በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 14

“በአንድ ልብ ወሰንን”

“በአንድ ልብ ወሰንን”

የበላይ አካሉ ውሳኔ ላይ የደረሰበት መንገድ እንዲሁም ውሳኔው ለጉባኤው አንድነት ያበረከተው አስተዋጽኦ

በሐዋርያት ሥራ 15:13-35 ላይ የተመሠረተ

1, 2. (ሀ) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው የበላይ አካል ለየትኞቹ አንገብጋቢ ጥያቄዎች መልስ መስጠት ያስፈልገው ነበር? (ለ) እነዚህ ወንድሞች ትክክለኛው መደምደሚያ ላይ መድረስ እንዲችሉ የረዳቸው ምንድን ነው?

 የሁሉም ልብ ተንጠልጥሏል። በኢየሩሳሌም የተሰበሰቡት ሐዋርያትና ሽማግሌዎች እርስ በርስ እየተያዩ ነው፤ ታሪካዊ ውሳኔ የሚያደርጉበት ሰዓት እንደደረሰ ገብቷቸዋል። የግርዘት ጉዳይ መልስ የሚያሻቸው አንገብጋቢ ጥያቄዎች አስነስቷል። ክርስቲያኖች የሙሴን ሕግ መጠበቅ አለባቸው? አይሁዳውያን በሆኑና ከአሕዛብ ወገን በመጡ ክርስቲያኖች መካከል ልዩነት ሊኖር ይገባል?

2 በአመራር ቦታ ላይ ያሉት እነዚህ ወንድሞች ብዙ ማስረጃዎችን መርምረዋል። በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘው ትንቢት ምን እንደሚል ተመልክተዋል፤ በተጨማሪም የይሖዋ በረከት መኖሩን የሚጠቁሙ ተሞክሮዎችን የዓይን ምሥክር ከሆኑ ሰዎች ሰምተዋል። ሐሳባቸውን አውጥተው በነፃነት ተነጋግረዋል። አሁን ለውሳኔ የሚያስፈልጋቸውን በቂ ማስረጃ አግኝተዋል። የይሖዋ መንፈስ ትክክለኛውን አቅጣጫ በግልጽ እየጠቆማቸው ነው። ታዲያ እነዚህ ወንድሞች የመንፈሱን አመራር ይቀበሉ ይሆን?

3. በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 15 ላይ የሰፈረውን ዘገባ መመርመራችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል?

3 ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የመንፈስ ቅዱስን አመራር መከተል ከፍተኛ እምነትና ድፍረት የሚጠይቅ ነው። መመሪያውን መቀበላቸው የአይሁድ የሃይማኖት መሪዎች ለእነሱ ያላቸው ጥላቻ እንዲጨምር ሊያደርግ ይችላል። የአምላክ ሕዝቦች ዳግመኛ የሙሴን ሕግ እንዲጠብቁ ለማድረግ ቆርጠው ከተነሱ አንዳንድ ክርስቲያኖችም ተቃውሞ ሊገጥማቸው ይችላል። ታዲያ የበላይ አካሉ ምን ያደርግ ይሆን? እስቲ እንመልከት። እግረ መንገዳችንን፣ እነዚህ ወንድሞች በዛሬው ጊዜ ላለው የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል ምን ምሳሌ እንደተዉ እንመረምራለን። እኛም በክርስቲያናዊ ሕይወታችን ውሳኔ የሚያሻቸው ጉዳዮችና ፈታኝ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን የእነሱን ምሳሌ መከተላችን ይጠቅመናል።

“የነቢያት ቃልም ከዚህ ጋር ይስማማል” (የሐዋርያት ሥራ 15:13-21)

4, 5. ያዕቆብ ከአምላክ ትንቢታዊ ቃል ላይ የትኛውን ሐሳብ ጠቅሶ ተናገረ?

