በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከበላይ አካሉ የተላከ ደብዳቤ

ከበላይ አካሉ የተላከ ደብዳቤ

ውድ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪ፦

በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ከቆሙት ሐዋርያት አንዱ እንደሆንክ አድርገህ አስብ። ኢየሱስ ፊትህ ቆሟል። ወደ ሰማይ ሊያርግ ሲል እንዲህ አለ፦ “መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በሚወርድበት ጊዜ ኃይል ትቀበላላችሁ፤ በኢየሩሳሌም፣ በመላው ይሁዳና በሰማርያ እንዲሁም እስከ ምድር ዳር ድረስ ምሥክሮቼ ትሆናላችሁ።” (ሥራ 1:8) በዚህ ጊዜ ምን ይሰማህ ነበር?

ምናልባትም የተሰጣችሁ ሥራ ሰፊ መሆኑን በማሰብ አዳጋች እንደሆነ ይሰማህ ይሆናል። ‘ቁጥራችን ጥቂት የሆነው ደቀ መዛሙርት “እስከ ምድር ዳር ድረስ” መመሥከር የምንችለው እንዴት ነው?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት እንደሚከተለው በማለት የሰጠው ማሳሰቢያም ትዝ ብሎህ ሊሆን ይችላል፦ “ባሪያ ከጌታው አይበልጥም . . . እኔን ስደት አድርሰውብኝ ከሆነ እናንተንም ስደት ያደርሱባችኋል፤ ቃሌን ጠብቀው ከሆነ ደግሞ የእናንተንም ቃል ይጠብቃሉ። ሆኖም የላከኝን ስለማያውቁት በስሜ ምክንያት እነዚህን ነገሮች ሁሉ ያደርጉባችኋል።” (ዮሐ. 15:20, 21) እነዚህን ቃላት ስታስብ ‘እንደዚህ ዓይነት ተቃውሞና ስደት እያለ በሚገባ መመሥከር የምንችለው እንዴት ነው?’ እያልክ ትጠይቅ ይሆናል።

ዛሬም እንደነዚህ ያሉ ጥያቄዎች በአእምሯችን ውስጥ መፈጠራቸው አይቀርም። የይሖዋ ምሥክሮች እንደመሆናችን መጠን የተሰጠንን ተልእኮ ለመወጣት “እስከ ምድር ዳር ድረስ” እንዲሁም “ከሁሉም ብሔራት” ለተውጣጡ ሰዎች በሚገባ መመሥከር ይኖርብናል። (ማቴ. 28:19, 20) አስቀድሞ በትንቢት የተነገረው ተቃውሞ እያለም ይህንን ተልእኮ መፈጸም የሚቻለው እንዴት ነው?

በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ሐዋርያትና የእምነት ባልንጀሮቻቸው በይሖዋ እርዳታ ተልእኳቸውን መፈጸም ችለዋል፤ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ ይህን የሚተርክ አስደሳች ዘገባ እናገኛለን። አሁን እያነበብከው ያለኸው መጽሐፍ ይህን ዘገባ ለመመርመርና በውስጡ የተገለጸውን ስሜት ቀስቃሽ ትረካ ለማጣጣም እንዲረዳህ ታስቦ የተዘጋጀ ነው። በመጀመሪያው መቶ ዘመን በነበሩት የአምላክ አገልጋዮችና ዛሬ ባሉት ሕዝቦቹ መካከል በርካታ ተመሳሳይነት መኖሩን ስታይ መገረምህ አይቀርም። የምንሠራው ሥራ ብቻ ሳይሆን ይህን ሥራ ለመሥራት የተደራጀንበት መንገድም ተመሳሳይ መሆኑን ታስተውል ይሆናል። በእነዚህ ተመሳሳይነቶች ላይ ማሰላሰልህ ይሖዋ ዛሬም የድርጅቱን ምድራዊ ክፍል እየመራ እንደሆነ ያለህን እምነት እንደሚያጠናክርልህ ጥርጥር የለውም።

የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍን መመርመርህ ይሖዋ እንደሚረዳህና ቅዱስ መንፈሱ እንደሚደግፍህ ያለህን እምነት ይበልጥ እንዲያጠናክርልህ ምኞታችንና ጸሎታችን ነው። በዚህ አጋጣሚ ስለ አምላክ መንግሥት ‘በሚገባ መመሥከርህንና’ ሰዎች የመዳንን መንገድ እንዲያገኙ መርዳትህን እንድትቀጥል እናበረታታሃለን።—ሥራ 28:23፤ 1 ጢሞ. 4:16

ወንድሞችህ

የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል