በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 5

“አምላክን እንደ ገዢያችን አድርገን ልንታዘዝ ይገባል”

“አምላክን እንደ ገዢያችን አድርገን ልንታዘዝ ይገባል”

ሐዋርያቱ የወሰዱት አቋም ለሁሉም እውነተኛ ክርስቲያኖች አርዓያ ይሆናል

በሐዋርያት ሥራ 5:12 እስከ 6:7 ላይ የተመሠረተ

1-3. (ሀ) ሐዋርያት በሳንሄድሪን ሸንጎ ፊት የቀረቡት ለምንድን ነው? ትልቁ ጥያቄስ ምንድን ነው? (ለ) ሐዋርያቱ የወሰዱትን አቋም ለማወቅ የምንጓጓው ለምንድን ነው?

 የሳንሄድሪን ሸንጎ አባላት በንዴት ጦፈዋል! የክርስቶስ ሐዋርያት በዚህ ከፍተኛ ሸንጎ ፊት ቆመዋል። ለምን? ሊቀ ካህናትና የሳንሄድሪን ሊቀ መንበር የሆነው ዮሴፍ ቀያፋ “በዚህ ስም ማስተማራችሁን እንድታቆሙ በጥብቅ አዘናችሁ ነበር” ሲል በቁጣ ተናገራቸው። በቁጣ የተሞላው ይህ ሰው የኢየሱስን ስም መጥራት እንኳ አልፈለገም። አክሎም እንዲህ አለ፦ “እናንተ ግን ኢየሩሳሌምን በትምህርታችሁ ሞልታችኋታል፤ የዚህንም ሰው ደም በእኛ ላይ ለማምጣት ቆርጣችሁ ተነስታችኋል።” (ሥራ 5:28) መልእክቱ ግልጽ ነው፦ ‘መስበካችሁን አቁሙ፤ አለዚያ ታገኟታላችሁ!’

2 ሐዋርያቱ ምን ምላሽ ይሰጡ ይሆን? የስብከት ተልእኮ የሰጣቸው ከአምላክ ሥልጣን የተቀበለው ኢየሱስ ነው። (ማቴ. 28:18-20) ሐዋርያቱ በሰው ፍርሃት ተሸንፈው ዝም ይሉ ይሆን? ወይስ በድፍረት በአቋማቸው ጸንተው መስበካቸውን ይቀጥላሉ? አሁን ትልቁ ጥያቄ፦ የሚታዘዙት አምላክን ነው ወይስ ሰውን? የሚለው ነው። ሐዋርያው ጴጥሮስ ሁሉንም ሐዋርያት በመወከል በእርግጠኝነት መልስ ሰጠ። የተናገረው ሐሳብ የማያሻማና ድፍረት የሚንጸባረቅበት ነበር።

3 እውነተኛ ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ሐዋርያቱ የሳንሄድሪን ሸንጎ ለሰነዘረባቸው ማስፈራሪያ የሰጡትን ምላሽ ማወቅ እንፈልጋለን። የስብከት ተልእኮው እኛንም ይመለከታል። አምላክ የሰጠንን ይህን ተልእኮ ስንወጣ እኛም ተቃውሞ ሊያጋጥመን ይችላል። (ማቴ. 10:22) ተቃዋሚዎች በሥራችን ላይ ገደብ ሊጥሉ ወይም ከናካቴው ሊያግዱት ይችላሉ። ታዲያ ምን እናደርጋለን? ሐዋርያቱ የወሰዱትን አቋምና በሳንሄድሪን a ሸንጎ ፊት እንዲቀርቡ ያደረጓቸውን ሁኔታዎች መመርመራችን ይጠቅመናል።

‘የይሖዋ መልአክ በሮቹን ከፈተ’ (የሐዋርያት ሥራ 5:12-21ሀ)

4, 5. ቀያፋና ሰዱቃውያን ‘በቅናት የተሞሉት’ ለምን ነበር?

