ምዕራፍ 2
“ምሥክሮቼ ትሆናላችሁ”
ኢየሱስ የስብከቱን ሥራ በግንባር ቀደምትነት እንዲያከናውኑ ሐዋርያቱን ያዘጋጃቸው እንዴት ነው?
በሐዋርያት ሥራ 1:1-26 ላይ የተመሠረተ
1-3. ኢየሱስ ሐዋርያቱን በተሰናበታቸው ጊዜ የነበረው ሁኔታ ምን ይመስላል? ምን ጥያቄዎችስ ይነሳሉ?
ሐዋርያቱ ከኢየሱስ መለየት አልፈለጉም። ከእሱ ጋር ያሳለፏቸው የመጨረሻዎቹ ሳምንታት ለእነሱ እጅግ አስደሳች ነበሩ! ኢየሱስ ከሞት መነሳቱ፣ በተስፋ መቁረጥ ስሜት ተውጠው የነበሩትን ሐዋርያት በደስታ እንዲፈነድቁ አድርጓቸዋል። ኢየሱስ ለ40 ቀናት ያህል ለተከታዮቹ በተደጋጋሚ ጊዜ በመገለጥ ተጨማሪ ትምህርትና ማበረታቻ ሲሰጣቸው ቆይቷል። በዚህ ዕለት የተገለጠላቸው ግን ለመጨረሻ ጊዜ ነው።
2 ሐዋርያቱ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ተሰብስበው ኢየሱስ የሚናገረውን እያንዳንዱን ቃል በትኩረት እያዳመጡ ነው። ንግግሩ ባያበቃ ደስ ባላቸው ነበር፤ ሆኖም ኢየሱስ የሚናገረውን ነገር እንደጨረሰ እጆቹን አንስቶ ባረካቸው። ከዚያም ምድርን ለቆ ወደ ላይ ከፍ ከፍ ማለት ጀመረ! ተከታዮቹ እያዩት ወደ ሰማይ ወጣ። በመጨረሻም ደመና ከዓይናቸው ሰወረው። ኢየሱስ ከእይታቸው ቢሰወርም ሐዋርያቱ ግን በትኩረት ወደ ሰማይ መመልከታቸውን አላቆሙም።—ሉቃስ 24:50፤ ሥራ 1:9, 10
3 ይህ ክስተት በኢየሱስ ሐዋርያት ሕይወት ላይ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል። ጌታቸው ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሰማይ አርጓል፤ ታዲያ አሁን ምን ያደርጉ ይሆን? እርግጠኛ የምንሆንበት አንድ ነገር፣ ኢየሱስ እሱ የጀመረውን ሥራ ማከናወናቸውን እንዲቀጥሉ አዘጋጅቷቸዋል። ታዲያ ይህን ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ኃላፊነት እንዲወጡ ያስታጠቃቸው እንዴት ነው? የእነሱስ ምላሽ ምን ነበር? ይህ ጉዳይ በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖችን የሚመለከተው እንዴት ነው? የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ የመጀመሪያ ምዕራፍ ለእነዚህ ጥያቄዎች የሚሰጠው መልስ ብርታት ይጨምርልናል።
“ብዙ አሳማኝ ማስረጃዎች” (የሐዋርያት ሥራ 1:1-5)
4. ሉቃስ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ ሰፍሮ የሚገኘውን ዘገባውን የጀመረው እንዴት ነው?
4 ሉቃስ ዘገባውን የጀመረው በቀጥታ ቴዎፍሎስን በመጥቀስ ነው፤ ቀደም ሲል ወንጌሉን የጻፈውም ለዚሁ ሰው ነበር። a ሉቃስ ይህ ዘገባው ከወንጌሉ የቀጠለ መሆኑን ግልጽ ለማድረግ ሲል በወንጌሉ መጨረሻ ላይ የጠቀሳቸውን ክንውኖች ትንሽ ለየት ባለ አገላለጽ በድጋሚ ጠቀሰ፤ አንዳንድ አዳዲስ መረጃዎችንም አካተተ።
5, 6. (ሀ) የኢየሱስ ተከታዮች ጠንካራ እምነት ይዘው እንዲቀጥሉ የሚረዳቸው ምንድን ነው? (ለ) በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች እምነታቸው “በብዙ አሳማኝ ማስረጃዎች” ላይ የተመሠረተ ነው የምንለው ለምንድን ነው?
