በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 9

‘አምላክ አያዳላም’

‘አምላክ አያዳላም’

ክርስቲያኖች ላልተገረዙ አሕዛብም መስበክ ጀመሩ

በሐዋርያት ሥራ 10:1 እስከ 11:30 ላይ የተመሠረተ

1-3. ጴጥሮስ ምን ራእይ አየ? ትርጉሙን መረዳታችን አስፈላጊ የሆነውስ ለምንድን ነው?

 ጊዜው 36 ዓ.ም. የመከር ወቅት ነው። የፀሐይዋ ሙቀት ደስ ይላል፤ ጴጥሮስ ያለው የወደብ ከተማ በሆነችው በኢዮጴ ነው፤ በአንድ ቤት ሰገነት ላይ ሆኖ እየጸለየ ነው። ወደዚህ ቤት በእንግድነት ከመጣ የተወሰኑ ቀናት አልፈዋል። የቤቱ ባለቤት ስምዖን የተባለ ቆዳ ፋቂ ነው፤ አብዛኞቹ አይሁዳውያን በእንዲህ ዓይነቱ ሰው ቤት ለማረፍ ፈቃደኛ አይሆኑም። a ጴጥሮስ እዚህ ቤት በእንግድነት ለማረፍ ፈቃደኛ መሆኑ በራሱ፣ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ጭፍን ጥላቻን እንዳሸነፈ የሚያሳይ ነው። ያም ቢሆን ጴጥሮስ ይሖዋ የማያዳላ አምላክ መሆኑን በተመለከተ ገና ሊማረው የሚገባ አስፈላጊ ትምህርት አለ።

2 ጴጥሮስ እየጸለየ ሳለ ሰመመን ውስጥ ገባ። በራእይ ያየው ነገር ማንኛውንም አይሁዳዊ የሚረብሽ ነው። ጨርቅ የሚመስል ነገር ከሰማይ ሲወርድ አየ፤ ጨርቁ ላይ በሕጉ መሠረት ርኩስ የሆኑ እንስሳት ነበሩ። ጴጥሮስ እንስሳቱን አርዶ እንዲበላ ሲነገረው “እኔ ንጹሕ ያልሆነና የረከሰ ነገር በልቼ አላውቅም” ሲል መለሰ። ይሁን እንጂ ከአንዴም ሦስት ጊዜ “አምላክ ንጹሕ ያደረገውን ነገር ርኩስ ነው ማለትህን ተው” ተብሎ ተነገረው። (ሥራ 10:14-16) ጴጥሮስ ባየው ራእይ ግራ ተጋባ፤ ብዙም ሳይቆይ ግን የራእዩ ትርጉም ግልጽ ሆነለት።

3 ጴጥሮስ ያየው ራእይ ትርጉም ምንድን ነው? የዚህን ራእይ ትርጉም ማወቃችን በጣም አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም ይሖዋ ለሰዎች ያለውን አመለካከት እንድንገነዘብ የሚያደርግ ትልቅ ቁም ነገር ያዘለ ራእይ ነው። እውነተኛ ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ስለ አምላክ መንግሥት በሚገባ መመሥከር ከፈለግን አምላክ ለሰዎች ያለው ዓይነት አመለካከት ማዳበር ይኖርብናል። ጴጥሮስ ያየውን ራእይ ትርጉም መረዳት እንድንችል ከዚህ ራእይ ጋር በተያያዘ የተከናወኑትን ነገሮች እንመርምር።

‘ዘወትር ወደ አምላክ መማለድ’ (የሐዋርያት ሥራ 10:1-8)

4, 5. ቆርኔሌዎስ ማን ነው? እየጸለየ ሳለስ ምን አጋጠመው?

4 ጴጥሮስ፣ ራእዩን ከማየቱ አንድ ቀን ቀደም ብሎ በስተ ሰሜን 50 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው በቂሳርያ የተከናወነውን ነገር አላወቀም፤ በዚያ የሚኖር ቆርኔሌዎስ የተባለ ሰውም መለኮታዊ ራእይ ተመልክቶ ነበር። በሮም ሠራዊት ውስጥ የጦር መኮንን የሆነው ቆርኔሌዎስ “ለአምላክ ያደረ” ሰው ነበር። b በተጨማሪም ቤተሰቡን በሚገባ የሚንከባከብና ከነቤተሰቡ “ፈሪሃ አምላክ የነበረው ሰው” ነው። ቆርኔሌዎስ ወደ ይሁዲነት የተለወጠ ሰው አይደለም፤ ያልተገረዘ አሕዛብ ነው። ያም ሆኖ ለተቸገሩ አይሁዳውያን ቁሳዊ እርዳታ በመስጠት ርኅራኄ ያሳይ ነበር። እንዲሁም “ዘወትር ወደ አምላክ የሚማልድ” ቅን ሰው ነበር።—ሥራ 10:2