4 ጴጥሮስና ዮሐንስ መስበካቸውን እንዲያቆሙ ለመጀመሪያ ጊዜ ትእዛዝ ሲሰጣቸው “ስላየነውና ስለሰማነው ነገር ከመናገር ወደኋላ ማለት አንችልም” በማለት መልስ እንደሰጡ አስታውስ። (ሥራ 4:20) ጴጥሮስና ዮሐንስ ከሳንሄድሪን ከወጡ በኋላ ከሌሎቹ ሐዋርያት ጋር በመሆን በቤተ መቅደሱ መስበካቸውን ቀጠሉ። ሐዋርያቱ የታመሙትን መፈወስንና አጋንንትን ማስወጣትን ጨምሮ ታላላቅ ተአምራትን ይፈጽሙ ነበር። ይህንንም ያደርጉ የነበረው “የሰለሞን መተላለፊያ” በተባለው ቦታ ነው፤ በቤተ መቅደሱ ምሥራቃዊ ክፍል የሚገኘው ይህ ባለመጠለያ ኮሪደር በርካታ አይሁዳውያን የሚሰበሰቡበት ቦታ ነበር። የሚገርመው ደግሞ የጴጥሮስ ጥላ ያረፈባቸው ሰዎች እንኳ ከሕመማቸው ይፈወሱ ነበር! አካላዊ ፈውስ ያገኙት ብዙዎቹ ሰዎች መንፈሳዊ ፈውስ ለሚያስገኘው የእውነት ቃል ጥሩ ምላሽ ሰጥተዋል። በዚህም የተነሳ “በጌታ ያመኑ እጅግ በርካታ ወንዶችና ሴቶች በየጊዜው በእነሱ ላይ ይጨመሩ ነበር።”—ሥራ 5:12-15

5 በዚህም የተነሳ ቀያፋና እሱ አባል የሆነበት ሃይማኖታዊ ኑፋቄ አባላት ይኸውም ሰዱቃውያን “በቅናት ተሞልተው” ሐዋርያቱን እስር ቤት ከተቷቸው። (ሥራ 5:17, 18) ሰዱቃውያን እጅግ የተቆጡት ለምን ነበር? ሐዋርያቱ ኢየሱስ ከሞት እንደተነሳ ያስተምሩ ነበር፤ ሰዱቃውያን ደግሞ በትንሣኤ አያምኑም። ሐዋርያቱ አንድ ሰው መዳን የሚችለው በኢየሱስ ካመነ ብቻ ነው ይሉ ነበር፤ ሰዱቃውያን ግን ‘ሕዝቡ እሱን እንደ መሪያቸው አድርገው መመልከት ከጀመሩ ሮማውያን የበቀል እርምጃ ይወስዱብናል’ ብለው ይሰጉ ነበር። (ዮሐ. 11:48) በመሆኑም ሐዋርያቱን ዝም ለማሰኘት ቆርጠው መነሳታቸው ምንም አያስገርምም!

6. በዛሬው ጊዜ በይሖዋ ሕዝቦች ላይ በዋነኝነት ስደት የሚቆሰቁሱት እነማን ናቸው? ይህስ ሊያስደንቀን የማይገባው ለምንድን ነው?

6 ዛሬም በይሖዋ ሕዝቦች ላይ በዋነኝነት ስደት የሚቆሰቁሱት የሃይማኖት መሪዎች ናቸው። እነዚህ ተቃዋሚዎች የመንግሥት ባለሥልጣናትንና መገናኛ ብዙኃንን ተጠቅመው የስብከት ሥራችንን ለማስቆም ይሞክራሉ። ታዲያ ይህ ሊያስገርመን ይገባል? በፍጹም። የምንሰብከው መልእክት የሐሰት ሃይማኖትን የሚያጋልጥ ነው። ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ተቀብለው ቅዱስ ጽሑፋዊ ካልሆኑ እምነቶችና ልማዶች ነፃ እየወጡ ነው። (ዮሐ. 8:32) ታዲያ የምንናገረው መልእክት የሃይማኖት መሪዎችን ቢያስቆጣ ያስደንቃል?

7, 8. መልአኩ የሰጣቸው ትእዛዝ በሐዋርያቱ ላይ ምን በጎ ተጽዕኖ አሳድሮ ሊሆን ይችላል? እኛስ ራሳችንን ምን ብለን መጠየቃችን አስፈላጊ ነው?