5 የኢየሱስ ተከታዮች ጠንካራ እምነት ይዘው እንዲቀጥሉ የሚረዳቸው ምንድን ነው? የሐዋርያት ሥራ 1:3 ስለ ኢየሱስ ሲናገር “ሕያው መሆኑን በብዙ አሳማኝ ማስረጃዎች አሳያቸው” ይላል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “አሳማኝ ማስረጃዎች” ተብሎ የተተረጎመውን ቃል የተጠቀመው “የተወደደው ሐኪም ሉቃስ” ብቻ ነው። (ቆላ. 4:14) ይህ ቃል በሕክምና ጽሑፎች ውስጥ ይሠራበት የነበረ ሲሆን ተጨባጭ፣ የማያሻማና ተአማኒ የሆነ ማስረጃን ያመለክታል። ኢየሱስ እንዲህ ያለውን ማስረጃ አቅርቧል። ለተከታዮቹ በተደጋጋሚ ጊዜያት ተገልጦላቸዋል፤ አንዳንዴ ለአንድ ወይም ለሁለት ሐዋርያቱ፣ በሌላ ጊዜ ደግሞ ለሐዋርያቱ በሙሉ፣ በአንድ ወቅት ደግሞ ከ500 ለሚበልጡ ወንድሞች እንደተገለጠ እናነባለን። (1 ቆሮ. 15:3-6) በእርግጥም ኢየሱስ አሳማኝ ማስረጃዎች አቅርቧል!
6 በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ ያሉ እውነተኛ ክርስቲያኖች እምነት “በብዙ አሳማኝ ማስረጃዎች” ላይ የተመሠረተ ነው። ኢየሱስ በምድር ላይ እንደኖረ፣ ለኃጢአታችን ሲል እንደሞተ እንዲሁም ከሞት እንደተነሳ የሚያሳይ ማስረጃ አለ? እንዴታ! በመንፈስ መሪነት በተጻፈው የአምላክ ቃል ውስጥ እምነት የሚጣልባቸው የዓይን ምሥክሮች ያሰፈሯቸው ዘገባዎች ይገኛሉ፤ በእርግጥም የሚያስፈልገንን አሳማኝ ማስረጃ ቃሉ ውስጥ እናገኛለን። እነዚህን ዘገባዎች የምንመረምርና የምናነብበውን ለመረዳት እንዲያግዘን ወደ ይሖዋ የምንጸልይ ከሆነ እምነታችን በእጅጉ ይጠናከራል። እውነተኛ እምነት፣ አንድን ነገር በጭፍን አምኖ ከመቀበል የሚለየው በጠንካራ ማስረጃ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ነው። እውነተኛ እምነት የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ወሳኝ ነገር ነው።—ዮሐ. 3:16
7. በማስተማሩና በመስበኩ ሥራ ኢየሱስ ለተከታዮቹ ምን ምሳሌ ትቶላቸዋል?
7 በተጨማሪም ኢየሱስ “ስለ አምላክ መንግሥት ይነግራቸው ነበር።” ለምሳሌ ያህል፣ መሲሑ መከራ እንደሚቀበልና እንደሚሞት የሚናገሩትን ትንቢቶች አብራርቶላቸዋል። (ሉቃስ 24:13-32, ) ኢየሱስ መሲሕ በመሆን ስለሚጫወተው ሚና በሚናገርበት ወቅት ስለ አምላክ መንግሥት እያስተማረ ነው ሊባል ይችላል፤ ምክንያቱም የአምላክ መንግሥት ንጉሥ እንዲሆን መቀባቱን እየገለጸ ነው። ምንጊዜም ቢሆን የኢየሱስ ስብከት ዋነኛ ጭብጥ የአምላክ መንግሥት ነበር፤ ዛሬ ያሉት ተከታዮቹ የሚሰብኩት መልእክትም ያተኮረው በዚሁ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ነው።— 46, 47ማቴ. 24:14፤ ሉቃስ 4:43
“እስከ ምድር ዳር ድረስ” (የሐዋርያት ሥራ 1:6-12)
8, 9. (ሀ) የኢየሱስ ሐዋርያት ምን ሁለት የተሳሳቱ አስተሳሰቦች ነበሯቸው? (ለ) ኢየሱስ ሐዋርያቱ አስተሳሰባቸውን እንዲያስተካክሉ የረዳቸው እንዴት ነው? ይህስ በዛሬው ጊዜ ላሉ ክርስቲያኖች ምን ትምህርት ይዟል?
8 ኢየሱስ ምድር ላይ ሳለ ለመጨረሻ ጊዜ ከሐዋርያቱ ጋር የተሰበሰበው በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ነበር። እነሱም “ጌታ ሆይ፣ ለእስራኤል መንግሥትን መልሰህ የምታቋቁመው በዚህ ጊዜ ነው?” በማለት በጉጉት ጠየቁት። (ሥራ 1:6) ሐዋርያቱ ይህን ጥያቄ ማንሳታቸው ሁለት የተሳሳቱ አመለካከቶች እንደነበሯቸው ይፋ እንዲወጣ አድርጓል። በመጀመሪያ ደረጃ፣ የአምላክ መንግሥት ተመልሶ የሚቋቋመው ለሥጋዊ እስራኤላውያን መስሏቸው ነበር። በሁለተኛ ደረጃ፣ ተስፋ የተደረገበት መንግሥት ወዲያውኑ መግዛት እንደሚጀምር ጠብቀው ነበር፤ “በዚህ ጊዜ” ማለታቸው ይህን ያሳያል። ታዲያ ኢየሱስ አስተሳሰባቸውን እንዲያስተካክሉ የረዳቸው እንዴት ነው?
9 ኢየሱስ የመጀመሪያው የተሳሳተ አስተሳሰባቸው ብዙም ሳይቆይ እንደሚስተካከል ሳያውቅ አይቀርም። ተከታዮቹ ከአሥር ቀን በኋላ አዲስ ብሔር ሲወለድ ማለትም መንፈሳዊ እስራኤል ሲቋቋም ይመለከታሉ! አምላክ ከሥጋዊ እስራኤላውያን ጋር የነበረው ግንኙነት ሊቋረጥ የቀረው ጊዜ ጥቂት ነበር። ሁለተኛውን የተሳሳተ አስተሳሰብ በተመለከተ ግን ኢየሱስ “ጊዜያትንና ወቅቶችን የመወሰን ሥልጣን ያለው አብ ብቻ ስለሆነ እናንተ ይህን ማወቅ አያስፈልጋችሁም” በማለት ደግነት የሚንጸባረቅበት ማሳሰቢያ ሰጣቸው። (ሥራ 1:7) ዓላማው የሚፈጸምበትን ጊዜ የመወሰን ሥልጣን የይሖዋ ብቻ ነው። ኢየሱስ ራሱ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት፣ መጨረሻው የሚመጣበትን “ቀንና ሰዓት” የሚያውቀው “አብ ብቻ” እንደሆነና በዚያ ወቅት ወልድም እንኳ ይህን እንደማያውቅ ተናግሯል። (ማቴ. 24:36) ዛሬም ቢሆን ክርስቲያኖች የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ የሚመጣበት ጊዜ ከሚገባው በላይ የሚያሳስባቸው ከሆነ ማወቅ ስለማያስፈልጋቸው ጉዳይ እየተጨነቁ ነው ማለት ይቻላል።
10. ሐዋርያቱ የነበራቸውን የትኛውን አመለካከት ማዳበር ያስፈልገናል? ለምንስ?