4 አሁን የኢየሱስ ወንድም የሆነው ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ መናገር ጀመረ። a ያዕቆብ ይህን ስብሰባ በሊቀ መንበርነት እየመራ የነበረ ይመስላል። ጠቅለል አድርጎ የተናገረው ሐሳብ የበላይ አካሉ የደረሰበትን መደምደሚያ የሚገልጽ ሳይሆን አይቀርም። በዚያ ተሰብስበው የነበሩትን ሰዎች እንዲህ አላቸው፦ “አምላክ ከአሕዛብ መካከል ለስሙ የሚሆኑ ሰዎችን ለመውሰድ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዴት ለእነሱ ትኩረት እንደሰጠ ሲምዖን በሚገባ ተርኳል። . . . የነቢያት ቃልም ከዚህ ጋር ይስማማል።”—ሥራ 15:14, 15

5 ያዕቆብ፣ ሲምዖን ወይም ስምዖን ጴጥሮስ የተናገረውን ሐሳብ እንዲሁም በርናባስና ጳውሎስ ያቀረቡትን ማስረጃ ሲሰማ ጉዳዩን ይበልጥ ግልጽ የሚያደርጉ ጥቅሶች ወደ አእምሮው ሳይመጡ አልቀሩም። (ዮሐ. 14:26) “የነቢያት ቃልም ከዚህ ጋር ይስማማል” ካለ በኋላ በአሞጽ 9:11, 12 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ ጠቀሰ። ይህ መጽሐፍ የሚገኘው በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ አብዛኛውን ጊዜ “ነቢያት” ተብሎ በሚጠራው ክፍል ውስጥ ነው። (ማቴ. 22:40፤ ሥራ 15:16-18) ያዕቆብ ጠቅሶ የተናገረው ሐሳብ ዛሬ በአሞጽ መጽሐፍ ውስጥ ሰፍሮ ከሚገኘው ሐሳብ የተወሰነ ልዩነት እንዳለው አስተውለህ ይሆናል። ያዕቆብ የጠቀሰው ከሰብዓ ሊቃናት ትርጉም ማለትም ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት የግሪክኛ ትርጉም ላይ ሳይሆን አይቀርም።

6. የተነሳውን ጉዳይ ይበልጥ ግልጽ ያደረጉት የትኞቹ ትንቢቶች ናቸው?

6 ይሖዋ “የዳዊትን ዳስ” የሚያቆምበት ጊዜ እንደሚመጣ በነቢዩ አሞጽ በኩል አስቀድሞ ተናግሯል፤ ይህ አገላለጽ ከመሲሐዊው መንግሥት መቋቋም ጋር የተያያዘ ነው። (ሕዝ. 21:26, 27) ታዲያ ይሖዋ ሥጋዊ እስራኤላውያንን ብቻ እንደገና ለእሱ የተለየ ብሔር አድርጎ ሊወስድ ነው ማለት ነው? በፍጹም! ትንቢቱ በመቀጠል ‘ከብሔራት የመጡ ሰዎች’ አንድ ላይ ተሰባስበው በአምላክ ‘ስም የተጠሩ ሰዎች’ እንደሚሆኑ ይገልጻል። ጴጥሮስ ጥቂት ቀደም ብሎ የሰጠውን ምሥክርነት አስታውስ፤ አምላክ “በእኛና [በአይሁዳውያን ክርስቲያኖችና] በእነሱ [ከአሕዛብ በመጡት ክርስቲያኖች] መካከል ምንም ልዩነት አላደረገም፤ ከዚህ ይልቅ በእምነታቸው የተነሳ ልባቸውን አነጻ” ብሎ ነበር። (ሥራ 15:9) በሌላ አባባል አይሁዳውያንም ሆኑ ከአሕዛብ የመጡት ሰዎች የመንግሥቱ ወራሾች እንዲሆኑ የአምላክ ፈቃድ ነው። (ሮም 8:17፤ ኤፌ. 2:17-19) ከአሕዛብ የመጡ ክርስቲያኖች መጀመሪያ መገረዝ ወይም ወደ ይሁዲነት መለወጥ እንዳለባቸው የሚጠቁም ሐሳብ በመንፈስ መሪነት በተጻፉት ትንቢቶች ላይ አይገኝም።

7, 8. (ሀ) ያዕቆብ ምን ሐሳብ አቀረበ? (ለ) ያዕቆብ “እንደ እኔ ውሳኔ ከሆነ” ሲል ምን ማለቱ ነበር?