7 ሐዋርያቱ እስር ቤት ሆነው ፍርዳቸውን ሲጠባበቁ፣ በጠላቶቻቸው እጅ ተገድለው ሰማዕት እንደሚሆኑ አስበው ሊሆን ይችላል። (ማቴ. 24:9) ሆኖም ሌሊት ላይ አንድ ፈጽሞ ያልተጠበቀ ነገር ተከሰተ፤ “የይሖዋ መልአክ የእስር ቤቱን በሮች” ከፈተ። b (ሥራ 5:19) ከዚያም መልአኩ “በቤተ መቅደሱ ቆማችሁ . . . መናገራችሁን ቀጥሉ” በማለት ግልጽ መመሪያ ሰጣቸው። (ሥራ 5:20) ይህ ትእዛዝ ሐዋርያቱ ያደረጉት ነገር ትክክለኛ መሆኑን አረጋግጦላቸው መሆን አለበት። በተጨማሪም መልአኩ የተናገረው ሐሳብ ሐዋርያቱ ምንም ነገር ቢያጋጥማቸው በአቋማቸው እንዲጸኑ ሳያበረታታቸው አይቀርም። “ንጋት ላይ ወደ ቤተ መቅደሱ ገብተው” በጠንካራ እምነትና በድፍረት “ያስተምሩ ጀመር።”—ሥራ 5:21

8 እያንዳንዳችን ራሳችንን እንዲህ ብለን መጠየቃችን አስፈላጊ ነው፦ ‘እኔስ ተመሳሳይ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙኝ በስብከቱ ሥራ ለመቀጠል የሚያስችል እምነትና ድፍረት አለኝ?’ በእርግጥም “ስለ አምላክ መንግሥት በሚገባ በመመሥከር” የምናከናውነውን ሥራ መላእክት እንደሚደግፉትና እንደሚመሩት ማወቃችን ብርታት ይሰጠናል።—ሥራ 28:23፤ ራእይ 14:6, 7

“ከሰው ይልቅ አምላክን እንደ ገዢያችን አድርገን ልንታዘዝ ይገባል” (የሐዋርያት ሥራ 5:21ለ-33)

“አምጥተውም በሳንሄድሪን ሸንጎ ፊት አቆሟቸው።”—የሐዋርያት ሥራ 5:27

9-11. ሐዋርያቱ መስበካቸውን እንዲያቆሙ የሳንሄድሪን ሸንጎ ለሰጣቸው ትእዛዝ ምን ምላሽ ሰጡ? ይህ አቋማቸውስ ለእውነተኛ ክርስቲያኖች አርዓያ የሚሆነው እንዴት ነው?

9 አሁን ቀያፋና ሌሎቹ የሳንሄድሪን ሸንጎ አባላት በሐዋርያቱ ላይ ውሳኔ ሊያስተላልፉ ተዘጋጅተዋል። በእስር ቤቱ ስለተከናወነው ሁኔታ ምንም የሚያውቁት ነገር ስላልነበር እስረኞቹን እንዲያመጧቸው ሰዎች ላኩ። የተላኩት ሰዎች እዚያ ሲደርሱ እስር ቤቱ በሚገባ ተቆልፏል፤ “ጠባቂዎቹም በሮቹ ላይ [ቆመዋል]።” እስረኞቹ ግን እዚያ የሉም፤ የተላኩት ሰዎች ይህን ሲያዩ ምን ያህል ተገርመው ሊሆን እንደሚችል አስብ። (ሥራ 5:23) ወዲያውም የቤተ መቅደሱ ሹም፣ ሐዋርያቱ ወደ ቤተ መቅደሱ ተመልሰው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እየመሠከሩ እንደሆነ ተነገረው፤ እስር ቤት እንዲገቡ ምክንያት የሆናቸውን ያንኑ ሥራ እየሠሩ ነው! የቤተ መቅደሱ ሹምና ጠባቂዎቹ በፍጥነት ወደ ቤተ መቅደሱ ሄዱ፤ ከዚያም እስረኞቹን ይዘው በሳንሄድሪን ሸንጎ ፊት አቀረቧቸው።