5 ቆርኔሌዎስ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ገደማ እየጸለየ ሳለ አንድ የአምላክ መልአክ ወደ እሱ ሲመጣ በራእይ አየ፤ መልአኩም “ጸሎትህና ምጽዋትህ በአምላክ ፊት መታሰቢያ እንዲሆን አርጓል” አለው። (ሥራ 10:4) ቆርኔሌዎስ መልአኩ በሰጠው መመሪያ መሠረት ሐዋርያው ጴጥሮስን እንዲጠሩት ሰዎች ላከ። ያልተገረዘ አሕዛብ እንደመሆኑ መጠን እስካሁን ተዘግቶ በነበረ በር የመግባት አጋጣሚ ሊከፈትለት ነው። መዳን የሚያስገኝለትን መልእክት ሊሰማ ነው።

6, 7. (ሀ) አምላክ ስለ እሱ እውነቱን ማወቅ የሚፈልጉ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች የሚያቀርቡትን ጸሎት እንደሚሰማ የሚያሳይ ተሞክሮ ተናገር። (ለ) እንደዚህ ከመሰሉ ተሞክሮዎች በመነሳት ምን ብለን መደምደም እንችላለን?

6 በዛሬው ጊዜስ አምላክ፣ ስለ እሱ እውነቱን ማወቅ የሚፈልጉ ቅን ሰዎች የሚያቀርቡትን ጸሎት ይሰማል? እስቲ አንድ ተሞክሮ እንመልከት። በአልባኒያ የምትኖር አንዲት ሴት ስለ ልጆች አስተዳደግ የሚናገር አንድ መጠበቂያ ግንብ ወሰደች። c ይህች ሴት፣ ቤቷ ሄዳ ያነጋገረቻትን የይሖዋ ምሥክር “‘ሴቶች ልጆቼን ለማሳደግ እንዲረዳኝ ወደ አምላክ ስጸልይ ነበር’ ብልሽ ታምኛለሽ? እሱ ነው የላከሽ! የልቤን ነው ያደረስሽልኝ፤ ያመጣሽልኝ ስፈልገው የነበረውን ጽሑፍ ነው!” አለቻት። ከዚያም ሴትየዋና ልጆቿ ማጥናት ጀመሩ፤ በኋላ ባለቤቷም መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ፈቃደኛ ሆነ።

7 እንዲህ ዓይነት ተሞክሮ ያጋጠማት ይህች እህት ብቻ ናት? በፍጹም! እንዲህ ያሉ ተሞክሮዎች በዓለም ዙሪያ በተደጋጋሚ ጊዜ ያጋጥማሉ፤ ይህ እንዲሁ በአጋጣሚ የሆነ ነገር ነው ለማለት ይከብዳል። ታዲያ ከዚህ በመነሳት ምን ብለን መደምደም እንችላለን? በመጀመሪያ ደረጃ፣ ይሖዋ እሱን የሚፈልጉ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች የሚያቀርቡትን ጸሎት ይሰማል። (1 ነገ. 8:41-43፤ መዝ. 65:2) በሁለተኛ ደረጃ፣ የስብከቱ ሥራችን የመላእክት ድጋፍ አለው።—ራእይ 14:6, 7

ጴጥሮስ “በጣም ግራ ተጋብቶ” ነበር (የሐዋርያት ሥራ 10:9-23ሀ)

8, 9. መንፈስ ቅዱስ ለጴጥሮስ ምን አሳወቀው? እሱስ ምን ምላሽ ሰጠ?