7 ያዕቆብ ይህን ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃና ሌሎች የሰጡትን አሳማኝ ምሥክርነት መሠረት በማድረግ የሚከተለውን ሐሳብ አቀረበ፦ “ስለዚህ እንደ እኔ ሐሳብ [“ውሳኔ፣” ግርጌ] ከሆነ፣ ተለውጠው አምላክን ማምለክ የጀመሩትን አሕዛብ ባናስቸግራቸው ይሻላል፤ ከዚህ ይልቅ በጣዖት ከረከሱ ነገሮች፣ ከፆታ ብልግና፣ ታንቆ ከሞተ እንስሳ ሥጋ እንዲሁም ከደም እንዲርቁ እንጻፍላቸው። ምክንያቱም ከጥንት ዘመን ጀምሮ በየከተማው በሰንበት ቀናት ሁሉ በምኩራቦች ውስጥ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ከሙሴ መጻሕፍት በማንበብ በውስጡ የሰፈረውን ቃል የሚሰብኩ ሰዎች ነበሩ።”—ሥራ 15:19-21

8 የስብሰባው ሊቀ መንበር እንደሆነ የሚገመተው ያዕቆብ “እንደ እኔ ውሳኔ ከሆነ” ብሏል፤ ታዲያ እንዲህ ሲል ሥልጣኑን ተጠቅሞ የራሱን ውሳኔ በሌሎቹ ወንድሞች ላይ ለመጫን እየሞከረ ነው? በፍጹም! “እንደ እኔ ውሳኔ ከሆነ” ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል “እንደ እኔ አመለካከት” ወይም “እንደ እኔ አስተያየት” የሚል መልእክትም ያስተላልፋል። ስለዚህ ያዕቆብ ሁሉንም ወክሎ ውሳኔ እያሳለፈ አልነበረም፤ ከዚህ ይልቅ የቀረበውን ማስረጃና ቅዱሳን መጻሕፍት የሚሰጡትን ሐሳብ መሠረት በማድረግ ጉዳዩን እንዲያጤኑት ሐሳብ እያቀረበ ነው።

9. ያዕቆብ ያቀረበው ሐሳብ ምን ጥቅሞች ነበሩት?

9 ያዕቆብ ያቀረበው ሐሳብ ጥሩ ነበር? በሚገባ! ምክንያቱም በኋላ ላይ ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ውሳኔ አድርገው ያስተላለፉት እሱ ያቀረበውን ሐሳብ ነው። ምን ጥቅሞችስ ነበሩት? በአንድ በኩል ከአሕዛብ የመጡት ክርስቲያኖች ‘እንዲቸገሩ’ የሚያደርግ አይደለም፤ ምክንያቱም በሙሴ ሕግ ላይ የሰፈሩትን ደንቦች እንዲጠብቁ አያስገድድም። (ሥራ 15:19) በሌላ በኩል ደግሞ የአይሁዳውያን ክርስቲያኖችን ሕሊና ግምት ውስጥ ያስገባ ነው፤ እነዚህ ወንድሞች ለዓመታት ‘በሰንበት ቀናት ሁሉ በምኩራቦች ውስጥ ከሙሴ መጻሕፍት ሲነበብ’ ሲሰሙ እንደኖሩ ይታወቃል። b (ሥራ 15:21) በእርግጥም የቀረበው ሐሳብ አይሁዳውያን በሆኑና ከአሕዛብ በመጡ ክርስቲያኖች መካከል ያለውን ወዳጅነት የሚያጠናክር ነው። ከሁሉ በላይ ደግሞ ይሖዋን የሚያስደስት ነው፤ ምክንያቱም ወደፊት ከሚገሰግሰው ዓላማው ጋር የሚስማማ ነው። መላውን የአምላክ ሕዝቦች ጉባኤ አንድነትና ደህንነት ስጋት ላይ ጥሎ የነበረው ጉዳይ እልባት ያገኘበት መንገድ አስደናቂ ነው! ዛሬ ላለው የክርስቲያን ጉባኤም እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው!

በ1998 በተደረገ ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ ወንድም አልበርት ሽሮደር ንግግር ሲያቀርብ

10. ዛሬ ያለው የበላይ አካል በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረውን የበላይ አካል ምሳሌ የሚከተለው እንዴት ነው?

