሮች ቀርበው አነጋገሯት። ወጣቷ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያስረዳት ሰው ለማግኘት ስትጸልይ እንደነበር ለአስፋፊዎቹ ስትነግራቸው በጣም ተገረሙ። ይህች ወጣት መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ተስማማች!
18. አገልግሎታችንን አቅልለን መመልከት የሌለብን ለምንድን ነው?
18 የስብከቱ ሥራ ታይቶ በማይታወቅ ስፋት እየተከናወነ ነው፤ አንተም በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ በመሆንህ ይህን ሥራ ከመላእክት ጋር የመሥራት መብት አግኝተሃል። ይህን መብትህን ፈጽሞ አቅልለህ አትመልከተው። በጽናት ተግተህ ማገልገልህን ቀጥል፤ እንዲህ ካደረግህ “ስለ ኢየሱስ የሚገልጸውን ምሥራች” በማወጅ ታላቅ ደስታ ታገኛለህ።—ሥራ 8:35
a ይሄኛው ፊልጶስ ሐዋርያው ፊልጶስ አይደለም። ከዚህ ይልቅ በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 5 ላይ እንደተመለከትነው ‘መልካም ስም ያተረፉ ሰባት ወንዶች’ ከተባሉት አንዱ ነው፤ እነዚህ ወንድሞች በኢየሩሳሌም ለሚኖሩት ግሪክኛ ተናጋሪና ዕብራይስጥ ተናጋሪ መበለቶች በየዕለቱ ምግብ የማከፋፈሉን ሥራ እንዲያስተባብሩ የተሾሙ ናቸው።—ሥራ 6:1-6
b ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው በዚያ ወቅት አዳዲስ ደቀ መዛሙርት በመንፈስ ቅዱስ የሚቀቡት ወይም መንፈስ ቅዱስን የሚቀበሉት በአብዛኛው በሚጠመቁበት ጊዜ ነበር። ይህም ከኢየሱስ ጋር በሰማይ ነገሥታትና ካህናት ሆነው የመግዛት ተስፋ እንዲኖራቸው ያደርጋል። (2 ቆሮ. 1:21, 22፤ ራእይ 5:9, 10፤ 20:6) በዚህ ጊዜ ግን አዲሶቹ ደቀ መዛሙርት በተጠመቁበት ወቅት በመንፈስ ቅዱስ አልተቀቡም። አዲሶቹ ክርስቲያኖች መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉትም ሆነ ከዚያ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ተአምራዊ ስጦታዎች ያገኙት ጴጥሮስና ዮሐንስ እጃቸውን ከጫኑባቸው በኋላ ነበር።
c ጃንደረባው የተጠመቀው እንዲሁ በስሜት ተነሳስቶ አልነበረም። ወደ ይሁዲነት የተለወጠ እንደመሆኑ መጠን የቅዱሳን መጻሕፍት እውቀት ነበረው፤ ስለ መሲሑ የተነገሩ ትንቢቶችንም ያውቅ ነበር። አሁን ደግሞ ኢየሱስ በአምላክ ዓላማ ውስጥ ስለሚጫወተው ሚና ግንዛቤ ስላገኘ ወዲያው ሊጠመቅ ችሏል።