10 በዚህ ምዕራፍ መግቢያ ላይ እንደተገለጸው በንዴት የጦፉት የሃይማኖት መሪዎች ሐዋርያቱ መስበካቸውን እንዲያቆሙ በግልጽ ነገሯቸው። ታዲያ ሐዋርያቱ ምን ምላሽ ሰጡ? ጴጥሮስ ሌሎቹን በመወከል “ከሰው ይልቅ አምላክን እንደ ገዢያችን አድርገን ልንታዘዝ ይገባል” በማለት በድፍረት ተናገረ። (ሥራ 5:29) ይህ የሐዋርያቱ አቋም ከዘመን ዘመን ለእውነተኛ ክርስቲያኖች አርዓያ ተደርጎ ሲነሳ ኖሯል። ሰብዓዊ ገዢዎችን ልንታዘዛቸው ይገባል፤ ሆኖም አምላክ አድርጉ ያለውን እንዳናደርግ ሲከለክሉን ወይም አታድርጉ ያለውን እንድናደርግ ሲጠይቁን ልንታዘዛቸው አንችልም። በመሆኑም በዘመናችን ‘የበላይ ባለሥልጣናት’ በስብከቱ ሥራችን ላይ እገዳ ቢጥሉም አምላክ ምሥራቹን እንድንናገር የሰጠንን ተልእኮ ከመፈጸም ወደኋላ አንልም። (ሮም 13:1) ከዚህ ይልቅ ትኩረት የማይስቡ የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ስለ አምላክ መንግሥት በሚገባ መመሥከራችንን እንቀጥላለን።

11 ሐዋርያቱ በድፍረት የሰጡት መልስ ቀድሞውንም ተበሳጭተው የነበሩትን የሸንጎ አባላት ይበልጥ ማስቆጣቱ አያስገርምም። ሐዋርያቱን “ሊገድሏቸው” ቆርጠው ተነሱ። (ሥራ 5:33) እነዚህ ደፋርና ቀናተኛ ምሥክሮች ሰማዕትነት የሚቀርላቸው አይመስልም። ደስ የሚለው ግን ፈጽሞ ካልጠበቁት አቅጣጫ እርዳታ የሚያገኙበት ሁኔታ ተፈጠረ!

“ልታጠፏቸው አትችሉም” (የሐዋርያት ሥራ 5:34-42)

12, 13. (ሀ) ገማልያል ለሸንጎው አባላት ምን ምክር ሰጠ? እነሱስ ምን አደረጉ? (ለ) በዛሬው ጊዜ ይሖዋ ሕዝቦቹን ሊረዳቸው የሚችለው እንዴት ነው? ‘ለጽድቅ ስንል መከራ እንድንቀበል’ ከፈቀደስ ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን?

12 “በሕዝቡ ሁሉ ዘንድ [የተከበረ] የሕግ አስተማሪ” የሆነው ገማልያል መናገር ጀመረ። c ይህ ሕግ አዋቂ ሐዋርያቱን “ለጊዜው ወደ ውጭ እንዲያስወጧቸው” ማዘዙ በሌሎቹ የሸንጎው አባላት ዘንድ ከፍተኛ ክብር የሚሰጠው ሰው መሆኑን ያሳያል። (ሥራ 5:34) ገማልያል፣ ከዚያ በፊት ተነስተው የነበሩትንና በኋላም መሪዎቻቸው ሲሞቱ ወዲያው የጠፉትን ቡድኖች እንደ ምሳሌ ጠቀሰ፤ ከዚያም መሪያቸው ኢየሱስ በቅርቡ የሞተውን ሐዋርያቱን ትንሽ እንዲታገሧቸው ሐሳብ አቀረበ። ገማልያል እንደሚከተለው በማለት ያቀረበው ሐሳብ አሳማኝ ነበር፦ “እነዚህን ሰዎች አትንኳቸው፤ ተዉአቸው። ይህ ውጥን ወይም ይህ ሥራ ከሰው ከሆነ ይጠፋል፤ ከአምላክ ከሆነ ግን ልታጠፏቸው አትችሉም። እንዲያውም ከአምላክ ጋር ስትጣሉ ትገኙ ይሆናል።” (ሥራ 5:38, 39) የሸንጎው አባላት የገማልያልን ምክር ሰሙ። ያም ሆኖ ሐዋርያቱን ገረፏቸው፤ “በኢየሱስ ስም መናገራቸውን እንዲያቆሙ” አዝዘውም ለቀቋቸው።—ሥራ 5:40