8 ጴጥሮስ ገና ሰገነቱ ላይ ነው፤ በራእዩ ትርጉም “በጣም ግራ [ተጋብቷል]።” በዚህ ጊዜ ቆርኔሌዎስ የላካቸው ሰዎች ቤቱ በር ላይ ደረሱ። (ሥራ 10:17) ጴጥሮስ በሕጉ መሠረት ርኩስ የሆኑትን እንስሳት ለመብላት ሦስት ጊዜ እምቢ እንዳለ አስታውስ፤ ታዲያ ከእነዚህ ሰዎች ጋር አብሮ ለመሄድና ወደ አንድ አሕዛብ ቤት ለመግባት ፈቃደኛ ይሆናል? ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የአምላክ ፈቃድ ምን እንደሆነ መንፈስ ቅዱስ በሆነ መንገድ ፍንጭ ሰጠው። ጴጥሮስ እንዲህ ተብሎ ተነገረው፦ “እነሆ፣ ሦስት ሰዎች ይፈልጉሃል። ስለዚህ ተነስተህ ወደ ታች ውረድ፤ የላክኋቸው እኔ ስለሆንኩ ምንም ሳትጠራጠር አብረሃቸው ሂድ።” (ሥራ 10:19, 20) ጴጥሮስ ርኩስ ስለሆኑ እንስሳት ያየው ራእይ፣ የመንፈስ ቅዱስን አመራር ለመቀበል ዝግጁ እንዲሆን ሳይረዳው አልቀረም።

9 ጴጥሮስ፣ ቆርኔሌዎስ ሰዎቹን ወደ እሱ የላካቸው በተሰጠው መለኮታዊ መመሪያ መሠረት መሆኑን አወቀ፤ በመሆኑም ከአሕዛብ ወገን የሆኑትን መልእክተኞች ቤት አስገብቶ “አስተናገዳቸው።” (ሥራ 10:23ሀ) ይህ ታዛዥ ሐዋርያ የአምላክ ፈቃድ ምን እንደሆነ ግልጽ እየሆነለት ስለመጣ ገና ከአሁኑ አመለካከቱን ማስተካከል ጀመረ።

10. ይሖዋ ሕዝቡን የሚመራው እንዴት ነው? ራሳችንንስ ምን ብለን መጠየቃችን ተገቢ ነው?

10 ዛሬም ቢሆን ይሖዋ ሕዝቡን የሚመራው ነገሮችን ደረጃ በደረጃ በመግለጥ ነው። (ምሳሌ 4:18) በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ‘ታማኝና ልባም ባሪያን’ እየመራ ነው። (ማቴ. 24:45) አልፎ አልፎ የአምላክን ቃል ከምንረዳበት መንገድ ጋር በተያያዘ ማስተካከያዎች ሊደረጉ ወይም አንዳንድ ድርጅታዊ አሠራሮች ሊለወጡ ይችላሉ። በመሆኑም ራሳችንን እንደሚከተለው ብለን መጠየቃችን ተገቢ ነው፦ ‘እንዲህ ያሉ ማስተካከያዎች ሲደረጉ ምን ምላሽ እሰጣለሁ? በዚህ ረገድ የአምላክ መንፈስ የሚሰጠውን አመራር ለመቀበል ፈቃደኛ ነኝ?’

ጴጥሮስ “እንዲጠመቁ አዘዛቸው” (የሐዋርያት ሥራ 10:23ለ-48)

11, 12. ጴጥሮስ ቂሳርያ ሲደርስ ምን አደረገ? ምን ትምህርትስ አግኝቶ ነበር?

11 ጴጥሮስ ራእዩን ባየ ማግስት ወደ ቂሳርያ ለመጓዝ ተነሳ፤ ቆርኔሌዎስ የላካቸው ሦስት ሰዎችና ከኢዮጴ የመጡ “ስድስት [አይሁዳውያን] ወንድሞች” በአጠቃላይ ዘጠኝ ሰዎች አብረውት ነበሩ። (ሥራ 11:12) ቆርኔሌዎስ “ዘመዶቹንና የቅርብ ወዳጆቹን ሰብስቦ” የጴጥሮስን መምጣት እየተጠባበቀ ነበር፤ በዚያ የተሰበሰቡት ሰዎች ሁሉ ከአሕዛብ ወገን ሳይሆኑ አይቀሩም። (ሥራ 10:24) ጴጥሮስ እዚያ ሲደርስ ከዚያ ቀደም አስቦት እንኳ የማያውቀውን ነገር አደረገ፦ ወደ አንድ ያልተገረዘ አሕዛብ ቤት ገባ! ከዚያም እንዲህ አለ፦ “አንድ አይሁዳዊ ከሌላ ዘር ጋር ይወዳጅ ወይም ይቀራረብ ዘንድ ሕጉ እንደማይፈቅድ በሚገባ ታውቃላችሁ፤ ሆኖም አምላክ ማንንም ሰው ንጹሕ ያልሆነ ወይም ርኩስ ማለት እንደማይገባኝ ገልጦልኛል።” (ሥራ 10:28) በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ፣ ራእዩ መበላት ያለበትንና የሌለበትን ነገር ከመግለጽ ያለፈ ቁም ነገር እንደያዘ ገብቶታል። ‘ማንንም ሰው [ሌላው ቀርቶ ከአሕዛብ ወገን የሆነን ሰው እንኳ] ርኩስ’ ማለት የለበትም።