10 ያም ሆኖ በኢየሱስ ሐዋርያት ላይ ለመፍረድ መቸኮል የለብንም፤ እነዚህ ሰዎች ከፍተኛ እምነት ነበራቸው። የተሰጣቸውን እርማትም በትሕትና ተቀብለዋል። በተጨማሪም ጥያቄውን ያነሱት በተሳሳተ አስተሳሰብ ላይ ተመሥርተው ቢሆንም ያቀረቡት ጥያቄ ጥሩ አመለካከት እንዳላቸውም ይጠቁማል። ኢየሱስ በተደጋጋሚ ጊዜ ለተከታዮቹ “ነቅታችሁ ጠብቁ” የሚል ማሳሰቢያ ሰጥቷቸው ነበር። (ማቴ. 24:42፤ 25:13፤ 26:41) የሐዋርያቱ ጥያቄ በመንፈሳዊ ንቁ መሆናቸውን ያሳያል፤ ይሖዋ እርምጃ ሊወስድ እንደሆነ የሚጠቁሙ ነገሮችን በጉጉት ይከታተሉ ነበር። በዛሬው ጊዜ እኛም እንዲሁ ዓይነት አመለካከት ማዳበር ያስፈልገናል። እንዲያውም የምንኖረው “በመጨረሻዎቹ ቀናት” ስለሆነ እንዲህ ማድረጋችን ይበልጥ አጣዳፊ ነው።—2 ጢሞ. 3:1-5
11, 12. (ሀ) ኢየሱስ ለተከታዮቹ ምን ተልእኮ ሰጥቷቸዋል? (ለ) ኢየሱስ ከስብከቱ ተልእኮ ጋር በተያያዘ መንፈስ ቅዱስን መጥቀሱ ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?
11 ኢየሱስ በዋነኝነት ሊያሳስባቸው የሚገባው ጉዳይ ምን እንደሆነ ለሐዋርያቱ ጠቁሟቸዋል። እንዲህ ብሏቸዋል፦ “መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በሚወርድበት ጊዜ ኃይል ትቀበላላችሁ፤ በኢየሩሳሌም፣ በመላው ይሁዳና በሰማርያ እንዲሁም እስከ ምድር ዳር ድረስ ምሥክሮቼ ትሆናላችሁ።” (ሥራ 1:8) ኢየሱስ ከሞት እንደተነሳ የሚገልጸው ምሥራች መጀመሪያ የሚታወጀው እሱ በተገደለበት በኢየሩሳሌም ነው። በኋላም ይህ መልእክት በመላው ይሁዳ፣ ከዚያም በሰማርያ ቆየት ብሎም ራቅ ባሉ አካባቢዎች ይዳረሳል።
12 ኢየሱስ ይህን የስብከት ተልእኮ የጠቀሰው እነሱን ለመርዳት መንፈስ ቅዱስ እንደሚልክላቸው በድጋሚ ቃል ከገባላቸው በኋላ መሆኑ የተገባ ነው። በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ “መንፈስ ቅዱስ” የሚለው አገላለጽ ከሚገኝባቸው ከ40 የሚበልጡ ቦታዎች አንዱ ይህ ነው። ስሜት ቀስቃሽ የሆነው ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በተደጋጋሚ እንደሚያጎላው ያለመንፈስ ቅዱስ እርዳታ የይሖዋን ፈቃድ መፈጸም አንችልም። በመሆኑም መንፈስ ቅዱስን ለማግኘት ዘወትር መጸለያችን ምንኛ የተገባ ነው! (ሉቃስ 11:13) ይህ መንፈስ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ አሁን ያስፈልገናል።
13. በዛሬው ጊዜ ላሉት የአምላክ ሕዝቦች የተሰጠው የስብከት ተልእኮ ምን ያህል ስፋት አለው? እኛስ ይህን ተልእኮ ለመፈጸም ልባዊ ጥረት ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው?