13 በዛሬው ጊዜም ይሖዋ ሕዝቡን እንዲረዱ እንደ ገማልያል ያሉ ተደማጭነት ያላቸው ሰዎችን ሊያስነሳ ይችላል። (ምሳሌ 21:1) ይሖዋ ኃያል የሆኑ ገዢዎችን፣ ዳኞችን ወይም ሕግ አርቃቂዎችን ከእሱ ፈቃድ ጋር የሚስማማ እርምጃ እንዲወስዱ በመንፈሱ ሊያነሳሳቸው ይችላል። (ነህ. 2:4-8) ይሁን እንጂ ‘ለጽድቅ ስንል መከራ እንድንቀበል’ ከፈቀደ እርግጠኛ የምንሆንባቸው ሁለት ነገሮች አሉ። (1 ጴጥ. 3:14) በመጀመሪያ ደረጃ፣ አምላክ ለመጽናት የሚያስችል ኃይል ሊሰጠን ይችላል። (1 ቆሮ. 10:13) በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ተቃዋሚዎች የአምላክን ሥራ ‘ሊያጠፉት’ አይችሉም።—ኢሳ. 54:17

14, 15. (ሀ) ሐዋርያቱ ከተገረፉ በኋላ ምን ተሰማቸው? ለምንስ? (ለ) የይሖዋ ሕዝቦች ስደት ሲደርስባቸው በደስታ እንደሚጸኑ የሚያሳይ ተሞክሮ ተናገር።

14 ሐዋርያቱ መገረፋቸው ደስታቸውን እንዲያጡ ወይም አቋማቸውን እንዲያላሉ አድርጓቸዋል? በፍጹም! እንዲያውም “ደስ እያላቸው ከሳንሄድሪን ሸንጎ ወጡ።” (ሥራ 5:41) ‘የተደሰቱት’ ለምንድን ነው? መቼም መገረፋቸው ያስከተለባቸው አካላዊ ሥቃይ በራሱ እንዳላስደሰታቸው የታወቀ ነው። ከዚህ ይልቅ ያስደሰታቸው፣ ስደት የደረሰባቸው ለምን እንደሆነ ማወቃቸው ነው፤ የተሰደዱት በይሖዋ ፊት ንጹሕ አቋማቸውን በመጠበቃቸውና ምሳሌያቸው የሆነውን የኢየሱስን ፈለግ በመከተላቸው የተነሳ እንደሆነ ገብቷቸዋል።—ማቴ. 5:11, 12

15 በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበሩት ወንድሞቻችን ሁሉ እኛም በምሥራቹ የተነሳ መከራ ሲደርስብን በደስታ እንጸናለን። (1 ጴጥ. 4:12-14) እርግጥ ነው፣ ዛቻ፣ ስደት ወይም እስራት በራሱ የሚያስደስት ነገር ነው ማለት አይደለም። ሆኖም ንጹሕ አቋማችንን መጠበቃችን ውስጣዊ እርካታ ያስገኝልናል። የሄንሪክ ዶርኒክን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ ለዓመታት በአምባገነናዊ መንግሥታት ሥር ከፍተኛ እንግልት ደርሶበታል። ነሐሴ 1944 ባለሥልጣናቱ እሱንና ወንድሙን ወደ ማጎሪያ ካምፕ ለመላክ ወሰኑ። ተቃዋሚዎቹ እንዲህ ብለው ነበር፦ “እነሱን ምንም ነገር እንዲያደርጉ ማሳመን የማይቻል ነው። ሰማዕት መሆናቸው ያስደስታቸዋል።” ወንድም ዶርኒክ ግን እንዲህ ብሏል፦ “ሰማዕት የመሆን ፍላጎት ባይኖረኝም ለይሖዋ ታማኝ በመሆኔ የሚደርስብኝን ሥቃይ በድፍረትና በክብር መቀበሌ ያስደስተኝ ነበር።”—ያዕ. 1:2-4

ሐዋርያት እንዳደረጉት ሁሉ እኛም “ከቤት ወደ ቤት” እየሄድን እንሰብካለን

16. ሐዋርያቱ በሚገባ ለመመሥከር ቆርጠው እንደነበር ያሳዩት እንዴት ነው? እኛስ ሐዋርያቱ የተጠቀሙበትን የስብከት ዘዴ እየኮረጅን ያለነው እንዴት ነው?