“ቆርኔሌዎስም ዘመዶቹንና የቅርብ ወዳጆቹን ሰብስቦ እየጠበቃቸው ነበር።”—የሐዋርያት ሥራ 10:24

12 እዚያ የተሰበሰቡት ሰዎች በሙሉ ጴጥሮስ የሚለውን ነገር ለማዳመጥ ጓጉተዋል። ቆርኔሌዎስ “ይሖዋ እንድትናገር ያዘዘህን ነገር ሁሉ ለመስማት ይኸው ሁላችንም በአምላክ ፊት ተገኝተናል” አለው። (ሥራ 10:33) ስለ ይሖዋ የማወቅ ፍላጎት ያለው አንድ ሰው እንዲህ ቢልህ ምን እንደሚሰማህ አስብ! ጴጥሮስ ንግግሩን የጀመረው በሚከተለው ልብ የሚነካ ሐሳብ ነው፦ “አምላክ እንደማያዳላ በእርግጥ አስተዋልኩ፤ ከዚህ ይልቅ ከየትኛውም ብሔር ቢሆን እሱን የሚፈራና ትክክል የሆነውን ነገር የሚያደርግ ሰው በእሱ ዘንድ ተቀባይነት አለው።” (ሥራ 10:34, 35) ጴጥሮስ፣ አምላክ ሰዎችን በዘራቸው፣ በብሔራቸው ወይም በሌሎች ውጫዊ ነገሮች እንደማይመዝን ተምሯል። ጴጥሮስ በመቀጠል ስለ ኢየሱስ አገልግሎት፣ ሞትና ትንሣኤ መሠከረ።

13, 14. (ሀ) በ36 ዓ.ም. ቆርኔሌዎስና ከአሕዛብ ወገን የሆኑ ሌሎች ሰዎች ክርስትናን መቀበላቸው ምን ነገር ይጠቁማል? (ለ) በሰዎች ውጫዊ ሁኔታ ላይ ተመሥርተን መፍረድ የሌለብን ለምንድን ነው?

13 አሁን ከዚያ ቀደም ታይቶ የማይታወቅ ነገር ተፈጸመ፦ “ጴጥሮስ . . . ገና እየተናገረ ሳለ” መንፈስ ቅዱስ “ከአሕዛብ ወገን [በሆኑት] ሰዎች” ላይ ወረደ። (ሥራ 10:44, 45) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰዎች ከመጠመቃቸው በፊት መንፈስ ቅዱስ እንደወረደባቸው የሚገልጽ ዘገባ የምናገኘው እዚህ ላይ ብቻ ነው። ጴጥሮስ፣ አምላክ እንደተቀበላቸው የሚያሳየውን ይህን ምልክት ሲያስተውል ከአሕዛብ ወገን የሆኑትን እነዚህን ሰዎች “እንዲጠመቁ አዘዛቸው።” (ሥራ 10:48) በ36 ዓ.ም. እነዚህ አሕዛብ ክርስትናን ሲቀበሉ አምላክ ለአይሁዳውያን ልዩ ሞገስ የሚያሳይበት ጊዜ አበቃ። (ዳን. 9:24-27) ጴጥሮስ ለአሕዛብ በመስበክ ረገድ ቀዳሚ በመሆን፣ ሦስተኛውንና የመጨረሻውን ‘የመንግሥቱን ቁልፍ’ ተጠቀመበት። (ማቴ. 16:19) ይህ ቁልፍ ያልተገረዙ አሕዛብ በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች እንዲሆኑ በር የሚከፍት ነው።