10 ቀደም ባለው ምዕራፍ ላይ የተጠቀሰን አንድ ነጥብ እንደገና እናንሳ፦ በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበረው የበላይ አካል ሁሉ ዛሬ ያለው የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካልም ማንኛውንም ጉዳይ በተመለከተ የአጽናፈ ዓለም ሉዓላዊ ገዢ ከሆነው ከይሖዋና የጉባኤው ራስ ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ መመሪያ ለማግኘት ይጥራል። c (1 ቆሮ. 11:3) የበላይ አካሉ ይህን የሚያደርገው እንዴት ነው? ከ1974 አንስቶ ምድራዊ ሕይወቱን እስካጠናቀቀበት እስከ መጋቢት 2006 ድረስ የበላይ አካል አባል ሆኖ ያገለገለው ወንድም አልበርት ሽሮደር እንዲህ ብሎ ነበር፦ “የበላይ አካሉ ረቡዕ ላይ ይሰበሰባል፤ በጸሎት አማካኝነት የይሖዋን መንፈስ አመራር በመጠየቅ ስብሰባውን ይጀምራል። እያንዳንዱ ጉዳይና እያንዳንዱ ውሳኔ የአምላክ ቃል ከሆነው ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚስማማ እንዲሆን ከፍተኛ ጥረት ይደረጋል።” በተመሳሳይም መጋቢት 2003 ምድራዊ ሕይወቱን እስካጠናቀቀበት ጊዜ ድረስ ለረጅም ጊዜ የበላይ አካል አባል ሆኖ ያገለገለው ሚልተን ሄንሼል ለ101ኛው የጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ተመራቂዎች ይህን ወሳኝ ጥያቄ አቅርቦላቸው ነበር፦ “አስፈላጊ ውሳኔዎችን ከማድረጉ በፊት ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ መመሪያ ለማግኘት የሚጥር የበላይ አካል ያለው ሌላ ድርጅት በዚህች ምድር ላይ ይገኛል?” መልሱ ግልጽ ነው!

‘የተመረጡ ሰዎችን ላኩ’ (የሐዋርያት ሥራ 15:22-29)

11. የበላይ አካሉ ያሳለፈውን ውሳኔ ጉባኤዎቹ እንዲያውቁት የተደረገው እንዴት ነው?

11 በኢየሩሳሌም ያለው የበላይ አካል በግርዘት ጉዳይ ላይ በአንድ ድምፅ ውሳኔ አስተላለፈ። ይሁን እንጂ በየጉባኤዎቹ ያሉት ወንድሞችም ስለ ጉዳዩ አንድ ዓይነት አቋም እንዲኖራቸው ማድረግ ያስፈልጋል፤ ለዚህ ደግሞ ውሳኔው በግልጽ፣ አዎንታዊ በሆነና በሚያበረታታ መንገድ ሊነገራቸው ይገባል። ታዲያ ይህን ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው? ዘገባው እንዲህ ይላል፦ “ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ከመላው ጉባኤ ጋር ሆነው ከመካከላቸው የተመረጡ ሰዎችን ከጳውሎስና ከበርናባስ ጋር ወደ አንጾኪያ ለመላክ ወሰኑ፤ በወንድሞች መካከል ግንባር ቀደም የሆኑትን በርስያን የሚባለውን ይሁዳንና ሲላስን ላኩ።” በተጨማሪም በአንጾኪያ፣ በሶርያና በኪልቅያ ባሉት ጉባኤዎች ውስጥ የሚነበብ ደብዳቤ በእነዚህ ሰዎች በኩል ላኩላቸው።—ሥራ 15:22-26

12, 13. (ሀ) ይሁዳና ሲላስ መላካቸው ምን ጥሩ ውጤት ነበረው? (ለ) የበላይ አካሉ የላከው ደብዳቤ ምን ጥሩ ውጤት አስገኝቷል?