16 ሐዋርያቱ ወዲያውኑ ወደ ስብከቱ ሥራቸው ተመለሱ። ያለምንም ፍርሃት “በየቀኑ በቤተ መቅደስም ሆነ ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ ስለ ክርስቶስ . . . የሚናገረውን ምሥራች . . . ማወጃቸውን ቀጠሉ።” d (ሥራ 5:42) እነዚህ ቀናተኛ ሰባኪዎች በሚገባ ለመመሥከር ቆርጠው ነበር። ኢየሱስ ክርስቶስ ባዘዛቸው መሠረት ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ መልእክቱን ያውጁ እንደነበር ልብ በል። (ማቴ. 10:7, 11-14) በትምህርታቸው ኢየሩሳሌምን ሊሞሉ የቻሉት በዚህ መንገድ እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። በዛሬው ጊዜም የይሖዋ ምሥክሮች የሚታወቁት ሐዋርያቱ በተጠቀሙበት በዚህ የስብከት ዘዴ ነው። ክልላችን ውስጥ እያንዳንዱን ቤት ማንኳኳታችን ምሥራቹን በሚገባ ለመመሥከር ያለንን ፍላጎት ያሳያል፤ ምክንያቱም ይህ የስብከት ዘዴ እያንዳንዱ ሰው ምሥራቹን የሚሰማበት አጋጣሚ እንዲያገኝ ያደርጋል። በእርግጥ ይሖዋ ከቤት ወደ ቤት በመሄድ የምናከናውነውን አገልግሎት ባርኮታል? አዎ፣ ባርኮታል! በዚህ በመጨረሻው ዘመን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ለመንግሥቱ መልእክት ጥሩ ምላሽ እየሰጡ ነው፤ ከእነዚህ መካከል ደግሞ ብዙዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ምሥራቹን የሰሙት የይሖዋ ምሥክሮች ቤታቸውን ባንኳኩበት ወቅት ነው።

“አስፈላጊ ጉዳይ” ለማከናወን የተሾሙ ብቃት ያላቸው ወንዶች (የሐዋርያት ሥራ 6:1-6)

17-19. ጉባኤውን ሊከፋፍል የሚችል ምን ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር? ሐዋርያትስ ችግሩን ለመፍታት ምን እርምጃ ወሰዱ?

17 አሁን ደግሞ ገና አዲስ የሆነውን ጉባኤ ስጋት ላይ የሚጥል አንድ ስውር አደጋ ተፈጠረ። ለመሆኑ ይህ ስውር አደጋ ምንድን ነው? በወቅቱ ከተጠመቁት ደቀ መዛሙርት ብዙዎቹ ከኢየሩሳሌም ውጭ የመጡ ናቸው፤ ወደ አገራቸው ከመመለሳቸው በፊት በዚያ ቆይተው ተጨማሪ እውቀት መቅሰም ፈልገው ነበር። በኢየሩሳሌም የሚኖሩት ደቀ መዛሙርት እነዚህ ሰዎች የሚያስፈልጋቸውን ምግብና ቁሳቁስ ለማሟላት በፈቃደኝነት የገንዘብ መዋጮ አድርገው ነበር። (ሥራ 2:44-46፤ 4:34-37) በዚህ ጊዜ ልዩ ትኩረት የሚያሻው አንድ ጉዳይ ተነሳ። “በየዕለቱ በሚከናወነው ምግብ የማከፋፈል ሥራ” ግሪክኛ ተናጋሪ የሆኑት መበለቶች ‘ቸል ተባሉ።’ (ሥራ 6:1) ዕብራይስጥ ተናጋሪ የሆኑት መበለቶች ግን ቸል አልተባሉም። የተፈጠረው ችግር በጉባኤው ውስጥ መድልዎ እንደተፈጸመ የሚጠቁም ነበር። ይህ ደግሞ ክፍፍል የሚፈጥር ከባድ ችግር ነው።