14 በዛሬው ጊዜ ያለን የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎችም ‘በአምላክ ዘንድ አድልዎ እንደሌለ’ እንገነዘባለን። (ሮም 2:11) “የእሱ ፈቃድ ሁሉም ዓይነት ሰዎች እንዲድኑ” ነው። (1 ጢሞ. 2:4) በመሆኑም በሰዎች ውጫዊ ሁኔታ ላይ ተመሥርተን መፍረድ የለብንም። የእኛ ተልእኮ ስለ አምላክ መንግሥት በሚገባ መመሥከር ነው፤ ይህ ደግሞ ዘራቸው፣ ብሔራቸው፣ ውጫዊ ገጽታቸው ወይም ሃይማኖታቸው ምንም ይሁን ምን ለሰዎች ሁሉ መስበክን ይጨምራል።

“መቃወማቸውን ተዉ፤ ደግሞም . . . አምላክን አከበሩ” (የሐዋርያት ሥራ 11:1-18)

15, 16. አንዳንድ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ጴጥሮስን የተቹት ለምንድን ነው? እሱስ ያደረገው ነገር ትክክል መሆኑን ያስረዳው እንዴት ነው?

15 ጴጥሮስ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ፣ የተፈጸመውን ሁኔታ ለመናገር እንደጓጓ ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ ያልተገረዙ አሕዛብ “የአምላክን ቃል እንደተቀበሉ” የሚገልጸው ወሬ ከእሱ ቀድሞ ኢየሩሳሌም ሳይደርስ አልቀረም። ጴጥሮስ እዚያ እንደደረሰ “ግርዘትን የሚደግፉ ሰዎች ይተቹት ጀመር።” “ወዳልተገረዙ ሰዎች ቤት” ገብቶ ‘ከእነሱ ጋር መብላቱ’ አበሳጭቷቸው ነበር። (ሥራ 11:1-3) አከራካሪው ጉዳይ ‘አሕዛብ የክርስቶስ ተከታዮች መሆን ይችላሉ ወይስ አይችሉም?’ የሚለው አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ‘ከአሕዛብ ወገን የሆኑ ሰዎች ይሖዋን ተቀባይነት ባለው መንገድ ለማምለክ ግርዘትን ጨምሮ ሕጉን ማክበር ይጠበቅባቸዋል ወይስ አይጠበቅባቸውም?’ የሚለው ነበር፤ አይሁዳውያን የሆኑት ደቀ መዛሙርት፣ ‘አሕዛብ ሕጉን ማክበር አለባቸው’ የሚል ጠንካራ አቋም ነበራቸው። በግልጽ ማየት እንደሚቻለው አንዳንዶቹ የሙሴን ሕግ መተው ከብዷቸው ነበር።

16 ታዲያ ጴጥሮስ፣ ያደረገው ነገር ትክክል መሆኑን ያስረዳው እንዴት ነው? የሐዋርያት ሥራ 11:4-16 እንደሚያሳየው በጉዳዩ ላይ የአምላክ አመራር እንዳለበት የሚያሳዩ አራት ማስረጃዎችን ጠቅሷል፤ እነሱም የሚከተሉት ናቸው፦ (1) ያየው መለኮታዊ ራእይ (ከቁጥር 4-10)፣ (2) መንፈስ ቅዱስ የሰጠው ትእዛዝ (ቁጥር 11, 12)፣ (3) መልአኩ ቆርኔሌዎስን ማነጋገሩ (ቁጥር 13, 14) እና (4) በአሕዛብ ላይ መንፈስ ቅዱስ መውረዱ (ቁጥር 15, 16)። ጴጥሮስ ቆም ብለው እንዲያስቡ በሚያደርግ አሳማኝ ጥያቄ ንግግሩን ደመደመ፦ “እንግዲህ አምላክ በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ላመንነው ለእኛ [ለአይሁዳውያን] የሰጠውን ያንኑ [የመንፈስ ቅዱስ] ነፃ ስጦታ ለእነሱም [ላመኑት አሕዛብ] ከሰጠ፣ ታዲያ አምላክን መከልከል የምችል እኔ ማን ነኝ?”—ሥራ 11:17

17, 18. (ሀ) ጴጥሮስ የተናገረው ነገር ለአይሁዳውያን ክርስቲያኖች መፈተኛ የሆነው እንዴት ነው? (ለ) በጉባኤ ውስጥ አንድነትን ጠብቆ ማቆየት ተፈታታኝ የሚሆነው ለምንድን ነው? ራሳችንን ምን ብለን መጠየቃችንስ ተገቢ ነው?