13 “እስከ ምድር ዳር ድረስ” የሚለው አገላለጽ ያን ጊዜ የሚያመለክተው የምድርን የተወሰነ ክፍል ነው። ይሁንና ቀደም ባለው ምዕራፍ ላይ እንደተመለከትነው የይሖዋ ምሥክሮች በአሁኑ ወቅት በመላው ዓለም እየሰበኩ ነው፤ አምላክ ሁሉም ዓይነት ሰዎች የመንግሥቱን ምሥራች እንዲሰሙ እንደሚፈልግ ስለሚያውቁ የተሰጣቸውን ተልእኮ ለመፈጸም ልባዊ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል። (1 ጢሞ. 2:3, 4) አንተስ ይህን ሕይወት አድን ሥራ በትጋት እየፈጸምክ ነው? ከዚህ የተሻለ አስደሳችና አርኪ ሥራ ፈጽሞ ልታገኝ አትችልም! ይሖዋ ይህን ሥራ ለመሥራት የሚያስችል ኃይል ይሰጥሃል። የስብከቱን ሥራ ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማከናወን ምን ዘዴዎችን መጠቀም እንደምትችልና ምን ዓይነት ዝንባሌ ማዳበር እንዳለብህ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ይጠቁምሃል።
14, 15. (ሀ) መላእክቱ የክርስቶስን መመለስ አስመልክተው ምን አሉ? ይህን ሲሉስ ምን ማለታቸው ነበር? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።) (ለ) ክርስቶስ የተመለሰው ‘በዚያው በሄደበት ሁኔታ’ ነው ሊባል የሚችለው እንዴት ነው?
14 በዚህ ምዕራፍ መግቢያ ላይ እንደተገለጸው ኢየሱስ ከምድር ከፍ ከፍ ካለ በኋላ ከእይታ ተሰውሯል። አሥራ አንዱ ሐዋርያት ግን ወደ ሰማይ እየተመለከቱ እዛው በቆሙበት ቀርተዋል። በመጨረሻም ሁለት መላእክት ተገልጠው ደግነት በተሞላበት መንገድ የሚከተለውን ተግሣጽ ሰጧቸው፦ “እናንተ የገሊላ ሰዎች፣ ወደ ሰማይ እየተመለከታችሁ የቆማችሁት ለምንድን ነው? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የተወሰደው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ ባያችሁት በዚሁ ሁኔታ ይመጣል።” (ሥራ 1:11) መላእክቱ ይህን ሲሉ አንዳንድ ሃይማኖቶች እንደሚያስተምሩት ኢየሱስ ያንኑ አካል ይዞ ዳግመኛ እንደሚመጣ መናገራቸው ነበር? በፍጹም! እንዲህ ማለታቸው አልነበረም። ይህን እንዴት እናውቃለን?
15 መላእክቱ ኢየሱስ “በዚሁ ሁኔታ” እንጂ “በዚሁ አካል” ተመልሶ ይመጣል አላሉም። b ታዲያ ኢየሱስ የሄደው በምን ዓይነት ሁኔታ ነው? መላእክቱ ሐዋርያቱን ባነጋገሩበት ጊዜ ኢየሱስ ከእይታ ተሰውሮ ነበር። ኢየሱስ ምድርን ለቆ በሰማይ ወደሚገኘው አባቱ በመሄድ ላይ መሆኑን ያስተዋሉት በዚያ የነበሩት ጥቂት ሰዎች ይኸውም ሐዋርያቱ ብቻ ነበሩ። ክርስቶስ የሚመለሰውም ከዚህ ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ መሆን ነበረበት። ደግሞም ክርስቶስ የተመለሰው በዚሁ ሁኔታ ነው። በዛሬው ጊዜ ኢየሱስ በንጉሣዊ ሥልጣኑ እንደተገኘ የሚገነዘቡት መንፈሳዊ ማስተዋል ያላቸው ሰዎች ብቻ ናቸው። (ሉቃስ 17:20) በመሆኑም እኛ የኢየሱስን መገኘት የሚያሳየውን ማስረጃ ማስተዋል ይኖርብናል፤ እንዲሁም ማስረጃውን ለሌሎች በመንገር እነሱም የጊዜውን አጣዳፊነት መገንዘብ እንዲችሉ መርዳት አለብን።
የሐዋርያት ሥራ 1:13-26)
“የመረጥከውን አመልክተን” (16-18. (ሀ) ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችን በተመለከተ ከሐዋርያት ሥራ 1:13, 14 ምን እንማራለን? (ለ) የኢየሱስ እናት ማርያም ከተወችው ምሳሌ ምን እንማራለን? (ሐ) ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች በዛሬው ጊዜ እጅግ አስፈላጊ የሆኑት ለምንድን ነው?