18 እየሰፋ በመሄድ ላይ ባለው የክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ እንደ በላይ አካል ሆነው የሚያገለግሉት ሐዋርያት ነበሩ፤ አሁን ከተነሳው ጉዳይ ጋር በተያያዘ ግን ‘ምግብ ለማከፋፈል ሲሉ የአምላክን ቃል የማስተማር ሥራቸውን መተዋቸው’ ተገቢ እንዳልሆነ ተሰማቸው። (ሥራ 6:2) ስለዚህ ለችግሩ እልባት ለመስጠት ሲሉ ይህን “አስፈላጊ ጉዳይ” የሚያከናውኑ “በመንፈስና በጥበብ የተሞሉ ሰባት ወንዶች” እንዲመርጡ ለደቀ መዛሙርቱ መመሪያ ሰጡ። (ሥራ 6:3) ለዚህ ሥራ ብቃት ያላቸው ወንዶች ያስፈልጉ ነበር፤ ምክንያቱም ምግብ ማከፋፈል ብቻ ሳይሆን ጥሩ የገንዘብ አያያዝ፣ ዕቃ ግዢና መዝገብ መያዝ የሚጠይቅ ሥራ ነበር። የተመረጡት ወንዶች በሙሉ የግሪክኛ ስም ነበራቸው፤ ምናልባት ይህ፣ ቅር ተሰኝተው በነበሩት መበለቶች ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኙ ሳያደርጋቸው አይቀርም። ሐዋርያቱ የተመረጡትን ሰዎች ሁኔታ በጸሎት ከመረመሩ በኋላ ይህን “አስፈላጊ ጉዳይ” እንዲያከናውኑ ሰባቱን ሰዎች ሾሙ። e

19 የተሾሙት ሰባት ወንድሞች ምግብ የማከፋፈል ሥራ ተሰጣቸው ሲባል ምሥራቹን ከመስበክ ኃላፊነታቸው ነፃ ሆነዋል ማለት ነው? በፍጹም! ከተመረጡት ወንድሞች መካከል አንዱ እስጢፋኖስ ሲሆን እሱም ደፋርና ቀናተኛ ምሥክር መሆኑን አስመሥክሯል። (ሥራ 6:8-10) ፊልጶስም ከሰባቱ ወንድሞች አንዱ ሲሆን “ወንጌላዊው” ተብሎ ተጠርቷል። (ሥራ 21:8) ስለሆነም ሰባቱ ወንድሞች የመንግሥቱን ምሥራች በቅንዓት መስበካቸውን እንደቀጠሉ ግልጽ ነው።

20. በዛሬው ጊዜ ያሉ የይሖዋ ሕዝቦች የሐዋርያትን ምሳሌ የሚከተሉት እንዴት ነው?

20 በዛሬው ጊዜ ያሉ የይሖዋ ሕዝቦች የሐዋርያትን ምሳሌ ይከተላሉ። ለጉባኤ ኃላፊነቶች የሚታጩ ወንዶች አምላካዊ ጥበብ እንዳላቸውና መንፈስ ቅዱስ በውስጣቸው እንደሚሠራ ያስመሠከሩ መሆን ይኖርባቸዋል። የበላይ አካሉ በሚሰጠው መመሪያ መሠረት ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃቶችን ያሟሉ ወንዶች፣ ሽማግሌዎች ወይም የጉባኤ አገልጋዮች ሆነው እንዲያገለግሉ ይሾማሉ። f (1 ጢሞ. 3:1-9, 12, 13) ብቃቶቹን የሚያሟሉት እነዚህ ወንዶች በመንፈስ ቅዱስ ተሹመዋል ሊባል ይችላል። እነዚህ ትጉ ወንድሞች ብዙ አስፈላጊ ጉዳዮችን ይከታተላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ እገዛ የሚያስፈልጋቸውን ታማኝ አረጋውያን መርዳት የሚቻልበትን መንገድ ያቀናጃሉ። (ያዕ. 1:27) አንዳንድ ሽማግሌዎች ከስብሰባ አዳራሾች ግንባታና ትላልቅ ስብሰባዎችን ከማደራጀት ጋር የተያያዘ ብዙ ሥራ ያከናውናሉ፤ በአካባቢያቸው ካሉ የሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴዎች ጋር ተባብረው የሚያከናውኗቸው ሥራዎችም አሉ። የጉባኤ አገልጋዮች ደግሞ ከእረኝነት ወይም ከማስተማሩ ሥራ ጋር በቀጥታ ተያያዥነት የሌላቸው በርካታ ሥራዎችን ያከናውናሉ። ሁሉም የተሾሙ ወንዶች በጉባኤና በድርጅቱ ውስጥ የሚሰጧቸውን ኃላፊነቶች አምላክ ከሰጠው የስብከት ተልእኮ ጋር ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ማስኬድ ይኖርባቸዋል።—1 ቆሮ. 9:16