17 ጴጥሮስ የተናገረው ነገር ለእነዚያ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች መፈተኛ ሆነ። በውስጣቸው ያለውን ጭፍን ጥላቻ ሙሉ በሙሉ በማስወገድ አዲስ የተጠመቁትን አሕዛብ እንደ ክርስቲያን ወንድሞቻቸው ይቀበሏቸው ይሆን? ዘገባው እንዲህ ይላል፦ “እነሱም [ሐዋርያቱና ሌሎቹ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች] ይህን በሰሙ ጊዜ መቃወማቸውን ተዉ፤ ደግሞም ‘እንዲህ ከሆነማ አምላክ አሕዛብም ሕይወት ማግኘት እንዲችሉ ንስሐ የሚገቡበት አጋጣሚ ሰጥቷቸዋል ማለት ነው’ እያሉ አምላክን አከበሩ።” (ሥራ 11:18) እንዲህ ዓይነት አዎንታዊ አመለካከት መያዛቸው የጉባኤው አንድነት ተጠብቆ እንዲቆይ አድርጓል።

18 በዛሬው ጊዜም አንድነትን ጠብቆ መኖር ለእውነተኛ ክርስቲያኖች ተፈታታኝ ሊሆን ይችላል፤ ምክንያቱም “ከሁሉም ብሔራት፣ ነገዶች፣ ሕዝቦችና ቋንቋዎች የተውጣጡ” ናቸው። (ራእይ 7:9) በብዙ ጉባኤዎች ውስጥ የተለያየ ዘር፣ ባሕልና አስተዳደግ ያላቸው ሰዎች እናገኛለን። በመሆኑም ራሳችንን እንዲህ ብለን መጠየቃችን ተገቢ ነው፦ ‘ጭፍን ጥላቻን ከልቤ ውስጥ ሙሉ በሙሉ አስወግጃለሁ? ለአንድነት ፀር የሆኑ የዓለም ዝንባሌዎች ተጽዕኖ እንዳያሳድሩብኝ እጠነቀቃለሁ? ለምሳሌ በአካባቢዬ ያሉ ሰዎች ለአገራቸው፣ ለብሔራቸው፣ ለዘራቸው ወይም ለባሕላቸው ያላቸው ስሜት ወንድሞቼን በምይዝበት መንገድ ላይ ተጽዕኖ እንዳያሳድር ቆርጫለሁ?’ የመጀመሪያዎቹ አሕዛብ ክርስትናን ከተቀበሉ ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ጴጥሮስ (ኬፋ) ምን እንዳጋጠመው አስታውስ። የሌሎች ጭፍን ጥላቻ ተጽዕኖ ስላሳደረበት “ራሱን ከአሕዛብ [ክርስቲያኖች] አገለለ”፤ በዚህም የተነሳ ጳውሎስ ተግሣጽ ሰጥቶታል። (ገላ. 2:11-14) እንግዲያው ጭፍን ጥላቻ ወጥመድ እንዳይሆንብን ምንጊዜም ጥንቃቄ እናድርግ።

‘ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች አማኝ ሆኑ’ (የሐዋርያት ሥራ 11:19-26ሀ)

19. በአንጾኪያ ያሉት አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ለእነማን መስበክ ጀመሩ? ውጤቱስ ምን ነበር?

19 ታዲያ የኢየሱስ ተከታዮች ላልተገረዙ አሕዛብ መስበክ ጀመሩ? ቆየት ብሎ በሶርያዋ አንጾኪያ ምን እንደተከናወነ ልብ በል። d በዚህች ከተማ ውስጥ በርካታ አይሁዳውያን ይኖሩ ነበር፤ በአይሁዳውያንና በአሕዛብ መካከል ግን ጥላቻ አልነበረም ማለት ይቻላል። በመሆኑም በአንጾኪያ ለአሕዛብ ለመመሥከር የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ነበር። አንዳንድ አይሁዳውያን ደቀ መዛሙርት ‘ግሪክኛ ተናጋሪ ለሆኑ ሰዎች’ ምሥራቹን መስበክ የጀመሩት በዚህች ከተማ ውስጥ ነበር። (ሥራ 11:20) እነዚህ ክርስቲያኖች ግሪክኛ ተናጋሪ ለሆኑ አይሁዳውያን ብቻ ሳይሆን ላልተገረዙ አሕዛብም ይሰብኩ ነበር። ይሖዋም ሥራቸውን ስለባረከው ‘ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች አማኝ ሆኑ።’—ሥራ 11:21

20, 21. በርናባስ ትሑት መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው? እኛስ አገልግሎታችንን በምናከናውንበት ጊዜ እንዲህ ያለውን ትሕትና ማሳየት የምንችለው በምን መንገድ ነው?