12 ይሁዳና ሲላስ “በወንድሞች መካከል ግንባር ቀደም” እንደሆኑ ተገልጿል፤ በመሆኑም የበላይ አካሉ ተወካዮች የመሆን ሙሉ ብቃት ነበራቸው። ከጳውሎስና ከበርናባስ ጋር እነዚህ ሁለት ሰዎች መላካቸው የግርዘትን ጥያቄ መልስ ብቻ ሳይሆን ከበላይ አካሉ አዲስ መመሪያ ይዘው እንደመጡም ግልጽ ያደርጋል። እነዚህ “የተመረጡ ሰዎች” ከአሕዛብ የመጡ ክርስቲያኖች ወዳሉባቸው ጉባኤዎች መሄዳቸው፣ ኢየሩሳሌም ባሉት አይሁዳውያን ክርስቲያኖችና ከአሕዛብ በመጡ ክርስቲያኖች መካከል ያለውን አንድነት ያጠናክራል። በእርግጥም ይህ ጥበብና ፍቅር የተንጸባረቀበት ዝግጅት ነው! በአምላክ ሕዝቦች መካከል ሰላምና ስምምነት እንዲሰፍን አስተዋጽኦ እንዳደረገ ምንም ጥርጥር የለውም።

13 ደብዳቤው ግርዘትን በተመለከተ ለተነሳው ጥያቄ መልስ የሚሰጥ ብቻ አይደለም፤ ከአሕዛብ የመጡት ክርስቲያኖች የይሖዋን ሞገስና በረከት ለማግኘት ምን ማድረግ እንዳለባቸው ግልጽ መመሪያ የያዘም ነበር። ደብዳቤው ላይ እንዲህ የሚል ቁልፍ ሐሳብ ተጠቅሷል፦ “ከሚከተሉት አስፈላጊ ነገሮች በስተቀር፣ ሌላ ተጨማሪ ሸክም እንዳንጭንባችሁ መንፈስ ቅዱስና እኛ ወስነናል፦ ለጣዖት ከተሠዉ ነገሮች፣ ከደም፣ ታንቆ ከሞተ እንስሳ ሥጋና ከፆታ ብልግና ራቁ። ከእነዚህ ነገሮች ሙሉ በሙሉ ከራቃችሁ መልካም ይሆንላችኋል። ጤና ይስጣችሁ!”—ሥራ 15:28, 29

14. መከፋፈል በነገሠበት ዓለም ውስጥ የይሖዋ ሕዝቦች አንድነት ሊኖራቸው የቻለው እንዴት ነው?

14 በዛሬው ጊዜ በዓለም ዙሪያ ከ100,000 በላይ በሚሆኑ ጉባኤዎች ውስጥ ከ8,000,000 በላይ የይሖዋ ምሥክሮች ይገኛሉ፤ ይሁንና በእምነታቸውም ሆነ በድርጊታቸው ፍጹም አንድነት አላቸው። ሁከትና መከፋፈል በነገሠበት ዓለም ውስጥ እንዲህ ዓይነቱ አንድነት ሊገኝ የቻለው እንዴት ነው? ለዚህ ዋነኛው ምክንያት የጉባኤው ራስ ኢየሱስ ክርስቶስ ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ ይኸውም በበላይ አካሉ አማካኝነት የሚሰጠው ግልጽና የማያሻማ መመሪያ ነው። (ማቴ. 24:45-47) ሌላው ምክንያት ደግሞ ዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበር የበላይ አካሉ የሚሰጠውን መመሪያ በፈቃደኝነት መታዘዙ ነው።

“ባገኙት ማበረታቻ እጅግ ተደሰቱ” (የሐዋርያት ሥራ 15:30-35)

15, 16. ግርዘትን በተመለከተ የተነሳው ጥያቄ የመጨረሻ ውጤት ምን ነበር? ይህ ጥሩ ውጤት እንዲገኝ ምክንያት የሆነውስ ምንድን ነው?

15 ከኢየሩሳሌም የተላኩት ወንድሞች አንጾኪያ ደረሱ፤ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ዘገባ ቀጥሎ የሆነውን ሲገልጽ “እዚያ የሚገኙትንም ደቀ መዛሙርት በአንድነት ሰብስበው ደብዳቤውን ሰጧቸው” ይላል። ታዲያ በዚያ ያሉት ወንድሞች የበላይ አካሉ ላስተላለፈው መመሪያ ምን ምላሽ ሰጡ? “[ደብዳቤውን] ካነበቡት በኋላ ባገኙት ማበረታቻ እጅግ ተደሰቱ።” (ሥራ 15:30, 31) በተጨማሪም ይሁዳና ሲላስ “ብዙ ቃል በመናገር ወንድሞችን አበረታቷቸው፤ እንዲሁም አጠናከሯቸው።” በዚህም የተነሳ እነዚህ ሁለት ሰዎች እንደ በርናባስ፣ ጳውሎስና ሌሎች የአምላክ አገልጋዮች ሁሉ “ነቢያት” ተብለው ተጠርተዋል፤ ምክንያቱም ነቢይ የሚለው ቃል የአምላክን ፈቃድ ለሌሎች የሚያውጅን ወይም የሚያሳውቅን ሰው ያመለክታል።—ሥራ 13:1፤ 15:32፤ ዘፀ. 7:1, 2