“የአምላክ ቃል መስፋፋቱን ቀጠለ” (የሐዋርያት ሥራ 6:7)

21, 22. ይሖዋ አዲስ የተቋቋመውን ጉባኤ እንደባረከው የሚያሳየው ምንድን ነው?

21 አዲስ የተቋቋመው ጉባኤ የገጠሙትን ፈተናዎች በይሖዋ እርዳታ አልፏል፤ ከውጭ ስደት፣ ከውስጥ ደግሞ ክፍፍል የሚፈጥር አደጋ ቢመጣም አልተበገረም። የሚከተለው ሐሳብ ጉባኤው የይሖዋ በረከት እንዳልተለየው በግልጽ ያሳያል፦ “የአምላክ ቃል መስፋፋቱን ቀጠለ፤ በኢየሩሳሌምም የደቀ መዛሙርቱ ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ ሄደ፤ በጣም ብዙ ካህናትም ይህን እምነት ተቀበሉ።” (ሥራ 6:7) በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ ከሚገኙት የጉባኤውን እድገት የሚገልጹ ዘገባዎች ውስጥ ይህ አንዱ ብቻ ነው። (ሥራ 9:31፤ 12:24፤ 16:5፤ 19:20፤ 28:31) በዛሬው ጊዜ በሌሎች የዓለም ክፍሎች የመንግሥቱ ምሥራች ምን ያህል እየተስፋፋ እንዳለ የሚገልጹ ሪፖርቶችን ስንሰማ አንበረታታም?

22 በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. በንዴት የበገኑት የሃይማኖት መሪዎች ተስፋ አልቆረጡም። ሌላ የስደት ማዕበል የሚነሳበት ጊዜ ሩቅ አልነበረም። በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ እንደምንመለከተው ብዙም ሳይቆይ እስጢፋኖስ አስከፊ የሆነ ስደት ደርሶበታል።

a ሳንሄድሪን—የአይሁድ ከፍተኛ ፍርድ ቤት” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

b በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ መላእክት በቀጥታ ከተጠቀሱባቸው 20 የሚያክሉ ቦታዎች ይህ የመጀመሪያው ነው። ከዚህ በፊት በሐዋርያት ሥራ 1:10 ላይ መላእክት “ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎች” ተብለው በተዘዋዋሪ መንገድ ተጠቅሰዋል።

c ገማልያል—በረቢዎች ዘንድ የተከበረ ሰው” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

d ‘ከቤት ወደ ቤት’ መስበክ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

e ይህን “አስፈላጊ ጉዳይ” ማከናወን ከባድ ኃላፊነት ስለነበር እነዚህ ወንዶች ከሽማግሌዎች የሚፈለጉትን ብቃቶች ያሟሉ ሳይሆኑ አይቀሩም። ይሁን እንጂ ወንዶች በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ሽማግሌዎች ወይም የበላይ ተመልካቾች ተብለው መሾም የጀመሩት መቼ እንደሆነ ቅዱሳን መጻሕፍት በግልጽ አይናገሩም።

f በመጀመሪያው መቶ ዘመን፣ አንዳንድ ብቃት ያላቸው ወንዶች ሽማግሌዎችን የመሾም ኃላፊነት ተሰጥቷቸው ነበር። (ሥራ 14:23፤ 1 ጢሞ. 5:22፤ ቲቶ 1:5) በአሁኑ ወቅት የበላይ አካሉ የወረዳ የበላይ ተመልካቾችን ይሾማል፤ የወረዳ የበላይ ተመልካቾች ደግሞ ሽማግሌዎችንና የጉባኤ አገልጋዮችን የመሾም ኃላፊነት አለባቸው።