20 በኢየሩሳሌም የሚገኘው ጉባኤ፣ ይህን የደረሰ መከር ለመሰብሰብ በርናባስን ወደ አንጾኪያ ላከው። ይሁንና በርካታ ሰዎች ምሥራቹን ስለተቀበሉ ሥራው ለበርናባስ ከአቅሙ በላይ ሳይሆንበት አልቀረም። ታዲያ ለአሕዛብ ሐዋርያ እንዲሆን ከተመረጠው ከሳኦል የተሻለ ሊረዳው የሚችል ይኖራል? (ሥራ 9:15፤ ሮም 1:5) በርናባስ ሳኦልን እንደ ተቀናቃኙ አድርጎ ይመለከተው ይሆን? በፍጹም! ከዚህ ይልቅ የእሱ እገዛ እንደሚያስፈልገው በትሕትና ተቀብሏል። ሳኦልን ለመፈለግ እሱ ራሱ ወደ ጠርሴስ ሄደ፤ በሥራው እንዲያግዘውም ወደ አንጾኪያ አመጣው። በዚያ ባለው ጉባኤ ውስጥ ያሉትን ደቀ መዛሙርት በማነጽ ለአንድ ዓመት ያህል አብረው ቆዩ።—ሥራ 11:22-26ሀ

21 እኛስ አገልግሎታችንን በምናከናውንበት ጊዜ ትሕትና ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? ትሕትና ያለብንን የአቅም ገደብ አምኖ መቀበልን ይጨምራል። ሁላችንም የተለያየ ጠንካራ ጎንና ችሎታ አለን። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንዶች መደበኛ ባልሆነ መንገድ ወይም ከቤት ወደ ቤት በመመሥከር ረገድ ውጤታማ ይሆናሉ፤ ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግ ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመር ግን ይከብዳቸው ይሆናል። በአንድ የአገልግሎት ዘርፍ ማሻሻያ ማድረግ እንዳለብህ ከተሰማህ ለምን ሌሎች እንዲረዱህ አትጠይቅም? ቅድሚያ ወስደህ እርዳታ መጠየቅህ በአገልግሎት ይበልጥ ፍሬያማ ያደርግሃል፤ ደስታህም ይጨምራል።—1 ቆሮ. 9:26

‘ለወንድሞች እርዳታ መላክ’ (የሐዋርያት ሥራ 11:26ለ-30)

22, 23. የአንጾኪያ ክርስቲያኖች የወንድማማችነት ፍቅራቸውን የሚገልጽ ምን ነገር አድርገዋል? በዛሬው ጊዜ ያሉ የአምላክ ሕዝቦችስ ምን ተመሳሳይ ነገር ያደርጋሉ?

22 ደቀ መዛሙርቱ “በመለኮታዊ አመራር ለመጀመሪያ ጊዜ ‘ክርስቲያኖች’ ተብለው የተጠሩት በአንጾኪያ ነበር።” (ሥራ 11:26ለ) አምላክ የሰጣቸው ይህ ስም በአኗኗራቸው የክርስቶስን ፈለግ በጥብቅ የሚከተሉትን እነዚህን ሰዎች ጥሩ አድርጎ ይገልጻቸዋል። ከአሕዛብ ወገን የሆኑ ሰዎች ክርስትናን ሲቀበሉ ከአይሁዳውያን ክርስቲያኖች ጋር የጠበቀ ወንድማማችነት መሥርተው ይሆን? በ46 ዓ.ም. ገደማ ታላቅ ረሃብ በተከሰተ ጊዜ ምን እንደሆነ ተመልከት። e በጥንት ዘመን ረሃብ ሲከሰት ይበልጥ የሚጠቁት ድሆች ነበሩ፤ ምክንያቱም ተቀማጭ ገንዘብም ሆነ ምግብ የላቸውም። በይሁዳ ካሉት አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ብዙዎቹ ድሆች ሳይሆኑ አይቀሩም፤ በመሆኑም ይህ ረሃብ በተከሰተበት ጊዜ እርዳታ አስፈልጓቸው ነበር። ከአሕዛብ ወገን የመጡትን ጨምሮ በአንጾኪያ የሚገኙት ክርስቲያኖች ይህን ሲያውቁ “በይሁዳ ለሚኖሩ ወንድሞች እርዳታ ለመላክ ወሰኑ።” (ሥራ 11:29) ይህ እውነተኛ የወንድማማችነት ፍቅርን የሚያሳይ ተግባር ነው።

23 በዛሬው ጊዜ ባሉት የአምላክ ሕዝቦች መካከልም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። በሌላ አገርም ሆነ በአካባቢያችን ያሉ ወንድሞቻችን ችግር ላይ እንደወደቁ ስንሰማ እነሱን ለመርዳት የቻልነውን ሁሉ እናደርጋለን። እንደ አውሎ ነፋስ፣ የምድር መናወጥና ሱናሚ ያሉ የተፈጥሮ አደጋዎች ሲከሰቱ ቅርንጫፍ ኮሚቴዎች የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎችን በአስቸኳይ ያደራጃሉ፤ እነዚህ ኮሚቴዎች ደግሞ በአደጋው ለተጠቁ ወንድሞቻችን አስፈላጊውን እርዳታ ይሰጣሉ። እነዚህ የእርዳታ ሥራዎች እውነተኛ የወንድማማችነት ፍቅር እንዳለን በተግባር ያሳያሉ።—ዮሐ. 13:34, 35፤ 1 ዮሐ. 3:17

24. ጴጥሮስ ያየውን ራእይ ትርጉም በቁም ነገር እንደምንመለከተው ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

24 በመጀመሪያው መቶ ዘመን ጴጥሮስ በኢዮጴ በአንድ ሰገነት ላይ ሆኖ ያየው ራእይ ለእኛ ለእውነተኛ ክርስቲያኖች ትልቅ ቁም ነገር ይዟል። የምናመልከው አምላክ አያዳላም። ስለ መንግሥቱ በሚገባ እንድንመሠክር ይፈልጋል፤ ይህ ደግሞ ዘር፣ ብሔር ወይም የኑሮ ደረጃ ሳንለይ ለሁሉም ሰዎች መስበክን ይጨምራል። እንግዲያው ለመስማት ፈቃደኛ ለሆኑ ሰዎች ሁሉ ምሥራቹን ለማድረስ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።—ሮም 10:11-13

ወንድሞቻችን ችግር ላይ እንደወደቁ ስንሰማ እነሱን ለመርዳት የቻልነውን ሁሉ እናደርጋለን

a አንዳንድ አይሁዳውያን፣ ቆዳ ፋቂዎችን ይንቁ ነበር፤ ምክንያቱም በዚህ ሙያ የተሰማራ ሰው የእንስሳት ቆዳና በድን መንካቱ አይቀርም፤ ከዚህም ሌላ ቆዳውን ሲያዘጋጅ እንደ ውሻ እዳሪ የመሳሰሉ ነገሮችን ይጠቀም ነበር። ቆዳ ፋቂዎች ወደ ቤተ መቅደሱ እንዲገቡ አይፈቀድላቸውም፤ የሚሠሩበት ቦታም ከከተማ ቢያንስ 50 ክንድ ወይም 20 ሜትር ገደማ መራቅ ነበረበት። የስምዖን ቤት “ባሕሩ አጠገብ” የሆነበት አንዱ ምክንያት ይህ ሊሆን ይችላል።—ሥራ 10:6

b ቆርኔሌዎስና የሮም ሠራዊት” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

cልጆችን ለማሳደግ የሚረዳ አስተማማኝ ምክር” የሚለው ርዕስ በኅዳር 1, 2006 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 4 እስከ 7 ላይ ይገኛል።

d የሶርያዋ አንጾኪያ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

e አይሁዳዊው ታሪክ ጸሐፊ ጆሴፈስ ይህ “ታላቅ ረሃብ” በንጉሠ ነገሥት ቀላውዴዎስ ዘመነ መንግሥት (41-54 ዓ.ም.) እንደተከሰተ ገልጿል።