16 ይሖዋ ለጉዳዩ ጥሩ እልባት ለመስጠት የተደረገውን ጥረት ሁሉ እንደባረከው ግልጽ ነው። ታዲያ ለዚህ ጥሩ ውጤት ቁልፉ ምን ነበር? የበላይ አካሉ ያስተላለፈው ግልጽና ወቅታዊ መመሪያ እንደሆነ ጥርጥር የለውም፤ የአምላክን ቃልና የመንፈስ ቅዱስን አመራር መሠረት ያደረገ ውሳኔም ነው። የበላይ አካሉ ውሳኔው ለጉባኤዎቹ እንዲተላለፍ ያደረገበት መንገድም ለተገኘው ጥሩ ውጤት አስተዋጽኦ አድርጓል፤ የተመረጡ ወንድሞች ወደየጉባኤዎቹ ሄደው ውሳኔውን ፍቅርና አሳቢነት በሚንጸባረቅበት መንገድ እንዲነግሯቸው አድርጓል።

17. የወረዳ የበላይ ተመልካቾች ጳውሎስ፣ በርናባስ፣ ይሁዳና ሲላስ የተዉትን ምሳሌ የሚከተሉት በምን መንገድ ነው?

17 ዛሬ ያለው የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካልም ይህንኑ ምሳሌ በመከተል ለዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበር ወቅታዊ መመሪያ ያስተላልፋል። ውሳኔዎች በሚደረጉበት ጊዜ፣ ግልጽ በሆነና በማያሻማ መንገድ ጉባኤዎች እንዲያውቁት ይደረጋል። ይህ የሚደረግበት አንዱ መንገድ የወረዳ የበላይ ተመልካች ጉብኝት ነው። የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት የሚያደርጉት እነዚህ ወንድሞች የተለያዩ ጉባኤዎችን በመጎብኘት ግልጽ መመሪያዎችንና ማበረታቻዎችን ይሰጣሉ። ጳውሎስና በርናባስ እንዳደረጉት ሁሉ እነሱም “እያስተማሩና ከሌሎች ብዙ ሰዎች ጋር ሆነው ምሥራቹን ይኸውም የይሖዋን ቃል እየሰበኩ” በአገልግሎት ረጅም ሰዓት ያሳልፋሉ። (ሥራ 15:35) በተጨማሪም እንደ ይሁዳና እንደ ሲላስ “ብዙ ቃል በመናገር ወንድሞችን” ያበረታታሉ እንዲሁም ያጠናክራሉ።

18. የአምላክ ሕዝቦች የይሖዋ በረከት እንደማይለያቸው እርግጠኞች መሆን የሚችሉት ምን ካደረጉ ብቻ ነው?

18 ስለ ጉባኤዎችስ ምን ማለት ይቻላል? በዚህ በተከፋፈለ ዓለም ውስጥ በምድር ዙሪያ የሚገኙት ጉባኤዎች ሰላምና አንድነት እንዲኖራቸው ያደረገው ምንድን ነው? ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ ቆየት ብሎ የጻፈውን የሚከተለውን ሐሳብ ልብ በል፦ “ከሰማይ የሆነው ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጹሕ ነው፤ ከዚያም ሰላማዊ፣ ምክንያታዊ፣ ለመታዘዝ ዝግጁ የሆነ። . . . ከዚህም በላይ የጽድቅ ፍሬ ሰላም ፈጣሪ ለሆኑ ሰዎች ሰላማዊ በሆኑ ሁኔታዎች ይዘራል።” (ያዕ. 3:17, 18) ያዕቆብ ይህን የጻፈው በኢየሩሳሌም የተደረገውን ስብሰባ በአእምሮው ይዞ ይሁን አይሁን የምናውቀው ነገር የለም። ይሁንና አሁን ከመረመርነው የሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 15 ዘገባ የምንረዳው አንድ ነገር አለ፤ ይሖዋ ሊባርከን የሚችለው በመካከላችን አንድነትና የትብብር መንፈስ እስካለ ድረስ ብቻ ነው።