16 ሐዋርያቱ “በታላቅ ደስታ ወደ ኢየሩሳሌም [መመለሳቸው]” አያስገርምም። (ሉቃስ 24:52) ይሁንና ክርስቶስ ለሰጣቸው መመሪያ ምን ምላሽ ይሰጡ ይሆን? የሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 1 ቁጥር 13 እና 14 ሐዋርያቱ በአንድ “ደርብ” ላይ ተሰብስበው እንደነበር ይናገራል፤ እነዚህ ክርስቲያኖች በዚህ መንገድ ሲሰባሰቡ ሁኔታው ምን ይመስል እንደነበረም አንዳንድ ትኩረት የሚስቡ ፍንጮች ይሰጠናል። በዚያን ዘመን በፓለስቲና የነበሩት አብዛኞቹ ቤቶች ደርብ ወይም ፎቅ የነበራቸው ሲሆን በውጭ በኩል ወደዚያ ለመውጣት የሚያገለግሉ ደረጃዎች ነበሯቸው። እዚህ ላይ የተጠቀሰው “ደርብ” በሐዋርያት ሥራ 12:12 ላይ በተገለጸው በማርቆስ እናት መኖሪያ ቤት አናት ላይ ያለ ደርብ ይሆን? ሆነም አልሆነ፣ እዚህ ላይ የተጠቀሰው ደርብ የክርስቶስ ተከታዮች መሰብሰብ የሚችሉበት መጠነኛና ምቹ የሆነ ቦታ እንደሚሆን ግልጽ ነው። ይሁንና በዚያ የተሰበሰቡት እነማን ናቸው? የተሰበሰቡትስ ለምንድን ነው?
17 በዚያ የተሰበሰቡት ሐዋርያቱ ብቻ ወይም ወንዶች ብቻ እንዳልነበሩ ልብ በል። የኢየሱስን እናት ማርያምን ጨምሮ “አንዳንድ ሴቶች” በዚያ ተገኝተው ነበር። ማርያም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለመጨረሻ ጊዜ በቀጥታ የተጠቀሰችው እዚህ ላይ ነው። ትሑት የሆነችው ይህች ሴት የተለየ ክብር እንዲሰጣት ሳትጠብቅ ከመንፈሳዊ ወንድሞቿና እህቶቿ ጋር ሆና ይሖዋን ለማምለክ በዚያ መሰብሰቧ የሚያበረታታ ነው። ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ አማኞች ያልነበሩት አራት ወንዶች ልጆቿ በዚህ ወቅት አብረዋት መሆናቸው ሳያጽናናት አይቀርም። (ማቴ. 13:55፤ ዮሐ. 7:5) ወንድማቸው ከሞተበትና ትንሣኤ ካገኘበት ጊዜ ጀምሮ አመለካከታቸው ተለውጦ ነበር።—1 ቆሮ. 15:7
18 በተጨማሪም ደቀ መዛሙርቱ የተሰበሰቡት ለምን እንደሆነ ልብ በል፤ ዘገባው “በአንድ ልብ ተግተው ይጸልዩ ነበር” ይላል። (ሥራ 1:14) ስብሰባዎች ምንጊዜም በክርስቲያኖች አምልኮ ውስጥ ትልቁን ቦታ ይይዛሉ። በስብሰባዎች ላይ የምንገኘው እርስ በርስ ለመበረታታት፣ መመሪያና ምክር ለማግኘት፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ በሰማይ የሚኖረውን አባታችንን ይሖዋን በኅብረት ለማምለክ ነው። በዚያ የምናቀርባቸው ጸሎቶችና የምንዘምራቸው የውዳሴ መዝሙሮች ይሖዋን እጅግ የሚያስደስቱት ከመሆኑም ሌላ ለእኛም ከፍተኛ ጥቅም ያስገኙልናል። ስለሆነም ቅዱስ የሆኑትንና እምነታችንን የሚገነቡትን እነዚህን ስብሰባዎች ፈጽሞ ቸል ማለት የለብንም!—ዕብ. 10:24, 25
19-21. (ሀ) ጴጥሮስ በጉባኤው ውስጥ ግንባር ቀደም ሆኖ ስለተጫወተው ሚና ከሚገልጸው ዘገባ ምን ትምህርት እናገኛለን? (ለ) ይሁዳ መተካት ያስፈለገው ለምንድን ነው? ለዚህ ጉዳይ መፍትሔ ለማግኘት ከተወሰደው እርምጃስ ምን መማር እንችላለን?