19, 20. (ሀ) በአንጾኪያ ጉባኤ ውስጥ ሰላምና አንድነት ሰፍኖ እንደነበር የሚጠቁመው ምንድን ነው? (ለ) አሁን ጳውሎስና በርናባስ በምን ላይ ማተኮር ይችላሉ?

19 አሁን በአንጾኪያ ጉባኤ ውስጥ ሰላምና አንድነት መስፈኑ በግልጽ ይታያል። የአንጾኪያ ወንድሞች ከኢየሩሳሌም ከመጡት ወንድሞች ጋር አልተከራከሩም፤ ከዚህ ይልቅ ይሁዳና ሲላስ መጥተው ስለጎበኟቸው ተደስተዋል። ምክንያቱም ዘገባው እንዲህ ይላል፦ “በዚያም የተወሰነ ጊዜ ከቆዩ በኋላ ወደላኳቸው ሰዎች [ወደ ኢየሩሳሌም] እንዲመለሱ ወንድሞች በሰላም አሰናበቷቸው።” d (ሥራ 15:33) በኢየሩሳሌም ያሉት ወንድሞችም፣ ሁለቱ ወንድሞች ስለ ጉዟቸው በሚነግሯቸው ነገር እንደሚደሰቱ ጥርጥር የለውም። የይሖዋ ጸጋ ስላልተለያቸው ተልእኳቸውን በደስታ አጠናቀው መመለስ ችለዋል!

20 አሁን የግርዘት ጉዳይ እልባት ስላገኘ ጳውሎስና በርናባስ ትኩረታቸውን በወንጌላዊነቱ ሥራ ላይ ማድረግ ይችላሉ፤ ዛሬ ያሉት የወረዳ የበላይ ተመልካቾችም ጉባኤዎችን ሲጎበኙ የሚያደርጉት ይህንኑ ነው። (ሥራ 13:2, 3) ይህ ለይሖዋ ሕዝቦች እንዴት ያለ በረከት ነው! ይሁንና ይሖዋ እነዚህን ሁለት ቀናተኛ ወንጌላውያን ይበልጥ የተጠቀመባቸውና የባረካቸው እንዴት ነው? በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ ይህን እንመለከታለን።

በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች በበላይ አካሉና በሚወክላቸው ወንድሞች አማካኝነት ከሚቀርቡላቸው መንፈሳዊ ዝግጅቶች ይጠቀማሉ

a ያዕቆብ—‘የጌታ ወንድም’” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

b ያዕቆብ ከሙሴ መጻሕፍት ላይም ማጣቀሱ ጥበብ የሚንጸባረቅበት ነው። እነዚህ መጻሕፍት ሕጉን ብቻ ሳይሆን ከሕጉ በፊት አምላክ ከሰዎች ጋር ስለነበረው ግንኙነት የሚገልጹ ዘገባዎችን ይዘዋል፤ ዘገባዎቹ፣ የሙሴ ሕግ ከመሰጠቱ በፊት የአምላክ ፈቃድ ምን እንደነበረ ይጠቁማሉ። ለምሳሌ ያህል፣ አምላክ ስለ ደም፣ ስለ ምንዝርና ስለ ጣዖት አምልኮ ያለው አመለካከት በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ በግልጽ ሰፍሯል። (ዘፍ. 9:3, 4፤ 20:2-9፤ 35:2, 4) በመሆኑም ይሖዋ አይሁዳዊ፣ አሕዛብ ሳይል መላው የሰው ዘር ሊጠብቃቸው የሚገቡ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ሰጥቷል።

d አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ቁጥር 34 ላይ ሲላስ በአንጾኪያ ለመቅረት እንደወሰነ የሚገልጽ ሐሳብ አስገብተዋል። (ለምሳሌ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጉም) ይሁንና ይህ ሐሳብ ከጊዜ በኋላ የተጨመረ ሳይሆን አይቀርም።