19 እነዚያ የክርስቶስ ተከታዮች አንድ ድርጅታዊ ማስተካከያ ማድረግ ያስፈልጋቸው ነበር፤ ይህን ጉዳይ በተመለከተም ቅድሚያውን ወስዶ የተናገረው ጴጥሮስ ነበር። (ከቁጥር 15-26) ጴጥሮስ ጌታውን ሦስት ጊዜ ከካደው ብዙም አልቆየም፤ ይሖዋ ይህን ሐዋርያ በዚህ መንገድ ዳግም የተጠቀመበት መሆኑ የሚያጽናና አይደለም? (ማር. 14:72) ሁላችንም ኃጢአት የመሥራት ዝንባሌ አለን፤ ስለሆነም ይሖዋ “ጥሩ” እንዲሁም ከልብ ንስሐ የሚገቡ ሰዎችን ‘ይቅር ለማለት ዝግጁ’ መሆኑን ማስታወስ ይገባናል።—መዝ. 86:5
20 ጴጥሮስ ኢየሱስን አሳልፎ የሰጠው ሐዋርያ ማለትም ይሁዳ በሌላ መተካት እንዳለበት ተገንዝቦ ነበር። ግን ማን ይተካው? የሚመረጠው ሐዋርያ፣ ኢየሱስ አገልግሎቱን ባከናወነበት ጊዜ ሁሉ እሱን የተከተለና ትንሣኤውን ያየ መሆን ነበረበት። (ሥራ 1:21, 22) ይህም ኢየሱስ እንደሚከተለው በማለት ከገባው ቃል ጋር የሚስማማ ነው፦ “እኔን የተከተላችሁኝ እናንተ በ12 ዙፋኖች ላይ ተቀምጣችሁ በ12ቱ የእስራኤል ነገዶች ላይ ትፈርዳላችሁ።” (ማቴ. 19:28) ከሁኔታዎቹ መረዳት እንደሚቻለው የይሖዋ ዓላማ፣ ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን ባከናወነበት ወቅት ሲከተሉት የነበሩ 12 ሐዋርያት ወደፊት ለምትቋቋመው አዲሲቱ ኢየሩሳሌም “12 የመሠረት ድንጋዮች” ሆነው እንዲያገለግሉ ነው። (ራእይ 21:2, 14) በመሆኑም አምላክ “የበላይ ተመልካችነት ሹመቱን ሌላ ሰው ይውሰደው” የሚለው ትንቢት በይሁዳ ላይ ተፈጻሚነት እንደሚያገኝ ጴጥሮስ እንዲያስተውል አድርጓል።—መዝ. 109:8
21 ምርጫው የተከናወነው እንዴት ነው? ዕጣ በመጣል ሲሆን ይህ ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የተለመደ አሠራር ነበር። (ምሳሌ 16:33) ይሁን እንጂ ዕጣ መጣል በዚህ መንገድ እንደተሠራበት የሚገልጽ ሐሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለመጨረሻ ጊዜ ተጠቅሶ የምናገኘው እዚህ ቦታ ላይ ነው። በኋላ ላይ መንፈስ ቅዱስ መውረዱ በዚህ ዘዴ መጠቀም እንዲቀር እንዳደረገ ግልጽ ነው። ያም ሆኖ ሐዋርያቱ ዕጣ የጣሉት ለምን እንደሆነ ልብ በል። “የሰውን ሁሉ ልብ የምታውቀው ይሖዋ ሆይ፣ ከእነዚህ ሁለት ሰዎች መካከል የመረጥከውን አመልክተን” በማለት ጸልየው ነበር። (ሥራ 1:23, 24) ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው ይሖዋ እንዲመርጥ ፈልገው ነበር። ኢየሱስ እንዲሰብኩ ከላካቸው 70 ደቀ መዛሙርት መካከል አንዱ እንደሆነ የሚታሰበው ማትያስ ተመረጠ። በዚህ መንገድ ማትያስ ‘ከአሥራ ሁለቱ’ መካከል ሆነ። c—ሥራ 6:2
22, 23. በዛሬው ጊዜ በጉባኤ ውስጥ ግንባር ቀደም ሆነው ለሚመሩን ወንድሞች መገዛትና መታዘዝ ያለብን ለምንድን ነው?
22 ይህ ሁኔታ፣ ድርጅታዊ አሠራር ለአምላክ ሕዝቦች ያለውን አስፈላጊነት ያስገነዝበናል። ዛሬም ቢሆን ለኃላፊነት ብቁ የሆኑ ወንድሞች በጉባኤ ውስጥ የበላይ ተመልካች ሆነው እንዲያገለግሉ ይሾማሉ። ሽማግሌዎች፣ እነዚህ ወንድሞች ለበላይ ተመልካቾች የተቀመጡትን ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃቶችን ያሟሉ እንደሆነና እንዳልሆነ በጥንቃቄ ይመረምራሉ፤ እንዲሁም የመንፈስ ቅዱስን አመራር ለማግኘት ይጸልያሉ። በመሆኑም ጉባኤው እነዚህን ወንድሞች በመንፈስ ቅዱስ እንደተሾሙ አድርጎ ይመለከታቸዋል። እኛም ለሚሰጡን መመሪያ ምንጊዜም በመገዛትና በመታዘዝ በጉባኤው ውስጥ የትብብር መንፈስ እንዲሰፍን የበኩላችንን አስተዋጽኦ እናደርጋለን።—ዕብ. 13:17
23 ደቀ መዛሙርቱ ከሞት የተነሳውን ኢየሱስን በማየታቸውና ድርጅታዊ ማስተካከያዎች በመደረጋቸው እምነታቸው ተጠናክሯል፤ አሁን ከፊታቸው ለሚጠብቃቸው ነገር በሚገባ ተዘጋጅተዋል። የሚቀጥለው ምዕራፍ በዚያ ወቅት ስለተፈጸመው ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ክንውን ያብራራል።
a ሉቃስ በወንጌሉ ላይ ይህን ሰው “ክቡር ቴዎፍሎስ ሆይ” በማለት ጠርቶታል፤ በዚህም የተነሳ አንዳንዶች ቴዎፍሎስ በማኅበረሰቡ ዘንድ የተከበረ ቦታ ያለው ሰው እንደሆነና በወቅቱ ገና አማኝ እንዳልነበረ ይገምታሉ። (ሉቃስ 1:3) በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ ግን ሉቃስ ይህን ሰው “ቴዎፍሎስ ሆይ” በማለት ብቻ ጠርቶታል። አንዳንድ ምሁራን ቴዎፍሎስ የሉቃስ ወንጌልን ካነበበ በኋላ አማኝ እንደሆነ ይገልጻሉ፤ ሉቃስ የሐዋርያት ሥራን ሲጽፍ የአክብሮት መግለጫ ያልተጠቀመው እንደ መንፈሳዊ ወንድሙ አድርጎ ስለቆጠረው እንደሆነ ይናገራሉ።
b እዚህ ላይ መጽሐፍ ቅዱስ የተጠቀመው አካላዊ “ቅርጽ” የሚል ትርጉም ያለውን ሞርፊ የተባለውን የግሪክኛ ቃል ሳይሆን “ሁኔታን” የሚያመለክተውን ትሮፖስ የሚለውን የግሪክኛ ቃል ነው።
c ቆየት ብሎ ጳውሎስ “ለአሕዛብ [የተላከ] ሐዋርያ” ተደርጎ ተሹሟል፤ ይሁንና ከ12ቱ መካከል ተቆጥሮ አያውቅም። (ሮም 11:13፤ 1 ቆሮ. 15:4-8) ኢየሱስ ምድር ላይ አገልግሎቱን ባከናወነበት ወቅት ጳውሎስ ኢየሱስን አልተከተለውም፤ በመሆኑም ይህን ልዩ መብት ለማግኘት ብቁ አልነበረም።